4 ለ 3 በጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ ላይ በኢቴቪ የተደረገ ክርክር

አንድነት ፓርቲ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁን በህዝብ ድጋፍና ጥያቄ ለማሰረዝ የጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ የሚፈለገውን ግብ ለመምታቱ በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ስር የሚገኘው ኢቴቪ በአዋጁ ዙሪያ የፓርቲዎችን አቋም የሚያንጸባርቅ መድረክ ማዘጋጀቱ ማሳያ ነው፡፡ኢህአዴግ ካድሬዎቹ አዋጁን በማንበብ አንድነቶች ለሚያነሱት መከራከሪያ ምላሽ ለመስጠት እንዲችሉ ትዕዛዝ ማውረዱም ሌላኛው የአደባባይ ድል ነው፡፡ [Click here to watch the video]

በነቢብ የህዝብ በገቢር የኢህአዴግ ልሳን የሆነው ኢቴቪ በአዋጁ ላይ ያላቸውን አቋም እንዲያንጸባርቁ የጋበዛቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ በአቶ በቀለ ነጋዓ፣ አንድነት በሃብታሙ አያሌው፣ ኢዴፓ በሙሼ ሰሙ፣ ሰማያዊ በይልቃል ጌትነት፣ ኢህአዴግ በሽመልስ ከማል፣በጌታቸው ረዳና በኢቴቪው ጋዜጠኛ ተወክለዋል፡፡

ክርክሩ በተራ መቀስ የተቆራረጠ መሆኑ

ኢህአዴግ ከምርጫ 1997 በኋላ በቀጥታ የቴሌቪዥን መስኮት የሚተላለፉ ክርክሮች ፎብያ የተጠናወተው በመሆኑ live debate አይመቸውም፡፡እናም ክርክሩ በቀጥታ አለመተላለፉ ለባለ መቀሶቹ ጥቅሙ ከፍ ያለ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው፡፡በሁለት ክፍል የተላለፈው ክርክር በተራ መቀስ መቆረጡን ለመመስከር ሶስተኛ አይን የማያስፈልግበትን አንድ ሁለት ነጥብ ልጥቀስ፡፡ከመሬት ተነስተው የኢህአዴጉ ተወካይ ተቃዋሚዎችን‹‹እንዴት ድራማ ነው ትላላችሁ››በማለት ይወርፏቸው ጀመር፡፡ክርክሩን ስራዬ ብሎ የተከታተለ ሰው እኚህ ሰው ለምን ያልተጻፈ ያነባሉ ብሎ ሊፈላሰፍ ይችላል፡፡ነገሩ ግን መዛባቱን የፈጠረው የሽመልስ ንግግር ሳይሆን ኢቴቪ ነው፡፡ ማለቴ መቀሱ፡፡

ጌታቸው ከዚህ በፊት አብሮኝ በአንድ መድረክ ሰርቷል ያሉትንና አሁን የአሰላለፍ ለውጥ በማድረጉ አንድነትን የተቀላቀለውን ሃብታሙን በነገር ወጋ ሲያደርጉት ታዝቢያለሁ፣ሃብታሙ በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ የሚለው ነገር እንደሚኖር መጠርጠሬ አልቀረምና ተራው ደርሶ የሚለውን ለማድመጥ ጆሮዬን ቀሰርኩ ነገር ግን የሃብታሙ ንግግር ከመሃል እንደጀመረ በሚያሳብቅ መልኩ ለጌቾ ይሰጠዋል ብዬ የጠበቅኩት ምላሽ ሳይቀርብ ቀረ፡፡ሴኮ ቱሬ ክርክሮችን በመቆራረጥ ጥበብ የተካኑ እንደነበሩ በአንድ ወቅት የድሮው ልደቱ (አዲስ ልደቱ እንዳሉ ስለማምን የቀድሞው ለማለት ተገድጃለሁ)ተናግረው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ሴኮ አሁን ስለሌሉ የኢቴቪ አዲሱ መቀስ ብዙም በቆረጣ ባለመካኑ ቆረጣው አይን ያወጣ ሆኖበታልና አልተሳካም፡፡

ያልተጠየቀ ‹‹መመለስ›› የጆሮ ህመም ይሆን?

ተቃዋሚዎች በአንድነት በሚባል መልኩ አዋጁ ከህገ መንግስቱ እንደሚጋጭ በመግለጽ ጭብጥ ለማስያዝ ሞክረዋል፡፡ሽመልስ እሳት ለብሰውና ከአንድ የህግ ባለሞያ በማይጠበቅ መልኩ እየደጋገሙ‹‹እንትን››እያሉ በሰጡት መልስ ‹‹ተቃዋሚዎች የእኛ አዋጅ የአሜሪካንን ወይም የአውሮፓን ስለማይመስል ህግ ለመሰኘት ብቁ አይደለም ይላሉ››ብለዋል፡፡አዋጁ የሰብዓዊ መብትን ይጋፋል ሲባሉም አራምባ በመርገጥ ‹‹ ለሽብርተኞች በሩን በመዝጋቱ የእኛ ህግ ከሁሉም የተሻለ ነው››ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ያልሰማ ጆሮ የሚሰጠውን መልስ ለማወቅ የሽመልስንና የጌታቸውን ንግግሮች ማድመጥ አቻ የሚገኝለት አይመስለኝም፡፡ለነገሩ በዋናነት የኢህአዴግ ዋነኛ ችግር ምላስ እንጂ ጆሮ የሌለው መሆኑ አይደል፡፡ተቃዋሚዎቹ አዋጁን በተመለከተ ለሚያነሷቸው ውሃ የሚያነሱ መከራከሪያዎች ኢህአዴጋዊያኑ ከተነሳው ሃሳብ ጋር ተያያዥነት የሌለውን ምላሽ መስጠታቸው ሟቹን መለስን በብዙ ነገር እንዳስታውስ አድርጎኝ ነገሩ የወል ችግራቸው መሆኑን ደመደምኩ፡፡

በዚህ አይነት በፖለቲካ ውሳኔ እንዳንረሸን ሰጋሁ

ሽብርተኞችን የመፈረጅ ስልጣን ፓርላማው አልተሰጠውም የሚለው መከራከሪያ በአቶ ሽመልስ አስደንጋጭ መልስ ተሰጥቶታል፡፡ፓርላማው ህግ የማውጣት እንጂ ህግ የመተርጎም ስልጣን የፍርድ ቤቶች በመሆኑ የፍርድ ቤቶችን ስራ ለፍርድ ቤቶች መስጠት ሲገባው ያወጣውን ህግ ለመተርጎም መሄዱ ህገ መንግስታዊ ጥሰት ነው ሲባል ሽመልስ ‹‹ይህ የፖለቲካ ውሳኔ ነው››ብለው አረፉት፡፡በእኛ አገር የፖለቲካ ፣የውድብ፣የቡድን ውሳኔ ምን እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡በፓርላማው ካሉት 547 መቀመጫዎች ኢህአዴግ 545 በመውሰድ ቤቱን ተቆጣጥሯል፡፡በዚህ የአንድ ፓርቲ ጉባዔ ፖለቲካዊ ውሳኔ ተላለፈ ማለት ምን አይነት ትርጉም እንደሚኖረው ለታዛቢ እንተወው፡፡ደግሞስ የማስረጃ፣የምስክርናየህግ ድንጋጌን የሚፈልግ ትልቅ ጉዳይ እንዴት ፖለቲካዊ ውሳኔ እንዲይዝ ይደረጋል ?ከዚህ በላይ ፍትህን መስቀል ከወዴት ይገኛል?

አወያይ ጋዜጠኛ ወይስ ኳስ አቀባይ?

የኢቴቪው ጋዜጠኛ ስሙን ከኢህአዴግ ተወካዮች ተራ አለማስመዝገቡ ብስጭቴን እንዳናረው መሸሸግ አይኖርብኝም፡፡ከመነሻው ‹‹ኢትዮጵያን የሽብር ስጋት ያሰጋታል ወይስ አያሰጋትም››የሚል ጥያቄ አንስቶ በአገሪቱ የደረሱ ጥቃቶችን በፊልም ማሳየት ምን ሊባል ይችላል?ይህንን ፊልም የሚመለከቱ ሰዎች ከመነሻው የጥያቄው መነሳት አስፈላጊነት ላይታያቸው እንደሚችል መገመት ባይከብድም አወያዮ ፊልሙን ጋብዟል፡፡

ፓርላማው ድርጅቶችን መፈረጁን በተመለከተ ፓርቲዎቹ ሲወያዮ የጋዜጠኛ ማልያ ያጠለቀው አወያይ ጣልቃ ገብቶ ‹‹የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስታወስ ያህል ፓርላማው የፈረጀው አልቃይዳ፣አልሻባብ፣ኦነግ፣ኦብነግንና ግንቦት ሰባትን ነው››ብሏል፡፡እንኳን ይህችን ያለ ሰፈሯ የመጣችን ዝንብ ለምናውቅ ሰዎች የጋዜጠኛው ማስታወሻ ግልጽ ናት‹‹ተቃዋሚዎች የሚከራከሩት ለአልቃይዳ ነው››ለማለት ነው፡፡ክርክሩ ግን ፓርላማው ከስልጣኑ ውጪ እየተጓዘ በመሆኑ ነገ ሌሎች ሰላማዊ ፓርቲዎችን ሽብርተኛ በማለት ሊፈርጅ ይችላል የሚል ነበር፡፡አወያዮ ልክ የኢህአዴግ ተወካዮች አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ ሲሰማውና የማርያም መንገድ ሲያጡ ዘው ብሎ በመግባት መውጫ መንገድ ያመቻቻል፡፡ኳሷ በተቃዋሚዎች እጅ በኢህአዴግ ሜዳ እየተንከባለለች ወደ ጎል ስትደርስ ጋዜጠኛው ፊሽካ ነፍቶ ኳሷ እንድትመለስ ያደርጋል፡፡

በእስካሁኑ ክርክር ለበቀለና ለሃብታሙ ኮፊያዬን አወልቃለሁ     

ክርክሩ ነገ ምሽት እንደሚለጥቅ ኢቴቪ ቃል ገብቷል፡፡የመጨረሻው ክርክር ቀርቦ ፋይሉ ከመዘጋቱ በፊት በግሌ ባደረግኩት ዳሰሳ የመጀመሪያው ምሽት የክርክር ኮከብ አቶ በቀለ ነግዓ የሁለተኛው ምሽት ፈርጥ ደግሞ ሃብታሙ አያሌው ነበር፡፡ሙሼ ረጋ ብሎ የሚያነሳቸው ነጥቦች ቦታ ሊሰጣቸው የሚገባቸው እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡

በቀለ ዘና እና ረጋ ብለው የሚወረውሯቸው ቃላቶች ድንጋይ ሆነው  በኢህአዴግ ላይ የሚያርፉ ቢሆኑ አቶ በረከት ስምኦን በሁለት ምርጫዎች ወግ እንደጠቀሰው ናዳ ሆነው ኢህአዴግን ከመንበሩ ባፈናቀሉት ነበር፡፡ ሃብታሙ ታሊባንን እንደ አገር በመውሰድና የጸረ ሽብርተኝነትን የምንቃወመው››በማለት ከመናገሩ ውጪ ነጥብ በነጥብ ያነሳቸው ሃሳቦች የሚጣል ነገር አልነበራቸውም፡፡ እንግዲህ ደግሞ ለነገው የነገ ሰው ይበለን፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on August 28, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.

3 Responses to 4 ለ 3 በጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ ላይ በኢቴቪ የተደረገ ክርክር

 1. Latta Ayanna+Germamme

  August 31, 2013 at 10:35 AM

  Excellent beginning. I thought EPRDF was totally shying away from such forums for good. It is a wonderful start coming back to it with all unskilled scissors. Had I been lucky enough, I would have watched those confused politicians arguing for the justifications of thier tricky formulations and drammas.
  I can not deny even if not the skill and ability, but courage of the EPRDF cadres in telling and defendining lies. I wonder where they were trained in this skill. Let Him give the opposition forces the patience to sit with proliferating viruses of lies and make discussions.

 2. nanusha

  August 31, 2013 at 10:56 AM

  The scissor man show it is really fantastic people from the opposition group real got the point. The EPRDFties were annoyed and disturbed, they were not capable of persuading the school children. In my view Habtamu should get 8.5, Bekele 8, Muchai 7.5, Yileqal and Shamel(yelesh)es 6, and Getachew 5 and the “Journalist” 4.5 out of 10.

 3. nanusha

  August 31, 2013 at 10:59 AM

  The scissor man show…. it is really fantastic…. people from the opposition group really got the point. The EPRDFties were annoyed and disturbed, they were not capable of persuading school children. In my view Habtamu should get 8.5, Bekele 8, Muchai 7.5, Yileqal and Shamel(yelesh)es 6, and Getachew 5 and the “Journalist” 4.5 out of 10. What is yours?