ያለ አስተማሪ – ለኢትዮጵያ ታማኝ ልጅ ለታማኝ በየነ

በሕዝብ ዘንድ የመወደድ ምስጢር [PDF]

(ዳኛቸው ቢያድግልኝ )

እጅግ ግሩም የሆነ ቁም ነገር አንዴ ከጀመሩት ሳይጨርሱ የማያቆሙት ነው። የትኛውም ዩኒቨርሲቲ ይህንን በአንድ ርእስ አካቶ እውቀት ሊሰጥበት አይቻለውም ይህ ልዩ ነው። በጣም ቀላል አቀራረብ ያለው በመሆኑ እንዲህ ያለ ጥልቅና ውብ የሆነን ነገር ሌላ ሰው ፈጽሞ ሊገልጸው አይችልም ብለው ቃልዎን ቃለአጋኖ ጨምረው ይሰጣሉ።

ለህሊናዎ ታማኝ ካልሆኑ አይጀምሩት ቢጀምሩትም ሊጨርሱት ይልቁንም ሊካኑት አይችሉምና ዝግጅትዎን በቅድሚያ ያጠናቅቁ ብለው ላልተረዱ ይመክራሉ። ታማኝ በየነ የሚስጥሩን ቁልፍ ለማስጨበጥ እንዲህ ይልዎታል። በሕዝብ ዘንድ መወደድ እንደዚህ ቀላል ነው። አዎን ለታማኝ ቀላል ቢሆንም መንገዱ ግን አንደርድሮ የሚያደርስ ቁልቁለት አይደለም። ታማኝ ለፖለቲካ መሪዎች ወይም መሪ መሆን ለሚሹ የፍቅርን ሀ ሁ፣ የመከበርን አቡጊዳ፣ የመስጠትን ወንጌል የመታመንን ዳዊት ለማስደገም ቆርጦ የተነሳ ሰው ነው ብለው ባደባባይ ይመስክሩለታል። ከወጣትነት እስከ ጉልማሳነት እንዲህ ነው የሄደበት። ብዙ የሀገር ፍቅር ስላለው ለሱም በሄደበት ፍቅር ይነጠፍለታል፣ ባንዲራ ይደረብለታል። ሆደ ቡቡ ነውና ይህ ያስደስተዋል እንዲህም ሆነን መኖር እኮ ይቻለን ነበር ብሎ ሲያስብ ግን የእንባው ከረጢት መቋጠርያውን ግድቡን አልፎ ይፈሳል። እየሳቀም ያለቅሳል። ይህንን አውቃለሁ አውቄም እመሰክራለሁ ሲሉ ልብዎን ኩራት ይሰማዋል። አዎ ያልተጻፈም እንኳን ቢሆን ስለታማኝ ሲያስቡ እንዲህ ያለ ነገር በምናብዎ ይታይዎታል። በተለይ የኔ ቢጤ ከሆኑ። ታማኝን አድንቀው አድንቀው የማይጠግቡ ከሆነ የዚህ አይነት ሃሳብ በልብዎ ቢሰፍርና ያንንም ቢጽፉ አያፍሩበትም። ታማኝ አያሳፍርዎትማ! ስለምን የርሱን ሃሳብ ከፍ አድርገው መናገርዎ ያሳፍሮታል? እንደ ፍልስፍና ሰው እንደ ሕዝብ ልጅ የኛን ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ይናገራል ቢባል የተጋነነው ጥቂት ነው። ሲያከብሩና ሲያደንቁ ደግሞ ትንሽ መረቅ ቢያደርጉበት ጥፋት የለውም። አይደል እንዴ? እርግጥ ክበን ክበን ካናታችን በላይ እናውለው አንልም። እርስዎ አንዲህ ሆነው አያውቁም? ጎሽ ሚዛናዊ ኖታ ስሜትዎ ዘለል አትልቦትም ማለት ነው። ይሁና እርስዎ እንዳሉት ይሁን። እንዲያው ልብዎ ተንጠልጥላ ይሆን? እንግዲያው በኔ ይሁንቦት ታማኝ መጽሀፍ አልጻፈም። ገና ነው መጻፉ ግን ይቀራል ብዬ አልገምትም። በረከት ስምዖንም አስጽፎአል። ብስራት አማረም እጫጭራለሁ ብሎ ታሪክ ቦጫጭሯል ደሞ ለመጽሀፍ አሉ? ይሁን እንጂ በስዕሉ ማርኬዎት ከሆነ አበጀሁ። አሳስቼዎት ከሆነ ግን ይቅርታ የታማኝን መጽሀፍ ላስተዋውቅዎ አይደለም። ታማኝ ከደቡብ አፍሪካ መልስ መወደድ እንዲህ ከሆነ ሌሎችም በተለይ የፖለቲካ መሪዎች ለምን የኔን እድል አያገኙም ማለቱን አስምረንበት ግን ያንን ሲል ምን ማለቱ ነበር የሚለውን በተን አድርገን ብናየውስ የሚል ሃሳብ ነው። አብረውን ቢዘልቁ ደስታችን ሲሆን ማንበብ ቢያቋርጡ ግን የሚያመልጦትን እውነት ከሌላ ሰው በድጋሚ ሊሰሙት እንደሚችሉ አስጠንቀን መቀጠላችን ነው። አዎን ደሞ ለሶስት ገጽ ምን አስኬዶትና የሰሚ ሰሚ ይሆናሉ? ቁጭ ብለው ያንብቡት። እንደሱ ይሻሎታል። ስንት መጽሀፍ የገለጡ አይደሉም?

ትዝ ይሎታል ያለ አስተማሪ መማር የሚቻሉባቸው መጻህፍት ያለ አስተማሪ ብለው ይጀምራሉ። በርካታ መጻህፍት በቢጫና ጥቁር ቀለም For Dummies የሚል መመልከትዎን እገምታለሁ። አዎን ያለ አስተማሪ ይህንን መንገድ ቢከተሉ የግድ ታማኝ በየነን ባይሆኑም ተወዳጅ ታማኝና አኩሪ ዜጋ መሆን ይቻልዎታል። በዚህ ስሜት የተነካ ሰው በአንድ ወቅት ታማኝ መሆን ጠፋን ብሎ ስንኝ ቋጥሮለት ነበር። ቅንጫቢው እንዲህ ይነበባል……

አዋቂ የፖለቲካ ሰዎች መታወቅ አቅቷቸዋል በህዝባቸውም ዘንድ ውዳሴን ክብርና ሞገስን ለማግኘት ብዙ መትጋት ይጠበቅባቸዋል። ምጡቅ የሚባሉ የሀይማኖት አባቶችም አንደዚሁ ታላቅነትን አባትነትን ለማግኘትና ለመታወቅ የታደሉ ጥቂት በጣም ጥቂት ናቸው። ግን የሚወደዱ ሰዎችን ማጥናትና የነሱን የመወደድ ሚስጥር ለማግኘት ሲሞክሩ የሚታዩ ሰዎች ጥቂት ናቸው። ጥቂቶቹም እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ታይተው ይሰወራሉ። መወደድ ግን ሚስጥር የለውም በጣም ቀላል ነው ይላል ታማኝ። መወደድ ያቃታቸው እንዲያውም በነርሱና በሬሳ ሳጥን መካከል ያለው እርቀት እየጠበበ የመጣ ፖለቲከኞች ነን የሚሉ ግን በስድብ የሰለጠኑ ቅናት አስጨፍኗቸው ይሰድቡታል። ተወዳጅን ሰው መስደብ ለመጠላት አደባባይ መውጣት እንደሆነ ማስተዋል ለተሳናቸው ሊታዘንላቸው ይገባል። ለነሱም ቢሆን ከፈለጉ በውስጣችን ትንሽ ቁም ነገር ተርፋለች ብለው ካሰቡ መወደድ እንደምን ቀላል እንደሆነ ከታማኝ ሊማሩ ይችላሉ። እንደምን ሆኖ ቀላል ይሆናል? ለሚሉ የሱን እውነት ይዤ የኔን ምሳሌ አቀርባለሁ።

የሕዝብ ልጅ መሆን ቀላል ነው አንድ ምሳሌ አነሆ ተዘፈነ ተዘፈነ ግን ለዘመናችን አለን የምንለው ቴዲ አፍሮ አልውደድህ ቢሉ እንኳ ያለማድነቅ አይችሉም። በቃ በግጥም ውበቱና መቀኘቱ ተደንቀው ሳያባሩ በወቅታዊነቱ፣ በብስለቱና በመልዕክቱ ጥራት ይገረማሉ። ይህንን ግሩም የሆነ መልዕክት ደግሞ በዜማ ነው የሚያቀርብልዎትና ጋደም ብለው ቢሰሙ፣ እየነዱ ቢኮመኩሙ፣ እየተዝናኑ ቢጨፍሩ ሁሉም ስፍራ ላይ ይመቾታል እናም ሊወዱት ይገደዳሉ። በተለይ ኢትዮጵያን የሚወዱ ከሆነ ሕዝብዋንና ታሪኳን የሚኮሩበት ከሆነ ምርጫ የሎትም። ሌሎች ምሳሌዎችም አሉ ግን ምሳሌዎቸን የመፈለጉን የቤት ስራ ለምን ለርስዎ አይሰጥም። ከፈለጉ ከራስዎ ይጀምሩና ታማኝ፣ ቴዲ እያሉ ይቁጠሩ ለሚቀጥለው ንባብዎ ይረዳዎታል። እናም በሕዝብ ዘንድ ለመወደድ ከትዕዛዛቱ መካከል አሥር ዋንኛ ምክሮችን እነሆ፦

1. ሀገርዎንና ሕዝብዎን ይውደዱ ያክብሩም
በሀገርዎ ስም ራስዎን በሕዝብዎ ስም ስልጣንዎን ብቻ የሚመለከቱ ከሆነ እይታዎን ገድበዋልና ጥቂቶቹን ለጥቂት ጊዜ ያታልሉ አንደሆን አንጂ ክብርን ፍቅርን ለዘለቄታው ሊያስገኝሎት አይችልም። ተሳክቶሎት ብዙዎች አብረዎት ሆ ሊሉ ይችላሉ ነገር ግን ሀገርዎንና ሕዝብዎን የማይወዱ ከሆነና ስልጣን እስኪጨብጡ ብቻ አሰላለፎትን ያሳመሩ ከሆነ ሆይ ሆይ ብሎ ስልጣን ላይ ያወጣዎት ሕዝብ ውይ ውይ ብሎ ያወርዶታልና በሕዝብ ዘንድ መወድድንና መከበርን ከፈለጉ በቅድሚያ ሀገርዎንና ሕዝብዎን ይወደዱ ያክብሩም።

2. መሰረትዎ እውቀትና እውነት ይሁን
ታማኝ አበክሮ የሚለው ይህንን ነው። ለእውነት የመታመንን ያህል በገዢ መሬት ላይ የሚያቆዮት ነገር የለም። በተለይ መታመንና መወደድን ከፈለጉ። እንዲያውም ለእውነት የሚቆሙ ከሆነ መውድድም መታመንም ሳይፈልጉት ይመጣል። ውርሱ እሱ ነዋ። አምርረው ሊጠሉዎት የሚችሉ ሰዎች ይኖራሉ። ቀጣፊዎችና ዋሾዎች ስምዎን ማጉደፍ ይሻሉ። መብጠልጠልና መነቀፍም ሊበዛብዎት ይችላል። ያ ግን ጊዜያዊ ነው ይልቁንም እኒህ ስም አጥፊዎች ከማንም በላይ የሚያከብሩትን የሚፈሩት እርስዎ ሀቅን እንቅ አድርገው ከያዙ ነው። ታድያ የእውነት መሰረቱ የዋህነት ሳይሆን እውቀት ነው። ያወቀ ለእውነት የቀረበ ነው። ልዩነቱ እውነትን ይዞ ለዚያ በመቆምና እውነትን አወላግዶ ለራስ ፍላጎት ማዋሉ ላይ ነው። እውቀትዎ ከእውነትዎ ጋር ሰመረ ማለት ግን በሕዝብ ዘንድ መወደድና ሞገስን ማግኘት ማለት ነው። በዚህ ቢተጉ መልካም ነው።

3. ውጥንዎ የግል ዝናና ጥቅም ብቻ አይሁን
ይህም ጥልቅ ምክር ነው ታማኝ ሰርቶ ያሳየውም ስለሆነ ምሳሌነቱ አይቸግሮትም። ዝናን ፈልገው መንገድዎን ከጀመሩት ጥቅምዎን ብለው አደባባይ ከቆሙ እርስዎ እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ኖት ብልጭ ብለው የሚጠፉ። ማነው ማነው ይባሉና ሳይታወቁ ይረሳሉ ምክንያቱም ሁለቱም ዝናና ጥቅም በራሳቸው መነሻና መድረሻ ስለሆኑ። አላማዎ መወደድና መከበር ከሆነ በዚህ መንገድ ሄደው የትም አይደርሱም። እርግጥ ነው ራስዎ ለራስዎ ዝነኛና ራስዎ የራስዎን ጥቅም ሊያገኙበት ይችላሉ። በሕዝብ የምትለው ቁልፍ ነገር ግን ክርስዎ ትነጠላለች።

4. የሕዝብዎን የልብ ትርታ ጠንቅቀው ይወቁ
አዩ ይህ ነው ዋንኛው የታማኝ ቁልፍ! የሕዝብዎን የልብ ትርታ ይወቁለት፣ እርሱን ሆነው ተናገሩ በርሱ ቦታ ሆነው ያስቡ እርሱ ይበጀኛል የሚለውን ይወቁለት። ታማኝን ተወዳጅ ያደረገው ያ ነው። የሕዝቡን ስሜትና እውነት ባማረ ቋንቋ በድፍረት መናገር መቻል። ይህ ድፍረት ይፈልጋል መስዋዕትነትም ያስከፍላል። ግን ያለጥርጥር የሕዝብ ፍቅርን ይቸራል። እርስዎ በጣም አዋቂ ሊሆኑ ይችላሉ የችግር መፍቻ ቁልፍ ብቻ ሳይሆን ቁልፎች ሊኖርዎት ይችላል። ግን የማውቅልህ እኔ ነኝ የሚበጅህም ይህ ነው ካሉት እሺ አይሎትም። እንኳን ሕዝብ ሕጻን ልጅም አሻፈረኝ ይላል። ስለዚህ የሕዝብን ተሳትፎ፣ መልካም ፈቃድና ፍላጎት መነሻዎ ያድርጉ ያ በሕዝብ ዘንድ የመከበርና የመወድድ መንገዱ ነው።

5. እውነትን ለመናገር ድፍረቱንና መንገዱን ይወቁበት
ይሄኛውም ጉደኛ ምክር ነው ልብ ብለው ያንብቡት። እውነት ጥሩ ነገር ነው ግን ደግሞ አንዳንዴ ይመራል፣ ውጤትን የሚፈልጉ ከሆነ ጊዜና ቦታውን ሊያውቁበት ይገባል። ከዚያ በላይ ደግሞ በምን መንገድ ነው እውነት ቢነገር ትንሽ መስዋዕትነት፣ ብዙ መረዳትና ጥሩ ውጤት የሚያመጣው ብለው ያስቡ። የአነጋገርዎ ለዛ፣ የአድማጭዎ የመረዳት አቅም፣ የሚያቀርቡት እውነትና የሚያመሳክሩበት ምሳሌ አግባብነት፣ ተቀባይነትን ለማግኘት ወሳኝ ነው። ስለዚህ እውነት መያዝዎና ባወጣ ያውጣው ማለትዎ ሳይሆን፣ የያዙት እውነት ሊያመጣ የሚችለውን ስኬት ማገናዘቡ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ነው ታማኝ አንድና ተመሳሳይ ነገርን በተለያየ መድረክ በተለያየ ቅርጽና ውበት በማቅረብ ቀልብ ለመሳብ አቅም ያለው። ስለዚህ በዚህ መንገድ ሄደው ታማኝን በልጠውት ቁጭ ቢሉ እርሱ ከልብ ይደሰታል። ያንን ነዋ የሚፈልገው እርስዎ ከበረቱለት እሱ ወደ ‘አዝማሪነቱ’ መሄድ ነው የሚፈልገው።

6. ይቅር ለማለትና ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ ይሁኑ
ካልጠፋ እውቀትና ልምድ ይቺ ይቅርታ መጠየቅ አትሆንሎት ይሆናል። ክብርዎን ስለሚወዱ ሳይበቀሉና የልብዎን ሳያደርሱ ይቅር ማለት አይወዱ ይሆናል። በኔ ይሁንቦት እርስዎ ብቻ አይደሉም ብዙዎች ይህንን ከደማቸው ውስጥ ማጽዳት ይከብዳቸዋል። ታድያ እርስዎ ዝቅ ብለው ይቅርታ መጠየቅ የሚችሉ ከሆነ የታደሉ ነዎት። ብዙዎች አሸናፊ መሆን ስለሚፈቅዱ ሰዎች በርስዎ ደስ ይላቸዋል። እርስዎም ይቅር ባይ ከሆኑ አሸናፊ ነዎት። በሁለቱም አቅጣጫ እርስዎ ትክክል ስለሚሆኑ ብዙ ተቃውሞ አይገጥሞትም። በሕዝብ ለመውደድ ከምክንያታቸው በፊት ስሜታቸውን ሊገዙ ይገባዎታልና ይቅርታ ጠያቂና ይቅር ባይ ከሆኑ የሰዎችን ልብ ያገኛሉ። አውነትና እውቀት ከርስዎ ጋር ከሆኑ ደግሞ አእምሮአቸውንም የርስዎ አጋር ማድረግ ይቻልዎታል። አበቃ ልብንና አእምሮን ወደርስዎ እንደማግኔት መሳብ ከቻሉ የመወደድ ቅመም የመታመን ጸጋ ከርስዎ ጋር ይሆናል።

7. የሕዝብዎን ባህልና ስነ ልቡና ጠንቅቀው ይረዱ
ከሀገርዎ ርቀው በጣም ርቀው ይኖሩ አንደሆን በወቅቱ ካለው የወገንዎ ስነልቦናና አስተሳሰብ ጋር ተራርቀዋል ማለት ነው። በኔ ይሁንቦት ከሀገርዎ ወጥተው ጥቂት ከቆዩ ብዙ ነገር ለርስዎ እንግዳ ነው። ስለዚህ በሩቅ ርቀት አውቀዋለሁ ብለው ከማሰብዎ በፊት ቁርኝት ይፍጠሩ። ምን ያስቀዋል ምን ያሳዝነዋል ብለው ያጣሩ። በድሮ መፈክር ዛሬ ሊያነሳሱት አይችሉም። የፈረንጅ አገር ልምድዎ ብቻውን የትም አያደርሶትም። ስለዚህ የልቡን ሊያውቁለትና ስሜቱን ኮረኩረው ሀሳቡን አስግረው ካሰቡበት ለመውሰድ ሊዋሃዱት ይገባዎታል። ከተዋሃዱትና ካወቁት የሚፈልገውን አሳምርው መናገር ከቻሉ ፍቅርና ክብር ሕዝቡ ሊቸርዎት የግድ ነው አልዎታለሁ።

አብረውትም እየኖሩ ላያውቁት ይችላሉ። ጠጋ ቀልቀል ይበሉ ወደሕዝቡ እንጂ ምጡቅና ረቂቅ ሆነው ቁልቁል አይመልከቱት። ቋንቋውን በደንብ ይወቁለት፣ ዘይቤውን ዘመነኛ ቃሉን ይረዱለት በተለይ ወጣቱን ጠንቅቀው ይወቁት። ወጣት ለአዲስ ሀሳብና ለለውጥ ቅርብ ነውና። ባሁኑ ዘመነኛ ቃል አቦ ይመቾት ይልዎታል ከደበሩትም ዱድ እስቲ ጫር ይሎታል መንገዱን ጨርቅ ያርግሎት ለማለት። እናም የሕዝብዎን ስነልቦና ስንልዎት የሁሉንም ለማለት ነው።

8. የችግሮችን ብዛት ሲቆልሉ መፍትሄ ማመላከቱንም ይወቁበት
አንዳንዴ የሚፎካከሩትን ራቁት ያስቀሩ እየመሰሎት ጥፋታቸውን ሲቆልሉ፣ አርግማኖትን ባናት ባናቱ ሲያወርዱት ጥሩ የሰሩ ይመስሎታል። እርስዎ ግን የተሻለ ነገርን እንዴት ሊሰሩ እንደሚችሉ ማሳየት ካላወቁበት በሰፈሩት ቁና ለመሰፈር ተዘጋጅተዋል ማለት ነው። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜዎን ያጠፉት በመቃወም ላይ እንጂ የሚደገፉበትን ነገር በማደራጀት ላይ አይደለምና ችግር ውስጥ ይወድቃሉ። ብዙዎች ለ አመታት ተቃዋሚ ሆነው የቆዩ ሰዎች ችግራቸውም ይኸው ነውና በዚህ ጉዳይ ላይ ከተቃዎሞዎ በላይ ሊሰሩ የሚችሉትን በውል ቢያውቁ ስልጣን እጅዎ የገባ ቀን የ እናቴ መቀነት አደናቀፈኝ አይሉም። ያኔ መቃወም ቀላል እንደነበረ ያውቃሉ አውቀውም ተመልሰው ተቃዋሚ የሚሆኑበትን ቀን ይመኛሉ። ይህ ደግሞ ለርስዎ ደግ አይደለም። አይመስሎትም? አዩ እኛ ተስፋ ፈላጊዎች ነን። ተስፋ አስቆራጭ ንግግር ካደረጉ በርስዎም ተስፋ ይቆረጣል። ለዚህ ነው የተስፋ ቃል ይዘው የሚመጡ የሚያሸንፉት። ኦባማን ልብ ይበሉ። ኦባማን ይሁኑ ግን አንሎትም የራስዎ እውነት የራስዎ ራዕይ አለዎትና!!

9. ለመማር የተጉ ለመተግበርም የቀለጠፉ ይሁኑ
መማር የማይሹ ከሆነ ወይ አርጅተው በቃኝ ብለዋል ወይም እርስዎ እብሪተኛ ኖት፣ ተምክህት አለቦትና የርስዎ ምኞትና ፍላጎት መወደድ ሊሆን አይችልም። ያሉት የሚገባዎ ቦታ አይደለምና ቆም ይበሉ። ራስዎን ይጠይቁና እንዲሁ እንዳሉ ከፈጣሪዎ ጋር የሚገናኙበትን ድልድይ ማለትም ጸሎትን ይምረጡና በዚያ ይትጉ በሕዝብ መወደድ ላይሆንሎት አይድከሙ። ፍላጎትዎ በሕዝብ መወደድና መከበር ከሆነ ግን ፈገግ ብለው ከትንሽ ከትልቁ ይማሩ፣ አስተማሪ አይደሉምና ማርክ መስጠቱ ይቅርብዎ። ይስሙና ይማሩ ከሕዝብ ስህተትም እኮ ትምህርት አለው ብለው ከፍና ዝቁን ይመርምሩ። ታድያ ደግሞ እርስዎ አላማዎ በሕዝብ ዘንድ መወደድ እንጂ ተመራማሪ መሆን አይደለምና ለተግባር የፈጠኑ ይሁኑ። የተማሩትን ይናገሩ ያልተማሩትንም ያልተረዱትንም አይደባብቁ አላውቅም ማለት ነውር የለውም የማያውቁትን አውቃለሁ ሲሉ ነው ችግሩ። ግን ደግሞ ለምሳሌነት ተምሮ ለማወቅ ሰርቶ ለመታወቅ ቀልጠፍ ይበሉ። ሕዝቡ የሚሻውን በርስዎ ሕሊናም እውነት የሆነውን ነገር ይተግብሩ። ምሳሌ ሲፈለግ እርስዎ ቀዳሚው ረድፍ ውስጥ ይሆናሉ። እርስዎ እባካችሁ እኔን ውደዱኝ ሳይሉ ስለርስዎ የሚመሰክሩ ብዙ ይሆናሉ። ተረዱት አይደል? ለመማር ትጉህ ሲሆኑ ለመተግበርም የቀለጠፉ ሲሆኑ ስኬት የርስዎ ናት! የርስዎ ስኬትም በሕዝብ ዘንድ መወደድና መከበር ይሆናል። ያንን ይዘው መወዝወዝ ነው።

10. በቡድንም በግልም የመስራት አቅምዎን ያዳብሩ
እርስዎ በግልዎ ጎበዝ ከሆኑ አበጁ እምነትዎ የሰናፍጭ ቅንጣትም አክላ ቢሆን ተራራ ዘወር ማድረግ የሚችልም ከሆነ ሸጋ ነው ግን በሕዝብ ዘንድ የመወደድ ግቡ ይህ ብቻውን አይደለም። ይልቁንም በጋራ የመስራትና የማሰራት ችሎታዎ ነው ዋና የሚሆነው። በጋር መስራት መቻል ማለት የሌሎችን ሀሳብ ማወቅና ማክበር ማለት ነው። ሰው ሲያውቁለት ሲያውቁበትና አክብረው ሲሰሙት እንደለማዳ እንስሳ ነው ታዛዥና ታማኝ፣ አንድ ሕጻን ልጅ ነው ደስታውን መደበቅ የማይቸል ያኔ እርስዎንም ይሰማዎታል።ለማዳ እንስሳ ንቀት እንዳይመስሎት እግዜር መረጠን ብለን እንጂ ልዩነታችን እኮ ብዙም አይደል። ታድያ ይህን ካወቁበት ምን መስማት ብቻ፣ ሕዝብ ያምኖታል ይከተሎታልም። ማስተባበር አይከብዶትም፣ መምራት አያስቸግሮትም የተበታተነውን ወደ አንድ ማምጣትም ለርስዎ ቀላል ይሆናል። ያንን ማድረግ ከቻሉ በሕዝብ መወደድና መታመን የርስዎ መታወቂያ ናት።

እንዲያ ነው እንግዲህ መጽሀፉም ትዕዛዝ ካስር ከበዛ ልጆች ተግተው አይማሩም ብሎ ነው አስሩን ትዕዛዛት አድርጎ ሁዋላ በ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ የሽነሸነው። እናም ይህን ያህል ይበቃል።

ዳኛቸው biadegelgne@hotmail.com

ደቡብ አፍሪካ ለታማኝ ሰው የሚሰጠውን ክብር በታማኝ አየችው። ይህ ጽሁፍም መታሰቢያነቱ ለታዋቂው የኢትዮጵያ ታማኝ ልጅ ለታማኝ በየነ ይሁን። መንደርደርያውም ከደቡብ አፍሪካ ጉብኝቱ መልስ የሰጠው ቃለ መጠይቅ ነው።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 29, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.