ፊፋ የኢትዮጵያን ውጤት “ሳይሰርዘው” አይቀርም (ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተንበታል)

(EMF) ለአለም ዋንጫ ማጣሪያ በሚደረገው ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡድን ከምድቡ 13 ነጥብ በማምጣት በ1ኛነት እየመራ ነው። ይህ ውጤት የተገኘው ቀሪ አንድ ጨዋታውን ሳይጨምር ሲሆን፤ እስካሁን በነበረው ሁኔታ በሴፕቴምበር ወር ላይ ከሴንትራል አፍሪካ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ቢያደርግም ባያደርግም ወደሚቀጥለው 3ኛ ዙር አልፎ ነበር። ሆኖም ዛሬ ፊፋ በድረ ገጹ ጭምር እንዳሳወቀው፤ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ቢጫ ያየ ተጫዋች ማሳረፍ ሲገባት፤ የፊፋን ህግ በመጣስ ስላጫወተች፤ ውጤቷ ሊሰረዝ እንደሚችል አሳውቋል። ዜናው ደስ የማይል ቢሆንም፤ መስማት እና ማንበብ የምንፈልገውም ቢሆን እንኳ የሆነውን ማወቅ አይከፋም በሚል ዝርዝሩን ቀጥሎ አቅርበነዋል።

fifa2

ይህ የሆነው ጁን 8 ቀን… ከቦትስዋና ጋር ባደረግነው ጨዋታ ቀደም ብሎ ቢጫ ካርድ አይቶ የነበረው ምንያህል ተሾመ ገብቶ በመጫወቱ ነው ተብሏል። ይህም የፊፋን አለም አቀፍ ጨዋታ ህግ አንቀጽ 8ትን የሚጥስ ነው ተብሏል። አንቀጽ 8፤ “እያንዳንዱ ተጫዋች ቅጣት የሌለበት ወይም መጫወት የሚችል መሆኑን ቡድኑ ማረጋገጥ አለበት።” ይላል። በርግጥም ምኑያህል ተሾመ በረስተንበርግ እና አዲስ አበባ ጨዋታ ላይ ቢጫ አግኝቷል። ስለዚህ ከቦትስዋና ጋር ባደረግነው ቀጣይ ጨዋታ መግባት አልነበረበትም። በመሆኑም ከቦትስዋና ጋር ተጫውተን ያሸነፍነው ጨዋታ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ይህም ከቦትስዋና ጨዋታ አልፈን፤ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያደረግነውንም ጨዋታ ውጤት ሊያበላሸው ብሎም ሊያሰርዘው ይችል ይሆናል፤ ተብሏል። ይህ ደግሞ 3 ነጥብ እንድናጣ ያደርገናል። 3 ነጥብ ካጣን ደግሞ ወደ 10 ነጥብ እንወርዳለን። ደቡብ አፍሪካም 8 ነጥብ ትሆናለች።

እንግዲህ ፊፋ በኢትዮጵያ ላይ ቅጣት ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አሳወቀ እንጂ፤ ቅጣቱ  ምን ሊሆን እንደሚችል ገና አልታወቀም። በኢትዮጵያ ቡድን ላይ ቅጣት ከተወሰነበት፤ አሁን ካለው ነጥብ ላይ 3 ነጥብ ጥሎ ሴፕቴምበር ላይ ከሴንትራል አፍሪካ ጋር ተጫውቶ ማሸነፍ ይገባዋል ማለት ነው። በዚያም ተባለ በዚህ ግን የፊፋ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ገና አልታወቀም። ፊፋ አሁንም ያለው ነገር ቢኖር፤ እርምጃ ለመውሰድ ጥናት እያደረኩ ነው የሚል ነው። ለነገሩ ፊፋ እየተመከተ ያለው የኢትዮጵያን ጨምሮ፤ ቶጎ እና ኢኩዋቶሪያል ጊኒም ማሰለፍ የማይገባቸውን ተጫዋቾች በማሰለፋቸው ጉዳያቸውን እየተመለከተ እንደሚገኝ ነው የገለጸው።

በህጉ መሰረት ሄደን 3 ነጥብ እንድናጣ ከተደረገ፤ ደቡብ አፍሪካ በቀጣይ ከቦትዋና ጋር ተጫውታ ካሸነፈች፤ እኛ ደግሞ በሴንትራል አፍሪካ ከተሸነፍን ደቡብ አፍሪካ 11 ነጥብ ስታገኝ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ እዚያው 10 ነጥብ ላይ ስለምትቀር በነጥብ ወድቀን ከውድድሩ ልንወጣ እንችላለን። አያድርገውና ምንም ቅጣት ካልተቀጣን ግን ከሴንትራል አፍሪካ ጋር ብንጫወትም ባንጫወትም (ፎርፌ ብንሰጥም)፤ ደቡብ አፍሪካ ከ3 ነጥብ በላይ ማግኘት ስለማትችል ማሸነፋችን የተረጋገጠ ይሆናል ማለት ነው። አሁን ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂዎቹ፤ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን በአንደኛ ደረጃ፣ የቀድሞው የቡድኑ መሪ አቶ አፈወርቅ ወይም የአሁኑ ቡድን መሪ አቶ ብርሃኑ፣ አሰልጣኞች አቶ ሰውነት እና አቶ ስዩም፤ በመጨረሻም ተጫዋቹ ምንያህል …በየደረጃው ስህተት ሰርተዋል። በመሆኑም በውጭ አገር እንደምናየው በስፖርታዊ  ጨዋነት፤ ፕሬስ ኮንፍረንስ አድርገው፤ ስህተታቸውን አምነው ህዝቡን ይቅርታ ማለት ይገባቸዋል። ሁሌ እንደሚደረገው በመሸፋፈን ማለፍ ጥሩ አይደለም። ከስህተት መማር አንድ ነገር ሆኖ፤ ስህተት ሲሰራም ይቅርታ ማለት መለመድ ያለበት ባህል ነው።

ምንያህል ተሾመ ቢጫ ያየበትን የረስተንበርግ ጨዋታ ወደኋላ መለስ ብለን እናስቃኛቹህ። በዚህ ጨዋታ ላይ ፋወል የሰራው ደቡብ አፍሪካዊው ስቲፈን ፒናር ነው። ሆኖም ዳኛው ቢጫ ካርድ የሰጡት ለምንያህል ተሾመ ነበር። የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ቢጫ የተሰጠው በስህተት መሆኑን፤ ቢጫው እንዲነሳለት ስለመጠየቁ ምንም መረጃ የለንም። በርግጥ ፌዴሬሽኑ “ያለአግባብ ቢጫ ተሰጥቶን ነበር” ብሎ አመልክቶ ከነበረና ውሳኔ ከተሰጠበት በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረው ክስ ተነስቶ፤ ቅጣቱ በገንዘብ ሊቀየር ይችል ይሆናል። ይህም ቢሆን ትንሽ ከበድ ይላል። በመሆኑም በህጉ መሰረት ከሄድን የፊፋ ህግ አንቀጽ 8 በመጣሱ ምክንያት… የቅጣት ስነ ስርአቱ  ቻፕተር  17፡4 መሰረት ቅጣቱ ተፈጻሚ ሊሆን ይችል ይሆናል። ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን እና ፊፋ የሚሉትን ከመስማት በቀር ብዙ የምንለው ላይኖር ይችላል።

የፊፋ “ቢጫ ካርድ ህግ” እያወዛገበ በመምጣቱ በተለያየ ጊዜ ሲቀያየር ሰንብቷል። ለምሳሌ ባለፈው የአለም ዋንጫ፤ በቡድን ደረጃ በሚደረግ ጨዋታ ወቅት፤ የሚሰጥ አንድ ቢጫ ካርድ ተጫዋቹ የሚቀጥለውን ወሳኝ ጨዋታ እንዳይጫወት የማያግድ ህግ ተሻሽሎ ወጥቶ ነበር። በሌላም ተጨማሪ የተሻሻለው የፊፋ ህግ መሰረት አንድ ቢጫ ካርድ የታየው ለዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው ጨዋታ ከሆነ፤ ተጫዋቹ ቀጣዩን ጨዋታ ሳይቀጣ መጫወት ይችላል። አሁንም በኢትዮጵያ ላይ የትኛው ህግ እንደሚጸና፤ ብሎም ቅጣቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ለማወቅ አዳጋች ሆኗል። ሆኖም ቅጣቱ ከፍ ካለ፤ ማስገባት የሌለብን ተጫዋች አስገብተን ያሸነፍንበትን ጨዋታ ውጤት እስከመሰረዝ ሊደርስ ይችላል። አሁን ዳኝነቱ በሜዳ ላይ ሳይሆን በቢሮ ደረጃ በመሆኑ፤ ኢትዮጵያ ክፉ ቅጣት እንዳያገኛት ጠንከር ያለ ስፖርታዊ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል።

አንድ ነገር ግን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከደቡብ አፍሪካ ጋር የተደረገውን ጨዋታ ጨምሮ፤ የኢትዮጵያ ተጫዋቾች በሜዳ ውስጥ የሚያሳዩት ስርአት የሌላቸው እንቅስቃሴዎች፤ ከአፍሪካ ቡድኖች በላቀ ሁኔታ የብዙ ቢጫ ካርዶች ባለቤት እያደረገን ይገኛል። ይህ ሁኔታ በአጭሩ ካልተቀጨ ብዙ ቢጫ ከማግኘታችን የተነሳ፤ ዘንግተን መጫወት የሌለበትን ተጫዋች አሰልፈን እስከማጫወት ደርሰናል። እናም ወደ አለም አቀፍ ፕሮፌሽናል ጨዋታ ስንቀላቀል፤ በክለብ ደረጃ የምናሳያቸውን አላስፈላጊ ስርአት አልባ እንቅስቃሴዎች ከወዲሁ ሊጤኑ እና ሊታረሙ ይገባል። የኳስ ችሎታ ብቻ ሳይሆን ስፖርታዊ ጨዋነትም አብሮ ይታሰብበት።

 

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 17, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.

4 Responses to ፊፋ የኢትዮጵያን ውጤት “ሳይሰርዘው” አይቀርም (ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተንበታል)

 1. kassu

  June 17, 2013 at 9:04 AM

  በጣም በጣም የሚገርም ድንቁርና እከሌ ከእከሌ የማይባል የብድን ድካምን የሚያመክኑ ሰዎች መሰባሰባቸው ይገርማል ከዚያም በላይ ተጫዋቹ አያውቅም እንዴ
  ምን ይባላል ደስታ ለዚያ ህዝብ ለተወሰኑ ቀናት እንኴ አብሮ እንዳይቆይ የተፈረደባት
  አዝናለሁ ህግ ህግ ነውና የሆነውን መቀበል ነው

 2. yoseph

  June 17, 2013 at 9:57 AM

  አቶ ሰውነት ቢሻው እንዲት ይህን ማመዛዘን አቅትዋቸው ለስህተት ተጋረዱ በውነቱ ያሳዝናል

 3. መስፍ ታድ

  June 17, 2013 at 10:21 AM

  ኢትዮጵያ ወደቀጣዪ ዙር ታልፋለች ግድየልም ምቀኝነት ዛሬ እልተጀመረም::

 4. አለም

  June 18, 2013 at 4:44 PM

  እንዲህ የመሰለ ስሕተት እንዴት ሊፈጸም እንደ ቻለ መገመት ቀላል ነው። ኮ/ል አወል አብዱራሂም የደደቢት ክለብ መሥራችና ባለቤት ናቸው። ምን ያህል ተሾመ በየነ የደደቢት ቡድን ተጫዋች ነው። ለብሔራዊ ቡድን ከሚሰለፉት አብዛኛዎቹ ከደደቢት ነው። ኮ/ል የህወሓት አባልና ታጋይ ናቸው። ደደቢት ክለብ ማለት ገንዘብ ማለት ነው። ፌዴሬሽኑና የመንግሥት አካላት በሙስና ለመዘፈቁ ምንም ማስረጃ ማቅረብ አያሻኝም። ሯጮቻችን ለአገራቸው እንደ መሮጥ ለአረብ አገሮች የሚሮጡት ፍትሓዊ አመራረጥና ድልደላ ስለሌለ ነው። አመራሩ ላይ የተሰየሙትን ባለሥልጣኖች ስም ይመልከቱ። በፌዴሬሽኑ ሆነ በመንግሥት ዘንድ የኮ/ል ተሰሚነት እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነው የሚሉ ቢኖሩ ወይ አታላዮች ናቸው ወይም ጅሎች ናቸው። አሁን የሚደረገው ሙከራ የምንያህል ስም ስለ ተቀያየረ አሳስቶ ነው ለማሰኘት ሙከራ እየተደረገ ነው። የአገርን ያህል ክብርና የሕዝብን ሞራል ሥራቸውን በግል ጥቅም በለወጡ ሰዎች ማበላሸት ማለት ይኸው ነው። ገና ምኑ ታይቶ? እስካሁን ያልተከሰቱ ስንት አሉ? ሕዝብ ዝም ብሎ ማለፍ የለበትም። ጥያቄው እስኪመለስ በዚህ ጉዳይ በንዝህላልነት ይሁን አውቀው በደል የፈጸሙ በሕግ መቀጣት ይኖርባቸዋል።