ግቡን የሳተ ቀስት! (አዲሱ የ ‘ኢሕአፓ’ ጠላት? …ነጻው ፕሬስ!)

(ከአትክልት እና ጓደኞቹ)

የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ላለፉት 20 ዓመታት በእሳት የተፈተኑ ቁርጠኞች ናቸው። እስርና እንግልቱን በተደጋጋሚ የወጡበት የወረዱበት ሸክም ነው። በጠራራ ፀሀይ በወያኔ ጥይት የተገደሉትን መርሳት ይከብዳል። ህክምና ተነፍገው ዘብጥያ ውስጥ የሞቱትንም ማስታወስ እንዲሁ… ይሰቀጥጣል። ዛሬም ወፍራም ወፍራም ክስ ተለጥፎባቸው ቃሊቲ ውስጥ የሚጉላሉትንም ልብ ይሏል።

 ይህ ሁሉ ፈተና ሀሳባችንን በነጻ የመግለጽ ተፈጥሯዊ መብታችንን አናስነካም በማለታቸው ነበር። በአቋማቸው እንደጸኑም ይኸው ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ከአቅም በላይ ሆኖባቸው የሚወዷትን ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱትም “ሩጫችንን” ጨረስን አላሉም። በያሉበት ከተማ በሬዲዮኖች ላይ ይሰራሉ ወይ ጋዜጣና መጽሔት ያሳትማሉ። አልያም በግልም ሆነ በጋራ እየሆኑ ድረ ገጾች ከፍተው ይንቀሳቀሳሉ። በቴሌቭዥን መስኮቶችም ቢሆን የተሰደዱለትን ሙያ ገፍተውበታል። ድሮም ትግላቸው ለሙያ ነጻነታቸው፤ ትላንትም ፍቅራቸው ለኢትዮጵያዊ ወገናቸው፤ ቀድሞም ህልማቸው ውዷ ሀገራቸው ነበረችና ትግላቸውን ቀጥለዋል… በየፈርጁ።

 እናም በቅርቡ የቀድሞውን አምባገነን የኮሎኔል መንግስቱን መጽሀፍ ያሳተመው የፀሐይ አሳታሚ ባለቤት አንዱ ነው። በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነትን እንዲከበር ከደከሙና እንደሻማ ከሚቀልጡ ወጣቶች መሀል ኤልያስ በትልቁ የሚጠቀስ ነው። ልክ እንደ ማናቸውም የዲሞክራሲ አላሚ ሁሉ ሕዝብ የማወቅ መብት አለው ብሎ የሚያምን ብርቱ።

 የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች ይህ ሁሉ ፈተና፣ ይህ ሁሉ መከራ፣ ይህ ሁሉ አፈና ሲካሄድባቸው የቆየው በገዥው የወያኔ መንግስት ነው። መክሰስ፣ ማሰርና ማንገላታት በማይታክተው፤ እንዲያም ሲለው ‘ማሰር ሰለቸኝ’ ብሎ በወታደሮቹ ተመክቶ የሚፎክረው አቶ መለስ ነበር። እነሆ አሁን ደግሞ አዲስ ጠላት፣ አዲስ ባላንጣ የተነሳ ይመስላል። …ኢሕአፓ።

 ብዙ ሰዎች በተለይም ‘ፓርቲው ህይወቴ ነው’ ብለው በመንቀሳቀሳቸው በደርግ ቡጢ የተደቆሱት ‘አሁንም አለን’ የሚሉትን የድሮ ጓዶቻቸውን ሲታዘቡ ቆይተዋል። መተኪያ የለሽ ዋጋ የከፈሉላት ድርጅታቸው የሞተችው በ70ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው ባይ ናቸው። የተወሰኑት ግን ላለፉት 30 ዓመታት በአንድ ግለሰብ መዳፍ ውስጥ መሾራቸው ሳይቆጫቸው ‘አለን’ ብለዋልና “የላችሁም’ አላልናቸውም። “አልሞትኩም ብየ አልዋሽም’ እስኪሉን ድረስ ሀሳባቸውን በነጻ እንዲያንጸባርቁ ነጻው ፕሬስ መድረክ ሆኗቸው ቆይቷል። በርግጥ ከስድብ ውጭ ተግባር የላቸውምና በየጊዜው ባንጠቅሳቸው ችግሩ የራሳቸው ነው። በዚህ መበሳጨትም አልነበረባቸውም።

 ኢሕአፓ በአንድ ዘመን ኃያል ድርጅት ነበር። እያደር እኔ በቆፈርኩት ቦይ ያልፈሰሰ ሁሉ ጠላቴ ነው ባይ ሆነና ተረት ሆኖ ቀረ። ያ… ትላንት በሚሊዮናት ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ የክብር ቦታ የነበረው ድርጅት ራሱን በራሱ ሲገዘግዝ… የተሻለ ሀሳብ ባቀረቡት ላይ ሁሉ የምላስ ጦር ሲመዝ ኖሮ… ኖሮ… እነሆ አሁን ትዝታ ብቻ ሆነ፤ ዛሬ ዛሬ በመላ ዓለም የተበተኑ አባላቱ ከመመናመናቸው የተነሳ ምናልባትም ‘በስም ሳይቀር ይተዋወቃሉ’ እየተባለ እስኪቀለድበት ደረሰ … ያሳዝናል።

 እንደነሱ በወሬ ሳይሆን በተግባር ከወያኔ ጋር ተፋጠው ሲታሰሩና ሲንገላቱ የኖሩ ተቃዋሚዎችን ሳይቀር ‘ስድብ’ በተባለች ብቸኛ ኃይላቸው ሲያዋርዷቸው ኖሩ። ሁሉንም አዳርሰው ጨረሱ መሰል ዛሬ ደግሞ ዘመቻቸው ወደ ነጻው ፕሬስ ቤተሰብ ዞሯል።

 “ትጽፉና ዋ!”፣ “ታሳትሙና… ዋ! አከስራችኋለሁ!” ይሉን ጀመር። የዚያ ስለዲሞክራሲና ሀሳብን የመግለጽ መብት መከበር ሺ-ምንተሺ ታጋዮችን የሰዋ ድርጅት ስም ለዚህ አሳዛኝ ተግባር ሲውል ከማየት በላይ የሚያሸማቅቅ ነገር ምን አለ?…

 ደብተራው

ይህ ስም ልባዊ ክብር ሊቸረው የሚገባ የአንድ የቀድሞ ታጋያቸው የትግል ስም ነው። የቀድሞ ያልነው አንድም በወያኔ እጅ ከወደቀ ከ2 አስርት ዓመታት በላይ በመቆጠሩ… ሁለትም በስሙ የተቋቋመው ድረ ገጽ እየሰራ ያለውን ስራ ቢያይ እንዴት ሊሸማቀቅ እንደሚችል በማሰብ ነው።

ደብተራው ተዋጊ ነው… ደብተራው ጸሃፊ ነው… ደብተራው አንባቢ ነው… ደብተራው ጽሁፍን አይፈራም። ደብተራው እንኳን መስተዋት ቤት የተቀመጡትን ኮሎኔል መንግስቱን ይቅርና የማንንም ጽሁፍ በብእሩ የመመከት ብቃት ያለው ጀግና ሰው ስም ነው።

 ይህ ሰው በእውነተኛ ስሙ ጸጋየ ገ/መድህን ይባላል። አውሮፓ ተቀምጦ ሲሳደብ የኖረ ሳይሆን በኢትዮጵያ ደንና ተራሮች ላይ ሲዋጋና ሲያዋጋ የኖረ ሰው ነው። ወያኔ ለስልጣን ከበቃ ከጥቂት አመታት በኋላ እስር ቤት እንደነበር አንዳንድ ሰዎች መስክረዋል። ዛሬ ድረስ በህይወት ስለመኖሩ ግን ማስረጃ አልተገኘም።

 የዚህን ላመነበት አላማ ግንባሩን የሰጠ ጀግና የትግል ስም የነጠቀው ድረ ገጽ ደግሞ በአንድ ለንደን በሚኖር ግለሰብ ስም ነው የተመዘገበው። ከአዘጋጆቹ ውጭ ሌላ አንባቢ የሌለው ስለመምሰሉም የድረ ገጽ አወዳዳሪ ኔትዎርኮችን ተጠቅሞ ማንም ሰው ማረጋገጥ ይችላል።

 ይህ ድረ ገጽ የአቶ እያሱ ኢህአፓ ልሳን ስለመሆኑ ብዙ ሰዎች ይናገራሉ። “ደብተራዎች”ም ሲያስተባብሉ ታይተው አያውቁም። ‘ፓርቲ’ውም ሲኮራባቸው እንጂ የኔ አይደሉም ሲል አልተደመጠም።

 ይህ ‘ልሳናቸው’ ታዲያ የዚህ ትውልድ ፍሬዎች ምን ማሳተም እንዳለብን… ማንስ ምን መናገር እንደሚችል ሊቆጣጠረን ደፈረ። …ያሳፍራል። ራሱን በራሱ የዲያስፖራው የሳንሱር ክፍል ኃላፊ ለማድረግ የደፈረው ደግሞ በአለም ዙሪያ ያሉ አባላቱና ደጋፊዎቹ ቁጥር ከአንዲት ጥንጥዬ የመንደር (የገጠር ቀበሌ) ህዝብ ቁጥር ጋር እንኳን በማይስተካከሉበት ሁኔታ ላይ ቆሞ ነው።… ቢዘገንንም ያስቃል።

 ግን ደግሞ እነዚህ ጥቂት ሰዎች ጉልበቱ ቢኖራቸው ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማሰቡም ተገቢ ሳይሆን አይቀርም። መቼም ላለፉት 20 አመታት ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት እንዲከበር ከወያኔ ጋር የታገለው ህዝብ ጭራሹኑ ወደ ዘመነ ደርግ ሲመለስ ማየት የሚወድ አይደለም። ኢህአፓ ግን ቢያንስ ይህን የአእምሮ ነጻነት በተመለከተ ከኮሎኔሉ ስለመሻሏ አንዳችም ምልክት አላየንም።

ቀስቱ በኮሎኔሉ ላይ ወይንስ በነጻው ፕሬስ?

‘ደብተራው’ የኮሎኔል መንግስቱን አዲስ መጽሀፍ በድረ ገጹ ሲለቀው በእርግጥ ኮሎኔሉን ለማጥቃት አስቦ አይደለም። ይህ ትውልድ የማወቅ መብቱን ለመገደብ እንጂ። ኮሎኔሉማ ብር ይዘው መኮብለላቸውን ድረ ገጹ ሚሊየን ጊዜ ሲያትት ሰንብቷል። ለአስረጅ ያህል ጥቂት ነጥቦች ማቅረብ ይቻላል።

1 – የኢህአፓ መሪዎች ባለፉት 20 ዓመታት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲነግሩን የኖሩት ኮ/ል መንግስቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ዘርፈው ስለመኮብለላቸው… ዚምባቡዌ ውስጥ ሰፊ እርሻ አቋቁመው ተንቀባረው ስለመኖራቸው ነበር። ይህንን አባባል እኛም እንጋራዋለን። ቢያንስ ቢያንስ ኮሎኔሉ አንድም አይነት የኑሮ ችግር እንደሌለባቸው እናምናለን። ከሀራሬ የሚታተሙ (ዘ-ዚምባቡዌያን የተሰኘውን ጋዜጣ ጨምሮ) የአገሪቱ የፕሬስ ውጤቶችም ሲመሰክሩ የኖሩት ይህንኑ ነው። …አቤት የቪላቸው ውበት?… የጠባቂዎቻቸውስ ብዛት?… በዚያ ላይ የእርሻቸው ስፋቱ?… ሌላም ሌላም።

ስለዚህ ኮሎኔሉን በገንዘብ ለመቅጣት ታስቦ የተወሰደ እርምጃ ተደርጎ መገለጹ ውሸት ነው። ይልቅስ ኮ/ሉ የሚፈልጉት መነበብ ነው። ‘ደብተራ’ዎች ሳያውቁትም ቢሆን ሊያግዟቸው ነበር የሞከሩት… እንደ አለመታደል ሆነና ገጻቸው ጎብኝ ስለሌለው እንዲሁም የብልግናቸው ተባባሪ መሆን የሚፈልግ ባለመኖሩ ለራሳቸውም ሳይሆኑ ኮሎኔሉንም ሳይጠቅሟቸው ቀሩ።

2 -ኮሎኔሉ ገንዘብ ኖራቸውም አልኖራቸው “የደም ገንዘብ “ ሊሰበሰብ አይገባውም። እርምጃየም ህጋዊ ነው የሚል አይነት አቋምም ለማንጸባረቅ ሞክረዋል። ይህም የለየለት ውሸት ነው። ከመሰረቱ ፕሪንሲፕል አለኝ ለማለት ቢሆን ኖሮ መጽሀፉ በታተመበት፤ እነሱም ህጉን አዛብተው ባጣቀሱበት የዲሞክራሲ ሀገር እንዳይታተም በፍርድ ቤት በከሰሱ ነበር። ከታተመ በኋላም ቢሆን ኮ/ሉ የገንዘብ ጥቅም ሊያገኙ አይገባም ብለው በሞገቱ ነበር። ልክ የህግ የበላይነትን እንደሚያውቅ ዲሞክራት ማለት ነው። እነሱ ግን ራሳቸው ከሳሽ፣ ራሳቸው ዳኛ፣ ራሳቸው አስፈጻሚ ሆኑና አረፉት…።

ይብሱንም ይህን የ’ባዶ ሜዳ አምባገነን” ተግባራቸውን አወድሱልኝ ብለው ደረቁ። ወያኔ ላይ ሲሆን የሚወገዘው አፈና ኢህአፓ ላይ ሲሆን እንዴትና በምን መለኪያ ነው ልክ ሊሆን የሚችለው?… ሰዎቹ ማሰብ የተሳናቸው ነው ሚመስሉት። አዎ ጌቶች ስለፕሪንሲፕል አታውሩን… አታውቁትምና፤ ሀሳብን በነጻነት ስለመግለጽ ባትነግሩን ነው የሚበጀው – ጠላቶቹ ናችሁና።

3 – ከሁሉ በላይ የሚገርመው የኮ/ሉን መጽሀፍ ያሳተሙ መቀጣት አለባቸው ማለታቸው ነው። ከመሰረቱ ይህ እምነታቸው አይደለም። ጭራሽም አይን ያወጣ ቅጥፈት እንጂ። ምክንያቱም ይህ የኮሎኔሉ መጽሀፍ የመጀመሪያ አይደለም። ከአሁን በፊት ጋዜጠኛ ገነት አየለ ከኮሎኔሉ ጋር ያደረገችው ሰፊ ቃለ ምልልስ በሁለት ክፍል መጽሀፍ ታትሞ ነበር። ኢህአፓ ያኔ የከፋት አትመስልም። የኮሎኔሉ ሀሳባቸውን የመግለጽ መብታቸው መከበሩም አልቆጫትም ነበር…

እንደ ‘ደብተራው’ አንባቢ የለሽ ያልሆነው በተለይ ለኢህአፓ ቀና አመለካከት በነበራቸው ዜጎች ዘንድ ዝነኛ የነበረው “ሐዋርያ” ጋዜጣ ወ/ሮ ገነትን በክብር ቃለ ምልልስ አድርጎላቸው ነበር። ያውም በሁለት ተከታታይ ክፍል (መስከረም 21 ቀን 1994 ዓ.ም ቅጽ 8 ቁጥር 2 እና ጥቅምት 21 ቀን 1994 ዓ.ም ቅጽ 8 ቁትር 3)። በሁለቱም እትሞች ላይ ታዲያ ጋዜጠኛ ገነት አየለ የመጀመሪያ ርእስ ሆና ነው የቀረበችው። ይህ ደግሞ ለኮሎኔል መንግስቱ ጥሩ ፕሮሞሽን (ማስታወቂያ) ነበር።

ኢህአፓዎችም መጽሀፉን አንብበው ሀሳብን በሀሳብ የሚመክቱበትና የሚተቹበት እድል እንዲያገኙ ጥሩ አጋጣሚያቸው ነበር። ለዚህ ተግባር “ሐዋርያ” በወቅቱ ሙገሳ አትርፋለች። ግን ልብ አድርጉ? የኮ/ሉ እና የወ/ሮ ገነት ቃለ ምልልስ የቀረቡባቸውን ሁለቱንም መጽሀፎች ያሳተመው በአቦይ ስብኃት ይቃኝ የነበረው ሜጋ ነበር። አዎ የወያኔው ሜጋ! ኢህአፓ ግን መጽሀፉን በነጻ አሰራጭታ ሜጋን ልቅጣ አላለችም። ስለ ኮሎኔሉ “የደም ገንዘብም” የፎከረችው ነገር አልነበረም። ልክ ዛሬ የእነ በረከት ስምኦን መጽሐፍን በነጻ እንዳልበተነችው ሁሉ በነወ/ሮ አዜብ ሜጋ ላይም “ቅጣት” ያለችውን ስርቆት አልፈጸመችም። ይልቅስ “ሐዋርያ” ጋዜጣ በወሰደችው እጅግ ተገቢ የሆነ ቃለ ምልልስ ሳቢያ ለፓርቲው ቀና አመለካከት የነበራቸው አንባቢያን የኮሎኔሉንም መጽሐፍ ያነቡ ዘንድ የሚያነቃቃቸው ፍንጭ (ማስታወቂያ) ነበር ያገኙት።

ይህ የኪሎኔሉ ቃል ያውም በሁለት ክፍል ታትሞ መሰራጨቱ ያላንገበገበው ‘ፓርቲ’…፤ ይህ የወያኔው ሜጋ አሳታሚ ተጠቃሚ መሆን ያልከነከነው “ድርጅት’ ዛሬ ጦሩን ሰብቆ የተነሳው በዚህ ትውልድ ሁሉንም የማወቅ መብት ላይ እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተማጋች በሆነው በፀሐይ አሳታሚና በባለቤቱ በኤልያስ ወንድሙ ላይ መሆኑ እጅግ ያሳፍራል። ፕሪንሲፕል ሲሉ መስማቱም ቅ…ፍ…ፍ… ይላል።

በኢህአፓ ያልተወገዘውን የወ/ሮ አዜብ ሜጋን በተመለከተ ብዙ ስንል ኖረናልና ዛሬ መጨመር አያሻንም። ኤልያስ ወንድሙንና ፀሐይ አሳታሚን በተመለከተ ግን መቋጫችን ላይ ጥቂት ማለት እንወዳለን።

ከዚያ በፊት ግን ይህ በአንድ ዘመን ማመዛዘን የሚችሉ ምሁራን ቤት የነበረው… ባንድ ወቅት ሀሳብን በሀሳብ መታገል የሚችሉ የነጠሩና የተሞረዱ ፀሀፍት መናኸሪያ የነበረው ፓርቲ ዛሬ ወና ቤት የታቀፈ፤ ኮምፓሱ የተሰበረበት፤ የጨለማ ተኳሽ መሆኑን አስመልክተው በየአቅጣጫው እየተሰነዘሩበት ያሉትን ትችቶች እንዴት ‘ለመመከት’ እንደወደደ ማንሳቱ ተገቢ ነው።

“አንዴ ሳያይ… አንዴ ሲያሳይ” እንደተነደፈው ጅል ሁሉ “አልሞትንም’ የሚሉት የፓርቲው ትራፊዎችን ርቃን ያስፈተሸው የደብተራው ጸያፍ ወንጀል ሳያንስ ‘አሲምባ’ የተባለው እህት ገጹ ደግሞ በ9 እንስሳት ስም ጥሪ የታጀበ ባለ 3 ገጽ ሙሉ የስድብ ኳኳታ አቅርቦ ‘ዳግም ሞታቸውን’ ሲናዘዝ አየን።

አሲምባ

የፓርቲው ሰራዊት ከደርግ ጋር ሊተናነቅ ጦሩን ያሰፈረበት ትግራይ ውስጥ ያለ ስፍራ ነበር። ያ… ድሮ ነው… ዛሬ ደግሞ “አልሞትኩም ብየ እዋሻለሁ” ለማለት የደፈሩ ጥቂት አባላቱ የሚሳደቡበት የኢንተርኔት ሜዳ ሆኗል… አሲምባ። ድረ ገጹ ምንም ሳያፍር በርዕሰ አንቀጽ ደረጃ አቋም አውጥቻለሁ ብሎናል። እውነቱ ግን 3 ገጽ ስድብ እንጂ አንድም የገለጸው ወይንም ለመግለጽ የቻለው ሀሳብ አልነበረም።

ያ… በ1960ዎቹ መጨረሻና በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሺ ምንተሺ ወጣቶችን የመሰጡ፣ …የተወሳሰቡ ሀሳቦችን አበራይተው ለመተንተን ብቃት በነበራቸው ፀሐፍቱ እነ ጎሕንና ዲሞክራሲያን ሲያስነብብ የነበረ ድርጅት ቢራቢሮ፣ አሜባ፣ ውሻ፣ በግ፣ ተኩላ፣ ቀበሮ፣ ፈረስ፣ ጅብ፣ ዶሮ የሚሉ ከ9 በላይ ፍጡራን ስም የታጨቁበት 3 ገጽ ስድብ ማቅረቡን ላየ በርግጥም ‘አልሞትንም’ የሚለው ክርክራቸው መራር ቀልድ ቢመስለው አይፈረድበትም።

‘አሲምባ’ በርዕሰ አንቀጽ ደረጃ ባወረደችው የስድብ ናዳ የማንንም ሀሳብ አልሞገተችም። የቃላት ኳኳታ እንጂ አንዳች ፍሬ ነገር አላስጨበጠችም። ይልቅስ ስለ ትውልደ ኤርትራዊነት በማውራቷ በቅርቡ የ’ደብተራውን’ ተግባር ከኮነኑት ሰዎች መሀል አንዱ ስለሆነው ስለተስፋየ ገ/አብ ማንሳቷ ይመስላል።

የተስፋየን የትላንት ውሎ መሞገት አንድ ነገር ነው። ለስደት የበቃበት ምክንያት ግላዊ ነው በሚል መጠየቅም ይቻል ይሆናል። ኢትዮጵያዊነቱን አስመልክቶ ግን ኢህአፓ (አሲምባ) ዜግነት ሰጭም ቀሚም ለመሆን መድከሟ ያሳፍራል። ከኤርትራ ሰው መወለድ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስከለክል ቢሆን ኖሮማ ፓርቲዋ ከማንም በላይ መፈተሽ ያለባት ራሷን ነበር። አምጠው ከወለዱኝ ስንቶቹ፣… ከሚመሩኝ ወይንም ሲመሩኝ ከኖሩት ስንቶቹ… ትውልደ ኤርትራ ናቸው? ብትል ኖሮ ዘር ቆጠራ ባልደከመች ነበር።

የሆነ ሆኖ የተስፋዬ ትችት እንከን ከነበረው አሲምባ አላሳየችንም። ወይ ጸሀፊው ልክ ነበር (ደግሞም ነው)፣ ወይ ደግሞ አሲምባም ሆነ ፓርቲዋ ሀሳብን በሀሳብ መሞገት የሚችል አንድስ እንኳ ሰው ጓዳዋ ውስጥ የላትም ማለት ነው? ያስብላል።

ያች ሀገር የተሳዳቢዎቹ የሆነችውን ያህል የእኛም፣ የተስፋዬም፣ የመንግስቱም፣ የእንቶኔና የእንቶኒትም ነች። ሀሳባችንን ለመግለጽ የኢህአፓን ፈቃድ ጭራሽ አንፈልግም። ሀሳብን ለመተቸት ግን ሀሳብን መታጠቅ እንደሚያስፈልግ እናውቃለን።

“አስተዋይነት ያነሰው ሰው ከሚጎርሰው በላይ ይቆርሳል’ እንዲሉ ስድብ ታጥቆ ሀሳብን መዋጋት ከቶም አይቻልም። እናም እንላለን፦ እባካችሁ እናንተ ጥቂት ሰዎች ሆይ የስደቱ አለም በረከት ስምኦን ለመሆን አትዳክሩ። ይልቅስ ከእንቅልፋችሁ ባንኑ። ዙሪያችሁንም አስተውሉ።

‘ጭለማ’ የተተኮሰባት ‘ፀሐይ’

ፀሐይ አሳታሚ የኤልያስ ወንድሙ አሳታሚ ድርጅት ነች። ኤልያስ ደግሞ በነጻ ፕሬስ ታሪክ የተፈተነ፣ የጋዜጠኞች ሁነኛ ተማጋችና ጠበቃ ነው። አገር ቤት በጋዜጠኖች ላይ የሚፈጸሙ ኢ-ፍትሐዊ ግፎችን ሽንጡን ገትሮ ሲሞግት ደክሞት አያውቅም። አፈናው በዓለም አቀፍ ተሟጋቾች እንዲፈተሽ… በአፋኞቹም ላይ የተባበረ ተጽእኖ እንዲደረግ ሳይታክት ለአመታት የደከመ አኩሪ ወጣት ነው። የፔን አሜሪካም የቦርድ አባል ሆኖ አስከ አሁን በኢትዮጵያ የመጻፍና የማሳተም መብት ጉዳዮች ላይ አኩሪ ስራ የሚሰራ ትጉህ ሰው ነው። ሊበረታታና አለንልህ ሊባል የሚገባው እንጂ የሚጠለፍና የሚጣል አልነበረም። ስህተት ቢሰራ እንኳ የሚመከርና የሚገሰጽ እነጂ የሚመታና የሚቀጠቀጥም አልነበረም።

ባለፉት 10 አመታት ውስጥ ያሳተማቸውን 50 መጻሕፍት ያስተዋለ ደግሞ ኢህአፓ እንደምታወራው የጥቅም ሰው ሳይሆን የሀገሩ የቁርጥ ቀን ውለተኛ መሆኑን ይረዳል። ተሳዳቢዎቹ አምሳው ላይ አምሳ ስም ሲለጥፉ ኤልያስ ግን ሀምሳ ታሪካችንንና ባህላችንን በአለም መድረክ የሚያስተዋውቁ የተመራማሪዎችን ስራ ሲያሳትም ነው የቆየው። አዎ ኤልያስ በነጻው ፕሬስ ተጋድሎ የተኮተኮተ የተግባር ሰው ነው።

ከኤልያስና ከፀሐይ አሳታሚ ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅ፣ በደብተራው የተጻፈው ጸያፍ ድፍረትም ከሞራልም ሆነ ከህግ አኳያ ምን ያህል የወረደ መሆኑን ለመታዘብ እንዲረዳን በታዋቂው የፖለቲካ ሳይንቲስት በፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም በቅርቡ የቀረበውን ጽሁፍ ተርጉሞ ማቅረቡን መርጠናል። ሰሞኑን ይዘነው እንወጣለን።

የአቶ እያሱ ኢህአፓም በሜጋ ላይ የሰነፈ ወንጭፏን በፀሐይ አሳታሚ ላይ መሰንዘሯ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነት ላይ የከፈተችው ዘመቻ ነውና እናወግዘዋለን፡ ወይ ተቃኑ አለያም ጡረታ መውጣት ታላቅ ክብርን እንደሚያጎናጽፍ ማመኑ ይበጃል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 26, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.