በውብሸት፣ በርዕዮትና በሌሎቹ ላይ “የጥፋተኝነት” ውሳኔ ተላለፈ

ሐሙስ ጥር 10 ቀን 2004 ዓ.ም፡- የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት መንግሥት በነኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል በከሰሳቸው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር እና ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ አሳለፈ፡፡ የቅጣትውሳኔ ለማስተላለፍ ለጥር 17 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡

ላለፉት አራት ወራት በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮና በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ቤት ሆነው ሲከራከሩ የነበሩት ሁለቱ ጋዜጠኞች፣ የፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን እና ወ/ሮ ሂሩት “መጀመሪያም እውነቱ እንዲወጣ ስንከራከር ከዚህ ፍርድ ቤት ፍትሕን እናገኛለን ብለን አስበን ሳይሆን እውነታው በታሪክ ተመዝግቦ እንዲቀር ነው፣ ይህንንም በማድረጋችን ዓለም በእኛ ክስና እስር የኢሕአዴግን መንግሥት ጠንቅቆ አውቆታል ብለን እናስባለን ሲሉ ለሪፖርተራችን አስታውቀዋል ፡፡

ፍርድ ቤቱ በመሐል ዳኛ እንዳሻው አዳነ በንባብ እንደገለጸው ከሆነ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ ካልተያዙ የውጭና የሀገር ውስጥ አሸባሪዎች ጋር ተካፋይ በመሆን፣ ራሳቸውን ግንቦት 7፣ የአርበኞች ግንባር፣ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር /ኦነግ/፣ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር /ኦብነግ/ በማለት የሚጠሩ፣ ከኤርትራ መንግሥትና ኤልያስ ክፍሌ በተባለው የኢትዮጵያን ሪቪው አዘጋጅና የሽብር ቡድኑ አስተባባሪ አሰባሳቢነትና አማካኝነትየጋራ ህቡእ ትጥቃዊና በሽብር የተደገፈ ሁሉን አቀፍ ትግል የማድረግ ጥምረት በመፍጠር እና የትብብር ስምምነት በመፈራረም ከሰኔ ወር 2000 ዓ.ም ጀምሮ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በተደራጀ የሽብር ድርጊት ለማፍረስ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡

በሀገር ውስጥ ህቡእ የሽብር ቡድን አደራጅተው ከውጪው ቡድን ጋር በመቀናጀት የጋራ የሽብር ስትራቴጂና እቅድ ላይ በመወያየት የሥራ ክፍፍል በማድረግ መነሻቸውን ከአዲስ አበባ ያደረጉ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ሐረር፣ ሐዋሳ፣ አሶሳ፣ ወለጋ፣ ጅጅጋና ጎንደር የኤሌክትሪክ፣ የስልክና ፋይበር ኔትዎርክ መስመሮችን ከጥቅም ውጪ ለማድረግ በመስማማት፣ በአሸባሪ ቡድኑ አስተባባሪ በኤልያስ ክፍሌ በኩል በስውርና በረቀቀ መልኩ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ”በቃ‘ የሚል ሕገ ወጥ ጽሑፎችና ወረቀቶች በመርካቶ፣ በሀብተ ጊዮርጊስ፣ ጊዮርጊስ፣ ጥቁር አምበሳ እና አውቶቡስ ተራ አደባባይ በማስለጠፍ፣ በጋዜጠኝነት ሽፋን በፎቶ በማንሳት፣ የማነሳሳትና የቅስቀሳ ሥራ በመስራትና በማሰራት፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመጣል መንቀሳቀሳቸውን የዐቃቤ ህግ ምስክሮች፣ የሰነድ ማስረጃዎች፣ በብሕራዊ ደኅንነት መስሪያ ቤት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተጠለፈ የስልክ ልውውጣቸው ሲያስረዳ በአንጻሩ የተከሳሾች የሰው ምስክሮች እና የሰነድ ማስረጃዎች ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ሊያስተባብሉ አልቻሉም ሲል ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

የዐቃቤ ሕግንም ሆነ የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡትን ማስረጃዎች ሁሉ “መርምሬያለሁ” ያለው ፍርድ ቤቱ “ተከሳሾች በሁሉም ክስ ጥፋተኛ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፤ የቀረበባቸውንም ክስ ማስተባበል አልቻሉም” ሲል የቅጣት አስተያየት ዐቃቤ ሕግንና የተከሳሽ ጠበቆችን ጠይቋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ብርሃኑ ወንድማገኝ ተከሳሾች የፈጸሙት ወንጀል ከአሸባሪ ድርጅት ጋር በመደራጀት፣ የአድማ ስምምነት በማድረግ፣ አባልና አመራር ሆነው በ2004 ዓ.ም ሁከት ሊፈጥሩና መሠረተ ልማት ሊያወድሙ ያሴሩት በሕጋዊ ፓርቲና በጋዜጠኝነት ሽፋን በመሆኑ የወንጀሉን አደገኝነት ስለሚያሳይና በእያንዳንዳቸው ላይ የቀረበባቸው ክስ ተደራራቢ በመሆኑ ወንጀሉን ከባድ ያደርገዋል፤ አራተኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ የግንቦት 7 አባል የነበረችና 3 ዓመት ጽኑ እስራት ተፈርዶባት ከዚህ ያልተማረች በመሆኑ በአጠቃላይ ቅጣቱ በከባድ ደረጃ እንዲያዝልኝ ሲል ጠይቋል፡፡

የ2ተኛ፣ የ3ተኛ እና የ4ተኛ ተከሳሾች ጠበቃ ደርበው ተመስገን የቅጣት አስተያየት ያቀረቡ ሲሆን አንደኛ ተከሳሾቹ በሕግ የተፈቀደ ተግባር ሲያከናውኑና ለማኅበራዊ ለውጥ ሲሉ ሕግ ያለፉ እንጂ በአፍቅሮተ ንዋይ፣ በቸልተኝነትና በወራዳነት ያከናወኑት አይደለም፤ በዚህም ላይ ወንጀል የተባለው ገና ያልተፈጸመ በመሆኑና ከዚህ በፊትም ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው፣ የሕዝብ አገልጋይና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸው ግንዛቤ ውስጥ እንዲገባ፣ አራተኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ሂሩትን በተመለከተ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ 67 መሠረት እንዲታይልን፣ በአጠቃላይ የቅጣት ውሳኔው በዝቅተኛ እንዲታይና ቅጣቱም እስር ከሆነ በገደብ እንዲያዝልን ካልሆነ ግን ቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው በቤተሰብ ላይ እንግልት ስለሚፈጥር ወደ ገንዘብ እንዲቀየርላቸው እጠይቃለሁ ብለዋል፡፡

የጋዜጠኛ ርዮት ዓለሙ ጠበቃ ሞላ ዘገየ በበኩላቸው ተከሳሽ በሙያዋ ምስጉን ጋዜጠኛና መምህርት ናት፣ ተፈጸመ የተባለው ድርጊት ላይ አስቀድማ አስባ ወይም በቸልተኝነት የተፈጸመ አይደለም፤ የጋዜጠኝነት ሥራዋን ስትሰራ እግረ መንግድ ባይ ዲፎልት ከእርሷ ሐሳብ ውጪ የሆነ ነው፤ ቀደም ሲልም ተከሳ ተወቅሳ የምታውቅ ልጅ አይደለችም፡፡ ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ይሄን ተመልክቶ ቅጣቱ በዝቅተኝነት ደረጃ እጅግ ቀሎ ቢቻል ቅጣቱ ወደገንብ ቢለወጥና በገደብ ቢደረግላት ስል ፍርድ ቤቱን እለምናለሁ ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ካደመጠ በኋላ ዐቃቤ ሕግ በአራተኛ ተከሳሽ ሂሩት ክፍሌ ላይ ያቀረበውን የቀድሞ የእስር ሪኮርድ በጽሑፍ በጽ/ቤት በኩል ከቀጠሮ በፊት እንዲያያይዝ፣ እንዲሁም የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኞቻቸው የቤተሰብ አስተዳዳሪ ስለመሆናቸው የሚያስረዳላቸውን የሠነድ ማስረጃዎች እንዲያይዙ ትዕዛዝ አስተላልፎ ችሎቱ ተበትኗል፡፡

Source: Addis Neger (ሙሉ ገ./አዲስ ነገር ኦንላይን)

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 20, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.