የፖለቲካ ፓርቲዎች ጩኸት ለህዝብ ወይስ ለስልጣን? ( ሀበሻ በየመን ክፍል 9)

                               [በግሩም ተ/ሀይማኖት]

አንድ ወዳጄ ‹‹..እንግዲህ እኔም እንደ የመኑ ፕሬዘዳንት አሊ አብደላ ሳላህ 32 አመት የመንን ሙጥኝ ልል ነው ወይስ እንደ እሳቸው ለየመን ህዝብ ሰሰለቸው በሰላማዊ ሰልፍ ‹‹ይርሀል›› ይሂድልን ልባል ነው? ወይ ጉዴ!!! ወይ ወገን ማጣት……ያልከው ምሬት አልበዛም ወይ አለኝ፡፡  እውነታው ግን ያ አይደለም፡፡

 እንዲያውም ራስ ወዳድ ስለሆንኩ የራሴን ብቻ አስታውሼ የኔውን አሰማሁ እንጂ ወገን አስታዋሽ ያጣሁት እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ የመን ያለ ስደተኛ ሁሉ አስታዋሽ፣ ሲራብ አጉራሽ..አላገኘም፡፡ እልቂቱን፣ ረሀቡን፣ በጥይት መነደሉን፣ ሞቱን፣ ጥቃቱን ሁሉ ሰሚ አላገኘም፡፡ እንኳን ሌላው ዜጋ ወገኔ አካሌ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊሰማው አልፈለገም፡፡ አልፈቀደም፡፡ ስላለው ችግር፣ በጥይት መርገፉን ባህር ሲያቋርጥ ያለውን ሰቆቃ ያላሰፈርኩብት..ኡኡኡኡ ድረሱልን ያላልኩበት ወቅት የለም፡፡ እዚህ የመን ሰነዓ ከተማ ውስጥ አሳባ የሚባል ቦታ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በጦርነቱ ተፈናቀሉ… በመጀመሪያው ጊዜ 4 ወገኖቻችን ሞቱ ብዬ ሬሳውን ራሴ ሆስፒታል ሄጄ ማየቴን ሁሉ አሰፈርኩ፡፡ የተፈናቀሉት ወገኖች የሚበሉት የሚጠጡት አጥተው መጠለያ ጠፍቶ መፍትሄ ይሰጠን ብለው UNHCR በር ላይ ወደቁ፡፡ እኛም ቀጣይ ነን መርገፍ ጀምረናል ብዬ ሁሉን አሰባስቤ ከሶስት ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን መፍትሄ ይሰጠን በማለት UNHCRን መጠየቅ ጀመርን፡፡

   ከመሀላችን አራት ሰው ወስደው ሲያስሩ እኔ የምፅፈውን ነገር እንዳቋርጥ ያለበለዚያ ችግር እንደሚገጥመኝ ተነገረኝ፡፡ UNHCR ቢሮው ጠርቶ የየመን ፖለቲካ ውስጥ እንዳትገባ ሲል አስጠነቀቀኝ፡፡ ማስጥንቀቂያው በወረቀትም ጭምር ነው የተሰጠኝ፡፡ ነገር ፍለጋ እንደሆነ ባውቅም እዚህ ጋር ወገን እየረገፈ በዝምታ የምቀመጥበት ምክንያት ስለሌለ ወገን ይደርስልናል ብዬ ችግሩን ማሰማት ጀመርኩ፡፡ እንዲህ እያለቅን እንዴት ወገናችን ዝም ይለናል ብዬ ላስብ? እኔም ላይ አንድ እርምጃ ቢወሰድ ወገኔ የህዝቡን ጩኸት አሰምቼው እንዴት ዝም ይላል የሚል ሀሳብ ሰነኩ እና እዚህ ያለውን ሰው ብሶት ባለችኝ አቅም መጫጫር ጀመርኩ፡፡ የሚያሳዝነው ግን ከንቱ ድካም፣ ከንቱ መሰዋዕትነት ነው የሆነብኝ፡፡ ዛሬ በUNHCR ቢሮውም ሆን በኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከስሻለሁ፡፡ ያም ቢሆን ውጤት ቢኖረው ደስ ባለኝ፡፡ ግን አንዱም ምላሽ ለመስጠት፣ ለወገኑ ችግር ለመረባረብ ፍቃደኛ አለመሆኑ አሳዝነኝ፡፡ እንዲህ አይነት ወገን ነው ያለኝ? እንድል አደረገኝ፡፡

ጥቂቶች.. በጣም ጥቂቶች ሊረዱን ተሯሯጡ አሁንም ይታገላሉ፡፡ አቶ ከባዱ፣ አቶ ኦባንግ ባለን ቅርርብ መረጃ እንለዋወጣለን፣ ሌፍተናንት በላይ፣ ሌፍተናንት ዩሀንስ…ጋዜጠኛ አሉላ ከበደ እና ዳንኤል ገዛኸኝ.. በቃ!…ይሄው ነው፡፡ አያሳፍርም?!! እነዚህ ብቻ ናቸው ወገኖቻችን? የወገኑን የጣር ጩኸት የማይሰማ፣ የወገኑ ቁስል የማያመው፣ የወገኑ ሞት የማያሳዝነው የያዘች ኢትዮጵያ የጣር ጩኸቷ መቼ ነው የሚሰማው? የመን ያለ ሀበሻ ወገን እያለው ወገን እንደሌለው ሀገር እያለው ሀገር እንደሌለው በሰው ሀገር ረገፈ፡፡ ስንቶች ሞቱ?     

    በሌላ ጊዜ ደግሞ እኛም ሻራ ሀየል አካባቢ ያለን ነዋሪዎች ይህው ጦርነት ደረሰብን፣ ከቤታችን ተፈናቀልን፣ ቤት ንብረት ጥለን ወጣን ተዘረፍን.. በጦርነት ወደቅን 12 ሰው ሞተ የቆሰለውም የዋዛ አይደለም፡፡ 85 ወገን የገባበት አልታወቀም፤ ወገን ስሙን…አረ ድረሱልን!!! ብያለሁ፡፡ ኤምባሲው ዜጎቹን የሚያስታውስ አይደለም፡፡ UNHCR ቢሮው ለኢትዮጵያዊያን ዝግ ነው፣መድሎ አለ፣ ቢሮው መፍትሄ ሊፍልግልን አልፈለገም፡፡ የወገን ያለህ!.. ያላልኩበት ጊዜ የለም፡፡ በስም ጠርቼ ሁሉ እባካችሁ ወገናችሁ በጦርነት እየረገፈ ነው ማድረግ ትችላላችሁ፣ ተሰሚነት አላችሁ ይባላል አልኩ፡፡ የእኛን ጩኸት ከመስማት ይልቅ ፊልም ስፖንሰር አድርገው ሲወደሱ የሰማናቸው ሰዎች አሉ፡፡ ለምን የስደተኛ ብሶት ይሰማሉ? ችግራችን ፊልም አይደለ? እየተዝናናን እንድንሞትም ፊልም ካዝጋጁልን ደስ ይላል፡፡ በመገናኛ ብዙሃን እንረዳቸዋለን የሚል ዝባዚንኪያም ይህ ምርጥ ኢትዮጵያዊነት ነው..ወገን ያልነው ወገናችን ያሳየን ምላሽ በአሳፋሪነቱ በጣም ያስደስታል፡፡ አሳፋሪ ስለሆነ ምላሹ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? የሚል ነገር እንድናስብ ያደርጋል፡፡

  በጦርነት መፈናቀላችን UNHCR በር ላይ መተኛታችን፣መፍትሄ ስጡን በማለታችን በአድማ በታኝ በፖሊስ መደብደባችንን፣ ከመቶ በላይ ሰው ጉዳት እንደደረሰበት ሁሉን ብገልፅ፣ ስንደበደብ በድብቅ የቀረፅነውን ቪዲዬው ብናሰራጭ ምን ምላሽ ተሰጠን? በርካታ ማስረጃዎች በሌለን አቅም ከፍለን ስንልክ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ ካልተጣለ በስተቀር ከላክንላቸው፣ጩኸታችንን ከሰሙት ውስጥ ማነው የደረሰልን? ማነው አይዟችሁ ያለን? ጥቂት ሰዎች በስልክ አናግረውናል፡፡ ሌላ ለጉዳያችን ትኩረት ሰጥተው የሚሮጡ ይኖራሉ፡፡ ለተራበው፣ ለተፈናቀለው ወገኔ ካለኝ ላይ ላጉርስ ያለ ሰው አለ? በስመ ተቃዋሚ ፓርቲነት የተሰየሙት፣ ትላልቅ የእርዳታ ድርጅት አላቸው የሚባሉትስ ይህ የወገን ሰቆቃ ካልተመለከታቸው ለየትኛው ወገን ነው የሚታገሉት፡፡ የሚረዱት? ስደተኛ ከኤሺያ ሳይቀር የሚያንቀሳቅስ ድርጅት የሚመሩ ሆነው ዝምታ ምሽግ ውስጥ መመሸጋቸው ወገናዊነት ነው?

  ተቃዋሚዎችስ የየትኛው ወገን ነው መብትን ለማስከበር፣ለየትኛው ወገን ዲሞክራሲያለማስፈን የሚታገሉት? ለምንድን ነው ተቃዋሚ ሆነው የተጎበሩት? እገሌ የፖለቲካ ፓርቲ የሚል ስም ይዞ ተቆንኖ መቀመጥ እና የመዋጮ ሳንቲም መጠበቅ ነው ተቃዋሚነት? ዛሬ ጩኸቱን ያልሰሙትን ህዝብ ነገ ስልጣን ላይ ሲወጡ በደለበ ብር ጆሯቸውን ሲደፍኑ ሊሰሙት ነው? ለነገሩ ረስቼው ነው ጠንካራ ራሱን የቻለ የቱ ነው ተቃዋሚ????

   የስልጣን ተቃዋሚ ወንበር ፈላጊ ይኖረን ይሆናል እንጂ ለህዝብ ጥቅም ያሰበ መብት ተጣሰ ያለ ተቃዋሚ፣ ብሶት የወለደው ተቃዋሚ የለንም፡፡ አሁን ገና መጠንሰስ ያለበት ይመስለኛል፡፡ በስም፣ በማዕረግ የተለበዱ ኩንታል ኩንታል አክለው ተጎብረው በንቀት አቆልቁለው የሚያዩን ሳይሆን እኛኑ ሆነው ከእኛው ጋር አልቅሰው፣ ችግራችን ችግራቸው የሚሆን እንባችን የሚያቃጥላቸው፣ ታግለው የሚያታግሉ የተቃዋሚ መሪዎች ከወጣቱ ክፍል ያስፈልጉናል፡፡ ያለበለዚያ ታማኝ በየነ እንዳለው የዶክተር እና ኢንጂነር ቁልል አስጠልቶናል፡፡

    በስም ተለብደው በየሚዲያ ላይ ቆርፋዳ እና ዲሪቷማ ቃላት ሲያዘንቡ መስማት የምንፈልግበት ጊዜ አልፏል፡፡ አሁን የህዝብ ጩኸት ጩኸታቸው የሆኑ ጠንካራ ተቃዋሚዎች እንፈልጋለን፡፡ በስደትም በሀገር ቤትም ያለውን ህዝብ ጩኸት የሚያዳምጥ ለመብት፣ ከጭቆና ለመላቀቅ የሚታገል ፓርቲ ያስፈልገናለን፡፡

    በተቃዋሚነት ከሀገሩ የተሰደደ የለም? ፓርቲያቸውን ሲደግፍ ታስሮ ተደብድቦ ሀገሩን የለቀቀ የለም? ታዲያ ተቃዋሚዎችስ ጩኸታችንን ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉት ለምን ይሆን? በቅርቡ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከቪኦኤ ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ያሉት ‹‹..በሰላማዊ መንገድ፣ በተለያየ መንገድ ሲታገሉ የነበሩ ጋዜጠኞች እንዲሁም ዜጎች በስፋት ሀገራቸውን እየለቀቁ በየጎረቤት ሀገር የሚሰደዱበት ዘመን ነው ያለው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በአለም ካሉ ሀገሮች አንደኛ ሳትሆን አትቀርም በፖለቲካ ምክንያት ዜጎቿ የሚሰደዱት..›› ብለዋል፡፡ የሳቸው ፓርቲ የመን ያለውን ሰቆቃ አላየ፣ አልሰማ ይሆን? ካየ ከሰማ ምነው ምላሽ አልሰጠን? አላየንም አልሰማንም እንዳይሉ የተለያየ መገናኛ ብዙሃን ከሚያደርሷቸው ወጭ በግሌ መረጃ ያላኩላቸው ጊዜ የለም፡፡ ታዲያ ምነው በሬዲዮ ብቻ…? ለህዝብ ነኝ ከተባለ ይህ ነው መንገዱ?

የመን ውስጥ ካለው ስደተኛ ኢትዮጵያዊ አብዛኛው የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ ነው፡፡ ኦነግ ነህ ተብሎ፣ ኦነግን ረዳችሁ ተብሎ፣ ደጋፊ ነህ እያሉ ታስሮ፣ ተገርፎ፣ ስቃዩን አይቶ የወጣው ይበዛል፡፡ በእርግጥም የኦሮሞ ሕዝብ በሙሉ የኦነግ ደጋፊ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኦነግም በውጭው አለም ጠንካራና ጥሩ ቦታ ያላቸው አባሎች አሉት፡፡ ድርጅቱም ወያኔ እንደሚለፍፈው ሳይሆን ተሰሚ እና ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ታዲያ ለኦሮሞ ልጆች ጩኸት የሰጠው ምላሽ ለምን ዝምታ ሆነ? እንቅስቃሴም ካለ መፍትሄ ላይ ለምን አልደረሰም? UNHCR በር ላይ ከወደቁት፣ መፍትሄ ይሰጠን ካሉት ውስጥ በርካታዎቹ ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ ደጋፊዎችም ናቸው.. ዝምታው ተሰብሮ መፍትሄ ሊደረግላቸው አይገባም? ካልሆነ ግን የድርጅቱ ለሕዝብ ነው የምታገለው ብሎ መጮህ ምንድን ነው ጥቅሙ?  ምንድነው ፋይዳው?

   ኦብነግ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከኦጋዴን ክልል የተፈናቀሉ፡፡ አማፂውን ረድታችኋል የተባሉ፣ የታሰሩ የተገረፉ..የተሰደዱ ኢትዮጵያዊ ሶማሌዎች በስደት የመን የሉም? ኦብነግስ ነፍጥ ይዞ መታገል ብቻ ነው አላማው? ለእነዚህ የብሄሩ አባት ችግር ምን ያደረገው አለ? ምንም ከሆነ መልሱ ለሕዝብ ነን እያሉ መጮህ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ነጠላ ዜማ ነው ማለት ነው?

    የሕዝብ ነኝ የሚሉ ተቃዋሚዎች የህዝብ መሆናቸውን ካላሳዩ፣ የሕዝብ ጩኸት ካልሰሙ ቀድሞውኑ ባልተፈጠሩ፡፡ ከተፈጠሩም ሕዝብ ሕዝብ እያሉ ባላላዘኑ፡፡ እስኪ እንያችሁ የሕዝብ ነን ያላችሁ….አሁንም ጊዜ አለ፡፡

           በቀጣይ እስክንገናኝ ሰላም ለሁሉ

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 24, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.