የፌዴሬሽኑ 30ኛ አመት ዝግጅትን እንዳየነው (ሙሉው የተቃውሞ ቪዲዮ አለን)

EMF – (ዝርዝር ዘገባ – በዳዊት ከበደ ወየሳ) እንደተለመደው አመታዊውን የስፖርት እና ባህላዊ ፌስቲቫል ለመከታተል ዲሲ ገብተን፤ ከዚያም ወደ ሜሪላንድ አቅንተናል። በየአመቱ የምናገኛቸውን የፌዴሬሽን ሰዎችና ሌሎች ጓደኞቻችንን “እንኳን ለ30ኛው አደረሳችሁ!” እየተባባለን ሰላምታ ተለዋወጥን። እሁን ጁን 30 ቀን፤ የመክፈቻው ዝግጅት በመሆኑ የመግቢያ ዋጋውን $20 ዶላር ከፍለን ወደ ውስጥ ዘለቅን። የስቴዲየሙን ዙሪያ የከበቡት የምግብ እና ደረቅ ነገር ሻጮች፤ በርካታ ናቸው። ከተለያዩ የአሜሪካ ክፍለ ግዛት እና ከኢትዮጵያ የመጡ፤ ንግዳቸውን የሚያስተዋውቁ፤ የበጎ አድራጎት የሚያደርጉ… ሁሉም ድንኳናቸውን ደንኩነው፤ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አድርገው የመክፈቻውን እለት ሞቅ ደመቅ አድርገውታል። (Video)

በሌላ በኩል የፌዴሬሽኑ ሰዎች ከድንኳን ድንኳን እየዞሩ፤ ቅሬታ ያላቸውን ቅሬታቸውን እየሰሙ ከአንዳንዶቹም ጋር እየተጨቃጨቁ እንደተለመደው፤ በግርግሩ ውስጥ ሌላ ግርግር ፈጥረዋል። የሚገርመው ነገር እኛ እዚያ በደረስንበት ወቅት አብዛኛው ነጋዴ የመግቢያ መታወቂያ ካርዱን ገና አላገኘም ነበር። ነጋዴዎቹ ብቻ ሳይሆኑ፤ በየአመቱ ይህንን ዝግጅት ለመዘገብ በስፍራው የሚገኙ ጋዜጠኞች የማለፊያ መታወቂያ ቀደም ብሎ ሊዘጋጅላቸው ሲገባ ምንም የተደረገ ነገር የለም። እኛን ጨምሮ የሌሎች ጋዜጠኞች ስም እና ፎቶ ከሳምንታት በፊት ለፌዴሬሽኑ ቢላክም፤ መታወቂያ የሚያዘጋጀው ሰው (አቶ ያሬድ) “ገና ዛሬ ነው ለኔ የተሰጠኝ” ብሎናል። ለነገሩ ጋዜጠኞች እየከፈልን መግባታችንን እንቀጥላለን። ቢያንስ ቢያንስ ግን… ፌዴሬሽኑ የዚህ መታወቂያ አሰጣጥ ጉዳይን እንዴት ማስተካከል አቃተው? ዘንድሮም በዚህ ረገድ ፈተናውን ያለፈ አይመስልም።

ነጋዴዎቹ አንዳንድ ቅሬታ እያሰሙ ነው (መቼም ነጋዴ ሁሌ እንዳስቸገረ ነው እንዳትሉን) ገና የመጀመሪያ ቀን በመሆኑ፤ እኛም “ቆይ እስኪ ተረጋጉ” ያልናቸው አሉ። እንዲህ እንዲህ እያልን ጉብኝታችንን ቀጠልን። አንዳንድ ጋዜጠኞች ልጆቻችንን አስከትለን ነው ስራችንን የምንሰራው። አማርኛው ቢጠፋባቸውም፤ ኢትዮጵያዊነት ያልጠፋቸው ልጆቻችን ከስር ከስራችን ኩስ ኩስ እያሉ ሁኔታውን በትግስት ይከታተላሉ። በተለይም ዛሬ የመክፍቻው ፕሮግራም ላይ ሌሎች የአካባቢው ልጆች መዝሙር እና ባህላዊ ዝግጅት ስለሚያደርጉ ያንን በጉጉት የሚጠባበቁ ብዙ ነበሩ።

በተያዘው ፕሮግራም መሰረት 7፡00 PM ላይ የመክፈቻው ዋና ፕሮግራም እንደሚጀመር ቢገለጽም፤ ምንም እንቅስቃሴ አላየንም። ጭራሹን “መብረቅ እና ቶርኔዶ ወደ ስቴዲየሙ እየመጣ ስለሆነ፤ ሜዳ ውስጥ ኳስ የሚጫወቱት እንዲወጡ፤ ተመልካቹም ከተጋላጭ ቦታ ተነስቶ ህንጻው ስር እንዲጠለል ተነገረ” ብዙዎቹ ተጠለሉ። ሌሎቹም ወጡ። እኛም ወደ ሆቴላችን ሄደን እንደገና ገባን።

ስንመለስ ግርግሩ ጨምሯል። ህዝቡ ቀደም ሲል ካየነው በአስር እጥፍ (ከዚያ በላይ ሳይሆን አይቀርም) ጨምሯል። ነጋዴዎቹም ምግብ መሸጥ ጀምረዋል። አንዳንዶቹ እጣን እያጫጫሱ፤ ቡና የሚያፈሉም ነበሩ። እኛም ቡና ቀምሰን፤ እንደገና ለስራ ተሰማራን። የመግቢያ መታወቂያ የሚሰጥበት ቦታ ላይ ረዥም ሰልፍ አየን። የዚህ ሰልፍ ነገር ማብቂያ ያለው አይመስልም። በመጪዎቹ ቀናት ደሞ ይብስበታል። የጋዜጠኛ መታወቂያ ባንይዝም፤ የፌዴሬሽኑ ሰዎች (እነ አቶ ዘውገ) “አረ ግቡ” ብለውን ወደ ስቴዲየሙ ውስጥ ዘለቅን። የአትላንታ ቡድን እየተጫወተ ነው። አሰልጣኛቸው ኤርሚያስ ነው። “ገባ በል። አረ አቀብለው” እያለ መመሪያ ይሰጣል። እነካቻ አብረውት አሉ። ጌቱ ከበደም ካቻምና የቡድኑ አሰልጣኝ ነበር። በርግጥ አሰልጣኝ ሆኖም ስላስቸገረ ዳኛው በቀይ ካርድ ከሜዳው እንዲወጣ አድርገውት ነበር። አሁን ከአዲስ አበባ መመለሱ ነው። ከአዲሱ አሰልጣኝ ከ ኤርሚያስ ጋር ሆኖ ቡድኑን ሲያበረታታ አየነው። “አንዳንዶቹን በቪዲዮም በፎቶም እያነሳን ለአንባቢዎች እናቀርባለ” ብለን እያሰብን ሳለ፤ ደግሞም ከአትላንታ ጋር የሚጫወተውን ቡድን እንኳን ጠይቀን መልስ ከማግኘታችን በፊት ሌላ ማስጠንቀቂያ በድጋሚ ተነገረ።

የመጀመሪያው መብረቅ እና ቶርኔዶ ከሄደ ከሶስት ሰአታት በኋላ እንደገና መጣ። “ተመልካቾቻችን መብረቅ እና ነጎድጓድ እንደገና እየመጣ ስለሆነ ጨዋታው ለሚቀጥለው 30 ወይም 45 ደቂቃ ይቋረጣል። ተጫዋቾችም ሜዳውን ለቃቹህ ወደ መልበሻ ክፍል እንድትሄዱ” ተባለ ና ዳኛው ፊሽካ ሳይነፋ ተቋረጠ። ተጫዋቾቹም ሄዱ፤ እኛም እንደገና ከሜዳው ወጣን። ከስቴዲየሙ ስንወጣ፤ “ዲሲ ላይ የሚደረገው የሌሎቹ ሰዎች ጨዋታስ እንዴት ሆኖ ይሆን?” እያልን ነበር። በርግጥ እዚያም ነጋዴዎቹ ተማረዋል። አንዲት ልጅ ገንዘብ ከፍላ ብትመዘገብም ድንኳን አልተሰጣትም ነበር። ከሌሎቹ ገና አልሰማንም። በርግጥ ቅድም አበበ በለውን አግኝተን፤ “ባዶ ነበር” ብሎናል። ‘ከነሱ ጋር ስለተጣላ ይሆናል’ ብለን ነገሩን በፈገግታ አልፈነዋል። ቢሆንም ግን ሌሎችም አበበ ያለን ደገሙልን። ጋዜጠኞች እንደመሆናችን መጠን በስፍራው ሄደን ካልዘገብን በቀር የስሚ ስሚ ወሬ ለአንባቢቻችን አናቀብም ብለን አለፍነው።

ይሄም ሆኖ የዲሲ ሰዎች ወሬ ማለቂያ የለውም። ሌላም ወሬ ሰማን። ይሄኛው ወሬ ለየት ያለ ስለሆነ ልናካፍላቹህ ወደድን። …እንደሰማነው ከሆነ፤ ሼኽ አላሙዲን እነዚያኞቹን ሰብስበው፤ “እኔ ገንዘቡ የተሰጠው ለአንድ ፌዴሬሽን መስሎኝ ነበር። ከመቼ ወዲህ ነው የተከፋፈላችሁት? ብትከፋፈሉስ በኔ ገንዘብ ነው እንዴ ህዝቡን ለሁለት የምትከፍሉት?” ብለው በቁጣ ተናግረዋቸዋል። ሲባል ሰምተናል፤ ገና አላረጋገጥንም። መቼም ሼኹ እንደዛ ብለው ከሆነ፤ መልካም ጅምር ነው… በሚል እንለፈው።

“ለምን ሄደን የነሱንም አናይም?” ብለን… ሁለት ጊዜ የቶርኔዶ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠው የሜሪላንድ ስቴዲየም መውጣት ጀመርን። የዲሲው ፊልም አንሺ ቴዲ በጨዋታ ትንሽ ያዘን። እናም የሆድ የሆዳችንን እያወራን ከስቴዲየሙ ልንወጣ ስንል፤ ወጥተንም ወደ ዲሲው ስቴዲየም ከመሄዳችን በፊት ሌላ ነገር አይናችንን ሳበው። ሁለት መኪኖች፤ የሼክ አላሙዲን ፎቶ ያለበትን ትራክ እየነዱ ሲመጡ አየን። ህዝቡ ወደዚያኛው እንዳይሄድ እና “Boycott” እንዲያደርግ የሚጠይቅ ባነር ነው። “አይ ዜና እዚሁ ተገኘሽ?” አልንና የዲሲውን ጉዞ አቆይተን የዚህን ነገር መጨረሻ መከታተል ጀመርን። መጀመሪያ… ትንሽ ሰዎች ነበሩ። ከዚያ ሌሎችም መጡ። በኋላም ላይ በዙ። እኛም ሁሉንም ነገር በቪዲዮ ቀረጽነው።
ከቀረጻው በኋላ “ቶርኔዶው እስኪያልፍ ወደ ሆቴላችን እንሂድ፤ በዚያውም ስልካችንን ቻርጅ እናድርግ” ብለን መኪናችንን አስነስተን ሄድን። ሆቴል ስንደርስ ደክሞን ኖሮ እራሳችንን ቻርጅ ለማድረግ ትንሽ እንቅልፍ (Nap ቢጤ) ወሰድን። ወደሜሪላንድ ስቴዲየም ተመልሰን የመክፈቻውን ፕሮግራም ለመስራት እቅድ ነበረን። 8፡00 PM አልፏል። ከዚህ በኋላ ወደኋላ መመለሱ ድካም ሆነብን። እናም 95 ሳውዝን ይዘን ወደ ዲሲ አቅጣጫ አመራን።

ዛሬም የጋዜጠኞች መታወቂያ የሚደርስልን አይመስልም። ከፍለን መግባታችን ሳይሆን፤ ተክፍተን መግባታችን አይቀርም። የኛም ዘገባ ከስፍራው ይቀጥላል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 1, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.