እስክንድር ነጋ እና አንዱአለም አራጌ እንዲፈቱ ተወሰነ

EMF- በሽብር ወንጀል ተከስሶ የ18 አመት ፅኑ እስራት የተፈረደበት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲለቀቅ ተወስኗል። የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አንዷለም አራጌን ጨምሮ ከ 700 በላይ የፖለቲካ እስረኞችም በዚህ ሳምንት ከእስር እንደሚፈቱ ተነግሯል።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በእስር ላይ ሆኖ ለ5ኛ ጊዜ የአለማቀፍ ሽልማት እንደተበረከተለት ይታወሳል። መቀመጫውን ኦስትሪያ ቬና ያደረገው በዓለም አቀፉ ፕሬስ ኢንስቲትዩት ባሳለፍነው ዓመት “የዓለም የፕሬስ ነፃነት ጀግና” ሲለው ዘ ሄግ ከተማ በዚህ ወር መግቢያ በተካሄደው የ2018 የፔን እና የኦክስፋም ኖቪፕ – “ሃሳብን የመግለጽ መብት” አዋርድ ተሸላሚ ሆኗል።

የ“ፔን ካናዳ ዋን ሂዩማኒቲ አዋርድ” እንዲሁም ፔን ኢንተርናሽናል ኒውዮርክ እስክንድር ድንበር ሳይገድበው ለዓለም ማህበረሰብ በፀሃፊነቱ ባበረከተው ጉልህ አስተዋፅኦ ሸልሞታል።

የእስክንድር ባለቤት ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል ኢሕአዴግ ባሳለፈው ውሳኔ እስክንድር ይፈታ ይሆናል የሚል ተስፋ እንደነበራት ተናግራ ነበር። ዛሬ እስክንድርን የመፈታት ዜና ስትሰማ ደስታዋን ለመግለጽ ቃላት አጥሯታል።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ እና ልዕሎችም በአሸባሪነት ተከሰው ከታሰሩ አመታት ያለፋቸው ሲሆን ከ 18 ዓመት እስከ እድሜ ልክ ቅጣት እንደተወሰነባቸው የሚታወስ ነው።

Share Button