በወቅታዊው የሚዲያ ነጻነት ጉዳይ – የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ነጻ ጋዜጠኞች መግለጫ አወጡ!!

Share

በፍትህ ጋዜጣና በአዘጋጁ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ፤ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት መብት ጨርሶ መጥፋቱን የሚያረጋግጥ ክስተት ነው!!
Click here to read the press release in PDF
 (በውጭ አገር ከሚገኙ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች የተሰጠ መግለጫ) August 12, 2012

የፍትህ ጋዜጣ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ብቸኛ የነፃ ፕሬስ አማራጭ በመሆን፤ የህዝብን የማወቅ መብት ተግባራዊ ለማድረግ የተጣለበትን ተጽ እኖና በአስቸጋሪ አፈና ተቋቁሞ ውስጥ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ሃምሌ 12 ቀን 2004 ዓ.ም ከአንባብያን እጅ መድረስ የነበረባት የፍትህ ጋዜጣ እትም ግን፣  አቶ መለስ በህመም ይሁን በሞት እስካሁን ባልተረጋገጠ ሁኔታ ከአገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ቦታቸው ላይ ለረጅም ጊዜ አለመገኘታቸውን አስመልክቶ ባጠናቀረው ዘገባ ምክኒያት፣ ለሕትመቱ ብዙ ሺህ ብሮች ከወጡበት በኋላ፣ የጋዜጣው ኮፒ ከማተሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ሳይወጣ እንዲታገድ ተደርጓል።በተጨማሪም የዚህ መንግስት መቀለጃ በሆነው ፍርድ ቤት የታተመው 30 ሺህ ጋዜጣ እንዲቃጠል ተፈርዶበታል። በዚህ በኩል ፍትህ ጋዜጣ፣ በአገራችን በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እሳት እንድትለበለብ የተፈረደባት የመጀመሪያዋ ጋዜጣ ናት።

  ይህ ሁሉ ሆኖ የፍትህ ሚኒስትር ባለስልጣናት ጋዜጣው በነፃነት ስራውን መቀጠል እንደሚችል በአንደበታቸው ቢገልጹም፣ አገዛዙ ግን በማተሚያ ቤቶች ላይ በፈጠረው ስውር ጫና ምክንያት ደፍሮ ጋዜጣዋን የሚያትም ድርጅት ባለመገኘቱ በተዘዋዋሪና በይፋ ፍትህ ጋዜጣ በመንግስት ታግዳለች።

የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ለፍኖተ ነጻነት በሰጠው ቃለ መጠይቅ ለበርካታ ግዜያት ከአገዛዙ ባለስልጣናትና የደህንነት ሰዎች የተለያዩ የመብት ጥሰቶች ተፈጽሞበታል። ይህ ሁሉ ህገ ወጥ ጫና የፍትህን ህትመት በተጽዕኖ ለማስቀረት ነው። ይህ ጥቃትና ጫና በተጠናከረ መልኩ ቀጥሎ አርብ ነሃሴ 4 ቀን 2004 ዓ.ም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መጥሪያ ሳይደርሰውና፣ ስለጉዳዩ ምንም አይነት መረጃ ሳይኖረው በፍርድ ቤት ሶስት ክሶች እንደተመሰረቱበት፣ እንደማንኛውም ሰው በራድዪ ሲነገር ሰምቷል። በዚሁ ራድዮ ጣቢያ የጋዜጣው አሳታሚ የሆነው “ማስተዋል አሳታሚ ድርጅት”ም ክስ እንደተመሰረተበት ተነግሯል። አንድ ዜጋ እዚያው ቅርባቸው እያለ  መጥሪያ ሳይደርሰው፣ የክስ ቻርጁን ሳያውቅ፣ በሌለበትና ባልተጠራበት ችሎት ክስ ሲመሰረትበት ጋዜጠኛ ተመስገን በታሪክ የመጀመሪያው ሰው ሳይሆን አይቀርም።

የህወሃት/ ኢህአዴግ መንግስት ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት የፕሬስ ነፃነት ጠላትነቱን በተደጋጋሚ አስመስክሯል። በርካታ የነፃ ፕሬስ ውጤቶችን አግዷል፤ በተለያዩ ጊዜያት “ህዝብን በመንግስት ላይ አነሳስታችኋል” ከማለት ጀምሮ “አሸባሪዎች” በሚል፤ ፍ/ቤቶችን ተገን አድርጎ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞችን አስሮ ከማንገላታት አሁንም እንዳልተቆጠበ እያየን ነው።

 ድህረ ምርጫ 97ን ተከትሎ ስርዓቱ በምርጫው ለደረሰበት ሽንፈት በግልፅ ተጠያቂ ያደረገው የነፃ ፕሬስ ጋዜጦችንና ጋዜጠኞችን እንዲሁም የሙያ ማህበራቸውን በመሆኑ፤ ሁሉም የጥቃቱ ዒላማ ነበሩ። በርካታ ጋዜጦች እንደዛሬዋ ፍትህ ሁሉ እገዳ ተደርጎባቸዋል። ከእነዚህ መካከል ነፃነት፣ ኢትኦጵ፣ አባይ፣ ሳተናው ሚኒሊክ፣ አስኳል፣ ጦማር፣ አዲስ ዜና፣ ጦቢያ፣ ልሳነ ሕዝብ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በተለይ ኢትኦጵ ጋዜጣ የ130 ሺህ የህትመት ትዕዛዝ ሰጥቶ በመታተም ላይ እንዳለ በደህንነቶች ጣልቃ ገብነት በተሰጠ ትዕዛዝ ህትመቱ እንዲቋረጥና የታተሙትም ጋዜጦች እንዲወረሱ መደረጉ ይታወሳል።

ከድህረ ምርጫ 97 በኋላ 14 ጋዜጠኞች ወህኒ ወርደው በፈጠራ የአገር ክህደትና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመገልበጥ ክስ ተከሰው ታሰሩ። ብዙዎች አገር ጥለው ተሰደዱ። የሙያ ማህበራችን ኢነጋማ በአገር ቤት ሙሉ ለሙሉ እንዳይንቀሳቀስ ታገደ። የጽ/ቤት ንብረቱ ተወረሰ። የታሰሩት ከተለቀቁ በኋላ በሁለተኛው የነፃ ፕሬስ ምዕራፍ ብቅ ካሉት ጥቂት ጋዜጦች “ፍትሕ” በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። የአዲስ ነገር እና የአውራምባ ታይምስ አዘጋጆችና ጋዜጠኞች በየጊዜው በደረሰባቸው ጫና አገር ጥለው በመሰደድ ጋዜጦቹ ሲዘጉ የስርዓቱ አራማጆች “ውጭ ለመውጣት በመፈለጋቸው ነው” ማለታቸው አይዘነጋም። ለአንዳንዶቹ ተጨማሪ ክስና የቅጣት ውሳኔ በተሰደዱበትም አልቀረላቸውም።

ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት አለሙንና እስክንድር ነጋን “አሸባሪዎች” ብሎ ክስ የመሰረተው የወቅቱ አስተዳደር፤ የፍትህ ጋዜጣን ማገዱ በኢትዮጵያ ጭል ጭል ሲል የነበረው የፕሬስ ነፃነት ሙሉ ለሙሉ መዳፈኑን የሚያመለክት፤ ብሎም አምባገነኑ ስርዓት በግልፅ መንግስት ያልፈለገውን በመፃፍ ማሳተም እንደማይቻል ያረጋገጠ የአፈናው ደረጃ እየጨመረ መሄዱን የሚያሳይ ነው።

በአገራችን የፕሬስ ነፃነት መረጋገጥ የዜጎች ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ህጋዊ መብት እንዲከበር መታገል ደግሞ የጋዜጠኞች ተልዕኮ ብቻ እንዳልሆነ ሁሉም ይገነዘበናል ብለን እናምናለን። ስለዚህም ለእውነት ተቆርቋሪ የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፦ ፍትህ ጋዜጣን አግደው፤ እንዲሁም ዋና አዘጋጁ ተመስገን ደሳለኝ ባልቀረበበት ችሎት ተሰይመው ክስ በመመስረት፣ በፍትህ ስም ፖለቲካዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተሰናዱ ያሉትን ዳኞች በመቃወም፤ በተጨማሪም ለፍትህ እና የፕሬስ ነጻነት ብሎም ለሙያቸው ክብር ሲሉ ህዝባችንን በቅንነት ስላገለገሉ በ“ሽብርተኛነት” ተወንጅለው ለእውነት መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ከሚገኙት የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ጎን በመቆም፤ በማንኛውም መልኩ አጋርነታችሁን እንድታሳዩ በአክብሮት እንጠይቃለን።
በውጭ አገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች

Share
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on August 11, 2012. Filed under AMHARIC/አማርኛ,FEATURED. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. You can leave a response or trackback to this entry

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*



English
Amharic       Geez help: [download] [help] [keybord]

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>