ተጠብቆ የነበረዉ፤  ግን ያልወጣዉ የሕወሓት – ኢሕአዴግ መግለጫ! (ኆኅተብርሃን ጌጡ)

ሰፊዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!  በሰዉ በላዉና ፋሽሽቱ  አስከፊዉ የደርግ ሥርዓት ስትረገጥ በነበረበት ወቅት፤ እኛ ከአብራክህ የወጣን ልጆችህ ላንተ ስንል በሥርዓቱ ላይ አሻፈረኝ ብለን ከከተማዉ ሕይወት የጫካዉን ጎስቁዋላ ሕይወት መረጥን። በእኛ የሕይወት መስዋዕትነት አንተ  ነፃነትህን እንድትጎናጸፍ የወጣትነት ሕይወታችንን ማጣጣም ረሳነዉ። የዩንቨርስቲ ትምህርታችንንም አቁዋረጥነዉ። አንተ በደርግ ሥርዓት በመሰቃየት ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆነህ እየኖርክ፤ እኛ ስለነገ የተሻለ ሕይወት ማሰብን ከቶዉኑ ልንመኘዉ አልፈለግንም። የጉርምስና ሕይወት ፍላጎታችንም አላሸነፈንም። ሁሉንም ነገር ጠብ እርግፍ አድርገን ትተን፤ በዉሳኔያችን ጸናን። ካንተ ነፃነት በሁዋላ ብለን፤ በቁርጠኝነት ወደ ደደቢት አመራን። አስከፊዉን የደርግ ሥርዓት ለመታገል አሐዱ ብለን መራራዉን ሕይወት ለመግፋት በጧቱ ተያያዝነዉ። ይህንንም ገድለ ድርሳናችንን አሁን ሕዝብ ተራራ ሆኖ አንቀጠቀጠን እንጅ፤ …ተራሮችን ያንቀጠቀጠዉ ትውልድ… በሚለዉ ባለ ሦስት ቅፅ ትረካችን ለንባብ ማብቃታችንን አትረሳዉም።

ጀማሪዎቹ ምንም እንኩዋ ቁጥራችን አነስተኛ እንደነበር ቢታወቅም፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እልፍ አዕላፍ ወጣቶች እየመጡ ተቀላቀሉን። የትግሉ ሜዳ ትግራይ ክፍለ ሀገር ቢሆንምና አነሳሳችንም ለእዚያዉ ክፍለ ሀገር ነፃ መዉጣት እንደነበር ባይዘነጋም፤ የማልሌት ርዕዮተ ዓለምን ፅንሰ ሀሳብ ማራመድ በማቆም፤ ከተነሳንበት በጣም ጠባብ አስተሳሰብም በመላቀቅ፤ መላ ኢትዮጵያን ለመግዛት መንቀሳቀስ የሚበጅ መሆኑን ተገንዝበን ፖለቲካዊ ቅኝታችንን ዘወርነዉ። በዚህ ረገድ እኛ በትረ መንግሥቱን እንደምንጨብጥ ሲረዱ፤  እኛን በመጠጋት በወቅቱ የባሕር ማዶ አማካሪዎቻችን የተጫወቱት ሚናም የሚናቅ አልነበረም። መላ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠርም ኢሕአዴግ የሚል ሀገር አቀፍ ጃንጥላ ዘረጋን። የእኛን ዓላማ የሚያሳኩ አሻንጉሊት ድርጅቶችም ፈልፍለን በአምሳላችን ፈጠርን። ሚናቸዉም እኛ ስንጠራቸዉ አቤት፤ ስንልካቸዉ ወዴት ከማለት ያለፈ አልነበረም። ወይንም በሌላ አገላለፅ እኛን ገና ሳያስነጥሰን ይማራችሁ ከማለት የዘለለ አልነበረም። በቃ!  ባንድ ቃል እኛን እንደ ሙሽራ አጅበዉ ሙሽራዬ እያሉ የሚያዜሙ ሰርገኞችን በአምሳላችን መፍጠር ቻልን።

ይህ ከሆነ ከ 27 ዓመት በሁዋላ ግን ምን እንደነካቸዉ ሳይታወቅ፤ አሁን ጸባያቸዉ  እየተቀየረ መጣ። አዎ!  ሁሉም ነገር ባለበት አይቀጥልም። እንዲያዉም ዘግይተዋል። ታሪክ እራሱን ይደግማል እንደሚባለዉ፤ እኛም ባሳዳጊያችን በሻዕቢያ ላይ ፀባያችን ተቀይሮ፤ ኤርትራን ካስረከብን በሁዋላ  ባድመ ሰበብ ሆና፤ ጦር እንደተማዛዝነዉ  ሁሉ፤ ሕወሓት የፈጠራቸዉ ድርጅቶችም ጦር ከመማዘዝ ደረጃ ገና ባይደርሱም፤ አመላቸዉ እንደወትሮው አይደለም። ሕዝብም ከጎናቸዉ እንደተሰለፈ የአደባባይ ምስጢር ነዉ። ይህም የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል። ከሕዝብ በላይ ምን ጉልበት አለና። በአመራር የአስተዳደር ጥበቡ የሕዝብን ልብ ያላሸነፈ መንግሥት የቀን መቁጠር ጉዳይ እንጂ፤ ስለ መዉደቁ አይቀሬነት ለማወቅ ኑፋቄ ዉስጥ መግባት አያስፈልግም። ከዳር እስከ ዳር ሕዝባዊ አመፁ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጥሏል። ማን ነበር? ካርል ማርክስ ነበር? …አመፅ ያረገዘን ኅብረተሰብ ታዋልዳለች… ሲል እንቅንጩን የተናገረዉ። የኢትዮጵያ ሰማይ አርግዟል። ደመናዉ አንዣቧል። ዝናብ ብቻ ይሁን በረዶ ቀላቅሎ ይጣል አለየለትም። በጎርፉ ማን እንደሚወሰድም የጎርፉን የፈሰስ አቅጣጫ  ለመተንበይ አስቸጋሪ ሆኗል። እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለዉ ግን ሁሉም ነገር በነበረበት እንዲቀጥል ግትር አቁዋም የምናራምድ ከሆነ፤ ጎርፉ እኛን መዉሰዱ አይቀሬ መሆኑ ነዉ።

በጎርፉ ልንወሰድም ይገባናል።  እኛም አብዝተነዉ ነበርና። አዲስ አበባ ስንገባ ወጣት ተጋዳላዮችን ያየ ሕዝብ፤ ፀጉራችን ተንጨፍርሮ፤ ማበጠሪያ ሳያዉቀዉ፤ ቅማል እንደወረረዉ፤ ውኃ ሳይነካዉ እኒህ ናቸዉ?  የደርግን ወታደር ያሸነፉት?  በማለት እንዳልተገረመ፤ እንዳላደነቀን  ለዓመታት እንዳልኖረ፤  የገባነዉን ቃል ረሳነዉ። የሕዝብ ብሶት የወለደነን፤ ብለን እንዳልፎከርን፤ ሕዝብን መርገጥ ጀመርን። ብሶት የወለደን ነን ብለን ተነስተን፤ ለሕዝብ ብሶት ወለድን። ገጠር እያለን በትግሉ ዘመን በእዉነትም ለሕዝብ የቆምን መሆናችንን የሚያመላክት ባሕርይ የተላበስን ነበርን። ቀምለን መታገላችንንም ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያዉቀዋል። አስከፊዉን የደርግን ሥርዓት በመጣላችንም ሙሉ ድጋፉን ሰጥቶን እንደነበር አንዘነጋዉም። ከተማ ስንገባ ግን ቀሚስ አደናቀፈን። የእኛን ውኃ ተጸይፈን፤ በእስኮትላንድ ዉኃ መዋኘቱን አበዛነዉ። ስኩዋር መቃም በጣም ለመድን። ሥጋዎ ደሙ ለመቀበል እንደ ታደሉ ባልና  ሚስት  እኛ በሙስና ቆረብን። ሰማይ ጠቀስ ፎቅ መገንባቱን ሥራዬ ብለን ተያያዝነዉ። ለዘላለም የምንኖርበት አስመስልነዉ። መሬት መቀራመቱን አስከ ሰባት ትዉልዳችን  አንበሸበሽነዉ። …መሬት የሕዝብ የሚሆነዉም በኢሕዴግ መቃብር ላይ… ብቻ እንደሆነ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርኃችን ደንግገን መሬትና  እኛ ክርና መርፌ ሆነን ተቆራኘነዉ። ያ ኤርምያስ ለገሰ የሚባል ሚኒስትር ደኤታችን የነበረ ሰዉ፤ …የመለስ ትሩፋትና … የመለስ ልቃቂት…. በተባሉት ሁለት ድንቅ መጻህፍቱ መሬት መቀራመትንና  የዝርፊያ ኢኮኖሚ ግንባታችንን አስመልክቶ በትክክል ያስቀመጠዉ ስለሆነ፤ እዚህ ላይ በመድገም እናንተን ላለመሰልቸት እናልፈዋለን።

ሕዝብ 27  ዓመት ሙሉ ታገሰን። እንደ እኛ ተንኮል ሳይሆን፤ እንደ ሕዝቡ ሆደ ሰፊነት እኛ እየኖርን ሕዝቡን አኗኗሪ እና የበይ ተመልካች አደረግነዉ። በገዛ አገሩ ባዕድ ሆነ። አያገባህም አልነዉ። እናም እኛ እራሳችን ወደ አመፅ ገፋፋነዉ። በተለይ በሀገሪቱ በቁጥር ደረጃ የወሳኝነት ሚና ያላቸዉን አንጋፋ ብሔሮች እርስ በርስ እያባለን ተጫወትንባቸዉ። ትንሽ አመላቸዉ ቀየር ሲልም፤ አንደኛዉን ነፍጠኛ፤ ሌላኛዉን ትምክህተኛ በማለት እንዲሸማቀቁ አድርገናቸዉ ኖርን። ወርድና ቁመት አሳጣናቸዉ። በየጊዜዉ ለሚነሳዉ መሠረታዊ የመብትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ሁሉ ተገቢ መንግሥታዊ መልስ በመስጠት ፋንታ … ይህ የነፍጠኞችና የትምክህተኞች ጥያቄ ነዉ… እያልን ጧት ማታ እነሱን በማሸማቀቅ ላይ ብቻ ባተኮረ ፖለቲካ እራሳችንን ስናታልል ኖርን።  የእኛን ቱልቱላ የሚነፋዉ ቲቪያችንና ሬዲዮናችንም  ይህን ፕሮፖጋንዳ ከማስተጋባት አንድም ቀን ወደሁዋላ ያለበት ቀን የለም። እኛን ጠባቦች ብለዉ እንዲጠሩን ግን አይፈቀድላቸዉም። እኛ የማንገሰስ፤ የማንደፈር ኃይሎች አድርገን እራሳችንን ቆጥረናልና። እንዲያም ሲል ሰይፍ ይመዘዝባቸዋል።

ግን አሁን አስራ አንደኛዉ ሰዓት ደረሰ። ያ ከይሲ ይቅርታ ባለ …  ራዕዩ … መሪያችን መሬት ይቅለለዉ ወይም እንደ ሥራዉ ይስጠዉና … ሁለቱ ብሔሮች አንድ የሆኑ ቀን፤ ያን ጊዜ ድርጅታችን ሕወሓት ያልቅላታል… እንዳለዉ ትንቢቱ በመፈጸም  ዋዜማ ላይ ነዉ። የያንዬዉ የጎንደሩ ሰላማዊ ሰልፍ መልክት አንሶ፤ አሁን ደግሞ ሰሞኑን ወለጋ ላይ በተደረገ ሕዝባዊ ሰልፍ …የኦሮሞ ጠላት አማራ አይደለም፤ የአማራም ጠላት ኦሮሞ ሊሆን አይችልም… ብለዉ ሲደግሙት የጋራ ጠላታቸዉን ለይተዉ አወቁ ማለት ነዉ። ከእኛ መካከል የዚህን መልክት ፍቺ  ምንነት የማይገነዘብ ፖለቲከኛ ካለ፤ ከስሜት ሕዋሳቶቹ አንደኛዉና ዋናዉ የጎደለዉ መሆን ይኖርበታል። እናም እንወቅበት።

አሁን እንደተለመደዉ አጣብቂኝ ውስጥ ስንገባ እየሸወድን የምናልፍበት ጊዜና ወቅት ላይ አይደለንም። እስረኛ መፍታትም አንድ መንግሥት አስፈላጊ ሆኖ በሚያገኝበት ወቅት ምሕረት ማድረግ የተለመደ አሰራር እንጂ፤ አዲስ አርምጃም አይደለም። በእርግጥ የሚፈቱ እስረኞችና  ቤተሰቦች ወገኖቻቸዉ ከእስር ሲፈቱ በደስታ መፈንደቃቸዉ አይታበሌ ነዉ። የሕዝባዊ አመፁ አነሳስና መሠረታዊ ምክንያት ግን በእስረኛ ማስፈታት አርምጃ ብቻ ተወስኖ የሚቀር እንዳልሆነ፤ ሳንወድ በግድ ልንዉጠዉ የሚገባን መራራ እንክብላዊ እዉነታ መሆኑን የግድ መቀበል ይኖርብናል። ባጭሩ ጉዳዩ …ቆቅ ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ… እንዳይሆንብን የተጠየቅነዉ መሠረታዊ ለዉጥ ስለሆነ፣ እኛ ከመሠረታችን እንለወጥ። እናም ሁላችንም ባሁኑ ሰዓት የማሰቢያ የስሜት ሕዋሳቶቻችን ጭራሽ ማሰብ ከማቆማቸዉ በፊት እና  እኛም፤ ሀገሪቱም ከመጥፋቷ አስቀድሞ፤ የኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚከተለዉን መግለጫ ለማዉጣት ተገዷል።

1ኛ. ማንኛዉም በሀገሩ ጉዳይ የሚያገባዉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያጠቃለለ አስቸኩዋይ ብሔራዊ ጉባዔ የሁሉም ምርጫ ስምምነት ባለበት ቦታ እንዲደረግ፤

2ኛ. እኛን (ሕወሓት/ኢሕአዴግን) ከእስካሁኑ ተግባራችን በመነሳት እምነት የሚጣልብን ሆነን ባለመገኘታችን፤  ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የሚስማሙበት አደራዳሪ ሀገሮች በአደራዳሪነት ጉባዔዉን እንዲመሩ፤

3ኛ. ጉባዔዉ በሚያደርገዉ ስምምነት መሠረትም  የሁለት ዓመት ዕድሜ ብቻ የሚኖረዉ የባለ አደራ መንግሥት እንዲቁዋቁዋም፤

4ኛ.  የባለ አደራ መንግሥቱ  ሀገሪቱ  የምትመራበት የወደፊቱ ሕገ መንግሥት እንዲረቀቅና በሕዝብ እንዲጸድቅ ካስደረገ በሁዋላ ሕዝብና ሀገርን የሚወክል መንግሥት በማስመረጥ ሕልዉናዉ እንዲከስም ይደረጋል፤

5ኛ. የባለ አደራ መንግሥቱ እንደተቁዋቁዋመ፤ የሀገሪቱ ብሔራዊ ጦርና የሀገሪቱ ጠቅላላ መንግሥታዊ መገናኛ ብዚኃን (ማስሚዲያ) አዉታሮች የሚመሩት በባለ አደራ መንግስቱ ሥልጣንና ቁጥጥር ስር ይሆናል፤

6ኛ. የባለ አደራ መንግሥቱ የመጀመሪያ ተግባር የፖለቲካና የኅሊና እስረኞችን ከእስር መፍታት ይሆናል፤ በደረቅ ወንጀል እንደ ነፍስ ግድያና ስርቆት በመሳሰሉት ካልሆነ በቀር፤ ከመንግሥት በነበረ የአመለካክት ልዩነት በተለይ የሽብርተኝነት ታፔታ ተለጥፎባቸዉ ዘብጥያ ወርደዉ በእስር የሚሰቃዩ የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኩዋይ እንዲፈቱ ያደርጋል፤

7ኛ. በፖለቲካ የአስተሳሰብ ልዩነታቸዉ ምክንያት ብቻ እንደ ባላንጣ በመታየታቸዉ እስርንና ግድያን፤ አፈናን በመሸሽ ከሀገራቸዉ የተሰደዱ ማናቸዉም ኢትዮጵያዉያን (ት) የባለ አደራ መንግሥቱ አስቸኩዋይ ጥሪ ከዋስትና ጋር ሰጥቷቸዉ ወደ ሀገራቸዉ እንዲመለሱ እንዲደረግ፤

8ኛ. የባለ አደራ መንግስቱ በሚያወጣዉ የሀገሪቱ ሕግ መሠረት የሕግ የበላይነት መስፈኑ ሲረጋገጥ፤ ሁሉም ተገዥነቱ ለሕግ መሆኑ ሲታመንበትና ሕግ በሀገሪቱ በተግባር መተርጎም ሲጀምር ሁሉንም አካላት ሕግ እንዲዳኛቸዉ ይደረጋል፤ የሕግ የበላይነት በሀገሪቱ መስፈኑ ሳይረጋገጥ በዘፈቀደና በስሜት በማናቸዉም ዜጋ ላይ የሚወሰድ አርምጃ አይኖርም፤

9ኛ. ካሁን በሁዋላ በሚፈጠር መንግሥት የሀገሪቱ ብቸኛ አሳቢና ባለቤት ጦሩንና የደህንነት መሥሪያ ቤቱን በእጁ ያደረገ አካል ብቻ አይደለም። ሀገሪቱ  የሁሉም ናት። በሀገሪቱ ጉዳይ የሚያገባዉም ሁሉንም ነዉ። የሀገሪቱ የመካለከያ ኃይልና የደህንነት መሥሪያ ቤቱም የሀገርንና የሕዝብን ደህነንት በማስከበር ተግባር ላይ ያተኮረ እንጂ፤ ትዕዛዝ በመቀበል ብቻ አፈሙዙን በሕዝብ ለይ የሚደቅን ብቻ መሆኑ ማክተም መቻል አለበት፤ይህንንም መርህ የባለ አደራዉ  መንግሥት በትክክል በተግባር ተርጉሞ አሳይቶ፤ የሀገሪቱን መንግሥት ማዋቀር መቻል ይኖርበታል፤

10ኛ. በታሪክ ለዘመናት በኩታ ገጠምነት የጉርብትና ባሕል ተሳስረዉ የኖሩትን እና የሚያስቀና የወንድማማችነት ግንኙነት የነበራቸዉን የጎንደርንና የትግራይን ክፍላተ ሀገራት አላስፈላጊ በሆነ የክልል ግጭት ስናቆራቁስ መኖራችን ስህተት መሆኑን አምነናል። በመሆኑም በስህተት ከጎንደር ክፍለ ሀገር ተቆርሰዉ ወደ ምዕራብ ትግራይ የተካለሉት፤ የወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ መሬቶች ወደ ነበሩበት የቀድሞ እናት ክፍለ ሀገራቸዉ ጎንደር እንዲመለሱ ተወስኗል። ባጭሩ የሁለቱ ክፍላተ ሀገራት የተፈጥሮ ድንበራቸዉም የተከዜ ወንዝ መሆኑን አምነን ተቀብለናል። የአካባቢዉ ተወላጆች … እኛ ከእናንተ ጋር አብረን የታገልነዉ ደርግን ለመጣል እንጂ፤  ትግሬ ለመሆን አይደለም… ሲሉም እንቅጩን ነግረዉናል። በዚህም ብቻ ባለመወሰን ከወሎ ክፍለ ሀገር ተወስደዉ ወደ ትግራይ የተካለሉት ግዛቶችም  ወደ ነበሩበት ወደ ቀድሞዉ የወሎ ክፍለ ሀገር እንዲጠቃለሉ ያለማመንታት በሙሉ ልብ ተቀብለነዋል፤ የእኛ ዓላም አሁን ሠላም መፍጠር ብቻ ነዉ፤

11ኛ. ላለፉት የመንግሥትነት ዓመታት በመንግሥታዊ መዋቅሩም ሆነ፤ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ጠቅላላ መዋቅሮች ይዞታ የአንድ ብሔር  የበላይነት ነግሶ ስለመታየቱ በስፋት እንደሚነገር ይታወቃል፤ የትግራይ ክልል በሥርዓቱ ተጠቃሚ ስለመሆኑም ሆነ አለመሆኑ እንዲሁ በየአደባባዩ (በየቦታዉ) የሚነገር የአደባባይ ምስጢር ነዉ፤ እኛ ላለፉት ከሁለት አስርት ዓመታት በዘለቀዉ የመንግሥትነት ዘመናችን ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ፤ ብሔር ብሔረሰቦች ያለምንም አድልዎ ለሁሉም በእኩልነት  ቆመን ኖረናል ባዮች ነን፤ የሁሉንም ብሔረሰቦች መብትና ጥቅምም አስከብረናል ባዮች ነን። ይሁን እንጂ በዚህ በኩልም የተንሸዋረረ አካሄድ ከነበረ፤  የባለ አደራዉ መንግሥት የጎበጠዉን እንዲያቃናዉ እምነታችን ነዉ፤

12ኛ. ሀገራችን በነበራት የመንግሥትነት ታሪኩዋ መንግሥታዊ የአወቃቀር ሥርዓቱ አሓዳዊ መንግሥት ሆኖ እንደኖረ ሁሉም የሚያዉቀዉ ታሪካችን ነዉ፤ በዚህ የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓትም ሁሉም የሀገራችን ሕዝቦች መብትና ጥቅም ተከብሮ የኖረ ነዉ ብለን ደፍረን መናገርም አንሻም፤ ይህንንም ከመሠረቱ በመለወጥ ሕወሓት/ኢሕአዴግ አዲስ ታሪክ ሰርቷል። ቁዋንቁዋን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም በመመሥረት ሕዝብን ከሕዝብ ጋር፤ ክልልን ከክልል ጋር በማጋጨት የአንድ ሀገር ሕዝብ በማይመስል መንገድ እንደ ዉጭ ጠላት እርስ በርስ እንዲጨፋጨፉ በር በመክፈት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫዉተናል። አሁን እየተነገረን ያለዉ እዉነታ ግን የእኛ ፌዴራላዊ አወቃቀር ሥርዓት መሥራት አለመቻሉን ነዉ። በተግባርም እየታዬ ያለዉ ይኸዉ ያገጠጠ እዉነታ ነዉ።  የባለ አደራ መንግሥቱ በሚቀርጸዉ አዲሱ የሀገራችን ሕገ መንግሥት ሥርዓት ይህ ዓይነት ችግራችንም  እልባት እንደሚያገኝ የበኩላችንን ድርሻ ለማበርከት በዚሁ መግለጫችን መጠቆም መቻላችን ምን ያህል ከመሠረታችን ለመለወጥ መዘጋጀታችንን በገሀድ ያሳያል ብለን እናምናለን።

13ኛ. ሕዝባዊ አመፁን ለማረጋጋትና ሕዝባችን በሰላም ወጥቶ እየገባ፤ ሰላማዊ ሕይወቱን እንዲመራ፤ ሀገሪቱም እንድትረጋጋ በማሰብ ሁኔታዎችን ግራና ቀኝ በሚገባ አሸጋግረን ባለማየት ለተደቀነብን መሠረታዊ ችግር ስር ነቀል መልስ ያልሰጠ መግለጫ ሰሞኑን መስጠታችን ይታወቃል። የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን የሰጠዉ መግለጫ በስህተት ስለሆነ፤ እንደገና ቀና ዉይይት ካደረገ በሁዋላ፤ ከላይ በተሰጠዉ በዚህ መግለጫ መሠረት ታርሞ ይህ ተሻሽሎ የወጣዉ መግለጫ ሥራ ላይ እንዲዉል ይደረጋል፤ ስለ ማዕከላዊ እስር ቤት ብሔራዊ ሙዚዬምነት ስለ መቀየር ጉዳይም የባለ አደራ መንግሥቱ የሚወስነዉ ይሆናል።

ዉድ የድርጅታችን አባላት፤ የትግል አጋር ጉዋዶቻችንና  መላዉ የትግራይ ሕዝብ !

ሕወሓት/ኢሕአዴግ  እንደ ፖለቲካ ድርጅትም ሆነ እንደ መንግሥት ለሀገሪቱ ያመነበትን ተግባር ፈጽሟል፤ ሕዝቡ ግን በእኛ መንግሥትነት አልረካም፤ ፊቱን አዙሮብናል፤ ጀርባዉንም ሰጥቶናል፤ በቃችሁ ዉረዱ፤ የእኛ አይደላችሁም ብሎናል፤ ይህ በየቀኑ የምናየዉ ክስተት ነዉ። መስሎን በመግደል የእሱ እንድንሆን፤ እንደተለመደዉም ሰጥ ለበጥ ብሎ እንዲገዛ  የሚቻለንን ሁሉ አደረግን። ከትናንቱ የአረብ አገሮች አብዮት እንኩዋ መማር አልቻልንም። አወዳደቃቸዉ እኛ ዘንድ የሚደርስ አይመስለንም። ብዙ አታለልን። ሸወድንም። የፖለቲካ አክሮባትም ሰራን። ግን ሁሉም የሽወዳ ዘዴያችን ከሸፈ። 11ኛዉ ሰዓት ላይ ደረስን። ደወሉ እየተደወለ ነዉ። የግድ ጆሯችንን ክፍት ማድረግ እንዳለብን አመን። ይችን አገርና ሕዝብ በድለናል። ሕዝብ ግን ይቅር ባይ ነዉ። የለበጣዉን ይቅርታ አቁመን፤ ከልብ ይቅርታ ከጠየቅነዉ ግን ይቅር ይለናል። ለሀገራችንና ለእራሳችን ስንል የግድ ይቅርታ መጠየቅና ብሄራዊ እርቅ ማዉረድ አለብን። ጋዜጣዊ መግለጫ ስንሰጥ ከሰማይ በታች ባለ ጉዳይ ሁሉ ለመነጋገር ዝግጁ ነን እያልን አናታለዉ። በ 1997 ቅንጅት የጠራውን የቤት ዉስጥ አድማ ለማክሸፍ ስንል በባለ ራዕዩ መሪያችን ይኸዉ ተመሳሳይ ዓረፍተ ነገር ተነግሮ ነበር። አሁንም የባለ ራዕዩ መሪያችን ጉዳይ አስፈፃሚ አድርገን ባስቀምጥናቸዉ ሰዉዬ ያንኑ አባባል ደገምነዉ። አባባላችንን ተግባራዊ ለማድረግ ግን እንቸገራለን። የምንናገረዉና የምንሰራዉ ሁለዬም አራምባና ቆቦ ነዉ። አሁን ምጥ ላይ ነን። ምጡን አዲስ ነገር በመዉለድ እንገላገለዉ። እናም እንዲህ ዓይነቱን የኃሳዌ መሲህ ትንግርታዊ ቁማር ጨዋታ አቁመን ለሀገርና ለሕዝብ ቃል እንግባ። ያንድ ሀገር ልጆች ነን፤ ይቅር እንባባል። በሃይማኖት አስተምህሮ፤ ንስሐ፤ ፀፀት በደለኛዉን እንዳልበደለ፤ ታደርገዋለች፤ ከበደሉም ታነጻዋለች ይላል። እናም በብሔራዊ ዕርቅ ሀገራችንንም  ሆነ እኛን እራሳችንንም ከሚደርስብን አደጋ እናድን። ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን ማዕከላዊ የማሰቃያ እስር ቤትም እንዳሰብነዉ ወደ ብሔራዊ ሙዚዬምነትም አይቀየርም። እኛዉ ስለምንገባበትም ባለበት ይቆያል። የሚቀየሩት ሠራተኞቹ ናቸዉ። 27 ዓመት የገረፉበት ክንዳቸዉ ዝሏል። አንድም ይቀየራሉ፤ አለያም እዚያዉ ይጠብቁንና ቦታዉን ያለማምዱናል። ከዓፄዉም ሆነ ከደርግ አወዳደቅ መማር ካልቻልን፤ የእኛም አወዳደቅ ቢብስ እንጂ የተሻለ እንደማይሆን ባፈጠጠ እዉነታ ላይ ነቢይነት አያሻም።

እንዲያዉም  የእኛን የከፋ የሚያደርገዉ ያን በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ፤ በኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ አንፀባራቂ ምዕራፍ ይዞ የኖረዉን የትግራይን ሕዝብ ጭምር ይዘነዉ የምንሞት መሆናችን  ነዉ። እኛን አምኖ፤ ከሌላዉ ኢትዮጵያዊ ወገኑ ነጥለነዉ መኖራችን ነዉ። ሆድና ጀርባ ሆኖ እንዲኖር ማድረጋችን  እራሱ የወንጀል ወንጀል ነዉ። ይህ ዓይነቱ አሳዛኝ የፖለቲካ ድራማ በሀገራችን ከመፈጸሙ በፊት ለሚታየዉ የሀገራችን ችግር ፈዉስ ነዉ ብለን ስለምናምን ሕወሓት/ኢሕአዴግ በዛሬዉ ዕለት ይህን መግለጫ አዉጥቷል። በመሆኑም በቅርብ ጊዜያት ዉስጥ ሥልጣናችንን ለባለ አደራ መንግሥት በማስረከብ የሀገሪቱ መፃኢ ዕድል ብሩህ ተስፋ እንዲኖረዉ …የሕዝብ ብሶት የወለደነን ብለን የፎከርነዉ ቃል ባዶ ሆኖ ተገኝቶ፤ እኛ እራሳችን ለሕዝብ ብሶት ሆነን መገኘታችን በሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት ስለተረጋገጠ፤ አጉል መንፈራገጥ ላለመላላጥ እንዳይሆንብን አሁን የደረስንበትን እርምጃ እንድንወስድ ተገደናል። በዚህ ቅቡልነት ሊኖረዉ ይችላል ብለን ያመንበትንም መግለጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ (ይቅርታ በእኛ ቁዋንቁዋ ሕዝቦች) እንደሚቀበለዉና ሙሉ ድጋፉንም እንደሚሰጠን እንተማመናለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

አዲስ አበባ

 

Share Button