<<ተመስገን!!..ቫት በልተን ቫት ጠጥተን እንኖራለን>>

(በግሩም ተ/ሀይማኖት)

  መቼም ሀገር ደርሶ የመጣን ስደተኛ በጥያቄ ማጠደፉ ያለ ነው፡፡ አሀ! ቀዬ መንደሩ አገር ሰፈሩ ሰላም ነው ወይ ማለት ነውር አይደለም እኮ!..እኔማ ጥሎብኝ ሀገር ላይ የተነፈሱትን ትንፋሽ ይተነፍሱልኝ ይመስል፣የኢትዮጵያን ጠረን ይዘውልኝ የመጡ ይመስል.. እስራቸው ገብቼ በወሬ መተግተግ ነው፡፡ አሁንማ ምን ያደርጋል ኢቲቪ ሁሉን ልቅም አድርጎ እውነት እውነቱን እያወራልን ሰዎቹን የሚያወሩት አሳጣቸው፡፡ ለጋዜጠኛ እውነት መናገር አሸባሪ በሚያስብልበት ሀገር ላይ ያለው ኢቲቪ ሰዓት እንኳን ለህዝቡ አዛብቶ ነው የሚያቀብለው እያሉ ያሙታል፡፡ ያሙታል አልኩ እንጂ እኔ አላማሁትም ልብ በሉ፡፡ ደግሞ የመን ያለው ኤምባሲ ኢትዮጵያና የመን ባላቸው የወንጀለኛ መለዋወጥ ስምምነት መሰረት ይሰጠኝ ብሎ ነገር እንዳይፈልገኝ፡፡ ለዛውም እነሱንስ ለምን ስራ ላስፈታ?በዲፕሎማት ፓስፖርት መጠጥ፣ ሽሮ እና በርበሬ አዙረው ከመሸጥ አልፈው አያውቁም እየተባሉ እንደሚታሙ እግረ መንገዴን ብነግራቸው ራሱ እኔኑ ነገር ሳይፈልጉኝ ይቀራሉ ብላችሁ ነው? ሰዓት እንኳን አያስተካክልም ወደሚሉት ኢቲቪ ልመለስ፡፡ አንድ ለእናቱ ከሆነው ኢቲቪ በኤክስቴንሽን ማዳቀል ዘዴ ይሁን እንደኮሶ ትል ራሱን ለሁለት እየከፈለ መልሶ እየተካ አራብተውት ኢቲቪ 4 ላይ ደርሰናል፡፡

 ተመስጌን ነው፡፡

 ያን እንጨት እንጨት ያለ ፐሮግራም ከማየት ሌላም አማራጭ መገኘቱ፡፡ መቼም ብሮድ ካስቱ ፀድቆ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ይኖረናል ማለት ዘበት ነው፡፡ አሁንማ የብሮድ ካስቱ ነገር እንደሆን ውሾን ያነሳ ውሾ..ሆነ፡፡ ኤጭ ሞኝ ነን እንዴ ነፃ-ፕሬሱ እንቅልፍ ነስቷቸው የሽብርተኛነት ታፔላ ለጥፈው..ለጥፈው ማስረጃ ማቅረብ እስኪያጥራቸው..ለጋዜጣው እንዲህ የበረገጉ ብሮድ ካስቱን አፅድቀው ይበዱ እንዴ? እንዲያውም አንድ ሰሞን ሌሊት ተኝተውም የሚያልሙት  ‹‹ወይ..ፕሬስ!..እኔን ብሎ ነፃነት ፈቃጅ..በምን ላጥፋቸው በምን ልዝጋቸው?›› ነበር የሚቃዡት ተብለው ይታማሉ-ሰውየው፡፡ የታሙትን ያህል ይታሙ እንጂ መቼ ዘዴ ጠፋለት ‹‹አሸባሪ..››

የበየህ ሰሞኑ በቀደምለት ከሀገር ቤት የመጣ ሰው መኖሩ ተነገረኝ እና ትንሽም ቢሆን ስለ ሀገራችን ያወጋኛል ብዬ አነፍንፌ እብስ…ስደርስ በቃኝ ሀገሬ አድጋ መንጥቃ ጎዳናው ላይ የሚበሉበት መስሎ ፅዳቱ፣ ጓዳ ጎድጓዳው መንገድ በቻይና ተሰርቶ እኔ ሰው ሀገር ‹‹ያ-ሀበሺ..ያ ኦርያ›› እየተባልኩ ምን አንከራተተኝ ብሎ የገባ ወዳጄ ነው፡፡ ጠላታችሁ ይደንግጥ አልደነገጥኩም፡፡ ትንቢት ይቀድም ለነገር እንደሚለው ቅዱሱ መፀሐፍ እኔም በሆዴ ለራሴ የገመትኩት ነበረኝ፡፡ ትንፍሽ ብልማ ትንሹ አባባ ታምራት ብለው ደግሞ አርቲስቶቻችን እና አትሌቶቻችን የመን ደጅ ይጥኑ?

“ምነው ተመለስክ?”

 ‹‹እስኪ ተወኝ ማየት እና መስማት አንድ አይሆን? እዚህ ኤምባሲ የሚያቸፈችፉት ከኢቲቪ ብሰው ስብከታቸው አታለለን፡፡ እቃችን ሸጠን ሀገር ገባን፡፡ ሀብታም የሚኖርባት ሀገር ሆናልሀለች፡፡ ደሀ ማየት እና ማሽተት ብቻ ነው ትርፉ፡፡ የሰራበትን ሳይበላው ለቫት በ50 አቅጣጫ ያወጣዋል፡፡ ቫት እና ባት፣ ቫት እና ላት…የሚገርምህ ቫት የሚባለው ለሴቶች ቅባት ሆኖላቸዋል መሰለኝ እንዴት ያምራሉ፡፡ የውበት ዘመን ነው ይባላል እንጂ ዘመኑ ሳይሆን የውበት የሚወለደው ራሱ ውበቱ ነው፡፡ ፐ!..ፐ!..ፐ!..ወዘናቸው..እዚህ አረብ ሀገር በአባያ ተጀቡነው…ተጀቡነው ሳይ ከርሜ እዛ ስደርስ ቫት ብቻ ሳይሆን ቫት እና ባት..ቫት እና ላት ነው ያስቸገረኝ፡፡ ቫቱ በየአቅጣጫው ኪሴን ሲጎረጉረው ባቱ እና ላቱ አይኔን አጥበረበረው፡፡..›› ለካ ይሄ ሁሉ አረብ ሀገራችን የገባው ወዶ አይደለም፡፡…ያየውን አይቶ ነው፡፡››

  ‹‹ለበላኸው፣ ለጠጣኸው፣ ላየኸው..ቫት ነው፡፡ ምን አለፋህ የረባ ድምፅ ያለው ፈስ ከፈሳህ ያው መፀዳጃ ፍለጋ ላይነህ የምትፀዳዳበትን ቫት ክፈል ልትባል ትችላለህ… መንገድ ላይ ቆሎ ስትገዛ ቫት ልትጠየቅ ትችላለህ…››ያው ቃለ አጋኖ እንዳለበት ሆኖ ማለት ነው፡፡‹‹..ሊስትሮው ስታስጠርግ ቫት አለ?..››ቂ..ቂ..ቂ.. ሳቄ አመለጠኝ፡፡

   ይሄን የነገረኝን የቫት ነገርን እያሰላሰልኩ የትላንትናው ትላንትና ወዲያ አንድ ወዳጄን ሰላም ልለው ወደ ኢትዮጵያ ደወልኩላችሁ፡፡ የመን ውስጥ ተከስታ የነበረችውን ጦርነት ሽሽትም ጭምር በቅርብ ወደ ሀገር የገባ ስደት ላይ እድሜውን የቀረጠፈ ነው፡፡ እሱ ብቻ አይደለም ብዙዎች አሁን ነገር ተለውጧል ሀገር ይሻላል፡፡ ቴሌቪዥኑ፣ ራዲዮው..ሰዉ እንደሚያወራው እየመሰላቸው ጓዝ ጉዝጓዛቸውን ጠቅልለው ያፈሯትን ሚጢጢ ዶላርና ትልቅ ቦርጭ ይዘው የመንን ደህና ሁኚ ብለው ወደ ሀገር የገቡ አሉ፡፡ ለእነሱ ‹‹እልልልልል….ታድላችሁ፤ ለእኛም ፈጣሪ መግቢያውን ያበጅልን…›› ብለን ሸኘን፡፡ አንዳንዶቹማ ዳግም የመንን አያሳየን በፊልምም ቢሆን ብለው በቀይ አስመትተው እብስ፡፡ እንዴት ደስ ይላል፡፡ ሀገር ተሻሻለች ተብሎ ከስደት መመለስን የመሰለ ምን ደስ የሚል ነገር አለ?

    ግን ችግሩ ያለው እዛ የጠበቁት አለመሆኑ ነው፡፡ አባል ያልሆነ በእንሱ ማህበር ያልተደራጀ ባለቤት እንደሌለው ውሻ ሲንከወከው ይኖራታል፡፡ ታዲያ ያ-የደወልኩለት ወዳጄ ቀዝዝ ባለ ድምፅ <<እባክህ ትንሽ ሳንቲም ፈልጌ በባህር ልመለስ ነው..›› አለኝ፡፡ ምክንያቱን ሲደረድር ‹‹ሁሉ ውሸት ነው፡፡ እንደሚወራው አይደለም። ስራው ቢኖር ለእያንዳንዱ ነገር ክፍያ ነው:: የምትሰራው እና የምታወጣው አይመጣጠንም…ህዝቡ ተፈራርቶ ነው የሚኖረው ሰላዩ እና ተሰላዩ አይታወቅም፡፡>> እያለ ሁሉን ሲያወራኝ የስልክ ሂሳቤ አናቴን ሊያዞረው ሆነ፡፡ ቢሆንም ግን ላረጋግጥ ብዬ ቫት እንዴት ይዟችኋል? አልኩት ደህና ነገር እሰማ ይመሰል፡፡

   ‹‹ተወኝ ወዳጄ እሱን ተወው፡፡ ብቻ ተመስጌን ማለት ነው፡፡ ቫት በልተን፣ ቫት ጠጥተን እንኖራለን፡፡ ግንባታውን መንገዱን ካየህ ተለውጧል፡፡ ቢያምር ቀለብ አይሆነኝ፡፡ ሀገሩ አምሯል ኑሮው ደግሞ ተገልብጧል..አለኝ፡፡

    አላወቀውም እንጂ ኑሮው ብቻ ሳይሆን ነገሩ ሁሉ ተገለባብጧል፡፡ ባለሀገር ነኝ ያለው ከውጭ ብር ይዞ በገባ ኢንቨስተር ተብዬ የውጭ ዜጋ እየተገፋ መሬቱን እየተነጠቀ ስደት መውጣቱን መች አወቀ፡፡ ለነገሩ እኔም ያወኩት ከራያ አካባቢ ወደ የመን በባህር መጥታ አሁን ወደ ሳዑዲ የሄደች ልጅ ባነጋገርኩበት ጊዜ ነው፡፡ የከብት ማዋያችን ሳይቀር ለፈረንጅ ሰጡት ከብቶቹን የት እናርጋቸው? ለዛውም ለእርሻም የተሰጠን መሬት ቢሆን የበሬ ግንባር ታክላለች፡፡ባለቤቴም ከተማ ለስራ ገባ እኔም ይሄው አለችኝ፡፡ ጎበዝ ብር ላለው የውጭ ዜጋ ዜግነታችንን፣ መሬታችንን የሚሸጥ ወያኔ ተንሰራፍቶ ያሻውን ሲያደርግ፣ የምትሸጥ የምትለወጥ ኢትዬጵያን፣ለነገው ትውልድ የማናስረክባት ሀገራችንን በዝምታ የምናያት..እስከመቼ ነው?   

          እስከመቼ እንጓዝ?

      በሀይል ተገዝተን እስከመቼ

      ሰላም ናፈቀን ወገኖቼ

      አረ! ዝምታው ምንድን ነው

      መብት ተገፈን የተኛነው?

              ወጥቶ መግባት ህልም ሆኖ

              መብት ጠፍቶ ተጨቁኖ

     ጎዳናዎች  በንጹሀን ደም ራሱ

     ዝምታው ይብቃ እንነሳ ተንሱ

             የወላድ እንባ ዋንጫ ሞልቶ

             ምሁራንን ከእስር ከቶ

             ነገር ዞሮ ፍርድ ተዛብቶ

      መብት ጠያቂ ሆኖ ወንጀለኛ

  አፋኝ ገዳይ ሲሆን ዳኛ

             ከዝንብ ማር አንጠብቅም

             በአድነት እንነሳ አማራጭ የለም

     ይሄ ነገር እስከመቼ  ይቀጥል? ሸንሽነው እንደፈለጋቸው የሚሸጧት ኢትዮጵያን… ዜግነታችን ረክሶ ብር ላለው ከመኖሪያችን የምንፈናቀልባት ኢትዮጵያን በዝምታ ማየቱ ነው የሚያዋጣው?

      ኢትዮጵዊ ነን እያልን ኢትዮጵያዊነትን ተነጥቀን እንዳናንቀላፋ፣ ሰላም አጥተን እንዳንነሳ ፍርሃት ሰንጎን እያንጎላጀጅን ዘመን ነጎደ፡፡ በሊዝ የምትቸረቸር፣ ብር ያለው መጫወቻ ያደረጋት ሀገር ይዘን የዝምታው ነገር ፍርሃት ይጭርብኛል፡፡ ጎበዝ ሀያ ዓመትን በዝምታ እንዳየናት ሰላሳኛዋንም ሳንደግማት እንቀራለን ብላቸሁ ነው? ደርግ የወደቀበት ሀያኛውን አመት የአሁኖቹ ሻጮች ትከሻችን ላይ ከተፈኛጠጡም እንዲሆ..ግንቦት መጥቶ ባለፈ ቁጥር እድሜያቸውን እያሰላን..የእኛ ያልሆነች ኢትዮጵያን ሲፈነጩባት፣ ገንዘብ ያለው ሲኮናተራት፣ ሲገዛት በሀገራችን ላይ ተመልካች ሆነን እሰከመቼ?….ተስፋ የሚጣልበት ተቃዋሚ የለም…የሀንበርገር ታጋዮች፣ በመዋጮ ገንዘብ የደለበ ኪሳቸውን ላለማክሳት ጠንከር ያለ ትግል አይታገሉ ወይ ትተው አይተዉ.. የሚሰማው ስሞታ የነገር ቡለታ እራሱን የቻለ እንኳ ሰላምታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ዛሬ ግን ወደድንም ጠላንም ጠንካራ ተቃዋሚ እኛው ልንመሰርት ግድ እያለን ነው፡፡ግን መተማመኑ ፈፅሞ የሚሰርግ አይመስልም፡፡ ትግል ካልሆነ የማይነቀል መርዛማ ዘንዶ ከላያችን አድፍጧል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ብሩክታይትን ከዘንዶው እንዳዳናት እኛም ኢትዮጵያን ከተጠመጠመባት ዘንዶ እናላቃት፡፡   

   ተመስጌን ቫት በልተን ቫት ጠጥተን እንኖራለን እንዳለው ሁሉም ተመስጌን ብሎ ይቀመጥ? ተሸጠን ተሸጠን ያለቅን እለት እዬዬ ማለት ያዋጣ ይሆን?

__._,_.___

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 22, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.