አጨራረሱ – በዳዊት ዳባ

አንድን አሮጌ አንባገነን ስርዓት አፈራርሶ በአዲስ ለመቀየር  የአሮጌው ስርአት ቁልፍ ቁልፍ ሰዎች መታሰር፤ መገደል አልያም  መሸሽ አለባቸው። ይህ በየትኛውም አይነት የትግል አይነት ይሁን በመጨረሻ ተፈፃሚ ነው። ‘አጨራረሱ” ትግሉ ላይ የጠቅላላ እቅድ ዋና ክፍልም ነው። ከሞላ ጎደል በአለም ላይ የነበሩ አንባገነኖች ሲቀየሩ የሆነው ይሄ ነው። በኛም አገር በህዝባዊ እንቢተኛነት ምክንያት የመግዛት አቅሙ አሟጦ የጨረሰውን  የሀይለስላሴ መንግስት እዛው አዲስ አበባ ውስጥ የተሰባሰቡ ወታደሮች የሚታሰረውን አስረው የተገደለው ተገድሎ የቀረው በሸሸበት ፍፃሜውን ሰርተውታል። በተመሳሳይ አሁን ባለተራ የሆኑት ገዥዎች የደርግን ስርአት በጦርነት አሸንፈው አዲስ አበባ ሲገቡ የሆነው ተማሳሳይ ነው። ብዙዎች የደርግ ባለስልጣናት ነገ ኑና እጃችሁን ስጡ ተብሎ በራዲዬ በተለፈፈበት ተግባራዊ አድርገውት የስርአቱ ፍፃሜ ሆኗል። የሐይለ ስላሴ መንግስት ተገርስሶ ወደወታደራዊ አገዛዝ ውስጥ ከገባንባቸው ምክንያቶች ዋናው በጊዜው ህዝብን ሲያታግሉ የነበሩ ድርጅቶች “መጨረሱ” ላይ ዝግጅት ስላልነበራቸው ነበር። አሁን ላይ ይህን ሁሉም የሚስማሙበት ነው። ባይስማሙም እስካሁን ስለነበረው ሁኔታ ከተፃፈውም ሆነ ከተነገረው እቅድ የነበረ መሆኑን የሚያሳይ ምንም መረጃ የለም። መኮንኖቹ ግን ስልጣን መቀማትን አቅደውበት ነበር። በቀጥታ የመጀመሪያ ስራቸው ስልጣኑን መቀማት ነበር። ሊተገብሩት የተሻለ አቅሙና አደረጃጀቱ ስለነበራቸው ፍፃሜውን ሰርተው ቀጣይ መንግስት መሆን ችለዋል።

አሁንም ያረጀ፤ የጨረሰና የታዳከመ አገዛዝ ነው ስልጣኑ ላይ ያለው። ዛሬም ቢሆን ባግባቡ አጨራረሱ ላይ ያቀደበትና በተገቢው ከውኖ ማሳካት የቻለ ስልጣኑን ይወስዳል። ይህ የማናስቀረው ሂደት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ብዙ ስጋቶች ይኖራሉ። የበዙት የስርአት  ለውጥ ውስጥ ሁሌም የሚኖሩ ናቸው። ማለት የሚቻለው ያሉ ስጋቶችን ግምት ውስጥ ባስገባ የተደላደለ ሽግግር ለማድረግ የሚያስችሉ መነገዶች ይኖራሉ ነው።

እርጅና የሚለው የድሜ ወይ የጊዜ ጉዳይ አይደለም። አገዛዙ መፍትሄ ብሎ የሚሞክረውም ሆነ እነደ መፍትሄ ተነግሮትም ሆነ ተመክሮ ሳይቀበላቸው የቀሩ  ሀሳቦች በሙሉ ተግባር ላይ ውለውስ ቢሆን ተብሎ ከተሰላ በሗላ የሚገኘው ውጤት ይህም ሆኖ አይተርፍም የሚል  ሲሆን ነው። አንድ አንባገነናዊ አገዛዝ እዚህ  ሁኔታ ውስጥ ሲኖር ፋፃሜውን ለማድረግ የሚያስችሉ እቅዶችን  የማስቀምጡ አስፈላጊነት አሌ የማይባል  ነው።  ሀላፊነት የሚሰማቸውና ለማሸነፍ የሚታገሉ ለውጥ ፈላጊዎች ከሆኑ ይሰሩታል። ብዙ አማራጮችን መርምሮና አስቀምጦ ከነዛ ውስጥ የተሻለውን በጥንቃቄ መምረጥንም ግድ ይላል። ቁም ነገሩ እንቅልፍ የሚያጣበትና ሀሳቡን ይዘውት ተኝተው ይዘውት ደግሞ የሚነሱን ይፈልጋል። አጨራረሱ ጥብቅ ሚስጥራዊነትን የሚፈልግ ቁምነገር መሆኑ እንዳለ እንዳይከሽፍ ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ጠቅለል ባለ ቀድሞ ማስታወሱ ጉዳት የለው አይመስለኝም። በዋናነት በዜጋው ዘነድ ሊመጣና ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ዱብ እዳ እንዳይሆኑም ማሰብ አለበት። ማወቁ ጥሩ ነው። የሽግግሩ ዋዜማና-ባሻገር ላይ ለምንሰጋባቸው ጉዳዬችም ፍቱን መድሀኒትነትም አለው ።

የትኛውም  “መፈፀሚያ” እቅድ  በዋናነት ሶስት ነገሮችን ግምት ወስጥ ባስገባ ተሰርቷል። የመጀመሪያው የአሮጌው ስርአት ዋና፤ ዋና ሰዎች ቦታ ቦታ ማስያዝ። ሁለተኛው ጊዜን ግምት ውስጥ ባደረገ ሊኖር የሚችለውን  የህግና የስርአት አልበኛነት ተቆጣጥሮ ሰላምና መረጋጋትን በቶሎ ማስፈን። ሶስተኛው መንግስት በቶሎ ማቆም ናቸው። የታጠቀ ሀይል እየተኮሰ ቤተ መንግስቱን በርግዶ ገብቶም ይሁን ህዘብን በገፍ አስወጥቶ  አሯርጦ እንዲያወጣቸው ይደረግ፤ አልያም ቤተመንግስት ውስጥ ተሰብስበው ከሰል እየሞቁ ባለበት አናታቸው ላይ ሌላ መንግሰት ይመስረት፤ ወይም ከገዛዙ ለለውጥ ዳተኛ የሆነውን ክፍል በማስወገድ ለየት ባለና በተደላደለ…  ፍፃሜዉ ይሰራ። ቀድመው መሰራት የሚገባቸው ስራዎች አንድ አይነት ናቸው። ልዩነቱ እንደትግል ምርጫው አይነት በምን ያህል ስፋትና ጥልቀት የሚለው ብቻ ነው።  ለስራው በቂ የሰው ሀይል፤ መረጃ በዋናነት፤ አፈፃፀሙን የሚያቅድና ተፈፃሚ የሚያደርግ አካል፤ ስራው ላይ እውቀት፤ ከአሮጌው ስርአት ውስጥ ለውጥን የተጠሙ ክፍሎች አጠቃቀም። በዜጋው ዘንድ ሊመጣ ያለው ለውጥ ላይ  የግንዛቤ ስራ ። ዲፕሎማሲና የተባበረ ለውጥ ፈላጊ። ለየትኛውም አይነት ፍጻሜውን መስርያ እቅድ ተረግጦ የሚነሳባቻው  ናቸው።

የሰው ሀይል፤-  አሁን በለውጥ ዋዜማ ላይ ሆነን አይደለም ዜጋው ለነፃነቱ ግድ አይሰጠውም በሚባልበትም ጊዜም ቁጥሩ ቢያንሰም ያለ ብዙና ተደደጋጋሚ ጥረት ታጋይና ይህን አይነት አገራዊ ሀላፊነትን ሊወጣ የሚችል ዜጋ ማፍራት ይቻል ነበር። እድሉን ያገኛል አያገኝም የሚለው ካልሆነ  አሁን አደባባይ ወጥቶ እየተቃወመ ያለው ዜጋ ሁሉ ትግሉ ላይ ተጨመሪ አገራዊ ሀላፊነትን ለመውሰድ እግረመንገዱን ፍላጎቱን እየገለፀ ነው። ስለዚህ ችግሩ ለስራው የሚያስፈልገውን የሰው ሀይል ከማግኘት በላቀ የሰው ሀይል አጠቃቀማችን ላይ ያለ ዳተኘነት ይሆናል ማለት ነው። የሚሰራ ሳይሆን የሚያሰራና መሰራቱን የሚከታተል ሀላፊ ያሻል። በጠቅላላ  አንድ አይነት ፍፃሜውን ማድረጊያ እቅድ ማስቀመጥ። የሚያስፈልገውን የሰው ሀይል በየስራ ዘርፉ መሙላት ይኖራል።

ለስራው የሚያሻው እውቀት በቀጥታ ከትምህርቴ ቤት፤ በስራ ልምድ፤ በእድሜ የዘናቸው የምንመጣቸው እንዳልሆኑ ግልፅ ነው። ሊታገል ቆርጦ ለገባና አገራዊ ሀላፊነቱን ለተቀበለ አቶ ሳሞራ የኑስ የጦር መሪ አቶ ጌታቸው ደግሞ የደህንነት ሀላፊ ከሆኑ ማንኛችንም! ነው ሚስጥሩ።እንዲህ ካሰብን ፍፃሜውን ሊሰራ የሚችል የሰው ሀይል አለን ማለት ነው። አሻግረን መዋረድና መጨቆን ለውጥን እንዲራብ ስላደረገው የሰው ሀይል ጨምረን ካሰላን  ከኛም በላይ የተላገጠበት ግን ስርዓቱን ያቆመ እጅግ ብዙ የሆነ የሰው ሀይል ደግሞ ለጊዜው በዛ ጎን ተሰልፎ አለ። ይህ የሰው ሀይል ትግሉ ላይም ሆነ አጨራረሱ ላይ የሚኖሩ ወሳኝ የሀላፊነት ቦታዎች ላይ ልምዱና እውቀቱ ሰተት እያለ ሄዶ የሚገጥም  ነው።

መረጃ፤- ባጭሩ ካለን እናሸንፋለን። ከሌለን አናሸንፍም። ካለን አጨራረሱን እናውቅበታለን። ከሌለን ትግሉ  ላልተወሰነ ጊዜ ይንዘላዘላል። ለማሸነፍ የሚያስፈልገን መረጃ አይነቱ ለማግኘት አስቸጋሪ የሆነው አይደለም። መረጃ ማሰባሰብ ማደራጀትና መጠቀም ትግሉ ላይ መሰራት ከሚገባቸው ስራዎች ሁሉ ያለብዙ የገንዘብ ወጪ ሊሰራ ከሚችሉ ግን ወሳኝ ከሆነ የስራ ዘርፍች አንደኛው ነበር።  ለስራው መነቃቃት ይሆናል ካልን ልክ እንደ ገንዘቡ መዋጮ በበይነ መረብ ሊሰበሰብ የሚችል አይነት መረጃ ነው አሸናፊ የሚያደርገን።  የመረጃን አስፈላጊነት የገባቸውና መለስተኛም ቢሆን አትኩሮት የሰጡትና የሰሩበት ወደ ነፃነት ይመሩናል።

እቅድና ተፈፃሚነቱን የሚከታተል አካል፦ አጨራረሱ ትግሉ ላይ የጠቅላላ እቅዱ አንድ አካል እስከሆነ ድረስ ቀድሞ በአግባቡ መታቀድም ሆነ  ባለቤት ያለው የመሆኑ ዋናነት ሁሉ የሚረዳው ነው። ይህን አይነቱ አካል አገር ውስጥ ቢሆን እሰየው። ካልተቻለ ሰማይ ላይም ይሁን መኖር ግን አለበት። እቅዱን ለማስቀመጥም ሆነ ሀላፊነቱን ለመውሰድ የግድ ወታደር መኮን ግን የለበትም። ለማቀድ መፍትሄን ማሰብን ልምድ ያደረገ ጭንቅላት፤ በቂ መረጃና ጊዜ ነው ሊገዛለት  የሚገባው።

የተባበረ ለውጥ ፈላጊ፦ እጅግ አስፈላጊ ነበር። የግድ መሆን ያለበት ግን አይደለም። መኖሩ ፍፃሜውን ከመስራት በላፈ ሽግግሩን አልፎም በቀጣይ የሚቆመውን  መንግስት ጠንካራ ለማድረግ የሚኖረው ፋይዳ የበዛ ነው። ትብብር በባህሪው የሌሎችንም መልካም  ፊላጎትና ፍቃደኛነት የሚያሻ ስለሆነ ምን ማድርግ ይቻላል። በኛ አገር ሁሉን ያካተተ ትብብር ለማድረግ መካተት ያለባቸው ብዙ ሆኑና አልተቻለም። አግላይነትና ተንኮል ተጨምሮበት  ሳይቻል የስርአት ለውጥ የሚሆን ይመስላል። ተችሎ ቢሆን ኖሮ ግን በዛሬው ያገራችን ጠቅላላ ሁኔታ የዚህ አይነቱ ትብብር እራሱን ችሎ “የመፈፀሚያ እቅድ” ሊሆን የሚችልበት እድል ነበረው።

“ የኢትዬጵያ ህዘብ ሆይ እናቶች፤ ገበሬዎች፤ ያገር መከላከያና የፖሊስ ሰራዊት አባላት፤ ሴተኛ አዳሪዎች፤መምህራንና አስተማሪዎች፤ በጠቅላላው መላው የኢትዬጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ከዛሬ ከዚህ ቀንና ሰዓት ጀምሮ ፍፁም ነፃ ህዝቦች ናችሁ። ከዛሬ ጀምሮ ይህን ስርዓት መታዘዝ ሆነ ማገልገል ለማንኛውም ዜጋ  የተከለከና ወንጀል ሆኗል”። አዋጅ ይኖራል።

መታወቅ ያለበን እኩልነትና የወያኔ የበላይነት መቀጠል አለበት በሚል አገዛዙ ለሁለት በተከፈለበት ሁናቴ ውስጥ ለለውጥ ፈላጊው ሜዲያውን ካገዛዙ ተታኩሶ መቀማት ላያስፈልግው ይችላል። ፍፁም የበላይነታቸውን ለማስቀጠል የህዋዋት ጀነራሎች መፈንቅለ መንግስት ሊሞክሩ ይችላሉ። ይህ ሲሆን ሀይለማርያምም ለማ መገርሳም፤ ገዱም አባላቱ ሁሉ በሚሊዬኖች በትግሬ ወያኔዎች ተገዳይ ታሳሪ ካነሰም ተራጋፊ ናቸው።

እውቀት፦ ቁርጠኝነት፤ ፃናት ፤ ታማኝነት ….የመሳሰሉት ጉዳዬች እጅግ አስፈላጊ ቢሆኑም ጥሩ ታጋይ እንጂ ሁሌ አሸናፊ የሚያደርጉ አይደሉም። ለዚህ ብዙ ምሳሌ መስጠት ይቻላል። ማሸነፍ የሚያስችል እቅድ ማስቀመጥና ማስፈፀም የሚችል እውቀት ሲኖር ግን ያኔ ማሸነፍ እርግጥ ሲሆን እያየን ነው። ከመነሻው መንግስት መሆን የማይገባቸውን ያንድ መንደር ሰዎች ያቆሙትን ስርአት  ሀያስድስት አመት ታግለን ለምን አላሸነፍንም? ሲባል ትግሉ ላይ ችግር ተደርገው የሚደረደሩት ምክንያቶች በሙሉ በግልፅ አይነገሩ እንጂ መፍትሄ የሌላቸው ስለነበሩ ነው እየተባለ መቼም አይደለም። ቢባልም የተቋቋሙበት አንድና አንድ አላማና ስራ ታግሎ ማሸነፍ ለሆነ አካል ይህንን አንድ ተግባር ከግብ ለማድረስ አቅቶት የሚደረደርው ሰበብ ተቀባይነት በጭራሽ ሊኖረው አይችልም። ለነገሩ ጭንቅላቱ ጠፍቶ ግን አይደለም። አናሰራው ሆኖ ነው። ባህሉ ነው የጠፋው። ለማንኛውም አንድ አይነት ፍፃሜውን መስርያ እቅድ አስቀምጦ ተፈፃሚ ለማድረግም ሆነ ከዋዜማው- እስከመባቻው ሊኖሮ የሚችሉ ተግዳድራቶችን ለማስቀረት መፍትሄ ማፍለቅ የሚችል ጭንቅላት አስፈላጊ ነው።

ካገዛዙ ጋር ተጣምረው ስላሉ ዜጎቻችን፤- ተጠቃሚ እንጂ ሁሉም እንደኛው ተጨቋኞች ናቸው። ይህ እውነትነቱ ተረጋግጧል። ይህን የማህበረሰብ ክፍል የለውጡ አካል ማድረግ ይቻላል ወይ?። ሆኖ እያየን ነው። አሁንም ቢሆን መሳርያ በጁ ያለው ቆርጦ ከወገኑ ጎን ይቆማል። እስካሁንም ያልቆመው  ስላላወቅንበትና ምንም ስለማንሰራ ብቻ ነው። መሳርያ በጁ ያለውን ቆርጠን እንስራው ካልን ያለምንም ማጋነን በተናጠል እያንዳንዳቸውን ልንደርሳቸው አቅሙ አለን። በተነጣል መድረሱ ያደከመናል ካልን ደግሞ ቀን ይቆረጥናን ሙሉ ትኩረትን ሰጥተነው የማሳወቅና የማዘጋጀት ስራ እንስራ ተብሎ ነበር። ጠቃሚነቱን አይተው ሀሳቡን ገዝተውት ቢሆን  ኖሮ ዛሬ

የሚኖረው ታሪክ የተለየ ነበር።  ትግል ላይ ነን ካልን ተሰርቶ ሊለወጥ የሚችል ለመሆኑ የኦሮሚያ ፖሊሶችን አይተን እንኳ ለመስራት ብርታት ሊሰማን ይገባል። ትንታኔና ነገር መጠሰቅ ነፃ አያወጣም። መስራት ሲገባን ብዙ እያወራን የህዝብን ትግል እየጎዳን ነው። ለአርባ ሚሊዮን ህዘብ ስንት ቄሮዎች ነው ያሉት?። ልክ በዛው መንገድ ለሁለት መቶ ወታደር ስንት መሪ ሊሆኑ የሚችሉ እንደሚያስፈልገን ማወቅ ይቻላል።

ሊመጣ ያለው ለውጥ ላይ የዜጋው  እይታ፦ ጥሩ አይደለም። ለዚህ ምክንያቱ ብዙ ነው። ስርአቱ እኔ ከሌለው ለንጫረስ ልንፋረስ ነው ይላል። ተቃዋሚዉም በግልፅ “አንተ ካሌለህ” ባይልም ይህንኑ የሚልበት ሁኔታ ነው ያለው። በዚህ ላይ ደግሞ ለውጥ በባህሪው አስፈሪነት አለው። አድሎንና ግፍን ተንገሽግሸን ለውጥን ደግሞ ፈርተን አይሆንም ተብሎ ነበር። ለውጡን በሚያንቀቀሳቅሱ ክፍሎች ጣናን የመታደጉ ጉዞ፤ በትግሬ ጀነራሎች ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች ገንዘብ የማሰባሰቡ ዘመቻ አይነት  ስራዎች  ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።  ጥሩ ህዝብ ነን። ባህር ዳር ላይ በአማራ ህዘብ ፖለቲካ አልነበረም። ፍፁም የሆነ አገርን መውደድ። ፍፁም የሆነ ፍቅር ነበር። የምር የሆነ ስጋትም አለ።  “የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው” የኦሮሞን ህዘብ ምን ያህል ፍቅር እንዲሰማው እንዳደረገ አይተናል።

ጠላት” ኦሮሚያ ውስጥ  ሰላምና መረጋጋት የለም እያለ ነው”። ማሸነፊያው መንገድ ሰላምና መረጋጋት ባለፈ አንድነት፤ ተነሳሽነት፤ ፍቅር እንዳለ ደግሞ ደጋግሞ ማሳየት ነው። ቆያይቶም ዶሞክራሲን፤ ነፃ ሜዲያ ማስጀመር ነው። የክልሉን የፍትህ ስርአት በነፃነት እንዲሲራ መልቀቅ ነው። ጠንካራ ለማ መገርሳ አይፈይድም። ጠንካራ ጨፌ ኦሮሚያ እንጂ።  በኦሮሞ ህዝብ ስም የተደራጁም ሆነ ህብረ ብሄራዊ ተቃዋሚ ድርጅቶች ሂዱና ኦሮሚያ ውስጥ ኦሆዲድን ፈትኑት። ሂዱ ስብሰባ ጥሩ ህዝብን አግኙ። ማበረታታና የሰከነ ለውጥን ማካሄድና ወጥመድ ከማበጀትና ከማሳጣት ጋር  ልዩነት ግን አለው። ይህ ካልገባንና ወጥመድ ከበዛን ለዋናው ጠላት የተሻለ እድል እየሰጠን ነው ማለት ነው።

በተረፈ መጪው ጌዜ መልካም ነው። ክፍታ ነው። በእርግጠኝነት ኢትዬጵያ ውስጥ ይህ የመጨረሻው አንባገነን ነው። ከዚህ በሗላ ስልጥንን ከየክልሉ መንግስቶች ጋር መጋራት ግዴታ ይሆኗል። ክልሎች ደግሞ ከየዞኖቹና ከተሞች ጋር መጋራት ግድ ነው። ይህ በሆነበት አንድ ፈላጭ ቆራጭ ታሪክ ነው። ፈላጭ ቆራጭ ከሌለ ደግሞ ጉልበተኞች እኛ ዜጎች ነን። ዲሞክራሲ፤ ናፃ ሜዲያ፤ ነፃ ምርጫ፤ ነፃ የፍትህ ስርአት ማን አባቱ ነው የሚከለክለን። እንጫረሳለን እንፋረሳለን ሽብር ነው። ሽብርተኖች ናቸው ይህን የሚሉት። መረሳት የሌለበት ይህን የሚለው  በዋናነት እራሱ የምንታገለው አካል ነው። ካልሆነም ጥላቻና ንቀት ደፍኗቸው ይህን ያህል ዘመን አብሮ የኖረንና ለአገሪቷ መሰረት የሆነውን ህዘብ ሊያውቁት በጭራሽ ያልቻሉ ናቸው።

ኦሮሞ  በውጪም በውስጥም ያለው አንድነቱንና ፍላጎቱን  አንድ ሚሊዬን ጊዜ አሳየ እኮ። ይሄ እንግዴ የትናንት ታሪክ አይደለም። የሌለ ልዩነት አለ ብሎ ሙግቱን ምን አመጣው?። የህዘብ ጥያቄ አዲስም አይደልም። ምንም የተደባበቀ ነገርም የለውም። አብሮ ለመኖር ለማፍቀርም ሆነ ለሌውን ለመወደድም ሆነ ለወገኑ ድህንነት ለመጨነቅ የሚደበቀው የሚተወው ጥያቄና ፍላጎትም የለም። መኖርም የለበትም። የጨፌ ኦሮሚያ ወደ አማራ ክልል ጉዞ ሰለጋራ አገር፤ ስለፍቅርና ስለሰላም በዋናነት ስለነፃነት የሚደረግ ነው። አለቀ። ለህዝብ ይሄ የዛሬም የአፍም አይደለም። ኑሮው ነው። ሁሌም ቢሆን በደሙ ጭምር ሲያደርገው የኖረው ነው። ትናንትም ዛሬም ሲያደርግ እንደነበረው ነገም ለመብት መከራከር፤ መታገልና ማስከበር ደግሞ ይኖረል። እውነቱ ነው የሚሻለው ብዬ ነው። ድሮም መብት የሆነውን ነገር ጥላቻ ነው ያሉትም ሆነ ዛሬም ኢትዬጵያ ኢትዮጵያ ተባለ “ታምር ተፈጠረ” የሚሉት ትምክተኞች ናቸው። ለነገ ልዩነት መፍጠሪያ ሊያዘጋጁን ነው። እነዚህ ትምክተኞች ይሄ ህዝባዊ እንቢተኛነት ከተጀመረ እንኳ ለአንዴ ትክክል መሆን አልቻሉም። ከህዝብ ትግል ጎን መቆምም አልቻሉም። ጥላቻቸውንና ንቀታቸውን ማሸነፍ ካልቻሉ መቼም ትክክል ሊሆኑ አይችሉምና  ህዘብ ሆይ አትስማቸው።

Share Button