የፓትርያርኩ ቀብር ሃሙስ ይከናወናል

የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ጉባኤ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከቀኑ በ6፡00 ሰዓት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲፈጽም ወስኖ አስታውቋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ካስታወቀበት ማግስት ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው፣ እነርሱን መጠጊያ ያደረጉት እነ እጅጋየሁ በየነና የ”ራእይ ለትውልዱ” ያሬድ ግርማ ሥርዐተ ቀብሩ የሚፈጸምበት ቀን ወደ ቅዳሜ፣ ነሐሴ 19 ቀን 2004 ዓ.ም እንዲራዘም እየጎተጎቱ ስለመሆናቸው ተነግሯል፡፡ ይህን ጥያቄያቸውንም ሐዘን ለመድረስ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ለሚመጡት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በመወትወት ለማሳመን ሲጥሩ መታየታቸውና አንዳንዶቹም “ሲኖዶሱን በሕግ እንጠይቃለን” እስከ ማለት መድረሳቸው ተዘግቧል፡፡ በእነርሱ ፍላጎት ሥርዐተ ቀብሩ ኀሙስ በሥራ ቀን መኾኑ ብዙ ሰው እንዲገኝ አያስችልም፤ አስከሬኑም ከቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በቀጥታ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲወሰድ መደረጉ ጉዞውን ያሳጥረዋል፡፡

በመኾኑም ሥርዐተ ቀብሩ የሚፈጸምበት ቀን ወደ ቅዳሜ፣ ነሐሴ 19 ቀን እንዲዛወር፤ አስከሬኑም ከቅድስት ማርያም በቀጥታ ወደ ካቴድራሉ መወሰዱ ቀርቶ በሠረገላው እንደተጫነ ወደ መስቀል አደባባይ እንዲያመራና ከዚያም ወደ ካቴድራሉ ተመልሶ እንዲፈጸም ቢደረግ ብዙ ሰው ተገኝቶ በተለያየ ቦታ ሐዘኑን ለመግለጽና ለመሰናበት ያስችለዋል፡፡ በአንድ ጊዜ በአንድ ቦታ እንደሚገኝ የሚጠበቀው ሕዝብ ብዛት “ለጸጥታ አጠባበቅ ከሚፈጥረው ጫና” አኳያ ሐሳቡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ድጋፍ አግኝቶ ጥያቄው ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ እንደነበር ነው የዜናው ምንጮች የተናገሩት፡፡

የፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከቀኑ በ6፡00 ሰዓት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲፈጽም ወስኖ አስታውቋል፡


ቅዳሜ፣ ነሐሴ 12 ቀን 2004 ዓ.ም ማምሻውን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቤተሰቦች በተገኙበት ተሰብስቦ በጥያቄው ላይ የመከረው ቅዱስ ሲኖዶስ ግን የቀደመ ውሳኔውን በማጽናት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በመገኘት ሐዘንን መግለጽ እንደሚቻል፣ ሥርዐተ ቀብሩም ቀደም ሲል በተገለጸው አኳኋን እንዲከናወን መስማማቱ ተገልጧል፤ እስከዚያው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አስከሬን አሁን በሚገኝበት ሃያት ሆስፒታል ተጠብቆ ይቆያል፡፡

በሥርዐተ ቀብሩ ላይ ተገኝቶ የሐዘን መግለጫውን እንደሚያቀርብ ያስታወቀው በሰሜን አሜሪካ በስደት ላይ ከሚገኙ አባቶች ጋራ የሚካሄደውን የዕርቀ ሰላም ንግግር ሲያመቻች የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ሁለት ልኡካን አዲስ አበባ እንደሚገቡ ተሰምቷል፡፡ ጉባኤው ባወጣው መግለጫ በሀገር ውስጥና በውጭ በሚገኙት አባቶች መካከል አንድነት መፍጠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳ እንዲሆን፤ ልዩነት በአንድነት ሳይፈታ ፓትርያርክ የመሾሙ ጉዳይ እንዲታሰብበት ለቅዱስ ሲኖዶስ ማሳሰቡና መንግሥት ለአንድነት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ መጠየቁ ይታወሳል፡፡

በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች በብፀዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር አፈጻጸም ላይ የበኩላቸውን ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት በማካሄድ ላይ መኾናቸው ተነግሯል፡፡ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ምንጮች ለደጀ ሰላም እንደገለጹት÷ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አባታዊ ክብር ሰጥቶ ከመሸኘት፣ ሥርዐተ ቀብሩንም ከቤተ ክርስቲያናችን ተቋማዊ ሓላፊነትና ገጽታ ተመልክቶ ለቀጣዩ በጎ ልምድ ከማቆየት አኳያ ምእመናኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
በዚህም መንፈስ ከሁሉም የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች የተውጣጡና በየክፍለ ከተማው የተሰባሰቡ መዘምራን የመዝሙር ጥናት በማድረግ ላይ መኾናቸው ተጠቁሟል፡፡ በቁጥር ከ138 በላይ በሚኾኑ የአዲስ አበባ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች የተመሠረተው አንድነቱ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሚቋቋመው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የቤተ ክርስቲያንን ዕድገት ለማፋጠን፣ ቤተ ክርስቲያን ከምእመናኑ ሰባ ከመቶ የሚኾነው ወጣት አጠቃላይ አያያዝ የተመለከተ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንድትቀርጽ ቀዳሚ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

Source: Deje Selam

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on August 21, 2012. Filed under NEWS. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.