ዴሞክራሲ በኢኮኖሚ ልማት ላይ ተጽእኖ ኣለው

ኣንዳንዶች ዴሞክራሲ ከኢኮኖሚ ልማት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ብለው ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ ዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ልማት ተፈጥሮኣዊ ግንኙነት ኣላቸው ወይም ዴሞክራሲ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ኣዎንታዊ ሚና ኣለው ብለው ኣጥብቀው ያምናሉ። ታዲያ በዚህች ኣጭር ጽሁፍ የነዚህን ወገኖች ሃሳብ በጥቂት በጥቂቱ ገረፍ ገረፍ ኣርገን ወደ መጨረሻ ላይ በግል ኣስተያየት ለመቋጨት ተነስተናል።

በመጀመሪያ ዴሞክራሲ ከልማት ጋር ግንኙነት የለውም የሚሉ ወገኖች በዴሞክራሲ ስለማያምኑ ኣይደለም። ዴሞክራሲ ለህዝቦች ኣስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው። ይሁን እንጂ ዴሞክራሲና የኢኮኖሚ እድገት በተራ በተራ ወይም ለየብቻ እንደየ ተፈጥሮኣቸው ሊያድጉ የሚገባቸው ናቸው የሚል ኣንድምታ ኣላቸው። የነዚህ ሰዎች የልብ ግፊት የሚመስለው ዴሞክራሲን የኢኮኖሚ እድገት ሊያመጣው ይችላል፤ የሰው ልጅ ኢኮኖሚክ ህይወቱ ሲሻሻል ፍላጎቱ እየጨመረ ይሄዳል የዴሞክራሲ ጥያቄውም እየጨመረ ይመጣል ስለዚህ የኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ማተኮር የህብረተሰብን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ኣይነተኛ መንገድ ነው የሚል ይመስላል።

እነዚህ ቡድኖች ኣልፈው ሄደውም ዴሞክራሲ በታሪክም ቢሆን ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ግንኙነት የለውም እስከማለት ይደርሳሉ። በነዚህ ሰዎች መረዳት የዛሬ መቶ ሁለት መቶ ኣመት በፊት ገና ዴሞክራሲ ሳይወለድ የኢኮኖሚ እድገት ነበር ሊሉ ይችላሉ። ምሳሌ ጥቀሱ ሲባል በፈጣን እድገቱዋ የምትታወቀው ደቡብ ኮርያም ብትሆን በ 1970ዎቹ ኢኮኖሚዋ መፈንዳት ሲጀምር ትተዳደር የነበረው በ ኣምባገነኑ ፕሬዚደንት ፓርክ ነበር። በዚያን ጊዜ የኮርያ ኢኮኖሚ ከመሬት የተነሳው ኢኮኖሚውን ዴሞክራሲ ስለደገፈው ኣይደለም ይላሉ።

የሲንጋፖሩ ሊኩዋን የው እና የድህረ ማኦ ቻይና መሪዎች ዴሞክራት ሳይሆኑ ለኢኮኖሚ እድገት ግን ከዴሞክራት መሪዎች በላይ ሰርተዋልሞ ይላሉ። የኣሁኑዋን ቻይናን ደሞ ኣጥብቀው ለመከራከሪያ የሚያቀርቡዋት ይመስላል። ቻይና በፖለቲካዊ ነጻነቱዋ ከኣለም መጨረሻ ከሚሰለፉ ኣገሮች ኣንዱዋ ስትሆን ድህነትን ለመቀነስ በምታደርገው ጥረት ደሞ በኣለም ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው ኣስር ኣገሮች መካከል ኣንዱዋ ናት። ይህ ተቃራኒ ሁኔታ የሚያሳየው የኢኮኖሚ እድገትና ዴሞክራሲ ባጣጥ በቀረጥ የማይገናኙ መሆናቸውን ነው እስከማለት ይደርሳሉ።

በሌለኛው ጎራ ያለው ኣመለካከት ደሞ የራቀ ነው። ሌሎች ደሞ ዴሞክራሲ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ኣለው ብለው ኣጥብቀው ያምናሉ። ከነዚህ ቡድኖች ውስጥ ኣንዳንዶቹ “በጎ ነገሮች ሁሉ ኣብረው ይሄዳሉ” ከሚል ቅን ስነ-ልቦና የመነጨ ነው። ሌሎች ደሞ በመረጃ የተደገፈ በቁጥር የተገለጸ ጥናት እያቀረቡ ዴሞክራሲ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ኣዎንታዊ ተጽእኖ ኣለው ይላሉ።

 

ብዙ በኢኮኖሚ የበለጸጉ ሃገራትን ስም እየጠሩ ዴሞክራቶች ናቸው ይላሉ። በኣንጻሩ ዲክተተርስ ያሉባቸውን ኣገራት ሲያዩ እጅግ ብዙዎቹ በኢኮኖሚያቸው የደከሙ ድሃዎች ናቸው። ይሄ የሚያሳየው ዴሞክራሲ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ስላለው ነው ይላሉ።በኣጠቃላይ እነዚህ ቡድኖች ዙሪያ መለስ ነጻነት ከሌለ ልማት ኣይፈጥንም። ልማት ያለ ዴሞክራሲም ጤነኛ እድገትን ኣያመጣም ብለው ይናገራሉ።ዴሞክራሲ ማለት ለዜጎች ስራ ፈጠራ ለተነሳሽነትና ለእምነት(trust)ጥሩ ከባቢ የሚፈጥር በመሆኑ ኢኮኖሚን በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተጽእኖ ያሳድርበታል ይላሉ።

የግል ኣስተያየት

ዴሞክራሲ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ኣለው የለውም የሚለውን ክርክር ከመጀመር በፊት ዴሞክራሲን መጀመሪያ መበየን ተገቢ ሳይሆን ኣይቀርም። የክርክሩ ጥራት የሚለካው ዴሞክራሲን በምናይበት መነጽር ነው። ዴሞክራሲ ስንል ወደ ኣይምሮኣችን ቀድሞና ኣይሎ የሚመጣው ነጻ ምርጫ ከሆነ ይህንን ግንዛቤ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ስናያይዘው የጠነከረ መረጃ ላይኖረን ይችላል። በየ ኣራት ኣምስት ኣመቱ ኣወዛጋቢ ያልሆነ ምናልባትም ኣስተማማኝ ምርጫ እያደረጉ ኣምባገነን ኣገር መሆን ይቻላል። ዴሞክራሲ ተቋማዊ ካልሆነና በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል ካልሆነ ምርጫ ብቻውን ከኢክኖሚ እድገት ጋር ያለው ግንኙነት ግልጽ ሆኖ ላይታይ ይችላል።

ዋናው ነገር ዴሞክራሲ ስንል የህዝቦች የልእልና (sovereignty of the people) ጥያቄ ነው። በተግባር ሲዘረዘር ደሞ ዜጎች እንደዜጋም እንደሰው ልጅነታቸውም ክብርና ምርጫቸው ሊጠበቅ ይገባዋል የሚል ዶክትሪን ነው።

ግለሰቦች ብዙ ሆነው ተሰባስበው መንግስት ሲያቆሙ ተቋማት ሲመሰርቱ የየግል ዝንባሌ(interest) ስላላቸው ነው። እነዚህ ተቁዋማት ደሞ የዜጎችን ቁሳዊ ህይወትም እንዲያሽሽሉ ዘዴ ወይም መንገድ ይሆናሉ ተብለው ነው። ዴሞክራሲ ስንል የነዚህን ተቋማት ንጽህና እና ፍታዊነት ማንሳታችን ነው። ታዲያ  እንዴት ነው ነጻ ፍርድ ቤት መኖር ያለ መኖሩ ከኢኮኖሚው እድገት ጋር በቀጥታ የማይያያዘው? በህጋዊ መንገድ ለመበልጸግ የፍትሁ ኣካል ገለልተኛነትና ታማኝነት በቀጥታ የኢኮኖሞውን እድገት ተጽእኖ ይፈጥርበታል። ከመቼውም በላይ ዛሬ መረጃና ገበያ በተቀላቀሉበት ዘመን እንዴት ነው ነጻ መረጃ ያለመኖሩ ኢኮኖሚውን በቀጥታ የማያገኘው?

 

ዴሞክራሲ በታሪክም ቢሆን ከሰው ልጆች ሁለንተናዊ እድገት ጋር ኣብሮ እያደገ የመጣ ነው። ዛሬ ኣድጎ የሚታየውን መልኩን ሳይዝ ዴሞክራሲ ኣልነበረም ማለት ኣይቻልም። ዴሞክራሲ በህዝቦች ልብና ባህል ውስጥ ነበር። ዴሞክራት ሳይሆኑ የኢኮኖሚ እድገት ኣመጡ የሚባሉት የድህረ ኮሚኒዝም ኦቶክራቶች ዴሞክራሲ የሚባል ነገር ምንም በልቦናቸው ኣልፈጠረባቸውም ማለት ኣይቻልም። ፍትህ እንዲመጣ፣ እኩልነት እንዲሰፍን፣የህዝቦች ልእልና እንዲከበር የኢኮኖሚው ክፍፍል እንዲሻሻል ሞክረዋል። ችግሩ በስልጣን የመቆየት ኣባዜ ነበር ግን ደሞ በህዝቦች ውስጥ የቀደመው የባለ ሙሉ ዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄ እየጠረገ ጣላቸው።

 

ዛሬ ህዝቦች ኣድገው ዴሞክራሲን ሰባዊ መብትን ኣጥብቀው በሚሹበት ሰኣት እነ ዲክተተር እንትና ዲክቴተር ሆነው ኢኮኖሚያቸው ኣድጉዋልና እኛም በዚህ መንገድ እንለፍ ማለት ካለማቀፉ ሁኔታም ሆነ ጊዜን ተከትሎ ካደገው የሰው ልጆች የኣስተሳሰብ እድገት ጋር ይጋጫል።

 

ዴሞክራሲ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የለውም የሚሉ ሰዎች ኣሁን የሚጠቅሱዋትን የቻይናን ጉዳይ ጥቂት ብናይ መልካም ሳይሆን ኣይቀርም። በርግጥ የቻይና ኢኮኖሚ ያለ ዴሞክራሲ ነው ወይ ያደገው?

 

ለቻይና እድገት ሶስት ጉዳዩች ጉሉህ ኣስተዋጾ ሳያደርጉ ኣልቀሩም

1)         የቀረጸችው ለእድገት ኣመቺ የሆነ የኢኦኖሚ ፖሊሲ

 

ይህ ፖሊሲዋ ቻይናን ባንድ በኩል የዴሞክራቲክ መልክ እንዳላት ያሳያል። ዛሬ ሶስት ኣራተኛ የሚሆነው የቻይና ህዝብ በፍትሁ በፍርድ ቤቶቻቸው መተማመን(trust) ኣላቸው። በዚህም ጣሊያንን ጨምሮ ከኣንዳንድ ዴሞክራት ኣገሮችም በላይ ቻይና በዚህ በኩል ተሽላ ተግኝታለች ማለት ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኣስር ከሚሆኑት ቻይናውያን ሰባቱ ኣመቺ የሆነ ኢንተርፕሩነር ኣካባቢ(environment) ተፈጥሩዋል ብለው ያምናሉ።

 

ቻይና የግል ተቁዋማቱን በለቀቀች ቁጥር ኣጠቃላይ እድገቱዋ እየጨመረ ሲመጣ ይታያል። የገበያ ነጻነት በሰጠች ቁጥር እድገትን ታያላች። ዛሬ የግሉ ሴክተር ከሃገሪቱ GDP ከፍተኛውን ድርሻ ይዙዋል። ይህ የኢኮኖሚ ፖሊሲዋ የዲክተተሮች መልክ የለውም ።

 

2) ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ሃብት (Social Capital) ኣላት

 

በሌጋተም 2011 ጥናት መሰረት በሚገርም መልኩ 60 በመቶ የሚሆኑት ቻይናውያን ሌሎችን የሚያምኑ ናቸው። ይህ መተማመን ትልቅ ሃብታቸው ሲሆን ይህም በኣንስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ኢንቨስት ለማደርግ ስንቅ ሊሆናቸው ይችላል። ተዋረዳዊ መተማመን(trust) ላጋራ እድገትና ልማት ግብዓት ነው።

 

3)      ሌላው በርግጥ ከውጭው ኣለምም ጋር ከፍተኛ ፍክክር ውስጥም የገባች ትመስላለች።  ይሄ ኤነርጂዋ ምናልባትም ግፊት ፈጥሮላት ሊሆንም ይችላል።

 

ዋናው ግን ከፍ ሲል ያነሳናቸው ሁልቱ ጉዳዩች የዲክቴተርስ ሳይሆን የዴሞክራት መልክ ይሰጣታል። ይህ ደባል ስብእናዋም ነው ኣንዴ ቅይጥ ሌላ ጊዜ ድብልቅ ኣገር እያልን እንድንጠራት ያደረገን። ታዲያ ቻይና ዴሞክራሲን ሙሉ በሙሉ ባለማስተነገዱዋ በኢኮኖሚ ያላደጉ ኣገሮች በምሳሌነት ሊጠቅሱዋት የሚገባ ኣይመስልም። ዴሞክራሲን ለኢኮኖሚ እድገት ሃይል ኣድርገው ያደጉ ብዙ ኣገሮች ኣሉና።

 

geletawzeleke@gmail.com

Reference

http://www.prosperity.com/

 

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 17, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.