ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ

DAGEN የተሰኘው ታዋቂ የኖርዌይ መጽሄት ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ያደረገውን ቆይታ ከጥቂት ቀናት በፊት ለንባብ አብቅቷል። ይሄው ዶ/ሩ ከጋዜጠኞች ግርማ እንድርያስ ሙላትና ከጆን ሬንዳል ጋር ያደረጉት ውይይት እንደሚከተለው ተመጥኖ በአማርኛ ተቀናብሯል።

በምእራባዊያን የውጭ ፖሊሲ ዙሪያ
የግንቦት ሰባት ንቅናቄ መሪ የሆኑት ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ በቅርቡ ከኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለስልጣናት ጋር ተወያይተው ነበር።

ውይይቱ በተለይም በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ዶ/ር ብርሃኑ ያስረዳሉ። አንደኛው ኖርዌይን ጨምሮ የአውሮፓ ኮሚኒቲና ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ከአምባገነኖች ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን ግንኙነት የቀረጹበትን የተሳሳተ ፖሊሲ የተመለከተው ነበር።

በአምባገነን አገዛዞች ስር መረጋጋት ሊኖር ስለመቻሉና በተወሰነ ደረጃም እድገት ማስመዝገብ ይቻላል የሚለው እምነት በምእራቡ አገራት ፖሊሲዎች ላይ መታየቱ እጅግ አሳዛኝ ስህተት ስለመሆኑ ዶ/ር ብርሃኑ ይተቻሉ።

“ይህ በሞደርናይዜሽን ቲዎሪ የተቃኘው የምእራቡ አለም ፖሊሲ ‘በአንድ የእድገት ደረጃ ላይ የደረሰ የተወሰነ ክፍል ህዝብ እንጂ ሌላው ለዲሞክራሲ ዝግጁ አይደለም ወይንም አይመጥንም’ የሚል እምነት ሲያራምድ ይታያል። አረቡን አለም ባህሉ አይፈቅድለትም…

አፍሪካዊያንማ- በጣም ኋላ ቀር ስለሆኑ እርሷቸው የሚል አይነት ሰንካላ ምልከታ ነው የሚታየው።

“ይህንን ደግሞ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በቅርቡ በይፋ ያመኑት ጉዳይ ነው።

‘የውጭ ፖሊሲያችን በተወሰነ ደረጃ ዘረኝነት ይታይበታል። የምእራቡ አለም ብቻ ነው ለዲሞክራሲ የተዘጋጀው በሚል መነጽር ማየታችን ስህተት ነው’ እስከማለት መድረሳቸውን ዶ/ር ብርሃኑ ያስታውሳሉ።”

በተለይ በዚህ ወቅት በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የተቀጣጠለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለምእራቡ አለም የሚያስተላልፈው ጠንካራ መልእክት አለው። ይህም ጊዜው ቁጭ ብለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን እንዲመረምሩ የግድ የሚል መሆኑን ነው። ባይ ናቸው።

“አለም እየተቀየረች ነው ያልተቀረው ግን ይህ ፖሊሲያችሁ ነው የሚል ጠንካራ ትችትም አቅርበውላቸዋል።

“አፍሪካዊያን በያሉበት ለዲሞክራሲ ይታገላሉ” የሚሉት ዶ/ር ብርሃኑ የምእራቡ አለም አሁኑኑ እጁን አስገብቶ ለሂደቱ እገዛ ካላደረገ በቀር የሚደርሰውን ቀውስ ማስቆም ያስቸግራል ብለዋል። ለአምባገነኖቹ አይነተኛውን የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጠው ምእራቡ አለም እንደመሆኑ ተገቢውን ተጽእኖ የማሳደር አቅሙም አለው።

“ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንግስት በ2008 ዓም ብቻ ወደ 3.2 ቢሊየን ብር በእርዳታ አግኝቷል። ይህ ገንዘብ ለአንድ ደሃ መንግስት ወታደራዊ ጡንቻ ማሳበጫና የደህንነት ተቋማቱን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ ሊሰጥ የሚችል ነው። “በእርግጥ እንደ እናንተ (ኖርዌይ) አይነት አገሮች የገንዘብ ድጋፍ ስታደርጉ ለትምህርትና ለዲሞክራሲ ሂደት ነው ትላላችሁ። ለዚህ የምታሳዩት ምን አላችሁ?” በሚል ባለስጣናቱን መጠየቃቸውን ዶ/ሩ ይጠቅሳሉ። ሙግታቸውን በዚህ አላቆሙም ። ኖርዌይ ባለፉት 20 አመታት ለኢትዮጵያ መንግስት ስትረዳ የቆየችው ከፍተኛ ገንዘብ ለዲሞርራታይዜሽን እገዛ ለማድረግ ከነበረ እስቲ በውጤቱ አገሪቱ ከዲሞክራሲ እየራቀች ሄደች ወይስ ወደ ዲሞክራሲ እየቀረበች መጣች? ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ ብለዋቸዋል። ለአስረጅ ያህልም ኢትዮጵያን በሁለት ሺህ አምስትና በሁለትሺህ አስር የምርጫ አመታት አናጽሮ ያያት ሰው ጭራሽ ከዲሞክራሲ ርቃ መሄዷን ነው የሚያረጋግጠው። ለዚህም ነው ወቅቱ ቁጭ ብሎ ፖሊሲያችሁን መመርመሪያና በእርግጥ ምን እየሰራን ነው ብሎ ግምገማ ማድረጊያ መሆን የሚገባው።

“ከኖርዌይ ግብር ከፋይ ህዝብ የሚሰበሰበውን ገንዘብ በእርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲረዳበት ከሆነ የምትልኩት ከአሁን በኋላ የምንረዳው ትክክለኛ ህዝባዊ ውክልና ላገኘ መንግስት ብቻ ነው የሚል ጥርት ያለ ፖሊሲ ሊኖራችሁ የገባል። እርዳታችሁ በትክክል ለህዝብ ጥቅም የሚውለው ያን ጊዜ ብቻ ነውና የሚል ክርክራቸውን አቅርበዋል።

እንደ ዶ/ር ብርሃኑ እምነት ከሆነ የምእራቡ አለም ጥርት ያለ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከወዲሁ ቢቀርጽ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ማስቆም ይቻላል። ግጭት ሳይፈጠር ሰላማዊ ሽግግር እንዲኖር ተጽእኖ የማሳደሪያው ጊዜ ደግሞ አሁን ነው። አንዴ የተቆጣ ህዝብ ሰልፍ ከወጣና አምባገነኖች መግደል ከጀመሩ በኋላ አደጋውን ለማስቆም ያስቸግራል።” የሚሉት ዶ/ር ብርሃኑ ብቸኛውና ትክክለኛ መንገድ ህዝብ ዲሞክራሲ ይገባዋል፣ ነጻነቱን ማስከበር ያስፈልጋል የሚል አቋም ወስዶ በግልጽ ከህዝቡ ጎን መቆም መሆኑን አመላክተዋል።

በዚህ ከባለስልጣናቱ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ገንዘባቸውን ለአምባገነኖች ጡንቻ ማፈርጠሚያ እንዳያውሉት አበክረው የጠየቁ ቢሆንም ይህ ተማጽኗቸው በኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዙሪያ ምን አይነት ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ግን ለመገመት አልፈለጉም።

በቤተ ክርስቲያናት ቃጠሎ ዙሪያ በቅርቡ በጅማ አካባቢ በእስልምናና በክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች መሀል የተቀሰቀሰውን ግጭትና በዚህም ሳቢያ አክራሪ ሙስሊሞች በርካታ ቤተ ክርስቲያናትን ስላቃጠሉበት ሁኔታም ለዶ/ር ብርሃኑ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። “በእርግጥ በአካባቢው የተፈጠሩ ሁኔታዎች ቀስቅሰውት ይሆናል እንደሰማሁት ሙስሊሞቹ ‘አንድ ክርስቲያን ቁርአን አቃጠለ’ የሚል ወሬ ተናፍሶላቸው ነበር ይባላል። ይሁንና ይህንንና መሰል ችግሮችን መመልከት የሚገባን ከምንጩ ነው” በማለት በመንግስት ደረጃ በይፋ የሚካሄደውን ከፋፋይ ፖሊሲ ይተቻሉ።


ፎቶ በአበበ ደመቀ

አምባገነኖች በሙሉ ህዝብን በመከፋፈል ሁሌም በስልጣን ላይ መቆየት የሚችሉ ይመስላቸዋል። የነጻነት ጥያቄ በጋራ እንዲነሳባቸው አይፈልጉም። ይልቁንስ ህብረተሰቡ ተከፋፍሎ አንዱ ወገን ሌላውን በጥላቻ እንዲያየው፤ በዚሀም ህዝቡ ይህ መንግስት ከሌለ በቀር በሰላም መኖር እንደማይችል አድርጎ እንዲያስብ ይመኛሉ። ይህ ባህሪ በሁሉም አምባገነኖች ላይ የሚታይ ነው። በተለይ በኢትዮጵያ ግን በእርግጥ እየተሰራበት ነው። በአገሪቷ ታሪክ የህዝቦች ዋንኛው መገለጫ የተገኙበት ብሄር ነው ብሎ በፖሊሲ ደረጃ ያስቀመጠው ይህ መንግስት ብቻ ነው። አንተ አንተን የሆንከው በጎሳህ ነው ትባላለህ። ትልቁ የመከፋፈያ መሳሪያቸው ደግሞ አንዱ ጎሳ በሌላው፣ የአንዱ ሀይማኖት ተከታይ በሌላ ሀይማኖት ተከታይ በሆነው ወንድሙ ላይ እንዲነሳ መገፋፋት ነው። ከአሁን በፊት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የጎሳ ግጭቶች ይሁነኝ ተብለው በመንግስት ተቀስቅሰው ነበር።

“በአሁኑ የቤተክርስቲያናት ቃጠሎ ወቅትም የአካባቢው ፖሊሶች ዳር ቆመው ይመለከቱ እንደነበር ኢሳት በሪፖርቱ አሳይቷል። ፖሊስ ችግሩን ለማስቆምም ሆነ እርዳታ ለመስጠት ያልፈለገበት ሁኔታ አጠያያቂ ነው። ስለዚህ ችግሩ በአካባቢው በተፈጠረ ሁኔታ የተቀሰቀሰ ሊሆን ቢችል እንኳን በመንግስት ደረጃ ሆን ተብሎ የሚካሄደው መከፋፈል ግን የግጭቶች መሰረታዊ ችግር ይሆናል።” እንደ ዶ/ር ብርሃኑ እምነት።

በኢትዮጵያ የተቃውሞ ኃይሎች ላይ የሚደረገውን ወከባ በተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች የሚደርስባቸውን ተጽእኖ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ብርሃኑ ሁነቱን የሚገልጹት በተለይ ከ1997 ዓም ወዲህ እንዴት እየባሰበት እንደመጣ በመገምገም ነው።

እንደሳቸው እምነት 1997 ዓ.ም ትንሽም ቢሆን ነጻ የሚመስል ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገበት አመት ነበር። በሂደቱ መንግስት በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን ማጣቱ በይፋ ታይቶ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያችን ሀገር በህዝቡ በጎ ፈቃድ መምራት እንደማይችል ያለ አንዳች ጥርጥር ተገንዝቧል። ቀረኝ ያለው ብቸኛ አማራጭ ሰፊ አፈና ማድረግና ህብረተሰቡን በፍርሃት ጠፍሮ መያዙን ብቻ ሁኗል። ባለፉት አምስት አመታት በተግባር ያደረጉትም ይህንኑ ነው። ይሁንና አሁን በሰሜን አፍሪካ የተስተዋለው ሁኔታ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ማናቸውም አምባገነን ቢሆን ያን በመሰለ የአፈና አገዛዝ ረዥም እድሜ ሊቀጥል እንደማይችል ያረጋገጠ እውነት ነው። ይህ ደግሞ እንደሌሎች አምባገነኖች ሁሉ እነሱንም ትልቅ ሽብር ውስጥ ከቷቸዋል። የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ሳይነሳ ለማፈን በመመኘት የቀድሞ ማጥቃት እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። ንቁ ተቃዋሚ የሆኑ በርካታ ሰዎችን እያሰሩ በአኳያው ደግሞ መጠነ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ እያሰራጩ ነው። ያም ሆኖ ግን ህዝባዊውን እንቅስቃሴ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣት ሊያስቆሙት አይችሉም።

የተቃዋሚ ኃይሎች ጥንካሬን በተመለከተ ሌላው ለዶ/ር ብርሃኑ የቀረበላቸው ጥያቄ የተቃዋሚ ኃይሎችን ጥንካሬ የሚፈትሽ ነበር። በሰሜን አፍሪካ በተለይ ደግሞ በሊቢያ ይህ ነው የሚባል ተቃዋሚ ድርጅት ባይኖርም ህዝቡን ከማመጽ ያስቆመው ነገር እንደሌለም ጥያቄው ላይ በንጽጽር ተመልክቷል።

“እንደሚታወቀው አምባገነኖች ይህ ነው የሚባልና መንግስት ሊተካ የሚችል ኃይል እንዲኖር አይፈልጉም” ይላሉ ዶ/ር ብርሃኑ። “ያሉትንም ለመበታተን ነው የሚደክሙት። ተጠናክሮ የቆመ የተቃውሞ ኃይል አለመኖር እነሱን የተሻሉ አስመስሎ እንዲያሳያቸው ነው ምኞታቸው። ሌላው አማራጭ ግን ቀውስ ብቻ ነው የሚሆነው የሚል ስጋት ህዝቡ ውስጥ ለማስረጽ ይፈልጋሉ።

“ቤን አሊን ተመልከቱ፣ ሙባረክን ወይንም ጋዳፊን ስሟቸው ሁሉም ህዝባዊ ጥያቄ ሲበረታባቸው የሰጡት መልስ ተመሳሳይ ነው። ‘እኔ ስልጣኔን ብልቅ ሀገሪቱ ቀውስ ውስጥ ትገባለች የእርስ በርስ ጦርነትም ይከሰታል።’ ነበር ያሉት ይህ የተበላበት ክርክር ሲሆን የሚያሳዝነው ግን የምእራቡ አለም መሪዎች በተወሰነ ደረጃ ሊቀበሉት የመፈለግ አዝማሚያ የሚያሳዩ መሆናቸው ነው።

“ይህ ወቅት በተግባር ያረጋገጠው ነገር ሌላው ቀርቶ የተቃዋሚ ፓርቲ ሳይኖር እንኳን ህዝብ ነጻነቱን ካገኘ ወደ እርስ በርስ ጦርነት የማያመራ መሆኑን ነው። ህዝቡ ነጻነት የሚመጣው ከሀላፊነት ጋር መሆኑን ጠንቅቆ ይገነዘባል።

“በታሂር አደባባይ የፈሰሰው ሰልፈኛ የመንገዱን ሰላም እያስከበረ፣ ሙዚየሙን ከሌቦች ተከላክሎ እየጠበቀ ነበር የሀላፊነት ብቃቱን ያረጋገጠው። የተደራጀ ሀይልን እያጠፉ ‘ሊተካኝ ዝግጁ የሆነ ኃይል ስለሌ ለእኔ ስልጣን ብለቅ ሀገሪቱ ትታመሳለች’ የሚለው የአምባገነኖች ጩኸት ትርጉመ ቢስ መሆኑ ነው በተግባር የታየው።

“በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ኃይል ነበር። ሰላማዊም ታጣቂም ኃይሎች አሉ። ባለፉት ጥቂት አመታት በተቃዋሚ ኃይሎች የተደረሰበት ግንዛቤም ህዝቡ በሚፈልገው ፍጥነት ነጻነታችንን ያላስገኘነው በጋራ መቆም ባለመቻላችን ነው የሚል ነው። በአሁኑ ወቅት ግን የተለያዩ የተቃዋሚ ኃይሎች በጋራ ስለመጭው ጊዜ እየመከሩና ትግላቸውን ማቀናጀት በሚችሉበት ስልት ላይ እየተወያዩ ነው። ይህ ደግሞ ተስፋችንን ካሳደጉ ሂደቶች አንዱ ነው። በብዙ ሰዎችና ተቃዋሚ ኃይሎች ዘንድ አሁን ያለው መንግስት በሀገሪቱ ታሪክ የመጨረሻው አምባገነን እንደሚሆን ጠንካራ እምነት አለ። በምርጫ አሸንፎ ለስልጣን የሚበቃ ማናቸውም መጭ መንግስት የግልም ሆነ የቡድን መብትን የሚያስከብር እንደሚሆን፤ መሰረቱም በዜጎች መሰረታዊ መብቶች መከበር ላይ እንደሚገነባ ግንዛቤ አለ። የተለያዩ ባህሎችና ቋንቋዎች የመከበር ሁኔታም ጥያቄ ውስጥ የማይገባ መሆኑን ሁሉም ስለሚስማማበት በብሄርም ሆነ በብሄራዊ ደረጃ የተደራጁ ኃይሎች ሁሉም በጋራ መስራት የሚችሉበትን እድል የሚፈጥር ሁኔታ ነው የታየው” ሲሉ ዶ/ሩ ያለቸውን እምነት ገልጸዋል።

የስደተኞች ጉዳይን በተመለከተ

ጋዜጠኞቹ ለዶ/ሩ ያቀረቡት ሌላው ጥያቄ በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በተመለከተ ነበር። ከጥቂት ወራት በፊት በዚያች ሀገር ውስጥ ለአመታት የኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የስራ ፈቃዳቸውን ተነጥቀው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በመጠየቃቸው በአንድ ቤተ ክርስቲያን ተጠግተው ብሶታቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ይታወሳል። እነዚህ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱ ችግር ይደርስባቸዋል ወይ?

የሚል ነበር ጥያቄው።

ዶ/ር ብርሃኑ የየግለሰቡን ኬዝ ስለማያውቁ ስለያንዳንዱ ለመመለስ እንደሚቸገሩ ካሳወቁ በኋላ ጥያቄው ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያደርጉ ስደተኞችን የሚመለከት ከሆነ ግን በኖርዌይም ሆነ በሌሎች ሀገራት የሚያቀርቡት የጥገኝነት ጥያቄ በጎ ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባው አጠንክረው ተሟግተዋል።

“በኢትዮጵያ ያለው መንግስት ጨካኝ ነው” ይላሉ ዶ/ር ብርሃኑ። የተቃዋሚ እንቅስቃሴዎችን የሚደግፉ ሁሉ ኢላማዎቹ ናቸው። ክሶች በነጻ ፍርድ ቤቶች ሙግት የሚካሄድባቸው አይደሉም። የፖለቲከ ክስ ከመጣ በአጭሩ ዳኞች ምን መፍረድ እንዳለባቸው ከመንግስት በቀጥታ የሚታዘዙባት አገር ናት ያለችን” የሚሉት ዶ/ር ብርሃኑ በጠቅላላው ገንቢ ነው የሚሉትን የመፍትሄ ሀሳብም እንደሚከተለው አመላክተዋል።

“የኢሚግሬሽን ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ዋናው መፍትሄ የኢትዮጲያን አይነት ሀገሮችን ወደ ዴሚክራሲ እንዲሸጋገሩ ማገዝ ነው። እነዚህ ሀገሮች ነጻና የዲሞክራሲ መብት የሚከበርባቸው ሀገራት መሆን ከቻሉ ያኔ የሚኖረው ስደተኛ የኢኮኖሚ እንጅ የፖለቲካ አይሆንም። አሁን ባለው ሁኔታ ግን አምባገነኑን የምትረዱት እናንተው ናችሁ፤ እነዚህ ስደተኞች ደግሞ በስርአቱ በደል ደርሶባቸው የተገፉ ናቸው። ታዲያ በየትኛው የሞራል መለኪያ ነው ከለላ ልንሰጣችሁ አንችልም ማለት የምትችሉት?” የሚል የሞራል ጥያቄ አቅርበዋል።

የቃለ ምልልሱ የመጨረሻው ጥያቄ በኢትዮጵያ ሊመጣ የሚችለው ቀጣይ እንቅስቃሴ ምን ሊመስል እንደሚችል የሚጠይቅ ነበር።

“የዲሞክራሲ ጥያቄውን ተንተርሶ የለውጥ እንቅስቃሴ እንደሚጀመር ጥርጥር የለኝም” ይላሉ ዶክተሩ። “ ይህም በቅርብ ጊዜ የሚሆን ነው። የተሳካ እንዲሆንም ማድረግ ያለብንን እያደረግን ነው። ውጤቱ የተረጋጋ እና ውስጣዊ ሰላም ያለው እንዲሁም መጠነ ብዙ ለሆኑ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ እንዲሆን እየሰራን ነው።

“ለውጡ በኛ ድርጅት ብቻ የሚመጣ አይሆንም። ሊሆንም አይገባውም። ሀገር ቤት ያሉትን ጨምሮ በሁሉም የተቃዋሚ ኃይሎች የጋራ ጥረት እንጂ። ሁሉን አቀፍ ሰፊ የድርጅቶች ህብረት እንዲኖር እየሰራን ነው። የኛ ጥያቄ ማን ወደ ስልጣን ይምጣ የሚል አይደለም።

እንዴት ይምጣ የሚል እንጅ። የምንታገለው ስለሂደቱ ትክክለኛነት እንጂ ስላሸናፊው ምንነት አይደለም።” ሲሉ ዶ/ር ብርሃኑ ምላሽ ሰጥተዋል።

__________

ስለ ቃለ ምልልሱ አስተያየት ካለዎት ጋዜጠኛ ግርማ እንድሪያስን በዚህ ኢሜይል ያግኙ girma077@gmail.com

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on March 29, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.