ደቡብ አፍሪካውያን ሌላ ዘመቻ ጀምረዋል (ኢትዮጵያ ተጨማሪ 3 ነጥብ ማጣት አለባት እያሉ ነው)

(EMF) ከቦትስዋና ጋር አድርገን በነበረው ጨዋታ ላይ፤ መሰለፍ የማይገባው ተጫዋች፤ ማለትም ምንያህል ተሾመ በመሰለፉ ምክንያት፤ ቦትስዋና በፎርፌ እንድታሸንፍ ተደርጎ ኢትዮጵያ ከነበራት 13 ነጥብ ተቀንሶባት 10 ነጥብ እንዲኖራት ይደረግ ይሆናል። ፊፋ ገና ውሳኔ ስላልሰጠበት የመጨረሻውን ውጤት ገና አላወቅንም። አዲስ ያወቅነው ነገር ቢኖር፤ ደቡብ አፍሪካውያን ከነሱ ጋርም ተደርጎ የነበረው ጨዋታ ተሰርዞ፤ ኢትዮጵያ ሌላ 3 ነጥብ መነጠቅ አለባት እያሉ ነው። ደቡብ አፍሪካውያን እንደሚሉት ከሆነ፤ “ሁለት ቢጫ ካርድ ያየው ምንያህል ተሾመ፤ አሁንም አንድ ጨዋታ ማረፍ ሲገባው ከኛ ጋርም በተደረገው ጨዋታ ላይ ተሰልፎ በመግባቱ ጨዋታውን በፎርፌ ልናሸንፍ ይገባል።” ከማለት አልፈው ይኸው ሃሳብ ወደ ተግባር እንዲለወጥ በፊፋ ላይ ግፊት እየፈጠሩ ይገኛሉ።

እንግዲህ እግር ኳሱ ከሜዳ አልፎ በቢሮ ደረጃ ማወዛገብ ጀምሯል። የኢትዮጵያ ፌዴሬሽንም ሆኑ አሰልጣኙ ወይም የቡድን መሪው ወይም ምንያህል እስካሁን በአደባባይ ይቅርታ አልጠየቁም። ይልቁንም ፌዴሬሽኑ ጣቱን ተጫዋቹ ላይ በመቀሰር ጥፋተኛ አድርጎታል። አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው መግለጫ ሲሰጡ፤ የፊፋ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ መድረሱን ገልጸው፤ ምጸት በተሞላበት አነጋገር፤ “እንግሊዘኛ አይችልም፤ ብለው ቢያስቡ እንኳን በአማርኛ ተርጉመውስ ቢሆን ቢያሳውቁኝ ምናለበት? እኔ እንኳን ብቀር ለአቶ ብርሃኑ (አዲሱ የቡድን መሪ ነው) ለምን አላሳወቁትም?” በማለት ምርር ባለ ሁኔታ ተናግረዋል።

አሁን ኢትዮጵያውያኑ የርስ በርስ ውዝግቡን ትተው ፊታቸውን ወደ ፊፋ መመለስ አለባቸው። የደቡብ አፍሪካውያኑ ዘመቻ ከሰመረላቸው፤ አሁን ካላን አስር ነጥብ ላይ ሌላ 3 ነጥብ ሊቀነስብን ይችላል። ይህ ማለት ደግሞ ደቡብ አፍሪካ በ8 ነጥብ ምድቡን እንድትመራ፤ ኢትዮጵያ እና ቦትስዋና በ2ኛ ደረጃ ላይ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል። “ይህ እንዳይሆን ምን እየተደረገ ነው?” ብለን ብንጠይቅ… መልሱ “በፌዴሬሽኑ በኩል ምንም ሲደረግ አላየንም” የሚል ይሆናል። ሆኖም በሴፕቴምበር ወር ላይ ከሴንትራል አፍሪካ ጋር ከሚደረገው የሜዳ ላይ ፍልሚያ ቀደም ብሎ ከፊፋ ጋር ሌላ ፍልሚያ ማድረጉ አስፈላጊ ሳይሆን አይቀርም። ምን መደረግ አለበት?። ወደሚለው ትንታኔ ከመግባታችን በፊት ጥቂት ወደኋላ እንመልሳቹህ።

ባለፈው ትንታኔያችን እንዳቀረብነው፤ ምንያህል ሁለተኛውን ቢጫ ካርድ ሲያይ የሱ ጥፋት አልነበረም። ግልጽ በሆነ ሁኔታ ስቲፈን ሲናር ጥፋት ሰርቶበት ሲያበቃ፤ ዳኛው ግን ቢጫ ካርድ የሰጡት ለምንያህል ነበር። መጀመሪያውኑ ፌዴሬሽኑ ይህንን ውሳኔ ሊቃወም እና ቢጫው ካርድ እንዲነሳ ማድረግ ይገባው ነበር፤ አልተደረገም። አሁን ወደኋላ ተመልሶ መከራከር ምንም የሚያመጣው ውጤት ባይኖርም፤ መከራከር ግን ያስፈልጋል። ውጤት ባይኖረም፤ (እንደግብጽ ቡድን በሌለ ነገር ላይ መከራከር ያስፈልጋል። ግብጾች ቀይ ካርድ ሊሰጣቸው ሲል “እንዴት ቢጫ ይሰጠናል?” ብለው አምርረው ይከራከራሉ) ስለዚህ ያለፈውን ጉዳይ ላይ ጠንከር አድርገን መከራከር ከቻልን፤ አሁን ከደቡብ አፍሪካ ሊሰነዘርብን ከሚችለው ሌላ አደጋ እንድን ይሆናል።

በደቡብ አፍሪካ በኩል እየተደረገ ያለው ዘመቻ ከተሳካ፤ በመጨረሻው የሴፕቴምበር ጨዋታ የማለፍ እድላችን በጣም የጠበበ ሊሆን ይችላል። አሁን ባለው ሁኔታ፤ ፊፋ 3 ነጥብ ቢቀነስብን አሁንም ከምድቡ አንደኛ ነን። ከሴንትራል አፍሪካ ጋር በምናደርገው ጨዋታ፤ ማሸነፍ በወሳኝነት ወደሚቀጥለው ደረጃ ያሸጋግረናል። እኩል መውጣትም ሁለተኛው አማራጭ ነው። እኛ በሴንትራል አፍሪካ ተሸንፈን፤ ደቡብ አፍሪካ ቦትዋናን ካሸነፈች ግን ጉዟችን እዚያ ላይ ያበቃል። ከዚህ ሁሉ በፊት ግን አሁን በደቡብ አፍሪካ በኩል፤ ሌላ ነጥብ እንድናጣ እየተደረገ ያለውን ዘመቻ መቋቋም ያስፈልጋል።

ቀጣዩ ጨዋታ ሴንትራል አፍሪካ ውስጥ፤ ሴፕቴምበር 6 ቀን፣ 2013 ይደረጋል። ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ላይ በሳላዲን ሰኢድ አማካኝነት ሁለት ጎል በማግባት ነበር፤ ሴንትራል አፍሪካን 2-0 ያሸነፍነው፤ አሁን ግን በአገራቸው፣ በደጋፊዎቻቸው ፊት ነው የሚጋጠሙት። ሁልጊዜ እናሸንፋለን ማለት አይቻልም። ሴንትራል አፍሪካ—ቡርኪና ፋሶን ባለፈው አመት 1-0 ያሸነፈ ቡድን ነው። ቡርኪና ፋሶ ደግሞ እኛን 4-0 አሸንፎ ከአፍሪካ ዋንጫ ያስወጣን ቡድን መሆኑ ይታወሳል። ስለዚህ እኛን 4-0 የቀጣንን ቡድን ካሸነፉት ሴንትራል አፍሪካዎች ጋር እንደምንጋጠም መዘንጋት አያስፈልግም። አዲስ አበባም ላይ ባደረግነው ጨዋታ፤ በአንድ አጥቂ በሳላዲን አማካኝነት 2 ጎን አስቆጥረን፤ በመከላከል ላይ ያተተኮረ ጨዋታ አድርገን… በራሳችን ሜዳ ላይ አስጨንቀውን እንደነበር መዘንጋት አያስፈልግም። ስለዚህ ንቀትም ሆነ መዘናጋት ሳያስፈልግ፤ በአንድ በኩል ከፊፋ ጋር እየታገልን በሌላ በኩል ደግሞ ለሴፕቴምበሩ  ጨዋታ እራሳችንን እያዘጋጀን መቆየት ይኖርብናል። ለማንኛውም መልካሙን ሁሉ በመመኘት እንለያቹህ!

 

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 19, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.