የዐለም ደቻሳ አሟሟት አጭር ዘገባ – ቅንብር አድማስ ሬዲዮ

ወጣት አለም ደቻሳ የ 33 ዓመት ወጣት ስትሆን ሊባኖስ የገባችው ከሶስት ወር በፊት መሆኑን ምንጮቻችን ይገልጻሉ። ሊባኖስ ከመግባቷ በፊት የመንም ለጥቂት ቀናት ቆይታለች። ከየመን በድንበር ተሻግራ እንደገባችም ታውቋል። እዚያም እንደደረሰች በአንዲት ሊባኖሳዊት ቤት በቤት ሰራተኝነት ትቀጠራለች። ለጊዜው ኑሮው ቢስማማትም፣ አብራት እንድትሰራ ከተቀጠረችው ሌላ ሊባኖሳዊት ወጣት ጋር ሊስማሙ አልቻሉም። ያቺ እንደ አለቃ የተሾመችባት ሊባኖሳዊትም አለምን ከዚያ ቤት አስወጣቻት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሊባኖስ ከኢትዮጵያ ሰራተኛ አልፈልግም በማለቷ፣ ዓለም ሊባኖስ የገባችውም ሆነ የተቀጠረችው በህጋዊው መንገድ አይደለም።

ዓለም ከወጣች በኋላ የሄደችው ወደ አስቀጠሯት ሰዎች (ኤጀንሲዎች) ነበር። እነሱም ለጊዜው ሌላ ሥራ እስኪያገኙላት ቢሯቸው የግድ መኖር ትጀምራለች። እዚያ ቢሮ ውስጥ እነሱ ለሷ ግድም አልነበራቸውም። በዚያ መሃል ተማርራ ክሎራክስ (በረኪና መሰል ፈሳሽ) እንደጠጣች መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚያ በኋላ ኤጀንሲዎቹ መልሰው ወደ ኢትዮጵያ ሊጠርፏት (ሊልኳት) ሲፎክሩ ስትሰማ፣ ወደ አገሯ መመለስ በፍጹም የማትፈልገው ዓለም፣ ከቢሮው ወጥታ ወደ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ሳይሆን እንዳልቀረ ወደተገመተ ቦታ ትሄዳለች። [ግምቱ የመጣው መጨረሻ ላይ አስቀጣሪዎቹ (ኤጀንሲዎቹ) የያዟት ኤምባሲው በር አካባቢ በመሆኑ ነው] … እዚያ መሄዷን ያወቁት አስቀጣሪዎችም በመኪናቸው ተከተታትለው ይደርሱባታል፣ በቪዲዮው ላይም እንደታየው፣ በግድ ከመንገድ ላይ እየጎተቱ ወደመኪናው ይጨምሯታል። እሷም “አልፈልግም፣ አልሄድም” እያለች ስትጮህ ሲሰማ፣ እነሱም በቋንቋቸው “ወደ አገሯ ነው የምንልካት፣ በግድ ትመለሻለሽ” እያሉ ሲጮሁባት ተሰምቷል።

በዚህ መሃል ቪድዮውም በመስራጨቱና በከተማው ቴሌቪዥንም በመታየቱ፣ ጉዳዩ የሳባቸው በጎ ፈቃደኞች “ሴንት ሩታ” የተባለ በካቶሊክ መነኮሳት የሚተዳደር ሆስፒታል ውስጥ ያስገቧታል። እዚያም ዶክተር ተመድቦላት ስትታከም ቆይታለች።

ዕሮብ ጠዋት ራሷን አጠፋች ከመባሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የአድማስ ሬዲዮ ጋዜጠኛ የተኛችበትን ሆስፒታል ክፍል ቁጥር አፈላልጎ ሊያናግራትና ኢትዮጵያውያን ድምጿን እንዲሰሙ፣ ስላለችበት ሁኔታ እና ስለምትፈልገው እርዳታ ሊያናገራት ሞከረ። በወቅቱ የሷን ጉዳይ በሃላፊነት ለመከታተል ጉዳዩን የያዘችው [ሶሻል ወርከር) ነበረች ስልኩን የተቀበለችው። ስሟም ኤሊየን ይባላል። በወቅቱ እዚያው ሆስፒታል ዓለም ያለችበት ቦታ ብትሆንም ፣ “ማቅረብ አንችልም፣ ዶክተሩ አልፈቀደም፣ ማናገር አይፈቀድም፣ እናንተ እነማናችሁ .. ወዘተ.” በሚሉ ጥያቄዎች ከግማሽ ሰአት ላላነሰ ጊዜ ከደወለው የአድማስ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ጋር ተሟገተች። በጊዜው ዓለም የአንድ ኢትዮጵያዊ ድምጽ ሰምታና ችግሯን ተናግራ ቢሆን ኖሮ፣ ቢያንስ አንድ ነገር አገኛለሁ የሚል ተስፋ ስለሚኖራት ራሷን አታጠፋም ነበር የሚል ዕምነት አለን።

የሆነው ሆኖ ቁጥራችንን ሰጥተን፣ ስማችንን አስመዝግበን መልሰን እንደውላለን ብለውን ተለያየን፣ ሳይደውሉ ሲቀሩ እንደገና በማግስቱ ይህችው ኤልየን የተባለችውና ጉዳዩዋን የያዘችው ሴት ጋር ደውለን “እባክሽ አቅርቢልንና ፣ ችግሯንን ያለችበትን ሁኔታ እንወቅ ፣ ለሌላውም እናሳውቅ” አልናት። እሷ ግን “አሁን ደህና ነች፣ እኔ ያለሁት ሌላ ቦታ ነው፣ ቢሆንም ግን እሷን ማናገር አይፈቀድም ተብሏል” አለችን።

በሚገርም ሁኔታ ግን ከሷ ጋር ስልኩን እንደዘጋን ወዲያው ከሊባኖስ የዓለም መሞት ተነገረን። ሶሻል ወርከሯ የሷን ጉዳይ የምትከታተል ሆና ሳለ፣ ከሷ ቀድሞ የልጅቷን መሞት እኛ ማወቃችን የሚገርም ነው።

ከሆስፒታሉ አካባቢ እንደሰማነው፣ ማክሰኞ ማታ ላይ ዶክተሯ ጎብኝቷታል። እሱም ሊያጽናናት በማሰብ “አይዞሽ ፣ ደህና ነሽ፣ ድነሻል ነገ ከሆስፒታል ትወጫለሽ .. ወደ አገርሽም ትሄጃለሽ” ብሏታል።

ነገሩ እዚህ ላይ ነው። ለካ እሷ ወዳገር ቤት መመለስ የሚለው ነገር ነበር በሽታዋ! .. ዶክተሩ ግን ያወቀ አለመሰለንም። በቪዲዮው ላይም ስትጮህ የነበረው ወደአገር ቤት ላለመመለስ ነበር። ምናልባት በዶክተሩ ንግግር የተነሳ ነገ ወዳገር ቤት ሊመልሱኝ ነው ብላ ሳትሰጋና ሳትደነግጥ አልቀረችም። ንጋት ላይ ነርሶች 5 ኤ ኤም ላይ መጥተው ሲያዩዋት ተኝታ ነበር ብለዋል .. አንድ ሰአት ያህል ቆይተው 6 ኤ ኤም ላይ ሲመለሱ ግን የተኛችበትን አንሶላ ቀድዳ በመሸምቀቅ ራሷን ሰቅላ ነው ያገኟት። …..

አለም ደቻሳ በአዲስ አበባ ዙሪያ በቡራዩ ከተማ ነዋሪ የነበረች ወጣት ናት። ሶስት ልጆችም አሏት። ከባለቤቷ ጋር የተፋታች መሆኑ ታውቋል። ገንዘብ ተበድራና ተለቅታ ለራሷም ለልጆቿም እንዲያልፍላቸው ለማድረግ ነበር አረብ አገር የመጣችው፣ ለዚያም ይመስላል ገና በሶስት ወሯ ምንም ነገር ሳትሰራ መመለስን የሞት ያህል የጠላችው።

ሆነም ቀረ፣ የሚረዳትና አይዞሽ የሚላት ባለመኖሩ ራሷን አጠፋች ተባለ። አሁንም በድጋሚ- የአድማስ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ከዚያ ሁሉ ልመና በኋላ ቢያናግራት ኖሮ ምናልባት ራሷን የማታጠፋበት ሁኔታ ይኖር ነበር የሚል ዕምነት አለን። ልክ እንደ ዓለም ፣ አሁንም ህይወት ጨለማ የሆነባቸውና በአሰሪዎቻቸው የሚሰቃዩ እህቶቻችን አሉ። እነሱንም እናስብ። ዓለም ራሷን ያጠፋችላቸውን ሶስት ልጆቿንም እናስብ። አንዳንድ ልጅ ስፖንስር አድርገን ማሳደግ ያቅተናል? በአረብ አገራት ያሉ እህቶቻችን የሚከበሩት መቼ ነው? እነሱ እንዲከበሩ ማድረግ ያቅተናል?
በዚህ ጉዳይ ላይ ሁላችንም መረጃዎችን መለዋወጥ እንድንችል “RESPECT OUR SISTERS” የሚል የፌስ ቡክ ገጽ ከፍተናል። ሁላችሁም “like” አድርጉት።

አድማስ ሬዲዮ፣ ለታሪክ ይሆን ዘንድ ከሶሻል ወርከሯ ጋር የነበረውን “አቅርቢልን ፣ አላቀርብም” ክርክር በቅዳሜ ፕሮግራሙ አየር ላይ ያቀርበዋል። www.admasradio.info [2pm-6pm EST]

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on March 17, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.