“መቼ ይሆን የምናርፈው?”:

ቀን፡ ሐምሌ 15፣ 2003 ዓም
የኦጋዴን ረሃብና ጭፍጨፋ
ላለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ላይ የተካሄደው ክህደትና ፖለቲካዊ ሸፍጥ ያደረሰው ማህበራዊና ሰብዓዊ ቀውስ ሞልቶ ፈሷል፡፡ ዜጎች ደረጃ ወጥቶላቸው ይረገጣሉ፤የሁላችንም አገር ለከሃዲዎችና ላገልጋዮቻቸው ገነት፣ ለሌሎች ገሃነብ ተደርጋ የስቃይና የመከራ ምድር ሆናለች፡፡ አቶ መለስ ፖለቲካቸውና ፖሊሲዎቻቸው ሁሉ አገርና ህዝብን አዘቅት እያወረደ ለመሆኑ ማስረጃ የሚደረደርበት ወቅት አልፏል፡፡ አሁን ወቅቱ አቶ መለስና በውሸት ላይ የተመሰረተውን አገዛዛቸውን ለመገላገል የምንተጋበትና በተጓዳኝ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመስረት የምንረባረብበት ወቅት ነው።

የአቶ መለስ አገዛዝ ልዩ መገለጫ ውሸት፣ በውሸት ላይ የተመረኮዘ ባዶ ሪፖርትና የወረቀት ላይ እድገት እንደሆነ ዓለምዓቀፍ ተቋማትና የሚያውቋቸው ሁሉ እየመሰከሩ ነው፡፡ ከማንም በላይ የችግሩ ሰለባ የሆነው እኛ ማረጋገጫ ነን፤ይፋ የወጣው ድርቅና ጠኔም ምስክር ነው::

የጋራ ንቅናቄያችን ባገራችን ረሃብ እያሰቃያቸው ላሉት ወገኖቻችን ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ የሚያደርገው የአቶ መለስን አገዛዝ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በኦጋዴን ህዝብ ላይ በዝግ የተፈፀመው ጭፍጨፋና ከቦታ ቦታ እንዳይዛወሩ ተከበው በቁም ጠኔ ያለቁ ንፁሃን ወንድሞቻችን ጉዳይ የህሊና ረፍት የሚነሳ በመሆኑ የሁሉም ዜጎች ትብብር እንደሚያስፈልግ ለማሳሰብ ይህንን የጥሪ መግለጫ አውጥተናል፡፡

አንድ ዕድሜያቸውን በውሸት የጨረሱ አዛውንት ነበሩ። ከውሸታቸው ብዛት የተጠሉና የተናቁ ከመሆናቸው በላይ ሰው ሁሉ ስለሚሸሻቸው ቤተሰቦቻቸው ያፍሩባቸ ነበር። እኚህ አዛውንት በሚሰሩበት መስሪያ ቤትም ወሬ ፈጥረው በማጣላት ይታወቃሉ። ቤተዘመድ ያፋጃሉ፤ ጎረቤት ዱላ ያማዝዛሉ፤ ትዳር ያፈርሳሉ፡፡ እሳቸው የለኮሱት ፀብ መዘዙ ሁሉን ስለሚያዳርስ በተግባራቸው የተማረሩ ሁሉ “ከዚህ ሽማግሌ እንዴት እንገላገል ይሆን” እያሉ የመገላገያቸውን ቀን ሲጠባበቁ አንድ ቀን አዛውንቱ በሰው መገደላቸው ተሰማ።

በአዛውንቱ ሞት የደስታ መግለጫ ተበተነ። ሁሉም “ተገላገልን” ተባባሉ። በሩቅ ያሉ በአዛውንቱ ላይ ካላቸው ጥላቻ ብዛት “አርቃችሁ ቅበሩት” የሚል መልዕክት አስተላለፉ። ሁሉም ደስታውን እየገለፀ የቀብር ስነስርዓት ደረሰ። በቀብር ስነስርዓቱ ላይ አንድ ችግር ተፈጠረ። የአዛውንቱን የህይወት ታሪክ የሚያዘጋጅና የሚያነብ ዘመድም ሆነ ጎረቤት ጠፋ። “አዛውንቱ በህይወት ዘመናቸው የፈፀሙት ምን መልካም ታሪክ አላቸው?” በማለት ጎረቤቶቻቸው ሲሳለቁ፣ የቤተሰቡን ችግር የተረዱ አንድ ቄስ “እኔ አስቀድሜ አዘጋጅቻለሁ፣ እኔው አነበዋለሁ” አሉና መፍትሄ ተገኘ።

የውሸታሙ አዛውንት አንድ መስመር የህይወት ታሪክ “አቶ እገሌ ሞቱ፣ ቤተሰቦቻቸውም አረፉ፣ እኛም አረፍን፣ እሳቸውም አረፉ’’ የሚል ስላቅ ሆነ። ቄሱ አስቀድመው ያዘጋጁት የአዛውንቱ የሕይወት ታሪክ ቀብራቸው ከተከናወነ በዃላ የመጥፎ ሰዎች መጨረሻ የሚገለፅበት መዘባበቻ ሆነ።

አቶ መለስ የበረሃውን ትግል ከተቀላቀሉ ጀምሮ የሚታወቁት በውሸታምነታቸው ነው።የቅርብ ባልደረባቸው የነበሩት አቶ ገ/መድህን ያዬህ የአቶ መለስን ውሸታምነት ሲገልፁ “መለስ ድንጋይ አንስቶ ዳቦ ነው ብሎ ከተናገረ ድንጋዩን ዳቦ ያደርገዋል’’ በማለት ነበር። የትግል ባልደረቦቻቸው ምስክርነትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት ሃያ ዓመታት በተግባር ያረጋገጡት ነገር ቢኖር አቶ መለስ የውሸት አባት መሆናቸውን ነው።

አዎ! በውሸትና በሕዝባዊ ትግል ውስጥ በተቀነባበረ ስውር ደባ የበርካቶች ህይወት ተገበረ።ህዝባዊ ታጋዮችና አታጋዮች ሃሰተኛ ምላስ ባለው መሰሪ ፖለቲከኛ ተበልተው ትግሉ፣ የትግሉ ሰማዕታትና የትግሉ ዓላማ ሙት ሆነ። በዚሁ ሳቢያ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በሀፍረት አለንጋ እንዲገረፉ፣ ማንነታቸው እንዲደበዝዝና አገራዊ ማንነታቸ እንዲጠፋ ሆነ። ይህም አልበቃ ብሎ ኢትዮጵያን ንብረቷን በመዝረፍና በማዘረፍ ህዝቦቿ ልጅ ልጆቻቸው ሳይቀር በባርነት ተላልፈው እንዲሰጡ የተወሰነባቸው ስለመሆኑ ጥርጥር የለንም።

ዛሬ ባገራችን በአቶ መለስ የሚመራው አገዛዝ እስካሁንም በሥልጣን የቆየው እንዳሻው የአገራችንን ህዝብና ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ እያወናበደ ሲሆን፣ በስልጣን በቆየበት ሃያ ዓመታት ያተረፍነው ነገር ቢኖር ውርደት፣ የሀብት ዝርፊያ፣ የርስ በርስ ግጭት፣ ድህነት፣ በዘር ላይ የተመሰረተ የጥላቻ ፖለቲካ ሲሆን በተለይም ሲሸፋፈን ቆይቶ ይፋ የሆነው የወገኖቻችን እጅግ አሳሳቢ የርሃብ አደጋ በየዘርፉ ካጋጠሙት ቀውሶች ጋር ተዳምሮ የአቶ መለስ የሃያ ዓመት ውሸትን መሰረት ያደረገ አገዛዝ ድምር ውጤት ውድቀት መሆኑን ያረጋገጠ ሆኗል።በተጨማሪም በስውርና በግልፅ የሚካሄውን ኢትዮጵያን የመበታተንና ህዝቦቿን የማዋረዱ ተግባር ልክና ገደቡ አልፎ የማንቋቋመው ደረጃ ላይ መድረሱን ያመላክታል። ታዲያ መቼ ነው “እኛም አረፍን የምንለው?”
አገራችን ያለችበት ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየከረረ መሄዱ በእጅጉ አሳሳቢ በመሆኑና የተሸሸገውን ቁጥር ሳይጨምር ራሱ ህወሃት/ኢህአዴግ እንዳመነው ከ5ሚሊዮን ህዝብ በላይ ለከፋ ርሃብ መጋለጡ አስደንጋጭና አሳፋሪ መርዶ ሆኖብናል። ችግሩ የስርዓቱ በሽታ የወለደው መሆኑ ደግሞ ውስጣችንን በጅጉ ያቃጥለዋል፤ ሀዘናችንንም ድርብ ያደርገዋል።ለዚህም ነው ዛሬ ሁሉም ወገኖች ለፍትህና ለርትዕ መነሳት አለባቸው በማለት ይህንን ጥሪ ለማስተላለፍ የወሰነው።

በእፉኚት እባብ በሚመሰለው የመለስ ፖለቲካ የተጠመቁ ካድሬዎች ለመለስ ኃይል ሆነው ብሄራዊ ማንነታችንን፣ ብሄራዊ ጥቅማችንን፣ ብሄራዊ አንድነታችንንና ጠላትን የሚያስደነግጠው አብሮነታችን ተገፏል። ሀብታችን ተዘርፏል። እየተዘረፈም ነው። ቁም ነገር በሌለው ጦርነት ተማግደናል። በኢትዮጵያውያን የመከላከያ ኃይሎች ደም የሚገኘው ዶላርና የፖለቲካ ቁማር ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተማገድንም ነው። በብሄር ፖለቲካ መርዝ የተለወሰው የመለስ አገዛዝ እርስ በእርስ ወንድማማች ህዝቦችን አጫርሷል፤ እያጨረሰም ነው ። በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የጅምላ ጭፍጨፋ ተከናውኗል። ምን ቀረ?

በጋምቤላ፣ በደቡብ ክልል፣ በኦጋዴን፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈፀመው ጭፍጨፋ አልበቃ ብሎ ወገኖቻችን በመለስ የፖሊሲ ስህተት በከፋ ድርቅ እየተገረፉ፣ መሬታቸው ግን ለባዕዳን እየተቸበቸበ ነው። ለመለስ ከኢትዮጵያዊያን ይልቅ የህንድና የቻይና ዜጎች በልጠዋል። የቱርክና የጅቡቲ ከበርቴዎች ክብር ተሰጥቷቸዋል። በኑሮ ውድነት ድፍን የአገራችን ህዝብ ኑሮ ተናግቷል። ጥቂቶች እየበሉ አብዛኞች ተርበዋል። በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ ያልቻሉ ህፃናት በትምህርት ገበታቸው ላይ እየወደቁ ነው።

ኢኮኖሚው በተወሰኑ ቡድኖች ቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጎ አብዛኞች ራሳቸውንና ልጅ ልጆቻቸውን ለባርነት አሳልፈው እንዲሰጡ እየተደረገ ነው። ጥቂቶች እየተንደላቀቁ አብዛኞች የበይ ተመልካች እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ስቃይና መከራ እየጠነከረ፣ እየከፋና እየከረረ ያለበት ፈታኝ ወቅት ላይ ነን። በመሆኑም በየትኛውም ደረጃና አይነት የፖለቲካ ትግል የተሰማራችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣ በዋናነት ባስቀመጥነው የወቅቱ የረሃብ አጀንዳና የኦጋዴን ወንድሞቻችን ላይ የደረሰው የጅምላ ጭፍጨፋ ገሃድ እንዲወጣ ትብብራችሁን እንድታደርጉ እንጠይቃለን። በጥሪያችን መሰረት የሚፈጠረው መረባረብ የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ጅማሮ የሚያመለክት እንደሚሆንም አንጠራጠርም።

የሕዝብ አንደበትና ተሟጋች የሆኑ የነፃ ፕሬስ ውጤቶችን ወደ መቃብር በማውረድ፣ ነፃ ጋዜጠኞችን በማሰቃየት፣ አገር ጥለው እንዲሰደዱ በማድረግ፣ በምትካቸው ህወሃት/ኢህአዴግ ሰራሽ ፕሬሶችና ቅምጥ ጋዜጠኞች ተወልደው የመለስን አገዛዝ በማቀንቀን በአገርና በህዝብ ላይ ክህደት እየፈፀሙ ይገኛሉ። ይህ ህዝብና አገር ላይ የሚፈፀም ክህደት የሚያከትምበትና የስርዓቱ መሪዎች ለፍርድ የሚቀርቡበት ጊዜ መቃረቡን በመረዳት ሳይመሽ በአርአያነት እንደሚጠቀሱት ጥቂት ፕሬሶችና ጋዜጠኞች የዜግነት ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለን እናምናለን።
አድር ባይ ብእርና ለጥቅም የተገዛ ጋዜጠኛነት እንዲያበቃ በጅምላ በተጨፈጨፉት፣ የረሃብ አለንጋ በሚገርፋቸው፣ በግፍ አገዛዝ በታሰሩትና በመለስ ስውር አጀንዳ እየፈራረሰችና እየተዘረፈች ባለችው አገራችን ስም ድምፃችንን እናሰማለን። ለልጅ ልጅ እንዲተላለፍ ታስቦ በመለስ ስውር አላማ ለኢትዮጵያ የተወጠነውን ሴራ በማክሸፍ አዲሲቷን ኢትዮጵያ በመመስረቱ ትግል ውስጥ የመሪነት ሚና የምትጫወቱበት ወቅት ላይ ናችሁና!
የኪነት ባለሙያዎች የህዝብ ስቃይና የአገር ውድቀት ከሚያስጨንቃቸው በላይ ህሊናቸውንና ስብዕናቸውን በንዋይ ሸጠው፣ ለሆዳቸው ተገዝተው ለመለስ ዜናዊ በመርዝ የተለወሰ ፖለቲካ በማጎብደድ ይቅር ሊባል የማይችል የአጫፋሪነት ተግባር ላይ ተሰልፈዋል።ይህ ሁሉ አልበቃ ብሏቸው አቶ መለስን ሸላሚና አመስጋኝ ሆነው ታማኝ አሽከርነታቸውን ሲያረጋግጡ ከማየት በላይ የሚያሳዝን የሞራል ግሽበት ይኖራል ብለን አናስብም። ውስን የኪነት ባለሙያዎችና ፀሐፍቶች ከሚያበረክቱት የትግል ስሜት የተሞላ ተግባር ውጪ አብዛኞች አገርና ህዝብ ሊረሳው በማይችለው የተጠያቂነት ጥፋት ውስጥ ተዘፍቀዋልና በጊዜ ህዝባዊነታቸውን እንዲያሳዩ እንመክራለን። በሌሎች አገሮች የኪነት ባለሙያዎችና ፀሐፍቶች እንደሚያደርጉት በግፍ ለተጨፈጨፉ፣ በረሃብ ለሚረግፉ፣ በነፃነት ጥማት ለሚሰቃዩ፣ ፍትህ ለተራቡ አንደበት እንዲሆኑ እንማፀናለን።

የአገራችን ምሁራኖችም ብትሆኑ ዝምታን መምረጣችሁ ከተጠያቂነት አያድናችሁምና የዜግነት ድርሻቸውን እየተወጡ ካሉት በጣት የሚቆጠሩ ባልደረቦቻችሁ ባልተናነሰ አገራችን እያመራችበት ካለችበት የውድቀትና የአፈና ስርዓት ነፃ የምትወጣበትን መንገድ ማፈላለግ ግዴታችሁ መሆኑን አበክረን እናሳስባለን። እናንተም እያንዳንዱ ዜጋ ነፃ የሚሆንባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ ስትመሠረት ተሳታፊ ሁኑ እንላለን።

የአገራችን ወጣቶች ያላችሁበት የፈተና ጊዜ ያለፈቃዳችሁ የተጫነባችሁ፣ የችግሩ ግንባር ቀደም ተጠቂዎች ብትሆኑም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ የምትጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነውና እንደወትሮው ሁሉ ወደፊት በምትረከቡዋት አገራችን ላይ እየተከናወነ ያለውን ስውርና ገሃድ ሴራ ተቃወሙ። በወገኖቻችሁ ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ አውግዙ።

የሐይማኖት አባቶችና መሪዎች እንደ እምነታችሁ የሚጠበቅባችሁን ከማድረግ ያገዳችሁን ምክንያት መዘርዘሩ ባያስፈልገንም ዝምታን መምረጣችሁ በምታመልኩትና በምታገለግሉት አምላክ ከቶውንም የሚወደድ አንዳልሆነ በዚህ አጋጣሚ እንጠቁማለን።

የዓለም መንግስታት፣ የአፍሪካ ህብረት አገሮች፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና የፍትህ ተሟጋቾች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ሁሉ አቀፍ የመገናኛ አውታሮች ወዘተ በኦጋዴን ንፁሃን ዜጎች ላይ በአሸባሪዎች ስም የተፈፀመው የጅምላ ጭፍጨፋ ገሀድ እንዲወጣ የበኩላችሁን ታደርጉ ዘንድ እናሳስባለን። በተለይም ለጋሽ አገራት ለድሃ ህዝቦች የምትሰጡት ርዳታ ድሃ ህዝቦችን በጅምላ ለመጨፍጨፍ ተግባር እየዋለ፣ እየተዘረፈ መሆኑን እያወቃችሁ፣በራሳችሁ አጣሪዎች ሪፖርት እየቀረበላችሁ ዝምታን የመረጣችሁበት አግባብ የተዛባ ነውና ለኦጋዴን ህዝብ ጩኸት ጆሮ ስጡ። በኦጋዴን የተፈፀመው የጅምላ ጭፍጨፋ በገለልተኛ አካላት እንዲጣራ ጫና በማድረግ ተባበሩ።

የመግለጫችን አንኳር ጉዳይ የወቅቱ አሳሳቢ ድርቅና የኦጋዴን ጉዳይ እንመለስ፤በ2006-2007 በኦጋዴን የተፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ አስመልክቶ በርካታ መረጃ አሰባስበናል። በወቅቱ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ታጣቂዎችን ለመደምሰስ በሚል ህወሃት/ኢህአዴግ መራሹ ብረት አንጋች ሃይል የወሰደው አስከፊና ሰብአዊነት የጎደለው ጭፍጨፋ በጥቂቱ ይህን ይመስላል።
1. በሶማሌ ክልል ተሰማርተው የነበሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የዓለም አቀፉን ቀይ መስቀልን ጨምሮ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደረገ። ውሳኔው በግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ በኩል ቅሬታ ቢያስነሳም አቶ መለስ አቋሜን አልቀይርም አሉ።
2. በአካባቢው የሚፈፀመውን ኢሰብአዊ ድርጊት የሚታዘቡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከአባቢው ከወጡ በኋላ ኦጋዴን በታጠቁ ሃይሎችና በከባድ መሳሪያ እንዲከበብ ተደረገ።ቀደም ሲል አሸባሪን ለመከላከል በሚል በአካባቢው በተተከሉ የርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች አማካይነት የኦጋዴን አርብቶ አደር ነዋሪዎች መስቀለኛ ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ።
3. ኦጋዴን ሙሉ በሙሉ ከተከበበ በኋላ ወደ ጅቡቲ፣ኬንያና ሶማሊያ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ተዘጋ። በተመሳሳይ ከጅጅጋ የሚወጣና ወደ ጅጅጋ የሚገባ ማንኛውም ዓይነት ሸቀጥ እንዳይንቀሳቀስ ተደረገ። በጅጅጋ የሸቀጦች ዋጋ ናረ። ስኳርና ፓስታ በኮንትሮባንድ እንኳን የማይገኙበት ሁኔታ ተፈጠረ፤ ኑሮም ጋለ። ነዋሪዎች ስጋት ላይ ወደቁ።ይህንን የሚያደርጉት ወንበዴዎች ናቸው በሚል የመለስ ካድሬዎች ቅስቀሳ አካሄዱ።
4. ለወራት ያህል በመለስ ታማኞች ትዕዛዝ ሰጪነት የተከበቡት የኦጋዴኖች በረሃብ ተጠበሱ። ችግሩ ሲጠናባቸው ሽማግሌ በመላክ “በረሃብ ማለቃችን ነው። እኛ ንፁሃን ዜጎች ነን። ህፃናት እየተጎዱ፣ ከብቶቻችን እያለቁ ነው’’ በማለት ከከበባው ለመውጣት ጥያቄ ቢያቀርቡም ትእዛዝ ከተላለፈላቸው የጦር አዛዦች ያገኙት መልስ ጥይት ነበር።በተፈጥሮዋቸው አንድ ቀበሌ መኖር የማይችሉ አርብቶ አደሮች ከቦታ ቦታ መዘዋወር ተከልክለው ለአራትና አምስት ዓመታት እንዴት ኖሩ? ምን ያህልስ ሰብአዊ ቀውስ ደረሰ?
ከወራት የስቃይ ኑሮ በኋላ የመጨረሻው የፍርድ ቀን ደርሶ በኦጋዴን የጅምላ ጭፍጨፋ ተካሄደ። ንፁሃን ጉድጓድ ተምሶ በጅምላ እንዲቀበሩ ተደረገ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መለስ ስለ ኦጋዴን ሲነሳ ያማቸው ጀመር። ከዋናው የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ጋር የሰላም ስምምነት አድርጌያለሁ ቢሉም አካባቢውን ገለልተኛ ወገኖች ገብተው እንዲመለከቱት ፈቅደው አያውቁም። ሰሞኑን የስዊድን ጋዜጠኞች ላይ የተወሰደው ርምጃም የዚሁ ሚስጥር ይወጣብኛል ፍርሃቻ አካል ስለመሆኑ ጥርጥር የለንም።

ኦጋዴን በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ተድበስብሶ ቢከርምም ዛሬ በሶማሊያ የተከሰተውን አስፈሪ ርሃብ ተከትሎ ይፋ መሆን ጀምሯል። ድርጅታችን በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ክልል፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተፈፀሙትን ጭፍጨፋዎች በመቃወም እንዳደረገው ሁሉ በኦጋዴን የተፈፀመው ጭፍጨፋ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ነው። የኦጋዴን ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ በመሆኑ ይህ መግለጫ የሚደርሳችሁ አካላት በሙሉ ድርጊቱን በመቃወም አግባብ ያለው ተፅዕኖ በማድረግ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ መድረክ ትግላችሁን እንድትቀጥሉ አጥብቀን እናሳስባለን።

በኦሮሚያ፣በአማራ፣በትግራይ፣በደቡብ፣በአፋር፣በድሬዳዋ፣በኦጋዴንወዘተየተከሰተው አስደንጋጭ ረሃብ ይፋ የሆነው መለስ አገራችንን ‹‹ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች አሳድጋለሁ፣ከንግዲህ የእህል እጥረት አያሰጋንም፣የእህል እጥረት ካጋጠመንም ከኪሳችን አውጥተን እንገዛለን›› በማለት ፀሐይ የሞቀው ውሸት ከዋሹ በወራት አድሜ ውስጥ መሆኑ፣የአገራችን ኢኮኖሚ በሁለት አኻዝ አድጓል፣ባገሪቱ የሚመረተው ሰብል በሚሊዮን ኩንታል ጨምሯል ወዘተ የሚል የፈጠራ ሪፖርት በተደጋጋሚ በሚቀርብበት ወቅት ላይ መሆኑ፣የመለስን በቅጥፈት ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ከማሳየቱም በላይ ወደፊትም መሻሻል ሊታይ እንደማይችል ያረጋገጠ ክስተት ሆኖ አግኝተነዋል።ስለዚህም “መለስም አረፉ፣ እኛም አረፍን፣ የሚነግዱበት ህዝብም አረፈ” የምንልበትን ጊዜ በማፋጠን አዲሲቷን ኢትዮጵያ በጋራ የምንመሰርትበትን መንገድ እንድናመቻች ከላይ ለዘረዘርናቸው አካላትና ለመላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ወደ ፖለቲካው መስመር ከገቡ በኋላ በመተጣጠፍ፣ ነባር ፖለቲከኞችን በመብላት የህወሓት ፊት አውራሪ ለመሆን የበቁት መለስ፣የቀደመውን የትግል መስመር አስተው ኢትዮጵያን በመበታተን፣ፖለቲካዊ ፋይዳዋን በማመናመን፣የህዝቦቿን ክብር በሃፍረትና በድህነት በማዋረድ፣የቀደሙትን ሰማዕታትና የትግሉን ዓላማ ሙት ያደረጉ በመሆናቸው መለስና ግብርአበሮቻቸው ለተራቡት ህዝቦች የሚላከውን ርዳታ በአግባቡ ያደርሳሉ የሚል እምነት እንደሌለንም ከወዲሁ ለመግለፅ እንወዳለን።

ከትግል ራስን ማሸሽ ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ያራዝመዋል። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ በሌሎች ትግል ተጠቃሚ የመሆን አስተሳሰብ ቦታ የለውም። በነፃነት ውስጥ የሚፈጠሩ ዜጎች የሚኖሩባት፣ሁሉም ዜጎች ነፃ የሆኑባት አገር ለመመስረት ለሚቀርብ የትግል ጥሪ ምላሽ መስጠት ራስን ነፃ የማውጣት ያህል ነው!!

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
*******************************************************************************************************************
ለዚህ ደብዳቤ ምላሽም ሆነ ለተጨማሪ መረጃዳይሬክተሩን ለአቶ ኦባንግ ሜቶ (obang@solidaritymovement.org) በመጻፍ ወይም ድረገጻችንን (www.solidaritymovement.org) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 23, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.