ድንቅ ውሳኔ በማስተላለፍ የተጠናቀቀው የኦነግ ስብሰባ በሚኒሶታ

(የዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ሪፖርተሮች) ለአንድ ለሁለት ሳምንታት ጋብ ብሎ ባልተለመደ መልኩ ጠፍቶ የነበረው የሚኒሶታ በረዶ ትናንት ማምሻውን አዲስ ዓመትን እየተቀበልን ባለበት ሰዓት መስታወት የመሰለ በረዶ ጥሎ ከተማዋን ነጭ በነጭ አድርጓታል። ነጭ ደግሞ የሰላም፣ የደስታና የአንድነት መግለጫ ነው። የኦሮሞ ነጻነት ግንባርም በሚኒሶታ ከኢትዮጵያውያን ጋር ባደረገው ሕዝባዊ ስብሰባ ታሪካዊ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ አዲሱን ዓመት ልክ እንደሚኒሶታ አየር ጠባይ በነጭ እንድንቀበለው አድርጓል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከሕዝብ ጋር ለመወያየት በጠራው ስብሰባ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በቪዲዮ ጄነራል ጀማል ገልቹ ነበሩ። ጄነራሉ ንግግራቸውን የጀመሩት እስካሁን በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስር ሆነው ለታገሉና ለተሰው ታጋዮች ያላቸውን አክብሮት በመግለጽ ግንባሩ እስካሁን ያደረገውን የትግል እንቅስቃሴ መርምረዋል።

ከዛም በኋላ በአሁኑ ወቅት ኦነግ ኢትዮጵያዊነቱን ተቀብሎ ለመታገል ለምን እንደወሰነ ለተሰብሳቢው አስረድተዋል። ጀነራል ከማል “እስካሁን ድረስ የኦሮሞ ሕዝብ ሲነገረው የነበረው ትክክል አልነበረም። አሁን ግን እውነቱን እየነገርነው ነው። ድሮ የኦሮሞን ሕዝብ ኢትዮጵያዊ አይደለህም እየተባለ ነበር። እውነቱ ግን የኦሮሞ ሕዝብ የኢትዮጵያ ግንድ ነው። እንዴት ነው ግንድ ከሆነበት የሚገነጠለው? “ ሲሉ ንግግራቸውን ቀጥለው “በአዲሱ የትግል አቅጣጫ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንታገላለን። ኦነግ አሁን ይህንን አዲስ የትግል አቅጣጫ የቀየሰው ዘመኑንና የዚህን ትውልድ አመላለከትና ተጨባጭ ሁኔታዎችን በመገንዘብ ነው” ያሉት ጄነራል ከማል ገልቹ “ትግላችን ኢትዮጵያን ለመምራት ሳይሆን የኢትዮጵያን ሲስተም በተሻለ ሲስተም መቀየር ነው” በማለት አሁን ያለውን የውሸት የወያኔ ፌደራሊዝም ወደተሻለ ፌዴራሊዝም መቀየር ነው አላማችን ብለዋል።

“ሕዝቦች እየተጨቆኑ ነው፤ ተከፋፍለን መታገል የወያኔን ዕድሜ ማራዘም ነው” ያሉት ጀነራሉ “አዲስ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊት ሃገር ኢትዮጵያን ለመገንባትና በጋራና በእኩልነት ለመኖር የአድነት ግንባር እንፍጠር” በማለት በሃገር ቤትም ሆነ በውጭ ሃገር የሚገኙ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተባብሮ ለአንድ ኢትዮጵያ የሚታገሉበትን ጥሪ አቅርበዋል። በዚህም ወቅት አዳራሹ በጭብጨባ ናኝቷል።

በስብሰባው ላይ የተገኙ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን አሁን ኦነግ በወሰደው አቋም እጅጉን መደሰታቸውን በመግለጽ “የኦሮሞ ባህላችን እና ቋንቋችን እስከተከበረ ድረስ እነዚህን መሪዎቻችንን ያመጡልንን ቅዱስ ሃሳብ ልንቀበል ይገባል” የሚሉ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። በመድረኩም በኦነግ አዲሱ የትግል አቅጣጫ ዙሪያ ጥያቄዎች ቀርበዋል። ከነዚህም መካከል በተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመስርቶ ስለነበረው ኤኤፍ ዲ፤ ከግንቦት ሰባት ጋር አብሮ ስለመሰራት፤ እንደዚሁም ስለሌሎች በርከት ያሉ ጉዳዮችና ስለአዲሱ የኦነግ የትግል አቅጣጫ ጥያቄዎች ቀርበው መድረኩን ሲመሩ ከነበሩት የኦነግ የማ ዕከላዊ ኮሚቴ አመራር አባል አቶ ተማም ባቲ እና ከድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አቶ አሚን ጁዲ ምላሽ ተስጥተዋል።

“የኦነግ የትግል ዓላማ መመሪያ እንጂ መተዳደሪያ አይደለም። መተዳደሪያውን የሚመርጠው ሕዝብ ነው።” ያሉት አቶ ተማም ባቲ “በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደርን ለመፍጠር ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብረን እንሰራለን። አሁን ያለው ስርዓት የብሄር ብሄረሰቦችን መብት እያስከበርኩ ነው ቢልም ውሸት ነው። ትክክለኛውን የሕዝቦች መብት ለማስከበር መነሳትና በአዲስ ሃሳብ አንድ ሆነን እንታገላለን” ብለዋል።

የግንባሩ ዋና ጸሃፊ አቶ አሚን ጁዲ “እስካሁን ድረስ ከማንም ጋር ግንባር አልፈጠርንም። ግን የራሳችንን ፕሮግራም ስንቀርጽ ነበር የቆየነው። ይህንን ዛሬ የወሰድነውን አቋም ማንንም ለማስደሰት ስንል አይደለም የወሰድነው። ለኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር ያስፈልጋታል፤ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት እንደወያኔ የውሸት ሳይሆን በትክክል የሚያስከብር ስርዓት መፈጠር ስላለበት ነው ይህንን ውሳኔ የወሰንነው።” በማለት አሁን ኦነግ የወሰደውን አዲስ አቋም አስረድተዋል።

“አሁን ያለው የወያኔ ፌደራሊዝም የኦሮሞን ሕዝብም ሆነ የሌላውን ሕዝብ መብት እያስከበረ አይደለም። አሁን ያለው ሲስተም በየሁለት ዓመቱ ጁነዲን እየተባረረ፣ አባዱላ እየተተካ፤ ኩማ እየመራ እየሄደ የመለስ ዜናዊን የቤት ሥራ ይሰራል እንጂ ምንም ዓይነት የሕዝብ ውክልና የለውም” ያሉት አቶ አሚን “የኛን መብት ከሚያስከብር ና ከሚያከበር ሁሉ ጋር አብረን እንሰራለን።” ብለዋል።

አቶ አሚን ንግግራቸውን ቀጥለው “የወያኔ አንቀጽ 39 (የብሄረሰቦች መብት እስከመገንጠል የሚለው) መሸንገያ አንቀጽ እንጂ የብሄረሰቦችን መብት ያስከበረ አይደለም። ሕገመንግስቱን ስትመለከቱት ይህንን አንቀጽ የሚያፈርሱ በርካታ ነገሮችን አስቀምጧል” ያሉት አቶ አሚን “አጼ ምኒልክ እና አጼ ሃይለ ሥላሴ ለሰሩት ጥፋት የልጅ ልጆቻቸው መጠየቅ የለባቸውም። ያለፈውን ታሪክ የመጽሀፍ መደርደሪያ ላይ አስቀምጠን አሁን ይህኛው ትውልድ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ መዘጋጀት አለበት እንጂ በአያቶቹ ጥፋት የሚከሰስ ትውልድ መኖር የለበትም። በዘር ተከፋፈሎ እንደዚህ ስንባል ነበር እየተባሉ መለያየት የሚጠቅመው አሁን ላለው የወያኔ ስር ዓት እንጂ ዲሞክራቲክ ትግሉን አይደለም። የኦሮሞ ሕዝብ አዲስ ትውልድ አመለካከቱ በጣም እያደገ ነው። ከኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ተባብሮ በአንድነት ተስማምቶ የሚኖርበትን ሁኔታ ይፈልጋል። ስለዚህ በጋራ በአንድ ኢትዮጵያዊነት ስር የሚያኖረንን ስልት መከተል አለብን” ሲሉ ተናግረዋል።

ዛሬ በሚኒያፖሊስ የተጠራው ስብሰባ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን እንዲያሳትፍ ቀድሞ የታቀደ ቢሆንም ትናንትና ከትናንት በስቲያ ዲሴምበር 30 እና 31 የድርጅቱ አመራር አባላት በዝግ ባደረጉት ስብሰባ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት ስብሰባ ከመጠራቱ በፊት የኦሮሞን ሕዝብ በቅድሚያ ማሳመን አለብን በሚል ተወስኗል። በዚህም መሰረት በቅርብ ቀን ትልቅ የኢትዮጵያውያን ስብሰባ እንደሚጠራ ኦነግ አስታውቋል። በዛሬው እለት ኦነግ ኢትዮጵያዊነቱን አምኖና ተቀብሎ ለአዲስ የትግል ስልት መዘጋጀቱን በርከት ያሉ የስብሰባው ታዳሚዎች ካለመንም ተቃውሞ ደግፈው ለስራ ተዘጋጅተዋል። ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኋላም እንኳን ደስ ያለን እየተባባሉ እንደነበር የዘ-ሐበሻ ጋዜጣ አዘጋጅ ተመልክቷል።

ስብሰባው በኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ብሄረሰብ ባህል መሰረት በአባቶች ምርቃት ነበር የተዘጋው። ትላልቅ አባቶች ባደረጉት ምርቃትም አዲሱ የትግል አቅጣጫ ከግብ እንዲደርስ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በስብሰባው ላይ ከተሳተፉት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የሆነውና በሚኒሶታ የሚኖረው ፉአድ አባነሻ ለዘ-ሐበሻ በሰጠው መግለጫ “እኔ እስካሁን ድረስ ባረጀው የኦነግ ሃሳብ ላይ ነበርኩ። የቀድሞው ትግል ስልት ጥሩ አለመሆኑን ተረድቻለሁ። እስካሁን ለወያኔ ተመቻችተን ነበር የተቀመጥነው። የሚያዋጣው አንድ ሆኖ በአንድ ላይ መታገልና አብሮ መኖር ነው። በዛሬው የኦነግ አዲስ የትግል ስልት በጣም ተደስቻለሁ። በጋራ ታግለን ሃገራችንን ከወያኔ ነጻ እናወጣታለን” ብሎናል።

የኦነግን መግለጫ ለማንበብ የሚከተለውን ይጫኑ OLF_National_Council_Press_Release_final

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 2, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.