ገዳማትን ማፍረስ፤ የአማራን ህዝብ ማፈናቀልና የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለማስቆም በአንድነት እንነሳ

ከአጥቃዉ ቦጋለ

የአማራዉ ህዝብ ከተወለደበት አገሩ በፋሽሽቱ የትግራይ ነጻ አዉጭ ግንባር (ወያኔ) እየተፈጸመ ያለዉ ግፍ የአማራን ትዉልድ ከዳር እስከዳር ለአመጽ እያስገደደ ነዉ። ወያኔ የትግራይን ወጣት አደራጅቶ በትግራይ ህዝብ ትብብር የጭቁን አማራ ህዝብን መሬትና ንብረት በጉልበት ቀምቶ በትዉልድ አገሩ እያሳደደ ለሞትና ለስደት የተዳረገዉ በሚሊዮን የሚቆጠር ነዉ።
በጎንደር ክፍለ ሃገር በጠለምት፤ በወልቃይት; በጠገዴና ሁመራ በመሳሪያ ሃይል አስገድዶ መሬቱን ቀምቶ የትግራይን ህዝብ አስፍሯል። ድርጊቱን የተቃወመ የአካባቢዉ ህዝብ በሽህ የሚቆጠረዉ ተገሎ አብዛኛዉ አገር ጥሎ ወቷል፤ የቀረዉ በትግራይ የጨለማ እስርቤት ጉድጓድ በሲቃይ ላይ ይገኛል።

በወሎ ክፍለ ሃገር የአላማጣ፤ የዋግና ራያን ህዝብ ለም መሬቱን ወደትግራይ አስተዳደር ክልል በጉልበት ወስደዉ የሚደርስበት ግፍ እጅግ የከፋ ነዉ። ዛሬ በአላማጣና ዋግ መሰብሰብና መደራጀት ቀርቶ ወንድ ልጅ የሆነ ዱላ ይዞ መንቀሳቀስ አይችልም። የወሎ ክፍለ ሃገር ህዝብ ከአፋር ህዝብ ጋር ያለዉን ታሪካዊ ሃረግ ለመበጠስና የወደፊቱን የታላቋን ትግራይ አጀንዳቸዉን እዉን ለማድረግ የአፋርን አካባቢ በመቆጣጠር ላይ ናቸዉ ህዝቡ ግን የሃያ ዐመታት ትግሉን ቀጥሏል።

በሽዋ ክፍለ ሃገር ከታላቁ መሪ ከአጼ ሚኒሊክ ን ወቀሳ ጋር አያይዘዉ የሽዋን ጭቁን አማራ ለማጥቃት ነፍጠኛ በሚል ስያሜ በተለጣፊ ድርጅቱ በኦዴድ አስተባባሪነት ግማሹን የአማራ መሬት ኦሮምያ ወደሚሉት ነጥቀዉ ኦሮሞና አማራን ለማጋጨት በመጣር ላይ ናቸዉ። የዚህ አካባቢ ህዝብ አዲስ አበባ ጉዳይ ማስፈጸም ተከልክሎና መብቱ ተነፍጎ ባህርዳር ጉዳዩን እንዲያስፈጸም ተገዷል። ኦሮምኛ ተናጋሪ አማራ ሳይቀር በዘሩ እዬታደነ በኦዴድ ባለስልጣናት የሚደርስበት እስራትና ግርፋት ከሚችለዉ በላይ ነዉ። ዛሬ በወያኔ ዘረኛ ስርዓት የሽዋ አማራ የልማትም ሆነ የፖልቲካ ተሳትፎ እንዳያደርግ አቀባ ተደርጎበት የመንዝና መርሃቤቴ ህዝብ በወያኔ አይነ ቁራኛ ከተያዘ ዘመናት አልፏል።

የጎጃም አማራ በሱዳን በኩል ያለዉ ለም መሬቱ ለሱዳን ተሽጧል። ይህን የድብቅ ሴራ ለማክሸፍ የጎጃምና የጎንደር ገበሬ ወያኔ ለዉጭ አገር የሰጠዉን ለም መሬት ለማስመለስ ያለፉት አራት አመታት በትግል ላይ ይገኛል። የአባይን ጌታ ዉሃ ተማዉ ሆኖ ወያኔወች መብራት ከአባይ ወደ ትግራይ ጎተዉ ሲወስዱ የጎጃም አማራ ግን አባይን እኛም ለምን እንጠቀም ብሎ መጠዬቅ እንኳን አይችልም። ከአሁን

በፊት በትልቁ ታልሞ ለልማት የተጀመረዉ የጣና በለስ የልማት ፕሮጀከትን ወያኔ ዘግቶ የግንባታዉ እቃ ሁሉ ወደትግራይ ተወስዷል። ወያኔ በአማራዉ ህዝብ ላይ እያካሄደ ያለዉ የማጥፋት ዘመቻ የአማራዉን ስብዕና በመዳፈር ማንነቱንና ታሪኩን አዛብተዉ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንደሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ በግልጽ የሚያዉቀዉ ሚስጥር ነዉ።

አማራዉ አገሩን ኢትዮጵያን ከራሱ አብልጦ የሚወድ ለሃገሩ ሉዓላዊነትትና ለህዝቦች አንድነት ቀናዊ የሆነ ነዉ። ቅድመ አያቶቻችን ደማቸዉን አፍሰዉ አጥንታቸዉን ከስክሰዉ ኢትዮጵያን አስከብረዉ ያቆዮአትን ታሪካዊ አገር አሁንም የአማራዉ አዲስ ትዉልድ አጥፊዉን ወያኔን ቡድን ለአንዴን ለመጨረሻ ጊዜ የዘር ስርዓትን ለማስወገድ በአንድነት ተነስተን በማስወገድ አገራችንና ህዝባችን ማዳን አለብን፣ ይህ የትግል ጥሪ በእሉኝታ የማናልፈዉ ታሪካዊ ጥሪ ነዉ።

ባለፉት 20 ዓመታት አማራዉ የራሱን ዘር ከጥፋት ለማዳን ተደራጅቶ ለመከላከል ባለመቻሉና ከሁሉም ኢትዮጵያዉያን ጋር ጎን ተባብሮ ለመታገል በአገር ፍቅር ያስተላለፈዉ የጩሕት ጥሪ ጀሮ ዳባ ልበስ በመባሉ አማራዉ ዋና ተጠቂ ሁኗል። የአጥቂዎቹ ጎራ ወያኔወች ብቻ ሳይሆኑ አጫፋሪወቻቸዉም አማራዉን አንገት ለማስደፋት የሚያልሙት ጋሻ ጃግሬዎች ጥቂት አይደሉም። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አማራዉን መድረክ ማሳጣት ብቻ ሳይሆን ነፍጠኛዉ አማራ አከርካሪዉ መሰበር አለበት ይላሉ።

አማራዉን ለማጥፋት የተነሱ የዉጭ ቅጥረኛች በመጨረሻም በሸረቡት በዘር ወጥመድ ታንቀዉ እራሳቸዉን እንደሚያጠፈ ያላወቁ ግብዞች በመሆናቸዉ በአማራዉ ሞትና ስቃይ የሚያንጨበጭቡና የወያኔን መፈክር አንግበዉ የጥላቻ መርዝ የሚረጩ ጊዜያዊ ደስታና ተድላ የሚሰማቸዉ ከንቱዎች በህዝብ ፊት ለፍርድ የሚቀርቡበት ቀን እሩቅ አይደለም

አማራ ሳይደራጅ ደካማ ሁኖ በማየታቸዉ ቀጥኘ ቢያየኝ ጅማት ለመነኝ ሆነና አማራን ዝቅ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን አማራ አይደለሁም እንዲል የሚሰብኩ ብዙ ናቸዉ። በዚህ ሴራ ሰለባ የሆኑ አማራ ወንድምና እህቶቻችን አማራዉ እንዳይደራች ጠበቃ ሁነዉ ይከራከራሉ። እንዲከራከሩ የሚወክሏቸዉ ግን አማራን የሚያጠቃዉ ክፍል ነዉ።

አሁን ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ ተቀናቃኝዎች አማራን የሚገመግሙት በደካማነት፤በፈሪነት፤ በሆዳምነትና ታሪክ ያበላሸና ኢትዮጵያ የሚል ስም የሚጠራ እሱነዉና ይጥፋ ባይ ናቸዉ። ጥንትም ጀግና እንዳልነበረም አሁንም ጀግና ያልሆነ ሽንታም በሙሉ አንደበታቸዉ ይናገራሉ። እጅ እና እግራቸዉ የታሰሩ ጀግና አማሮች በእስር ቤት የሚነገራቸዉም ይህ ነዉ። ባለፉት ዘመናት በስህተት ስልጣን የያዘ አማራ ገዛን ይላሉ። ስለሆነም ጥሩም ሆነ መጥፎ ለሰሩት መንግስታት አማራዉ ተጠያቂ ነዉ ብለዉ ይከሳሉ። ለዚህም

አሁን መቀጣት ያለበት ህብረተሰብ እርሱ መሆን አለበት እያሉ ጧት ማታ ሞቱን ይመኛሉ ፣ ግንባር ግንባሩን ለማለትም ዝግጁ ናቸዉ። ከአሁን በፊት በአጋዚ ጦር አሸናፊነት ምርጫ ማሸነፋቸዉን የሚያሳይ መፈክርም ያሰማሉ፤ ታጥቀን አንድንሞክራቸዉም በተደጋጋሚ ይጋብዙናል። ስለሆነም አፋችን ዘግተን እጃችን አጣምረን ቤታችን ብንቀመጥም ዘራችን ለማጥፋት ወያኔ ቆርጦ ተነስቷል

ሰሞኑን የከፈቱት ዘመቻም አቅም ካለ የግጠሙኝ አዋጅ ነዉ። አማራዉ ደክሟል በሚል ድምዳሜ ተነሳስተዉ ገሎ መጣል ብቻ ሳይሆን አማራን ከመቃብሩ አዉቶ መጣልም የወያኔ መርሃ ግብር ሁኗል። የወያኔ የሰሞኑ ድፍረትም አገር የማፍረስ ስራዉን አጧጡፎ የቀጠለዉ ለዚህ ነዉ። የተቀደሱ ታሪካዊ ገዳማትን ማረስና ማፍረስ፤ መዝረፍና ማቃጠል ብቻ ሳይሆን የቅዱሳን አባቶችን አጽም ከመቃብር እያወጡ በጫካ መጣል ነዉ። በዋልድባ ገዳም እየደረሰ ያለዉ ግፍ ይህነዉ።

የአማራን ህዝብ መግቢያ መዉጫ ያሳጣዉ ወያኔ ባለፉት ቀናት እንዲሁ 78,000 በደቡብ ክልል የሚኖሩ አማሮች ሰርተዉ የሚኖሩበት ቤትና ንብረታቸዉን ተነጥቀዉ የደቡብን ክልል ጥለዉ ኢንዲወጡ ከመንግስ ትዛዝ ተላልፎ የተወሰኑት አዲስ አበባ ሲደርሱ አብዛኛዉ ወላጆችና ህጻናት መዳረሻቸዉ ጠፍቷል። የተፈናቀሉት አዛዉንቶችና ህጻናት በበሽታና እርሃብ ሲቃ የወገን ያለህ የሚሉት የእግዚአብሄር ቤት በሆነዉ ቤተክርስቲያን እንኳን መጠለያ እንዳያገኙ በወያኔ የዉስጥ ትዛዝ ተላልፎ እጣፈንታቸዉ በግዞት መጋዝን ታስሮ መቀመጥ ሁኗል። የወያኔ ብቀላ በአማራ ህዝብ ላይ ማለት ይህ ነዉ። በአማራ ህዝብ ላይ መዝመት ግን ለአገራችንም ሆነ ለደቡብ ክልል የወያኔ ተለጣፊ መሪዎች በቀጣዉ ወራት ጥሩ ዜና እንደማሆንላቸዉ እርግጠኛ ነኝ።

ይህ በደቡብ ኗሪ በሆነዉ አማራ ህዝብ ላይ የተፈጸመዉ በደል የመጀመሪያ አይደለም፤ የአሁኑ ግፍ የደረሰበት የህዝብ ብዛት ግን ወያኔ ኤርትያዉያን ከአስር ዐመታት በፊት በባድመዉ እልቂት ተወልደዉ ካደጉበት ከኢትዮጵያ ለቀዉ እንዲወጡ አስገድዶ ከተካሄደዉ ዘረፋ ጋር በጣም ተመሳሳይነት አለዉ። እጅግ የሚያሳዝነዉና የሚገርመዉ ግን በወያኔ አገዛዝ የደቡብ ክልል የኢትዮጵ የጎሳ ፌደራሊዝም ግዛት ዉስጥ የዜግነት ህጋዊ ቦታ በሆነዉ አካባቢ ነዉ። የተላለፈዉም ትዛዝም በወያኔ የፖሊት ቢሮ አካል ሲሆን አቶ ሃይለ ማሪያም ደሳለኝም ዋነኛ አሰስተባባሪ ናቸዉ።

ከእንግዲህ ከዚህ የበለጠ ሞትም ሆነ ዉረደትን ቁመን ለመጠበቅ ፍጹም ፍቃደኛ መሆን የለብንም። የአማራዉ ወጣት ሃይል ተደራጅቶና ታጥቆ በመከላከልና ብሎም አሸናፊ በመሆን የነጻነቱና የአገሩ ባለቤት የመሆን ብቃቱ ስላለዉ ሳይዉል ሳያድር ትግሉን አጧጡፎ ወደፊት መግፋት አለበት።

የመላዉ ኢትዮጵያ ህዝብም በሚኖርቤት አካባቢ ሁሉ የወያኔን የዘረኛ ገዥወች ቀንበር አሽቀንጥሮ ለመጣል በአንድ ድምጽ እጅና ጓንት ሁኖ አመጹን ማፋፋምና ፍርሃትን ሰብሮ አሸናፊ እንደሚሆን እርግጠኛንት በዚህ ጽሁፌ እመሰክራለሁ። እኔም በአማራነቴና ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያዊነቴ በምችለዉ ሁሉ ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ (አዴሃን) ጎን ተሰልፌ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ።

አማራን ማዳን ለኢትዮጵያ መቆም ነዉ!!!

ጸሃፊዉን ለማግኘት peopleforum@yahoo.com

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on April 4, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.