ፓትርያርኩን ያልጨመረ የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ በመካሄድ ላይ

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 8/2009) — ያለ ፓትርያርኩ ፍላጎትና ፈቃድ፣ ፓትርያርኩን ያልጨመረው የመጀመሪያው የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ በማካሄድ ላይ ይገኛል። ስብሰባው ዛሬ ረቡዕ ጠዋት ሲጀመር ጉባዔውን ለማቋረጥ ብዙ ሙከራ ያደረጉት ቅዱስነታቸው ሳይሳካላቸው ቀርቷል ተብሏል። በመጨረሻም አጀንዳው ቀርቦ ሊጸድቅ ችሏል። የዕለቱ ብቸኛ አጀንዳ “ፓትርያርኩ የተፈጸሙ አስተዳደራዊ በደሎች” በመሆናቸው ይህንን አጀንዳ ለመመልከት በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ቅዱስነታቸው መውጣት እንዳለባቸው ሲነገራቸው አሻፈረኝ ብለዋል። በዚህ መልኩ ለብዙ ሰዓታት ብጥብጡ ቀጥሎ በመጨረሻ ቅ/ሲኖዶሱ ሁሉጊዜም ከሚካሄድበት አዳራሽ በመውጣት አባቶች ባገኙት በሌላ ሥፍራ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ጉባዔው ስብሰባውን ሲቀጥል ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በሰብሳቢነት እንዲመሩ የመረጣቸው መሆኑም ታውቋል።

ይህንን ጉባዔ ለማካሄድ ብዙ እንቅፋት ገጥሞት እንደነበር የደጀ ሰላም ምንጮች አስታውቀዋል። በተለይም የቅዱስነታቸው ደጋፊዎች የሆኑት ብፁዓን አበው ገብርኤል፣ ይስሐቅ፣ ገሪማ፣ ኤርምያስና ሙሴ አደናቃፊ ተግባራትን ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ነበር ተብሏል። በተጨማሪም ብፁዓን አባቶችን በስልክ “እንገላችሁዋለን፣ እናጠፋችሁዋለን” እያለ የሚያስፈራራው የወ/ሮ እጅጋየሁና የግብረ አበሮቻቸው ቡድን በዚሁ ተግባሩ ቀጥሏል ተብሏል። ሴትዬዋ ሽጉጥ መታጠቃቸውን ቢያንስ በሁለት አጋጣሚዎች ያሳዩ ሲሆን በሙስናና በቤተ ክርስቲያን ዝርፊያ ሀብታም የሆኑት ሰዎች ቡድን በብፁዓን አባቶች ላይ አደጋ እንዳይጥል መንግሥት ጥበቃ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዳዩን በጥሞና በመከታተል ላይ የሚገኘው መንግሥት “የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ እንደሚቀበል” ፍንጭ ማሳየቱ ታውቋል። ነገሩ በርግጥ በዚህ መልክ ከቀጠለ እና መንግሥት የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ውሳኔ አክብሮ ከተቀበለ በማስፈራራትና “ወየውላችሁ መንግሥት ከኔ ጋር ነው” የሚለው ቅዱስነታቸው ዛቻ ፍሬ ያጣል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ቤተ ክርስቲያን በርግጥም ራሷን በራሷ በእውነተኛ ነጻነት ማስተዳደር የምትጀምርበት አዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ያደርገዋል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 8, 2009. Filed under NEWS. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.