ይህን ያለው ማነው? “ትግሬን ወደ መቀሌ!ንብረቱን ወደ ቀበሌ!”

ደረጀ ሀብተወልድ -ሆላንድ
ይህን ጥያቄ፤ ለአንድ ጤነኛ ሰው ቢያቀርቡለት፤”እንደዚህ የሚሉት(ያሉት)፤ለትግሬዎች ጥላቻ ያላቸው ናቸው”ሊል እንደሚችል ግልፅ ነው።ይህ አያከራክረንም።አከራካሪ የሚሆነው፤እነዛ፤ ለትግሬዎች ጥላቻ ያላቸው፤ እነማን ናቸው?” የሚለው ተከታይ ጥያቄ ነው።
ግን.. ይህን ያለው ማን ይመስላችሁዋል?
ቅንጅት? የቅንጅት ደጋፊዎች?ህብረት? የግል ጋዜጦች? ወይስ ሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች?
“ትግሬን ወደ መቀሌ፤ንብረቱን ወደ ቀበሌ” ብሎ በአደባባይ ያወጀው፤ ህወሀት ቢሆንስ ምን ይሰማችሁዋል?ምንስ ትላላችሁ?
በእርግጥ ህወሀት፤በገዛ አባሎቹ ደምና ሬሳ ላይ እየተረማመደ የመጣ ድርጅት ስለመሆኑ፤የድርጅቱ መስራቾች የነበሩ ሳይቀሩ በአደባባይ ሲመሰክሩት የሰማነው ሀቅ ነው።በስመ-ዲሞክራሲ ምሎና ተገዝቶ የተነሳው ህወሀት፦”የአመለካከት ልዩነት አንፀባርቀዋል” የሚላቸውን አባሎቹን በጅምላ እየገደለና እየቀበረ መምጣቱን፤ አፋችንን ደም ደም እሰከሚለን ድረስ ሰምተናል።ህወሀት፤ሌላው ቀርቶ ምንም በሌለበት ምድረ-በዳ፤አንድ ላይ ውለው የሚያድሩ ወንድና ሴት ታጋዮች፤ተፈጥሯዊ ስሜታቸውን መጋራታቸውን- እንደ ከባድ ወንጀል ቆጥሮ፤ብዙዎችን በሞት የቀጣ ጨካኝ ድርጅት መሆኑንም እናወቃለን።(የሁዋላ ሁዋላ ግንኙነቱ እንዲፈቀድ የተደረገውም፤ፍቅርን -በጠመንጃ ማቆም ባለመቻሉ ነው)

እሽ፤ይህስ ይሁን።ሚዛን ባያነሳም፤እንዲያ ያደረጉት፤ በጫካ ህግ ይተዳደሩ ስለነበር ነው ሊባል ይችላል።ዛሬ፤ከሁለት አስርት ዓመታት የሥልጣን ቆይታ በሁዋላ፤ በገዛ ወገኖቻቸው ላይ እስከዚህ ድረስ የጨከኑበት ምክንያትስ ምንድነው?
ምን ዓይነት ልብ ቢኖራቸው ነው በብዙሀን መገናኛ፦”ትግሬን ወደ መቀሌ… “ እያሉ በወላጆቻቸው ላይ የሚዘገንን እሳት ለመጫር የጨከኑት?
ነው ወይስ “እናቱን የሚጠላ፤አባቱን የሚረግም ትውልድ ይፈጠራል”የሚለው የመፅሐፉ ትንቢት እየተፈፀመ ይሆን?
ይህን ነገር ዛሬ ልገልጠው የፈለግኩት፤በተባለው ጉዳይ ያለውን እውነታ፤በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፤በተለይም የትግራይ ህዝብ ማወቅ ስላለበት ነው።እኔ የደረስኩበት እውነት ደግሞ፤ ፦ይህ ፀያፍ አባባል፤ከህወሀት- የተንኮል ጭንቅላት ውስጥ መውጣቱን የሚያረጋግጥ ነው።እርግጠኛ ያልሆንኩት፤የአባባሉ ባለቤት ወይም ደራሲው ፤መለስ ይሆኑ? ወይስ አባባሉን በአደባባይ ያወጁት ራሳቸው ቴዎድሮስ ሀጎስ? የሚለውን ብቻ ነው?

በአጭሩ ላብራራ፦
በግንቦት 97 ምርጫ ዋዜማ ፤ማለትም ሚያዚያ 29 ቀን ኢህአዴግ በጠራው ህዝባዊ ስብሰባ ፤ታዛቢዎች እንደገመቱት፦ ወደ 500 መቶ ሽህ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መስቀል አደባባይ ይገኛሉ።ከነዚህ መካከል የሚበዙት፤በየቀበሌዎች አማካይነት ሰልፍ ይወጡ ዘንድ “የቡና መግዣ” እየተባለ 20 እና 30 ብር የተሰጣቸው ናቸው።
ሰልፈኛውን በመስቀል አደባባይ ሢያዩ በደስታ የሰከሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩም፤”ይህ ማዕበል፤ ምንም ዓይነት ማጭበርበር ሳያሰፈልገው፤ተቃዋሚዎችን በማያዳግም ሁኔታ በድምፁ ይቀጣቸዋል!”ብለው ተናገሩ።ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ከመድረክ ውደ ህዝቡ ሊወርዱ ሲሉም፤ አጃቢዎቻቸው ፤ተከላክለው መለሷቸው።
ይሁንና፤እኩለ ቀን ላይ ሰልፉ ተጠናቅቆ ሰልፈኞች ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፤ብዙዎቹ የቅንጅትን አርማ በጣታቸው እያሳዩ ነበር።
ያን ደማቅ ሰልፍ ያዩት ኢህአዴጎች ግን፤ቢያንስ በዛ ቀን፤” ሰዎች የቅንጅትን አርማ አሳዩ” የሚለውን ወሬ ፤ማመን ብቻ ሳይሆን መስማትም አልፈለጉም።ቀኑ፤ እነ መለስና በረከት “ይህን ተቃዋሚ ነኝ ባይ ሁሉ፤ጠራርገን በላነው”እያሉ ‘ቺርስ!’ ያጋጩበት ነው።መለስ፤በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ፤ውጪ ወደሚገኙ ወዳጆቻቸው ስልክ እየደወሉ፤”አያችሁልኝ ወይ አዲስ አበባን ከጎናችን እንደሆነ” ብለዋል ተብሎ ይወራል።
በማግስቱ እኔን አይድርገኝና!
ገና የሚያዚያ 30 ጎህ ሲቀድ፤ በጎቹን ወደ አራት ኪሎ እየነዳ የመጣ አንድ ነጋዴ፤ ልክ ቤተ-መንግስቱ አካባቢ ሲደርስ፤ ድምፁን በሀይል ከፍ አድርጎ፦”እናንተ፤ እንኳን እኔን በጎቼን አትሸውዱም!ማንን እንደምንመርጥ እናውቃለን!!የበጎቼን ቀንድ ተመልከቱ!” እያለ ይጮኸ ነበር።
የቅንጅት ህዝባዊ ስብሰባ የተጠራው ከቀኑ 8፡00 ሰዐት ላይ ቢሆንም፤መንገዶች ሁሉ ወደ መስቀል አደባባይ የሆኑት ግን ፤ገና ከረፋዱ 4፡00 ሰዐት ጀምሮ ነበር።
ከቀኑ 6፡00 ሰዐት ሲሆን፤ መስቀል አደባባይ ተረታ። ከወደ በቅሎ ቤት የሚመጣው፦ ርቼ ላይ፤ከወደ ልደታ የሚግተለተለው፦ ሜክሲኮ አደባባይ ላይ፤ከወደ ቦሌ የሚተምመው፦ኦሎምፒያ ላይ፤ከፒያሳ የሚወርደው አምባሳደር ላይ፣ ከወደ አራት ኪሎ የሚጎርፈው፦ውጪ ጉዳይ ጋር፣ ከወደ መገናኛ የሚፈሰው ፦ኡራኤል ጋር ቆመ።የአዲስ አበባ መሬት አረገደ፤ ተንቀጠቀጠ።በሰማዩ ላይ ፤ ነፃነትና ተስፋ ፈነጠቀ።
የትናንቱን ስብሰባ “ማዕበል” ብለው የጠሩት መለስ፤ የዛሬውን የማዕበሎች እናት( ሱናሚ ) በቲቪ ሲመለከቱ፤ ቤተ-መንግስት መቆየትን አልፈለጉም።ሆኖም፤ከዛ መውጣታቸው-በሹመኞቻቸው ከተሰማ ደግሞ፤ ሌላ ችግር ሊፈጠርባቸው ሆነ።ዐይናቸውን ኢቲቪ ላይ አፍጥጠው ምን እንደሚሻላቸው በማሰላሰል ሳሉ ነበር ድንገት፦ ”ማምለጥ ነው የሚሻለው፤ለጫማው ሁዋላ ይታሰብበታል”የሚል ማስታወቂያ በቲቪው ብቅ ያለው። ጊዜ አላጠፉም።ወደ ደብረዘይት አየር ሀይል ስልክ ደወሉ። ሄሊኮፕተር ቤተ-መንግስት መጣች።መለስን፦ከቤተሰባቸው ጋር ወደ አየር ሀይል ግቢ ይዛ በረረች።
አዎ! ሚሊዮኖች፤በአደባባይ ነፃነታቸውን አወጁ።ፍላጎታቸውን ገለፁ።ዲሞክራሲን ዘመሩ-ሚያዚያ 30/97 ዓ.ም።

የራሳቸውን “የልማትና የዲሞክራሲ”ዘፈን ፤በራሳቸው ቴሌቪዥን እየሰሙ፤ ራሳቸውን ሲሸነግሉና በአየር ላይ ምስማር ሲመቱ ለከረሙት የጋሪ ፈረሶች(ኢህአዴጎች)፤ክስተቱ አስደንጋጪና አስጨናቂ ሆነ።ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ ቢኖር፤ኢህአዴግ ለአንድ ቀን እንኳ ሥልጣን ላይ ውሎ ማደር የማይችል- በህዝብ የተጠላ ድርጅት መሆኑን ዓለም አወቀ።ይህም፤ኢህእዴግን ያለ ቅንጣት የይሉኝታ እንጥፍጣፊ የቆሰለ አውሬ አደረገው።
አዎ!..ከእራፊ ጨርቅ ባልተሻለ የዲሞክራሲ ጭምብል ተሸፍኖ የነበረው የኢህአዴግ እርቃን ፤ሀፍረተ-ሥጋው እስኪታይ ድረስ መገላለጥ ጀመረ።
“ኢህአዴግ ነኝ” የሚል ቡድን ሥልጣን በያዘ በ15ኛው ዓመት፤ በ8ተኛው ወር፤ በ30 ኛው ቀን፤ ምሽት ላይ የጫካው ወያኔ፦በጫካው ራዲዮ አንባቢ በሴኮቱሬ ጌታቸው አማካይነት፦ “ደርጎችንና ኢንተርሀምዌዮችን እንታገላቸዋለን “! ” የሚል ቅስቀሳ እያደረገ፤ በቁምጣው ብቅ አለ።
”የዚህ ዓይነት አስፈሪ ቅስቀሳ ያየሁት፤ ደርግ 60ዎቹን ሚኒስትሮች ሊረሽን ሲል ነው”ያለኝ ሰው አለ። በእርግጥም! ከደርግ ቀረርቶ የቀረ ነገር ቢኖር፤ማርሹና “የፍዬል ወጠጤ”ው ብቻ ነው።
ያን ደም ደም የሚሸት ፕሮፓጋንዳ በአስተርጓሚ የሰሙት የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ፤ ክብርት አና ጎሜዝም፤ወደ በረከት በመሄድ፦”ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢንተርሀምዌይ ናቸው” የሚለው ቅስቀሳ እንዳስደነገጣቸውና ተገቢ እንዳልሆነ ይነግሯቸዋል።ኢህአዴግ፤ “ኢንተርሀምዌይ” ማለት የጀመረው ገና የምርጫ ቅስቀሳው ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ቢሆንም፤በረከት ግን፦በቅንጅት ሰልፍ ላይ በድሩ አደም፦”… ኢህአዴጎችን፤ ግንቦት 7 ቀን ወደመጡበት ነው የምንመልሳቸው”ማለታቸውን ለአና ጎሜዝ በመጠቆም፤ ኢህአዴግ-ተቃዋሚዎችን፦“ኢንተርሀምዌይ” ያላቸው ፤< እየሄዱበት ካለው አደገኛ መንገድ በመነሳት> እንደሆነ ይገልፁላቸዋል።አናጎሜዝም፤በተባለው ጉዳይ ከተቃዋሚ መሪዎች ጋር እንደሚነጋገሩ ቃል በመግባት፤በኢህአዴግ በኩል የዛ ዓይነት አደገኛ ቅስቀሳ ዳግም እንዳይደረግ ይማፀናሉ።ከዚያም፤ ወደ ቅንጅት መሪዎች በመምጣት፤ በድሩ አደም ባሉት ነገር ላይ ከተነጋገሩ በሁዋላ፤ዳግም የዚያ ዐይነት ንግግር እንዳይሰማ ጠንከር ያለ ምክር ያስተላልፋሉ።
ይሁንና፤ በበድሩ አደም ንግግርና-በኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ መካከል ያለውን ልዩነት፤ አና ጎሜዝ መገንዘባቸውን ሰምቻለሁ። አንዳንድ፦ ሆነ ብለው ዐይናቸውን የጨፈኑ ወገኖች ግን፤ ከሁለቱ ወገን የተሰሙትን አባባሎች፤ መሣ ለመሣ አድርገው ሊያዩዋቸው ሲሞክሩ ነው የተመለከትኩት። ይህ ታላቅ ስህተት ነው። በእርግጥ ላይ ላዩን አሰላለፋቸውን ከህዝባዊ ማዕበሉ አቅጣጫ ጋር በማመሣሰል ፤ በውስጣቸው ግን በኢህአዴግ መሸነፍ ሲብከነከኑ ለነበሩ ጥቂት “በዘርና በጥቅም ሻሽ ለተሸበቡ ሰዎች፤ የአቶ በድሩ ንግግር ጥሩ ምክንያት እንደሆነላቸው ይታወቃል።”ሆድ ለባሰው፤ማጭድ አታውሰው” አይደል የሚባለው?
እናጢነው ከተባለ፤በሁለቱ አባባሎች ውስጥ ያለው ዋናውና መሠረታዊው ልዩነት፤ ”ኢንተርሀምዌይ “የሚለው የኢህአዴግ ቅስቀሳ እየተለቀቀ ያለው፤ገና የምርጫ ቅስቀሳ ከመጀመሩ አንስቶ በድርጅት ደረጃ ታምኖበት ሲሆን፤ የአቶ በድሩ ንግግር ግን ፤ ሚያዚያ 30 ቀን ባዩት የደጋፊ ብዛት በደስታ ሢሰክሩ ከውስጣቸው የወጣ የግል ስሜት እንጂ፤በቅንጅት የታመነበት አይደለም።
ለዚህም ነው ቅንጅት፤ በድሩ ያሉት ነገር ፓርቲውን እንደማይወክልና የድርጅቱ አቋም እንዳልሆነ የሚገልጽ ማስተባበያ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራዲዮ በማግስቱ የላከው። ሆኖም፤በነ በረከት ትዕዛዝ ማስተባበያው እንዳይነበብ ታግዷል።
ከዚህም ባሻገር የበድሩን ንግግር በቅንነት እንየው ከተባለ፤ ለስህተት የተጋለጡት ከጥንቃቄ ጉድለት ወይም ከስሜት ስካር እንጅ፤በኢህአዴግ እንደተባለው፦ እኩይ አስተሣሰብ ስላላቸው አይደለም።
እስኪ ያሉትን እንየው፦
”ኢህአዴችን ፤ግንቦት 7 ቀን በካርዳችን….”እዚህ ድረስኮ ደህና መጥተዋል ጎበዝ።አንዳንዶቻችሁ፤ ምናለ በአጭሩ “..በካርዳችን እንቀጣቸዋለን” ቢሉ ኖሮ ልትሉ ትችላላችሁ። አዎ!ቢሉ ጥሩ ነበር። ግን አላሉም።የሰው ባህር ላይ ነዋ የቆሙት። በቃ የሰልፈኛው ዳርቻ፤ ሰማይ ጥግ ደርሶ ሲያዩት፤ ቀልባቸውን ሳቱ።ከዚያ በሁዋላ ያሉትን ነገር፤ እኛ ሰማነው እንጂ፤እርሳቸው አያውቁትም።
ያሉትም፤“….በካርዳችን ወደ መጡበት እንመልሳቸዋለን!”ነው።
እስኪ ደጋግማችሁ አንብቡት። ምን ትርጉም ሰጣችሁ?ኢህአዴግ፤በወረቀት ወደ መጣበት ሲመለስ እስኪ አስቡት።
ለዚህም ነው፤ በድሩ አደም በዚህ አባባላቸው በተጠየቁ ቁጥር፤ ብዙ ጠጥቶ የሰከረ ሰው፤ በስካር መንፈስ ስለተናገረው ነገር የተጠየቀ የሚመስለኝ።
ከቅንጅት መሪዎች ጋር በታሰርን ጊዜ አቃቤ ህግ “ለዘር ማጥፋት ሙከራ”ክሱ ካቀረባቸው የቪዲዮ ማስረጃዎች አንዱ፤ይኸው የአቶ በድሩ ንግግር ነበር።አቶ በድሩ ስለተናገሩት ነገር ያብራሩ ዘንድ በፍርድ ቤቱ ሲጠየቁ፦” ኢህአዴግ የአራት ድርቶች ግንባር እንደሆነ፤በኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ከአራቱ ድርጅቶች፤ በርካታ(278) መቀመጫዎች ያሉት ኦህዴድ እንደሆነ፤ < ኢህአዴጎችን፤ ግንቦት ሰባት ቀን በድምፅ ካርዳችን ውደመጡበት እንመልሳቸዋለን> የሚለው አባባል፤ ለህወሀት ብቻ እንደተነገረ ተደርጎ መተርጎሙ ሊገባቸው እንዳልቻለ፤በሌላ ቢተረጎምም፤እርሳቸው ለማስተላለፍ የፈለጉት መልዕክት፤ በምርጫው እናሸንፋለን የሚለውን እንደሆነ፤ አብራርተዋል።
በዚያም ተባለ በዚህ፤ በድሩ አደም፤ በዚህ አባባላቸው የጠቀሙት፤ ወይም ጥይት ያቀበሉት፤ የፕሮፓጋንዳ ዝናሩ ባዶ ቀርቶ ለነበረው ኢህአዴግ ነው።
ከአንድ ሳምንት በሁዋላ ግንቦት 7 ቀን ምርጫው ተካሄደ።በጥቂት ቀናት ውስጥ ቀድሞ የተገለፀው የአዲስ አበባ ውጤት፤የሚያዚያ 30ው ሰልፍ ነፀብራቅ ነበር።ኢህአዴግ፤ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ተሸነፈ ብቻ ሳይሆን፤ ተዘረረ።
መለስም፤ የድርጅታቸውን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሰብስበው፦”የአዲስ አበባን ህዝብ ምን አድርጋችሁት ነው?”ማለታቸው ተሰማ።ህዝቡ የጠላው ግን ፤በጠቅላላ ኢህአዴግ የሚባልን የደካሞች ስብስብ እንደሆነ ያውቃሉ። የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር ደግሞ ራሳቸው መለስ ናቸው።ሆኖም፤ የራስን ስብዕና አጉልቶ ሌሎችን ማንኳሰስ ፤ በኢህአዴግ ውስጥ የተለመደ- አባላትን የማሸማቀቂያ ስልት ነው። እናም፤እርሳቸው አዲስ አበባ ቢወዳደሩ ያሸንፉ ይመስል፤ሌሎቹን(ቁስለኞቻቸውን)ሰብስበው፦”የአዲስ አበባን ህዝብ ምን አድርጋችሁት ነው?”አሉ።
“ በአዲስ አበባ ቢወዳደሩ ያሸንፉ ይመስል” ስል፤ በትግራይ ፤”ተወዳድረው አሸንፈዋል” እያልኩ አይደለም።ቀደም ካለ ጊዜ ጀምሮ እስከ ምርጫው ዋዜማ ድረስ በተለያዩ ጊዜያት ለሥራ ወደ ትግራይ ሄጃለሁ። በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች ይታይ የነበረው አንፃራዊ ነፃነት፤ትግራይ ውሰጥ ፈፅሞ የለም።ጋዜጦቻችን፤በተለያዩ ከተሞች በስፋት መነበብ በጀመሩበት በምርጫ 97 ዋዜማ እንኳ፤ወደ ትግራይ ክልል አስገብተን ማከፋፋል አንችልም ነበር።ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ በአውቶቡስ የሚሄድ መንገደኛ፤መርካቶ የገዛውን የግል ጋዜጣ፤አላማጣ ከተማ ሳይደርስ መጣል ግዴታው ነው።
አማራጭ ሀሳቦችን የመስማትና የማንበብ ዕድል፤ከሌሎች አካባቢዎች በባሰ መልኩ ትግራይ ውስጥ የተከለከለ ነው።በተለይ እንደመቀሌና፣አክሱም ከመሣሰሉት ከተሞች ትንሽ ወጣ ሲባል፤አፈናውና ቁጥጥሩ እጅግ ይከፋል።
ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ትንሽ ነፃነት እንደሚሰማቸው የነገሩኝ የትግራይ ነዋሪዎች በርካታ ናቸው።
ስለ አገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ የተሣሳተ ግንዛቤ፤ ስለ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ እጅግ አደገኛ አስተሣሰብ እንዲይዙ የተደረጉትም ብዙዎች ናቸው።
ሌላው ቀርቶ፤“ቅንጅት የሚባለውፓርቲ ካሸነፈ፤መንግስቱ ሀይለማርያም በአየር ይደበድባችሁዋል”ተብለው፤ ከፍ ያለ ስጋት ያደረባቸው ሰዎች ሁሉ አጋጥመውኛል።በቃ፤ከካድሬዎች ቅስቀሳ ውጪ ሌላ ነገር እንዳይሰሙና እንዳያስቡ የታፈኑ ዜጎች።
እንግዲህ ኢህአዴግ ፤በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ትግራይ ውስጥ ከራሱ ጥላ ጋር ተወዳድሮ ያሸነፈው። “መለስ ተወዳድረው አሸንፈዋል” የሚለውን ለመቀበል የሚከብደኝም፤ ለዚህ ነው።ከዚያ ይልቅ እንደ ድብ ድብ ጨዋታ “አፍኜ ብበላ” ብለው_አፍነው በልተዋል ማለቱ የሚሻል ይመስለኛል።
ከዚያስ…

በትግራይ አፍነው ያገኙት የምርጫ ውጤት ፤ከአዲስ አበባ ጋር ፍፁም ተቃራኒ መሆኑን ሲየዩ ፤ትግራይ ውስጥ ሲረጩት በነበረው መርዝ ፕሮፓጋንዳ እንደተጠቀሙ አድርገው የቆጠሩት ህወሀቶች፤መርዙን በአገር አቀፍ ደረጃ ማሰራጨት ፤ከክልሉ ውጪ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን በማስተባበሩ ረገድ ሊጠቅመን ይችላል ብለው ሳያስቡ አልቀሩም።
ምክንያቱም፤ምርጫውን ተከትሎ በየትኛውም ስፍራ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ያሳዩት አቋም ፤ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህቶቻቸው የተለዬ አልበረም።
የአዲስ አበባን ብንወስድ፦
-የትግራይ ተወላጆች በብዛት በሚኖሩበት በተክለሀይማኖት ፤ኢህአዴግ የተሸነፈው እጅግ አስደንጋጭ በሆነ ልዩነት ነው።
-ሚያዚያ 30 ቀን በተጠራው የቅንጅት ሰልፍ ላይ ጭፈራውን እየመራ በቴሌቪዥን ሲታይ የነበረው ታዳጊ ፤የትግራይ ተወላጅ ነው።
-ከቤተ- መንግስት ሠራተኞች 85 በመቶ የሚሆኑት ድምፃቸውን የሰጡት ለቅንጅት ነበር።
– ኢህአዴግ፤ በአዲስ አበባ ከነበሩት ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ አባላት፤ድምፃቸውን የሰጡት 100 ሺህ እንኳን አልሞሉም ነበር። ሌላም ሌላም…

ኢህአዴግ፤ በህልሙም፤በውኑም አስቦት ከማያውቀው መራር እውነታ ጋር ተፋጠጠ።
የቀረው አማራጭም፤የጀመረውን የኢንተርሀምዌይ ቅስቀሳ በማጠናከርና የትግራይን ህዝብ ከሌሎቹ ጋር በማጋጨት፤ ለአንድም ቀን ቢሆን የስልጣን እድሜን ማራዘም ብቻ ሆኖ ታየው።ስለዚህም፤ህዝቡ፤ ከመሶበ፦ ለቤት ግንባታ ሲሚንቶ ሲጠብቅ፤እነሱ ተንኮል ከተመላው ጭንቅላታቸው ክብሪት ፈብርከው፤ ያችኑ ጎጆውን የሚበላ አደገኛ እሣት ጫሩ። በተለይም “የአብራኩ ክፋዮች ነን”እያሉ በሚነግዱበት በትግራይ ህዝብ ላይ፤ቤንዚን አርከፍክፈው ማቆሚያ ሌለው እሣት ለቀቁ።
አዎ! የባህሩ ሆድ ባይሰፋ ኖሮ ፤ እንደነሱማ፤ ሩዋንዳን በሆንን፤ ሰዶምንም በመሰልን ነበር።
+++++++++++++++++++++++++++++++++
የተለያዩ ክልሎች የምርጫ ውጤቶች እየተገለፁ ነው።ብዙ ጊዜ እንደማደርገው፤ ዛሬም ፤ቢሮ ውስጥ ሥራዬን እየሠራሁ የተለያዩ የራዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እከታተላለሁ።በ አንድኛው ራዲዮ ዜና ከተነበበ በሁዋላ ፤ የህወሀት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ቴዎድሮስ ሀጎስ ለቃለ-ምልልስ እንግዳ ሆነው ቀረቡ።
በቃለ-ምልልሱ፤የቅንጅት ደጋፊዎች አዲስ አበባ ውስጥ፤የትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ አደገኛ ፕሮፓጋንዳ እየነዙ መሆናቸውን፣ይህ አደገኛ አዝማሚያም፤ ድርጅታቸውንና የትግራይ ህዝብን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚገፋፋ መሆኑን በሀይለ-ቃል ተናገሩ።
በትግራይ ህዝብ ላይ “ተሰራጨ”ያሉትን ፕሮፓጋንዳ ይገልፁለት ዘንድ ጋዜጠኛው ላቀረበላቸው ጥያቄም፦” ትግሬን ወደ መቀሌ፤ንብረቱን ወደ ቀበሌ እየተባለ ነው”አሉ።
እኔ አድማጩ ብቻ ሳልሆን፤ጋዜጠኛው ራሱ ሳይደነግጥ የቀረ አይመስለኝም።
“ይህን ያለው ማን ነው?” በማለት ጥያቄውን አስከተለ።
“እንደዛ እየተባለ አዲስ አበባ ውስጥ ዳር እስከ ዳር እየተወራ ነው።በግል ጋዜጦች ላይም እየተፃፈ ነው” አሉ።
እንዲህ ብሎ የፃፈው የትኛው ጋዜጣ እንደሆነ ግን አልተናገሩም። በደፈናው ነው የግል ጋዜጦች እንዲያ እያሉ እየፃፉ ነው ያሉት።
ባልደረቦቼ ቡና ጠጥተው ሲገቡ፤ቃለ-ምልልሱን ካፊቴሪያ ውስጥ ሰምተውት ኖሮ፤ በጋዜጦች “ተፃፈ “ስለተባለው ነገር እየተነጋገሩ ነበር።
“ እንደዛ ብሎ የፃፈው ማን ሊሆን ይችላል?” ለሚለው ጥያቄ ግን፤ግምታቸውን ማስቀመጥ ከብዷቸዋል። ምክንያቱም፤በወቅቱ የትግራይ ተወላጆችን አስመልክቶ በግል ጋዜጦች እየተስተጋባ የነበረው ሀቅ፤ ቴዎድሮስ ሀጎስ ካሉት ተቃራኒ ነበር።ብዙዎቹ ነፃ ጋዜጦች፦”የትግራይ ህዝብ እንደሌሎቹ አንፃራዊ ነፃነት ቢያገኝ፤ኢህአዴግን እንደማይመርጥ የተክለሀይማኖቱ የምርጫ ውጤት በቂ ምስክር ነው”የሚለውን እውነታ ነበር እያጎሉ ያሉት።ለዚህም ነው “ እገሌ ጋዜጣ ይሆናል እንደዛ የሚጽፈው”ብሎ መገመት ከባድ የሆነው።
ቴዎድሮስ ሀጎስ የጋዜጣውን ማንነት ባለመጥቀሳቸው” ሳቢያ በእኛ ላይ የቤት ስራ ወደቀብን። ከነገሩ ስስነት አኳያ እንደዛ የፃፈውን ጋዜጣ ለመለየትና ለማወቅ ወስነን የተጠናከረ ፍለጋ ማድረግ ጀመርን።
በጊዜው ይታተሙ የነበሩ ሁሉንም ጋዜጦች “ሰብስክራይብ” እናደርግ ስለነበር፤ከሁዋላ ጀምሮ በዘመቻ መልክ ለተከታታይ ቀናት አሠስን።በጥረታችን ፈልገን ማግኘት ሲያቅተን በሌሎች ጋዜጦች ላይ ከሚሠሩ ጓደኞቻችን ጋር በጉዳዩ ዙሪያ አወራን።እነሱም፤ቴዎድሮስ ሀጎስ በራዲዮ እንዳዛ ካሉ በሁዋላ፤አባባሉን አንዳንድ ሰዎች ሲደግሙት መስማታቸውን፤ሆኖም፤እንደዛ ብሎ የፃፈው ጋዜጣ ግን፤ ማን እንደሆነ ሊደርሱበት አለመቻላቸውን ገለፁልን።በድጋሚ፤ሁሉንም ጋዜጦች በደንብ እያገላበጥን ማየታችንን አረጋገጥን።ሳናያቸው የቀሩን ጋዜጦች አዲስ ዘመን፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲና ኢፍቲን ብቻ ነበሩ። ምናልባት፤ (ልክ እንደ አሁኑ ኢትዮ-ቻነል) ፤ከጋዜጠኝነት ተግባር ወጣ ብለው የዝግ ስብሰባ ቃለ-ጉባኤ እያተሙ፦ የወሬ ማቀበል ተግባር ላይ ተሠማርተው የነበሩት ኢፍቲኖች፤ በአሉባልታ አምዳቸው ላይ፤እንዳዛ ብለው ጽፈው ይሆን?ብለን እስከማሰብም ደረስን።ግን እነሱም ላይ የተባለውን ጽሁፍ ልናገኘው አልቻልንም።ታዲያ እንዲያ ብሎ የፃፈው ማን ይሆን?
አንድ ጥያቄ ደጋግሞ በጆሮዬ ላይ ማንቃጨሉን ቀጠለ፦

ቴዎድሮስ ሀጎስ ያሉት እውነት ሆኖ፤ የተባለው ፀያፍ ነገር በጋዜጣ ላይ ቢፃፍ እንኳ፤ እርሳቸው አባባሉን እንዴት በራዲዮ ያስተጋቡታል?
ሁላችንም እንደምናውቀው፤ በወቅቱ የራዲዮ ስርጭቶች አብዛኛውን የአገራችንን ክፍል የሚሸፍኑ ናቸው። የጋዜጦቹ ስርጭት ደግሞ፤የጨመረበት ጊዜ ቢሆንም እንኳ ከሬዲዮ ጋር ሲነፃፀር፤ በጣም ውሱን ነው።ያ ብቻም አይደለም። በፅሁፍ ከሚነበብ ነገር ይልቅ በቃል(በራዲዮ)የሚነገር ነገር ወደ ህዝብ ውስጥ የመስረፅ ሀይሉ ከፍ ያለ ነው።ቴዎድሮስ ሀጎስ፤ “በጋዜጦች ተፃፈ”ያሉትን ነገር(ቢፃፍ እንኳ) ፤ በራዲዮ የነዙት፤ ይህን ስለማያውቁ ከሆነ፤በሚቀጥለው ቀን ከሥልጣናቸው ሊባረሩ ይገባ ነበር።
ግን ስለማያውቁ አልነበረም—“ከእጃችን ሊያመልጠን ነው” ብለው የተጨነቁለትን ስልጣን አንድ ቀንም ቢሆን ለማቆየት የታያቸው አማራጭ ፤በትግራይ ህዝብ ላይ እሳት መልቀቅ ስለነበር ነው እንዲያ ያደረጉት።
ይህን ሁሉ ያስተዋለው የነፃነት ጋዜጣ አምደኛም፦
“ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፤የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ”
ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ
“እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል”
ኢህአዴግ
በሚል ርዕስ ትዝብቱን ለአንባቢዎቹ አካፈለ።
አዎ! ሰዎቹ – ከሰውነት ተራ ወርደው ወደ እንሥሳት ጎራ ስለተቀላቀሉ፤ የአህያዋን ብሂል የነሱ ማድረጉ ትክክልና ተገቢ ነበር።
++++++++++++++++=

ከዚህም ሁሉ በሁዋላ ፤አልፎ አልፎም ቢሆን ያን ዘረኛ አባባል “ፃፈ” የተባለውን ጋዜጣ ለማግኘት ሞክሬያለሁ።
“በስንት ፍለጋ ያልተገኘ ጋዜጣ ፤በራሱ ጊዜ መምጣቱ አልቀረም”በማለት ለመጨረሻ ጊዜ ጋዜጣውን እንደማገኘው እርግጠኛ ሆኜ የፈለግኩት፤እስር ቤት እያለን፤
ዐቃቤ ህግ፤ በጋዜጠኞች ላይ ለመሰረተብን ክስ እንደ ሰነድ ማስረጃዎች የቆጠራቸው በርካታ ጋዜጣዎች፤ ከክሳችን ጋር እየተያያዙ እንዲታደሉን ሲደረግ ነው።
በጣም ያሳዝናል። “ብሔራዊ የአንድነት መንግስት ይቋቋም!” ብለን የፃፍንባቸውን ጋዜጦች እንደ ወንጀል ማስረጃ ያቀረበብን ዐቃቤ ህግ፤ “ትግሬን ወደ መቀሌ…”ብለን የፃፍንበትን ጋዜጣ ግን ማቅረብ አልቻለም- ያውም በመሰረተብን የዘር ማጥፋት ክስ፤ ዓለም እየሳቀበት። (በነገራችን ላይ፤ በዘር ማጥፋት ተከሰን ለእሥር ከተዳረግነው 15 ጋዜጠኞች ፤ሦስቱ የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ይህ በመቶኛ ሢሰላ 20 % መሆኑ ነው።የራሳቸውን ዘር ሲያጠፉ አስቡት)

አዎ! እውነቱ ይኸው ነው።
አስራ አምስት “ቀንደኛ”ጋዜጠኞችን ለመክሰስ በመንግስት ተመርጠዋል ከተባሉት ከነዚያ ሁሉ ጋዜጦች ውስጥ፤ቴዎድሮስ ሀጎስ ያሉት ነገር ፈፅሞ የለም።
ታዲያ እርሳቸው ከየት አመጡት?
አሁንም በስደት ምድር ላይ ሆኜ ፤ ማጣራቱን አልተውኩም።ቃሉን፤ ኮፒ እና ፔስት አድርጌ ጎግል ላይ እስከመፈለግ ደርሻለሁ።የሰጠኝ መልስ ግን፦did not match any documents የሚል ነው።
ስለዚህም፤ቴዎድሮሰ ሀጎስን ፦“እወክለዋለሁ” በሚሉት በትግራይ ህዝብ ስም እጠይቃቸዋለሁ፦
ይህን ያለው ማነው?
“ትግሬን ወደ መቀሌ!ንብረቱን ወደ ቀበሌ!”

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on November 16, 2011. Filed under COMMENTARY. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.