የፐ/ር ኤፍሬም ይሳቅ ቡድን ከቀድሞ የኦነግ አመራር ጋር

Prof. Ephrem in hague[Read inPDF] በፐሮፌሰር ኤፍሬም ይሳቅ የሚመራ አንድ ቡድን ከቀድሞ የኦነግ አመራር ጋር ባለፈው ሴፐቴምበር 19 – 21, 2008 (እ.ኤ.አ.) በ ሄግ: ኔዘርላንድስ ከተማ ውይይት አድርገው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል:: ውይይቱ እንዲካሄድ የሆላንድ: የኖርዌይና የጀርመን መንግስታት በገንዘብ የረዱ መሆናቸውም ተገልጿል:: በውይይቱ ላይ ፐ/ር አኤፍሬም: ፓስተር ዳዓኤል እና አምባሳደር የተገኙ ሲሆን: ከ ኦነግ በኩል ደግሞ አቶ ለንጮ ለታ: አባ ቢያ አባ ጆቢር እና አቶ ዲማ ነጎ ተገግተው ከተወያዩ በሁዋላ ቀጣዩን ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ ማድረግ እንዳለባቸው ተስማምተው ተለያይተዋል::

ወያኔ ምርጫ 97ን በገሃድ ካጭበረበረ በሁዋላ በንጹሃን ዜጎች ላይ እራሱ የሚዘገንን ግፍ ፈጽሞ ሲያበቃ- ወንጀሉን በቅንጅት መሪዎች: በነጻ ፐሬስ ጋዜጠኞችና በሙያ ማህበራት መሪዎች ላይ ማመካኘቱ ለመላው አለም የአደባባይ ሚስጥር ነበር:: በተለይ ጉዳዩ እራሱ ባቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን በይፋ ሲጋለጥ ነበር ወያኔ ማጠፊያው ያጠረው::

በሃገር ውስጥ የነበረው ስር የሰደደ የኢኮኖሚ: የፖለቲካና የማህበራዊ ኑሮ መናጋት ያስከተለው አለመረጋጋት – በአንድ በኩል: ስርአቱ የውጭ እርዳታ ጥገኛም በመሆኑ በምእራባውያን ይደረግ የነበረው ግፊት – በሌላ በኩል: – ከዚያ ሁሉ በላይ ደግሞ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የመለስ ዜናዊን የጥገኛ ስርአት እረፍት እንደነሱት በኢህአዴግ ውስጥ ያሉትም ይመሰክራሉ::

በምርጫ 97 ሃገሪቱን እንዲመሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ስለመርጣቸው ብቻ በሃገር ክህደት ወንጀል ተከሰው ቃሊቲ ሲማቅቁ የነበሩ የህዝብ እንድራሴዎች ጋዜጠኞችና የሲቬክ ማህበር መሪዎችን ከነበሩበት የግፍ እስር ለማስፈታት ሚና ሲጫወቱ ከነበሩት ውስጥ የፐሮፌሰር ኤፍሬም ይሳቅ ስም በስፋት ይነሳል:: ፐሮፌሰር ኤፍሬም ይሳቅ ታዋቂ ግለሰቦችን በማሰባሰብ: ከቤተ-መንግስት ቃሊቲ በመመላለስ በመጨረሻ እስረኞቹ እንዲፈቱ ጥረት አድርገዋል::

ፐሮፌሰር ኤፍሬም የሚመሩት የሽማግሌ ኮሚቴ ምንም እንኳን ጥረቱ ቢደነቅም በብዙዎች ሲተች ይሰማል:: ኮሚቴው ከሚደርስበት ትችት ዋናው: “ኮሚቴው አውቆትም ይሁን ሳያውቅ የኢህአዴግን እድሜ ለማራዘም የተቋቋመ: የስርአቱን ጥቅም የሚያስጠብቅ ስብስብ ነው::” የሚለው ነው:: ይህንን ትችት የሚሰነዝሩት ሃይሎች እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት ኮሚቴው የአቶ መለስ ስርአት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ችግሮችን ለማብረድ ሲሯሯጥ መታየቱ ነው::

በዚያ ለኢሃዴግ አስቸጋሪ በነበረበት ወቅት የቃሊቲ እስረኞች ፊርማቸውን እንዲያኖሩና ከእስር እንዲወጡ የሽማግሌው ኮሚቴ የገባቸው ቃል-ኪዳኖች (ቅድመ-ሁኔታዎች) ነበሩ:: ከነዚህም መካከል ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የፖለቲካ ውይይቱ እንደሚቀጥል ነበር:: ይህ አልሆነም::

እስረኞቹ ከቃሊቲ ከወጡ በሁዋላ የሽማግሌ ኮሚቴው በየመገናኛ ብዙሃኑ አቶ መለስን ከማመስገን ውጪ ችግሮቹ እንዲፈቱ ያደረጉት አንዳች ጥረት አልነበረም:: ይልቁንም የቅንጅት መሪዎችን በጋራ ሳይሆን በግል እየጠሩ የመክፋፈል ሚና ተጫውተዋል ተብሏል::

ኮሚቴው እውነተኛና ገለልተኛ ከሆነ ይህን ለምን እንዲሆን አላደረገም? ገዢው ፓርቲ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ይሆን? ታዲያ ይህንኑ ለምን ለህዝብ ይፋ አያደርጉትም?

የቅንጅት ሰም “ከሜዳው ውጭ” በሆነበት በአሁኑ ወቅት የወያኔ አይን ያለው በኦነግ ላይ ይመስላል:: ኦነግንም “ከሜዳው ውጭ” ለማደረግ፡፡ የኦነግ አመራር ለሁለት በተከፈለበት ወቅት የወያኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣውን መግላጭ ያስተውሏል::

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on October 5, 2008. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.