ድርቅ፤ ረሃብ፤ የውጭ ርዳታና የምግብ ዋስትና የማጣታችን አዙሪት

ከንጉሤ ጋማ

በአሁኑ ወቅት በአፍሪቃ ቀንድ አገሮች በሶማሊያ፤ በኬንያ፤ በጂቡቲና በኢትዮጵያ በ60 አመት ታሪክ ዉስጥ ያልታየ በአይነቱ አስከፊ የሆነ የድርቅ አደጋ ተከስቷል። በዚህም 4.5 ሚሊዮን በሚሆኑ ወገኖቻችን ላይ የሞት አደጋ አንዣቧል።

በመላዉ አለም በድርቅና በረሃብ በመደጋገም ከሚጠቀሱትና ከሚታወቁት አገሮች ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። አለመታደል ሆኖ እንጂ ኢትዮጵያ ባላት ለም የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ ልትሆን ብትችል በምግብ ሰብል እራሷን መቻል ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአካባቢዉ ተጠቂዎች መድረስ ያስችላት እንደነበር አያከራክርም።

ግልፅነት፤ ተጠያቂነትና በሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የመልካም አስተዳደር አለመኖር የረሃባችን መሰረታዊ ምንጭ ነዉ። የምግብ ዋስትናችን አለመረጋገጥና በረሃብተኛዉ ስም ከዉጭ በሚገኘዉ ርዳታ ባለፀጋና የስልጣን ባለቤት የሆኑ ጥቂት የገዢ መደብ አባላትን፤ ደጋፊዎቻቸዉንና አቀባዮቻቸዉን ጥቅም ያስቀራል፤ይጎዳል። በሚሊዮን በሚቆጠረዉ ድሃ የህብረተሰብ ክፍል ህይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰዉ ሞትና ዉድቀት፤ ስደትና ዉርደት በየስርአቱ በጣት ለሚቆጠሩ ጥቂቶች የብልፅግናና የቅንጦት ሕይወት የማይነጥፍ የገቢ ምንጭ መሆኑ አያከራክረንም።

የዚህ ፅሑፍ አላማ በኢትዮጵያና ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪቃ አገሮች በየጊዜዉ የሚከሰተዉን የረሃብ አደጋ በተመለከተ በካናዳ ኦታዋ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ርዕስ ቀልቤን ስለሳበዉ በግርድፍ ትርጉም መሰረታዊ ነጥቦቹን ለአንባቢያን ለማካፈል ነዉ። ለተሟላ ግንዛቤ አንባቢዎቼ ዋናዉን ፅሁፍ እንዲያነቡ እመክራለሁ።

ፕሮፌሰር ማይክል ቾሱዶ-ቪስኪ Michel Chossudovsky በኢትዮጵያ ዉስጥ የረሃብን ዘር መዝራት Sowing the Seeds of Famine in Ethiopia በሚለዉ የዛሬ 10 አመት እኤአ በመስከረም 2001 ባቀረቡት ፅሁፍ

http://www.globalresearch.ca/index.php?context=va&aid=366

በአፍሪቃ ቀንድ አገሮች በየጊዜዉ ለሚታየዉ ረሃብና የማህበራዊ ዉድመት ምክንያቱ የአለም የገንዘብ ድርጅት/ አይ ኤም ኤፍ/ እና የአለም ባንክ ያረቀቁት “የኢኮኖሚ ፈዉስ” structural adjustment program (SAP), ነዉ።

መድሃኒት ተደርጎ የተቆጠረዉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በግብርና ላይ የተመሰረተዉን ኢኮኖሚ በማጥፋት በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብን ድህነት ዉስጥ የጣለ በአንፃሩ የዩናይትድ ስቴትስ የባዮ ቴክ ኮርፖሬሽኖች ለነበራቸዉ ድብቅ አላማ፤ ጥቅምና ትርፍ በር የከፈተ ነበር

በግብርናዉ ዘርፍ የተለመዱት የእህልና የጥራጥሬ ዘሮች በረሃብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ርዳታ ምክንያት በሚመጡት በዘመናዊ ዘዴ በተዳቀሉና በተሻሻሉ ዘሮች በየደረጃዉ እንዲተኩና እንዲጠፉ ተደረገ።

ግዙፍ የሆኑ የምግብ ድርጅቶች ከአለም የንግድ ድርጅት በሚያገኙት ድጋፍ እየተረዱ በየአገሩ መንግስታት የያዟቸዉን የምግብ ፕሮግራሞች እንዲሰርዙ አስገደዱዋቸዉ። የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ክምችት እንዳይኖር፤ የዘር ባንክ፤ የእርሻ አክስቴንሽን አግልግሎቶችና የእርሻ ብድሮች እንዲቋረጡ በማድረግ ከግል ጥቅማቸዉ አንፃር የግብርናዉ ኢኮኖሚ እንዲወድቅና የረሃብ አደጋዎች እንዲደቀኑ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጠሩ።

በተጨማሪ በአለም የንግድ ድርጅት ህግ መሰረት የእርሻ ባዮ ቴክ ድርጅቶች የገበያ ሃይሎችን የግል መጠቀሚያቸዉ በማድረግ ለገበሬዎች በሚያቀርቡት “ምርጥ ዘር” ምክንያት የባለቤትነት ክፍያ/ ሮያሊቲ / እንዲከፈላቸዉ እስከማድረግ ደረሱ።

የአለም ባንክና የአለም የምግብ ድርጅት እንዲተገበር ያደረጉት ነፃ ገበያና መራራ የሆነዉ የኢኮኖሚ “መድሃኒት” / የስትረክቸራል አጀስትሜንት ፕሮግራም/ structural adjustment program (SAP), የግብርና ጊዜያዊ ሰራተኞችንና መሬት የሌላቸዉ ገበሬዎችን የከፋ ድህነት ዉስጥ ጣላቸዉ።

ይህ በእንዲህ እያለ አለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ለምግብ ሰብል መጥፋት፤ የአየር ንብረትን የሰብአዊ ቀዉሱ ብቸኛ ምክንያት በማድረግ ያቀርባሉ።

የደርግ ስርአት ከስልጣን እንደተወገደ በለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ የአስቸኳይ ጊዜ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮግራም Emergency Recovery and Reconstruction Project (ERRP) በችኮላ ተግባራዊ መሆን ጀመረ። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ፤ በአሜሪካ የዉጭ ፖሊሲ የተደገፈዉ የአለም የገንዘብ ድርጅት “የፈዉስ መድሃኒት” ለኢትዮጵያ ታዘዘላት።

የማህበራዊ በጀት እንዲቀነስ ሲደረግ በሌላ በኩል ወታደራዊ ወጪዎች በከፊል በልማት ስም በሚመጡ ርዳታዎች በመደጎም እኤአ ከ1989 ወዲህ እንዲጨምር ተደርጓል። አሜሪካ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ለሁለቱ አገሮች የጦር መሳሪያ ሻጭ ሆነች፡፡ ከብድር በሚገኝ ገንዘብ የጦር መሳሪያ እንድትገዛ የተደረገች አገር ወደ ዉጭ ከምትልካቸዉ ምርቶች የምታገኘዉን የዉጭ ምንዛሪ ከግማሽ በላይ ለብድር ክፍያ እንድታዉል ተገደደች።

በአለም ባንክና በአለም የገንዘብ ድርጅት የተረቀቀዉን የፖሊሲ ፍሬም ዎርክ ወረቀት Policy Framework Paper (PFP) ኢህአዴግ ተቀበለዉ። አበዳሪዎች በመንግሰት የተያዙ ተቋማት፤ የንግድ፤የገንዘብ ድርጅቶች ፤ የመንግሰት እርሻና ፋብሪካዎች የመሳሰሉት ወደ ግል ሃብትነት እንዲዛወሩ፤ ፕራይስ ወትር ሃዉስ ኩፐር Price Waterhouse Cooper የተባለዉ ድርጅት ሽያጩን እንዲያስተባብር ሃላፊነት ተሰጠዉ። በሌላ በኩል ስልጣንን ከፌዴራል መንግሰት ወደ ታች  በማዉረድ ስም ብሪተን ዉድስ The Bretton Woods institute በተባለ ተቋም አስተባባሪነት ክልላዊ መንግስታትን የማዋቀር ስራ ተካሄደ።

የአለም ባንክ በጠየቀዉ መሰረት የእርሻዉን ገበያ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ፤ የመንግስት የዋጋ ቁጥጥር እንዲገታና ለገበሬዉ የሚሰጠዉ ድጎማ እንዲቆም ተደረገ።

በትራንስፖርትና በጭነት ዋጋዎች ላይ የነበረዉ ቁጥጥር እንዲነሳ በመደረጉ የእህል ዋጋ በገጠሩ አካባቢ ከሚገባዉ በላይ ናረ። በሌላ በኩል የእርሻ ግብአቶች ማዳበሪያንና ዘርን ጨምሮ በግል ነጋዴዎች እጅ እንዲወድቁ ተደረገ።

ፓየነር ሃይ ብሪድ Pioneer Hi-Bred የተባለዉ አለም አቀፍ ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሰት በብቸኝነት ካቋቋመዉ የኢትዮጵያ የምርጥ ዘር ድርጅት ጋር በጋራ እንዲሰሩ ተደረገ። ነፃ ገበያን ለማስፋፋት መንግሰት የሚወስዳቸዉን እርምጃዎች ለማበረታታት በ1992 በርካታ መጠን ያለዉ የማዳበሪያ እርዳታ ለገበሬዉ ተሰጠ።

አጠቃላይ አዝማሚያዉ በገጠሩ አካባቢ በተለይም ድሃ ገበሬዎች በያዟቸዉ አነስተኛ ምርት በሚሰጡ እርሻዎች ላይ ትልቅ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልዩነት መፍጠር መሆኑ በግልፅ ይታይ ነበር። ማዳበሪዉና ምርጥ ዘሩ በተወሰነ ደረጃ በተለይ በንግድ እርሻዎች ላይ ለዉጥ አምጥተዉ ነበር። በ1997 አትላንታ መሰረቱን ያደረገዉና በቆሎን ለማዳቀል የሚዉሉ የባዮ ቴክኖሎጂ ማሳሪያዎችን የሚያስተዋዉቀዉ የካርተር ማእከል፤ “ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እህል ለዉጭ ገበያ ማቅረብ ጀመረች” በማለት በኩራት ገለፀ።

በ1984/85 በኢትዮጵያ በደረሰዉ የከፋ የረሃብ ወቅት የተቋቋሙ የአስቸኳይ ጊዜ የእህል ማከማቻዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደረጉ። በአንፃሩ በአዉሮፓ ህብረት አገሮች ዉስጥ እንዳይገባ የተከለከለዉ በእፅዋት ኢንጂነሪንግ የተመረተዉ የአሜሪካ በቆሎ በአስቸኳይ የምግብ ርዳታ ስም በአፍሪቃ ቀንድ እንዲራገፍ ተደረገ።

በ1998/2000 በተከሰተዉ የረሃብ አደጋ ወቅት በከፍተኛ ጥቅም የበቆሎ ግዢዉንና የማጓጓዙን የስራ ኮንትራት የወሰዱት አርቸር ዳንኤል፤ ሚድላንድ Archer Daniels Midland (ADM)  እና ካርጊል ኮርፖሬሽን Cargill Inc የተባሉ የአሜሪካ ድርጅቶች ነበሩ ።

የአለም የምግብ ፕሮግራምን የመሳሰሉ ድርጅቶች ሁሉ እነዚህን ከሚገባዉ በላይ  በእፅዋት ኢንጂነሪንግ በመታገዝ የሚመረቱ የአሜሪካ ምርቶችን ከዩናይትድ ስቴትስ የአለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ እንዲያድሉ ተደረገ፤ አንዳንዶችም የተበላሹና የነቀዙ እህሎች ነበሩ።

አንድ የደቡብ አፍሪቃ ባዮ ዎች ቡድን South Africa’s Biowatch ” አፍሪቃ የአለም የቁሻሻ መጣያ ተደርጋ ተቆጥራለች፤ ጥራቱን ያልተቆጣጠሩትን ምግብና ዘር በእርዳታ መስጠት ሩህሩህነት ሳይሆን አፍሪቃን የዉጭ ርዳታ ጥገኛ ማድረግ ነዉ።” በማለት በወቅቱ ጽፏል። በሌላ በኩል በምግብ ለስራ ፕሮግራም ድሃ ገበሬዎች ከማምረት ይልቅ በሚሰፈርላቸዉ ምግብ በተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ላይ የጉልበት ስራ እንዲሰሩ ይደረግ ነበር።

በቡና ምርት ላይ የተሳተፉ አነስተኛ ገበሬዎች እንዲሁ በተለያየ መንገድ እንዲዳከሙ ተደርገዋል። ካርጊል ኢንኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ በተቋቋመዉ የስራ ተባባሪዉ የኢትዮጵያ ኮሞዲቲስ ኤክስቼንጅ Ethiopian Commodities አማካይነት የቡናና የእህል ገበያዉን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩት።

ከሁለት ሄክታር በታች በሆነ መሬት ላይ ከአገሪቱ አጠቃላይ የቡና ምርት 90-95% የሚሆነዉን የሚያመርቱት ቁጥራቸዉ ከ700 ሺህ የማያንሱ አነስተኛ ገበሬዎች በእርሻ ብድርና ሌሎች ድጋፎች አለማግኘትና ዝቅተኛ ተመን በተሰጠዉ የቡና ሽያጭ መነሻ ዋጋ ምክንያት ብዙ ጉዳት ዉስጥ እንዲወድቁ ሆነ።

ገበሬዉ ይጠቀምባቸዉ የነበሩት የአገሪቱ የማሽላ፤ ገብስ፤ ጤፍ የመሳሰሉት ዘሮች በተለያየ መንገድ በትላልቅ የዉጭ ድርጅቶች በተቋቋሙና የአለም ባንክ በፋይናንስ በደገፋቸዉ የዘር አቅራቢ ድርጅቶች ፈቃድ ስር እንዲወድቁ ተደረጉ።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ከአለም አቀፍ የበቆሎና የስንዴ ዘር ማሻሻያ ማእከል International Maize and Wheat Improvement Center (CIMMYT) ጋር በመተባበር የኢትዮጵያንና የሜክሲኮን የበቆሎ ዘሮች ለማዳቀል ይሰራል። እኤአ በ1940ዎቹ በፎርድና በሮክፌለር ፋዉንዴሽኖች ድጋፍ የተመሰረተዉ የበቆሎና የስንዴ ማሻሻያ አለም አቀፍ ማእከል በእርሻ ንግድ ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶችና በብሪታኒያ ከሚገኘዉ ኖርማን ቦርሎግ ኢንሰቲትዩት Norman Borlaug Institute, በመተባበር የዘር ምርምር ከሚያደርጉ ድርጅቶች  ጋር የጥቅም ግንኙነት ነበረዉ።

የገጠር ማሻሻያ ፋዉንዴሽን ወይንም Rural Advancement Foundation (RAFI) የተሰኘዉ ድርጅት “የኢትዮጵያን የማሽላ ዝርያዎች በማብቀል የአሜሪካ ገበሬዎች በያመቱ 150 ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ” በማለት በጊዜዉ ጠቅሷል።

እኤአ በ1998 የ1984/85 የደረሰዉን የድርቅ አደጋ ተከትሎ ከዕፅዋት ጄኔቲክ ማእከል Plant Genetic Resource Centre ጋር ችግሮችን መቋቋም በሚችሉ ዘሮች ላይ ምርምር ያደርግ የነበረዉ ተቋም ወይንም Seeds of Survival (SoS) የተባለዉ ፕሮግራም እንዲዘጋ ተደረገ።

የዚህ ተግባር ስዉር አጀንዳ በየአካባቢዉ በመባዛት በተለምዶ ይሰራጩ የነበሩት ችግር መቋቋም የሚችሉ ዘሮች ልዉዉጥ በገበሬዎች መካከል እንዳይካሄዱ ለመግታት ነበር።   የዘር ባንኮች በ1998/2000 ሙሉ በሙሉ ባዶ እንዲቀሩና ገበሬዉ ዘሩን እስኪበላ ችግር ዉስጥ እንዲወድቅ ተገደደ።

ረሀብ በአለም ባንክና በአለም የገንዘብ ድርጅት አማካይነት የተወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ዉጤት ነዉ። የማሻሻያ ፕሮግራሞቹ የኢትዮጵያን የእፅዋት ዝርያ በእጅጉ እንዲጠፋ አድርገዋል። ገበሬዉ በአካባቢ ደረጃ የሚያደርገዉ የዘር ልዉዉጥ በዘር አቅራቢ ድርጅቶች አማካይነት በሚሰራጩ የተዳቀሉና የተሻሻሉ የእፅዋት ዘሮች ተተኩ።

በሌላ በኩል ለድሃ ገበሬዎች የሚደረገዉ የምግብ ርዳታ የዘር እህልንም እንዲጨምር ተደረገ። የአለም የምግብ ፕሮግራምና የአሜሪካ የአለም አቀፍ የልማት ድርጅት ርዳታ ማዳበሪያንና የዘር እህልን በማካተት የእርሻ ንግድ የሚያስፋፉ ድርጅቶች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አደረጋቸዉ። የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታና የማሻሻያ ፕሮግራሞች መፍትሄ ከመሆን ይልቅ ለረሃብ ምክንያት መሆናቸዉን ፕሮፌሰር ማይክል ቾሱዶ-ቪስኪ “በኢትዮጵያ ዉስጥ የረሃብን ዘር መዝራት” በሚል ርእስ ባቀረቡት ፅሁፍ ገልፀዋል።

የኢኮኖሚ ባለሙያዉ የሰነዘሯቸዉ ጭብጦች በኢትዮጵያ በየጊዜዉ ለሚደርሰዉ እልቂት አስተዋፅኦ እንዳላቸዉ ባንክድም በድርቅና በረሃቡ ስም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅማቸዉ እንዳይነጥፍ  ከምግብ ርዳታ፤ ከሞት ከዉርደትና ከስደት አዙሪት እንዳንወጣ ገዢዎቻችን፤ ደጋፊዎቻቸዉና አቀባዮቻቸዉ ቀንደኛ ጠላቶቻችን መሆናቸዉን በሚገባ እንረዳለን።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 28, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.