128 ኢትዮጵያዊያን ተፈቱ… አብዛኛው በእሳት ተቃጥለዋል (ሀበሻ በየመን ክፍል 12)

[በግሩም ተ/ሀይማኖት] -(Graphic Images: Viewer Discretion Advised)

    ከአንድ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በግሩፕ በተደራጁ ሰዎች የመን ውስጥ ታፍነው እንዳሉ ተይዘው የተለቀቁ እና ጉዳት የደረሰባችውን በማግኘቴ አወኩኝ፡፡ ሌሎች ሰዎችን ‹‹ወገኖቻችን ታግተዋል..›› በማለት አስተባብሬ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ብለን ወዳሰብነው ክፍል ሰሞታ አቀረብን፡፡ ክስ ካቀረብንባቸው ቦታዎች መካከል የየመን ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶን 128 የታፈኑ ኢትዮጵያዊያንን አስፈታ፡፡ እልልልል…..የሚያስብል ነው፡፡ እኔ ብያለሁም ያውም ድምጼን ከፍ አድርጌ፣ በደስታ ሰክሬ ጮኬያለሁ፡፡ እስኪ አንድ ቀን እንኳን ወግ ይድረሰኝ እና በአስደሳች ዜና ገድ ልበል ብዬ ነው፡፡ ‹‹ወግ አይቀርም ብሎ ይሸታል እንኩሮ..›› የሚሉት አይነት መሆኑ ነው፡፡ ከላይ የመፈታታቸውን ጉዳይ ስናይ እንጂ ወረድ ሲል የተፈጸመባቸው ግፍ ማሳዝኑ አይቀርምና ወግ አይቀርም… ብሎ ያልኩት አፌን ሞልቼ አስደሳች በማለቴ ነው፡፡

     ኢትዮጵያዊያኑን ከጅቡቲ በጀልባ ከማሰፈር ጀምሮ በተቀናጀ ሁኔታ ነው አፈናውን የሚፈጸሙት፡፡ 156 በህገ-ወጥ መንገድ አስገቢዎች እና አፋኞች በጀልባ ከማሳፈር ጀምሮ፣ ስድስት የሳዑዲ አረቢያ ድንበር ጠባቂዎች፣ አራት የየመን ድንበር ጠባቂዎች፣ በአራት ሽፍታች፣ 12 በዘረፋ የተሰማሩ፣ 4 ህግ አስከባሪዎች ሆነው በቅንጅት ነበር ይህን አስከፊ ተግባር ሲያደርጉ የቆዩት፡፡ ‹‹..እኛ ሀገርማ እንዲህ አይነት ሰብዓዊነት የጎደለው የሀራም ስራ አይሰራም፡፡ የሀይማኖተኞች ሀገር ነው…›› ያሉኝ የሁማ ራይት ሰራተኛ ይህን ዝርዝር የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ሲያደርግ ምን ብለው ይሆን? ነፃ ከወጡት እነዚህ 128 ኢትዮጵያን ውስጥ ወንዶች፣ ሴቶች፣ የ11 አመት ልጅ ጨምሮ ህፃናት እና ከስልሳ አመት በላይ የሆኑ ሽማግሌዎች አሉበት፡፡ በህይወት ከተፈቱት ሌላ የሞቱም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሁለት ግለሰቦች ቤት ውስጥ ታፍነው ከወር በላይ ሲደበደቡ እና በእሳት ሲቃጠሉ ቆይተው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ነው የተገኙት፡፡ (የመን መብራት ከአመት በላይ ችግር ስለሆነ ሻማ ውድ ነው ታዲያ ሰው እንደ ሻማ ማቃጠላቸው ምን አስበው ይሆን? መቀለዴ አይደለም፡፡ ቢሆንም ደግሞ ለምዶብናል፡፡ በችግራችን መቀለድ፣ መጥፎ ነው ስንባል ወደዛ መሮጥን፣ አደጋ ስንባል ሞክረን ካላየን ያለማመን ተጠናውቶን የለ?)

      ብር አለያም እስር ተብለው ታግተው ሲደበደቡ የቆዩት ኢትዮጵዊያኖች የሁለት የመናዊ ግለሰቦች ቤት በሀይል እርምጃ ሲፈተሸ ነው የተገኙት፡፡ በዱላ ብስቁል ያሉ፣ በርሃብ የተጎዱ..ድካም እንግልት ያጠቋቆራቸው፣ አብዛኛዎቹ ከሰው እርዳታ ውጭ መራመድ ያልቻሉ ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው የአጋቾቹ አለቃ አብደላ አብዶ አል-ዋህሺ ቤት 49 ኢትዮጵያዊያን ታፍነው ተገኙ፡፡ በሁለተኛው የአፋኞች አለቃ ካሊድ ሞሀመድ አብሲ ቤት ደግሞ 79 ኢትጵያዊያን ተገኝተዋል፡፡ ሰው ላይ ሊፈጸም የማይገባው ኢ-ሰብአዊነት በተላበሰ ሁኔታ ግፍ የተፈጸመባቸው መሆኑን የየመን ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል፡፡

የታፈኑበት ቦታ ሀረጥ የተባለ በባህር የሚገቡበት እና ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚሄዱበት መካከል ወደቡ አቅራቢያ ነው፡፡ ይህ ቦታ ይበልጥ የሚታወቀው ከሞካ ወደ ሳዑዲያ መጓጓዣ ጠረፍ መሆኑ ነው፡፡ ታጋቾቹ ኢትዮጵዊያን በአጋቾቹ በደረሰባቸው ድብደባ እና በእሳት የማቃጠል ጭካኔ ከፍተኛ ጉዳት የገጠማቸው ከሀምሳ ስባት የሚበልጡ ሰዎች በአሁኑ ሰዓት በህክምና ላይ ነው የሚገኙት፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ ራሱ ላይ በደረሰበት የዱላ ድብደባ የመርሳት ችግር የተከሰተበት /የት እንዳለ፣ ማን እንደሆነ፣ ቤተሰቦቹን..አብረውት ያሉትን ጓደኞቹን ሁሉ ማስታወስ ያልቻል በፎቶው ላይ ተኘረቶ የሚያዩት/ አንድ ወንድማችን አለ፡፡ እስካሁን ራሱን ያላወቀ ከመሆኑን ውጭ ምን ያህል ጊዜ በዚህ ሁኔታ እንደሚቀጥል ለማወቅ አልተቻልም፡፡ ከመካከላቸው አይኑ የጠፋ፣ እጁ የተሰበረ፣አፍንጫው ከአገልግሎት ውጭ የሆነ….እንዳሉበት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ፎቶግራፉም ይህን ያሳያል እና…

      ፎር ዋርድ እንደሚባለው እኔም ወደኋላ ልምለስ እና ስለእነዚህ ልጆች መረጃውን ያገኘሁበትን ሁኔታ ላስታውስ ወደድኩ፡፡ ከዚህ ቀደም እንደ ጻፍኩት በአጋጣሚ ትዕዝ ወደምትባለው የየመን ሶስተኛ ከተማ ሄድኩ፡፡ አብረውኝ ካሉት ጋር መንገድ ላይ ያገኘናቸውን በባህር የገቡ በስቋላ ኢትዮጵያዊያን አናገርን፡፡ ከጅማ አካባቢ የመጡ በመሆናቸው ኦሮሚኛ ብቻ ስለሆነ የሚችሉት በአስተርጓሚ ተግባባን፡፡ የነገሩኝን ለማጣራት ሞከርኩ፡፡ በሌላ አጋጣሚ በድብደባ እጁን የተሰበረ ልጅ አገኘሁ፡፡ ማስረጃ አድርጌ ሁማን ራይት፣ ሀገር ውስጥ ሚኒስቴር፣ ፍትህ ሚኒስቴር፣ ሁድ የሚባለው በተቃዋሚዎች የሚመራው የኖቬል ተሸላሚዋ ከረማን ያለችበት የሰብዓዊ መብት ድርጅት አመለከትን፡፡ እዚህ ጋር የማላልፈው አብረውኝ የተሯሯጡ ሌሎች ልጆችም አሉ፡፡ በስሱ አመስግኛለሁ..ይድረሳቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ እያለሁ ነበር በክፍል 11 ላይ ያልውን ዘገባ ያቀረብኩት፡፡ ከዚህ ዘገባ በኋላ ድንገት አንድ በ00251114…. የሚጀምር ስልክ ጥሪ ደረሰኝ፡፡

     መቼም ከኢትዮጵያ የሚደውል ወዳጅ ዘመድ ነው ብዬ በጉጉት ተወጥሬ ‹‹ሀሎ!..›› አልኩ በጎርናናው ድምጼ ጉሮሮዮን ለወሬ እያጸዳሁ፡፡ ምላሽ ለመስማት ጆሮዬን ሪከርድ የሚለው ላይ ክሊክ አድርጌያለሁ፡፡ ለስለስ ያለ የሴት ድምጽ ‹‹ህይወት እባላለሁ..›› በሚል መልዕክቱን ማንቆርቆር ጀመረ፡፡ ‹‹..ሀበሻ በየመን የሚለው ፅሁፍህ ላይ አብዱል ገዊ በሚባለው ሰውዬ ስለተያዙት ልጆች አነበብኩ የአጎቴ ልጅ ተይዞ ገንዘብ ላኩ ተብለናል፡፡…›› አለችና ልጁ ደውሎ የሰጣትን ስልክ ቁጥር ሰጠችኝ፡፡ ህይወት ቢሆንም ስሟ hiwi mare በሚል ነው ፌዝቡክ ላይ ያለችው፡፡

      ይሄኛው አፋኝ እስካሁን ስሙን ያልሰማሁት ከሚገባው በላይ ጨካኝ የተባለ እንደሆነ ስልኩን ደውዬ ሳናግረው ሀብታሙ የሚባለው የደወልኩለት ልጅ ነገረኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ስልኩ ከሰውየው ጀሌዎች ውስጥ የአንዱ ነው፡፡ የዋናው አለቃ ስሙ ዘይን አሊ አብዱራህማን ይባላል የመንግስት ከፍተኛ ባለማዕረግ ሲሆን መኖሪያው አደን የሚባለው የየመን ሁለተኛ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ከ1000 በላይ ኢትዮጵያዊያን ከአስር ባላነሱ ቦታዎች ከፋፍሎ ማገቱን ለማወቅ ቻልኩ፡፡ በመጀመሪያ ክስ ያነሳንበት ሞካ አካባቢ ያለው አብዱል ገዊ ለጊዜው ሸሽቶ ወደ ጅቡቲ አምልጦ አዩ የሚባል ቦታ ተቀመጠ፡፡ እዛም ሆኖ ግን በጀልባ የሚጫኑትን እያየ ደውሎ በዚህ ሰዓት ይገባሉ ብሎ ስለሚነግራቸው ሰራተኞቹ ማገቱን ቀጠሉ፡፡ አካባቢው ላይ በአጠቃላይ ከአስራ ዘጠኝ የሚበልጡ ቡድኖች ኢትዮጵያዊያንን እያገቱ የየመን 50.000 ሪያል ወይ የሳዑዲ 900 ሪያል አለያም የኢትዮጵያ 5000 ብር እንዲያስልኩ ታጋቾቹን እያስደወሉ ያሰቃያሉ፡፡ በእሳት ያቃጥላሉ፣ የፈላ ውሀ ውስጥ ይነክሯቸዋል፡፡ በዱላ ይደበድቧቸዋል፡፡ ይህን አስፀያፊ ስራ የሚሰሩ ቅጥረኛ ኢትዮጵያያንም መኖራቸውን መስማት ደግሞ የበለጠ ውስጥ ያደማል፡፡

 እነዚህ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት የሚፈልጉ ህገ-ወጥ ኢትዮጵያዊ ተጓዦች በአጋቾች ከደረሰባቸው ጉዳት ሲያገግሙ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት /IOM/ እንደተረከባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሀረጥ የሚባለው መጠለያ ክምፕ ውስጥ ናቸው፡፡ እንደ ድርጅቱ ቃል አቀባይ አባባል ከሆነ ከUN ጋር በመተባበር ከእገታ ነጻ የወጡትን ሰዎች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ የወንጀለኞቹን ጉዳይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል በህግ እንደሚከታተሉ ገልጸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ የመጀመሪያው ሳይሆን ካለፈው አመት ጄንዋሪ 1 ጀምሮ ዘንድሮ የዘንድሮው ጄንዋሪ 24 ድረስ 170 ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያዊያን ከየቦታው እያገኙ ወደ ሀገር መመለሳቸውን የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት ቃል አቀባይ አቀብለውናል፡፡ ካቀበሉን ወሬ መካከል በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ 90 ወንዶች፣ 10 ሴቶች፣ 50 ህፃናት፣ 20 ሽማግሌዎች ጉዳት ደርሶባቸው አግኝተው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ አይናቸው ጠፍቶ እጃቸው ተሰብሮ ወደ ሀገር መመለሳቸውን እንጂ አጋቾቹን በህግ ለመፋረድ እንዳልሞከሩ ነው፡፡ እንደ ምክንያት ያስቀመጡት ሀገሪቷ ያለችበት ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ እንደሆነ ነበር፡፡

      ከቅርብ ጊዜ በኋላ ከ10 አመት ጀምሮ ያሉ ህፃናት በሚያስገርም ሁኔታ በጅቡቲ በኩል እያደረጉ ፍልሰቱን የተያያዙት መሆኑን የአይን እማኞች ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ ያናገርኳቸው ሰዎች እንደገለጹልኝ ህጻናቱን ይዘው ወደ ሳዑዲ የሚጓዙት በአብዛኛው በእድሜ ገፋ ያሉት ሰዎች እንደሆኑ እና አፀያፊ ነገር ለመፈፀሚያ አሳልፈው ሊሸጧቸው እንደሆነም ገልጸውልኛል፡፡ ገዢዎቹ አረቦች እየተጠቀሙባቸው ከብት እረኝነትም እንደሚያሰሯቸው ሳዑዲያ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያንም በይፋ ይናገራሉ፡፡ ይህ የሳዑዲ አረቢያ ጉዞ የብዙዎችን ህይወት የቀጨ፣ የትም ያስቀረ እና ብዙዎችን ለጁፒተር ሆቴሉ የግብረሰዶሞች ስብሰባ የጋበዘ ጠንቀኛ ነገር ሀገራችን ውስጥ የዘራ መሆኑ አይካድም፡፡

        መንግስት ቁጥጥሬን አጥብቂያለሁ ወደ ጅቡቲ የሚሄዱትን እየያዝኩ ነው ቢልም እለት ከእለት የሚጎርፈው ሰው እየጨመረ እንደሆን ይታወቃል፡፡ ከመጨመሩም ጋር በተያያዘ ነው ኢትዮጵያዊያንን ማገቱን በተቀናጀ መልኩ ያጧጧፉት፡፡ ይህ ሁኔታ ቀጣይ ሆኖ ሁሌ እንደ እሳት እራት ወደ መጥፊያችን እንሮጥ እንዳንከርም መንግስትም ሌሎች የሚመለከታችሁ እና ህዝቡን ማስተማር ያለባችሁ አካላት በርቱ እንቅስቃሴ ልታደርጉ ይገባል፡፡ የመን ውስጥ እንዳለው ኢትዮጵያ ኤምባሲ ላንቲካ አንሁን እባካችሁ፡፡ በቀጣይነት አሁን ታግተው ያላሉት ለማስለቀቅ ምን መደረግ እንዳለበት መንግስትም ሆን እያንዳንዳችን ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ድምጻችሁን ማሰማት የምትችሉ ሁሉ እባካችሁ ቀሪዎቹን ለማስፈታት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በድጋሚ ትግል እንዲያደርጉልን ቀስቅሱ…ቀሪ ከ800 በላይ ኢትዮጵያዊያን በአጋቾች እጅ ናቸው፡፡ ምን ማድረግ ይሻላል?

Ethiopians in yemen 12

Ethiopians in yemen - part 12

                   እስኪ ቸር ያሰማን!!!!!!!

                         አሜን!!

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on March 10, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.