የዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ ሙሉ ንግግር

ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ በዋሺንግተን ዲሲ ተገኝተው ያደረጉት ንግግር ከዚህ ቀደም በቪዲዮ መውጣቱ ይታወቃል። ሆኖም በጽሁፍ መልክ ሳይወጣ ጥቂት ቆይቶ ነበር። እንደው ለታሪካዊነቱም ጭምር የዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳን ሙሉ ንግግር ከዚህ ቀጥሎ አቅርበነዋል።

Judge Birtukan Midekessa


“ስቴዲየሙ ይዘጋል” ብለው አስፈራርተውኛል! ነገር አላበዛም: እኔ ሁለት ነገር ነው ማለት የምፈልገው:ከሁሉ አሰቀድሞ ቅድምም ለመናገር እንደፈለኩት የዚህን ፐሮግራም አዘጋጆች በጣም አመሰግናለሁ: እግዚአብሄር ያክብርልኝ ስላከበራችሁኝ እላለሁ: ከዚያ በላይ ደግሞ እናንተ ሁላችሁም እዚህ የተገኛችሁም፣ ያልተገኛችሁም ኢትዮጵያውያን ደርሶብኝ በነበረው ችግር ከጎኔ ስለቆማችሁ፣ የማቴሪያል የሞራል እርዳታ ስላርጋችሁልኝ በጣም፣ በጣም፣ በጣም፣ ከልብ፣ ከልብ ላመሰግናችሁ አወዳለሁ።

እውነቴን ነው ለስሜት መግለጫ ሌላ ነገር፣ ሌላ ቃላት ቢኖር ጥሩ ነበረ፣ ..ከተፈታሁበት ጊዜ ጀምሮ አገር ውስጥ ያሉ ወገኖቼ፣ በየቦታው አገር ቤትም እያለሁ እዚህም ድረስ መጥተው ያላቸውን ስሜት፣ ለኔ የነበራቸውን ሃዘኔታ፣የጸለዩትን ጸሎት ያደረጉትን ድጋፍ ሲገልጹ እኔም በጣም የሚከብደኝ ነገር ነበረ። እዚህም በናንተ መሃል ተገኝቼ ይህንኑ ነው የተረዳሁት: እኔም ባልነበርኩበት ጊዜ የሆነውን ሁሉን ነገር አውቃለሁ። ዛሬ ሻምበል እኔ ባለሁበት በመዝፈኑ የተሰማውን ስሜት መገመት እችላለሁ ምክንያቱም እያለቀሰ ዘፍኖታል ይህንን ዘፈን: ዘፈኑን መስማት ግን ለኔ በጣም ይከብደኛል ከሚገባኝ በጣም የሚያለፍ ነው ብዬ የምር ስለማምን ነው። አና ሁላችሁም ያደረጋችሁልኝ ፍቅር ያሳያችሁኝ መልካም ስሜት ለኔ ከሚገባኝ በላይ ነው ብዬ ነው የማምነው አሁንም ደግሜ ሁላችሁንም እግዚአብሄር ያክብርልኝ::

ሌላ አንድ ነገር መናገር የምፈልገው የዚህ ፕሮግራም ዋና አላማ እንደገባኝ ከሆነ ኢትዮጵያዊነትን ማወደስ የሚል አላማ ያለው ነው: እያሰብኩ ነበረ፣ ኢትዮጵያዊነት ዛሬ ኢትዮጵያ የምትወደስ ነች ወይ? አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት እኛ ያለንበት ሁኔታ የሚወደስ ነገር ነወይ? የሚከበር ነገር ነው ወይ? የሚለውን ነገር ሁላችንም ብንጠይቅ መለሱ አሉታዊ ነው ብዬ አምናለሁ: ምክንያቱም ኢትዮጵያ የነጻነት አገር አደለችም፣ ኢትዮጵያ የፍትህ አገር አደለችም: ኢትዮጵያ አሁንም ዜጎቿ ከድህነት ጋር የሚኖሩባት፣ በእፍረት የሚያቀረቅሩባት፣ እንደናንተ እንደብዙዎቻችሁ በስደት የሚሸሹባት አገር ነች: ስለዚህ አናወድሳት ወይ? ብለን ብንጠይቅ አይ ማወደስስ አለብን ነው መልሱ: ስናወድሳት ግን ምንን አስበን ነው? ኢትዮጵያ ታላቅ ሐገር ነበረች ስለሱ እኔ የምናገረው ነገር አደለም ታሪክ ያሰተምረናል።: ግን ኢትዮጵያ ታላቅም ትሆናለች ብለን ማመን እንችላለን ማመንም አለብን በዬ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ መወደስ አለባት።

ተሰፋ ማድረግ በጣም አሰቸጋሪ እንደሆነ ግን አውቃለሁ: ብዙዎቻችን ፖለቲካ ውስጥ ያለንም የሌለንም፣ ያገራችን ጉዳይ ግድ የሚለን ዜጎች በሙሉ ያየናቸው፣ ያጋጠሙን ነገሮች አገራችን ያለችበትን ሁኔታ ስናይ፣ ስንገመግም የምናገኘው ነገር ተስፋ ለማድረግ በጣም አሰቸጋሪ መሆኑን አውቃለሁ። ቅድም ክሪስ እዚህ ስለ ሌሎች አገሮች ሲነግራችሁ ነበረ: ብዙ ምሳሌዎች ማነሳት ይቻላል ተሰፋ ለማረግ ምክንያቶች: የሰው ልጆች በታሪክ ውስጥ ያሸነፏቸው ተግባራቶች ማንሳት ይቻላል።

እኔ ግን ተሰፋ ለማረግ እኔን እዩ እላለሁ! ከዛሬ አመት በፊት በጣም ጠባብ የሆነች ክፍል ውስጥ ለብቻዬ ተቀምጬ በብቸኝነት እሰቃይ ነበር: ስቃዩ ደግሞ ዘሬ ስናወራው ሊቀል ይችላል ግን በጣም፣ በጣም ጥልቀት ያለው ስቃይ ነበር: አልረሳውም አንድ ጋዜጠኛ እዚህ እየጠየቀኝ ነበር ስለ ጥላሁን ምን ሃሳብ አለሽ? የሞተ ጊዜ የት ነበርሽ? አለኝ: የሞተ ጊዜማ ባዶ ቤት ነበርኩ፣ የሚያናግረኝ ስው አጥቼ ለማን እንደምተነፍሰው፣ ስለስራው ምን እንደምል? የተሰማኝን ሰሜት ለማ እንደምናገረው ግራ ገብቶኝ ፖሊስ መጥቶ በሬን አስከሚከፍት እጠብቅ ነበር: መቶ በሬን ሲከፍተው ሞተ አደል? ሰማችሁ አደል? ሰማሽ አደል? ስላት ቆልፋብኝ ሄደች: ሀዘንን እንኳ ማዘን የሚቻለው የሚጋራህ ሰው ሲገኝ ነው! እውነቴን ነው የምላችሁ በዚያን ሁኔታ ውስጥ ቁጭ ብዬ የነበረኩበት ነገር ለዘላለም ሊቀጥል እንደሚችል በጣም ብዙ ቀን አሰቤያለሁ: ለብዙ ጊዜ የማያቸው ነገሮች ግድግዳዎች፣ መታጠቢያ ቤት በሉት ሽንት ቤት በሉት በጣም አነስተኛ ነገር አለ። በቆርቆሮ ነው የታጠረው፣ ያ ቆርቆሮ፣ ከዚያ ደግሞ አልፎ የሚሰማው የዋርድያዎች ድምጽ ዛሬ ስለዋርድያዎች ድምጽ ግን ሳነሳ እንደቅሬታ ሊሆን ይችላል የኔ ግን ትንሽ ያስደስተኝ ነበር: ከጸጥታ የነሱ ድምጽ ይሻለኝ ነበር ምን እንደሚሉ እንኳ ባይገባኝ።

ምን ልላችሁ ነው? ከዛ መከራ ከዛ ብቸኝነት ወጥቼ ዛሬ አንድ ብቻ የነበርኩት በጣም ብዙ በሚወዱኝ ሰዎች መሃከል ተከብቤ እገኛለሁ: ዛሬም ተስፋ አረጋለሁ ስላገሬ፣ ዛሬም ህልም አልማለሁ፣ አጠንከሬ አልማለሁ፣ በናንተ አምናለሁ፣ በራሴ አምናለሁ፣ በልጄ አምናለሁ፣ በሚመጡት የልጅ ልጆች ሁሉ አምናለሁ: ስለዚህ ኢትዮጵያ ታላቅ ነች እላለሁ: ልትወደስ ይገባታል እላለሁ: እናንተም በዚህ ሃሳብ እንደምትስማሙ አምናለሁ: መልክቴ ይኸው ነው። ኢትዮጵያ ልትወደስ የሚገባት ታላቅ ሐገር ነች: ታላቅነቷን ለማየት ግን ሁሌም ተስፋ ይኑረን፣ ሁሌም ባንድነት እንቁም: አንድነታችን ሁሉንም የሚያቅፍ፣ ሁሉንም የሚያሰባስብ፣ የኢትዮጵያን የጋራ መኖሪያነት የሚያወድስ ይሁን።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 14, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.