ህወሃት ከክልል የፖለቲካ ድርጅትነት ወደ የአውራጃ ድርጅትነት የተሸጋገረበት ጉባኤ

ህወሃት ከተመሰረተ ከጥቂት አመታት በኋላ የመጀመሪያው መሰንጠቅ (‘ህንፍሽፍሽ’) የመጣውና ከመስራች አባሎች ውስጥ እነ ኃይሉ መንገሻን ያበረረው፣ አመራሩ የሚሽከረከረው በአድዋ፣ አክሱም፣ ሽሬ ሰዎች ብቻ እየሆነ መምጣቱንና፣ ከተቀሩት አውራጃዎች የመጡትን ያገላሉ የሚል ክስ በመመስረታቸው ነበር።

ያንድ አካባቢ ሰዎች ማለትም የአድዋ ሰዎች ድርጅቱን የመቆጣጠር ወሬ፣ ውስጥ ውስጡን ለረጅም ጊዜ ሲናፈስ የከረመ ቢሆንም፣ ዘንድሮ ከተካሄደው የመሃከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በኋላ የተዋቀረው አዲሱ የስራ አስፈጻሚ አካል ባብዛኛው በአድዋ ሰዎች የተሞላ በመሆኑ፣ከዚህ ቀደም የነበረውን ጥርጣሬ ዕውን በማድረግ ህወሃትን ወደ አውራጃ ድርጅትነት ቀይሮታል።

በዚህ አንጻር ራሳቸውን የባዝ ሻሊስት ፓርቲ ነን አያሉ ሲፎክሩ የነበሩት የ ሳዳምና የ አሳድ ፓርቲዎች መሬት ላይ ያሉ ሁኔታዎች መጠጠር ሲጀምሩ፣ የፓርቲዎቻቸውን መዋቅር በታማኝ የ ጎሳ አባሎቻቸው የበላይነት ስር ማድረግ አንደጀመሩ ሁሉ ፣ ምናልባትም የነ ስብሐት ቡድን መሬት ላይ ያለው ህዝባዊ ዓመጽ ስጋት ላይ ስለጣላቸው፣ ይሄን በመከተል ሊሆን ይችላል የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባሎችን በአድዋዎች ያሸጋሸጉት ብሎ ማሰብ ይቻላል ።

እየተቆራረጠ ወራት የፈጀው (መስከረም 21 ተጀምሮ ህዳር 21 መጠናቀቁ) በመሃከላዊው ኮሚቴ መግለጫ ለምን 35 ቀን የፈጀ በሚል እንደተገለጸ እንቆቅልሽ ነው!) የህወሃት ‘ማእከላዊ ኮሚቴ’ ስብሰባ የ ‘ታላቁን መሪ ‘ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ከህወሃት የስራ አስፈጻሚ አባልነት አባሮ፣ የማእከላዊ ኮሚቴ አባልነቷን ለ’ጊዜው’ በማገድ፣ አባይ ወልዱን ከህወሃት ሊቀመንበርነትና ፣ ከህወሃት የስራ አስፈጻሚ አባልነት በማውረድና፣ ተራ የመሃከላዊ ኮሚቴ አባል በማድረግ፣ በየነ ምክሩን ከህወሃት የስራ አስፈጻሚ አባልነት በማውረድና ተራ የመሃከላዊ ኮሚቴ አባል በማድረግ፣ ብርሃነ ኪዳነማርያምን (ማረት) የመሃከላዊ ኮሚቴ አባልነቱን በማገድ ፣ አዲስ አለም ባሌማና ዓለም ገብረዋህድን ደግሞ ስህተታቸውን ነቅሶ አውጥቶና ገስጾ ተጠናቋል ተብሏል ።

በዚህ አላበቃም ፣ በመቀጠል ደብረጽዮንና ፈትለወርቅ የህወሃት ሊቀመንበርና ምክትል ተደርገው መሾማቸውና ፣ ከስራ አስፈጻሚው አካል በተባረሩትና በቴዎድሮስ አድሃኖም አለመኖር የነበረውን ክፍት ቦታ ደግሞ ፣ አብርሃም ተከስተ፣አስመላሽ ወ/ስላሴ ፣ጌታቸው ረዳንና ኪይሪያ ኢብራሂምን፣ አዲሶቹ የህወሃት የስራ አስፈጻሚ አባል ተደርገው የመመረጣቸውን ዜና ካድሬዎቹ ሞቅ ሞቅ በማድረግ እያናፈሱት ይገኛሉ። ይባስ ብሎ አንዱ ቀንደኛ ካድሬ ‘ይሄ ሂደቱ የመጀመሪያ ምእራፍ ቢሆንም የኢትዮጵያን ህዝቦች አንኳን ደስ አላችሁ ብል መቸኮል አይሆንም ‘ በማለት የአመቱን ምርጥ ስላቅ አበርክቷል ።

እነዚህ ቀንደኛ ካድሬዎች እንደሚሉት ህወሃት ከፊቷ ተጋርጦባት ያለውን አደጋ ‘እንደነስር በየጊዜው ጉልበቷን የማደስ’ ረጅም ታሪክ ስላላት ልዩነቶቿን ፈታ ተጠናክራ ተመልሳለች እያሉ ቢፎክሩም ፣ ልክ ‘ነስር በሰላሳ አመቷ ጥፍሯን ነቅላ በአዲስ ተክታ ፣ ሹል አፏን በድንጋይ ሞርዳ(አንዱ ነፈዝ ካድሬማ ማንቁርቷን በአዲስ ቀይራ ብሏል!) ለዳግም ሰላሳ ዓመት ትኖራለች እንደሚሉት ልብወለድነቱ የተረጋገጠ አፈታሪክ ፣የህወሃትም ታድሶ መምጣት ከልብወለድነት አያልፍም።

የህወሓት መሀከላዊ ኮሚቴ አባላት ቁጥር 45 ሲሆን፣ እስካሁን ማንም ያልካደውና ሆኖም ግን የድርጅቱ ህገ ደንብ ተጥሶ፣ የመሀከላዊ ኮሚቴ አባላት ያልሆኑ 18 (ማለትም የአጠቃላይ ኮሚቴውን 40% የሚሆኑ) የቀድሞ ታጋዮች የስብሰባው አካል በመሆን ‘ ስር ነቀል ግምገማውን ‘ አብረው ማካሄድ ብቻ ሳይሆን በስተመጨረሻ የተወሰኑት ውሳኔዎችም ላይ አሻራቸው በግልጽ መታየቱ ስለድርጅቱም ሆነ ስለ ስብሰባው ብዙ የሚነግረን ነገር አለ።

አንዳንድ ጊዜ እንደፈለጉት በመናገር ልቅ መሆናቸውን የሚያሳዩት አቦይ ስብሃት፣ከእድሜያቸው መግፋት፣ ወይንም ከድርጅቱ በመለስና በደጋፊዎቹ የደረሰባቸው መገፋት ያሳደረባቸው ተጽአኖ አዳክሟቸዋል ተብሎ ቢገመትም፣ መለስ ከሞተ በኋላ በነበሩት አምስት አመታት የተካኑበትን የፊውዳል መሰሪነት በመጠቀም ህወሃት አመራር ውስጥ ያሏቸውን የስጋም ሆነ፣ በአምቻ ጋብቻ የተዛመዷቸውንና ሌሎችን በመጠቀም ኃይላቸውን ሲያሰባስቡ ከርመው ፣ መቀሌ ተሰብስቦ ለነበረው ጭፍራ፣ የጭፍራ አለቃ አንደነበሩና፣ የበስተመጨረሻውም ውሳኔ የሳቸው ሙሉ ይሁንታ አንደነበረው ግልጽ ነው።( አህት፣የአህት ባል፣ የወንድም ልጅና ሌሎችም ዘመድ አዝማዶች የዚህ ስብሰባ ተካፋዮች ነበሩ ) ከዚህም አልፎ አንዳንድ የትግራይ ድረገጽ ተሳታፊዎች የአዲሱን የህወሃት ስራ አስኪያጅ ቡድን ስብጥር ተመልከተውና፣ አብዛኞቹ ከአንድ አካባቢ ብቻ የመሆናቸው ሚስጥር የአቦይ ስብሐት ቡራኬ መሆኑን እየጠቆሙ ነው።

አነዚህ ኩነቶች ተዳምረው ነው አንግዲህ በዚህ አይነት ድባብ ውስጥ የተካሄደ ስብሰባና ውጤቱ ህወሃትን የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስችሎታል የሚለው የካድሬዎች ድምዳሜ ተአማኒነት የለውም የሚያስብለው ።ምናልባትም ከዚህ ስብሰባ በኋላ፣ ልክ የነስዬ ቡድን ከድርጅቱ ሲባረር እንደተደረገው ፣ በተዋረድ ቀበሌ ድረስ የሚካሄደው የተሸናፊው ወገንን ምንጠራ ፣ ድርጅቱን የበለጠ እንድሚያዳክመው መገመት ይቻላል።

መቀሌ ላይ ከትሞ በነበረው የጭፍራ ስብሰባ በተካሄደ አውጫጭኝ ዋና ሰለባ የሆኑት አባይ ወልዱና አዜብ መስፍን ሲሆኑ፣ አዜብን ለመወንጀል ተመልምሎ የነበረው በየነ ምክሩም ተልዕኮውን ከጨረሰ በኋላ፣ እሱም ከስራ አስፈጻሚ አባልነት ተባሯል። አዜብ ላይ ለረጅም ጊዜ አቂመው ወቅት ሲጠብቁ የነበሩት አቦይ ስብሀት በበቂ ተበቅለዋል ፣ ምናልባትም ከተመቸ ጊዜያዊ እግዷ ወደ ሙሉ ማስወገድ የሚሸጋገርበትና ከ(ትካል እግሪ ምትካል ትግራይ ወይም በእንግሊዝኛ ስሙ EFFORT) ሃላፊነቷ የሚያስነሱባት ሰዓት ሩቅ አይደለም።

ዛሬ ዛሬ ካድሬዎቹ ስለ አባይ ወልዱ ብዙ ብዙ ቢሉም በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ 2000 አም ጀምሮ የህወሀትና የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ አካል አባል የነበረ፣ከ1998 አስከ ከ2010 የክልሉ ም/ፕሬዘዳንት ከዛ ወቅት ጀምሮ ደግሞ ፣ በ 2015 የህወሃት ሊቀመንበር ሆኖ አስኪመረጥ ድረስ ደግሞ ፕሬዘዳንት ተብሎ ክልሉን ያገለገለ ሰው ነው። ይሄንን ስል ስለብቃቱም ሆነ ስለ ችሎታው ይሄ ነው ብዬ መናገር ባልችልም ፣ ድርጅቱ ግን ይመጥነኛል ብሎ አመራር አድርጎት ለረጅም ጊዜ እንደተጓዘ ለመጠቆም ያህል ነው። እንደውም ባለፈው ሰሞን በሱ መሪነት ክልሉ ባደረገው አኩሪ ተግባር ከአንድም ሁለት አለማቀፋዊ ሽልማት በማስገኘቱ ሃገራዊ ኩራትና ክብር አጎናጽፎናል ተብሎ ሲፎከርም ነበር!

መሃከላዊ ኮሚቴው ባወጣው የአቋም መግለጫ የሚቀጥለው ይነበባል’አመራሩ የሃሳብና የተግባር አንድነት የጎደለው፣ ፀረ ዴሞክራቲክ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ በስፋት የተነከረ፣ በተልዕኮ ዙርያ በመተጋገልና በመርህ ላይ የተመሰረተ አመራር የማይሰጥ፣ ህዝብንና አላማን ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ክብርንና ጥቅም የሚያስቀድም መሆኑ ታይቷል፡፡’

በጣም የሚገርመው ይሄን ከላይ የተሰጠውን መግለጫ ያወጣ መሃከላዊ ኮሚቴ ግን በዚህ ‘ስር ነቀል ግምገማ’ ተብሎ በተካሄደው ቴአትር፣ ያለ ወቀሳ ያለፋቸው ደብረጽዮንና ጌታቸው አሰፋ መሆናቸው ነበር። ሁለቱም በፌደራል መንግስት ውስጥ ካላቸው ስልጣን በላይ ፣ የህወሃት የስራ አስፈጻሚው አባላት የነበሩ፣ ደብረጽዮንን በሚመለከት የድርጅቱ ም/ሊቀመንበር የነበረ ፣ ጌታቸው ደግሞ ከስራ አስፈጻሚ አባልነቱ በተጨማሪ የሀገሪቱ የደህንነት ሃላፊነቱን ስልጣን በመጠቀም ህወሃት ውስጥ ተቀናቃኝ ሊሆኑ ይችላሉ የሚላቸውን እነ ኢሳያስናና ገብረዋህድን ወደ ወህኒ ሲወረውር የነበረ ነው።

ከዚህም አልፎ ባለፈው ሶስት ዓመት መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይግባ በሚል ተቀጣጥሎ ከነበረው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴ አንስቶ፣ በኦሮሚያ የተካሄደውንና በመካሄድ ላይ ያለውን ትግል፣ በአማራ ክልልና በኮንሶ ይካሄድ የነበረውን ዴሞክራሲያዊ ትግል ለማፈንና ለመደፍጠጥ፣ ለሺዎች መሞትና መታሰር መሃንዲስና አቀነባባሪ የነበሩ ሰዎች ‘ፀረ ዴሞክራቲክ ተግባር ውስጥ በስፋት የተነከረ አመራር’ ነበር ከተባለ በኋላ በምን ተአምር ያለወቀሳ ሊታለፉ ቻሉ ያስብላል ። ወይንስ የፌደራል ስልጣናቸውን ተጠቅመው የሚፈጽሙት ወንጀልና የሚያካሂዱት ፀረ ዴሞክራቲክ ተግባር ሊያስወቅሳቸው አይገባም የሚል ድርጅታዊ ውስጠ ደንብ አለ?

ከካድሬዎቹ ልፈፋ ባሻገር፣መሬት ላይ ያለው ሀቅ የሚያሳየው ቢኖር ድርጅቱ ወደ መንደርተኛ ድርጅትነት እይተለወጠ፣ ትግራይ ውስጥም ቢሆን አግላይነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ መምጣቱን ነው። በረኸኛውና ስልጣኑን ሙጭጭ ያለው የህወሃት ቡድን የወጣቱን ትውልድ የልብ ትርታ በቅጡ ለማዳመጥ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ ባመነው መሰረት የገዥ መደብ ባህርይ በመላበሱ፣ በክልሉ ያለው ሕዝብም ቅሬታ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን ነው።

ይሄ በክልሉ የሚታየው ሁኔታ በብዙ መቶ እጥፍ በጠቅላላው በሀገሪቱ ለማለት በሚቻል መልኩ፣ የግፍ አገዛዝ በቃን በሚለው፣ ከሶስት ዓመት በላይ በመካሄድ ላይ ያለ ሰፊ ሕዝባዊ ትግል፣ ይሄም የህዝብ ትግልና እንቢተኝነት በሌሎች የኢህአዴግ ድርጅቶች ላይ ጫና በመፍጠር በውስጣቸው መነቃቃት ፈጥሮ የህውሃትን የበላይነት መገዳደር መጀመሩ፣ የህወሃትን አመራር የህልውና አደጋ ፊቱ ላይ አንደተጋረጠ አድርጎ አንዲመለከት ያደረገው ቢሆንም፣ችግሩን ለመቋቋም የሚመጥን ተክለ ሰውነት ያለው አይመስልም።

ለማናቸውም የህወሃትን መሃከላዊ ኮሚቴ ስብሰባና ውስኔዎች አስመልክቶ ሊባል የሚችለው ፈረንሳዮቹ አንደሚሉት ‘plus ça change, plus c’est la même chose”በግርድፉ ‘ነገሮች የበለጠ የተለወጡ በመሰሉ ቁጥር ያው መሆናቸው ወይንም አለመለወጣቸው ግልጽ ይሆናል’ አንደማለት ብለን መደምደም አንችላለን።

አበጋዝ ወንድሙ

Share Button