… አንዱ ሲሰበር ዘጠኝ ይቀራል፤ የእስረኞቹን መለቀቅ አንድ ብለናል! – ከያሬድ ኃይለማርያም

የካቲት 9፣ 2018 እ.አ.አ

በእኩይ ሥራዎቹ የጠለሸው ወያኔ ከተሸከማቸው ሃጢያቶች አንዱን ለማራገፍ ሲታገል ማየት ይበል የሚያሰኝ ነው። ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ይቅር ባይነት እጅግ ከባድ ፈተና በሆነበት የፖለቲካ ባህላችን ውስጥ መቶ ሃጢያት የተሸከመውን ወያኔን አንዱን ከላዩ ላይ ለማራገፍ ሲውተረተር መደገፍና ማበረታታት በብሶትና ክፌት ውስጥ ለተዋጠ ሕዝብ ይከብድ ይሆናል። ይሁንና ለአገር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሲባልም ቢሆን ሥርዓቱ ተገዶ እያጥወለወለውም ይሁን በፈቃዱ  የሚወስዳቸውን አንዳንድ በጎ እርምጃዎች ማበረታታት ግን ተገቢ ይመስለኛል። በዶ/ር መራራ የተጀመረው እስረኞችን የመልቀቅ እርምጃ አሁን ደግሞ ታዋቂውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን እና አንዷለም አራጌን ጨምሮ ከ700 በላይ እስረኞች ሰሞኑን በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲለቀቁ መንግስት መወሰኑን በትላንቱ የዜና እወጃ ሰምተናል። እንኳን 700 ይቅርና የአንድ በግፍ የታሰረ እስረኛ ነጻ መውጣት ማን የማያስደስተው አለ። እጅግ ደስ ብሎኛል።

ዜናውን ስሰማ አንድ የልጅነት መዝሙር ትዝ አለኝና ለራሴ ማንጎራጎር ጀመርኩ፤ “አሥር አረንጓዴ ጠርሙሶች በግርግዳ ላይ፤ ድንገት አንዱ ወድቆ ሲሰበር ዘጠኝ ይቀራል”። መዝሙሩ ሁሉም ጠርሙሶች ተሰባብረውና መደርደሪያው ባዶ እስኪቀር ድረስ ይቀጥላል። እነዚህን ጠርሙሶች ወያኔ ባለፉት 26 አመታት ውስጥ ቂም፣ ጥላቻ፣ ጎጠኝነት፣ እብሪት፣ ሙስና፣ ግፍና በደል፣ መድሎ፣ ዝርፊያ፣ ስደት፣ እስራት፣ ግድያ፣ አገር ግንጠላ፣ መሬት ንጥቂያ እና ሌሎች በርካታ መርዞችን እየቀመመ ሞልቶ የደረደራቸው መስለው ታዩኝ። ከእነዚህ መርዝ ከተሞሉ ጠርሙሶች ውስጥ አንዱ በከፊል ሲሰበርና በውስጡ የያዘውን ንጹሐን ዜጎችን ካለወንጀላቸው በሃሰት እየወነጀሉና ማስረጃ እየፈበረኩ ዘብጥያ የማውረጃው መርዝ በከፊል ሲፈስ ታየኝ። በሌሎቹ ዘጠኝ ጠርሙሶች ውስጥ ያሉትን መርዞች እያሰብኩ በአንዱ ጠርሙስ መሰበር ግን እጅግ ደስ አለኝ። ተስፋም አደረኩ፤ የቀሩት ዘጠኝ የመርዝ ጠርሙሶች ተሰባብረው ሲያልቁ ያኔ ኢትዮጵያም ወደ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና ልታቀና ትችላለች ብዮ ተመኘሁ፤ ተስፋም አደረኩ።  

ይህ እርምጃ እስረኞችን ከመልቀቅም ያለፈ አገራዊ ፋይዳ ያለው ስለሆነ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነገር ይመስለኛል። በተፈጥሮው ግትር የሆነው የወያኔ ሥርዓት አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለኝም ሲል ቆይቶ በተግባር ግን እነዚህን በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች መልቀቁ አፉ እንጂ ልቡ የተረታ መሆኑ በግልጽ ያሳያል። ለእኔ ከሚናገሩት የበለጠ አገሪቱንና ሕዝቡን እጅግ እየጎዳ ያለው በተግባር የሚያደርጉት ነገር ስለሆነ በነካ እጃቸው እንዲሁ ሌሎች በጎ እርምጃዎችን እየወሰዱ በሚዲያ ግን ያሻቸውን ቢቀላምዱ ግድ የለኝም። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ‘ሙልጭ ያለ ሽብርተኛ ነው’ እያሉ ባደባባይ ነገር ግን ቢለቁትና ከቤተሰቡ ቢቀላቀል፣ በቀለ ገርባን ‘የለየለት የነውጥ አራማጅ ነው’ እያሉ ቢለቁትና በነጻነት እቤቱ ቢገባ፣ ‘በእኛ እስር ቤቶች ማንም ሰው ላይ የስቃይ እርምጃ አይወሰድም፣ ተደርጎም አያውቅም’ እያሉ ነገር ግን እስረኞችን ማሰቃየታቸውን ቢያቆሙልንና እንደ ማዕከላዊ ያሉ የማሰቃያ ስፍራዎችን ቢዘጉልን፣ ‘ይች አገር ያለእኛ ትጠፋለች’ እያሉና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሁሉ ጭራቅ አስመስለው ባደባባይ እያብጠለጠሉ ነገር ግን ሁሉንም (ትጥቅ ያነገቡትን ጭምር) የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ አገራዊ የእርቅና የመግባቢያ ጉባዔ እንዲካሄድ መንገዱን ቢከፍቱ ምን ግድ ይለናል። ለእኔ የሚያደርጉት ስለሚያጠግበኝ ሃጢያታቸውን ለመሸፋፈን እርስ በእርሱ ለሚጋጨው ፕሮፓጋንዳቸው ቁብ የለኝ።

አንዷን የመርዝ ጠርሙስ እየሰበረ ያለውን ወያኔን እያበረታታን የተቀሩትን ዘጠኙን የመርዝ ጠርሙሶች ከቻለ በራሱ አቅምና በጎ ፈቃድ፤ ካልቻልም የተጀመረውን ሕዝባዊ ቁጣ በማጠናከር ተገዶ እንዲሰባብር እና እራሱንም፣ አገሪቱንም ሆነ ሕዝቡን ካንጃበቡት አደጋዎች ይታደግ ዘንድ ማሳሰብ ግድ ይላል።

  • በቀለ ገርባን፣ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሌሎቹ የፖለቲካ እስረኞች ሙሉ በሙሉ እስኪለቀቁ፣
  • የዜጎችን የፖለቲካና የሲቪል መብቶችና ነጻነቶችን የሚገፉት ጠርናፊ ሕጎች እስኪለወጡ፣
  • የማነነትና የድንበር ጥያቄ በማንሳታቸው የተነሳ ለወከባ፣ እንግልትና መድልዖ የተዳረጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄ በሕግ አግባብ ፍትሃዊ ምላሽ እስኪያገኝ፣
  • እንኳን የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ቀርቶ እያንዳንዱ ግለሰብ በአገሩ ጉዳይ ወሳኝና ባለቤት መሆኑን ሥርዓቱ አምኖ ተቀብሎ ሁሉን አሳታፊ የሆነ የመፍትሔ፣ የእርቅ፣ የሰላምና ብሄራዊ መግባባት የሚካሄድበት ‘የአገር አድን ጉባዔ’ ጥሪ እሲኪያደርግና አስፈላጊ የሆኑትን ቅድመ መደላድልና ሁኔታዎች ሥርዓቱ እስኪያመቻች ድረስ፤

የተጀመሩን ሕዝባዊ ንቅናቄዎች የሚቀጥሉ ይመስለኛል። ለነገሩ ሥርዓቱ ለማስገደድ ‘ሲስሟት ቀርቶ ሲስቧት’ አይነት ሁኔታ ውስጥ ስላለን ሕዝባዊ ቁጣውን ከመቀጠል የተሻለ አማራጭ ያለም አይመስለኝም። የሥርዓቱ ባለሥልጣናት አሁንም ወደ ህሊናቸው ተመልሰውና ግብዝ ከሆኑ አድራጎቶቻቸው ተቆጥበው ‘ከቀረ የዘገየም’ እንደሚሻል ተረድተው ለቀሩት የሕዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ቢሰጡ አገሪቱን ከግጭት፤ ሕዝቡንም ከእርስ በእርስ እልቂት ሊታደጉት ይችላሉ። የቀረው ለማንም አይበጅም።

 

ቸር ያሰማን

     

Share Button