“ሽቦ ግቢ እንገናኝ” ሊቀር ነው

(ግርማ ደገፋ ገዳ)

ሽቦ ግቢ በጣም ልዩ ስፍራ ነው። በልዩ ልዩ ቀለማት ባበዱ ቢራቢሮዎችና በልዩ ልዩ የወፎች ዝማሬ የተዋበ ነው። በአረንጓዴው መስክ ላይ ጋደም ብለው የወደፊት የትዳር ዓለማቸውን የሚያልሙ የፍቅር ጓደናሞች፣ ክንድ ለክንድ ተያይዘው በነዚያ በሚያማምሩት የሆላንድ ዛፎች ጥላ ሥር ሆነው የፍቅር ጉዞ የሚያደርጉ ፍቅረኛሞች፣ አልያም ዛፍ ሥር ተቀምጠው የሚያጠኑ ወጣቶችን ማየት የተለመደ ነው። መለስተኛ ጫካ ከሚመስሉትና በሥነሥርዓት ከተተከሉት ዛፎች ውስጥ እየተሽለኮለኩ መጫወት፣ በቀላሉ የሚረሳ አይደለም። የአካባቢው የድሮ ወጣቶች፣ ግን የዛሬ ጎልማሶች፤ ያንን ሲያስታውሱ አንድ ነገር ብቻ ነው ሊቀድማቸው የሚችለው─እንባ።

Wenji

ሆላንዶች አበባ ይወዳሉ። ወንጂ ውስጥ ያላመጡት አበባ የለም። በተለይ ሽቦ ግቢ ውስጥ ከሆላንድ የመጡ አበቦችና ዛፎች በብዛት ይታያሉ። ቤታቸውና ቢሯቸው ዓይን በሚማርኩ ልዩ ልዩ አበቦች የተከበበ ነው። ሽቦ ግቢ ያደጉ ያካባቢያችን ልጆች፣ ማለዳ ከእንቅልፋቸው ተነስተውና መስኮታቸውን ከፈት አድርገው፣ እነዚያን ውብ አበባዎች እየተመለክቱ፤ “Today is a beautiful day” ይላሉ ብለን እናስባለን።

ወንጂ ሲነጋ ፍቅር ነው። ሲመሽም ፍቅር ነው። ቆንጆ ማየት ሲያስፈልግ ወደ ሽቦ ግቢ ወረድ ትላለህ። እነሩት፣ እነየውብዳር፣ እነማርብል፣ እነገነት፣ እነኤልሳ እና እነናፍቆት አሉልህ። በDutch Style ባማረ የሸክላ ጡብ ከታነጸው የሆላንዶች ቪላ ውስጥ ተወሽቀውልሃል። እድለ ቢስ ሆነህ ባታገኛቸው እንኳ፣ በሰፈራቸው ማለፉም አስደሳች መሆኑን አስቀድመህ ስለምታውቅ፤ አትናደድም። ይልቅ የማይጠገበውን የአበቦቹን ውበት እያደነቅህ፣ ነፋሻማውን ውብ የሽቦ ግቢ አየር ትኮመኩማለህ። ያውም በነጻና በነጻነት! …..ስለዚህም ትደሰታለህ።

በወንጂ ዘር ቆጥሮ ፍቅር አልነበረም፤ ጭራሽ አልተወለደም። ሁሉም ራሱን የሚያየው በዚህ ምድር ላይ አንድ ቦታ ላይ  መወለዱን ነው። ራሱ ሊቆጣጠረው በማይችለው ሁኔታ መፈጠሩን ነው። ስለዚህም፣ ሴቷ ‘ፍቅር አስያዘኝ’ ባለችው ላይ መጣበቅን ነው። ወንዱም ‘ጨርቄን አስጣለችኝ’ ባላት ላይ መደፋትን ነው። አጥሩ ፍቅር ነው። መንገዱ ፍቅር ነው። ኳስ ሜዳው ፍቅር ነው። ትምህርት ቤቱ ፍቅር ነው።

ወንጂዎች የትም ይሂዱ የት ለፍቅራቸው ‘ዘረኝነት’ ከመስፈርቱ ውስጥ የለም። እስቲ አንድ የድሮ ጓደኛህን አፈላልግና ያገባት ሴት ከየት እንደሆነች ጠይቀው። በመልሱ ትገረማለህ! የምታውቃት ሴትም ካለች አፈላልገህ ጠይቃት፤ መልሷ አንጀትህን ያስደስተዋል። ከዚያም “ይሄ ጸሐፊ እውነቱን ነው፤ ግን ማነው?” ትላለህ። ለነገሩ ባትለኝም ግድ የለኝም፤ እኔ ለዚያ አይደለም የጻፍኩትና! …..እንደዚያ ዓይነት ነገሮችን ለማሰብ ጊዜ ያለኝ ይመስለሃል? አትንከራተት!

‘ወንጂዋን፣ ሲፒ፣ በርባዶስ፣ ወተቴ፣ አጣና ሞሪስ፣ ስኳር ሞሪስ…..’ የሚባሉ የሸንኮራ አገዳ ዘሮች ነበሩ። ሸንኮራ ሲያስፈልግህ፣ ግራ ቀኝህን ታያለህ። እነ ጋሽ አባቼ፣ ሎንጌ፣ ቢክ፣ ጢቆ፣ ታምሩ እና ሌሎችም ጋርዶች ጠመንጃና ረጃጅም ዱላ ይዘው በስፍራው አለመኖራቸውን ታረጋግጣለህ። ከዚያ ከአረንጓዴው ማሳ ገባ ብለህ፣ ከመለሎው ሸንኮራ ሰበር አድርገህ፣ ልምድ በሚጠይቅ የአላላጥ ስልት እየሸረከትከው ታጣጥመዋለህ። ጣፋጩ የሸንኮራ ጭማቂ አንጀትህን ሲያርሰው ይታወቅሃል። ከአፍህ ተርፎ በአገጭህ ላይ ኮለል እያለ መሬት ላይ ‘ጧ!’ ሲልም ይሰመሃል። ጆሮህ እና ዓይንህ ደግሞ የጋርዶችን የአሰሳ ድምጽና እንቅስቃሴ ይከታተላሉ!

ጋርዶቹ ከመጡብህ በአንዱ አቅጣጫ ፈጣኑን ሩጫህን ትለቀዋለህ። ሆድህን ቀዝፎ ይዞት የነበረውም ጣፋጭ ጭማቂ ብን ይላል። ማምለጥህን ስታረጋግጥ፣ በጭማቂው የነጣጣውን አፍህንና አገጭህን በተገኘው ውኃ ትጠራርጋለህ። ቤትህም ስትደርስ ሃይለኛ ጨዋ ትመስላለህ። አባትህ ገልመጥ ሲያደርጉህ፤ ደብተሮችህን ታወጣና የነኬሚስትሪና ጆግራፊን የቤት ሥራ መሥራት ትጀምራለህ። ልብህ ግን ሁለት ቦታ መከፈሉ እውነት ነው፤ አንዱ ከሽቦ ግቢ ቆነጃጅት፣ አንዱ ደግሞ ከሸንኮራ አገዳ ጋርዶቹ።

ዛሬ ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ገብተው ከተመረቁና ጥሩ፣ ጥሩ ሥራ ከያዙት አብዛኛዎቹ እኔ አሁን በምነግራችሁ የታሪክ መስመር ውስጥ ያለፉ ናቸው። ዲፕሎማቶች አሉ። ኢንጂነሮችና ዶክተሮች ብዙ ናቸው። ሰዓሊያን፣ ደራሲያንና ጋዜጠኞች አሉበት። በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የመምሪያ ኃላፊ የሆኑ አይቆጠሩም። ወደ ውጭም ዘልቀዋል። በፌስቡክ ተሰባስበውም ስለወንጂ መወያየት ጀምረዋል። …..ግን አጣና ሞሪስ እና ስኳር ሞሪስ ምን ማለት ነው? ድሮ ምንም ግድ የለንም። አሁን ግን ስሙ ራሱ ግርም ይላል። አጣና ሞሪስ እና ስኳር ሞሪስ ብሎ ሸንኮራ! …..እስቲ እሱን ለቀቅ እናድርግና ስለ ኳስ እናውራ!

በወንጂ፤ በየመንደሩ የተዘጋጁት ኳስ ሜዳዎች በእግር ኳስ አፍቃሪዎች ተሞልተው ነው የሚታዩት። የአባት ቡድኖች አሉ። የወጣቶች አሉ። የታዳጊዎች አሉ። የሴት ወጣቶች አሉ። የማሊያዎች ዓይነትና ዲዛይን ትንግርት ነው። አፖሎ፣ መታፈሪያ ጋረደው፣ አንድነት፣ ገብረሕይወት፣ ስኳር ምንጭ፣ ሳምሶን፣ ወንድማማች፣ የንጋት ጮራ፣ ሰሜን በር፣ ዋልያ፣ ምስራቅ ቡልኬት፣ ቀይ ኮከብ፣ ጭማድ፣ ግረፍ፣ ክተት በአየር፣ ቴክኒክ በልጅነት፣ ክተት በደቂቃ፣ የነገው ተስፋ፣ ቀስተ ደመና፣ ነጻነት እና የመሳሰሉት የወጣቶችና የታዳጊ ቡድኖች ስሞች ነበሩ።

ኳስ ሜዳዎቹ እረፍት የላቸውም። ከሰኞ እስከ አርብ በተለማማጆች ይጠቀጠቃሉ። ቅዳሜና እሁድ የግጥሚያ ቀናት ናቸው። በግጥሚያ ቀናት ከኳስ ሜዳዎቹ የሚነሱት የድጋፍ ጩኸቶች የትና የት ነው የሚሰሙት። ተጋጣሚዎቹ ኳስ ሜዳው ውስጥ ሲተናነቁ፤ ተመልካቾቹ  ማዶ ለማዶ ተፋጠው ሲበሻሸቁ ማየትና መስማት ያስደስታል። አንዳንድ ተጫዋቾች ከተመልካቹ መሃል የሚወዷት ቆንጆ ካለች፣ የሚያሳዩት የአጨዋወት ስልት ተአምር ነው። ሌላ ጊዜ ነካ ሲያደርጓቸው ድፍትና ስብር ብለው እየተንፈራፈሩ “እሪጎሬ ይሰጠን!” እያሉ የሚጮሁት ሁሉ፤ በኃይለኛ ጠረባ ሲመቱ እንኳ፤ አይወድቁም። ጠረባውን እንደምንም ችለውና እንደምንም ተንገዳግደው በመቆም፣ ጥንካሬያቸውን ያሳያሉ። ከዚያም፣ ቆንጂት ወዳለችበት አቅጣጫ በቆረጣ እያዩ፤ “አየሽ ጥንካሬዬን!” መልእክት ይሰዳሉ።

ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ፣ በአንድ ወቅት፣ “የወንጂ ሕዝብ ከአፍሪካ እንደ ግብጹ ዛማሌክ፣ ከአውሮፓ ደግሞ እንደ እንግሊዙ ሊቨርፑል ዓይነት የእግር ኳስ ፍቅር ያለው ሕዝብ ነው” ብሎ ነበር። ያንን ያለው ለእኔና ለወንጂ ነዋሪ መሰለህ? አይደለም። በኢትዮጵያ ብሔራዊው ሬዲዮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ያ ሁሉ ከተባለለት አካባቢ፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ለመሰለፍ የበቁት (እኔ እስከማውቀው ድረስ) ተስፋዬ ኤርጌቾና ሰለሞን አየለ ብቻ ናቸው። በእርግጥ ሰለሞን አየለ፣ ለወጣቱ ብሔራዊ ቡድን ግብጽ ላይ ብቻ ነው የተጫወተው። ለአንድ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ለመጫወት ኮንትራት ፈርሞ፣ ከኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ላይ አጭሩ ስሙን ትቶ መራቁን፣ ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ያስታውሳሉ። ዛሬ የት እንዳለ ባላውቅም፣ የኳስ ጥበቡን ተአምር ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም ሊያሳይ የሚችል ሰው እንደነበር መሰክርለታሁ። ሰለሞን አየለ የተፈጠረው ለኳስ ብቻ ነበር፤ ለሌላ ለምንም አይደለም። እሱም ያንን ሰለሚያውቅ ይመስለኛል፤ አስመራ ዩኒቨርሲቲን ተሰናብቶ ወደ እግር ኳስ ዓለም የተቀላቀለው።

የቅርጫት ኳስ ሜዳ አለ። የሜዳ ቴኒስ መጫወቻ አለ። መዋኛ አለ። መሮጪያ ሞልቷል። ምን ያደርጋል መዋሸት፤ ከግጥሚያ በኋላ ያሸነፈውም የተሸነፈውም ወደ ሸንኮራ ማሳ ወረድ ማለቱ አይቀርም። መሸትሸት ሲል ደግሞ የዛሬን አያድርገውና ቆንጆ ፍለጋ ወደ ሽቦ ግቢ፣ ሳይቤሪያ፣ ቡልኬት ሰፈር፣ መስታዎት ሰፈር፣ ሚስማር ሰፈር፣ ሲሚንቶ ሰፈር፣ ጆንያ ሰፈር፣ ቆርቆሮ ሰፈር፣ አንዳይን ሰፈር፣ ኩራዝ ሰፈር፣ ገፈርሳ፣ ዓለምጤናና ፕላንቴሽን ይኬዳል። አንዳንድ ሰፈር ያሉት ቢንቢዎች ደግሞ፣ ኃይለኛ ናቸው። ብዛታቸው የትና የት ነው። ጥቋቁርና ወደል፣ ወደል ቢንቢዎች! ግን የሚፈራቸው የለም። የሰሜን ኮሪያን ሚሳዬል ታጥቀው ቢመጡ እንኳ፤ አይፈሩም! …..ፐ! ታየኝ’ኮ የወንጂ ልጅ ቢንቢ ሲፈራ! በቢንቢ ምክንያት ቆንጆ ሳያይ ውሎ ሲያድር! እም! …..ዛሬ እነየወንጂ ቆነጃጅት ሃቁን እወቁት፤ በነዚያ ሁሉ ቢንቢዎች እየተጠበጠበ ነበር የወንጂ ጎረምሳ እናንተን ያሳድድ የነበረው። ጎበዝ ናቸው አይደል?

ማር ቆራጭና ዓሳ አጥማጅ ለመሆን መጣጣርም በወንጂ አለ። ማር ቆራጭ የሆነ ጎረቤት ያለው ታዳጊ፣ ቀፎ እንዴት እንደሚሰራና እስከ ማር ማጣጣም ድረስ ያለው ሂደት ምን እንደሚመስል፣ ከማር ቆራጭ ጎረቤቱ ይኮርጃል። መቃ ለመግዛት ገንዘብ ስለማያገኝና ቤተሰቡም የማር ቆረጣውን ሙያ እንደማይደግፉለት አስቀድሞ ስለሚያውቅ፣ መቃን የሚተኩ ቀፎ መስሪያዎችን ለመሰብሰብ በተለምዶ ‘ቅመም’ ተብሎ ከሚጠራው ሰፊ ማሳ ውስጥ ይገባል። ‘ቅመም’ የደረሰ ሸንኮራ ከታጨደ በኋላ፣ የሚቀጥለው ዙር ሸንኮራ ከመተከሉ በፊት የሚዘራ፣ የመሬት ማዳበሪያ ተክል ነው። ጥቅጥቅ ያለና ከሰው ቁመት በላይ ነው። አዴይ አበባም ቅመም ከሚባለው ተክል ጋር አብሮ ስለሚያድግ፣ የቅመም ማሳ ባበበ ጊዜ፤ በቢጫ እርድ የተሞላ ባሕር ነው የሚመስለው። ከዚያ እርሻ ውስጥ በሚገኙ ጠንከር ያሉና ልፍስፍስ ተክሎች፣ ማር ቆረጣ የሚያምራቸው ታዳጊዎች፣ ቀፎ ይሰራሉ። እበት ለቅልቀው፣ አጫጭሰውና አጥነው ቀፏቸውን ይሰቅላሉ።

ከትምህርት ቤት መልስ ደብተራቸውን ወርውረው መጀመሪያ የሚሮጡት ወደ ቀፏቸው ነው። አሳሽ ንቦች ቀፎያቸውን ሲያስሱት ይደሰታሉ። ወደ ሰፈር ተመልሰውም ዜናውን ለጓደኞቻቸው ያበስራሉ። ከትንሽ ቀናት በኋላ፣ ንቦች ቀፏቸውን ለቤትነት መርጠውት ተጠቃለው ሲገቡ፣ ደስታቸው ድርብርብ ይሆናል። ከዚያም፣ ቀፎውን ካለበት የመጀመሪያ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማሻገር እቅድ ያወጣሉ። ማንም ከማይደርስበት ረጅምና አስቸጋሪ ዛፍ ላይ እንደምንም በገመድ ወጥተው ይሰቅሉታል። ጥቅምት ወር ሲገባ ማር ለመዛቅ እያለሙ ይከርማሉ። ችግሩ፣ ያንን ቀፎ እንደራሱ በናፍቆት የሚጠብቅ ሌላ ቡድን ስለሚኖር፤ ሁሉም ባለቀፎ የራሱን ማር ቆርጦ መላሱ እምብዛም ነው። እነዚያ ቡድኖች፣ ከዚያ ረጅምና አስቸጋሪ የዛፍ ጫፍ ላይ በቀላሉ ወጥተውና ቀፎውን አውርደው፣ ማሩን ያጣጥሙታል። ባለቀፎ ታዳጊም፣ መጥፎውን ዜና የሰማ እለት ለያዥ ያስቸግራል፤ ግን በነጋታው ይረሳና የራሱን ቡድን ፈጥሮ ወይም ሌላ ቡድን ውስጥ ተቀላቅሎ፣ ሌላ ሰው የሰቀለውን የደረሰ ቀፎ ማሰስ ይጀምራል። ዓሳ ማጥመድም ያንን የመሰለ ታሪክ አብሮት አለ።

ወንጂ ውስጥ ሰርግና ሞት ሲኖር አንዱ ለአንዱ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ጊዜ አይበቃም። የአካባቢው ነዋሪች ናቸው ዘመዶች። በደንብ ያስደስታሉ፤ በደንብም ያስተዛዝናሉ።

በሰርግ ወቅት እናቶች፣ የዳክዬዎች መዋኛ የሚያካክሉ ድስቶችን ጥደው ሰፈሩን በወጦች ሽታ ያንቀጠቅጡታል። ወገባቸውን በመቀነት አስረው ገብሱን ይፈትጉታል፣ ጌሾውን ይወቅጡታል። የመንደሩን ጋኖች በቁመትና በስፋት አሰልፈው ጠላ፣ ፊልተርና ጠጁን ያሰናዱታል። አባቶች፣ ረጃጅምና ስለታም ቢላዋ እንደ ባንዲራ እያውለበለቡ በሬና በጎች ሲደፉ ነው የሚታዩት። የሰፈር ጎረምሶችም፣ በኃይለኛ መጥረቢያዎች የባሕር ዛፍ ግንዲላ ሲተረክኩ ማየት የተለመደ ነው። ሕጻናት ደግሞ በየሱቁ ይላላካሉ። መኪና ያለው መኪናውን፣ ሞተር ያለው ሞተሩን ለሰርግ ያሰልፋል። ሙሉ ቤቱን ለሰርጉ ዝግጅት የሚሰጥ ሞልቷል። ያን ሰሞን የሰፈሩ ሰው ሁሉ ባሕላዊ ዘፋኝ ይሆናል። እስክስታ በሽበሽ ነው። ወገብ ይዞ “ያዝ እንግዲህ! …..እንዲያ ነው እንጂ! …..በል‘ማ!” እስክስታው ይጦቫል። የሰርጉ እለት ራት ሲበላ፣ ወጥና እንጀራ የተከማቸበት አካባቢ በስውር ሄደው፣ ወጥ በከኔተራቸው የሚሰርቁ ልጆችም አሉ። ቀይ ወጡ እግራቸው  ላይ እየተንተባጠበ ይሮጣሉ። ምክንያቱም ወጡ አንጀት እንጂ እግር ለማቃጠል መች ተሰራ?! …..ድፎ ዳቦና የሙሽሮችን ኬክ መጠበቅ ከባድ ሥራ ነው። ጦርነት መሔድ ቀላል ሳይሆን አይቀርም። እሱ’ጋ የተመደበ ሰው በሰርጉ ዙሪያ የሰፈር ጠላት ሊኖረው ይችላል፤ በጊዜም የሚያጣራ ይመስለኛል!

የትም ለቅሶ ሲኖር የሃዘን ተካፋይ ከሚሆኑት አንዱ አቶ ተስፉ ናቸው። ቀብር አይቀሩም። የሚገርመው አቶ ተስፉ እድር የላቸውም።

ቀይ፣ ቀጠንና ረዘም የሚሉት አቶ ተስፉ፣ በንጹህ ሸሚዝና ብሉ ጂንስ ነው የሚታወቁት። ያ የሳቸው Signature ነው። ብዙ አይናገሩም። ብዙ መሥራት እንጂ ወሬ አይወዱም። ቤታችው ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ ፈርኒቸሮች የተሰሩት፣ በእሳቸው ነው ይባላል። ያውም በትርፍ ሠዓታቸው። እኚህ ጨዋና ባለሙያ ሰው፣ የስኳር ፋብሪካውን የElectronic Instruments Department Head ሆነው ነው ያገለገሉት። “ሥጋ ያስረጃል፣ አትክልት ነው መመገብ” እያሉም ይመክራሉ ይባላል።

ማምሻው ላይ የወንጂ ልጆች ተሰባስበው ሲጫወቱ፣ አንዳንዱ “እኔ እንደ ሰር ገብረሃና (አስተማሪ የነበሩ) ወንደላጤ ነው የምሆነው” ሲል፤ ሌላው ደግሞ “እኔ እንደ ተስፉ፣ ሥጋ ብዙ አልበላም” ሲባባሉ መስማት አዲስ አይደለም።

ዛሬ አላውቅም። የሚቻልም አይደለም። የሚቻል ከሆነ እንደገና ወንጂ ለመወለድ ብዙ ምክንያቶች አሉ።

የቀድሞ ወላጆች ከብዙ ቦታ የተሰባሰቡ ናቸው። የተለያየ ቋንቋ አላቸው። ከየተወለዱበት ወይም ካደጉበት ሥፍራ ያመጡት ነው።  ያ ቋንቋ ሁሉንም ስለማያግባባ ሁሉም አንድ ቋንቋ ይጋራሉ─አማርኛ! …..ቤት ውስጥ ከቤተሰብ ጋር ትግርኛ፣ ጉራጊኛ፣ ከምባትኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሃዲይኛ፣ ሶማሊኛ፣ እና ሌሎቹም መግባቢያ ናቸው። የቤትን ደጃፍ አንድ እርምጃ ከተራመዱ በኋላ፤ እነሱ አይሰሩም። አንዳንድ ወላጆች ራሳቸው አፋቸውን የፈቱበትን ቋንቋ ልጆቻቸው እንዲያውቁላቸው ማስተማራቸውም አልቀረም። ጥሩ አድርገዋል። አንዳንዶቹ  ችለውታል። አንዳንዶቹ መስማት ብቻ። አንዳንዶቹ፣ ከምንም ውስጥ የሉበትም። …..እንዲያ ሆኗል የቋንቋ ትምህርትና ስልጠናው ጉዳይ በወንጂ!

ልጆች በምንም ምክንያት ስለዘራቸው ከማይጨነቁባት ስፍራ አንዷ ወንጂ ነበረች። ሁለት ነገሮች ግን በጣም ያሳስቧቸዋል፤ ትምህርትና እግር ኳስ! …..በቃ! …..በነሱ ብቻ አትምጣበት። ….በሌሎቹ ግድ የለም። እናም ዳግም እድል ካለ የትም አትወለድ፤ …..ግን ወንጂ ተወለድ! …..ሕጻናት፣ እናቶቻቸው ገበያ ሄደው ቢራቡ፣ የጎረቤት እናቶችን ጡት ጠብተው የሚያድጉባት አካባቢ ናት። ያንን የሚያስብ የዛሬ ጎልማሳ፣ ከማልቀስ ውጭ የሚያመጣው ነገር አለመኖሩን ሲያስብ፤ ሃዘኑ ይበረታበታል።

ሽቦ ግቢ ከሚገኘው ከዘመናዊው መዋኛ ለመዋኘት፣ 18 ብር በዓመት ይከፈላል። መዝናኛው ‘ቲ─ሃውስ’ ይባላል። እሷን የከፈለ አባት ለቤተሰቡ ካርድ ይሰጠዋል። ከዚያ ቤተሰቡ እንደፈለገ ዓመት ሙሉ ይዋኛል። የአባልነት ካርድ ያልተገዛለት ጎረምሳ ደግሞ ማንንም አይለምንም፤ በአጥር ሾልኮ ይገባል። ከተነቃበት ልብሶቹን ሰብስቦ፣ በገባበት አጥር እየሮጠ ይወጣል። ማምለጥ ካልቻለ ይያዝና በአብዮት ጥበቃ የጀርመን ሞተር ላይ እንደ ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ምርኮኛ ራቁቱን ተቀምጦ፣ ወደ አብዮት ጥበቃ ይገባል። ከዚያ እየተሳቀበት ራቁቱን ይጠበጠባል። አብዮት ጥበቃ ውስጥ ደርዘን የሚሆኑ የአለንጋ ዓይነቶች አሉ። እንደአለንጋ የማትቆጠረዋ፣ ቀጭኗ የበግ ጉማሬ ናት። የመጨረሻ ወፍራሙ ደግሙ መሬት ውስጥ የሚቀበረው የስልክ ኬብል። ስም ደግሞ አላቸው፤ ዘነበች፣ አዘነጋሽ፣ ገስጥ፣ መዝምዜ፣ …..እያለ ይቀጥላል። ከመዋኛ ቦታ የተያዘ ታዳጊ፣ በየትኛው አለንጋ እንደሚጠበጠብ ገራፊዎቹ ልምድ ስላላቸው በሙያቸው ባልገባም፤ እየተሳቀበት ራቁቱን እንደሚጠበጠብ ግን እርግጠኛ ነኝ።

ሞተር ላይ መታየት ያልመረጠ ደግሞ፣ እነሩት፣ እነየውብዳር፣ እነማርብል፣ እነገነት፣ እነኤልሳ እና እነናፍቆት ወደ ቲ-ሃውስ ሲገቡ በአጥሩ አሾልኮ ያያይ። የአጥሩ ስለታም ሽቦዎችና እሾኮች ጆሮውን፣ ትከሻውንና ጸጉሩን ቢጨመድዱትም ግድ የለውም። ከዚያም ወደ ልብስ መቀየሪያ ሲሄዱ በዓይኑ ይከተላል። Life Saver ሆነው የሚያገለግሉትን ጋሼ ዳምጤን ማየቱ አይቀርም። ከዚያም በዋና ልብስና በዋና መነጽር ሆነው ከመቀየሪያው ሲወጡ ያያል። ምራቁን እየዋጠ “ዋው!” ይላል። መዋኛው ዙሪያ ካሉት ግልጽ ሻወሮች ከአንዱ ገላቸውን ተለቃልቀው፣ ወደ መዋኛው ተገልብጠው ሲገቡ ያያል።

“ማየት አልበዛም?” እንዳትል። መጨረሻ ላይ ጉዱን ታያለህ።

ከጥልቁ ውኃው ወጣ ሲሉ፣ ረጃጅም ጸጉራቸው ጀርባቸው ላይ ለሽ ብሎ ያያል። በሚያማምሩት እጆቻቸው መነጽሮቻቸውን ከአይኖቻቸው ላይ አንስተው፣ ፊታቸው ላይ ያለውን ውኃ ሲጠርጉት ያያል። ውኃው ውስጥ ሲምቦጫረቁና ሲጫወቱ አይቶ ከጠገበ በኋላ፤ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል። ማታ ላይ፣ በሰፈሩ በሚደረጉት የተረት፣ እንቆቅልሽና ዜናዎች መድረክ ላይ፤ እነሩት፣ እነየውብዳር፣ እነማርብል፣ እነገነት፣ እነኤልሳ እና እነናፍቆት እንዴት ተገለባብጠውና ውኃውን ሃምሳ ቦታ ተርክከው እንደገቡ ይናገራል። የመነጽራቸው ቀለም፣ የዋና ሙታንታቸው ዲዛይን እና ምን ይባባሉ እንደነበር ሁሉ አትቀረውም። እየሳቁ “ሃይ!” እንዳሉት ሁሉ ጨምሮ ያወራል። የአጥሩ ስለታም ሽቦዎችና እሾኮች ጆሮውን፣ ትከሻውንና ጸጉሩን ጨምድደውት ይሰቃይና እንባውን ባራቱም ማእዘን እያራገፈ “ወይኔ እማዬ የዛሬን ብቻ!” እያለ ያነባ እንደነበር አያወራም። እሱ ክልክል ነው፤ ለዜና አይመችም።

አንዳንዱ ደግሞ የቲ-ሃውስን መዋኛ አይለማመጥም። ምን በወጣው ‘የጭቁን ዋና’ እያለለት! …..ከፋብሪካው ጀርባ ካለው ከአዋሽ ወንዝ ተመንትፎ ከመጣው ቀጭንና ረጅም መስመር የመሰለ ውኃ ውስጥ ይገባል። “እድሜ ለጭቁን ዋና!” እያለ የዋና ሱሱን ከዚያ ይወጣል። ከቲ-ሃውስ ራቅ ያለ አካባቢ ያሉት ወደ ቲ-ሃውስ ጭራሹኑ አይመጡም። ትልላቅ ኩሬ አለላቸው። 2ኛ ኩሬ፣ 5ተኛ ኩሬ፣ 7ተኛ ኩሬ፣ 9ነኛ ኩሬ፣ 10ኛ ኩሬ …..ኩሬ በኩሬ የሆነ ቀዬ ነው። ልብስ እያወለቁ ዘሎ መግባት ነው። ካርድ የሚጠይቅ የለም። 18 ብር አምጡ የለም። ሞተር ብስክሌት ላይ ራቁት መቀመጥ የለም። ግን፣ ቤት ሲገቡ አንድ ነገር አለ─ዱላ።  ወላጆች ኩሬ ዋኝቶ የመጣ ልጅ ያውቃሉ─አመዳም ነው። “አትዋኝ ያልኩህ ኩሬ ውስጥ ዋኝተህ መጣህልኝ! በኋላ ቢሊሃርዚያህን ስትሸምት እኔ ሆስፒታል በመመላለስ መከራዬን አላይም!” ቷ! በጥፊ። ልጆችም ምክንያት አያጡም። “አስተማሪያችን ናቸው፣ የቤት ሥራ ነው ዋኙ!” ያሉን። “ሃገራችሁን አንድ ቀን በዋና ትወክላላችሁ!”

ዳግም ወንጂ ለመወለድ የሚያስመኘው አንዱ፤ አዲስ አመት ሲመጣ ይካሄድ የነበረው የሙዚቃ ማርሽ ትርኢት ነው። በየሰፈሩ ከሚገኙት ሱቆች ትላልቅ የሲጋራ ካርቶኖች ይሰበሰቡና፤ በመቀስ እየተቆረጡና በስቴፕለር እየተሰፉ፣ ጠማማና ወልጋዳ ኮፍያ ይሰራባቸዋል። ያረጁ የከሰል ማንደጃዎችና አሮጌ ትላልቅ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ ከያንዳንዱ ታዳጊ ወጣት ቤት በግድ ይመጣሉ። በቁመት እየተሰለፉ የሙዚቃ ባንዱ ልምምድ ይጀመራል። የበዓሉ ቀን፣ በየሰፈሩ ትርኢት ማሳየት ይቀጥላል። እናቶችም፣ የነዛን አሮጌ የከሰል ማንደጃዎቻቸውንና ጎድጓዳ ሳህኖቻቸውን ጉዳይ የደረሱበት እለት፣ ምድረ ታዳጊ ጉዱ ነው። ታፋው በቁንጥጫ ሲለበለብና አናቱ በማመሲያ ሲቀወር፤ “ጅቦ ነው አምጣ ያለኝ! …..እትዬ እከሌ ድረሱልኝ! ወይኔ ተቃጠልኩኝ!” ይላል። ይህ በየመንደሩ ያለው ነው።

ዋናው የወንጂ ሙዚቃ ባንድ (እነ ለማ ድማሙ፣ በኋላ በኢትዮጵያ ደረጃ ሙዚቃ አቀናባሪና የቻቺ ታደሰን የእርዳታ ሥራ በኦርጋኒስትነት ያጅብ የነበረ፣ ነፍሱን እግዚአብሄር ይማረው፣ ሳይጠገብ ነው ያለፈው፣ እነሱ ያሉበት) በወንጂ ዋና፣ ዋና መንገዶች ላይ እየተዘዋወረ የማርሽ ሙዚቃዎችን ያሰማል። ከናዝሬት የአጼ ገላውዲዎ (ዛሬ፣ አዋስ) ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባንድም አንዱ ወንጂን አድማቂ ነበር። ባንዶቹ ያንን የመንገድ ላይ የሙዚቃ ትርኢት አሳይተው እንደሄዱ፤ የየሰፈሩ ታዳጊዎች፣ አጥር እየሰበሩ ዱላ ማሽከርከር ይጀምራሉ። “ልጅህን ያዝልኝ። አጥሬን እንደ ጉማሬ ሙልጭ አድርጎ ፈጀው” የሚባል ስሞታ ይቀጥላል።

የሰራተኛው መኖሪያ ሰፈሮችም በሚገባ የጸዱና አጥሮቹም አጫጭሮች ናቸው። ልዩ፣ ልዩ የአበባ ተክሎችንም በየደጁ ላይ የሚያስቀምጥ ሰራተኛ ብዙ ነው። በየቤቱ ፍራፍሬ እንደልብ ይታያል። ከፓፓያ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ሮማንና ዘይቱና (ነጩና ቀዩ) ቢያንስ አንዱን ያልተከለ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ጅምናስቲክ መስሪያ፣ ቦቻ መጫወቻና ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶች አላቸው። አካባቢውም Community Center ይባላል። እድሜው ለፊልም ያልደረሰ ልጅ ፊልም አይገባም። የሚታዩት ፊልሞችም በድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በኩል ተመርጠው የሚመጡ ነበሩ። ከተለያዩ ሃገራት የሚመጡ የሰርከስ ትርዒት ቡድኖች፣ ህብረተሰቡን በነጻ የሚያዝናኑት በነዚያ ሲኒማ ቤቶች ነው። ከአዲስ አበባ የሚመጡት ቴአትሮችም የሚስተናገዱት ከዚያ ነው። ከሃይማኖቶች ጋር የተያያዙ ጉባኤዎችና መንፈሳዊ ጭውውቶች አይቀሩም። ሃገራዊ፣ አካባቢያዊና ድርጅታዊ ስብሰባዎችም ይከናወኑባቸዋል።

‘ቲ-ሃውስ’ የሆላንዶች መዝናኛ ነበር። ጥቁር ሰው ከዚያ አይገባም ሲባል እሰማለሁ። አጼ ኃይለ ሥላሴ፣ የአውሮፓ ንጉሳውያን ቤተሰቦችን ይዘው ቲ-ሃውስ ሲመጡ፣ የሚነጠፍ Red Carpet አለ። ከሆላንድም ይሁን ከቤልጂየም ንጉሳዊያን ቤተሰቦች ጋር የሥራም ይሁን የግል ጉብኝት በወንጂ ሲያደርጉ፣ ቲ-ሃውስ አረፍ ብለው ሻይ ቡና ይላሉ። ዜናው ደግሞ ‘ዜና ሸንኮራ’ ይባል በነበረው ባለቀለምና ባለሁለት ቋንቋ (አማርኛና እንግሊዝኛ) ትልቅ ጋዜጣ ላይ፣ ቀልብ ከሚስቡ ትላልቅ ፎቶግራፎች ጋር ቦግ ብሎ ይወጣል። ጋዜጣው፣ በቁመቱ አዲስ ዘመንን ያክል ነበር። ዛሬ፣ በኮፒውተር እየተሰራ፣ በቢሮ ወረቀት እየተባዛ፣ በመከራ የተወሰነ ቦታ ላይ መሰራጨት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ስሙም ‘ዜና ወንጂሸዋ’ መሰለኝ። የዛሬ ስንትና ስንት ዓመት ‘ዜና ወንጂሸዋ’ ላይ ጽሁፍ እልክ ነበር። ሁለት ጊዜ ብቻ ወጥተው አይቻለሁ፤ ያውም ተቆራርጠው!

ቀድሞ በነበረው ጋዜጣ ላይ ከሚወጡት ቁምነገሮች መካከል፤ በወንጂ ሆስፒታል የሚወለዱ ሕጻናት ስም ዝርዝር፣ በአካባቢ ንጽህና የሚያሸንፉ ተሸላሚዎችና አካባቢያዊ ዜናዎች ይገኙበታል። የጋዜጣው ሪፖርተሮች የነበሩ እነ አቶ ድንቁ ስሜ፣ አቶ አያሌው ብርሃኔ እና አቶ አብይ፤ ጥሩ፣ ጥሩ ጽሁፎችን ይጽፉ ነበር። ከሰራተኛው መካከልም፣ የግጥምና የሥነ-ጽሁፍ ዝንባሌ የነበራቸው ይሳተፉበት ነበር። ይህንን ሁሉ ታሪክ ከድርጅቱ ቤተ─መጽሐፍት የተከማቹትን የድሮ ወረቀቶችን አንብቤ ነው የተረዳሁት። እናም ከስንት ዓመት በኋላ ለማስታወስ የሞከርኩትን ነው የጻፍኩት።

ይህ ሁሉ ታሪክ እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑት፣ ሁለት የስኳር ፋብሪካዎች ናቸው። የሆላንድ ካምፓኒ በሆነው ኤችቪኤ ኢንተርናሽናል፣ የዛሬ ስልሳ ዓመት ገደማ ነበር የተተከሉት። በሚቀጥለው ዓመት፣ ሁለቱም ፋብሪካዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፈርሰው ስለሚቀበሩ፣ ከላይ ልገልጸው የሞከርኩትን ታሪክ ወንጂ ላይ ዳግም አናይም። ወንጂ የተወለዳችሁ ወይም ያደጋችሁ በሙሉ እርማችሁን ከወዲሁ አውጡ፤ ከሚቀጥለው ዓመት በኋላ “የትውልዳችን መንደር” የምትሉት ቦታ (ያለ ሁለቱ ስኳር ፋብሪካዎች) Ghost City ይሆናል። እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ፣ ለዘመናት ባሕላቸውን ጠብቀው በአካባቢው በሰላም ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በኃይል ተፈናቅለው፣ በመቃብራቸው ላይ ነው እነዚህ ሁለት የስኳር ፋብሪካዎች የታነጹት። ዛሬ፣ ወይ ለቀድሞዎቹ ማኅበረሰብ አልሆነ ወይ አዲስ ለተፈጠረው፣ ሁለቱም ማኅበረሰብ ተጎጅ ሆኑ። የሁለት ትውልድ የአናኗር ዘይቤ እንዳይቀጥል ተፈረደ፤ አንዱ ባሕላዊ አንዱ ዘመናዊ። …..ሰንሰለቱ ተበጠሰ።

የማኅበረስብ ጉዳይ ላይ ወይም ይህን ከመሰለው መስክ ጋር በሚጎዳኝ መስክ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን፣ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ዝም ብለው ማየታቸውም ሌላው አሳዛኝ ክስተት ሆኖ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል። በተለይ ደግሞ በአካባቢው ተወልደው ወይም አድገው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሱ ምሁራንና የፖለቲካ ሰዎች ውስጥ፤ አንዳቸውም እንኳ ድምጻቸውን ለማሰማት አለመሞከራቸው ትዝብት ነው። “አይ ወንጂ! …..ያለው ማኅበራዊ ኑሮ’ኮ!” ማለት ብቻ ዋጋ የለውም። እሱማ አይን እያየ ሊቀበር ነው። ኳስ ሜዳዎቹ፣ አበባዎቹ፣ ዛፎቹ፣ ሳሮቹ፣ ሰፈሮቹ፣ የነሩት፣ የውብዳር፣ ማርብል፣ ገነት፣ ኤልሳ እና ናፍቆት መንደር፤ ተረት ሆነው ሊቀሩ ጉዟችውን ጀምረዋል። ከዓመት በኋላም “ሽቦ ግቢ እንገናኝ” የለም።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 31, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.