የገደለን ሲሞት!

ዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ)

ጨርቅ ያለው ባንዲራ፣ ሳጥኑ ላይ አርፎ፣ ሰረገላው አምሮ፤

በጋጋታ አጀብ፣ ጥሩንባ ሲነፋ፣ ሲደለቅ ከበሮ፤

እዬዬ እያሉ፣ ሺዎች ሲያለቅሱለት፣ ለሞተው እሬሳ፤

እንደ ሰው እያዘንኩ፣ እንባ ግን አጠረኝ፣ ቂም ይዣለሁሳ?! (Click here to read in PDF)

 

የገደለን ሞቶ፣ አፈር ተምሶለት፤ እንደሰው ሲቀበር፤

ህሊና ባይኖረኝ፣ ደረቴን ጥዬለት፣ ባለቀስኩኝ ነበር።

እምቢ አለኝ ህሊና፣ ትዝታውን ጨልፎ፣ ሃዘን እየቀዳ፤

ደርሶ እያስታወሰኝ፣ የታሰርኩበትን፣ ጣሪያና ግድግዳ።

በጨለማ እስር፣ ብቻዬን ቁጭ ብዬ፣ ያልኩትን ሳይረሳ፤

“እንደራሄል እንባ፣ ጸሎትህ ተሰምቷል፣ በል አሁን ተነሳ፤”

ሲለኝ ህሊናዬ፣ የጥንቱን አስታውሶ፣ የጸሎቴን ብሶት፤

ለማን ምን እያልኩኝ፣ እንዴት ላልቅስ አሁን፣ የገደለን ሲሞት?

ህሊና መጥፎ ነው፣ ያለፈን አስታውሶ፣ ብሶቴን ቀስቅሶ፤

ለቅሶ ስመለከት፣ ቁስሌን እየነካ፣ አሳመመኝ ደርሶ።

 

ህሊና መጥፎ ነው፣ በትዝታ ወስዶ፣ በሃዘን መለሰኝ፤

የሙታንም ጩኸት፣ መቃብር ፈንቅሎ፣ “እንዳትረሱን” አለኝ።

የወላጆች እንባ፣ ዛሬም ሳይታበስ፣ ምሬቱ ሳይጠፋ፤

እንዴት ብዬ ላልቅስ፣ የገደለን ሲሞት፣ ያጠፋን ሲጠፋ?!

የሰባት አመት ልጅ፣ ያላንዳች ጥፋቱ… በጥይት ተመትቶ፤

ወጣት አዛውንቱ፣ ያለፍትህ ታስሮ፣ ስንቱ ወጣት ሞቶ፤

“እናቴን ገደሏት! ድረሱልን!”፣ ስትል ፊቷ በ’ንባ ርሶ፤

እንዴት ብዬ ልርሳ፣ የሃዘኑን ዘመን፣ ያለምዙሪያን ለቅሶ?!

 

አንዷለም አራጌ፣ እስክንድር፣ ውብሸት፤ እርዮት አለሙ፣

ያለ አንዳች በደል፣ በግፍ የታሰረው፣ ክርስቲያን እስላሙ።

ይታዘቡኝ ሙታን፣ ሰማዕት የሆኑት፣ ከመንገድ የቀሩ፤

ነጻ ጋዜጠኞች፣ እነ አስራት ወልደየስ፣ እነ አሰፋ ማሩ።

እርቀ ሰላም ሳይወርድ፣ ይቅር ሳንባባል፣ የሞተው ተክሶ፤

“ስጋ ብፅዖት ጓዴ!”፣ ቃል ለምድር ለሰማይ፣ እኔ የለኝም ለቅሶ።

 

በዚያ ክፉ ዘመን፣ አንድ ላይ በጸሎት፣ ያልነውን ሳይረሳ፤

“አምላክ ሰውን ሰጠ፣ አምላክ እሱን ነሳ፣ ተመስገን በሉሳ፤”

ሲለኝ ህሊናዬ፣ በፍርዱ እንዳልገባ፣ በፈጣሪ ስራ፤

እዬዬን ለደላው፣ ለቅሶውን ለነሱ፣ ሰጠሁኝ በተራ።

ህሊና መጥፎ ነው፣ የቁስሌን ጠባሳ፣ እያሳየኝ በቀን፤

በለቅሷቸው ዜማ፣ ትዝታን ተቀኘሁ፣ እያልኩ “ለሚያልፍ ቀን”።

 

መታሰቢያነቱ፡ብዕር አሸብሮት፣ ጩኸት አስበርግጎት፣ “ጀግና አይሞትም” ካሉ፤

እሱን ለገደሉት፣ ከሱ በላይ ጀግኖች፣ ስም ስጧቸው በሉ።

 

 

 

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on August 23, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.