ኢትዮጲያ “ልሂቃኖቿ” የማያዝኑላት ሀገር – ኤድመን ተስፋዬ

እውቁ ኢኮኖሚስት ዳግላስ ኖርዝ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ብልፅግናም ሆነ ቀውስ ከሀገሪቱ ተቋማዊ ጥንካሬ ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ በመግለፅ አብዛኛዎቹ ደሀ ሀገራት ድህነት መንስኤ ከገነቡት ተቋም ጥንካሬ ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ ይተነትናል፡፡ እንደ ኖርዝ ሁሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጋናን በጎበኙበት ወቅት አፍሪካ የሚያስፈልጋትም ሆነ ያጣችው ጠንካራ ግለሰብ ሳይሆን ጠንካራ ተቋም ስለመሆኑ በመግለፅ ለአፍሪካ  ሀገራት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግር መፍትሄው ጠንካራ ተቋም  መገንባት ስለመሆኑ አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል፡፡ በምንገኝበት የሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የተቋማት ሚና ለሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግር መፍትሄ ከመሆናቸው ጋር በቀጥተኛ ሁኔታ ተገናኝ በሆነ ሁኔታ የሚታይ ሲሆን፣ይህ የተቋማት ሚና  ስኬት ደግሞ ተቋሙን በሚመሩት እና በሚያንቀሳቅሱት ግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡  ዘመን ተሻጋሪው ኢኮኖሚስት አማርታሲያን ሴን ለምርታማነት ምክንያት ከሆኑት ውስጥ አንዱ የሆነው የሰው ሀይል ከሌሎቹ በተለየ ለኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው ያደረገው ከሰው ልጅ የማሰብ እና ከመራመር ፀጋው ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ ይገልፃል፡፡ ይህ የሴን ንድፈ ሀሳብ ተለጥጦ ሲታይ የሰው ሀይል ለምርታማነቱ ምክንያቱ ጉልበቱ ብቻ ሳይሆን በዋነኛነት እውቀቱ ነው እንደማለት ነው፡፡

የልሂቃኖችን እውቀት እንደ ግብአት በመጠቀም ህዝባቸውን ከማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በማውጣት ኢኮኖሚያቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት ከቻሉ ሀገራት ውስጥ ጀርመን አንዷ ስትሆን፣ጀርመን በሰው በላው ሂትለር በተማገደችበት ጦርነት ማክተም በሁአል አንድ የነበረው ሉአላዊ ግዛቷ ለሁለት ከመከፈሉም ባለፈ በሂትለር መሪነት በአራቱም የአለም ማእዘን  በተማገደችበት ጦርነት የተነሳ  ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ መጋለጧ ከጦርነቱ በህይወት የተረፈውን ዜጋዋን ለከባድ የኑሮ ፈተና እንዲጋለጥ መንስኤ ሆኖታል፡፡ ለ ሁለት የተከፈለው ሉአላዊ ግዛቷ አንድ በመሆን ኢኮኖሚዋን አሁን ላይ ከአውሮፓ ሀገራት ግዙፉ ኢኮኖሚ እንዲሆን ካስቻሉት ውስጥ በዋነኛነት የሚጠቀሱት የሀገሪቷ ልሂቃኖች ስለመሆናቸው በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ባለሞያዎች የሚገልፁት ጉዳይ ነው፡፡

ፕሮፌሰር በህሩ ዘውዴ የኢትዮጲያ ልሂቃን ታሪክ ጅማሮው ከአድዋው ድል በሁአላ እስከ ዳግማዊው የጣሊያን ወረራ ባሉት አራት አስር አመታት መሆኑን ይጠቅሳሉ። በዚህ ወቅት የነበሩትን ልሂቃኖች የመጀመሪያዎቹ የሀገራችን ልሂቃኖች ይሏቸዋል። እ.ኤ.አ ከ 1941 እስከ 1971 ድረስ ያሉትን በሀገራችን የልሂቃን ታሪክ ሁለተኛው ትውልድ ስለመሆናቸው በመጥቀስ እ.ኤ.አ  ከ1971 እስከ አሁን ድረስ ያሉትን ሶስተኛው ትውልድ ስለመሆናቸው በጥናቶቻቸው ይገልፃሉ፡፡ ፕሮፌሰር በህሩ ዘውዴ ከአድዋው ድል በሁአላ እስከ ዳግማዊው የጣሊያን ወረራ ባሉት አራት አስር አመታት ግዜ ውስጥ የነበሩትን በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆኑትን ልሂቃን የነበሩበት ግዜ የአድዋ ድል ከፈጠረው መነቃቃት፣በዛ ያሉ ኢትዮጲያውያን በአውሮፓ ዘመናዊ ትምህርት ተምረው ወደ ሀገራቸው ከመመለሳቸው፣በዛ ያሉት ልሂቃን የጃፓንን እድገት እንደ ሞዴል ከመውሰዳቸው እና ለሀገራቸው እድገት ምን አይነት መንገድ መከተል ይገባናል በሚሉ ክርክሮች የተሞላ መሆኑ ግዜውን የተለየ እንዲሆን ያደረገው ምክንያት ስለመሆኑ ይገልፃሉ፡፡

አቶ አሰፋ ጫቦ በበኩላቸው መሬት ላራሹ በሚል መሪ ቃል ንጉሱን ከስልጣን ያወረደውን እና ስልጣኑን በሚሊተሪው የተነጠቀውን ትውልድ በአንድ በኩል  መሬት ላራሹ የሚለውን መርህ የተገበረውን ደርግ የነበረበትን የልሂቃን እጥረት ቀረብ ብሎ ከሞሙላት ይልቅ የሶሻሊስትም  ወኪል እኔ ነኝ  በሚል እሰጣ ገባ በሌላ በኩል ባልተሰጠው ውክልና እራሱን የአንድ ብሄር ወኪል በማድረግ ወደ አላስፈላጊ እልቂት የገባ ስለመሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡ ፕሮፈሰር መሳይ ከበደ በበኩላቸው ፕሮፈሰር ባህሩ ዘውዴ ከጊዜ ቀውደም ተከተል አኩአያ በሁለተኛ ድፍ ላይ ያስቀመጡትን የልሂቃን ትውልድ ለሀገሩ ያለው ፍቅር ምሳሌ የሚሆን ስለመሆኑ በመጥቀስ የትውልዱ ስህተት የኢትዮጲያን ችግር በምእራቡ አስተምህሮት  ብቻ ለመፍታት መሞከሩ ስለመሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡

አሁን ላይ የሚገኙት የሀገሪቷ ልሂቃኖች ለሀገራቸው  ምን አይነት የልሂቅነት አስተዋእፆ እያደረጉ ነው  የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ ያለው ምልከታ በአብዛኛው መነሻው የልሂቃኖቹን እና የህወሃት- ኢህአዴግ ግንኙነት እንዲሁም  ህወሃት- ኢህአዴግ በየዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ነፃነትን በተመለከተ ከወረቀት ባለፈ በነባራዊነት የሚከተለውን ፖሊሲ ማእከል ያደረገ ነው፡፡

የ “ልሂቃኖቻችን”  ሁለት ጠርዞች

ገዢው ፖርቲ የሚለፍፈውን  ማረጋገጫ የሚሰጥለትን እና አመጣውት የሚለውን ልማት እንዲያስተጋባለት በአስተማሪነትም ሆነ በአመራርነት በየዩኒቨርስቲው ያስቀመጠውን ልሂቅ ድጋፍ እና እውቅና እየሰጠ ፖርቲውን የሚሞግቱትን መኮነኑ እና ፀረ ልማት አድርጎ መበየኑን እንዲሁም በየዩኒቨርስቲዎቹ የአካሚክ ነፃነት አለመኖሩን በምክንያትነት በማቅረብ እንደ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ያሉ  ሙሁራኖች ልሂቁ በሀገሪቷ ጉዳዮች ላይ ያለው ሚና እምብዛም  እንዲሆን ለመሆኑ ተጠያቂው   ገዢው ፖርቲ ስለመሆኑ ይናገራሉ ፡፡  እንደ ፕሮፌሰር አለማየው ያሉ ምሁራን በበኩላቸው ልሂቁ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ሚናው ለመቀዝቀዙ   ገዢው ፖርቲን ተጠያቂ ከሚያደርጉት ምክንያቶች እኩል  የልሂቃኖቹ  አድርባይነት በሀገሪቷ ጉዳይ ላይ እውቀትን ማእከል ያደረገ ሚናቸውን እንዳይወጡ እንዳደረጋቸው ይተነትናሉ፡፡

ከላይ በተጠቀሰው የፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ሙግት የሚስማሙ ወገኖች በአንጋፋዎቹ እና በአደባባይ ሙሁራኖቹ ዶክተር ዳኛቸው ዘውዴ እና ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ላይ የደረሰውን ሁነት በማስረጃነት በማንሳት የሀገራችን ልሂቃኖች የሀገራቸውን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁነት ከአካዳሚካዊ እይታ አኩአያ በነፃነት እና በገለልተኝነት የመፈተሻቸው ነገር ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሁን ላይ ለተቀዛቀዘበት ምክንያት ገዢውን ፓርቲ ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

የልሂቅነት ሃላፊነት እውቀትን ለሀገር ችግር መፍቻ መሳሪያነት ማዋል ስለመሆኑ የጀርመን ልሂቃንን ተሞክሮ በምሳሌነት በመጥቀስ የሚሞግቱት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዢው ፖርቲ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመር ወጣ ያለ ልሂቅ ማየት ያለመፈለጉ ነገር እንዳለ ሆኖ የልሂቅነት እዳው እና ሀላፊነቱ እንደዚህ አይነት ግትር መንንግስታዊ ስርአትን በእውቀት መሞገት ስለመሆኑ በመጥቀስ ከኢህአዴግ ግትርነት እኩል ልሂቁ ከሀገሩ ችግር ይልቅ ለግል ጥቅሙ ቅድሚያ መስጠቱ ባልተለመደ መልኩ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሆን ብሎ እንዲያንቀላፋ እንዳደረገው ሲገልፁ በ2009 የፌደራል ኦዲተር መስሪያ ቤት ከፍተኛ የሆነ ሙስና ተንሰራፍቷል ብሎ ከጠቀሳቸው የሀገሪቷ ተቋሟች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ስለመሆናቸው መግለፁን   በአስረጂነት በመግለፅ ነው፡፡

ስለ ጓደኛህ(ባልንጀራህ) ባህሪ ንገረኝና ስለ አንተ ባህሪ ልንገርህ እንዲሉ አበው በአንድ ሉአላዊ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስክ የሚያስመዘግቡት መሻሻልም ሆነ እንደ ህዝብ  በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስክ የሚደርስበት መመሰቃቀል ህዝቡ ውክልና ሰጥቶት ህዝቡን የሚያስተዳድረው መንግስት በሚከተለው ፖሊሲ እና ፖሊሲውን ለመተግበር ባለው አቅም ላይ  የተንጠለጠለ ነው፡፡ ሀገራዊ ፖሊሲ በነባራዊነት የህዝብን ኑሮ ሊያሻሻል የሚችለው ፖሊሲው ሲነደፍ የሀገሪቷን ተጨባጭ ቁሳዊ እና ሰዋዊ ሀብት ያገናዘበ፣ የሀገሪቷን ታሪክ፣የህዝቦቿን ባህል እና የህዝቦችን ስብጥር ከግምት ያስገባ ሲሆን እና ፖሊሲውን ከወረቀት ባለፈ ወደመሬት ለማውረድ ህዝብን በውክልና የሚያስተዳድረው መንግስት ፖሊሲውን የማስተግበር አቅም ሲኖረው እንደሆነ የእድገት ኢኮኖሚስቶች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡

የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል በሚል የሚነደፉት ፖሊሲዎች በነደፋው ወቅትም ሆነ ፖሊሲዎቹን ከወረቀት ባለፈ ወደመሬት ለማውረድ በሚደረገው እንቅስቃሴ መንግስታዊው ሀላፊነት ከሚከተለው እርዮተ አለም ጋር በተገናኘ ሁለት አይነት አካሄድ ያለው ነው፡፡  መንግስት እንደ መንግስት የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል የሚነድፈውን ሀገራዊ ፖሊሲ እንደ መንግስት ያመነበትን ፖሊሲ ከሚከተለው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እርዮት አለም አንፃር በማሰላሰል ለመተግበር የሚሄድበት አንደኛው አካሄድ ሲሆን  ሀገራዊ ፖሊሲውን ከመንግስታዊ እርዮተ አለሙ በመነጠል ለፖሊሲው ተግባራዊነት የቁጥጥሩን ሚና ብቻ የሚወጣበት ደግሞ ሁለተኛው አካሄድ ነው፡፡  

የሶስተኛው አለም ደሀ ሀገራትን በተለይም የአፍሪካ ሀገራትን ዘመን የተሻገረ ድህነት መንስኤዎችን በተመለከተ በጥናት የተደገፈ ምክንያትን የሚያቀርቡ ሙሁራኖች የሚስማሙበት ጉዳይ የቅኝ ግዛት ተፅእኖ እንዳለ ሆነ ለሶስተኛው አለም ደሀ ሀገሮች በለይም ለአፍሪካ ሀገራት ድህነት ዋነኛው ምክንያት ከፖለቲካዊው ስርአት ገለልተኛ የሆነ ጠንካራ ተቋማትን ሀገራቱ አለመገንባታቸው እና የፖለቲካው ስርአት ከእውቀታቸው ይልቅ ፖለቲካዊ ምልከታቸውን ወይም ፖለቲካዊ ወገንተኘነታቸውን ብቻ በማየት ሙሁራኑን ማቅረብን ማእከል በማድረጉ  የተነሳ ስለመሆኑ  ነው፡፡   

“ልሂቃኖቻችን” ችግር ፈቺ ወይስ ዘራፊ?

ያደጉ ሀገራት ታሪክ እንደሚያሳየን ሙሁራን በእውቀት የዳበረ ግለሰብ በመፍጠር፣ ከድህነት ለመውጣት መሳሪያ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር እና ህግ እና ደንብን አክብሮ የሚሄድ ተቋምን በመገንባት  ለሀገራቸው ማህበረሰባዊ እና   ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለሁለተኛው አለም ጦርነት መንስኤ በሆነው ሂትለር ስትመራ የነበረችው ጀርመን በሂትለር አመራር በገባችበት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስ በአጭር ጊዜ ሀገራዊ አንድነቷን በጠበቀ መልኩ ኢኮኖሚዋን በጠንካራ መሰረት ላይ በመገንባት የአውሮፓ ግዙፍ ኢኮኖሚ ለማድረግ ሙሁራን የተጫወቱትን ሚና የሚጠቀስ ነው፡፡ መሁራን ለሀገር ኢኮኖሚ የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት አካዳሚካዊ ነፃነት እና ከፖለቲካዊ ተፅእኖ መውጣት ያለባቸው መሆኑን በመጥቀስ  ሙሁራኑ ለሀገራቸው የሚያበረክቱት ሚና አሉታዊውም ሆነ አዎንታዊው ውጤቱ በመንግስታዊው ስርአት ላይ የተንጠለጠለ ስለመሆኑ   በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ሙሁራን ይናገራሉ፡፡

ለዘመናት በድህነት የቆዩ ሀገራችንን የመሳሰሉ ሀገራት ከድህነት ለመውጣት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚኖር ሙስና ዋነኛ መንስኤው ድህነት ሲሆን፣  ለሙስና ምቹ ሁኔታ የሚፈጥረው ደግሞ ተጠያቂነት የሌለበት ስልጣን ነው፡፡  የሀገርን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁነት በፖርቲ መነፅር ብቻ በሚያይ ስርአተ መንግስት ውስጥ ከሙስና ጋር በተያያዘ ያለው ተጠያቂነት የሚመዘነው የባከነውን ወይም ለግል ጥቅም የዋለውን ሀገራዊ ሀብት ማእከል ባደረገ መልኩ ሳይሆን ሙስናውን የፈፀመው ባለስልጣን ለፓርቲው ካለው ታማኝነት፣ሎሌነት በተለይም የፖርቲው አውራ ከሆነው ግለሰብ ጋር ካለው ግንኙነት እና ታማኝነት አኩአያ ስለመሆኑ በአንባገነናዊ ስርአት ውስጥ ለሚፈፀመው ሙስና ያለን ተጠያቂነት በተመለከተ ጥናት ያደረጉት ፕሮፌሰር ካርል ሄነሪክ ይገልፃሉ፡፡

በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር በከፍተኛ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችም ሆነ ከመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ውጪ  የሚገኙ ብዙሀኑ የሀገራችን ሙሁራን በየጊዜው  ኢህአዴግ የሚሰጣቸውን የልማታዊ መንግስት ስልጠና ኧንካ ለሞሞገት የማይደፍሩ ከመሆናቸው ባለፈ  በሀገሪቷ በህወሃት መሪነት የሚካሄደውን ግድያ ለማውገዝ ላለመድፈራቸው ምክንያቱ በእኔ እምነት  የገዢው ፖርቲ አንባገነንነት፣ የሙሁራኑ አካዳሚያዊ እውቀት አናሳነት እና አድርባይነት  ነው፡፡

Share Button