የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳደር የግምገማ ውጤት ተገለበጠ!

“ሙስናን ለመዋጋት የተካሄደ ግምገማ በሙስና ተደመደመ”

በጋምቤላ ሲካሄድ የሰነበተው ግምገማ ከሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ ውጪ መወሰኑ አነጋጋሪ ሆነ። በክልሉ በተለያዩ የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራ የተሰማሩ ባለሃብቶችና ነጋዴዎች የግምገማው ውጤት እንዲገለበጥ አስገምጋሚዎቹን ማሞዳሞዳቸው ተጠቁሟል።

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የመረጃ ምንጮች እንዳስታወቁት፣ የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ጋሕአዴን/ ከፌደራል ኢህአዴግ ፅህፈት ቤት በተላኩት አቶ ዘመዴ ዘመድኩንና አቶ አለባቸው ንጉሤ አማካይነት ከታህሳስ 17 ቀን 2004 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ድርጅታዊ ግምገማ አጀማመሩ ጥሩ ነበር።

 ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የጋሕአዴን አባል ለጋራ ንቅናቄያችን ሲያስረዱ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ የወሰነው ውሳኔ የተገለበጠው ከሙስና ጋር በተያያዘ ነው። “ተገለበጠ” ስላሉት ውሳኔ ሲያስረዱ ሙሉ በሙሉ በሥራ አስፈጻሚው የተወሰነው ወሳኔ፤ አቶ ኦሞት ኦባንግ ከፕሬዚዳንትነት መንበራቸውና ከፓርቲው ሊቀመንበርነት አሰናብቷል። አቶ ጓናር የር በተመሳሳይ ከምክትል ፕሬዚዳንትነትና ከፓርቲው ኃላፊነታቸው ያገለለ ሲሆን፣ ሌሎች የከፋ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች አለባቸው የተባሉ ሁለት ሥራ አስፈፃሚዎች ኮር ፖዎችና ጀምሰ ዴንግ ከሥራ አስፈጻሚ እንዲወገዱ ያደረገ እንደነበር አመልክተዋል።

 ባለሥልጣኑ ውሳኔው ተገልብጦ ፕሬዚዳንቱ በኃላፊነታቸው እንዲቆዩ የተደረገበትን ምክንያት ባይዘረዝሩም በደፈናው “ሙስናን ለመታገል የተካሄደ ግምገማ በትልቅ ሙስና ዋጋ እንዲያጣ ሆነ። ችግር እንዳይከሰት ስጋት አለኝ” የሚል መልስ ሰጥተዋል።

ለጋራ ንቅናቄያችን ስም ዝርዝር አካቶ ከስፍራው የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው አስገምጋሚዎቹን ለመደለልና ፕሬዚዳንቱን ለመከላከል በክልሉ ሰፋፊ መሬት ያላቸው ባለሃብቶችና ነጋዴዎች ስብሰባ በማካሄድ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አሰባስበዋል። ባለሃብቶቹንና ነጋዴዎቹን በማስተባበርና መዋጮውን በማሰባሰብ ሥራ ላይ ከማዕከል ፕሬዚዳንቱን እንዲያማክሩ የተላኩት አቶ ብሌን ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል።

ሙሉ በሙሉ በጥፋተኛነት ተፈርጀው እስር እንደሚጠብቃቸው የተገለጸላቸው አቶ ኦሞት ኦባንግ የፕሬዚዳንትነት መንበራቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ይፋ ሲደረግ ከወረዳ የመጡ የበታች አመራሮችን ጨምሮ በመሰብሰቢያ አዳራሹ ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞ ተሰንዝሮ ነበር።

በግምገማው የተሳተፉ የፓርቲው አባላት በወቅቱ ስለነበረው ተቃውሞ ያስረዱን “ሰው የማይወደው፣ የሥራ አፈጻጸም ችግር ያለበት፣ ለሰላምና ለጸጥታ ችግር የሆነ፣ በሙስና የተጠመቀ፣ በተለያዩ ወንጀሎች የሚጠየቅ ሰው በኃላፊነት ማስቀጠል አግባብ አይደለም። ችግርም ያስከትላል . . .” በሚል በእልህ የሚናገሩ ነበሩ። ይሁን እንጂ አቶ ኦሞትን በኃላፊነት ለማስቀጠል አስቀድሞ የተወሰነ ስለነበር  የተሰጠው ምላሽ ማስፈራሪያና ማሸማቀቂያ ነበር።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 16, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.