የጋምቤላ ወቅታዊ ሁኔታ እየተወሳሰበ ነው

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
መጋቢት 3 ቀን 2004 ዓ ም

17 የሚሆኑ ንፁሃን ተገደሉ

በጋምቤላ እጅግ አሳዛኝ፣አስደንጋጭ፣ጭካኔ የተመላበት ግድያ ተፈጽሟል።ቤተሰቦች ውድ ልጆቻቸውንና አጋሮቻቸውን አጡ።አገርም ልጆቿን ተነጠቀች።እንዲህ ያለውን አሰቃቂና ሰብአዊነት የነጠፈበት አረመኔያዊ ተግባር የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ክፉኛ ያወግዘዋል።ይታገለዋል።ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንዲቀርቡና ከድራማው በስተጀርባ ያሉትን ክፍሎች ለማጋለጥ ከፍትህ ወዳዶችና ከህዝብ ጋር አብሮ ይሰራል።

ትናንት መጋቢት 3 ቀን 2004 ዓ ም ከቀኑ 10 ሰዓት ከ30 አካባቢ ከጎደሬ ወደ ጋምቤላ በሚጓዝ መካከለኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ ተሳፍረው በነበሩ ተማሪዎችና የተለያዩ ወገኖች “ካርሚ” በምትባል ቦታ ላይ በድንገት የተፈፀመው ጥቃት ውድ የሆነውን የሰው ልጆች ህይወት ቀጥፏል።ድርጊቱ የተፈፀመው የመከላከያ ሰራዊት የመከማቻ ካምፕ ቅርብ ርቀት ላይ መሆኑና አደጋውን ተከትሎ እየወጡ ያሉት መረጃዎች ከወንጀሉ በስተጀርባ የማን እጅ እንዳለበት የሚያመላክቱ መሆናቸው ሃዘናችንን ድርብ ያደርገዋል።ለወደፊትም ስጋት ውስጥ እንድንወድቅ አድርጎናል።

“ወንጀል ክልል የለውም።ወያኔ/ኢህአዴግ ያድርጉት የታዘዙ ግለሰቦች፣ሽፍቶችም ይሁኑ በገንዘብ የተገዙ ቅጥረኞች፣ከእውነት ጋር ስለምንቆም፣ስለፍትህ ስለምንጨነቅ፣ከወንጀሉ በስተጀርባ ያሉት ሊደበቁ አይችሉም፤ህግ ፊት ይቀርባሉ ” በማለት ጥልቅ ሃዘናቸውን የገለጹት የንቅናቄያችን መሪ አቶ ኦባንግ ሜቶ ለሟች ቤተሰቦችና ሃዘኑ ለጎዳቸው ሁሉ መጽናናትን እንዲሆንላቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ይኸው የአስራ ሰባት ንፁሃን ህይወት ያለፈበት ድንገተኛ ጥቃት ዘጠኝ የሚሆኑ ወገኖችንም አቁስሏል።አስካሁን ባለን መረጃ መሰረትና ይህን ሪፖርት አስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ የአሰቃቂው ድራማ ባለቤቶች አልተያዙም።ባገዛዙም ሆነ በክልሉ በኩል የተሰጠ መግለጫ የለም።

ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲመለሱ፣ሰላማዊ ዜጎች ለግል ጉዳያቸው የተሳፈሩበትን ተሽከርካሪ አረመኔዎች አድፍጠው በመጠበቅ ካስቆሙ በሁዋላ ጥይት በመተኮስ በፈፀመት የወንጀል ድራማ የተቃጠላችሁ ወገኖች፣ፍትህ ወዳዶች፣የሰላም ሃይሎች፣የድራማው ሰለባ የሆናችሁ ቤተሰቦች፣ወንድሞች፣እህቶች፣እናቶች፣አባቶች እንዲሁም የስርዓቱ አገልጋይ ወገኖቻችን ወቅቱ ማስተዋልና ጥበብ የሚጠይቅ በመሆኑ ከመቼውም በላይ ሰብአዊነትን አስቀድሙ።ሰላማችሁን ጠብቁ።እንደ ቀድሞው ጎሳ፣ቀበሌና ብሄር ሳትሉ፣ቆለኛ ደገኛ በማለት ሳትከፋፈሉ ተሳስባችሁ ኑሩ።

ስደት፣ረሃብ፣ድህነት፣እርዛት… የሚፈራረቅብን ሳያንሰን ወደ እርስ በርስ ብጥብት እንድናመራ የተወጠነ ወጥመድ ከፊታችን ተቀምጦልናል።በግፍ የተጨፈጨፉ ወንድሞቻችን ደም ያፈሰሱትን ወደ ፍርድ ለማቅረብ ከጫፍ በደረስንበት በአሁኑ ወቅት ዳግም የእልቂት ዜና መስማታችን እንዳሳዘነን በድጋሚ እየገለጽን፤የጋራ ንቅናቄው የማጣራቱንና የምርመራውን ስራ እንዳጠናቀቀ ዝርዝር ሪፖርት በማዘጋጀት ይፋ እንደሚርግ ከወዲሁ ይገልጻል።

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
ለዚህ ደብዳቤ ምላሽም ሆነ ለተጨማሪ መረጃ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነትን (media@solidaritymovement.org) በመጻፍ ወይም ድረገጻችንን (www.solidaritymovement.org) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on March 14, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.