“ሊበሏት የፈለጓትን …”፡ ኢህአዴግ “ደካማ” ብቻ ሳይሆን ወንጀለኛም ነው!

[PDF] ይህ ጽሁፍ “ከመለስ ካድሬዎች አንዱ ነኝ” የሚሉ የኢትዮሚድያ አንባቢ ለጻፉት “መልስ ለአንዳርጋቸው ፅጌ” ለሚለዉ ጽሁፍ የተጻፈ መልስ ወይም ግሳፄ ነው። በ“መልስ ለአንዳርጋቸው ፅጌ” ውስጥ የተገለጹት ሃሳቦች በተወሰነ ደረጃ/ተራ (structure) አልተቀመጡም፤ እኔ ግን ለአንባቢ አይን ይቀል ዘንድ በየአንቀጹ የተገለጹትን ሃሳቦች ተራ በተራ ቁጥር በመስጠት መልስ ለመስጠት ሞክሬአለሁ። ቦታ ስለማይበቃ የሳቸውን ሃሳብ እንዳለ አልገለበጥኩትም፤ ስለዚህ የኔን ጽሁፍ በደንብ ለመረዳት የሳቸውን ጽሁፍ አስቀድሞ፣ ወይም ጎን ለጎን አኑሮ ማንበቡ ሳይበጅ አይቀርም። በነገራችን ላይ፦ ለጽሁፉ መልስ ለመስጠት የተነሳሳሁት ኢትዮሚድያ ላይ ስላገኘሁት ብቻ እንዳው እርባና አግኝተውበት ይሆናል ብዬ ነበር። መልሴን የጻፍኩትም ለመጀመሪያ ጊዜ ጽሁፉን እያነበብኩት ነበር። ጊዜዬን በከንቱ እንዳባከንኩትም የተረዳሁትም ጽሁፉን ከጨረስኩት በኋላ ነው። ከጻፍኩት አልቀር ደግሞ የሚፈልግ ካለ ያንብብ ብዬ ነው ለድህረ-ገጾች የላኩት። ቀጥታ ወደ ጽሁፉ፦
“ሊበሏት የፈለጓትን ዥግራ ቆቅ ነች” ይሏታል፡ ኢህአዴግ “ደካማ” ብቻ ሳይሆን ወንጀለኛም ነው!

አቶ ካድሬ፦

ከጽሁፍዎት ጅማሬ እርስዎ ኢህአዴግን የመረጡት “የተሻለ” ፓርቲ እስኪመጣ እንደሆነ ሊያስረዱን ይሞክራሉ። እንግዲህ እግዜር ጸሎት አልመልስ ሲል ሳጥናኤልን ታቅፎ መቀመጥ ጽድቅ መሆኑ ነው?

እንዲያው ለነገሩ ነው እንጂ እኔ እርሶ የሚሉትን አምኜ አይደለም። ጽሁፎትን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያነበበ “ድንቄም! እኒህን ሰው ብሎ ደግሞ ‘የተሻለ’ ነገር አዋቂ!” ማለቱ የማይቀር ነገር ነው። እርስዎ እንዳሉን፣ ሲጀመርም ሲጨረስም የነፍሰ ገዳዩ መንግስት ካድሬ ነዎት እንጂ እንዲያው ስለ አገሪቱ ጨንቆዎት እንደማንኛዉም ተራ ዜጋ እውነትንና ላገር የሚበጅን ነገር የሚያፈላልጉ አይመስሉም። በጽሁፍዎ ግን ለማስመሰል የሚፈልጉት ያንን ነው። ምናልባት እንግዲህ አስቀድመዉ “ካድሬ ነኝ” ማለትዎ እና በጽሁፍዎም ዉስጥ እዚህም እዚያም ኢህአዴግን መዉቀስዎ “ግልጽ” እና “ምክናያታዊ (Objective)” ያስመስለኛል ብለዉ ገምተዉ ይሆናል። አዬ፣ ‘አንኳን ይቺ የዝንብም ጠንጋራ አታመልጠኝ’ አለ ያግሬ ሰው ሲተርት።

ደግሞ የኦባማን ጉዳይ እዚህ ጋር ምን አመጣው? ኦባማ ጥቁር ሰው እንኳን ፕሬዚዳንት ሊሆን ቀርቶ ስራ እንኳ ለማግኘት መከራ በሚያይበት ሃገር፤ የእስላም ስም ይዞ ይቅርና ተስላም ጋር ትንሽ ንክኪ ያለው ሰው በጥርጣሬ አይን በሚታይበት ሃገር ነው ፕሬዘዳንት ልሁን ብሎ የተነሳው። ገና ካነሳሱ በቆዳው ቀለም እና በስሙ ብቻ disadvantaged የሆነ ሰው ነው። ግንቦት 7 ደግሞ በህዝባቸው ዘንድ ተቀባይነታቸው ታላቅ በሆነ ሰዎች የተመሰረተ እና ሰገራ እንደ ነካው እንጨት ህዝብ የጠላዉንና የተጸየፈዉን መንግስት ሊታገል የተነሳ ድርጅት ነው። በኦባማ ተቃራኒ፤ ለርስዎና ለሥራዎ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ፤ ካነሳሱ advantaged የሆነ ድርጅት ነው። ለዚህና ለሌላም ምክንያቶች ነው እንደርሶ ካለ ኑሮው በካድሬነት ተጀምሮ ከሚያበቃ ሰው ጋር አሉባልታን ለመግጠም ሲሉ ጊዜያቸዉን ማባከን የማያስፈልጋቸዉ። የርሶ ብጤዎች ከየጉራንጉራቸው ድንጋይ ሲወረውሩ ከየት እንደመጣ ለማወቅ ያገር ልጅ የነ አንዳርጋቸዉን ማብራሪያ አይጠብቅም – ምንጩን ያውቀዋልና።

ደግሞም፤ በፖለቲካ ስራ ዉስጥ ሁሉም አሉባልታ እኮ ክፉ አይደለም። እንዳንዱን ወሬ እኮ ምን አልባት የግንቦት 7 ሰዎች እራሳቸው እናንተ ተቀባብላችሁ መዘመራችሁን እያዪ እንደ ድል እየቆጠሩት ይሆናል።

በርግጥም የርሶ ችግር ይገባኛል። የግንቦት 7 ስዎች ኢህአዴግ እና ተለጣፊ ትሎቹ ከሚያመርቱት አሉባልታ ጋር ፊት ለፊት አልገጥም ሲሉ የእርስዎ ስራ መታጣቱ ነው፤ ኢህአዴግም እንደለመደዉ ተቃዋሚዎችን በአሉባልታና በወቀሳ እየነረተ የፖለቲካውን ሜዳ manipulate የሚያደርግበትን ስልት ማጣቱ ነው። ቸገራችሁ እኮ! ድሮ ግዜ የወቀሳና የአሉባልታ ዉዥንብር አውርዳችሁበት አልሞት ያላችሁን ቡድን፤ ወይ ሰዎችን በጉቦ በመግዛት እና ክቡር ፍርድ ቤቶችን በማሾርሞጥ ቡድኑን ማስፈረስ፤ አልሆን ሲል መሪዎቹን ሰብስቦ እስር ቤት መስደድ ነበር ዘዴያችሁ። አሁን ግዜ ግን ሰዎቹ ራቁባችሁ! አልደረስ አሉ! መፍትሄው ምን ይሆን? የኦባማ ካምፔን እንደመሰረተው አይነት የግንቦት 7ን ወቀሳዎች እና መልክቶች “እንዲቋቋም” ብቻ የሚሰራ ቡድን ተመስርቶ ይሆን? አይገርመኝም! ይልቁንስ እጅግ በጣም ዘግይታችኋል፤ አጀማመራችሁም በጣም ደካማ ነው ባይ ነኝ – በተለይም ይህ ጽሁፍ የመጀመሪያው ዋና ስራ ከሆነ!

ለማንኛዉም፣ እስኪ በጽሁፍዎ ዉስት ያነሷቸውን ነገሮች እንያቸው፦

የግንቦት 7ን ህዝብን የማስተማር ግዴታ፦ እየተወጣው ነው! ያ “ጥራቱን ያልጠበቀ” ጋዜጣ የሚሰራዉም ያን ስራ ነው። ያንንም ስራ ደግሞ ለማስፋፋት እያቀደ እንዳለ ተገልጿል። ጠዋት ማታ የማንም ተራ ካድሬ የሚወረውራቸውን አሉባልታዎችና መሰረተ-ቢስ ወቀሳዎች ፊት ለፊት መዋጋት ግን ህዝቡን ማስተማርና ማንቃት ሳይሆን ጊዜን ማባከን ነው።

ስለ አቶ አማረ፦ የሰዉየዉን ለፕሬስ ነፃነት መታገል ወይም እንደሚታገሉ መናገር “ወያኔ” ከመሆን አለመሆናቸው ጋር ምን የሚያገናኘዉ ነገር አለ? አቶ መለስ እራሳቸው ለ”ነፃነት” ሲዋጉ የወጣትነት እድሜአቸዉን በጫካ አጥፍተዉት የለ እንዴ። አቶ አማረ ቀድሞ የኢህአዴግ አባል የነበሩና በነፃው ህትመት ስራ ለመሰማራት የለቀቁ ነጋዴ ናቸው። ይህ ሃጢያት የለበትም፤ ነገር ግን ስለ እርሳችዉና ሊያደርጓቸው ስለሚችሉት ዉሳኔዎች የሚያስተምረን ነገር አለ። ለአመታት ልክ እንደማንኛዉም ነፃ ህትመት፣ ምናልባትም በተሻለ መንገድ፣ ሂስ ሲያስፈልገው ሂስ፣ ዉዳሴም ሲያስፈልገው ዉዳሴን ለመንግስት ሰጥተዋል። (እና የነ አቶ ብርሃኑም ለሳቸዉ ያላቸው ክብር የመነጨዉ ከዛ አይነቱ ነገር ሳይሆን አይቀርም። ደግሞም አቶ ብርሃኑ በመልካምነቱ የታወቀ ነዉና አንዳንዴ “ለጅብም” ቢሆን benefit of the doubt ካልሰጠነዉ የሚል አናዳጅ ሰው ነው።) ለኢህአዴግ የሚሰጡት ወቀሳም ምናልባት “ከቤት ሰው” ከሚሰጠው ተለይቶ አይታይ ይሆናል። ኢህአዴጎች አካባቢ እራሳቸዉን “በመገምገም” እና “ሂስ በመስጠት” መቸም በጣም የታወቁ ናቸው። ከውጪ ሲመጣ ነው ችግሩ! ታዲያልህ፣ አቶ አማረ እንደዚያ “ነፃዉን” ህትመት ሲያገለግሉ ቆዩና፤ በ97 ነፃዉ ህትመት “ሞትኩ፣ ተወጋው፣ ተጠቃው…ድረሱልኝ፣ እሪ!” እያለ ሲጮህ ክድት አረጉታ! “ተቃዋሚ ያለሽ፤ የእዉነት ያለሽ አሁንስ ባይኔ መጣሽ!” ነገር ሆኖባቸዉ ያዥጎደጉዱብን ጀመር የክህደትን እና የሃሰት ዉንጀላን መዓት! “አይን” እኮ የምለው ኢህአዴግን (ብቻ) አይደለም። ንግድም አለ። ሁለቱንም አቻችሎ መሄድ ለንደሳቸው አይነት ሰው በጣም አስፈላጊ ነው። ለፕሬስ ህግ መታገል እና ከበረከት ስምዖን ጋር ግብ ግብ መግጠም (እርስዎ እንደሚሉት) እንደ ትልቅ የማስታወቂያ (marketing) ስራ ሊተረጎም ይችላል። ካልሆነም፣ ምናልባት ሰውየዉ ከልባቸው ከሆነ የሚታገሉት፣ እሱም ቢሆን “ወያኔ” ላለመሆናቸው በቂ መከላከያ አይደለም። “ወያኔ” የሳቸዉን አጋርነት በፈለገበት በዚያች አጨናናቂ ጊዜ እንደተገኙለት አይን ያለው እና በዚያ ሰሞን ጽሁፋቸውን ያነበበ ሁሉ ይረዳዋል። ስለዚህ ማንም ሰው ተነስቶ “ወያኔ” ናቸው ብሎ ቢወቅሳቸዉ ምን እንዳይኮን ነው?

ስለ ግንቦት ሰባት አሉባልታዎችን ፊት ለፊት አለመግጠም፦ ከላይ ያንብቡ። በተጨማሪም፡ – ግንቦት 7 እንቅስቃሴዎቹን ሁሉ አስቀደሞ አስቦና አወያይቶ የሚያደርግ ድርጅት ነው። አስፈላጊ መስሎ ሲታየዉ ለአሉባልታዎች መልስ እንደሚሰጥ አልጠራጠርም። ነገር ግን፣ አሉባልታዎች ማለቂያ የላቸውምና፣ ለያንዳንዱ ቁጭ ብሎ መልስ እየሰጠ ጊዜ ማባከን የለበትም። አንዳንድ አሉባልታዎች ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ጥቅም አላቸው! ለነገሩ የርስዎ ፅሁፍ፣ ግንቦት 7 “የኛ ፖለቲካ አላማ ከኢህአዴግ ፊት እርምጃዎችን ቀድሞ የሚሄድ ፖለቲካ ነው” ብሎ ያለውን እዉነታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው!

ግንቦት 7 እንደሚለው ኢህአዴግን እና ደጋፊዎቹን “እንቅልፍ ስላለመንሳቱ” የዘረዘሯቸው ምክንያቶች፦ በመሰረቱ፣ እንቅልፍ ባይነሳችሁ ኖሮ አርስዎ ይህንን ጽሁፍ ባልጻፉ ነበር። እስኪ ለማንኛዉም ግን “ማስረጃዎትን” እንመልከት፦

“መረጃዎ” ‘ግንቦት ሰባት እስካሁን እየሰራ ያለው ስራ በአሜሪካና በአውሮፓ ከሚደረጉት ስብሰባዎች ፈቀቅ ያለ አይደለም’ የሚልበት ምክንያት ድርጅቱ አብዛኛዉን ስራዉን የሚሰራው በህቡዕ ስለሆነ ነው – ካላወቁ።

በአዲስ አበባ ደግሞ ‘ጥራቱን ያልጠበቀው’ን የግንቦት 7 ልሳን በጉጉት የመጠበቁ ስሜት እየወረደ መሆኑን የተገነዘቡት ባዲስ አበባ ብብት ዉስጥ እንደ ቴርሞ ሜትር ያለ የጉጉት መለኪያ መሳሪያ አስገብተው መጠኑን ለክተው ነው? እንደዚያ ያለ ዘዴ ተጠቅመዉ ካልሆነ አናምኖትም! ምክንያቱም እርስዎ የኢህአዴግ ካድሬ ነኝ ብለዉናል። የኢህአዴግ ካድሬዎች ደግሞ የሚታወቁበት ትልቁ ገድላቸው፣ እንኳን የህገ ወጡን ግንቦት 7 ይቅርና የህጋዊ ፓርቲዎች ደጋፊዎች ናቸው የሚሏቸዉን ሰዎች ስም እየሰበሰቡ ማሳሰርና ማሳረድ ነው! እና እንደዚ ላሉ ሰው-በላዎች ሰው ምን ሆንኩ ብሎ ሚስጥሩን ሊያወጋ?! (ጋዜጣውን ለመጠበቅ ጉጉት እንዳለ ግን መናገርዎ አንዳንዴ እውነት አንደምንም ብሎ አፈትልኮ እንደሚደርሶ ያሳያል፤ ከዛ ኋላ እጁን ይዘው ቢጠመዝዙት እንኳ!) ኢትዮጵያ ዛሬን እና ግንቦት 7ን ደግሞ ምን አገናኛቸዉ?! ኢትዮጵያ ዛሬ ነፃ ዜና የሚነገርበት እና የሁሉም ወገን ሃሳቦች የሚስተናገዱበት ድህረ-ገጽ ነው። ግንቦት 7 የራሱ እምነት ያለው የፖለቲካ ድርጅት ነው፤ የሚፅፋቸዉም ነገሮች ምንም እዉነት አዘል ቢሆኑም ሌሎች ሃሳቡን እንዲቀበሉት እና እሱ ወዳለበት ምእራፍ እንዲመጡ ለማድረግ የሚሞክር ነው። የርሶ ነገር ደግሞ የኢህአዴግን የፖለቲካ ክፍል አሰልጣኞችም መድከም ጭምር የሚያሳይ ነገር ሆነብኝ፤ እንዴት ነው ነገሩ?!

ስለ አምባሳደር ተስፋዬ ሀቢሶ፦ የቀድሞ አምባሳደሮች “አምባሳደር እክሌ” ተብለው ሲጠሩ ሲሰሙ የመጀመሪያ ጊዜዎት ነው?

ስለ አቶ አንዳርጋቸዉ ፓርቲ መቀያየር፦ ከኢህሃፓ ጋር ወይም ከሚከተሉት ርእዮተ አለም በዚህም ሆነ በዚያ ያልተነካካ የዚያ ጊዜ ትውልድ ያለ አይመስለኝም። እኔን የሚገርመኝ የሰዎች ባንድ ወቅት የዚያ ፓርቲ አባል መሆን አለመሆን ሳይሆን ዘመናት ባለፉ ቁጥር፣ እነዛም ዘመናት ያ ፓርቲ የያዘው ርእዮተ አለም እንደማይሰራ እና አላማዉንም ለማስፈጸም ሲል የተከተላቸው ዘዴዎች ለሃገራችን እንዳልበጁ እያሳየ አንዳንዶች የሙጥኝ ብለው መቅረታቸው ነው። አንድ ነገር ሞክረው እንደማይስራ ሲያውቁ ሌላ መፍትሄ ፍለጋ የሚሄዱ ሰዎች ብሩኮች ናቸው – ወደ መፍትሄ የመቅረብ እድላቸው ከፍ ያለ ነውና! የሰውየዉን ንግግር የሰማና የሚጽፉትን ጽሁፍ ያነበበ ባለ ቀና ልብ ኢትዮጵያዊ፣ አዳዲስ ግንዛቤዎችን እና የሁኔታዎችን መቀየር ግምት ዉስጥ በማስገባት የሚያደርጓቸው የአላማ ሳይሆን የአካሄድ ለውጦች ቀና ሰለመሆናቸው ጥርጥር አይኖረውም። እርስዎን ግን አልፈርድብዎትም! የሚኖሩለት መንግስት ድርቅናን እንደ ጥንካሬ፤ ከሌሎችና ከጊዜ ተምሮ ባካሄድ ላይ ለውጥ ማድረግን እንደ ድክመት የሚቆጥር የመሃይሞች ራስ ነውና!

የግንቦት 7 የትብብር አላማ፦ እዚህ ጋ ደግሞ ግንቦት 7 ለትብብር አላማው ምሰሶ ያደረጋቸውን ሁለት ዋነኛ ነጥቦች ትተው ስለ ብሄር ፖለቲካና ስለ ኤርትራ ጉዳይ ውትወታ መግባትዎ ፕሮፓጋንዳ መሞከርዎት ነው፤ መስመር ማስለቀቅዎ?! ድንቄም! የግንቦት 7 የፖለቲካ ፕሮግራም የኢትዮጵያን ህዝብ የስልጣን ባለቤት ማድረግ ነው! ይህንንም አላማ ወደ ተግባር ለመተርጎም ካስቀመጣቸው ነጥቦች ዉስጥ አንዱ ማንኛቸዉንም ስለ ኢትዮጵያ ያገባናል የሚሉ ሰዎችና ድርጅቶችን ማሰባሰብ እና ለዚህ አላማ እንዲሰሩ ማስቻል ነው። ይህንንም አንድነት ለማስቻል ደግሞ ሁሉም ሊስማሙባቸዉ የሚችሉ ሁለት ነጥቦችን አስቀምጧል። እነዚህም፦ የስልጣን ሽግግር የሚደረገው በምርጫ እንደሆነ መስማማትና ኢትዮጵያ የምትባለዉን ሃገር ህልውና መቀበል ናቸው። እዚህ ዉስጥ አንድም ስለ ብሄር ፖለቲካና ስለ ኤርትራ የሚናገር ነገር የለም!

ሰላማዊውን ትግል በተመለከተ፦ ለሰላማዊው መንገድ መደብዘዝ ምክንያት የቀድሞዉን ቅንጅት መሪዎችና ኢህአዴግን እኩል ተጠያቂ ማስመሰልዎ፣ ካድሬ መሆንዎን ባይነግሩን፣ ሲሻል አውቆ የተኛ፣ ሲከፋ ደግሞ ነገር ጭራሽ የማይገባዎት መሆንዎን የሚያሳይ ነው። ድንቄም የተሻለ ፓርቲ ጠባቂ! እኔ የቅንጅት መሪዎች ለምን ፓርላማ ገቡ አልገቡም የሚለው የደከመው ክርክር ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም። አንድ የማይካድ ነገር ቢኖር ግን ጉዳዩ የመብት ጉዳይ መሆኑ ነው። ያንን ደግሞ ማመን የኢትዮጵያን ህዝብ እንደ ባሪያ አድርገው መብቱን እየረገጡ ሊገዙት ለሚፈልጉት የኢህአዴግ ሰዎችና ህሊናቸው ለዶለዶመባቸዉ ጀሌዎቻቸዉ፣ ወይም ደግሞ የባርነት አስተሳሰብ ዉስጣቸዉ ሰርጾ ገብቶ የነፃነት ትርጉም ለጠፋቸው በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ይገባኛል። እርስዎ የትኛው እንደሆኑ እግዜር ይወቅ! እዚህ ጋር ግን ጠቅሼ ላልፍ የምወደው፡ ዛሬ ዛሬ እንዴት ነው እንዳው…የኢህአዴግ ባለሟሎች የቅንጅት መሪዎችን ከኢህአዴግ ጋር አንድ መመዘኛ ላይ የማስቀመጡን ነገር ተያይዘዉታል። “ኢህአዴግ የተሻለ ነው” አይደለም እኮ የምትሉት፤ “ሁለቱም እኩል ጥፋተኞች” እንጂ። “ኢህአዴግ የተሻለ ነው” የሚሉ የሉም ለማለት አይደለም። እንዳዉም አብዛኛው የፕሮፖጋንዳ ስራ ያተኮረው እህአዴግ ሃገር ጠባቂና ቅንጅት “የወንበዴዎች ስብስብ” እንደሆነ ለማስረዳት በመሞከር ነው። ያንኛዉን አካሄድ፣ አውቀው ካንቀላፉት ደጋፊዎቹ በስተቀር የሚቀበለው እንደሌለ ያውቃል። ስለዚህ፣ እኔን እንደሚመስለኝ እንግዲህ ከሱኛው ጎን ለጎን የሚሄድ፣ የኢህአዴግን ባለሟሎች ምክናያታዊ አድርጎ ለማሳየት የሚሞክር፣ ኢህአዴግን ለተወሰኑ ነገሮች የሚወቅስ፤ ነገር ግን ከቅንጅት በታች ሳይሆን ከሱ እኩል የሚያኖረው፣ ተጠያቂነታቸዉን እኩል የሚያደርግ ስልት መሆኑ ነው። የስልቱም አላማ ኢህአዴግን ተነሱ ጋር አንድ የክስ ወንበር ላይ በማስቀመጥ የነሱን ፅድቅ እንዲጋራ፣ እነሱንም ደግሞ የሱን ሃጢያት ተጋርተው፤ ኢህአዴግን አንስቶ ብቸኛው ፃድቅ ለማድረግ የሚደረገው ሙከራ ከወደቀ፣ ባይሆን ከተቀናቃኞቹ እኩል ማኖርና እነሱም የሱን ያህል ቆሻሻ እንዲሆኑ ማድረግ ይመስለኛል። የርሶም እንግዲህ ጽሁፍ ያንን ስልት የተከተለ መሆኑ መሰለኝ። ነገር ግን፣ የርሶ ምክንያታዊ ለመሆን መሞከር ገና ርእሶት ላይ ነው ባፍጢሙ የተደፋው።

ስለ ይቅርታ ጥየቃው፦ እንዳው እርሶ እንዳሉት አንዳንድ የቅንጅት መሪዎች ፊርማውን የፈረሙት “የንግድ አመክንዮን” ተጠቅመዉ ነው እንበል። በመጀመሪያ ደረጃ የፖለቲካ ስነ-ምግባር የሚባል ነገር ወይም መፃፍ እንዳለ አላውቅም። ቢኖርም በፖለቲካ ዉስጥ እንዳንድ “የንግድ አመክንዮን” አትጠቀሙ የሚል አይመስለኝም፤ ካለም ሞኝነት ይመስለኛል። ለማንኛዉም…የርሶን የክርክር ነጥብ ባዶነት ለማሳየት እንጂ የቅንጅት መሪዎች የነጻነት መብት እና እሱንም ነፃነት ለማስከበር የሚወስዷቸዉ እርምጃዎች justification አስፈልጓቸዉ አይደለም። በተጨማሪም፣ የነሱ “ጥፋተኞች እንዳልሆንን እናውቃለን” ማለት ተቀባይነት እንዳለዉና እንደሌለው ከማተትዎ በፊት እስራቸዉና የተወሰነባቸዉ ፍርድ ፍትሃዊ መሆኑን ማሳየት አለብዎት። ግን አይችሉም። የማይችሉባቸውም ምክንያቶች ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ለኔ ግልጽ የሆኑት ግን፣ እንዲያ ቢያደርጉ፣ አንደኛ፣ የንግግርዎት መሰረት ስለሚናድብዎት ነው። ሁለተኛ ደግሞ፣ ኢህአዴግ ፈርሞ የመዉጣትን ወይም የመሞትን ምርጫ ጠረጴዛዉ ላይ ባኖረላቸዉ ጊዜ የቀመረው ስልት እና ወዲያውም ከእስር ቤት እንደወጡ ያሳየው፣ እድሜ ልካቸውን ይሄንን ወረቀት እየመዘዝኩ “ጥፋተኛነታቸዉን” እንደተናዘዙ አሳስባቸኋለሁ፤ ያቺ ወረቀትም የእዉነት መጀመሪያና መጨረሻ ትሆናለች ብሎ ነበር። ሳይሆንለት ቀረ! ወረቀቱን ሰው ሊያከብረው ይቅርና የፊርማው አስተባባሪዎች ሳይቀሩ ገበናቸዉ ወጣ! ይባስ ብለው አንዳንዶቹ ፈራሚዎች “ሰራንልህ!” ይመስል ተኢህአዴግ አገዛዝ ርቀው ሄደው ይሳለቁበት ጀመር። እና እንግዴህ እርስዎም ባልሞት ባይ ተጋዳይነት ያንን አፈር ድሜ የበላን ስልት የህይወት እስትንፋሽ ሊተነፍሱበት መሞከርዎ ነው መሰል። አለበለዚያማ እንዳው የጤናማ ሰው አእምሮ ተጠቅመው ከሆነ የቅንጅት መሪዎችን ዉሳኔ እንደ “ህሊና መሸጥ” የሚተቹት…እስኪ እንዳው አንድ ዘራፊ ጦር እሰፈርዎት ገብቶ፤ ወታደሮቹም ወደ ደጅዎት መጥተው ሴት ልጅዎትን “እንድፈራት ስጡን” ቢሉዎት፤ ልጆትን ቁም ሳጥን ዉስት ደብቀው “እቤት ዉስጥ የለችም” ብለው በነፍስዎ ቢምሉ ኋላ ዋሹ ተብለው ሊኮነኑ ነው?! እስኪ ደግሞ…ወታደሮቹ ልጆትን ወስደዉቦት ለማስመለስ ሲያለቅሱና ሲለምኑ፤ “ሚስትህን ልታመጣልን ቃል ከገባህ፣ ልጅህን ይዘህ መሄድ ትችላለህ” ቢሉዎት እና እርሶ ሚስቶትንም ልጆትንም ይዘዉ በጓሮ ቢጠፉ ኋላ ሊኮነኑ ነው?! ይልቁንስ (አእምሮዎት ጤናማ ከሆነ)፣ “ጠላቶቼን በቂልነት መንፈስ በመምታት የማምለጫን መንገድ የከፈትክልኝ አምላክ ተባረክ!” ብለው ነው አምላኮን ማመስገን ያለብዎ!

ስለ መስዋእትነት፦ በርግጥም እርስዎ እንዳሉት፣ “የተሻለ” ፓርቲ ስላጣ ነፍሰ ገዳይን መንግስት ታቅፎ የሚቀመጥ እና መልካምን ዘዴ ፍለጋ ላይ ታች የሚሉትን ለማንቋሸሽ በመሞከር አጥፊውን መንግስት የሚያግዝ እንደ እርስዎ ያለ ሰው እንኳን ከግንቦት 7 ጋር ሊጋራው ይቅርና “መስዋእትነት” ስለሚለው ቃል ሊያውቀው የሚችለው አንዳችም ነገር የለም! ደግሞ ያልገባኝ ነገር፡ ድርጅቱን የሚወቅሱት የሚከተለዉን አካሄድ ስለማይደግፉት ነው ውይስ ጊዜ እያጠፋ ስለሆነ ነው? ምክንያቱም እነዚህ ሁለቱ ነገሮች አንድ ላይ ሊሄዱ አይችሉም። ለማንኛውም ግን፣ መስዋእትነትን እና ጊዜን በተመለከተ፦ መስዋእትነት ማለት መጥነዉ ሳይደቁሱ ወጥ መወጥወጥ አይደለም፤ እየሮጡ ሄደዉም “ዘራፍ!” ብለው ጦር ላይ መላተም አይደለም! አንድን ነገር ታግሎ ለማሸነፍ በተለያዩ መንገዶች መሄድ ይቻላል። እንደ ፍየል ዘለው እየተላተሙ ያሸነፈው ሲያሸንፍ ያሸንፍ ብቻ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ እንደ አንዳንድ ትሎች ከውስጥ እየሰረሰሩ ገብተው ታላቁን ዛፍ ጉድ ማድረግም ዘዴ ነው። Mr. Incredible የአደገኛው ሮቦት ሆድ ዉስጥ ገብተው ሆድ እቃዉን አበላሽተው እንዳኖሩት ማለት ነው። አሸናፊ የሆነን ዕቅድ ለመገንባት ትዕግስት እና የረቀቀ ዘዴን መዘየድ አስፈላጊ ነው። ብዙ ሰዎች ዘዴ መዘየድ ሲያቅታቸው በመስዋእትነት እና በጀግንነት ጥላ ስር በመደበቅ ያልበሰለ እንጀራ ሊያበሉን ይሞክራሉ። ግንቦት 7 እንደዚያ እንዲሆን ምኞቴ አይደለም ካካሄዱም እንደዛ አይመስልም።

ፓርላማ ስለ መግባት፦ አሁንም ይህ ክርክር ብዙዎች የደከሙበትና የማያልቅ ጉዳይ ነው። የእርሶን ነጥቦች ግን ለማርከስ ያህል አንዳንድ ነጥቦችን ሳላነሳ አላልፍም። የቅንጅት ሰዎች ፓርላማ ቢገቡ ኖሮ ሊገኙ ስለሚችሉት “ጥቅሞች” ከተወራ፣ እርስዎ ከጠቀሷቸው ሁለት በግምት ላይ የተመሰረቱ ጥቅሞች በተጨማሪ፣ እርግጠኛ ነኝ፣ ብዙዎች ሊዘረዘሩ ይችላሉ። (በተቃራኒው ሲወራም እንዲሁ።) ነገር ግን፣ እንደርሶ ያሉ ሰዎች የማይመልሷቸዉ ብዙ ጊዜ የተሰነዘሩ ጥያቄዎች አሉ፦ “እነዚህ ሰዎች ፓርላማ ከገቡ በኋላ በሰላም የመንቀሳቀስና እነዚህን የሚባሉትን ‘ጥቅሞች’ ለመሰብሰብ ምን ዋስትና አለ? ፓርላማ ገብተዉ በስቃይ ላይ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ጉዳይ የዚህን ዋስትና ጉድለት የሚያሳይ አይደለም ወይ?” እንዲሁም ደግሞ፦ “የህግ የበላይነት ሳይረጋገጥ ፓርላማ መግባት ጥቅሙ ምንድን ነው?”

ኢህአዴግ ለዲሞክራሲ “አዲስ” ስለመሆኑ፦ ይሄኛው ነጥብ ደግሞ እንግዲህ “ኢትዮጵያ ለዲሞክራሲ ዝግጁ አይደለችም” የሚለው ወንድም መሆኑ ነው መሰለኝ። እዚህ ጋ ብዙ ወደ አእምሮ የሚመጡ ግራ የሚያጋቡ ሁኔታዎች አሉ። “ተስፋዬ ለማራቶን ሩጫ አዲስ ነው” ብሎ ቢል አንድ ሰው፣ እኔ ማራቶን ዉድድር ዉስጥ ለመግባትና ለማሸነፍ ወይም ለመጨረስ፣ ለተወሰነ ጊዜ አድካሚ የሆነና ፅናትን የሚጠይቅ ስልጠና ያስፈልገኛል ማለት ነው። ያንን ሳላደርግ ማራቶን ሩጥ የሚለኝ ሞቴን የሚፈልግ ሳይሆን አይቀርም። ስለዚህ፣ እርግጥ ነው ከመደረጋቸው በፊት ዝግጅት ሊደረግባቸው የሚገባ ነገሮች ብዙ ናቸው። ነገር ግን፣ ለምሳሌ፦ አንድ የገበያ ቀን የስድስት አመት ልጄን መኖሪያችን ከሆነች ካንዲት የገጠር ሰፈር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ከተማ አስከትዬው እየሄድኩ ነው እንበል። ወንዙ ጋር ስንደርስ ረጅሙ ድልድይ ላይ አልወጣም ብሎ እምቢ ይላል – ፈርቶ! እና ይዤው ወደ ሰፈር ተመልሼ አስራ ስምንት አመት እስኪሞላው ልጠብቅ?! ደግሞ አስራ ስምንት አመት ከሞላዉ በኋላ “አሁንም ዝግጁ አይደለሁም” ቢልስ – እንደ ኢህአዴግ?! ድልድይን መሻገር ማራቶን እንደ መሮጥ ስልጠና አያስፈልገዉም! ድልድይ የመሻገሩ ስራ የሚጀምረው ልጁ አንድ እርምጃ ሲወስድ ነው፤ ከዚያም ወደ ኋላ አለመመለስ! ይልቁንስ አንድ በአንድ እፊቱ የተደቀኑትን እርምጃዎች ብቻ መውሰድ! ዲሞክራሲ ማለት ሰማይ ቤት ተቁላልቶና በስሎ ያንዲት አገር መንግስት የተወሰነ አመት ካስቆጠረ በኋላ ወደ ታች የሚወርድ ነገር አይደለም! ዲሞክራሲ ማለት ከደመና በላይ ርቆ የተሰቀለና ኢህአዴግም እሱን ለማምጣት ሰማይ ላይ መብረርን ሊማርበት የሚያስፈልገው ነገር አይደለም! ዲሞክራሲ ማለት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንደ ጠላት ማጥቃትን አቁሞ ባገራቸው የመንቀሳቀስና የመስራት መብታቸዉን ማክበር ነው። ደሞክራሲ ማለት ህዝቡ የፈለገዉን መሪ ሲመርጥ እሺ ብሎ መቀበል እና የራስን ተራ መጠበቅ ነው። ዲሞክራሲ ማለት ነፃው ፕሬስ ሰደበኝ ብሎ የሰዉን በነፃነት ሃሳብን የመግለፅ መብት አለመከልከል ነው። እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ደግሞ ኢህአዴግ ብዙ እድሎች ነበሩት። ይህንንም ለማድረግ ያልቻለው “ዝግጁ” ስላልሆነ ሳይሆን ስለማይፈልግ ብቻ ነው! “አገሪቱም ለዴሞክራሲ ዝግጁ አይደለችም፤ እኔም አይደለሁም” ተብሎ ቁጭ ከተባለማ፣ በቃ ክርስቶስ እስኪመለስም ማናቸዉም ዝግጁ አይሆኑም! እንዳዉም፤ እንዲያው አባባሉን እንዳለ እንቀበለውና፦ አንድ ሰው ሃገሪቱም እኔም ለዲሞክራሲ ዝግጁ አይደለንም የሚል ግኝት ላይ ከደረሰ፤ በጤናማ አዕምሮ አስተሳሰብ፣ ያ ሰው ማድረግ ያለበት በተቻለዉ መጠን ተግቶ ተሟሙቶ ወደ ዴሞክራሲ የሚወስደዉን መንገድ መገስገስ ነው! ቁጭ ብሎ ወደ ደሞክራሲ የሚወስደዉን ዕድል ሁሉ እየጨፈለቁ “ዝግጁ አይደለንም” ማለት የሃሰተኞች የግዜ መግዣ ዉትወታ ብቻ ነው! ሌላው ግራ አጋቢ ጉዳይ ደግሞ ይሄ “ዝግጁነት” እንዲመጣ ምን ያህል አመት እንደሚያስፈልገው ነው። ለመሆኑ ማነው መንግስታት ለዲሞክራሲ “ዝግጁ” የሚሆኑበትን ግዜ የሚወስነው? አዩ፣ አንድ ያልገባዎት ነገር ያለ ይመስለኛል። የዲሞክራሲ መሰረታዊ መገለጫው የህዝብ የወሳኝነት መብቱን መጎናፀፍ ነው! እንዲያ ከሆነና ዲሞክራሲ እንደሚገባን ካመኑ፣ ታዲያ ሌላ ሰው ዉሳኔዉን ባሻዉ ጊዜ እስኪወስንልን ጥበቃዉን ምን አመጣው?!

አቶ አንዳርጋቸዉ በህጋዊ ፓርቲዎች ላይ ስላላቸው አቋም፦ ገፅ 5 ላይ፣ ጽሁፍዎ የባሰዉን መያዣ መጨበጫ ጠፋዉ። አቶ እንዳርጋቸው ስም ሳይጠቅሱ የተናገሩትን ስለ አንድነት ፓርቲ እንደሆነ እርግጠኛነትዎትን ተናገሩ – መረጃ ሳያቀርቡ። አንድ መሰረተ-ቢስ ግምት ልፍቀድልዎ። ቀጥለዉም መንግስት ቢወገድ አብረን እንሰራለን ማለታቸው እንደሆነ ተናገሩ። ሁለተኛ መሰረተ-ቢስ ግምት ነዉ፤ ግን እሳቸው ያሉት እንደዛ ቢሆንስ? “አይ! መጫረስ ነው ያለብን!” አንዲሉ ነው የሚጠብቁት?! እንዴ! ሰውየው፣ የድርጅቱን ፕሮግራም ያነበቡ መስሎኝ! ግንቦት 7 እኮ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ እና ኢትዮጵያ በምትባለው ሃገር ህልውና ከሚያምን ከማንኛዉም ድርጅት ጋር እሰራለሁ ነው የሚለው! አንድነት ደግሞ ይህንን መስፈርት ከሚያሟሉ ፓርቲዎች አንዱ ነው! የአንድነቶች ከግንቦት 7 ጋር ለመስራት ፈቃደኛ መሆን አለመሆን ሌላ ጥያቄ ነው። እስካሁንም እንደዛ አይነት ነገር ይቀበላሉ ብሎ ለመገመት የሚያስችል ምንም መልክት አላስተላለፉም፤ ይልቁንስ ስለ ሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ ምርጫቸው ደግመው ደጋግመው ሲናገሩ ነው የሚታዩት። ምናልባትም እርስዎ የሚደግፉት ፓርቲ እርሶ እንደሚሉት “አንድነት የግንቦት 7 ቅርንጫፍ ነው” ብሎ በሃሰት ከመወንጀሉ በፊት እንሱን ቢጠይቅ ሳይሻል አይቀርም። ደግሞ እሷን የሃሰት ዉንጀላ ለመወርወር አቶ አንዳርጋቸዉን መጥቀስና ያላለውንም ነገር መጨማመሩን ምን አመጣው? ከመቼ ወዲህ ነው ሰው በሃሰት ለመወንጀል ፈቃድ መጠየቅ የጀመራችሁት?

አቶ አንዳርጋቸው ያለው ነገር እና የንቅናቄው ስኬታማነት፦ ሰላማዊ እና ህጋዊ የሆኑ ፓርቲዎችን ማሞጋገስና ለነሱም ስኬትን መመኘት እንዴት ተብሎ እርሶ ወዳሉት አቶ አንዳርጋቸው በንቅናቄው ስኬታማነት ላይ ጥርጣሬ እንዳለው ተደርጎ ሊተረጎም አንደሚችል መቼም አእምሮዎን የሚያይ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው! አሁንም ቢሆን የሚወቅሱትን ድርጅት አላማ የተረዱ አይመስለኝም። ግንቦት 7 ያስቀመጣቸውን ሰፊ መሰረታዊ መስፈርቶች እስካሟሉ ድረስ የተለያዩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን፣ ከነአመለካከታቸዉና ከነትግል ስልታቸው ለማሰባሰብ የተነሳ ድርጅት ነው። ስለዚህም እንደ አንድነት ያሉ ፓርቲዎችን ማሞገጋሱ እና ለመርዳት መሞከሩ ከአላማው እና ከሚከተለው ስልት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነው። ያም ተግባር ደግሞ የስልቱ አንድ ምእራፍ ብቻ እንጂ እልፋ እና ኦሜጋው አይደለም!

የሰላማዊ እና ሰላማዊ ያልሆኑ ቡድኖች መሰረታዊ ልዩነት፦ ሰላማዊ ያልሆነን መንገድ የመረጡ ቡድኖች ሁልጊዜ እንደ ኢህሃዴግ “ፈታኝ” የሆነ ጊዜ በመጣ ቁጥር ጡንቻቸዉን እንደሚጠቀሙ፤ ሰላማውያኑ ደግሞ ተቃራኒውን እምደሚከተሉ እርግጠኛ ሆነው ይነግሩናል። ይሄ ሃሰተኛ ብቻ ሳይሆን ብዙ ታሪካዊ ክስተቶችን ከግምት ውስጥ ያላስገባ የሰነፍ ንግግርም ነው (lazy analysis)። በታሪክ ዉስጥ፣ በተለያዩ ሃገሮች በሃይል ስልጣን ላይ ወጥተው በምርጫ የወረዱ አሉ። አንዲሁም ደግሞ፣ በሰላማዊ ምርጫ ስልጣን ላይ ወጥተው ውረዱ ሲባሉ ህዝብ የጨረሱ አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይም ብዙ ተጽፎበታል ብዙም ተብሎበታል። ጆሮ ያለዉም ሰምቷል።

ስለ አቶ ልደቱ ጠላት መሆን አለመሆን፦ ግንቦት 7 በአቶ ልደቱ እና በፓርቲው ላይ ስላለው አቋም የማውቀው ነገር የለም። ለሱም ተብሎ የተለየ አቋም የሚኖር አይመስለኝም። የርስዎም የርሳቸዉን ነገር በዚህ አኳሃን ማንሳት አልገባኝም። ግንቦት 7 ወረድ ብሎ የአሉባልታ ምከታ ስራ ዉስጥ እንዲገባ ከመመኘትዎ የተነሳ መቸም የማያመጡት ነገር የለም ማለት ነው! አሁንም ጠርቶ ሊታይ የሚገባው ነገር፡ የግንቦት 7 አላማ ህዝብን የነፃነት ባለቤት ማድረግ ነው። ባሁኑ ሰዓት ስልጣን ላይ ቁጭ ብለው ያንን በመከላከል ላይ ያሉት መለስ እና ግብረአበሮቹ ናቸው! እስከምናውቀው ድረስ፣ ምንም እንኳ ለህዝብ ታማኝ ተቃዋሚ መሆናቸው ጥርጣሬ ከፈጠረ ቢዘገይም፣ አቶ ልደቱ አፋቸውን አውጥተው ከመንግስት ህገ ወጥ ተግባራት ጎን መቆማቸዉን አልተናገሩም። አቶ መለስን ልርዳ ብለው ተነስትው ከሳቸው ጎን ከተሰለፉ እሳቸዉም እንደ መለስ የግንቦት 7 ብቻ ሳይሆን የህዝብ ጠላት መሆናቸው አይቀሬ ነው።

በሰላማዊ ትግል ማመን፦ በሰላማዊ ትግል ማመን conditional መሆን እንደሌለበት ይነግሩናል። ማን ባለው? ከዛው ቀጥለው ደግሞ “ፖለቲካ መሰረታዊ እምነት እና አቅጣጫዎች ከሌሉት ለስህተት እና ለንቅዘት የተዳረገ ይሆናል::” ደግሞ የፖለቲካ ቡድኖች መሰረታዊ እምነት መያያዝ ያለበት ከሚመርጡት የትግል ስልት ጋ ብቻ ነው ያለው ማነው? የአንዳንዶች መሰረታዊ እምነት ነጻነታችዉን ማስከበር ቢሆንስ? የትግል ስልት መምረጥ የሚመጣው ለምን እንደሚታገሉ ካወቁ በኋላ ነው። እንዳንዶች የሰላምን፣ ሌሎች የትጥቅን፣ ሌሎች ደግሞ ሁሉን ያካተተን መንገድ ሊመርጡ ይችላሉ። በመረጡት የትግል ስልት ላይ በመመስረት አቅጣጫ እንዳላቸዉ ወይም እንደሌላቸው መናገር አይቻልም፤ እሱ መመዘን የሚችለዉ ከውጤታቸው በመነሳት ነው።

“ሰላማዊ ከሆነ ለምን በህቡእ መደራጀት አስፈለገ”? መልሱ፦ ሰላማዊ ማለትና ህጋዊ ማለት ሁለት የተለያዩ ነገሮች ስለሆኑ። ሰላማዊ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ህጋዊ ናቸው ማለት አይደለም። በህገ መንግስቱም ላይ እንኳ ህጋዊ መሆናቸው የተደነገጉ ነገሮች ኢህአዴግ “ለዲሞክራሲ ዝግጁ ስላልሆነ” አይፈቅዳቸውም። “ሰላማዊ ከሆነስ እንዴት ብሎ ነው ከግንቦት 7 መርህ ከሆነው የ<አመፅንም ትግል ጨምሮ> ከሚለው ፕሮግራም ጋር የሚስማማው?” መልሱ፡ የግንቦት 7ን ፕሮግራም ካጣቀስን የዚያ ምክንያቱ የግንቦት 7 አንድን ስልት እንደ ቀኖና ይዞ አለመዞርና የተለያዩ ስልቶችን የመጠቀም አላማ ነው። ባማርኛ ቋንቋ ደግሞ ከሄድን የርሶ ጥቅስ እንደሚያሳየው “ጨምሮ” የሚለው ቃል አለ። “ጨምሮ” ሲባል ከተጠቀሰው ነገር ሌላ ተጨማሪ ነገሮች እንዳሉ ያሳያል። የርሶ ጥያቄ ግን አንድ ድርጅት የሰላማዊና የአመጽ ትግሎችን አንዴት አብሮ ማስኬድ ይችላል ከሆነ፤ ይልቁንስ እኔ ልጠይቆት፦ ምን እማይሄዱበት ምክንያት አለ? በነገራችን ላይ አቶ አንዳርጋቸው በጻፉት ጽሁፍ ዉስጥ አንድም፣ እርሶ እንደሚሉት፣ “እርስ በራሱ የተምታታ” ነገር የለም። እርሶ ግን ነገር እየቆረሱ የተምታታ ነገር እንዳለ ለማስመሰል የሞኝ ስራ ሰርተዋል። ላንባቢዎት ካለዎት ንቀት የመነጨ ነው ወይስ መቸም ሁሉም ሰዎች ጽሁፉን አላነበቡትም በሚል ተስፋ ነው?

“የኢህአዴግ” ህገ-መንግስት፦ ኢህአዴግ ያስረቀቀዉና ያጸደቀዉ ህገ-መንግስት አንዳንድ ሰዎች ከፖለቲካ አመለካከተቻዉ በመነሳት ከሚጠሏቸዉ አንቀጾች በስተቀር የሰብዓዊ መብቶችን በመተንተን ረገድ እንዳው ባፍሪቃ ዉስጥ እንኳ ተወዳዳሪ እንደሌለው ብዙዎች የሚያምኑበት ጉዳይ ነው። ኢህአዴግ እራሱ እነዛን ህጎች ቢያከብራቸው ኖሮ ተሱ ጋ ጠላትነት እንደማይኖረን እያወቅን ከህገ-መንግስቱ (አሁን ባለበት ሁኔታ) ጋ ምን አጣላን? ህገ-መንግስቱ ደግሞ እርሶ ሊቀጥፉን እንደሚሹት “የኢህአዴግ መንገድ” አይደለም። ያ ቢሆንማ ኖሮ ይሄ ሁሉ ጥል ባልነበረ! ህገ-መንግስቱ በተለያዩ የአለም አቀፍ ስምምነቶች የሰፈሩ እና ተፈጥሮአዊ የሰብዓዊ መብቶች ናቸው ተብለው የሚታወቁን እሴቶች ያዘለ ነው። ኢህአዴግ ግን እነዚህን ሁሉ መብቶች የሰበረና መስበር የቀጠለ ገዢ ፓርቲ ነው። የንትርኩም ሁሉ መንስዔ የኢህአዴግ የህገ-መንግስቱን መንገድ መከተል አለመፈለግ ነው።

በዘውጌ የተደራጁ ድርጅቶች፦ በየቦታው ተበታትነው ያሉ ድርጅቶችን ባላቸው ተመሳሳይ አቋም አሰባስቦ እና ልዩነታቸዉንም በህዝብ ፊት አቅርበው በምርጫ ለመፈረጅ እንዲስማሙ ማድረግ የቱጋ “አድር ባይነት” እንደሆነ ከባዶ ስድብ ባሻገር በምንም አላሳዩም።

ኦነግ እና ኦብነግ፦ የግንቦት 7 የትብብር መስፈርቶች በግልጽ እንደሚያሳዩት፤ ድርጅቱ የኢትዮጵያን ህልዉና ከማይቀበሉ ቡድኖች ጋር አይሰራም። ነገር ግን፤ የማይቀበሉ ካሉ በውይይት ሃሳባቸዉን ቀይረዉ እንዲመጡ ማድረግ የሚችል ከመሰለው ወደ ኋላ የሚል አይመስለኝም። ደግሞ፤ እስካሁን ድረስ ግንቦት 7 ከተጠቀሱት ቡድኖች ጋር ስምምነት ላይ ደርሶ ትብብር ገጥሟል የሚል መረጃ የለም። ቢደርስም የሚሆነው፣ እነዚህ ድርጅቶች ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ከተቀበሉና ሉዓላዊነቷን ካከበሩ ብቻ ነው። ስለዚህ፣ ጥርጣሬዎትን እንደ እውነታ እያቀረቡ መከራከርዎ የሚጠቅመዎ አይመስለኝም።

ኤርትራ፦ በግንቦት 7 ንቅናቄ ፕሮግራም ላይ አሰብን መልሼ አመጣለሁ፤ ኤርትራንም ከናት አገሯ ጋር አዋህዳለው የሚል ነገር አይቼ አላውቅም።

ሁለገብ የትግል ስልት፦ ከዚህ በላይ በቁጥር 13 ላይ እንደሆነው አይነት፣ አንድ ቅንጭብ ሃሳብ ከጽሁፉ ዉስጥ ይወስዱና ምን አይነት “እንድምታ” እንዳለዉ የራስዎትን ትርጉም ይሰጡታል። በዛ ላይ ደግሞ በመመስረት መሰረተ-ቢስ የሆነ ትርጉም ይሰጡታል። እንደገና ደግሞ ቀድሞዉኑ መሰረተ-ቢስ በሆነ ሃሳብ ላይ በመቆም ሌላ አስቂኝ የሆነ መሰረተ-ቢስ ግምት ደግሞ ይሰነዝራሉ። እንግዲህ በኢህአዴግ ቤት “እውነት” የሚቁላላው እንዲህ መሆኑ ነው? በጽሁፍዎት 7ኛ ገፅ እራተኛ አንቀጽ ላይ፦ “<ሁለገብ የትግል ስልት> የሚለው እንዲሁ ምስጢራዊ እና ረቀቅ ያለ እንደሆነ እንድንረዳው የተፈለግን ያስመስለዋል::” በማለት አንዲት ሃረግ ቀንጭበው የራስዎትን ትርጉም ይሰጧታል። ያም ብቻ ሳይሆን ይህ “ሁለገብ የትግል ስልት” ምን እና ምንን እንደሚያካትት የአቶ አንዳርጋቸው ጽሁፍ በጥልቅ ከማተቱም በሻገር እርሶም ትናንሽ እየቀነጣጥቡ ከዚህ በፊት ባሉት ገጾች ተከራክረዋቸዋል። እና ታዲያ ሚስጥሩ ያለው የቱጋ ነው? ከዛ ቀጥለዉም፡ – ኢህአዴግን እንዲህ አድርገን እንረታዋለን የትግል ስልታችንም በዚህ መንገድ ነው ብለን ከነገርነው ትግላችን አይሳካም የሚል እንድምታ ያለው ይህ ሀሳብ…” ብለው ደግሞ ምንም ከተባለው ነገር ጋር የማይገናኝ መሰረተ ቢስ ሃሳብ ይሰነዝራሉ። ያም ሳያንሶት፦ “ጠላቴን እንዴት እንደምገጥመው ከነገርኩት ወይም ካወቀ ያሸንፈኛል ከሆነ አባባሉ በጠላቱ መበለጥ ያወቀው የግንቦት 7 ንቅናቄ የማይዳሰስ ነው ማለት ነው::” ብለው ከየት እንዳመጡት የማይታወቅ ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ። ልክ እኮ የርሶ ነገር የሚመስለው…አንድ ቁጥሮቹን ሳይደምር በፊት የድምር ዉጤቱን የሚያውቅ ሰዉና፤ ቁጥሮቹ ደግሞ ያንን ድምር እንደማያመጡለት ሲያይ ሁለት ሶስቱን ቁጥሮች የድምሩን ውጤት ያመጡለት ዘንድ እንደሚቀይር ሰው ነው።

ዘጠኙ የማጠቃለያ ነጥቦች፦ አቶ አንዳርጋቸው በማጠቃለያዉ የጠቀሳቸው ዘጠኝ ነጥቦች፣ ምናልባትም ሚስጥር አዘል ከሆኑት ከሁለቱ የመጨረሻ ነጥቦች በስተቀር፣ የግንቦት 7 መሪዎች ከንቅናቄው መመስረት ከወራት በፊት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ባወጧቸው የተለያዩ ጽሁፎችና ባደረጓቸው ንግግሮች ለህዝብ የተገለጹ ናቸው። አይን ያላቸው አንብበዋል፣ ጆሮ ያላቸዉም ሰምተዋል፤ የሚቃወሙት ተቃውመው የሚደግፉት ደግፈዋል። እንግዲህ አውቆ የተኛዉንና የለገመዉን ደግሞ ድርጅቱ እየዞረ ወተት እንዲያግት መጠበቅ ተገቢ አይመስለኝም። ለነገሩ ነው እንጂ አቶ ካድሬ፣ ምንም እንኳ ድርጅቱ አላማቸዉን ለለወጡ የመንግስት ካድሬዎች ሳይቀር በሬ ክፍት ነው ቢልም፤ እኔ በውነቱ የአባልነት መረጃ ሲጠይቁ የሚላክሎትን የአባላት ስነ-ምግባር ኮድ አልፈው አባል የሚሆኑ አይመስለኝም። እርስዎ ከእዉነት ጋር ያለዎት ግንኙነት እንደዛ ቅንነትንና ወንደማማችነትን፤ እንዲሁም ደግሞ መተማመንን ለሚሻ ትግል የሚጣጣም አይመስለኝም፡፡

ከዚህ ቀጥለዉም ድርጅቱ እርስዎን አሳምኖ አባል ለማድረግ ስላልሞከረ “አለበለዚያ ንቅናቄው የተሰማራበት የጦር ሜዳ ኢንተርኔት ትግሉም ስብሰባ እና ተቃውሞ ሰልፍ ነው ማለት ነው:: ይህ ደግሞም ብርሀኑ ነጋ ወደ አገሩ ላለመግባት ለህዝቡ ያቀረበው ምክንያታዊ ስልት ነው የሚለውን ልጋራ ነው::” ብለው ገምድለው ፍርድ! ለመሆኑ አቶ ካድሬ፣ “logic” ስለሚባለው ነገር ሰምተው ያውቃሉ? ምንድነው ነገሩ? እኔ እንዳው ትንሽ አታሎም ቢሆን የተወሰኑ ምስኪኖችን ልብ ለመግዛት ጥረት ታደርጋላችሁ ብዬ ስለምገምት እንጂ፣ ፈጠራ እየፈጠራችሁ ለፍርድ ቤትም ማስረጃ የማቅረብ ልምድ እንዳላችሁ ጠፍቶኝ አይደለም። ከመቼ ወዲህ ነው ያንድ ድርጅት እርስዎን ለማግባባት መሞከር አለመሞከር የድርጅቱ ማንነት መገለጫ የሚሆነው? በቃ፣ ግንቦት 7 ስብሰባ ከማካሄድ በስተቀር ምንም ስራ እየሰራ አይደለም የሚለውን ዉንጀላ በማስረጃ አስደግፈው ማስረዳት ሲያቅትዎት ዉንጀላዉን እራሱን ድግም አድርገዉት ቁጭ! በዛ ማስረጃ ባልቀረበለት መሰረተ-ቢስ ዉንጀላ ላይ ደግሞ በመመስረት ዶ/ር ብርሃኑን ውቅስ! ጎበዝ! ይሄ ነው ኢህአዴግ!

የሶስት ወር ርዝመቱ፦ “አንዳርጋቸው በአቶ መለስ <መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው> ስላልተባለ ግንቦት 7ን ጠንካራ እና ኢህአዴግን ያንቀጠቀጠ አድርጎ ቆጥሮታል:: መልሴ ምኑ ተነካና በሶስት ወር ምጥ ማስወረድ አንጂ ልጅ ስለማይሆን ለአስተያየቱም ራስንም ለመመዘን ጊዜው በጣም ልጅ ነው::” ነው እንዴ? ታድያ እርስዎ በጽሁፍዎ ገጽ 2 አንቀጽ 1 ላይ ምን ሲያረጉ ኖሯል? ግንቦት 7ን ሲመዝኑትና ሲያጣጥሉት አይደል። ባንድ በኩል በዚህ ሶስት ወር ውስጥ ምን ሰራችሁ እያሉ የተሰራውን ማጣጣል፤ ድርጅቱንም በጊዜ ማጥፋት መወንጀል። ትንሽ ዘግይቶ ደግሞ ሶስት ወር እንዲህ ያለ ግምገማ ለማድረግ አጭር እንደሆነ መናገር። ይሄ ማወላወል ይባላል።

የተሻለ ፓርቲ፦ ኢህአዴግን የሚደግፉት የተሻለ ፓርቲ እስኪመጣ ነው ብለው ይነግሩናል። ይህም ዉሳኔ ላገር እንደሚበጅ ይጠቅሳሉ። ምርጫ ስለታጣ ኢህአዴግን ታቅፌ ተቀምጫለሁ የሚለው አመለካከት ምክንያታዊ አይመስለኝም። ገለልተኛ ሆነው “የተሻለ” ፓርቲ እንዲመጣ መስራት ይችሉ ነበር። ይሄ የመኖርና የመሞት ጉዳይ አይደለም። ብዙ ሌላ ምርጫዎች ያሉበት ጉዳይ ነው። ኢህአዴግ ዉስጥ የገባሁት ከዉስጥ ሆኜ ለማሻሻል ነው ብለው እንኳ ቢሉ፤ ከአካሄድዎት እንኳን ኢህአዴግን ለማሻሻል ይቅርና “የተሻለ” የሚለውን ቃል ትርጉም የሚያውቁም አይመስሉም። እስኪ በዚህ ጽሁፍዎ ዉስጥ እንዲያው ለማስመሰል ያህል እዚህም እዚያም ኢህአዴግን ከመውቀስ ይልቅ ምን የሰጡት መሰረታዊ ለውጥ የሚያስፈልገው ሂስ አለ? ምንም የለም። እናም ኢህአዴግን ከሞላ ጎደል ባለበት ሁኔታ ይወዱታል ማለት ነው። እንደዛ ከሆነ ደግሞ መቼም ቢሆን “የተሻለ” ፓርቲ አይገኝሎትም። አሁን ኢህአዴግን ለማሞጋገስ ይህ ሁሉ መሃላ ምን አስፈለገው? እንዲያው ወደድኩት በቃ ቢሉስ!

በመጨረሻው አንቀጽዎት ላይ የኢህአዴግን “ድክመት” ከዉጭ አገር የሥራ አለቃ ፊት መጋረፍ ጋር ማወዳደርዎ እጅግ በጣም አስቂኝ ነው። በተጨማሪም ኢህአዴግ ያለበት እርሶ ሊቀጥፉን እንደሚሞክሩት “ድክመት” ብቻ አይደለም። ኢህአዴግ ብዙ ዜጎችን ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ያሰረና የገደለ፣ በጦር እና በዘር ማጥፋት ወንጀል ወደ ፊት ሊያስከስሱት የሚችሉ ተግባራትን የፈጸመ፣ የአገሪቱን ዳር ድንበር በግድ የለሽነት እና በማን አለብኝነት ተነስቶ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ለጎረቤት አገሮች በመስጠት የሃገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ፤ እነዚህንም ተግባራት ከማድረግ እስካሁን ያለተቆጠበ ወንጀለኛ ድርጅት ነው! “ሊበሏት የፈለጓትን ዥግራ ቆቅ ነች” ይሏታል እንዲሉ፤ እርሶም የርሶን ከወንጀለኞቹ ጋር መዛመድ justify ለማድረግ መሆኑ ነው የኢህአዴግን ጉድ በ “ድካም” አድበስብሰው ለማለፍ የፈለጉት።

በመጨረሻም፡ እኔ እንደዚህ ጽሁፍ መላ ቅጡን ያጣ፣ እያንዳንዱ አረፍተ ነገር በመሰረተ ቢስ ዉንጀላ ወይም ምክናያታዊ ባልሆነ እና logical sense በማይሰጥ ሃሳብ የተሞላ ጽሁፍ ካጋጠመኝ ሰነባብቷል። እኔ መቸም አንድ ጽሁፍ ኮምፒውተር ላይ ታይፕ አድርጎ ወደ ፒ ዲ ኤፍ ለውጦ ኢ-ሜይል ማድረግ እስኪችል የተማረ አበሻ አንድ ወይም ሁለት ምክንያታዊነትን የሚፈልጉ ኮርሶች አልወሰደም ለማለት ይቸግረኛል። ካላዋቂነት ሳይነሳ የተጻፈ ጽሁፍ ከሆነ ደግሞ ሊሆን የሚችለው ብቸኛው ነገር፣ ሆን ተብሎ ግንቦት 7ን መልስ እንዲሰጥ ለማስገደድ እና በዚያም አሉባልታዎችን ወደመዋጋት ስራ እንዲገባልዎት ሳይሆን አይቀርም። ሲያምሮት ይቅር!

በተስፋዬ ማሩ tesfamaru@gmail.com

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 26, 2008. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.