ገሀነም ደርሶ መልስ! ይድረስ ለአንድ የሀገሬ ወታደር!

አቢይ አፈወርቅ

“ቅዱስ ማለት ራሱን ንጹህ ለማድረግ ሙከራውን የማያቋርጥ ሀጢያተኛ ነው ይላሉ። ምናልባትም የህይወቱን 3/4ኛ ጊዜ ያሳለፈው በተንኮል ይሆናል። ይሁንና ቀሪውን የእድሜውን ሩብ በቅዱስ ተግባር በማሳለፉ ስሙ ሲወደስ ይኖራል።” ይህን ያሉት ኔልሰን ማንዴላ ናቸው። በኛ ዘመን ሰሌዳ ህዳር 30 ቀን 1972 ዓ.ም ከእስር ቤት ሆነው ለቀድሞዋ ባለቤታቸው ለዊኒ ማንዴላ ከላኩላት ደብዳቤ ላይ የተነቀሰ አባባል ነው። “አንዴ ሌባ – ሁሌም ሌባ” ከሚለው ጭፍን ድምዳሜ ርቆ ለክፉዎች እንኳ በህይወት እስካሉ ድረስ በጎ የመሆን ጀምበር እንደማትጠልቅባቸው የሚያሳይ ይመስለኛል።

ይህንን መልእክት በመግቢያዬ ማስቀደሜ በተለይ ላንተ የመከላከያ ሰራዊቱ አባል ለሆንከው ለአገሬ ዜጋ ለመጻፍ ያሰብኩትን ሀሳብ ጠቋሚ ይሆናል የሚል እምነት ስላለኝ ነው።

ወታደሩ ወንድሜ ሆይ፦ ከዚህ በኋላ አንተን የወያኔ ወታደር ብዬ ልጠራህ አልፈልግም። ለማንም አገዛዝ ባሪያ ያልሆነ፤ ለህዝብና ለህገ መንግስቱ ብቻ የቆመ፤ ማስተዋል የሚችል የ’አገሩ ወታደር’ ለመሆን የማትችልበት ምክንያት አልታይህ ስለሚለኝ። የኢትዮጵያን እድገት የሚመኝ፣ የህዝቧ ህመም የሚያመው፣ ማሰብና ማመዛዘን የሚችል ሀገር ጠባቂ ትሆንልኝ ዘንድም በጽኑ ስለምመኝ። የህወሀት ገዥዎች በስልጣን ላይ መቆየት ብዙሀኑን የአገሬ ህዝብ ከፍተኛ ስጋት ላይ የሚጥለውን ያህል በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከአቶ መለስ መንግስት ጋር ሰልፋቸውን አሳምረው የቆዩ ወገኖችን ደግሞ የአገዛዙ መውደቅ ሊያስቡት የማይፈልጉት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሊከታቸው እነደሚችል ይገባኛል። አንተ ወንድሜና ጓደኞችህም ለዚህ መንግስት በስልጣን መቆየት የጀርባ አጥንት ስለነበራችሁ የመንግስት ለውጥ ቢመጣ የበቀልና የቅጣት መአት እንደሚወርድባችሁ ልታስቡ እንደምትችሉ እገምታለሁ።

የቅርብ ዘመን ታሪካችን ሳይቀር እጣህን – እያገለገልካት ከቆየኸው ከወያኔ ጋር አመሳስለህ እንድታስባት ሊያስገድድህ ችሎ ይሆናል። ባለፈው የደርግ ስርአት ውስጥ ሚና የነበራቸው ሹማምንት በአብዛኛው ዛሬም ድረስ ዘብጥያ ናቸው። ብዙዎችም እስር ቤት ውስጥ ነው የሞቱት። የቀድሞው የመከላከያ ሰራዊት አባላትም የከፋ ግፍ እንደተፈጸመባቸው ካንተ ከወንድሜ በላይ ምስክር የለም። መጨረሻቸውም የትም ተበትኖ መቅረት ነው የሆነው። ሌላው ቀርቶ ከወደቀው መንግስት ጋር በርቀትም ቢሆን ተነካክተዋል የተባሉ ሁሉ ‘የኢሰፓ – ንክኪ’ እየተባሉ በይፋ ሲገለሉ መቆየታቸውን ከቶም እንደማትረሳው አውቃለሁ።

አንተ ግን ያ እጣ እንዲደርስብህ አትፈልግም። እኔም ያ እጣ እንዲደርስብህ አልፈልግም። ግን እኮ ወንድሜ፣ ይህን መሰሉ ክፋትና በቀል ሁሌም ቢሆን የሚፈጸመው ባለጠብመንጃን ባለጠብመንጃ ሲጥለው ብቻ ነው። በሰላማዊ ትግል ለውጤት በሚበቃበት አገር ሁሉ ግን ጦሩ የአንድ አገር ጦር እንጅ የአንድ ፓርቲ አገልጋይ አይሆንም። ለዚህ አባባሌ ብዙ ምሳሌዎችና ማስረጃዎች ላቀርብልህ እችላለሁ።

ህዝብ እኮ መሀሪ ነው። እንኳንስ አንተን ‘በዚህች ሀገር በደል ይቁም’ በሚል እምነት ለህዝብ እኩልነትና ነጻነት በረሃ ገብተህ ለታገልከው፤ ወይም ላንተ አገር ተደፈረች በሚል በባድመ ጦርነት ወቅት ተመልምለህ በዚያው ውትድርናን ሙያህ አድርገህ ለቀረኸው፤ ወይም ላንተ አንድም አይነት ሌላ የስራ መስክ በማጣትህ ውትድርንው አለም ለገባኸው… ቀርቶ በይፋ እየፎከሩ በብዙ ሽህ ወገኖችህ ላይ እልቂት ያወጁ፣ በጎሳ ሸንሽነው እያጋጩ የሚጨፍሩ፣ ያለምንም ይሉኝታ በጠራራ ጸሀይ እየዘረፉ በሀብት ላይ ሀብት የከመሩ አምባገነን አለቆችህ ሳይቀሩ የመጨረሻዋን የህይወታቸውን ሩብ ዘመን ወደ በጎ ተግባር ቢመለሱ አትጠራጠር ወንድሜ ህዝብ ምህረትን አይነሳቸውም። እንዲያውም በመግቢያዬ እንዳነሳሁት ቅዱስ ሲወደሱ በኖሩ ነበር።

ያም ሆኖ ግን ወንድሜ አለቆችህ ለዚህ ከቶም ዝግጁ አልሆኑም። ከህዝብ በላይ የሚንቁት ደግሞ እመነኝ አንተን ታጣቂውን ወንድሜን ነው። “ለምን” ብለህ የማትጠይቅ፣ “ግደል” ሲሉህ የምትገድል ህሊና ቢስ ከንቱ ነህ ብለው ያስባሉ። በአንተ እንደሰው ባልቆጠሩህ ወንድሜ ተመክተውም እንዳሻቸው ሲያስገድሉና ሲመዘብሩ ለዘለአለሙ መኖር ያልማሉ። የትም ርቀው ሳይሄዱ በዚህቹ በፈረደባት አፍሪካ እንኳ በትክክለኛ ምርጫ ስልጣን ለማስረከብ የተገደዱ መሰል አምባገነኖች ስላገኙት ምህረት ማሰብ የሚጀምሩት ምናልባትም አንተ ወንድሜ “ለምን?” ማለት ስትጀምር ብቻ ይሆናል። እስቲ አብነት ላንሳልህ። ልክ እንደ አቶ መለስ በወታደሮቻቸው እየተመኩ ፍጹም አምባገነን ሆነው ከቆዩ የአፍሪካ መሪዎች መሀል ነጻ ምርጫ ለማድረግ ተገደውና የህዝብን ድምጽ አክብረው መንበራቸውን የለቀቁት የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ የቤኒኑ ማቲዮ ኬሮኮ ነበሩ። እኒህ ወታደራዊ አምባገነን ከአስራ ዘጠኝ አመት አፋኝ አገዛዝ በኋላ በተማሪዎች ተጀምሮ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተቀጣጠለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ አስገዳጅነት ወደ ዲሞክራሲ የሚያሻግረውን ሂደት ጀመሩ። እ.ኤ.አ በ1991 ዓ.ም በህዝብ ድምጽ መንበራቸውን ሲለቁም በአመራር ዘመናቸው ለተፈጸሙት ዘግናኝ ድርጊቶች መጸጸታቸውን ገልጸው ህዝባዊ ይቅርታ በመጠየቅ ነው።

የ’ኮሮኮ ጦር’ ይባሉ የነበሩት የቤኒን ወታደሮች ምን የሆኑ ይመስልሀል? እንደ ደርግ ዘመን ወታደሮች የበቀል መአት የወረደባቸው? – እንዳይመስልህ። የማንም ፓርቲ አሽከር ያልሆነ የአገራቸው የቤኒን የመከላከያ ኃይል ሆነው ነው የቀጠሉት።

ህዝብ እኮ መሐሪ ነው። እንኳንስ የጦር ሀይሉን፤ ጭፍን አምባገነን ሆነው የኖሩትን ኬሮኮን እንኳን በአመራራቸው ስር የደረሰውን ልክ የሌለውን በደል እያስታወሰ በቅጣት የተነሳባቸው አልነበረም። ይልቁንስ በመጨረሻው የስልጣን ዘመናቸው የወሰዱትን እርምጃ ሊያወድስላቸው ወደደ። ማንዴላ እንደጠቀሱት አይነት ቅዱስ ሊያደርጋቸውም ፈለገ። ይብስ ብሎም ለዚህ ለታደሰው አዲሱ ማንነታቸው ያለውን አክብሮት ለመግለጽ ሲል ከአምስት

አመታት በኋላ አገራቸውን ይመሩ ዘንድ (ለመጀመሪያ ጊዜ) በድምጹ መረጣቸው። ልብ አድርግ ወንድሜ እኚህ ሰው ልክ እንደ አቶ መለስ አምባገነን ነበሩ። በስልጣን ዘመናቸው ብዙ ወንጀሎችን ፈጽመዋል። ህዝብ ግን ‘አንዴ ሌባ – ሁሌም ሌባ’ ባይ አይደለምና የበቀል በትሩን ከመሰንዘር ይልቅ የመጨረሻውን ምእራፍ በጎ ተግባራቸውን ነው ያወደሰው። አቶ መለስ ይህንን መስማት አይፈልጉም። አንተ ወንድሜ ግን ነገ ከወያኔ መንግስት መውደቅ በኋላ ሁሉ የምንኮራብህ የኢትዮጵያ ወታደር እንድትባል እመኛለሁ።

ልክ እንደ ቱርክ የመከላከያ ሰራዊት ሁሉ የህዝብ አመኔታ በማያወላውል መልኩ በአንተ፤ አገርና ህገ መንግስት ጠባቂ ልትሆን በምትችለው ወንድሜ ላይ እንዲያርፍ አልማለሁ። የቱርክ ጦር ሀይል በእኛ ዘመን አቆጣጠር በ1915 ዓ.ም ሙስጠፋ ከማል አታቱር የቱርክን ሪፐብሊክ ከመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለአንድም ፓርቲ ሳያድር የአገሪቷን ሁሉን አቀፍ ፖለቲካ ጠባቂ ሆኖ ነው የቆየው። ስልጣን ላይ የሚወጣ ማናኛውም ፓርቲ ቢሆን ህገ መንግስቱን እንዳይንድ፣ ህዝቡን እንዳይበድል ከማንም በላይ የሚፈራው የአገሪቱን የጦር ኃይል ነው። ህዝቡ ደግሞ ከማንም በላይ የሚመካው በጦር ኃይሉ ነው። በቅርቡ የተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት የሚያሳየውም ይህንኑ ነው።

አንተ ወንድሜም ህዝብ የሚመካበት፣ መንግስታት የህዝቡን መብትና ህገ መንግስቱን ለማክበር የሚገደዱበት ሀይል እንጂ እንዳሻቸው ‘ግደል!’ ብለው የማያስገድሉህ፣ ‘አፍን!’ ብለው የማያሳፍኑህ የሞት ማሽናቸው እንዳትሆንብኝ አልማለሁ። ቢያንስ ከዚህ በኋላ ‘በቃ! – ያልታጠቁ ወገኖቼ ላይ አልተኩስም” እንድትል እመኛለሁ። አለቆችህ አንተን ካልናቁ ህዝብን ያከብራሉ። አንተን ማክበር ከጀመሩ የወንድም እህቶችህን፣ ያክስት ያጎቶችህን፣ የጓደኞች የጎረቤቶችህን መብት መግፈፍ ያቆማሉ። አትጠራጠር ወንድሜ ይህች አገር የሰላምና የእድገት ሆና እንተም ለዘለአለሙ ታሪክ የሚጠራህ ባለውለታዋ የመሆኑ እድል በጅህ ነው።

አፌን ሞልቼ ‘የኢትዮጵያ ወታደር’ ልልህ እፈልጋለሁ። እጣ ክፍልህን ከአገሪቷ ጋር እንጂ በግፍ ባህር ከተጠመቁ አምበገነኖች ጋር የማታቆራኝ የአገር ዋልታ ስትሆን ለማየት እጓጓለሁ። መንግስታት መጥተው ይሂዱ። ህዝብ ያውጣቸው። ህዝብ ያውርዳቸው። አንተ ወንድሜ ግን ሙያተኛ የአገር ጠባቂ ሁንልን። በተግባር ህሊና ያለህ መሆንህን ህልና ቢስ አድርገው ለሚቆጥሩህ አለቆችህ አሳያቸው። እንደ ግብጽ ወታደሮች ሰልፈኞች አቅፈው የሚስሙኝ፣ ታንኬ ላይ የአበባ ጉንጉን የሚያኖሩልኝ የአገሬ ልጅ ነኝ በላቸው። ይልቅስ ለእነሱም ቢሆን መባነን ከቻሉ እንዳልመሸ አሳያቸው። እነ አቶ መለስ ያፈሰሱትን ደም ብዛት ባስታወሱት ቁጥር መቸም ምህረት እንደማያገኙ ያስቡ ይሆናል። ሲበቀሉ የኖሩ ናቸውና የወደቁ ቀን የሚጠብቃቸውን ፍርድ ማሰቡ በራሱ ሊያስበረግጋቸው ይችላል። ጭራሽም የያዙትን ስልጣን እንደ ነብር ጭራ ነው የሚያዩት። ይህም የሆነው ከታሪክ ለመማር ከቶም የማይፈልጉ በመሆናቸው ብቻ ነው።

በቤኒን ኬሮኮ ከስልጣኑ በምርጫ ከወረዱ ከመንፈቅ በኋላ በዛምቢያም የተስፋ ጮራ ፈንጥቆ ነበር። ከ27 አመታት በላይ በአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ሲገዙ የቆዩት ኬኔት ካውንዳ ነጻ ምርጫ ለማድረግ ተገደዱ። ህዝቡም ‘በቃ!’ አላቸውና ተቃዋሚያቸው ፍሪደሪክ ቺሉባን መርጦ ሾመ። መሀሪው ህዝብ ካውንዳን አልቀጣቸውም። ህዝብ የካውንዳ ጦር እያለ ያማው የነበረው ሰራዊትም የአገሩ የዛምቢያ ጦር የሚል ካባ ነው የለበሰው። በታንዛኒያም በኡጃማ (የአፍሪካ ሶሻሊዝም) ፍልስፍናቸው ለ21 አመታት ያህል አገራቸውን የመሩት ሙያሊሙ (መምህር) ጁሊየስ ኔሬሬ እ.ኤ. የዘመን አቆጣጠር በ1985ዓ.ም ነበር ራሳቸውን በጡረታ ያገለሉት። ይህ በአህጉራችን ብርቅ ተግባር ነበር። ስለዚህ ድፍን ታንዛኒያ ብቻ ሳይሆን አለምም አክብሮቱን ቸራቸው። እንዲያውም ከሁለት አመታት በፊት የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት ኔሬሬን “የአለም ማህበራዊ ፍትህ ጀግና” በሚል የክብር ስም ጠሯቸው።

የጎረቤታችን ኬንያ ዳንኤል አራፕ ሞይ በረዥሙ የስልጣን ዘመናቸው በህዝቡ ላይ እንዳደረሱት ግፍ ቢሆን ኖሮ ቀሪ እድሜያቸውን ዘብጥያ ባሳለፉ ነበር። ይሁንና በስልጣናቸው የመጨረሻ እርከን ላይ ህዝባዊውን ግፊት ተቀብለውና አገራቸውን ለነጻ ምርጫ አብቅተው ስልጣን በመልቀቃቸው ዛሬ ተከብረውና ተሰምተው እየኖሩ ነው። እንዲያውም ለብዙ አመታት የፖለቲካ ባላንጣቸው የነበሩትና በእግራቸው የተተኩት ሞዋይ ኪባኪ የዛሬ አራት አመት ገደማ የሞይን የዳበረ ልምድና ስለ አህጉሪቱ ያላቸውን የጠለቀ እውቀት በማወደስ ‘የሰላም ልኡኬ’ ብለው ወደ ሱዳን ልከዋቸው እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህ አያስቀናም ትላለህ ወንድሜ?…

አቶ መለስ ከኔሬሬ ይልቅ የኮሎኔል መንግስቱን፣ ከካውንዳ ይልቅ የሙባረክን፣ ከሞይ ይልቅ የቤን አሊን መንገድ ነው የመረጡት። የህይወታቸውን 3/4ኛ ዘመን በጥፋት አሳልፈው በቀሪዋ ሩብ ዘመናቸው ከመታደስና ከመወደስ ይልቅ በዚያው በጥፋት ጎዳናቸው ህዝብ እየፈጁ መቀጠል ነው የፈቀዱት። እኒህ ሰውዬ ፈሪ ናቸው። የጨበጡትን የነብር ጭራ የሚለቁበት የሞራል ድፍረት የላቸውም። የሚመኩትም በአንተ በወንድሜ ጭፍን ታዛዥነት ላይ ነው። እሳቸው ከሌሉ አንተም እንደማትኖር ይዋሹሀል፤ ከቶም ማሰብ የማይችል፣ ህጻናትና ሴቶች ላይ ሳይቀር ለመተኮስ የማያመናታ ህሊና ቢስ አሽከራቸው አድርገው ይቆጥሩሀል።

‘በቃኝ!’ በላቸው ወንድሜ ‘ለምን?’ በላቸው። በ1997 ዓ.ም እንደሆነው ሁሉ ብሶቱን ከማስተጋባት ውጭ አንዳችስ እንኳ ባልታጠቀ ወገንህ ላይ ዳግም ለመተኮስ እንደማትፈልግ ይወቁት፡፤ የታዳጊ ነብዩ አይነት ቦርቀው ያልጠገቡ የአገሬ ህጻናት ላይ ዳግም ቃታ የሚስብ ህሊና እንደማይኖርህ ንገራቸው። ፍትህ ርቧቸው፣ ግፍ አድቅቋቸው፣ እሪታቸውን ለሚያሰሙ ንጹሀን ተገቢ ምላሻቸው ከእንግዲህ የጥይት አረር አይሁን ወንድሜ። የህዝብ ብሶት ተንተክትኳል። ፍትህ ፍለጋ አደባባይ የሚወጣበት ቀንም ሩቅ እንዳልሆነ እመን። ይህ ህዝብ ጠላትህ አይደለም። እንደ ሰው ልሁን፣ ፍትህ አልጣ፣ መብቴን አትንኩ ከሚል ጥያቄ ውጭ ማንንም የመበቀል ፍላጎት የለውም። ከምንም ነገር በላይ በግብጽ እንደታየው በአንተ በወንድሜ ታንክ ላይ አበባ መሰካት ይፈልጋል። ቃታ አልስብበትም ብለህ እንድትጸና እና በፍቅር እቅፍ አድርጎ እንዲስምህም ይመኛል። የገዥ አገልጋይ ሳይሆን የአገር መመኪያ ትሆንለት ዘንድ ነው ህልሙ። … አትግደለው ወንድሜ?!

ይህችን ጽሁፍ ስጀምር መልእክቴን የከፈትኩት ኔልሰን ማንዴላ ከወር በፊት ባሳተሙትና የእስር ቤት ትዝታቸውን በተለይም የቆዩ ደብዳቤዎቻቸውን አካቶ ከወጣው ‘ከራስ ጋር ውይይት’ ከሚለው መጽሐፋቸው ላይ አንዲት መልእክት በመምዘዝ ነበር። እኒህ ማንዴላ ደግሞ ብዙ ጠቃሚ ትምህርት ያስተላለፉ ሰው ናቸውና እኔም ጽሁፌን ከአመታት በፊት ካሳተሙት ‘ወደ ነጻነት የሚደረግ ረዥም ጉዞ’ ከሚለው መጸሐፋቸው ላይ ቃል በቃል ባይሆንም አንዲቷን ነጥብ ጠቅሼ መቋጨት ወደድኩ።

“እነዚህ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን በአገዛዙ ያለአግባብ ሲጠቀሙ እንደመኖራቸው ነጻነት ቢመጣ ተበዳዩ ህዝብ ይበቀለናል በሚል ስጋት የተዋጡ ናቸው። የእኛ ትግል የበቀል ሳይሆን የበደልን ምእራፍ ዘግቶ ሁሉም ዜጋ እኩል በነጻነት የሚኖርባት የሁላችን የሆነች አገር መፍጠር መሆኑን ዋስትና ልንሰጣቸው ይገባል። ከዘረኛነት ነጻ ለመውጣት ስንታገል እነሱንም ከፍርሀታቸው ነጻ እንዲወጡ እንርዳቸው”

_____________________________

በእሳት ተፈትኖ ነጻነቱን አሳልፎ ላለመስጠት በጽናት የቆመው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አማርኛ ጽሁፎቹን በተቻለን መንገድ አገር ቤት ላሉ አንባቢያን እንድናስተላልፍለት ጠይቆን ነበር። ውጤቱ ጥሩ እንደሆነም ገልጿል። እኔም የእስክንድርን ጽሁፍ በኢ-ሜይል ተባዝቶ አነበብን ያሉ ሰዎች አጋጥመውኛል። ይህች አጭር ጽሁፍም በተለይ የመከላከያ ሰራዊቱ አባል ከሆኑ ሰዎች እጅ እንድትደርስ እጓጓለሁ። ፖስታቸው ውስጥ ወይ በራቸው ላይ ወድቃ ያገኟት ዘንድ ምኞቴ ነው።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on March 8, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.