ጠቅላላ ዕውቀት ፤ ይህን ያውቁ ኖሯል? – አዲስ ጉዳይ መፅሔት

አሁን የምናስነብባችሁ የሀብታሙ ስዩምን ስራ ነው፡፡ የሀምሌ 20 2005 ዓ.ም አዲስ ጉዳይ መፅሔት ላይ የወጣ ነው፡፡ በጣም የወደድነው ፅሁፍ ነው! አንብባችሁ ስትጨርሱ የተሰመችሁን ስሜት አስፍሩት፡፡ ወዳጆቻችሁ እንዲያነቡት ደግሞ ተጋሩት! መልካም ንባብ!

አባቶቻችን ወለዱን እንጂ የአባቶቻችን ልጆች አይደለንም፡፡
(ሀብታሙ ስዩም)

አባትህና አባቴ አብሮነታቸውን እየዘከሩ በሳቅ ይርገፈገፋሉ፡፡ግዴለም ይሳቁ ቢያንስ እስካሁን ጸረ-ሳቅ አዋጅ አልወጣም፡፡
‹‹ወይ መሃመድ በሳቅ ገደልከኝ እኮ¡››
‹‹እነ ጃዋር በሜንጫ ከሚገድሉህ እኔ በሳቅ ብገድልህ ይሻላል ብየ እኮነው – ተክለማሪያም፡፡››
አባትህና አባቴ እንዲህ ናቸው፡፡ እኔና አንተ ለፍልሚያ ቀን የምንቆርጥበትን ጉዳይ እነሱ ቀልድ ብቻ ይመዙበታል፡፡
አባትህና አባቴ እዚህ ካፌ ከገባን ጀምሮ ጥርሳቸው አልተከደነም፡፡
አንተና እኔ ግን ጥርሳችን አልተፈለቀቀም፡፡
በልብህ ትዝትብኛለህ…በውስጤ አንገራግርብሃለሁ፡፡
‹‹አንተን ለመድፋት አንድ ተምር እስኪቀር እፋለምሃለሁ፡፡›› ስትል ይሰማኛል፡፡
‹‹አንተን ለመቅጨት የሊቀ መልአኩን ጎራዴም ቢሆን እዋሳለሁ፡፡›› ስል ይሰማሃል፡፡
‹‹ ተጫወቱ እንጂ !››ይሉናል ጠረጴዛ የተጋሩን አባቶቻችን
‹‹እንጫወታለን !››እንላለን ባዶ ብርጭቆ የምናማስል ልጆቻቸው፡፡
እንደማንጫወት እናውቀለን፡፡
አንተ ከቃፊር ጋር ወሬ ትተሃል፤
እኔ ከአህዛብ ጋር ንግግር አቁሜያለሁ፡፡
ያ ፖለቲከኛ የዘራብህ ጥላቻ ፊትህ ላይ አብቧል፤
ያ አወቅሁባይ የጋተኝ ንቀት ፊቴ ላይ አብለጭልጯል፡፡
አባትህና አባቴ የኔና አንተን ጠላትነት ወዳጅነታቸው ሸፍኖታል ፤ጨዋታቸው ደምቋል፡፡
‹‹መሃመድ እንጂ››
‹‹ወየ ተክሌ!››
‹‹ትዝ ይሉሃል ፊደል ያስቆጠሩን ቄሰ ገበዝ ድልነሳ!››
‹‹የስንቱን ተማሪ ጆሮ ያስረዘሙትን ሰው እንዴት እረሳለሁ፡፡ ሳስበው ሳስበው ከሃጂ ሰመተር ጋር መንታ ይመስሉኛል !››
‹‹ ትክክል ብለሃል ሁለቱም የተማሪ ጆሮ እንደደማካሴ ማልመዝመዝ ነፍሳቸው ነበር፡፡››
‹‹ግን እኮ ሃጂ ሰመተር ይወዱህ ነበር››
‹‹ለምን አይወዱኝ እጃቸውን ቢዘረጉ የማያጡት ጆሮ ነበረኝ፡፡››
‹‹ አይ ተክሌ – ሆነም ቀረም ሁለት ውለታ ውለውልህ አልፈዋል፡፡››
‹‹ እርግጥ ነው የመጀመሪያው ውለታቸው ጆሮየን የጥንቸል ማድረጋቸው ነው፤ሁለተኛውና የማልረሳው ግን በአረበኛን የተነጠሰች ነገር እንዳታልፈኝ ማስተማራቸው ነው፡፡ መምህሬ ድልነሳ ደክመዋል አሉ፡፡ ‹በዚህ ሰሞን መጥታችሁ ጠይቁኝ ብለዋል፡፡ ‹‹በተለይ ሙሃመድ ያኔ ከፊደል ቀ ሣትዘል ስላቋረጥክ በዚህ ሰሞን ቤቴ ናና እስከ ፐ እንጨርሳለን ብለውሃል፡፡››
‹‹‹ሀሀሀ አላሉህም…እያንዳንድሽን መጀመሪያ ፊደል በመቀጠል ሳንቲም መቆጠር ያስተማርኩሽ እኔ አይደለሁሁሁ…ሀሀሀ››

ሰማህ አይደል…አባትህ ሙስሊም ናቸው ፊደል የቆጠሩት ግን ከክርስቲያን ተማሪዎች ጋር ከቄስ እግር ስር ነው፡፡ እኔም ሰምቻለሁ አባቴ አረበኛ የተስተማረው ከሙስሊም ብላቴናዎች ጋር ከሼክ ጥላ ስር ነው፡፡ ለአባቶቻችን ኢማምና ጥምጣም ልዩነት የላቸውም፡፡ ሁለቱም እውቀትና ስክነት በሞላባቸው ጭንቅላቶች ላይ የሚታሰሩ ማዕረጎች ናቸው፡፡ አየህ አባቴና አባትህ ደጎች ነበሩ፡፡ እኔና አንተ ግን ደደብ ነን፡፡
ተማሩልን ብለው ውጭ ላኩን ተምረን መጣን፡፡
ጀነት የሚገባው በክርስቲያን ወንድምህ ላይ ክንድህን ሳይሆን ሜጫህን ስታሳርፍ እንደሆነ ያ ከንቱ ነገረህ፡፡ ገነት የምትቀርበኝ በሙስሊም አብሮአደጌ ልብ ላይ ፍቅር ሳይሆን ጦር ስቀበቅብበት እንደሆነ ያ እንከፍ አስተማረኝ፡፡ አስተማሪያዎቻችን የጀሃነም ሃገር አክሲዮን አባላት መሆናቸው ግን ታይቶን አያውቁም፡፡ የኛ መማር ልዩ የሚያደርገው ይሄ ነው የመምህራችን እንጂ መምህራችንን የፈጠረው አምላክ ድምጽ አይሰማም፡፡
አባቶቻችን ወሬያቸው ደርቷል፡፡
‹‹ተክሌ እንጂ ››
‹‹ወየ መሃመድ››
‹‹አብማ ማሪያምን ያህል ደብር አስጠግናለሁ የሚል ኮሚቴ የኔ ገንዘብ ሃጢያት ይሆንብኛል ብሎ ነው ያልተቀበለኝ፡፡ ››
‹‹ወግድ እንደችኩል ፖለቲከኛ የምን ነገር ማንሻፈፍ ነው፡፡ anger first ሆንክ እንዴ፡፡ ››
‹‹ኧረ እኔ ETHIOPIA FIRST ነኝ gojjam first መሆንም መብቴ ነው እዚህ ሃገር መጥበብ እንጂ መጠበብ ምሁር ማስባሉን ትቷል፡፡ ግን ለምን አልተቀበሉኝም?››
‹‹ …ባንተ ስም እኔ ቀድሜ ስለከፈልኩ ነዋ፡፡››
‹‹እኔ ብር አጣሁ አልኩህ?››
‹‹እኔ ብር አጥቸ ነው መስጊድ የተተከለ ጊዜ ለእኔ የከፈልክልኝ፡፡…››
‹‹ሃገር መከፋፈል ወንጀል ባለሆነበት ዘመን መወጮ መክፈልን ወንጀል አደረከው እኮ፡፡››
‹‹ይሁንልህ እኔ በዚህ ሰሞን ‹ሁልህም በሃይማኖትህ መሽግ› በሚለው አዋጅ ሰፈራችንንም የነካት መስሎኝ ነው፡፡››
‹‹አይ እሱንስ ተወው የብዙአየሁን ታሪክ እየሰማ እንዲህ ባለ ጅልነት አይዘፈቅም፡፡››
አባቶቻችን የብዙአየሁን ታሪክ እያሰቡ ፈገግ አሉ፡፡
ልጆቻቸው ያወሩትን እያሰብን ብልጭ አለብን፡፡
ሰማህ አይደል ሙስሊም አባትህ ለደብር ማስጠገኛ ያዋጣሉ፡፡ እኔም ሰምቻለሁ ክርስቲያን አባቴ ለመስጊድ ማሳዳሻ ይሰጣሉ፡፡ ለአባቶቻችን ሁለቱ ልዩነት የላቸውም፡፡ ሁለቱም ፈጣሪ እያፈራረቀ የሚያርፍባቸው ቤቶቹ ናቸው፡፡ አየህ አይደል አባትህና አባቴ ነፍሶች ናቸው እኔና አንተ ግን ነፈዞች ነን፡፡
ተማሩልን ብለው ውጭ ላኩን ተምረን መጣን፡፡
በዚያ ረህመት የሚገኘው አድባራት ላይ እሳት ስትለቅ እንደሆነ አስተማሩህ፡፡ በዚያ ረድኤት የሚገኘው መስጊዶችን ማቆሚያ ስትነፍግ እንደሆነ አስተማሩህ፡፡ አስተማሪዎቻችን እኔና አንተ በምንፈጥረው እሳት ስለሚያበስሉት የግፍ እራት አስበን አናውቅም፡፡ የኛ መማር ልዩ የሚያደርገው ይሄ ነው የመምህሮቻችን ማበረታት እንጂ መምህሮቻችንን የፈጠራቸው አምላክ መባባት አይሰማንም፡፡
‹‹የብዙአየሁን ታሪክ ተርክላቸውማ መሃመድ!››
‹‹ባንተ ያምራል እኔ መተርከክ ላይ እንጂ መተረክ ላይ እስከዚሁ ነኝ፡፡››
‹‹‹ሀሀሀሀ ይሁን እንግዲህ …ብዙአየሁ ታወቂ የጎጣችን ነዳይ ነው፡፡ የት ይደርሳል የተባለ ተማሪ ነበር…ኋላ ላይ ውሎው በብዙ ጥበት እና በትንሽ እውቀት ከተሞሎ መጽሃፍትና ወና ራሶች ጋር ሲሆን ነገር ተበላሸ፡፡ ብሄር ነክ ጠቦች ላይ ከድንጋይ በመቀጠል የሚገኝ ሰው ብዙአየሁ ሆነ፡፡ከዩኒቨርሲቲ ተባረረ ወደ ጎጣችን መጣ ችግሩ ባሰበት ከሰው መግባበት ከበደው ጎዳና ወጣ ተቸግሮ ሞተም፡፡
ብዙአየሁ የሞተው ተርቦ ነው፡፡ የገደለው ግን የሰፈሬው ንፍገት ሳይሆን የሱ ጥበት ነበረ፡፡
በሞቱ ሳምንት የሆነው እንዲህ ነው፡፡
አንድ ፈረንጅ ቀረበው አንድ ብር አውጥቶ ሊሰጠው ዘረጋ ፡፡ብዙአየሁ ‹‹ከሊጥ መሳይ ነጭ ዳረጎት አልቀበልም!›› ብሎ አስቀየመው፡፡
በነጋታው አንድ ጥቁር አሜሪካዊ ሊመጸውተው ተጠጋ፡፡ ብዙአየሁ ‹‹ከአፍሪካ ውጭ ከተወለደ ባሪያ አልቀበልም!›› ብሎ አስቀየመው፡፡
በሶስተኛው ቀን ናይጄሪያዊ ሰው ሊሰጠው ቀረበው፡፡ ብዙአየሁ ‹‹በቅኝ ተገዥ ከነበረ ጥቁር አልቀበልም!›› ብሎ አስቀየመው፡፡
በአራተኛው ቀን ኢትዮጵያዊ አባት ‹‹ ያዝ ስሙኒ አሉት፡፡ ብዘአየሁ ‹‹ከነፍጠኛው ስርአት ርዝራዥ ስሙኒ አልቀበልም!›› ሃይማንዎትዎም ከኔ አይገጥምም ብሎ አስቀየማቸው፡፡
በአምስተኛ ቀን ከሚፈልገው ብሄር እና ሃይማኖት የመጣ ጎረምሳ ድፍን አስር ብር ‹‹ተቀበለኝ ››አለው፡፡ ብዙአየሁ ‹‹ከሰፈራችን ሰው ካልሆነ አልቀበልም !››አለ፡፡
በስድስተኛው ቀን ከሰፈሩ ሰዎች መጠው እንርዳህ አሉት፡፡ ብዙአየሁ ግን ‹‹ከእኛ ቤት ካልመጣ በቀር አልቀበልም፡፡›› ብሎ አስቀየማቸው፡፡
ለናት ለባቱ ብቸኛ ልጅ እሱ ብቻ ነውና በቀጣይ ቀን የመጣለት ሰው ከእነሱ ቤት ሳይሆን ከመዘጋጃ ቤት ነበር፡፡
ሰማህ አይደል አባትህ የመጥበብ መጨረሻ መጥፋት እንደሆነ የተማሩት ድሮ ነው፡፡ ሰማሁ አይደል አባቴ የመጥበብ ዳርቻ መተላለቅ እንደሆነ የተማሩት ጥንት ነው፡፡ ለአባቶቻችን ሰው ሁሉ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁሉም ተመሳሳይ የፈጣሪ መንፈስ የተሞላባቸው ባለ ብዙ ቀለም መስፈሪያዎች ናቸው፡፡
አየህ አይደል አባትህና አባቴ ቅኖች ናቸው እኔ እና አንተ ግን ቅልራስ ነን፡፡ በዚያ ለሃይማኖትህ ያለህ ክብር የሚለካው በረፈረፍከው እሬሳ ክምር እንደሆነ ነገሩህ፡፡ በዚያ ለምወደው ፈጣሪ ያለኝ መውደድ የሚገለጸው በቀነጠስኩት አንገት ቁልል እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ የኛ መማር ልዩ የሚያደርገው ይሄ ነው፡፡ የገፋፊዎቻችን መንደቅደቅ እንጂ ገፋፊዎቻችንን የፈጠራቸው አምላክ መንሰቅሰቅ አይታየንም፡፡
‹‹ ተጫወቱ እንጂ !››ይሉናል አባቶቻችን
‹‹እንጫወታለን !››እንላለን ልጆቻቸው፡፡
እንደማንጫወት እናውቀለን፡፡
እንጫወት ካልንም ጨዋታችን መጀመር ያለበት የአባቶቻችን ልጆች ከመሆን ጀምሮ ነው፡፡
እስከ አሁን አባቶቻችን ወለዱን እንጂ የአባቶቻችን ልጆች አይደለንም፡፡ እነሱ በፈጣሪ ስም የሚተዛዘኑ መላእክቶች ናቸው፡፡እኛ ግን በፈጣሪ ስም የምንፋጅ ሰይጣኖች ነን፡፡

→ →
መፅሔት – አዲስ ጉዳይ
አምድ – ኑሮ
ርዕስ – ‹‹አባቶቻችን ወለዱን እንጂ የአባቶቻችን ልጆች አይደለንም፡፡››
ፀሀፊ – ሀብታሙ ስዩም
ወቅት – ሐምሌ 20 2005 ዓ.ም

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 31, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.

3 Responses to ጠቅላላ ዕውቀት ፤ ይህን ያውቁ ኖሯል? – አዲስ ጉዳይ መፅሔት

 1. Fasamtigre

  July 31, 2013 at 4:10 PM

  Very good article,unity is important.may god destroy woyanne

 2. Tola

  August 1, 2013 at 4:05 PM

  Our fathers have never been friends and we will never be. Our history shows we had been fighting each other for long time before Menelike got modern weapon to get the upper hand. Do you guys really know what it means to be friends? How can we chat as we speak different languages? We can’t sit together because you guys are descendants of kings and we were created to serve you. Sorry, we are different! !!

 3. Dechas

  August 1, 2013 at 4:55 PM

  dear tola,
  what you say is not true. Indeed, there was conflict and war in Germany, Ethiopia and UK sometimes ago. There was no modern country today, that able to form the current map without conflict and war. Ethiopia can’t be different.

  However, even yesterday, there was such a friendship between our fathers. I was fed from the burst of my Muslim friend, and he too. We celebrated from hear Muslim holidays, and they did ours. I prayed in Christian church constructed in collaboration.

  The current situation comes due to the wrong TPLF propaganda! That is all about. When they were at dedebit, they planed that, making rift between Muslim and Christians, via encouraging Muslims and suppressing Christians. That is how the current Muslims generation was pushed to learn flawed facts. It was done on purpose, a bomb tplf has cultivated for bad days. But Muslims and Chrstians were friends and it never went the way tplf wanted to go. But i have to believe they are also successful, at least in cultivating some like Jawar. educated but think less than our fathers who never went to even local school, leave along famous one where jawar went.

  An educated but useless generation! what is education if it cant answer at least simple questions?