<<ሲሉ ሰምታ….>>

(በደረጀ ሀብተወልድ)
የምርመራ ጋዜጠኝነት( Investigative journalism)፤ መረጃ በማደራጀቱም ሆነ ዘገባውን በማቀናበሩ ረገድ ከመደበኛው የጋዜጠኝነት ተግባር የተለየ ችሎታን፣ብቃትን፣ጥንቃቄንና ድፍረትን ይጠይቃል። በተለይ የምርመራ ሪፖርቶች ብዙውን ጊዜ የሚያነጣጥሩት በሥልጣን አናት ላይ በተቀመጡ ሹመኞችና ከነሱ ጋር ንክኪ ባላቸው ኩባንያዎች፣ድርጅቶች፣ ፋብሪካዎችና መሰል ልዩ ልዩ ተቋማት ላይ በመሆኑ፤ህይወትን እስከማጣት የሚያደርሱ በርካታ ተግዳሮቶች(challenges)የተጋረጡበት ዘርፍ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ለጋዜጠኞች በሚሰጥ ወርክሾፕ ላይ ስለምርመራ ጋዜጠኝነት የሚቀርበው ምሳሌ፦ የዋተር ጌት ቅሌት ነው። ከዚያ ባለፈ ፦”በኢትዮጵያ የምርመራ ጋዜጠኝነት ተሠርቶ ያውቃል ወይ?”ለሚለው ጥያቄ፤ በደርግ ሥርዓት በነጋዜጠኛ ንጉሤ ተፈራ አማካይነት አፋር ክልል ውስጥ ይፈጸም የነበረ የሙስና ቅሌት መጋለጡ ይጠቀሳል። ይሁንና እነ ጋዜጠኛ ንጉሤ የፈጸሙት ተግባርም፦እንደ ምርመራ ጋዜጠኝነት ጅምር ሙከራ እንጂ፤እንደተሟላ የምርመራ ሪፖርት አልተነገረንም።

ሀቁ ይህን በሚመስልበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ፈርስቱ ቢንያም (ቤን)፤ ሰሞኑን የምርመራ ሪፖርት ሠራሁ ይለናል። < <ጋዜጠኛ አበበ በለው በሚስቱ ስም ኢትዮጵያ ቤት መሥራቱን መረጃ አግኝቻለሁ>> የሚለው ቤን፤ < ይህ እንደ ምርመራ ሪፖርት ይመዝገብልኝ> እያለ ነው።

< ሲሉ ሰምታ ለስሟ መጠሪያ ቁና ሰፋች> አሉ መምሬ አከለ?
-በመጀመሪያ ደረጃ የእዚህ ጉዳይ አጠቃላይ ጭብጥ ለምርመራ ሪፖርት የሚሆን ነወይ?ብለን ስናየው፤ መልሱ በአጭሩ ሊሆን አይችልም የሚል ነው።ምክንያቱም የምርመራ ጋዜጠኝነት ዘገባ ጭብጥ የሚሽከረከረው፤ በአገርና በህዝብ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ በሚችሉ በላቁና በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ነው።አንድ በፍርድ ቤት የተፈረደበት ዜጋ ኢትዮጵያ በባለቤቱ ስም ቤት መሥራቱ ፤ለምርመራ ጋዜጠኝነት ጭብጥ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። በጣም ተራ ጉዳይ ነው።ያ ሰው ያን በማድረጉ ከራሱ አልፎ ሊጎዳ የሚችለው አገርና ህዝብ የለም። በዚያ ላይ ቤተ-ሠሪው አካል በመሬት ግዥም ሆነ ግብር በመክፈል ምንም ስህተት አለመፈጸሙ ሲታይ፤ ቤን < የምርመራ ሪፖርት>ብሎ የለጠፋትን አሉባልታ የምናስቀምጥባት ቦታ ይጠፋናል።

-በሁለተኛ ደረጃ ጋዜጠኛ አበበ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚስቱ ስም ቤት አለው ብለው እየተናገሩ ያሉት የኢህአዴግ ሹመኞችና ደጋፊዎች ናቸው። በአንፃሩ አበበ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ነገር እንደሌለው ነግሮናል።ከምርመራ ሪፖርት ብቻ ሳይሆን ከመደበኛ የጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር አንዱ፤ ሙሉነት(completeness) የሚባለው ነው። አንድ ዘገባ የሁሉንም ወገኖች አስተያዬት ማከተት አለበት እንደማለት ነው።በቤን ዘገባ ላይ ግን የአበበ በለው ሀሳብ ወይም አስተያዬት አልተካተተም። ስለዚህም ቤን በጉዳዩ ዙሪያ በድረ-ገጹ ላይ < የምርመራ ሪፖርት>ብሎ የለጠፈው ጽሁፍ፤ እንኳን የምርመራ ሪፖርት ሊሆን ፤ተራ ዜናም ሊባል አይበቃም ማለት ነው።

ከዚሁ ከሙሉነት ነጥብ ጋር አያይዘን ማዬታችንን ስንቀጥል፤ የቤን ሪፖርት ያላካተተው የአበበን አስተያዬት ብቻ አይደለም። ለምሳሌያችን እንዲመቸን< < ቤቱ በአበበ ባለቤት ስም የተሠራ ነው>>ብለን እንውሰድ ብንል እንኳ፤ባለቤቱ በራሷ መንገድ መሥራት አትችልም ወይ?፣ ባልና ሚስት አንድ አቋም ይኖራቸዋል ብሎ መደምደም ይቻላል ወይ?፣ ባል< በህግ> ስለተፈረደበት፤ሚስት በስሟ የሠራችው ቤት መታገድ አለበት የሚለው ውሳኔስ፤ ከህግ አኳያ እንዴት ይታያል? ከሚሉት በርካታ ጥያቄዎች፤ የቤን ጽሁፍ ለአንድኛቸው እንኳ መልስ የሰጠ አይደለም።ተራ ፕሮፓጋንዳ ነው።እዚህ ላይ ሌላው አስገራሚ ነገር፤በየአደባባዩ፦< ሴት ከወንድ እኩል ናት> የሚሉን ገዥዎቻችን፤ ሚስት የራሷ አቋም እንደሌላት ገምተው በስሟ የሠራችውን ቤት- የባሏ ነው ብለው መደምደማቸው ነው-ትምክህተኞች!!

– በሦስተኛ ደረጃ -ከላይ የምርመራ ጋዜጠኝነት በባህሪው ብዙውን ጊዜ ቁንጮ ባለስልጣናትና ከነሱ ጋር ንክኪ ባላቸው አካላት ላይ የሚያነጣጥርና አንድን ጋዜጠኛ የህይወት ዋጋ ጭምር የሚያስከፍል ነው ብያለሁ። የቤንን ሥራ ከዚህ አንጻር ስንመዝነው ደግሞ ይበልጥ አስቂኝ ይሆናል።ምክንያቱም አበበ በባለሥልጣን እየታደነ ያለ ጋዜጠኛ ነው። ቤን ደግሞ ከአሳዳጆቹ ባለስልጣናትና ከከፍተኛው የአገሪቱ ቱጃር ጋር የተሰለፈ ሰው ነው። ከዚህ አኳያ አበበ -በቤን ዙሪያ የምርመራ ሪፖርት ሊሠራ ይችል ካልሆነ በስተቀር፤ የአሳዳጆቹ አጋር የሆነው ቤን በተሳዳጆች ላይ የምርመራ ሪፖርት ሊሠራ የሚችልበት ዕድል እጅግ በጣም ጠባብ ነው። ስለሆነም ቤን ፤ ከአንድ ወገን(ምናልባትም ከጓደኞቹ )ያገኘውን ዶክመንት ስለለጠፈና እየዘነጠ ወደ ፍትህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በመግባት- ተዘጋጅተው እንዲጠብቁት የታዘዙለት ባለስልጣን ጋር እያወራ ቪዲዮ ስለተቀረጸ፤< የምርመራ ሪፖርት ሠራሁ> ማለቱ፤ ትልቅ ድፍረትና ነውረኝነት ነው።

እንዴ ቤን፤ እኛ በየጊዜው ስለተለያዩ ግለሰቦችና ሹመኞች ስንት መረጃዎች ይደርሱናል መሰለህ? እነዚህን መረጃዎች የፈለገውን ጊዜ ያህል ቢወስድ በተቻለ መጠን ከሚመለከታቸውና ጉዳዩ ከሚያገባቸው አካላት ሳናጣራ እንደወረዱ ብለቃቸው እንዳንተ ዓይነት ስንትና ስንት < <የምርመራ ሪፖርት>>ባስቆጠርን ነበር። ግን ያን እንድናደርግ አስተዳደጋችንም ሆነ ሙያዊ ሀላፊነታችን አይፈቅድልንም።
አዎ! ከአንድ ወገን የተሰማን ወሬ ቀዳዳው ሰፊ እንደሆነ ወንፊት እንዳለ እየዘረገፉ፦ < የምርመራ ሪፖርት ሠራሁ> ማለት፤ በተከበረው የጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የተቃጣ ከባድ የድፍረት ወንጀል ነው።

ሁለት ማስታወሻዎች፦
1-ለምሳሌ እንዲያመቸን በሚስቱ ስም ቤት ተሠርቷል ብለን እንውሰድ አልኩ እንጂ፤አበበ በሚስቱ ስም ቤት ሠርቷል አላልኩም
2-ባለፉት 21 ዓመታት በግሉ ፕሬስ በኩል በተሠሩ ሥራዎች ዙሪያ ሰፊ ጥናት ቢደረግ፤ ሽልማት ሊያስገኙ የሚችሉ የምርመራ ሪፖርቶች ሊገኙ እንደሚችሉ እገምታለሁ

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on October 3, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.