ጥሪ! ለሥርተከል አገራዊ ለውጥ

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ –

እስካሁን ከቱኒሲያ ተነስቶ ወደ ግብጽና ሌሎች አገሮች አሁን ደግሞ ወደ ሱዳን እየተዛመተ የመጣው የለውጥ እንቅስቃሴ የተጀመረውና እየተከናወነ ያለው በማንም ሳይሆን በሕዝብ ነው፡፡ በሕዝብ አነሳሽነት የሚደረግ የለውጥ እንቅስቃሴ በፖለቲካ ፓርቲዎች ጠባብ ፕሮግራም እስካልተጠለፈ ድረስ ውጤቱ ያማረ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ሰላምና ፍትሕ የማምጣት ዕድሉ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የአገራችንን ሁኔታ በተመለከተ ለተለያዩ አካላት የሚከተሉትን የድርጊት ሃሳቦች ለማቅረብ እንወዳለን፡፡

  1. 1.     ለኅብረብሔራዊና በጎሣ ለተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ለነጻአውጪ ግንባሮችና ንቅናቄዎች፡-

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ይህ እንቅስቃሴ ሕዝባዊ እንደመሆኑ በሕዝብ መነሳሳትና መመራት ይጠበቅበታል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ሕዝቡ የሚጠይቃቸውን በመመለስ የሕዝቡ አገልጋይ መሆን ነው እንጂ የሕዝቡን እንቅስቃሴ ለራሳቸው የፖለቲካ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ማድረግ አይደለም፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ድርጅት ትግሉን በመጥለፍና ለውጡን የራሱ ምርኮኛ በማድረግ ሕዝባዊ እንቅስቃሴውን የጥቃት ዒላማ ከማድረግ መቆጠብ አለበት፡፡ ይህ እንቅስቃሴ የሥልጣን ሽኩቻ የሚደረግበት ሳይሆን ሕዝባችን ነጻ የሚወጣበትና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መሠረት የሚጣልበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ 

በብሔር የተደራጁ ድርጅቶችም ሆኑ የነጻ አውጪ ግንባሮችም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም አገሪቷን ሊበታትን ከሚችል ድርጊት ፈጽሞ መቆጠብ ይገባቸዋል፡፡ ባለፉት ሥርዓቶች በርካታ የሕዝባችን ጥያቄዎች በሚፈለገው መልኩ አለመመለሳቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ስለሆነም የብሔር ተኮርና የነጻአውጪ ግንባሮች ጥያቄ ከዚህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ብቅ ብላ በምትወጣው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አብሮ የሚመለስ መሆኑን ተገንዝባችሁ ሕዝባዊውን ለውጥ መቀላቀል ይጠበቅባችኋል፡፡

  1. 2.     ለገዢው ፓርቲ አባላት፣ ካድሬዎች፣ ለመከላከያ፣ ለደኅንነት እና ለፖሊስ ሠራዊት፡-

ህወሃት/ኢህአዴግ ባለፉት 20 ዓመታት ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍሎ ለራሱ የሥልጣን ማራዘሚያ ሲያደርግ በተለይም የትግራይ ተወላጆችን እና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሲጠቀም ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ቢያደርጉት የማይከፋፈልና ‹‹ነብር ዥንጉርጉርነቱን እንደማይለቅ›› ፈጽሞ የማይለያይ ሕዝብ መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል፡፡ በመሆኑም ገዢውን ፓርቲ እስካሁን በወገናዊነትም ይሁን በግል ጥቅም በመነሳሳት ስትደግፉ የነበራችሁ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመከራ እየኖረ እናንተ ለፓርቲው ባላችሁ ታማኝነት ብቻ ‹‹በነጻነት›› ልትኖሩ አትችሉም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ሁሉም ነጻ ካልወጣ ማንም ነጻ መሆን አይችልምና››፡፡ ስለሆነም ይህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እናንተንም ነጻ የሚያወጣ መሆኑን በመገንዘብ ከሕዝብ ጋር የምትቆሙበትና ለትግሉ ድጋፍ የምትሰጡበት መልካም አጋጣሚ አሁን ነው፡፡ ዕርቅ ናፋቂውና መሐሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎኑ እስከቆማችሁ ድረስ ለእናንተም ነጻነት እንደሚታገል አስተውላችሁ አጋርነታችሁን በምታገኙት አጋጣሚ ሁሉ እንድትገልጹ እናሳስባለን፡፡

ሕዝባዊው ለውጥ በቱኒሲያና በግብጽ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት አገዛዞቹ የልዩ ጥበቃ ሠራዊታቸውን በሕዝቡ ላይ አዝምተው ነበር፡፡ ሆኖም ሠራዊቱና የልዩ ጥበቃ ኃይሉ የሰማው ለዓመታት ሲታዘዝ የነበረውን የመሪዎቹን ቃል ሳይሆን የሕዝቡን ነበር፡፡ በሕወሃት/ኢህአዴግ ትዕዛዝ የሠራዊቱ አካላት እንዲሁም የደኅንነቱ ክፍል በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ድርጊት ሲፈጽም መቆየቱ የማይካድ ነው፡፡ አሁንም ተመሳሳይ ድርጊት የመከላከያና የፖሊስ  እንዲሁም የልዩ ጥበቃው ኃይል እንዲፈጽም ከአቶ መለስ ትዕዛዝ ሊሰጠው ይችላል፡፡ የተሰጣችሁን ትዕዛዝ የምትፈጽሙት የኢትዮጵያ አብራክ ክፍይ በሆኑት ወገኖቻችሁ ላይ መሆኑን በማወቅ ከዳግመኛ ስህተት እንድትቆጠቡ እናሳስባለን፡፡ ‹‹ትዕዛዝ ነው የምፈጽመው›› በሚል ሰንካላ ምክንያት የኢትዮጵያን እናቶች ደግማችሁ እንዳታስለቅሱ፤ ይልቁንም ከወገናችሁ ጋር በማበር የሕዝባዊው ለውጥ አካል እንድትሆኑ በጥብቅ እናሳውቃለን፡፡

  1. 3.     ለተማሪና ለወጣቶች

በኢትዮጵያ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ተማሪዎችና ወጣቶች ከፍተኛውን ሚና እንዲሁም መስዋዕትነት ሲከፍሉ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑም የለውጥ እንቅስቃሴ ከፍተኛውን ሚና የምትጫወቱ እናንተ መሆናችሁ አይጠረጠርም፡፡ ስለዚህም ይህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሰላማዊና ሁከት አልባ ትግል እንዲሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ሕዝባዊ እንደመሆኑ የንግድ፣ የልማት፣ የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማት አደጋ ላይ ከሚጥል ተግባር በመቆጠብ በ1997 የታየውን ዓይነት ሰላማዊ የተቃውሞ ትዕይንት የማሳየት ብቃታችሁን እንድትወጡ ጥሪ እናደርጋለን፡፡ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከበቀልና ከጥላቻ ፍጹም የጸዳ እንዲሆንና ፍትሕን የምታገኙት ከመንገድ ላይ በኃይልና ሁከት ሳይሆን በአዲሲቷ ኢትዮጵያ በሚመሠረቱት የፍትሕ ተቋማት መሆኑን ተገንዝባችሁ ራሳቸውን ከጥፋት ልትጠብቁ ይገባል፡፡ እንቅስቃሴው በቴክኖሎጂ የመገናኛ ውጤቶች ብቻ የሚታገዝ ሳይሆን አገር በቀል በሆኑ የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችንም በመጠቀም በተለያዩ ቦታዎች በአንድ ጊዜ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የወጣቱና ተማሪው ኃይል የአጼ ኃይለሥላሴን ሥርዓት በገረሠሠበት ጊዜ ሕዝባችን አንዳሁኖቹ ፌስቡክና ትዊተር ይቅርና የስልክ አገልግሎት እንኳን በቅጡ እንዳልነበረው በማስብ ያሁኑ ትውልድ ብዙ የሚማረው አለ፡፡

4.  ለነጋዴና ሠራተኛው ኅብረተሰብ

በቱኒሲያና ግብጽ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት፣ የኑሮ ውድነትና ሥራአጥነት የለውጡን ሂደት እንዳቀጣጠለ በግልጽ የታየ ተግባር ነው፡፡ በኢትዮጵያም እየተከሰተ ያለው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ አይደለም፡፡ እንዲያውም ነጋዴውን ኅብረተሰብ ከሕዝቡ ጋር ለማቃቃር ሆን ተብሎ በሸቀጦች ዋጋ ተመን ሰበብ እየተፈጸመ ያለው ተግባር ነጋዴውን ከኅብረተሰቡ ጋር ይበልጥ ሊያስተሳስረው የሚገባ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ሠራተኛውም እንዲሁ በዚህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የዳር ተመልካች ሳይሆን ንቁ ተሳታፊ የመሆን ኃላፊነት አለው፡፡ ጊዜው ከዕለት ጉርሱ በላይ የሚያስብበት ምቹ ወቅት መሆኑን በመገንዘብ ነጋዴው ከፍቅረንዋይ፤ ሠራተኛውም ከመንግሥት ምንዳ ባርነት ነጻ በመውጣት የሕዝባዊ እንቅስቃሴው ደጋፊ አካል የምትሆኑበት ጊዜ አሁን ብቻ ነው፡፡

5.  ለሚዲያ እና በውጪ ላለው ኢትዮጵያዊ

በውጪ አገራት በሚዲያ ሥራ ማለት በሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ የዜና ድረገጾች፣ ወዘተ ላይ የተሰማራችሁ በሙሉ የዚህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አካል በመሆን ድጋፍ መስጠታችሁ የተሰማራችሁበት ሙያ የሚያስገድዳችሁ ነው፡፡ በመሆኑም ከወገናዊነት፣ ከጠባብነት፣ ከፋፋይነት፣ ወዘተ ፍጹም በጸዳ መልኩ ሕዝቡ ሊደርሰው የሚገባውን መልዕክት የማድረስ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡ ዘመኑ ባፈራቸው የቴክኖሎጂ እሴቶችና ሌሎች ከዚህ በፊት ያልተፈተሹ ስልቶችን በመጠቀም መረጃዎች ወደኢትዮጵያ የሚደርሱበትን መንገድ መቀየስ ቀዳሚው ተግባራችሁ ነው፡፡ በውጪ ያሉ ወገኖቻችንም እስካሁን ለአንድ ፓርቲ ወይም ድርጅት እንደሰጣችሁት ዓይነት የገንዘብም ሆነ የሌላ ድጋፍ ሳይሆን እንቅስቃሴው ሕዝባዊ እንደመሆኑ ራሳችሁን ቀስቃሽ፣ አደራጅና መሪ በማድረግ የምታገኙትን መረጃ አገር ቤት ለሚገኙት ቤተሰቦቻችሁ፣ ጎረቤቶች፣ ዘመዶቻችሁ፣ ወዘተ እንዲደርሳቸው በማድረግ የትግሉ አጋር እንድትሆኑ እናሳስባለን፡፡ ሕወሃት/ኢህአዴግ በነፍስወከፍ ካድሬ በማዘጋጀት ሕዝቡን ሸብቦ እንደያዘ ሁሉም የሚያውቀው ሃቅ ነው፡፡ በመሆኑም በውጪ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን እናንተም ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምሥረታ ከሕዝባችሁ ጋር በመሰለፍ የዚህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አካል ልትሆኑ ይገባል፡፡ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የምታገኙትን ዜና ለዓለምአቀፍ የመገናኛ አውታሮች – አልጃዚራ፣ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ወዘተ በማስተላለፍ የሕዝባችን ትግል ለዓለም እንዲደርስ የማድረግ ኃላፊነት የእናንተ ነው፡፡

6.  ለምሁራን

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ አገራት ውስጥ ምሁራን ከፍተኛ ተደማጭነት አላቸው፡፡ የሚናገሩት ቃልም ሆነ የሚሰጡት አስተያየት ብዙሃኑ በአንክሮ የሚከታተለው ነው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በድሃ አቅሟ ያስተማረቻቸው ምሁራን ጥቂት አይደሉም፡፡ በዚህም ምክንያት የለውጥ እንቅስቃሴ በሚካሄድበት አጋጣሚ ሁሉ የምሁራን ሚና ከፍተኛ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ ውስጥም ይሁን በውጪ ያላችሁ ኢትዮጵያዊ ምሁራን የዚህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አካል መሆናችሁ ለሕዝባችሁ ከምታበረክቱት መልካም ነገሮች በዋንኛነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ሕዝባዊው እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን አቅጣጫ ጠቋሚ የሆኑ ሃሳቦችን በድፍረት በማፍለቅ ለትግሉ ውጤታማነትና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምሥረታ የበኩላችሁን አስተዋጽዖ የምታደርጉበት ታሪካዊ አጋጣሚ አሁን ነው፡፡

በመጨረሻም – ይህ በ‹‹ግፋ በለው›› እና በ‹‹ተነስ›› ትዕዛዝ የሚጀመር ትግል ሳይሆን ጀማሪውም መሪውም ሕዝብ መሆኑን እንዲሁም ነጻነታችን ከፈጣሪ የተሠጠን እንጂ ከምዕራባውያን የሚቸረን አለመሆኑን ንቅናቄያችን በጽኑ ያምናል፡፡ ስለሆነም ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ነጥቦች ላይ በተከታታይ መግለጫዎችን የምናወጣ ሲሆን ይህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ፍትሕ እንደሚያስገኝ ንቅናቄያችን ያለውን ሙሉ ዕምነት ይገልጻል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ የሕዝባችን የነጻነት ጥያቄ የሚመለስበት፣ ለዘመናት ባገራችን ለተንሰራፉ ችግሮች የመፍትሔ መሠረት የሚጣልበት፣ ሰላምና ብሔራዊ ዕርቅ የሚሰፍንበት፤ ‹‹ከዘረኝነት ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጥባት›› አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትገነባበት ይሆናል፡፡

ስለሆነም እንደ ነብዩ እንባቆም ‹‹አምላክ ሆይ ስንጮህ የማትሰማን እስከ መቼ ነው? ከሚፈጸምብን ግፍ የማታድነን እስከ መቼ ነው?›› በማለት በየእምነታችን ‹‹የኢትዮጵያን እጆች ወደ ፈጣሪ እንዘርጋ››፡፡

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

***************************************************************************************************

ለዚህ ደብዳቤ ምላሽም ሆነ ለተጨማሪ መረጃ ዋና ዳይሬክተሩን ለአቶ ኦባንግ ሜቶ (obang@solidaritymovement.org) በመጻፍ ወይም በስልክ (202) 725 -1616 በመደወል ወይም ድረገጻችንን (www.solidaritymovement.org) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 3, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.