“ፖለቲካ በቃኝ፣ እግዚአብሔርን አገለግላለሁ” ታምራት ላይኔ

Tamirat Layneበፍሬው አበበ እና በታምሩ ጽጌ (21 December 2008)  — የኢትዮጵያ የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ በቀጣይ ሕይወታቸው በቀጥታ በፖለቲካ ውስጥ ከመሳተፍ ይልቅ በቤተክርስቲያን እግዚአብሔርን ለማገልገል መወሰናቸውን አስታወቁ፡፡ አቶ ታምራት ትላንት አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው በእህታቸው መኖሪያ ቤት በተለይ ለሪፖርተር ጋዜጣ “ዓላማዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ማገልገል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠላም፣ ፍቅር የሚያገኝበትን እመኛለሁ” ብለዋል፡፡

“እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው የፖለቲካ ድርጅት (ፓርቲ) የሚባሉ ሃሳቦች ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሩ ናቸው የምላቸውን ሃሳቦች እንደ ፖለቲከኛ ሳይሆን ሠላምና ፍቅርን እንደሚፈልግ ግለሰብ በመልካም መንገድ እገልፃለሁ” በማለት አቋማቸውን ገልፀዋል፡፡

አቶ ታምራት የሚፀፅታቸው ነገር ይኖር እንደሆን ተጠይቀው “ምንም የሚፀፅተኝ ነገር የለም፡፡ ከፀፀት ይልቅ ወደኋላ ተመልሼ ማድረግ ያለብኝንና የሌለብኝን ነገር ምን ነበር ብዬ ትምህርት ነው የምወስደው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ታምራት አያይዘውም “ሕዝብን ከዚህ በፊት ጠቅሜያለሁ ብዬ ራሴን አላሞካሽም፡፡ እግዚአብሔር ራሳችሁን ከፍ ከፍ አታድርጉ ነው የሚለው፡፡ ባሳለፍኳቸው ወቅቶች እዚህ እዚህ ላይ ተሳስቻለሁ፣ አጥፍቻለሁ የምላቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህን ነገሮች ትምህርት በምይዝባቸው መንገድ የማያቸው ይሆናል” ብለዋል፡፡

ሕዝብን ጐድቷል ተሳስቻለሁ የምለው ባለፉት ዘመናት ኮሚኒስት ነኝ ብዬ ማሰቤ ነው ያሉት አቶ ታምራት፣ “በዚህ አስተሳሰብ እግዚአብሔርን ካድኩት፣ ይህ ለእኔ ትልቁ ጥፋቴ ነበር” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ ታምራት ላይኔ የአንድ ወንድ ልጅ እና የአንድ ሴት ልጅ አባት መሆናቸውንና፣ በአሁኑ ወቅት ልጆቻቸው ከባለቤታቸው ጋር በአሜሪካን አገር እንደሚኖሩ ገልፀዋል፡፡

አቶ ታምራት ስለቤተሰቦቻቸው ሲናገሩም ..እኔ በታሰርኩ ጊዜ ወደኬንያ ሄደው ብዙ ተንገላተው፣ ብዙ ችግር አይተዋል፡፡ እግዚአብሔር በከፈተላቸው መንገድ ሄደዋል፡፡ አሁን በደህና ሁኔታ ላይ ናቸው.. በማለት አስረድተዋል፡፡

ወደቤተሰቦቻቸው በቅርቡ ይጓዙ እንደሆነ ተጠይቀው “የምሄድበትን ጊዜ እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው፡፡ ለጊዜው የወሰንኩት ነገር የለም” ሲሉ መልሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የ54 ዓመት ጎልማሳ የሆኑት አቶ ታምራት ባለፈው ዓርብ ዕለት የተለቀቁት በአመክሮ ከ12 ዓመታት እሥር በኋላ ነው፡፡

አቶ ታምራት ላይኔ በይፋ የመንግሥት ስልጣናቸውን ጥቅምት 14 ቀን 1989 ዓ.ም. ከማጣታቸው በፊት በኢሕአዴግ ሽግግሩ ዘመን የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በኋላም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የመከላከያ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በፖርቲ ደረጃ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ነባር ታጋይና ዋና ፀሐፊ፣ የኢሕአዴግ ምክትል ሊቀመንበር ነበሩ፡፡

የታምራት ከሥልጣን መወገድ መነሻ

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከጥቅምት 11-12/1989 ባካሄደው ስብሰባ አቶ ታምራት ላይኔ በድንገት ከፓርቲ ዋና ጸሐፊ ኃላፊነታቸው እንዲነሱ ወሰነ፡፡ የፓርቲው የውሣኔ መነሻ በወቅቱ በይፋ አይገለፅ እንጂ ውሎ አድሮ ታምራት ላይኔ በሥነ ምግባርና በብልሹ አሠራር ውስጥ መቆየታቸውን ለፓርላማ ቀርበው በአንደበታቸው አረጋገጡ፡፡ በዚሁ ንግግራቸው ከጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ጀምሮ እስከ ድርጅት አባሎቻቸው ድረስ የሰጧቸውን ምክር ሳይሰሙ መቆየታቸውን አከሉ፡፡

ጠ/ሚ መለስ በፓርላማው ስብሰባ ላይ ተገኝተው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ጥንካሬ ላይ ያላቸው አቋም መሸርሸሩን ተናግረዋል፡፡ አክለውም “በብረትና በእሳት ያልወደቁትን በስኳር ፈተና ማለፍ አቅቷቸዋል” ሲሉ ወርፈዋቸዋል፡፡ አቶ ታምራት በዘመነ ኢሕአዴግ ከሙስና ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሥልጣናቸውን በማጣት የመጀመሪያው ሰው ሆነው ጉዳያቸው ወደ ክስ ተላለፈ፡፡

ሆኖም አቶ ታምራት ጉዳያቸው በፍ/ቤት መታየት ከጀመረ በኋላ ቀደም ሲል በፓርላማ ያደረጉት ንግግር ተገድደው የፈፀሙት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክሱ አመጣጥና ጭብጥ

የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ አቶ ታምራትን ጨምሮ 9 ተከሳሾች ላይ መጋቢት 18 ቀን 1989 ዓ.ም የመጀመሪያውን ክስ አቀረበ፡፡ ክሱም ሲታይ ቆይቶ ጥር 25 ቀን 1992 ዓ.ም የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጠ፡፡ የክሱ ፍሬ ነገር (ጭብጥ) በሶስት ተከፍሎ የቀረበ ነበር፡፡

የመጀመሪያው ክስ የመንግሥትን ዕዳ ለመክፈል በሚል ከሼህ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲ የወሰዱት 16 ሚሊዮን ዶላርና የ1ሺህ ቶን ቡና ሽያጭ ዋጋ ከሌሎች ግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን ለግል ጥቅም አውለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ገበያ ድርጅትም ተገድዶ ብድር ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል የሚል ነው፡፡ በዚህ ክስ 1ኛ ተከሳሽ አቶ ታምራት ከአልአሙዲ ዕዳ መክፈያ ተበድሬዋለሁ ያሉት ገንዘብ የዕዳ አከፋፈል ሥርዓት አልተከተለም፡፡ ገንዘቡም ለዕዳ መክፈያ ሳይሆን ለ4ኛው ተከሳሽ ለአቶ ሁሴን አብደላ ቃሲም (የወ/ሮ ሻዕዲያ ልጅ) የባንክ ሒሳብ ውስጥ ነው የገባው፡፡ ከዚያም ለንደን የሚገኘው የአቶ ሁሴን አብደላ አካውንት ጅቡቲ ወደሚገኘው ወደ ወ/ሮ ሻዕዲያ አካውንት ተላልፏል፡፡ ወ/ሮ ሻዕዲያ ገንዘቡን ከራሳቸው አልፎ ለአቶ ሁሴን ማከፋፈላቸውን፣ በአቶ ታምራት ላይኔ የ4 ዓመት ወንድ ልጅ ብሌን ታምራት ስም በሲዊዘርላንድ ባንክ አካውንት ከፍተዋል የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡

ሁለተኛው ክስ አቶ ታምራት የአፋር፣ የሶማሌ፣ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል ክልሎች በ1998 የበጀት ዓመት በጀቱ ከሚመለስ የኮንስትራክሽን ዕቃ ብትገዙበት ይሻላል በማለት 67.3 ሚሊዮን ብር ራሚስ ኢንተርናሽናል ለሚባል ድርጅት ጨረታ አሸንፏል በሚል እንዲሰጥ አድርገዋል የሚል ነው፡፡ ለይስሙላ እና አጃቢ እንዲሆኑ ዜዚ ትሬዲንግ እና ሃንዛለሙና የሚባሉ ድርጅቶች በጨረታው መሳተፋቸውም ተጠቅሷል፡፡

ሶስተኛው ክስ ከዓለም ባንክ በተገኘ ገንዘብ ለመንገድ ሥራ በወጣው ጨረታ ዱሜዝ የተባለ ኩባንያ አሸንፎ እያለ ሶጅያ ለሚባል የፈረንሣይ ኩባንያ 1 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ በማለት ዱሜዝ ተሰርዞ ሶጅያ አሸናፊ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ገንዘቡንም አብረው ተከስሰው የነበሩት ወ/ሮ ሻዲያ ናዲም ተቀብለዋል የሚል ነው፡፡

ፍ/ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ጥር 25 ቀን 1992 ዓ.ም አቶ ታምራት ላይኔ በሶስቱም ክሶች ጥፋተኛ ናቸው ሲል ወስኗል፡፡

ይህንን ተከትሎ መጋቢት 5 ቀን 1992 ዓ.ም የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ባስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ አቶ ታምራት ላይኔ በ18 ዓመት እሥራት እና 15ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ ጥሎባቸዋል፡፡

በተጨማሪም በቡና ሽያጭ የተገኘውና በወ/ሮ ሻዕዲያ የባንክ ሒሳብ የገባው 4.2 ሚሊዮን ዶላር፣ በሦስተኛው ክስ የተመለከተው የሶጂያ ኩባንያ ቃል ከተገባው 1 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 3ኛ ተከሳሽ ሒሳብ የገባው 900ሺ ዶላር ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን ወስኗል፡፡

ከሼህ አልአሙዲ የተገኘው 16 ሚሊዮን ዶላር 3ኛ ተከሳሽ ሒሳብ ቁጥር አስቀድሞ የገባው 9 ሚሊዮን ዶላር፣ 5ኛ ተከሳሽ ገቢ ያደረጉት 556ሺ 324 ብር ከ05 ዶላር፣ 4ኛ ተከሳሽ የወሰዱት 6 ሚሊዮን 443ሺህ 144ብር ከ70 ዶላር ለባለቤቱ እንዲመለስ በአብላጫ ድምጽ ወስኗል፡፡

በአቶ ታምራት ላይኔ መዝገብ ከቀረቡት 9 ተከሳሾች መካከል ሁለቱ ሴቶች ነበሩ፡፡ እነሱም ወ/ሮ ሻዕዲያ ናዲም እና ወ/ሮ ማርታ ገ/ህይወት ሲሆኑ 2ኛ፣6ኛ፣7ኛ፣8ኛ ተከሳሾች መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍ/ቤቱ ቀደም ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡ የወ/ሮ ሻዕዲያ ልጅ ሁሴን አብደላ ውጭ አገር በመሆናቸው ፍ/ቤት ሊቀርቡ ስላልቻሉ ጉዳያቸው በሌሉበት ታይቷል፡፡

የፍትሐብሔር ክስ ጉዳይ

የፍትሐብሄር ክስ ሐምሌ 30 ቀን 1989 ዓ.ም የተመሠረተ ነው፡፡ በክሱ የተካተቱት አቶ ታምራት፣ አቶ ጉልላት፣ ወ/ሮ ሻዕዲያ፣ አቶ ንጉሴ እና አቶ ሁሴን ናቸው፡፡ የክሱ ምክንያትም ተከሳሾች አለአግባብ የተወሰደውን የመንግሥት ሐብት ማለትም 1ሺህ ቶን የቡና ዋጋና ልዩ ልዩ ወጪዎች ለማስከፈል በብር 32 ሚሊዬን 512ሺህ 346 ብር ግምት የቀረበ ነው፡፡ ይኸው ክስ የፍትሕ ሚኒስቴር ሐምሌ 14 ቀን 1990 ዓ.ም ላሻሽል ብሎ ካሻሻለው በኋላ በፍትብሔር ኃላፊነት በብር 34 ሚሊዮን 209 ሺህ 987 ብር ከ96 ሣንቲም ከፍ በማድረግ ሲታይ ቆይቷል፡፡

በውጪ ባንክ ተቀምጧል ስለተባለው ገንዘብ

አቶ ታምራት ላይኔ በልጃቸው ስም በስዊስ ባንክ አስቀምጠውታል የተባለውን 8 ሚሊዮን ዶላር ለማስመለስ መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ ገል..ል፡፡

ቢቢሲ በፎከስ ኦን አፍሪካ ፕሮግራም አቶ ታምራት ላይኔ በስዊስ ባንክ ያስቀመጡትን ገንዘብ የኢትዮጵያ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ለመስጠት ማቀዱን፣ ነገር ግን ተቃዋሚ ካለ በ30 ቀናት እንዲያሳውቅ የባንኩ ባለሥልጣናት ማስታወቃቸውን ጠቅሶ መጋቢት 25 ቀን 1990 ዓ.ም ዘግቦ ነበር፡፡ በወቅቱ የአቶ ታምራት ላይኔ ጠበቆች በቪኦኤ በኩል ሁኔታውን በማስተባበል “ደንበኛችን በስዊስ ባንክ ያስቀመጡት ገንዘብ የለም” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

በወቅቱ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ሙስናን ለመዋጋት ሞዛምቢክ ማፑቶ ላይ በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ የስዊስ ባንክ ሙስናን ያበረታታል ሲሉ ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ይህንን በምሣሌ ሲያስረዱም “አንዲት ሴት የሲዊዘርላንድ አምባሳደር በተገኙበት በስዊስ ባንክ ያለ ገንዘብ ይመለስ ብላ ፈርማልን ነበር፡፡ የስዊስ ባንክ ግን የሴትየዋ ወኪል ነኝ የሚል ግለሰብ አቤቱታ በመስማት አልመልስም አለን፡፡ በእኛ አመለካከት ዋናው ሴት በፊርማዋ ገንዘቡ ይመለስ ስትል ወኪል የሚባለው አይመለስም በማለቱ ገንዘብ መከልከሉ ትክክል አይመስለኝም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ ጠ/ሚኒስትሩ ሴትየዋ ያሏቸው ወ/ሮ ሻዕዲያ ናዲም ሲሆኑ ወኪል የተባለው ልጃቸው ሁሴን ቃሲም እንደነበር ታውቋል፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on December 21, 2008. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.