የግንቦት ሰባት ስብሰባ በዳላስ

በተክሌ (መስከረም 27/ 2002)  — መስከረም 25 መሆኑ ነው? እኛ ተናጋሪዎቹ፡ እኛ እንግዶቹ ወደ ውስጥ ስንገባ፡ የዳላስ ክራውን ፕላዛ ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከግማሽ በላይ ሞልቷል። ስብሰባው ከተጠራበት ሰዓት ሰላሳ ደቂቃ በላይ ዘግይተን መጀመር ግን አልፈለግንም። ዶ/ር ብርሀኑ መሀል ቁጭ አለ። አቶ ዘነበ ሀይለማሪያም ገነሜ በስተግራ፡ ልጅ ተክሌ ደግሞ በስተቀኝ ተቀመጠ። የመድረኩ መሪና ሰብሳቢው አቶ አበበ እንግዶቹን አስተዋወቀ። ስብሰባው ተጀመረ። አቶ ዘነበ ተናገረ መጀመሪያ። ከአ.አ.ዩ. ስድስት ኪሎ ግቢ እስከ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡ ከውጭ ጉዳይ እስከ የመን፡ ከየመን አሜሪካ እስኪደርስ ላለፉት ስድስት ሰባት አመታት ያለፈበትን የፖለቲካ ሰቆቃና ፈተና ተረከልን። በነገራችን ላይ ዘነበ ገነሜ ስድስት ኪሎ እያለን መግባባት አይኑረን እንጂ አንድ ላይ ነበርን። ዘነበ ገነሜ ራሱ ነው በተለምዶ ባባቱ ስም ሳይሆን፡ ዘነበ ሀይለማሪያም፡ ባያቱ ስም እንደሚጠራ ያወሳው፡ ዘነበ ገነሜ። ደግሞም ያያትን ስም ማንሳት መልካም ነው። በራሳችንና ባባታችን ስም ማንነታችን የተደበቀ ሰዎች ባያታችን ማንነታችን ይገለጣልና ለኛ ለአንድነት ሀይሎች የአማራ ስብስቦች ብቻ ሳንሆን የሌሎች ብሄሮች ተወላጆችም እንዳለንበት ያሳያል። ለዚህ ነው እኔም ባለፈው ሰሞን አባቴን ያሳደጉትን ሳይሆን አባቴን የወለዱትን፡ ያያቴን ስምና ደም የጻፍኩላችሁ።

ዘነበ ቁጥብ ነው። አፈ ጮሌ አይደለም። የዋህም ይመስላል። በቁጥብነትና በየዋህነት ግን መናገር ያለበትን ሁሉ ተናገረ። ጥያቄ ስለጠየቀ፡ የኢትዮጵያን ጥቅም ይጎዳል ብሎ ስለተናገረ፡ ስለባለሙያዎችና ካድሬዎች ስብጥር ስለጠየቀ፡ በብሄራቸው እንጂ በችሎታቸው ስላልተቀጠሩ ሰዎች ስለመረመረ “የአመለካከት ችግር ያለበት” እየተባለ የደረሰበትን መከራ አወሳን። ግን ለምንድነው የትግራይ ተወላጆች ለዚያውም በብቃታቸው ሳይሆን በካድሬነታቸው ወይም በታጋይነታቸው ብቻ በየኤምባሲው በብዛት የተሰገሰጉት? አንዱ ጥያቄ ነው። “አንተ ችግር አለበህ እንዴ በዚያ?” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሰዎች በችሎታቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው ሳይሆን፡ ጥቂት ባለሙያዎችን ከፊት አድርጎ የተቀረውን በሙሉ ግን በቀድሞ የህወሀት ወታደሮች የተሞላ መስሪያ ቤት መሆኑንና በተለይ በኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች በሚገኙ ኤምባሲዎች ውስጥ የሚሰራው ስራ ሁሉ እንዴት ኢትዮጵያን ይጠቅማል ሳይሆን እንዴት ለሕወሀት ስጋት የማይፈጥሩ ሁኔታዎችን በነዚያ አገራት ውስጥ መፍጠር ይቻላል በሚል ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናገረ። ጥቂት ጥያቄዎች ቀረቡለት፡ እነሱንም አስተናገደ። ምሳሌዎችም ሰጠ።

ከዚያ ልጅ ተክሌ ቀጠለ። እኔ ማለት ነች፡ ዘጋቢው። እኔ ጋዜጠኛው ብል ደግሞ፡ የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች፡ እነ ክንፉ ሊቀየሙኝ ነው። ስላለንበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ዳስሼ፡ ስለኤርትራ መንገድ (መቼም የኤርትራ መንገድ ምን ያህል እንደናፈቀኝ ታውቁታላችሁ) እንዲሁም ስለግንቦት 7 አስፈላጊነት፡ እንደገናም ደግሞ ስለ ኦሮሞና መሰል ብሄርተኞች እና አንድነት ሀይሎች፡ ከነሱ ጋር ያለንን ግንኙነትም እንዴት ብናደርግ መልካም እንደሆነ አስሼ፡ ኦው ሌላ የረሳሁት ነገር፡ “እንዴት ሕወሀት የማንንቀውና በቀላሉ የማይሸነፍ ሀይል” እንደሆነም ጭምር ተናግሬ ተቀመጥኩ። ዶ/ር ብርሀኑ ስለደርግና ኢህአዴግ፡ (ኢህአዴግ የሚባል ነገር የለም ሕወሀት ብሏል ገብሬ/ገብረመድህን አርአያ)፡ አገዛዝ፡ የኢህአዴግ፡ ማለቴ ሕወሀት አገዛዝ እንዴት ከደርግ የበሰ እንደሆነ፡ በፍርድቤት፡ በመከላከያ እንዲሁም በሌሎችም ዘርፍ፡ የሕወሀትን ከደርግ የተለየ አይን ያወጣ ዝርፊያና ቅጥፈት አትቶ አበቃ። ከዚያ ጥያቄና መልስ ሆነ። ሰዉ አስተያየት ሰጠ፡ ጥያቄም ጠየቀ። እኛም መለስን። አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ተደጋጋሚ ናቸው። ስለሰላማዊ ትግልና ምርጫ። እኔና ዶ/ር ብርሀኑ እንለያያለን በዚህ ላይ። ልዩነታችንን በሌላ ቀጣይ ጽሁፍ ላይ እገልጻለሁ። እስከዚያው ግን እነዚህ ሰዎች፡ “ጉዶች” ይላቸዋል ደ/ር ብርሀኑ፡ በምንም መልኩ ስልጣናቸውን ለመጠበቅ ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይሉና በሰላም ለመውረድ ያልተዘጋጁ መሆናቸውን አሰመረበት።

ስለግንቦት ሰባት ስልትና ስለኤርትራም ተጠየቀ፡ ዶ/ር ብርሀኑ። አብራራ። በጣም ግልጽ ነን ብለን የምናስብበት ጉዳይ በማናቸውም መንገድ ሕወሀትን እንታገላለን፡ እንነቅላለንም የሚለው ስልታችን ሆኖ ሳለ፡ ይሄ የስልት ጉዳይ ዘወትር በየስብሰባው ጥያቄ ሆኖ መነሳቱ ግርም እንደሚለው ገለጸ። በማናቸውም መንገድ፡ ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ፡ እንኩዋንስ ከኤርትራ ከጋኔንም ጋር ቢሆን፡ አብሮ ከመስራት ወደኋላ እንደማይል ተናገረ። በዚህን ግዜ እኛ የኤርትራ መንገድ የሚናፍቀን ሰዎች በደስታ ዘለልን። ግን፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የመረጠው ብቻ እንጂ ማንም ኢትዮጵያን ወክሎ መደራደር እንደማይችልና ግንቦት ሰባትም የህዝብ ውክልና ስለሌለው ኢትዮጵያን ወክሎ ከኤርትራም ይሁን ከሌሎች መንግስታት ጋር መነጋገርና መደራደርም እንደማይችል ተናገረ። ግን ኢትዮጵያን ወክሎ እንጂ እንደ ግንቦት ሰባት የሚያደርጉትን እያደረጉ እንደሆነ ተናግሯል። ስብሰባው ከ3፡30 እስከ 8፡30 ቀጠለ። አምስት ሰዓት ላይ መቀመጫ ወንበር አልነበረም። የተሰወሰኑ ሰዎችና የስብሰባው አስተባባሪዎች ቆመው ማዳመጥ ነበረባቸው። እጅግ በጣም የገረመኝ ነገር፡ ባለቤቱ በሷም ይሁን በልጆቿ ላይ ጉዳት ያላደረሰ መኪና ግጭት ደርሶባት፡ ተጠርቶ ከሄደው የስብሰባው ሊቀመንበር በስተቀር፡ የሆነ ቦታ ላይ መቆም ስለነበረበት በግድ ስብሰባው እስኪቆም ድረስ፡ ሰዉ ሁሉ በተመስጦና በንቃት ይከታተል ነበር። ይሄንን ስብሰባ ከመናፈቃቸው የተነሳ፡ ድክም ብሏቸው ከስራ መጥተው ሁሉ እስከመጨረሻው ስብሰባውን የተከታተሉ ሰዎችን አግኝቻለሁ። የተሳታፊው ሰዉ ስብጥር በእድሜ ረገድ የተለያየ ሲሆን፡ የሴቶች ተሳትፎ ግን አናሳ ነበር።

ከሁለት መቶ ሀምሳ ሰው ውስጥ ከአምስት ያልበለጡ ሴቶች ብቻ ነበሩበት። ስብሰባው መጀመሪያ ላይ፡ ለሰብአዊ መብት መከበርና ለዴሞክራሲ መምታት መስዋእትነት ለከፈሉና ለሚከፍሉ ሁሉ የህሊና ጸሎት ተደርጓል። በዚህ ውይይት ከመደሰቱ የተነሳ፡ አንድ በእለቱ ወይም በዚያው ሰሞን ልደቱን ያከብር የነበረ ወጣት፡ “በቃ የልደት ስጦታዬን አገኘሁ” ብሏል።

የረሳሁት ነገር፡ ስለቤተክርስቲያንና በየከተማዎቹ ስለሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰባት ሚናዎችምተነስቶ ነበር። ይሄን ጉዳይ እኔ እንድመልሰው እድል ተሰጥቶኝ፡ የማይክ ጥማቴ እስኪወጣልኝ ድረስ ሃሳብ ሰጥቼበታለሁ። በእለቱ ጠዋት በዳላስ ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ ተገኝቼ፡ የየትኛው ቅዱስ ወይም ጻድቅ እንደሆነ ያልጠየቅኩትና ያላወቅኩት በዓለ ንግስ ተሳትፌያለሁ። በግንቦት ሰባት ስብሰባና ከዶ/ር ብርሀኑ ጋር በነበረን ቆይታ ብደሰትም ግን፡ የዳላስ ቆይታዬ፡ በቤተክርስቲአንና በፓትሪያርክ ጉዳይ በአገር ልጅነትና በመሰል ጉዳዮች ላይ የነበረኝን ጭንቀትና ሀዘን አብሶብኝ ተመልሻለሁ። እንደውም በአሜሪካን አየርመንገድ ላይ ሆኜ ነገሮችን ሳሰላስል፡ ትግሉ ከእጃችን እያመለጠን ነው እንዴ የሚል ጥያቄ ወጥሮኝ ነው ሲያትል የደረስኩት። በሸዋና በጎንደር ሰዎች መካከል ስላለ ሽኩቻ ትግሉን እንዴት እየጎዳው እንደሆነ፡ የዚህ የማህበረ ቅዱሳንና የፓትሪያርክን ጉዳይ፡ የቤ/ክንን ሚናና ቀጣዩን አካሄዳችንን የተመለከተውን ዘገባዬን፡ በዳላሱ ስብሰባ ላይ ካቀረብኩት ወረቀት ጋር አያይዤ በዚሁ ሳምንት አቀርብላችኋለሁ። እስከዚያው ግን መልካም ሳምንት።

ፊታውራሪ ተክሌ ነኝ። በነገራችን ላይ እዚያ ዳላስ በቆየሁበት ወቅት ዳላሶች በቫንኩቨርና አካባቢው ላይ ፊታውራሪ አድርገው ሾመውናል። እኔ እንኩዋን ደጃዝማችነትን ነበር የተመኘሁት።

ከዳላስ መልስ፡ መስከረም 27/ 2002, ወይም October 7, 2009፡ ቫንኩቨር ካናዳ

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on October 7, 2009. Filed under NEWS. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.