የዐፄ ምንሊክ መመረዝ፤“የእቴጌ ጣይቱ እጅ አለበት?!”

ሰሎሞን ተሠማ ጂ. –

(ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ – ፍንዳታ፡፡ 1966 ዓ.ም)

የዳግማዊ ዐፄ ምንሊክ ኃይለ-መለኮት ልደትና አሟሟት አሁንም እያነጋገረ ነው፡፡ አሁንም ስል ንጉሠ ነገስቱ ካረፉ ከ99 ዓመታት በኋላም ማለቴ ነው፡፡ አንድ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሚሰራ ጀርመናዊ ዶክተር (ዎልበርት ስሚት) የሚባል፣ በዐፄ ምንሊክ አሟሟት ላይ “የእቴጌ ጣይቱም እጅ አለበት?!” አለ፡፡ “እንዴት ሆኖ! እንደምን ተደርጎ!” ስልም በራስ መኮንን አዳራሽ ተሟገትኩኝ፡፡ “ወይስ የጀርመናዊውን ወቀሳ ለጣይቱም ለማከፋፈል እየሞከርክ ነው” ስል አበክሬ ጠየቅኩኝ፡፡ የመቀሌው ሰውዬ መልስ ግን፣ “ይህ ጉዳይ መቶ አመት ያለፈው ነገር ነውና፣ ቀለል አድርገን እንየው” የሚል ነበር፡፡ ለእኔና ለብዙ ኢትዮጵያውያን የዐፄ ምንሊክና የእቴጌ ጣይቱ ውለታ በአመታት ርዝማኔ ስለማይደበዝዝብን የሚከተለውን ለማለት ተነሳሳሁ፡፡………

ቅንጭብጫቢዎችን ከዚህም ከዚያም የቃረመው ዶር. ስሚት እንደሚለው ከሆነ፣ “ንጉሠ ነገስቱን የመረዝኩት እኔ ነኝ” ብለው ተናዘዋል እየተባሉ ከሚታሙትና ከሚጠረጠሩት የንጉሱ ቅርብ ሰዎች መካከል አንዱን “ራስ ሙሉጌታ ናቸው” ከጣይቱ ጋር ተመሳጥረው ለማለት ይሞክራል፡፡ ራስ ሙሉጌታ ደግሞ በዐፄ ምንሊክ ዘመን በበጅሮንድ ማዕረግ የገንዘብ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ሌላኛው የንጉሠ ነገስቱ የግቢ ሚኒስትር አዛዥ መታፈሪያ ነበሩ፣  በጀርመናዊያኑ የዐፄ ምንሊክ ሃኪሞች ዘንትገራፍና ስቴንኩሁለር በግልፅ የተጠረጠሩት፡፡ “እኛ ንጉሠ ነገሥቱን ለማዳን ስንጣጣር ስራችንን እግር በእግር ተከታትለው እያበላሹብን ነው፤” ተብለዋል፡፡ የሃኪሞቹንም ስሞታ በከንቲባ ገብሩ በስተርጓሚነት ለእቴጌ ጣይቱ ተናገሩ፡፡ እቴጌ ጣይቱም የሰጡት መልስ “ከማያውቁት መልዓክ፣ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል፤” አይነት ነበር፡፡ እቴጌይቱ እንዲህ ሲሉ ለሃኪሞቹ መለሱ፤ “እነዚህ ሁለት ባለስልጣኖች ከልጅነታቸው ዠምሮ በቤተ መንግስታችን አብረውን የኖሩና በፍፁም የማንጠረጥራቸው ታማኞቻችን ናቸውና በፍፁም የትም አይሄዱም፤” ሲሉ በከንቲባው ቱርጁማንነት ፍርጥም ብለው ተናገሩ፡፡
ሙሉውን ሃተታና የንጉሠ ነገስቱን መመረዝ በተመለከተ ኮል. አልኸንድሮ ዴል ባዬ የተባለው ኩባዊ በ1928 ዓ.ም በጻፈው መጽሐፉ ላይ እንዲህ ሲል ይተርከዋል፡፡
****************
ራስ ሙሉጌታ የጦር መነፅራቸውን አንስተው በሚያፏጨው ጥይት መሃል ቀጥ ብለው ቆሙ፡፡ በድንገት ተኩሱ ጨመረ፡፡…..የሚያደነቁር የእሩምታ ተኩስ በድንገት ተከፈተ፡፡ ጥቁሩ አለቃ ይዋዥቁ ጀመር፡፡ ሁለቱንም እጆቻቸውን ወደ ሆዳቸው ወሰዱና ወደቁ፣ ቆስለዋል፡፡ ከጎናቸው ተጠጋሁ፡፡ የጦር ሜዳ ደንብ ልብሳቸው የጠቆረ ብዛት ያለው ደም አርሶታል፡፡ እጃቸውን ዘረጉልኝ፣ ሊናገሩ ነው፡፡ ፀጥ ሊሉ ነው? ሞቱ?
****************
ዓይኖቻቸውን ገልጠው ግን ወደማይንቀሳቀሱት ወደ ራስ ሙሉጌታ አጎነበስኩ፡፡ እጆቼንም በመዘርጋት ግራና ቀኝ አንቀሳቀስኳቸው፡፡ ሆዳቸው በከፍተኛ ደረጃ ተመትቶ ተበታትኖ ነበር፡፡ ጥይት ሆዳቸውን በግራ በኩል ከፍ ብሎ መትቶት በቀኝ በኩል ዝቅ ብሎ ወጥቷል፡፡ የጥይቱ መውጫ ቀዳዳ ሰፊና ለሞትም የሚያበቃ ነበር፡፡ የራስ ሙሉጌታ የሕይወታቸው መውጫ በዚህ በኩል እንደሆነ ያሳያል፡፡ ሆኖም ግን ራስ ሙሉጌታ ገና አልሞቱም ነበር፡፡ ባለ በሌለ ሃይላቸው በሁለቱም መዳፋቸው ያንን የወደቁበትን አፈራማና አባጣ ጎርባጣ መሬት ተደገፉት፡፡ ደማቸው ግን እንደ ጎርፍ ይወርዳል፡፡ ራሳቸውንና ደረታቸውን ቀና አድርገው ቁጭ አሉ፡፡ እኔ በጉልበቴ ተንበረከኩ፡፡ አንገታቸውን ጎንበስ አድርገው ሆዳቸውን ማየት ጀመሩ፡፡ ፊታቸው ላይ ፈገግታ ይነበባል፡፡ እንደማይተርፉ በሚገባ አውቀውታል፡፡
“ምን ታስባለህ ፈረንጅ?” ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ ልክ የሌላ ሰው ጉዳይ ይመስል፡፡ “በጣም የሚገርም ልዩ ነገር ነው፤ አያምም!” አልኳቸው፡፡ ደም እንደጎርፍ ሲፈሳቸው ይታያል፡፡
ሳላስበው በድንገት የሰጠኋቸው መልስ እውነት ነበር፡፡…….
ራስ ሙሉጌታ ከንግዲህ ለሶስት ደቂቃ እንኳን አይቆዩም፡፡ በድጋሚ ሳቁ፡፡……..
………. “በሕይወት ዘመኔ ጥሩ መንገድ ተጉዣለሁ፡፡” ሲሉ በተኩራራና በሚያምር የቲያትር ድምፅ ተናገሩ፡፡ “ከምንም የሆንኩትን ለመሆን ችያለሁ፡፡ አሁን መሞት እችላለሁ፡፡”………
……….“አዳምጥ ፈረንጅ፣” በማለት ቀጠሉ፡፡ “ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሃይላቸው ራስ መሆኔን ያውቃሉ፡፡ ሆኖም ግን ሰዎች ከሚገምቱት በላይ ሃይለኛና ብዙ ማድረግ እንደምችል ግን በፍፁም አያውቁም፡፡
“ሁሉም ሚኒሊክን ያከብራል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክም ውስጥ ትልቁ ሰው አድርገው ያዩዋቸዋል፡፡ የምይሸነፉም ሰው አድርገው ይቆጥሯቸዋል፡፡”
ንግግራቸውን ገታ ለማድረግ መዳፋቸውን ጭብጥ አደረጉት፡፡ በሃይልም አንቀሳቀሱት፡፡
“እናም፣ ምንሊክን የምበልጠው ትልቁ ሰው እኔ ነኝ፡፡ እኔ ነኝ የኢትዮጵያውያንን ጀግና የገደልኩት፡፡”
“እርሶ ነዎት የገደሏቸው? …..እንዴት?”
“በመርዝ ነው የገደልኳቸው፡፡”
ራስ ሙሉጌታ በነገሩ በመደነቄና በመገረሜ ያስደሰታቸው ይመስል ጨካኝና ሃይለኛ በሆነ አስተያየት በዓይናቸው ቃኙኝ፡፡
“አዲስ አበባ ላይ አንድ ግሪካዊ ዶክተር ነው መርዙን የሰጠኝ፡፡ ያለ ህመም ሞት፣ የሚታይ ፍንጭ የሌለው፡፡ ገዳይ ወይም ዱካው ያልተገኘ ሞት፡፡ ሁሉም ነገር በሚስጢር ሆነ፡፡ በአንዲት የቡና ሲኒ ምንሊክ ምትን ፉት አሏት፡፡ ማንም በፍፁም የጠረጠረ የለም፡፡ ከኢትዮጵያ ችሎት ውስጥ ማቀነባበሩን ከረዱኝ ሶስት ታላላቅ ሰዎች-በስተቀር፡፡”
“ሦስት የወንጀሉ ተባባሪዎች?” ነው ያሉኝ እያልኩ ጎተጎትኳቸው፡፡
“አይደለም፣ ጠንቋዮች!”
“አስፈላጊ ነበር?….” ቃላቶቹ ከአፋቸው ሳይወጡ ቀሩ፡፡ ዳግም ደከሙ፡፡ እጃቸው ሙሉ በሙሉ ዛለ፡፡ የእኚህ ጦረኛ ሽማግሌ ገላ መሬት ላይ አረፈ፡፡……
ኮል. አልኸንድሮ ዴል ባዬ (1928) ፅፎት፤ ተስፋዬ መኮንን ባይለየኝ (ዶር.) (1992) ቀይ አንበሳ፡፡1 ብሎ ከተረጎመው መጽሐፍ፣ ከገፅ 188-190 በከፊል የተወሰደ፡፡
ብዙውን የዚህን መፅሐፍ ነገር አምኖ መቀበል እንደማይገባ የታሪክ ተመራማሪዎች ይገልፃሉ፡፡ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ በተለይ፣ ይህ “ቀይ አንበሳ” የተባለው መጽሐፍ፣ በብዙ ማስረጃዎች ተመሳክሮ ተዓማኒነት የሚጎለው መሆኑን አስምረውበታል፡፡ እንዲያውም ይላሉ፣ “ይህ ኩባዊ ኮሎኔል በጭራሽ በጦር ግንባሩ ቦታ ላይ አልነበረም፡፡ ካልነበረ ደግሞ ራስ ሙሉጌታን ፈፅሞ ሊያናገራቸውም ሆነ በዚያች ቀውጢ ሰዓት ኑዛዜያቸውን ሊቀበል አይችልም፡፡” ካሉ በኋላ፣ “ኮሎኔሉ በታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ እንደ “ቁጩ” የሚታይ ሰው ነው!” ብለዋል፡፡
****************
ከ1857 እሰከ 1881 ዓ.ም. የሸዋ ንጉሥ፣ ከ1882 እስከ 1906 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው ያስተዳደሩት ምንሊክ “በእርግጥ ተመርዘው ነበርን?” የሚለውን ጥያቄ ብዙ የምንሊክ ታሪክ አጥኝዎች አንስተውታል፡፡ አንዳቸውም ግን መቋጫ አልሰጡትም፡፡ ለምን ይሆን? ለሚሉ አንባቢዮቼ አንዳንድ ለአእምሮአቸው የሚረዱዋቸውን መረጃዎች እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
አንደኛ፣ ኩባዊው ኮሎኔል አንዲት ፍንጭ አግኝቷል፡፡ እርሱም፣ ራስ ሙሉጌታን ባገኘበት ወቅት (አግኝቷቸው እንደሆነም ማንም አላረጋገጠም?!) ምናልባት ስለመርዙ ሃሜቱና ስለ ከንቲባ ገብሩም ጀርመን ኤምባሲ መሸሸግ ቢሰማ አያስደንቅም፡፡ ለነገሩ፣ ይሄንን ለማወቅም ሆነ ለመስማት ኢትዮጵያ መምጣትም አያስፈልገውም፡፡ ስለዚህም፣ ይሄንን “የአደባባይ ጉድ” ኩባዊው ባለበት ሆኖ ቢሰማው አያስደንቅም፡፡ (ከዚያ በኋላም፣ ወሬ አጠያይቆና አተቻለውን ያህል ቀላቅሎና አቀነባብሮ የ11 ወራት ገድሌ ነው ያለውን ጽሑፍ ፅፎ ይሆናል፡፡ በተለይም፣ በጦርነቱ የመጀመሪያ ሁለት አመታት በስደት ላይ ይኖሩ የነበሩትን ኢትዮጵያውያን አፈላልጎ በመጠየቅ የተረዳውን ያህል ፅፎ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ዶር. ተስፈዬ መኮንን ስለደራሲው በቂ መረጃ ቢሰጡበት ይሻላል፡፡)
ሁለተኛ፣ ጀርመናዊያኑ ሃኪሞች (ዶር.) ማክስ ስቴንኩህለርና በህክምና ጉዳይ እንዲያማክር አብሮት የመጣው (ዶር.) አልፍሬድ ዜንትግራፍ በሚያዝያ 2 ቀን 1901 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቡ፡፡ በሚያዝያ ወር 1900 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ በመጀመሪያው የደም ግፊት ክፉኛ ታመው ነበር፡፡ የሞሪሺየስና የፈረንሳይ ሃኪሞች አክመዋቸው የኩላሊትና የተዛማጅ ምልክቶችን አግኝተዋል፡፡ ሆኖም፣ ከሁለት ወር ተኩል በኋላ የንጉሠ ነገሥቱ ግማሽ አካል በድን ሆነ፡፡ ስለዚህም፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ባለሙሉ ስልጣን ሚኒስቴር (ዶር.) ፍሬድሪክ ሮዘን አማካኝነት ለጀርመኑ ንጉስ ዳግማዊ ዊልሄልም ተጽፎ ሴንትገራፍና ስቴንኩህለር አዲስ አበባ ደረሱ፡፡ ከንቲባ ገብሩ አስተረጓሚ ሆነው ተመደቡላቸው፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ በጅሮንድ ሙሉጌታ (በኋላ ራስ) እና የግቢ ሚኒስትሩ አዛዥ መታፈሪያ ከከንቲባ ገብሩ ጋር የግል ፀብና ቂም እንደነበራቸው ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ (1983፡623-4)2 ይጠረጥራሉ፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ፣ እቴጌ ጣይቱ በነሐሴ 15 ቀን 1901 ዓ.ም ለዳግማዊ ዊልሄልም በፃፉት ደብዳቤ ላይ፣ ስለመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የኤምባሲ ጥገኝነት ጠያቂ (Asylum seeker)፣ ከንቲባ ገብሩ ሴረኝነት በቁጭት ጽፈዋል፡፡ (ብዙ ኢትዮጵያውያን ጥሊያን ኤምባሲ በ1983 ዓ.ም ስለተሸሸጉት የደርጉ ባለስልጣናት በስሜትና በቁጭት ለምን ያወራል? ከነሱ 84 ዓመታት ቀድመው ከንቲባው ተጠግተው ነበር፡፡)
ሦስተኛ፣ዳግማዊ ዐፄ ምንሊክና የጀርመኑ ንጉስ ዳግማዊ ዊልሄልም የቆየ ቁርሾ ነበራቸው፡፡ ጉዳዩ ከውጫሌ 17 ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ዐፄ ምኒሊክ ከአውሮፓ ኃያላን ወይም መንግስታት ጋር ለሚዋዋሉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ ንጉሠ ነገሥት በኩል ለመጠቀም እሺ ብለዋል፤” የሚለውን የተጭበረበረ የጣሊያንኛ ትርጉም ለማስተባበልና ባለሙሉ ስልጣን ንጉሠ ነገሥት መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሲሉ ለስድስት የውሮፓ ሀገሮች መንግስታት ደብዳቤ ጽፈው ስለነበረ፣ ዳግማዊ ዊልሄልም ከጣሊያን ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላለማወክ ሲል ምንሊክን አጣጥሏቸው ነበር፡፡ ከአስራ አራት አመታት በኋላ ዶክተሮቹን ሲልክ የህክምና አገልግሎታቸውን ብቻ እንዲሰጡ አላካቸውም ይሆናል፡፡ ምክንያቱሞ፣ የዐፄ ምንሊክ ኃኪም ሆኖ የመጣው ዶር ስቴንኩሁለር የጀርመን ኤምባሲ ካውንስለርነትንም ደርቦ ይሰራ እንደነበር ለሚያውቅ ደግሞ ይበልጥ የጀርመኑን ንጉሥ ከመጋረጃ ጀርባ አሉ ብሎ ሊጠራጠር ይችላል፡፡ ምናልባተም ደግሞ የጣሊያኑ ንጉሠ ነገሥት ሰላላ እጁን ለቂምና ለበቀል በስረዝሞት ይሆናል፡፡
በአጠቃላይ፣ ከዐፄ ምንሊክ ህመምና አሟሟት ጀርባ ዓለም-አቀፍ ሴራ አለ ብለው ከሚያምኑት ኢትዮጵያውያን መሃከል ነኝ፡፡ የንጉሡ ህመም ጠንቶ ከጥቅምት 1902 እስከ ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም ድረስ ቀጥሎ “አይሰሙም፤ አይለሙም” ነበር፡፡ የእስራኤሉ ኤሪያል ሻሮን ሆኗል እንደሚባለው ያለ ነፍስ-ግቢ፣ ነፍስ-ውጪ ላይ ነበሩ፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜም ሙሉ የማስታመሙንና የመንከባከቡን ስራ የተወጡት እቴጌ ጣይቱ ነበሩ፡፡ የመንግስታዊውን አመራርም በተቻለ መጠን ለመወጣት በብርቱ እየተጣጣሩ ባለቤታቸውን አስታመዋል፡፡
ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም. በአንጎለላ ኪዳነ ምህረት ተወልደው፣ በታህሳስ 03 ቀን 1906 ዓ.ም. አዲስ አበባ አረፉ፡፡ ልጃቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ (በኋላ ንግስት ዘውዲቱ) እንዲህ ስትል ሙሾ አወረዱ፡፡
                                           ሰላሣ ሦስት ዘመን፣ የበላንበቱ የጠጣንበቱ፤
                                            “በትኅሣሥ ባታ ለት፣ ተፈታ ወይ ቤቱ?!”
ዋቢ መፅሐፍት
1ኛ. ኮል. አልኸንድሮ ዴል ባዬ (1928) ፅፎት፤ ተስፋዬ መኮንን ባይለየኝ (ዶር.) (1992)
ቀይ አንበሳ፡፡ ብሎ ከተረጎመው፡፡ አዲስ አበባ፡፡
2ኛ. ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ፡፡ (1983)፡፡ ዐፄ ምንሊክ፡፡ አዲስ አበባ፡፡ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት
ታተመ፡፡
(ይህ መጣጥፍ በአዲስ ጉዳይ መፅሔት ሰኔ 17 ቀን 2004 ዓ.ም ዕትም ላይ ወጥቶ ነበር፡፡)
ሰሎሞን ተሠማ ጂ. (semnaworeq.blogspot.com)
Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 26, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.