የግንቦት ማስታወሻ – ከተስፋዬ ገብረአብ

Tesfaye Gebreab [Read in PDF]… አዲሱ ለገሰ ከጤንነቱ መበላሸት ሁኔታ ጋር ተደማምሮ ስልጣን ላይ መቆየት እንደማይፈልግ ማመልከት የጀመረው ከሚሊኒየሙ ዋዜማ ጀምሮ ነበር። ተፈራ ዋልዋ፣ “የታገልነው ለዚህ አልነበረም!” እና “መምራት አቅቶናል!” የተባሉ ሁለት ነጠላ ዘፈኖችን ውስጥ ውስጡን ማንጎራጎር መጀመሩን በምሰማበት መንገድ ሰምቻለሁ። … መለስ ዜናዊ፣ “ህላዌ ዮሴፍ ሆይ! አንተ አማራ ብቻ ነበርክ፣ አማራ ብቻ ሆነህም ትኖራለህ!! ስለሌላው አያገባህም!” ብሎት ሲያበቃ አረንጓዴዋን ቀንሶ በቀይና ቢጫ ቀለማት ያማረች ክራቫት አሰረለት። ከኢህዴን ላይ የተቀነሰችው አረንጓዴ ቀለም ሁመራ መሆኗም በሹክሹክታ ተናፈሰ።…

የግንቦት ማስታወሻ 

ከተስፋዬ ገብረአብ 
 

      እነሆ! ዛሬ ቅዳሜ ነው።  

      እለቱም ግንቦት 9፣ 2009።  

      ትናንት ደግሞ ግንቦት 8 ነበር። በአበሻ የዘመን አቆጣጠር ልክ የዛሬ ሃያ አመት ግድም “ጥቂት ጄኔራሎች” ኰሎኔል መንግስቱ ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገው ነበር። ሳይሳካላቸው በመክሸፉ ዛሬ በህይወት የሉም። ማንኛውም አጥንት – አስከሬን ሆነዋል። አምላክ የጄኔራሎቹን ነፍስ ይማር። እኒያ ሰዎች ከነሙሉ ችግራቸው ከኰሎኔል መንግስቱ የተሻሉ ዜጎች ነበሩ ብዬ አምናለሁ።  

      ቀደም ሲል ደግሞ ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ ጃንሆይን ለማስወገድ በመሞከራቸው የዚያ ዘመን ወጣት ትውልድ ጃንሆይን መንካትና መድፈር እንደሚቻል ትምህርት ማግኘት መቻሉ ይታመናል። ሰሞኑን ደግሞ ታሪክ ራሱን ለመድገም ሞከረ። የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ርእሰ አጀንዳ ሆኖ ሲያነጋግረን ሰነበተ።  

      እኔም ታዲያ ምንም ስንኳ የፓለቲካ ተንታኝ ባልሆንም፣ እንደ ጋዜጠኛነቴ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየቴን በጨረፍታ ለማኖር ፈቅጄያለሁ። ለነገሩ ይቺን “ብጫቂ ወረቀት” የመጫር አሳብ የመጣው ከኔው አልነበረም። በፀጥታ ተቀምጬ፣ “የደራሲው ማስታወሻ” የሚል ስም የሰጠሁትን ቀጣይ መፅሃፌን እየፃፍኩ ሳለ የethioforum.org ዋና አዘጋጅ ክንፉ አሰፋ መስመር ላይ አገኘኝና፣ 

       “የሰሞኑ ግርግር ላይ አስተያየትህን ለምን አትፅፍም?” ሲል ጠየቀኝ።  

* * *

      የሰሞኑን የመፈንቅለ መንግስት ግርግር ጉዳይ ከማንሳቴ በፊት ግን በዚህ ወቅት የማንም የፖለቲካ ድርጅት አባል አለመሆኔን ከወዲሁ መግለፅ ግዴታ ሆኖ አጊንቸዋለሁ። ቀደም ሲል የወያኔ አባል ለመሆን የበቃሁትም ባልጠበቅሁት ሁኔታ ከተራራ ወደ ሸለቆ እንደ ኳስ እየተጠለዝኩ መሆኑን በ“ጋዜጠኛው ማስታወሻ” አውግቼያችሁዋለሁና እሱን እዚህ አልደግመውም። ይህን ርእሰ ጉዳይ ማንሳት ያስፈለገበት ምክንያትም በቅርቡ ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ እየታማሁ በመሆኑ ነው።  

      በመሰረቱ በግንቦት 7 አባልነት መታማት የሚያኮራ ነው።

      የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የመግባት ሃሳብ ቢኖረኝ ኖሮ ግንቦት 7 ከአማራጮቼ አንዱ በሆነ ነበር። ቅሬታዬን መግለፅ የፈለግሁትም የአብርሃ በላይ ድረገፅ አትሞት የነበረው አንድ ፅሁፍ ግንቦት 7ን ለማጥቃት ሆን ተብሎ በወያኔ ካድሬዎች የተፃፈ ሊሆን ይችላል ብዬ በመገመቴ ነበር። “የአድአው ጥቁር አፈር” በሚል ርእስ ኢትዮሚዲያ ድረገፅ ላይ የታተመው ፅሁፍ ከኔ በላይ ግንቦት7ን የሚያጠቃ ሆኖ ነበር ያገኘሁት።  

      በዚያን ሰሞን የፀሃፊውን ማንነት ለማወቅ ብዙ ጥረት አድርጌ ነበር። ፍንጭ የሚሰጠኝ ግን ጠፋ። ‘ያያ አባ ቦር’ በሚል የብእር ስም ግንቦት 7ን ከኔ ጋር ደርቦ በቃላት መድፍ ሲደበድበኝ የከረመው ፀሃፊ ለካስ የሩቅ ወዳጄ ኦቦ በፈቃዱ ሞረዳ ኖሮአል።  

      በፈቃዱ ሞረዳ በፃፍው መጣጥፍ እኔን ‘ወኔ ቢስ፣ፈሪ!’ ብሎ የቻለውን ያህል በሚያጥላሉ ቃላት ሲገልፅ፣ ራሱን ደግሞ ‘የግንባር ስጋ’ ወይም ‘ጀግና’ ‘እውነተኛ ጋዜጠኛ’ ሲል ገልፆአል። እዚህ ላይ ማንበቤን በማቆም ጥቂት ተክዤ ቆየሁ። በፈቃዱ ስለራሱ ጀግናነት በአደባባይ እስኪናገር ድረስ ርግጠኛ መሆን ከቻለ በውነቱ በጣም እድለኛ ሰው ሆኖ ይሰማኛል። ጀግና መሆን መልካም ነው። ሰዎች በምርጫቸው ፈሪ ሆነው አያውቁም። ለነገሩ የጀግንነትና የፈሪነት መለኪያዎች ከቶ ምን ይሆኑ? ስንት አይነት ጀግንነቶችስ አሉ? እና በፍቃዱ ሞረዳ ራሱን ጀግና ብሎ እኔን ወደ ፈሪዎች ቀበሌ የላከኝ በየትኞቹ መለኪያዎች ይሆን?       

      በፍቃዱ 1981 ጀምሮ እንደሚያውቀኝም ፅፎአል።

      እውነቱን ነው።

      ግጥሞቹን በጣም ስለምወዳቸው ራሴ ነኝ ፈልጌ የተዋወቅሁት። እኔ ከዚያ በፊት በስነግጥሞቹ አውቀው ነበር። እሱም እንደኔው ሃረር ላይ ያቺኑ የፉገራ ፖለቲካ ተምሮ ነበርና እኛ ስንመረቅ በፍቃዱ የኢሰፓ ጋዜጠኛና ካድሬ ሆኖ መጣ። አዲሳባን እንጂ ጦርነትን አያውቃትም። ሃረር ላይ ግማሽ ሰአት ያህል ስነፅሁፍ ነክ ወሬ ተጨዋውተን ተለያየን። በዚሁ አበቃ። በፍቃዱ ሞረዳ ወደ አዲሳባ፣ እኔ ወደ አሰቃቂው ጦርነት ተለያየን። መልአከ ሞት ደግሞ ሬሳ በዝቶበት ነው መሰለኝ፣ 

      አንተን ለጊዜው አንፈልግህምብሎ ሳይወስደኝ ቀረ። 

      ደርግ ወድቆ አዲሳባ ስንገባ ከበፈቃዱ ጋር በድጋሚ ተገናኘን። አሁን ደግሞ ሁለታችንም ስደተኞች ነን። ከስደቱ በሁዋላ ወያኔን በጋራ እንታገለዋለን ብዬ ስጠብቅ በፈቃዱ ሞረዳ ፊቱን ወደኔ አዙሮ በባዙቃ ይደበድበኝ ያዘ። አብርሃ በላይም፣  ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የበፈቃዱ ሞረዳን ፅሁፍ ከድረገፁ ነቅሎ ጣለው። እንዳልኳችሁ ግን የግንቦት 7 አምባሳደር” ሆኜ አስመራ ልጓዝ እንደተዘጋጀሁ የሚገልፀውን የፈጠራ ፅሁፍ የፃፈው በፈቃዱ ሞረዳ ሊሆን ይችላል ብዬ አልገመትኩም ነበር።  

       ያን ሰሞን ታዲያ ለቀጣዩ መፅሃፌ ከበፈቃዱ ሞረዳ ውብ ግጥሞች፣ “ጀጎል” የተባለችውን ልጠቀምባት በማሰብ፣ “ጀጎል’ የተባለች ግጥምህን ላክልኝ” የሚል ኢሜይል ፃፍኩለት። በጀጎል ፈንታ በኔ ላይ ያለውን ጥላቻ የሚተርከውን ፅሁፍ በፒዲፍ አስሮ ላከልኝ። “የአደአው ጥቁር አፈር” መድፈኛ እሱራሱ እንደሆነም ነገረኝ።  

      በእውነቱ ወያኔዎች በዚህ ነው የሚበልጡን። የራሳቸውን ሰው በመደብደብ ሃይል አያባክኑም። በፍቃዱ ሞረዳ እኔን በመደብደብ ወያኔን ብቻ ነው ማስደሰት የቻለው። በርግጥ በፍቃዱ ወደ ኦነግ ስለ መግባቱ ያልተረጋገጠ ጭምጭምታ ወሬ ሰምቻለሁ። ወሬው እውነት ከሆነ ለገጣሚው ያያ አባ ቦር መልካም ትግል እመኝለታለሁ… 

      በዚያን እለት ምሽት ወደ ፕሪቶሪያ ደቡብ ነዳሁ። የከተማችን ደቡባዊ አቅጣጫ ኮረብታማ ነው። ገና ሙሉ በሙሉ አልመሸም ነበር። ባቡሮች የጉልበት ሰራተኞችን እየጫኑ፣ ፕሪቶሪያን እያቋጡ፣ በውበቱ ከቶውንም ተወዳዳሪ ወደሌለው ወደ ኩዋዙሉ ናታል ከፍለሃገር ይከንፋሉ። ኮረብቶቹ በጣም ውብ ሲሆኑ ጃኪቻን የተባለው የፊልም አክተር “…” የተባለውን ፊልም ለመስራት እኒያን ኮረብቶች ተጠቅሞባቸዋል። እዚያ ኮረብታ ላይ ወጣሁና ቁጭ አልሁ። ቁጭ አልኩ ብቻዬን።  

      በወርቃማው ዘመን ስለ ተፈጠሩት የሩስያ ደራስያን አሰብኩና ቅናት ሰቅዞ ያዘኝ። በአንድ ወቅት ሃያስያን ወደ ቶልስቶይ ቀርበው ስለ ቼኾቭ ጠይቀውት ነበር።

      ሳያመነታ እንዲህ መለሰ፣

      “ወደድኩም ጠላሁም አንቶን ቼኾቭ እንደሚበልጠኝ አመኜያልሁ!!”  

* * * 

      የሆነው ሆኖ በፈቃዱ ሞረዳ ስለ ግንቦት 7 የገመተውን እንርሳውና እንደ አንድ የስነፅሁፍ ሰው በሰሞኑ አጀንዳ ላይ የግል እይታዬን ላውጋችሁ….. 

      ከትናንት በስቲያ ግንቦት 7 ነበር እለቱ።

      መለስና በረከት የኰሎኔል መንግስቱ ርኩስ መንፈስ ምን ሹክ እንዳላቸው ባይታወቅም፣ እንደ መርዶ ነጋሪ በጠዋት ተነስተው፣ “ግንቦት 7 ወንበራችንን ሊሰርቅ ሲል ለጥቂት ያዝነው!!” ሲሉ በጩኸት ነገሩን።  

      አያያዘናም በረከት፣

      “ለግንቦት 20 ሲያስቡን፣ ግንቦት 7 ላይ አስቀረናቸው” አለን።

    በርግጥ በረከት እንደዚህ ሲል አልሰማሁትም። አይልም ግን አይባልም።

     

      እንደዋዛ ከጀመርኩት ወግ ወዲያ ማዶ ታዲያ አያሌ መራራ አጀንዳዎች አሉ። በአስር ሺዎች የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ እስረኞች በየማጎሪያው የከፋውን ስቃይ እየተቀበሉ ይገኛሉ። ቴዲ አፍሮ አንዱ ነው። ብርቱካን ሚደቅሳ – ሁለት። ገመቹ አባቢያ – ሶስት። ገመቹን የሚያውቀው አለ? ምናልባት የምናውቀው ጥቂቶች ሳንሆን አንቀርም። የኦነግ ታጋይ ነበር። ወያኔ አስሮታል። ከናይሮቢ አፍነው ወሰዱትና አሁን የት እንዳለ አይታወቅም።  

      የስንቱ ስም ተዘርዝሮ ይቻላል?  

      በርግጥ የሹርሹራ ጓደኛ ስለሆነው ገመቹ በቀጣዩ መፅሃፌ በስፋት አወጋችሁዋለሁ። “ሹርሹራ ደግሞ ማነው?” ትሉ ይሆናል። ለማንኛውም ሹርሹራ በህይወት የለም። የወለጋ ምድር ላይ በክብር አርፎአል። እንግዲህ በየማጎሪያው ከተወረወሩት ወገኖቻችን መካከል እነ ጄኔራል ተፈራ ማሞ የዚህ ማስታወሻ መነሻና ማእከል ናቸውና ወደዚያው ልዝለቅ…. 

* * *

      ወያኔ አብላጫ ቁጥር ባላቸው ብሄሮች መካከል እንዴት አክሮባት እየሰራ መዝለቅ እንዳለበት የቤት ስራውን የሰራው ደርግ ከመውደቁ በፊት እንጂ ትናንት አልነበረም። ቀድሞውንም በተዳከመ የግንኙነት ማእቀፍ ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጣራው ተደርምሶበት፣ የሚያገናኙት የጋራ የስሜት ክሮች እየተበጣጠሱ አንዱ ለሌላው ጠላት በሚሆኑበት ጎዳና ላይ ሲደነቃቀፍ ዘመናት ባጅተዋል።

 

      ጄኔራል ከማል ገልቹ ከ150 በላይ የታጠቁ የሰራዊት አባላትን አስከትሎ  የኤርትራን ድንበር ሲያቋርጥ “የወያኔ ሰራዊት ፍፃሜ ተቃረበ!” ተብሎ ነበር። የጄኔራሉን መኮብለል ተከትሎ በረከት ሰምኦን በሰጠው ቃለምልልስ   “ተገላገልን!” ሲል ነበር የገለፀው። ወያኔ ራሱን የሚያጠናክርበት በር ተከፈተለት። ከ20 ሺህ ያላነሱ ኦሮሞ ወታደሮች ከየጦር ክፍሉ ተመንጥረው ትግራይ ውስጥ ታሰሩ። በመቶዎች የሚገመቱ ኦሮሞ መኮንኖች ደግሞ ደሴ አካባቢ ወደሚገኝ ወታደራዊ እስር ቤት ተላኩ። መኮንኖቹን የተረከበቻቸው የእስርቤቱ ሃላፊ፣ ኮሎኔል ብራ የተባለች ነባር የህወሃት አባል ስትሆን፣ የአሉላ ክፍለጦር ኮሚሳር ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ በጨካኝነቷ ትታወቃለች። ኮሎኔል ብራ የሃገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖችን እርቃናቸውን አስቁማ  ታስገርፋለች። እንደ ወይራ በጠነከረ የጎማ ዱላ ተደብድበው፣ፓራላይዝድ ሆነው ዛሬም ድረስ ማገገሚያ ጣቢያ የተቆለፈባቸው አንድ ሁለት መኮንኖችን አውቃለሁ።  

      መኮንኖቹ በግርፊያው ወቅት የተጠየቁት አንድ አጭር ጥያቄ ብቻ ነበር፣ 

      “ከኦሮሞ ጄኔራሎች መካከል ከኦነግ ጋር ግንኙነት ያለው ማነው?” 

      ድብደባው ሲበዛባችው የአባዱላን ስም ጠሩ።

      ኮሎኔል ብራ ወቀጣው እንዲቆም አዘዘችና ያገኘችውን “ምርጥ የምርመራ ውጤት” ለአለቆቿ አቀረበች። አለቆቿ ግን አባዱላ ዝንተአለም እንደማይከዳ ያውቁ ነበር።

      ጄኔራል ከማል ሰራዊቱ ውስጥ በህቡእ ካደራጀው የኦነግ ደጋፊዎች መካከል ሲሶውን እንኳ ይዞ አለመውጣቱን ገልዖ ነበር። ይህ ለወያኔ እልል በቅምጤ ሆነለት። በዚያ ሰበብ ምንጠራውን ለማካሄድ በቂ ምክንያት አገኙ። ከጠረጋው በሁዋላ በጎደለ ለመሙላት በተደረገው የስልጣን ሽግሽግ ወያኔ ከአማራ የሰራዊቱ አባላት ድጋፍ ለማግኘት ጥቂት ሞካክሮአል። በዚያን ጊዜ አፍንጫ ሲመታ አይን ሳያለቀስ ቀረ። 

      ይህን ዘዴ ወያኔ ደጋግሞ ይጠቀምበታል።

      ቅንጅት አዲሳባ ላይ በምርጫ ሲያሸንፍ በአንድ አዳር ፊንፊኔ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ሆና አደረች። በዚሁ ሰሞንም ኢህአዴግ አዳማ ከተማ ላይ ባዘጋጀው አንድ ግብዣ ላይ የኢህአዴግ አባላት በትግርኛና በኦሮምኛ ብቻ ጨፈሩ። አባዱላም የሚያምነው ታቦት ስላልነበረው በጠመንጃ ስም እየማለ ታሪካዊ ንግግር አደረገ። ግብዣው ላይ የነበሩ እንደሚተርኩት አባዱላ እንባው ባይኑ ቸፈፍ ብሎ፣  

      “ፊንፊኔ ወደ እናት ክልሏ እንደምትመለስ ህልም ነበረኝ!!” ሲል እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ ድምፁን ቢለቀው ዝቋላና ካካ ተራሮች ደግሞ ያንን በገደል ማሚቷቸው በኩል አገማሸሩት።  

      አባዱላ እንባውና ህልሙን አጣጥሞ ሳያበቃ መለስ ዜናዊ ጠርቶ፣  

      “ህልምህን ህፃናት የማይደርሱበት ቦታ አስቀምጠው። ለጊዜው ግን አዳማ ትቆያላችሁ” አለው።

      

      ወያኔ ሁለቱ አብላጫ ቁጥር ያላቸውን ብሄሮች በተመሳሳይ ጊዜ አጥቅቷቸው አያውቅም። አንዱን ሲያጠቃ የሌላው ድጋፍ ስለሚያስፈልገው የፈረቃ ቁማር ይቆምራል። የህወሃት አባላትም ምንጊዜም ፍርድ ሰጪ ዳኛ ሆነው መካከል ላይ ይገኛሉ። የኮሜዲያን ክበበው ገዳ “ገብረመድህን” የተባለው ገፀባህርይ ለዚህ አባባሌ እንደ መልካም ማሳያ ሊጠቀስ የሚችል ነው። 

      የሰሞኑ፣ “የመፈንቅለ መንግስት ድራማ” ለአየር ከበቃ በሁዋላ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በቃለመጠይቁ ሲገልፅ እንደነበረው ከጄኔራል ከማል ኩብለላ በሁዋላ በሰራዊቱ ውስጥ በተካሄደው ጠረጋ የአገዛዙ ስርአት ዘረኛ አካሄድ ላይ ጥያቄ ያሳደሩ ምርጥ የሰራዊቱ አባላት በአብዛኛው እየታፈኑ ተሰውረዋል።  

      ወያኔን እንቅልፍ የሚከለክሉ የሰራዊቱ አባላት አንድ ባንድ እየተመነጠሩ ጥጋቸውን ይዘዋል። ሃይሌ ጥላሁን ሊጠቀሱ ከሚችሉት መካከል ነው። በሰሞኑ “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” ጣት ከሾለባቸው መካከልም ሃይሌ ዋናው መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ያወጋሉ። ዳሩ ግን ወያኔ በዚህ ጊዜ በቀጥታ ጄኔራል ሃይሌን ሊነካው እንደማይፈልግ የምናውቅ ከጥቂት በላይ ነን። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጄኔራል ሃይሌን የተመለከቱ ጥቂት አስገራሚ ወጎች ነበሩ። በዚያን ወቅት የህወሃት ጦር ኮማንደሮች በከባድ መሳሪያ ግዢ ሰበብ በሚሊዮናት ዶላር ኮሚሽን እየበሉ የመሆናቸው ወሬ አየሩን በክሎት ነበር። ጄኔራል ሃይሌ ደግሞ እዚሁ ግዢ አካባቢ የተመደበ ባለስልጣን ነበር። እና ድምፁን ከፍ አድርጎ በስብሰባ ላይ እንዲህ ሲል ተናገረ፣ 

      “እኔ እዚህ ተቀመጬ የሃገሪቱን ገንዘብ አትበሉም! ስትዘርፉ እያየሁ ዝም አልላችሁም!” 

      ጄኔራል ሃይሌ ከነታምራትና በረከት ጋር ኢህዴንን ከመሰረቱት ነባር ታጋዮች አንዱ ሲሆን፣ አዲስአበባ እስክትያዝም በኢህአዴግ ደረጃ ትግሉን የመራ ሰው ነው። በስብሰባ ላይ የህወሃት ኮማንደሮችን እንዲያ ከተናገረ በሁዋላ ግን የሃይሌ ጉዳይ ያለቀለት ሆነ። “ጡረታ!” አሉና አገለሉት። ጉዳዩ ተራ የእድሜና የአስተዳደር  ጉዳይ ቢሆን ኖሮ፣ ሳሞራ የኑስ ቀድሞት ጡረታ ሊወጣ በተገባ ነበር። እነደሰማሁት ጡረታ ከወጣም በሁዋላ ሃይሌ አላረፈም። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ፣

       “እንተዋወቃለን!” እያለ ይናገራል አሉ።

      እነ ሳሞራም “የትም አይደርስ” በሚል ችላ ብለውት ሰንብተዋል።  

      እንግዲህ በዚህ መረጃ ዙሪያ አንዳንድ ፍንጮችን ማሽተት የሚገድ አይሆንም። ዛሬ በመፈንቅለ መንግስት ወይም በሽብርተኛነት ስም ተይዘው የታሰሩት  ከፍተኛና ጄኔራል መኮንኖች ከሃይሌ ጥላሁን ጋር ያላቸውን የጠበቀ ግንኙነት ወያኔም ሆነ የቅርብ የብአዴን አባላት አሳምረው ያውቁታል። 

      የመፈንቅለ መንግስቱን ወሬ እንደሰማሁ የሚፃፉትን ዜናዎችና ዜና ትንታኔዎች ለማንበብ ሞክሬ ነበር። ወያኔ ጉዳዩን ከመፈንቅለ መንግስት ወደ  ሽብርተኛነት ሊለውጠው ለምን እንደፈለገ ገልፅ ነበር። “ሽብርተኛነት ክስ ለመመስረት የሚያመች ሲሆን፣ ባንፃሩ “መፈንቅለ መንግስት” የሚለው ግንቦት 7 የተባለውን ድርጅት ዝና ይበልጥ ከፍ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት አሳድሮባቸዋል። “ከሰራዊቱ እየተመነጠሩ ያሉት አማራ መኮንኖች የግንቦት 7 አባላት ናቸው ወይስ አይደሉም?” የሚለው ጥያቄም አከራካሪ አይደለም። ቢሆኑም ብርሃኑና አንዳርጋቸው፣ “አባላቶቻችን ናቸው!” ብለው ይነግሩን ዘንድ አንጠብቅም። ይህ ለታሪክ የሚቆይ ይሆናል። እንደምንሰማው ግን ከግንቦት 7 ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያልመሰረቱ፣ በአላማው ዙሪያ በራስ አነሳሽነት የተደራጁ ወጣቶች የክፍለ ሃገር ከተሞችን እያጥለቀለቁ ይገኛሉ። በየአካባቢው “ወንድም ጋሻ!” የመሆን የአርበኛነት ስሜት ተቀስቅሷል። ብርቱካን ሚደቅሳ እንደገለፀችው፣ አንድ አላማ በህዝብ ተቀባይነት ካገኘ የሚያደራጀውን አካል ሳይጠብቅ እንደ መንፈስ ይሰራጫል። ቀደም ሲል ለቅንጅት አላማዎች ህይወታቸውን የሰጡት አብዛኞቹ ወጣቶች በአባልነት የተመዘገቡ እንዳልነበሩ እናስታውሳለን። የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ሰለባ የሆነውን ሰፊ ህዝብ እንተወውና በዚህ ቀውጢ ወቅት ተፈራ ዋልዋ ራሱ የግንቦት 7 ደጋፊ ሆኖ ቢገኝ አይደንቀኝም።  

      ከመነሻው ብአዴኖች ውስጣቸው ጥሩ አለመሆኑን የውስጥ መረጃዎች አሉኝ። ከኢህአዴግ አራት አባል ድርጅቶች መካከል ክፉኛ ሞራሉ ተነክቶ በቀውስ ላይ የሚገኘው ብአዴን ነው።

      ኦህዴድን በቀላል ቋንቋ ላስቀምጥላችሁ!

      አመራሩ ንፁህ ወያኔ ሲሆን፣ አባላቶቹ ደግሞ በአብዛኛው የስራ እድል ለማግኘት ድርጅቱን የተቀላቀሉ በአመለካከት ወደ ኦነግ የሚቀርቡ ናቸው።

      “ደቡብ ህዝቦች” በሚል ስም አባይ ፀሃዬ ያቋቋመው ድርጅት “አለ ይባላል በሳይንስ ግን አልተረጋገጠም” እየተባለ የሚቀለድበት፣ ዶክተር ካሱ ይላላ እንደፈለገ የሚያንገላታው ከሞቱት በላይ ያለ እቁብተኛ ነው።

      

      ወደ ብአዴን ስንመጣ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ወድቀዋል። መለስ ዜናዊ እንደሚለውም ቀዩን የፈንጂ መስመር ረግጠዋል።  

      አመራሩን በጨረፍታ ላስጎብኛችሁ… 

      አዲሱ ለገሰ ከጤንነቱ መበላሸት ሁኔታ ጋር ተደማምሮ ስልጣን ላይ መቆየት እንደማይፈልግ ማመልከት የጀመረው ከሚሊኒየሙ ዋዜማ ጀምሮ ነበር። ተፈራ ዋልዋ፣ “የታገልነው ለዚህ አልነበረም!” እና “መምራት አቅቶናል!” የተባሉ ሁለት ነጠላ ዘፈኖችን ውስጥ ውስጡን ማንጎራጎር መጀመሩን በምሰማበት መንገድ ሰምቻለሁ። ህላዌ ዮሴፍ ቀድሞውንም “ከኢህአፓ መንፈስ አልተላቀቁም!” እየተባሉ ከሚታወቁት አንዱ ነበር። ህላዌ “ኢትዮጵያዊነት!” የሚል መንፈሳቸው ጠንካራ ከነበሩ የቀድሞ የኢህአፓ ትንታጎች አንዱ ነበር። የሽግግር መንግስቱ ስራ ከጀመረ በሁዋላ መለስ ዜናዊ፣

      “ህላዌ ዮሴፍ ሆይ! አንተ አማራ ብቻ ነበርክ፣ አማራ ብቻ ሆነህም ትኖራለህ!! ስለሌላው አያገባህም!” ብሎት ሲያበቃ አረንጓዴዋን ቀንሶ በቀይና ቢጫ ቀለማት ያማረች ክራቫት አሰረለት። ከኢህዴን ላይ የተቀነሰችው አረንጓዴ ቀለም ሁመራ መሆኗም በሹክሹክታ ተናፈሰ። ጄኔራል ሃይሌ ጥላሁን ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ለይቶለታል። መኮንኖች ክበብ ብቅ ሲል፣ “እነዚህ የቀን ሌቦች፣ ተጫወቱብን!” ማለቱን ቀጥሎአል።  

      ከምርጫ 97 አንድ ወር ቀደም ብሎ መኮንኖች ክበብ ላይ በተደረገ አንድ ግብዣ ላይ ስብሃት ነጋ፣

      “ነፍጠኛው ወደ ስልጣን ይመጣል ብሎ የሚያልም ካለ የዋህ ነው!” ብሎ ሲናገር ህላዌ ዮሴፍ የሚጠጣው ትን ብሎት ወደ መፀዳጃ ቤት መሄዱ ተሰምቶአል። 

       ብአዴን ማለት እንግዲህ እነዚሁ ናችው። ያልተጠቀሱ ቢኖሩ ታደሰ ጥንቅሹና በረከት ስምኦን ናችው። ታደሰ ብአዴን ውስጥ የህወሃት ትክል መሆኑ ነው የሚነገርለት። በረከት ያው በረከት ነው። በወያኔ ዘረኛ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ የወገኖቹን የስቃይ ጊዜ ከሚያራዝም፣ አንዴ ጎንደር ሌላ ጊዜ ቡግና ከሚንከራተት፣ “አማራ ነኝ!” እያለ በምድረበዳ ከሚጮህ፣ የጎንደር ልጅነቱን አክብሮ፣ በኢትዮጵያዊነቱ ቢፀና እንዴት ባማረበት? 

      የሆነው ሆኖ ከመነሻው ብአዴኖች ውስጣቸው ጥሩ አለመሆኑን ገልጫለሁ። ከአባላቶቻቸውና ከህዝቡ የሚመጣውን ግፊት ከቶውንም ሊቋቋሙት ተቸግረዋል። ብአዴኖች በህወሃት ላይ የቆየ ቅሬታ እንዳላቸውም “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ላይ መግለፄ አይዘነጋም። ብርሃኑ ነጋ ጠቁሞት እንዳለፈውም ሰራዊቱ ውስጥ ቁጣ አለ። የሰሞነኛው ግርግር ከግንቦት 7 ባሻገር የብአዴን ውስጣዊ ሁኔታ ላይ እንዳተኩር ያደረገኝም ብአዴን የወያኔን ዘረኛ ፖሊሲ እያስፈፀመ መቀጠል ከማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ይበልጥ ግልፅ እየሆነ በመምጣቱ ነው። ከበረከትና ከታደሰ ጥንቅሹ ባሻገር ያሉት የብአዴን የአመራር አባላት የጄኔራል ሃይሌ ጥላሁንን ቁጣ ቢጋሩ አይደንቀኝም። 

      “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” የተባለውን መፅሃፍ በረከትና ተፈራ ዋልዋ እነዳነበቡት ሰምቻለሁ። በረከት ጠረጴዛ እየደበደበ፣ “ውሸታም!! የውሸት ክምር!!” አለ ተባለ። ተፈራ ግን፣ “የሚያውቀውን ፅፎአል” ማለቱን ሰማሁ። እኔን የሳበኝ ሁለቱ የጥንት ጓደኛሞች የሁለት አለም ሰው መሆን የመጀመራቸው ፍንጭ ነው።

      ተፈራ አይኑን መግለጥ ጀምሮ ይሆን?

      በርግጥም ሚስቱን እስከ ማሰር ሊደፍሩት የበቁበትን ምክንያት እንደ ተራ ስህተት የሚታይ ሊሆን አይችልም። ተፈራና አዲሱ ያሻውን ያህል የስልጣን ጥመኞች ቢሆኑም፣ የመከላከያ አባላቶቻቸውና የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸው እንደ አይጥ እየተለቀሙ ወደ ኮሎኔል ብራ ሲላኩ ድርጊቱን በደስታ ሊያስተናገዱት ከቶ አይችሉም። ለዘመናት ውስጥ ውስጡን ሲበላላ የባጀው የብአዴንና የህወሃት ሽኩቻ ካለፉት ጊዜያት በላቀ ደረጃ ወደ ግጭት አምርቶአል።  

      ህወሃት ብአዴንን ለማዳከም ይህን ጊዜ ለምን እንደመረጠ መረዳትም ከባድ አይደለም።

      ምርጫ 2010 እየቀረበ ነው።

      የማጭበርበሪያ ሜዳው ከወዲሁ መደልደል እንዳለበት ግልፅ ነው። “ኢትዮጵያዊነት” የሚል ባንዲራ የሚያስቀድሙ ሃይሎችና የትጥቅ ትግል ያወጁ፣ ኦነግ፣አርበኞች፣የኦጋዴን ነፃ አውጪ የመሳሰሉ አማፅያን “የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች!” ተብለው ተፈርጀዋል። ወያኔ “የግንቦት 7” እና “የአንድነት” ፓርቲዎችን ሁለትነት አለማመኑም ግልፅ ነው። በቀጣዩ ምርጫ ወያኔ እንደለመደው ሊያጭበረብርና ጠመንጃ ሊጠቀም ሲሞክር የግንቦት 7 ትንታጎች መብረቅ እንዳያወርዱበት ሰግቶአል። ብአዴን ለግንቦት 7 የመፈልፈያ ጫካ ሊሆን እንደሚችልም ወያኔ ከምርጫ 97 በቂ ትምህርት አጊኝቶአል። እና ግንቦት 7 ወጣት ወታደሮቹን ይዞ የማይቀርለትን ፍልሚያ የሚጋፈጥ ከሆነ በርግጥም ማእከሉ መከላከያ ነው የሚሆን። የሰሞኑ የመፈንቅለ መንግስት ድራማ እንዲህ ሰፊና አሻገሮ የተመለከተ ስለመሆኑ ከቶ ምን ጥያቄ አለውና?  

      የብአዴን አመራር በበረከት ሰንሰለት ተጠፍሮ የታሰረ ተስፋ የቆረጠ አካል እንደመሆኑ በህወሃት የሚታዘዘውን የጎጥ አስተሳሰብ ተፈፃሚ የማድረግ ብቃቱን አጥቶአል። ይህ ማለት ግን ህወሃት አልቆለታል ማለት አይደለም። “ኢትዮጵያዊነት” የሚል ባንዲራ ያስቀደሙ ሃይሎች ሲበረቱበት አባዱላ ገመዳን ጠርቶ አንድ የቤት ስራ እንደሚሰጠው ከወዲሁ የሚጠበቅ ነው። አሁንም አፍንጫ ሲመታ አይን ካላለቀሰ ወያኔ ሊሳካለት ይችላል። 

      ወገኖቼ ሆይ!

      ምን ቀረ?

      ቀሪው ግልፅ ነው….

      በቀጣዩ ምርጫ መለስ ዜናዊ ስልጣኑን እንደሚለቅ ነግሮናል። መለስ ቃሉ አይታመንም። አሳ የላሰው ድንጋይ ነው። በአሁኑ ንግግሩ “አሁንስ በቃኝ! እለቅላችሁዋለሁ!!” ማለቱን ግን እኔ በበኩሌ አምኜዋለሁ። መለስ በርግጥም ስልጣኑን ሊለቅ ወስኖአል። አማራጭም የለውም። ሁኔታዎችንና እድሜውን አስለቶ የቤት ስራውን ሰርቶ አብቅቶአል። ሆኖም ብቻውን እንደማይለቅም አስባለሁ። የፖሊት ቢሮ አባላቱን ሁሉ በትልቅ ዘንቢል ሸክፎ ዘወር ይል ዘንድ እንጠብቃለን። ይሁን እነጂ የዚህች ሃገር መከራ እዚህ ላይ ያበቃል ብላችሁ አትጠበቁ። የሚወራው እውነት ከሆነ አስመራ የተማረው ባለመነፅሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም መለስን ተክቶ ኢህአዴግን ሊመራ እጅጌውን ሰብስቦአል። የቅንጅት መሪዎች ከመፈታታቸው ቀደም ብሎ ስዬ አብርሃ ከእስር የተለቀቀበት የስምምነት ምስጢርም ያልተነካ ወሬ ነው። ህወሃት አንድ አስገራሚ ጠባይ አለው። ጥንካሬ ሲሰማው ርስበራስ ይባላሉ። ጠላት ሲበረታባቸው ደግሞ ልዩነታቸውን መሳቢያ ውስጥ አስቀመጠው ባንድ ሰልፍ ለውጊያ ይዘጋጃሉ። የስዬ አብርሃ በድንገት የመፈታትና የተቃዋሚ ንቅናቄ ውስጥ መገኘት የህወሃት ራስን የማዳን ስትራቴጂ አካል ስለመሆኑ የሚጠራጠር ካለም የዋህ ፖለቲከኛ መሆን ይኖርበታል።  

      ባጭሩ ቀጣዩ የሃይል አሰላለፍ በአንድ ወገን መለስና ቡድኑን የሚተካው ሃይል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በስዬና በገብሩ የሚመራው ሃይል ይሆናሉ። ከዚህ ባሻገር ያሉ ሃይሎች እጣ ፈንታ ገብሩና ስዬን መቀላቀል አለያም መጥፋት ይሆናል። ስልጣን ከሁለቱ ሃይሎች እጅ እስካልወጣች ድረስም የህወሃት አላማዎች እንደተጠበቁ ይቆያሉ። ከዚህ ባሻገር መለስ ለግሉ የሚመኛቸው ጥቂት ነገሮች አይጠፉም። የሞ ኢብራሂም ሽልማት ቀዳሚው ይሆናል። ለገንዘቡ ሳይሆን ለክብሩ።  

      ይህ የወያኔ ሂሳብ ይሳካ ይሆን? ለማንኛውም ትግሉ ቀጥሎአል!… 

* * *

      እነሆ! ዛሬ ቅዳሜ ነው… 

      እለቱም ግንቦት 9፣ 2009። 

      ፕሪቶሪያ ቁጭ ብዬ እኔም ይቺን እጫጭራለሁ። የደቡብ አፍሪቃ ክረምት ከነጓዙ ገብቶአል። ዛሬ ጠዋት ከቤት ስወጣ ቆፈኑና ዝናቡ ፕሪቶሪያ ላይ እንደጉድ እየወረደባት ነበር። ያፍሪቃ መሪዎች አብዛኞቹ ፕሪቶሪያ ገብተዋል። ጃኮብ ዙማ መንበረ ስልጣኑን የሚረከብበት እለት ዛሬ ነው። የኛው አዛውንት ጋሽ ግርማም ገብተዋል። መኖሪያ ቤቴ ከቤተመንግስቱ ብዙም አይርቅ። እንደምንም እየተሹለከለክሁ ወደ ሰኒሳይድ አቅጣጫ ነዳሁ። አብዛኞቹ አበሾች እዚያ ቀበሌ ይኖራሉ። ሰኒሳይድ ውብ ናት። ሰኒፓርክ የተባለ አንድ ትልቅ የገበያ አዳራሽ አለ። እዚያ ገባሁና በረንዳው ላይ ቁጭ አልኩ።  

      ሰኒሳይድ በደስታ አብዳለች።

      የዙሉ ጎሳ አባላት የቆዳ ልብስ ለብሰው ባህላዊ ጭፈራቸውን ያስነኩታል። እኔም ደስ አለኝ። ይህቺን መጣጥፍም መጫጫር ጀመርኩ። ሰጫጭር ቆየሁና ቀና ስል ለካስ አጠገቤ ካለ ጠረጴዛ ላይ አንዲት ነጭ ደቡብ አፍሪቃዊት ብቻዋን ቁጭ ብላለች፣

      “ጋዜጠኛ ነህ እንዴ?” ስትል ጠየቀቺኝ።

      ለማሳጠር ያህል፣

      “ነኝ አዎ!” አልኩ።

      “በምርጫው ስራ በዝቶባችሁ ከረመ?”

      “እኔ እንኳ ደስተኛ አይደለሁም” አልኳት “….ምንም ስራ የለም። ምርጫው ቢጭበረበርና ግርግር ቢኖር ስራ ይኖረን ነበር..”

      ቀልዱ ገብቶአት ሳቀች። እናም፣

      “እናንተ ስራ ብታጡ ይሻላል” አለች። 

      በርግጥም ደቡብ አፍሪቃውያን ዛሬ ተደስተዋል። በጣም ተደስተዋል። ምርጫው በሰላም አለቀ። አልተጭበረበረም። እና ፕሪቶሪያ ደስ ብሎአታል። እንኳን ደስ ያላት።

      

      አዲሳባስ ለዚህ አይነቱ የደስታ እለት የምትበቃው መቼ ይሆን? 

      E-mail: ttgebreab@gmail.com 

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on May 21, 2009. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.