የዋጋ ግሽበቱ የሚቆመው መቼ ነው?

Reporter — ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት በአብዛኛው የከተማ ነዋሪ የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው፡፡

ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚጐርሰው አጥቶ ሲሰቃይ፣ መካከለኛ ገቢ የነበረው የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ ሌላው ቀርቶ መሠረታዊ ፍላጐቶቹን ማሟላት የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የኢኮኖሚ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና የመንግሥት ባለሥልጣናት የግሽበቱ ምንጭ ምንድነው? የሚቆመውስ መቼና እንዴት ነው? በሚለው ላይ አሁንም ድረስ የሚያስማማቸው ነጥብ ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡ ግሽበቱን ለማስቆም መንግሥት ወስዶት የነበረው የዋጋ ተመን ዕርምጃም ምንም ውጤት ሳያስገኝ እንዲነሳ ተደርጓል፡፡ የኅብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታ ግን ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ነው፡፡ በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጀውን ዘገባ ዝርዝር ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡

ዳቦ የያዙ ሁለት ስስ ፌስታሎች በእጁ አንጠልጥሏል፡፡ የፊት ገጽታውን እንዲሁም አለባበሱን በመመልከት ሰውዬው ምናልባትም መካከለኛ ገቢ አላቸው ከሚባሉ ሰዎች ተርታ ሊመደብ ይችላል፡፡ ለም ሆቴል ጫፍ ጋ ሲደርስ ከተሳፈረበት ታክሲ ወርዶ ወደ ሾላ በሚወስደው መንገድ በእግሩ መጓዝ ጀመረ፡፡ ጥቂት እንደተራመደ መለስ ብሎ አስፋልት ዳር ምድጃ ላይ በቆሎ እየጠበሱ ወደነበሩ ሴቶች ጠጋ ብሎ ዳር ላይ የነበረችውን ሴት፣ ‹‹ይቺ ስንት ነች?›› በማለት ጠየቀ፡፡ እሳት ላይ የነበረችውን መጠነኛ በቆሎ በጣቱ ለማመልከት እየሞከረ፡፡ ትንሽ ራቅ ብሎ ስለነበር የቆመው ሻጯ ድምጿን ከፍ አድርጋ ‹‹ሦስት ብር›› ስትለው፣ ምንም ሳይናገር ረጅም ፉጨት እያፏጨ ጭንቅላቱን በመነቅነቅ ቀስ እያለ ወደኋላ መራመድ ጀመረ፡፡

በየጊዜው እየጨመረ በመሄድ ላይ የሚገኘው የሸቀጦች የዋጋ ንረት ዝቅተኛም ሆነ መካከለኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮን አክብዶታል፡፡ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ መድኅን በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 09/10 ውስጥ ነዋሪ ናቸው፡፡ ወይዘሮዋ ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት ሲሆኑ፣ በየሰው ቤት ልብስ በማጠብና እንጀራ በመጋገር በቀሪው ጊዜያቸው ደግሞ በቤታቸው ጥቢኛ ዳቦ ጋግረውና ስኳር ድንች ቀቅለው ጉልት ገበያ ወስደው በመሸጥ ነበር ኑሯቸውን ሲገፉ የቆዩት፡፡

እርሳቸው ይህንን ሥራ ሲሠሩ በነበረበት ወቅት ባለቤታቸው በአናፂነት ሙያ ይሠሩ ስለነበር ብዙም ለቤት ወጭ አይቸገሩም ነበር፡፡ ነገር ግን ወይዘሮዋ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የጤና መታወክ ስለገጠማቸው ሥራቸውን አቁመው ሕክምና ሲከታተሉ አሳልፈዋል፡፡

ባለቤታቸውም በእርጅና ምክንያት ቤት ውስጥ በመዋላቸው ቤተሰቡ የሰው እጅ እንዲመለከት ሆኗል፡፡ ወይዘሮ ሙሉ በተወሰነ ደረጃ ባለፈው ወር የጤናቸው ሁኔታ መጠነኛ መሻሻል በማሳየቱ ከገጠማቸው ችግር ለመውጣት የተወሰነ ገንዘብ ይዘው ወደ ቀድሞ ሥራቸው ለመመለስ ማቀዳቸው አልቀረም፡፡

የገበያው ሁኔታ ግን እጅግ ከብዶ ነው የጠበቃቸው ‹‹ጥብኛ ለመጋገር የሚያስፈልገው ዱቄት አንዱ ኪሎ ከአምስት ብር ተነስቶ አሥር ብር ከሃምሳ ሳንቲም ሆኗል፡፡ ስኳር ድንችም እንዲሁ ዋጋው ንሮ ነው የጠበቀኝ፤›› ሲሉ ወ/ሮ ሙሉ ገበያው እንዳስደነገጣቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹የባህር ዛፍ ቅጠል እንኳ ከ10 ብር ተነስቶ 20 ብር ገብቷል፤ እንዴት ነው የሚጋገረውና የሚቀቀለው?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ሕክምናውንም የተከታተልኩት ከቀበሌ ደሃ መሆኔን አጽፌ ነው፤ ቤተሰቤንም ሲደግፍልኝ የቆየው ወዳጅ ዘመድ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ለመነገድ ብነሳ ሁሉ ነገር ተወዷል፡፡ የምነግድበት ገንዘብም የለኝም፡፡ አቅም ኑሮኝ ሥራውን ብጀምር እንኳ ደንበኞቼ በማቀርብላቸው ዋጋ የሚገዙኝ አይመስለኝም›› ሲሉ ኑሮው ግራ እንደሆነባቸው ወ/ሮ ሙሉ በትካዜ ውስጥ ሆነው ይናገራሉ፡፡

አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ድፍን የአዲስ አበባ ሕዝብ ለባብሶና አሸብርቆ ሲወጣ የደላው ቢመስልም ውስጡ ግን በኢኮኖሚ ክፉኛ የተጎዳ ነው፡፡ የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሟል፡፡ ዛሬ አራት ዲጂት ደመወዝ ምንም ማለት አልሆነም፡፡ ከችግር አያላቅቅም፡፡ ሰው ግን ኑሮውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና ማለቱን አላቋረጠም፡፡ በዚህ ሒደት ከሚገኙት የኅብረሰብ ክፍሎች መካከል አቶ ጌታቸው አበበና ወይዘሮ አልማዝ አሰፋ የተባሉ ባልና ሚስት ይገኙበታል፡፡

ጥንዶቹ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ነዋሪ ሲሆኑ፣ ሁለቱም የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው፡፡ በትዳር አብረው መኖር ከጀመሩ ከ15 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ በእነዚህም ዓመታት ውስጥ ሦስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ባልየው በወር የሚያገኙት የተጣራ ደመወዛቸው ከሁለት ሺሕ ብር በላይ ሲሆን፣ የሚስትየው ደመወዝ ደግሞ ከሁለት ሺሕ ብር ትንሽ ዘለል ይላል፡፡

የሚኖሩት የግለሰብ ቤት ተከራይተው ነው፡፡ ቤቱ በጣም ጠባብ የሆኑ ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡ በአንደኛው ክፍል የባልና ሚስቱ አልጋ ተዘርግቷል፡፡ ሌላው ክፍል ደግሞ ልጆቹ ማታ፣ ማታ ይተኙበታል፡፡ ቀን ቀን ደግሞ እንደሳሎን ያገለግላል፡፡ ዕቃ በዕቃ ላይ ተደርድሯል፡፡ ለመቀመጥና ለመነሳት ወይም ለመንቀሳቅስ ከተፈለገ ጠንቀቅ ብሎ መራመድ ግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ ድንገት በንክኪ ዕቃው ይናድና ይሰባበራል፡፡ ‹‹ይኼውልህ ለዚህች ቤት በየወሩ 1,500 ብር እንከፍላለን፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ መብራትና ውኃ በቆጠረ ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ሆኖ ደግሞ ውኃና መብራት አባከናችሁ እንበላለን፤›› አሉ ወይዘሮ አልማዝ ልጆቹ ያዘረከረኩትን ዕቃ እየሰበሰቡ፡፡

አቶ ጌታቸውም የአንደኛውን ልጅ ራስ በቀኝ እጃቸው እየደባበሱ ‹‹ለእኔ፣ ለባለቤቴና ለልጆቼ ከሰኞ እስከ ዓርብ ድረስ ለትራንስፖርት ብቻ በየቀኑ 26 ብር አወጣለሁ፡፡ የእኔ ደመወዝ የሚውለው እነዚህን ወጪዎችና የቤት ኪራይ በመሸፈን ሲሆን፣ ቀሪውን ጊዜ የምንግደረደረው በባለቤቴ ደመወዝ ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ 600 ብር ለ50 ኪሎ ጤፍ መግዢያ ይውልና የቀረውን እንደነገሩ እናደርገዋለን፡፡ የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ኑሮ ነው እያካሄድን ያለነው፡፡ የልጆች ትምህርት ቤት ወጪ፣ የምግብና የሌሎች ፍጆታ ዕቃዎችን ወጪ የመሸፈን አቅማችን ተሟጥጧል፤›› ሲሉ ምሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡

‹‹አኗኗራችን ከሞቱት በላይና በሕይወት ካሉት በታች ነው፤›› የሚሉት አቶ ጌታቸው ለእርሳቸውና ለባለቤታቸው አልባሳት መግዛት ካቆሙ ዓመታት እየተቆጠሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የልብስ አምሮታቸውን የሚወጡት ፒያሳና መርካቶ በሚገኙ ቡቲኮች ውስጥ “ዊንዶው ሾፒንግ” በማካሄድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ እንዴት ገላገለን መሰለህ? ዩኒፎርም ባይኖር ኖሮ በተማሪዎች መካከል የልብስ ውድድር ይፈጠራል፡፡ በዚህም የተነሳ ልጆቻችን ማስተማር አንችልም ነበር . . .” ብለው ሳይጨርሱ፣ ‹‹የሁለታችንም ደመወዝ ሊያኖረን አልቻለም፡፡ እስቲ እባክህ እንዲያው ለጌታቸው የፓርት ታይም ሥራ ፈልግለት፤›› ሲሉ ተማፅኖ አቀረቡ ወይዘሮ አልማዝ፡፡

ከአሥራ አምስት ዓመት በፊት የአቶ ጌታቸው ደመወዝ 600 ብር፣ የባለቤታቸው ደግሞ 200 ብር እንደነበር፣ በወቅቱም ገንዘብ ዋጋ ስለነበረው የምግብ ፍጆታቸውንና ሌሎች ወጪያቸን ችለው ባንክ የቁጠባ ሒሳብ እንደነበራቸው አስረድተዋል፡፡ ደመወዛቸውም እያደገና እየተሻሻለ ቢመጣም ኑሮው የዚያኑ ያህል እየከረረ መጥቶ አሁን መቋቋም ወዳልቻሉበት ደረጃ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ካለፈው ዓመት ወዲህ የምግብ፣ የትራንስፖርትና የአልባሳት ዋጋ አልቀመስ እያለ መምጣቱን ባልና ሚስቱ ይናገራሉ፡፡ በደህና ጊዜ ባንክ ያስቀመጡትን ገንዘብ እያወጡ ለችግራቸው ማቃለያ እንዳዋሉትም ይገልጻሉ፡፡ ‹‹አሁን ተቀማጭ ብሎ ነገር የለም፡፡ ደመወዝ መጣ ወዲያው እልም ይላል፡፡››

ቀደም ባሉት ዓመታት በክልል የሚገኙ ዘመዶቻቸውን በዓመት አንዴ እየሄዱ ይጐበኟቸውና አነስተኛ ገንዘብ በመስጠትም ይደጉሟቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ዛሬ ግን ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ድጐማውንና ጉብኝቱን እንዳቋረጡ ገልጸዋል፡፡

በክልል ካሉት ቀርቶ እዚሁ አዲስ አበባ ከሚገኙ ዘመዶቻቸው ጋር በዕለተ ሰንበት እንኳን ተገናኝተው እንደማያውቁ ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹ኢኮኖሚው የኅብረተሰቡን አንገት አስደፍቶታል፡፡ በዚህም የተነሳ እርስ በርስ ከመፈቃቀርና ከመረዳዳት ይልቅ ራስ ወዳድ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ሁሉም ኑ ቡና ጠጡ መባባልን እርግፍ አድርጎ ትቶ ቤቱን ዘግቶ መቀመጥና የኑሮ ውድነት ያስከተለውን ችግር እንደአመጣጡ ተቀብሎ መኖር ግድ ሆኖበታል፤›› ይላሉ አቶ ጌታቸው፡፡

ከከተማ ወጣ ብላችሁ እንደአቅማችሁ ቤት ተከራይችሁ ለምን አትኖሩም? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ይኼንን ጉዳይ አጥተነው አይደለም፡፡ ከከተማ ወጣ ካሉ የትራንስፖርት እጦት አለ፡፡ ትራንስፖርት ቢኖርም ዋጋው የትየለሌ ነው፡፡ እንኳን ወጣ ብለን መሀል ከተማ ሆነንም የትራንስፖርት ችግር በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤›› ሲሉ አቶ ጌታቸው መልሰዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ከሳቸው በታች ያሉትን ሰዎች አኗኗር ሲመለከቱ እንደሚጽናኑ፣ ቤተሰባቸው ጤነኛ መሆኑ ደግሞ እንደሚያረካቸው ተናግረዋል፡፡ ዛሬ እኮ ቢታመሙም ሕክምናውና የመድኃኒቱ ዋጋ ንሯል፡፡ ሐኪሙም በሽተኛውን የሚየየው ከሙያ አንጻር ሳይሆን ከቢዝነስ አንጻር እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ፡፡

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ከላይ የተጠቀሱት ዓይነት ታሪኮች የሚጋሩ በርካታ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጐች አሉ፡፡ ምናልባትም ከአሥር ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰምቶ የማያውቀው ‹‹ግሽበት›› የሚለው የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ ከላይ የተጠቀሱት ዓይነት የአገሪቱ ዜጐች ምሬት መገለጫ ሆኗል፡፡

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው የመጋቢት ወር የዋጋ ዕድገት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ35 በመቶ ጨምሯል፡፡ ይህ የዋጋ ንረት ባለበት ሁኔታ ደግሞ መንግሥት በሚቀጥለው በጀት ዓመት ከ117 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ለማድረግ አቅዷል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መንግሥት የታመመውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለማስተካከል ይረዱኛል ያላቸውን የተለያዩ የማክሮ ኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነቶች ተግብሯል፡፡ በያዝነው ዓመት መስከረም ወር ላይ የወሰደው የ20 በመቶ የብር ምንዛሪ ዋጋ ማስተካከያ፣ በፋይናንስ ተቋሞች ላይ የተወሰደው የቁጥጥር ዕርምጃና የሸቀጦች የዋጋ ተመን ዕርምጃዎች በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት ናቸው፡፡

ይኼው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ዳታ በ2008/2009 በኢኮኖሚው ላይ ተከስቶ የነበረው ከፍተኛ ግሽበት ተመልሶ ሊመጣ እንደሚችል የሚያሰጋ መሆኑን፣ በዚህም እያገገመ የነበረውን የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ደረጃ የሚዳክምበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ያመለክታል፡፡

ለግሽበቱ ዋና ምክንያት ነው በሚል ከሚያከራክረው የአቅርቦትና የፍላጐት አለመጣጣምና፣ በዓለም አቀፍ ገበያ የሸቀጦች ዋጋ መናርና የፊሲካልና የገንዘብ ፖሊሲ ችግር ለግሽበቱ ምክንያቶች ናቸው የሚለውን ሐሳብ መንግሥት ያጣጥለዋል፡፡ በኋላ ላይ ደግሞ ፖሊሲ አውጭዎቹ ፊታቸውን ወደ ገበያው በመመለስ የግሽበቱን ምክንያት ለማስረዳት ሞከሩ፡፡

የገበያ ውድድር አለመኖርና ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች በአንድንድ ሸቀጦች ላይ የሚጥሉት አግባብ ያልሆነ ዋጋ ለግሽበቱ ምክንያት መሆኑን የገለጹት እነኚሁ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ይረዳናል ያሉትን የዋጋ ተመን ተግባራዊ ቢያደርጉም ችግሩ ተባባሰ እንጂ ሊስተካከል አልቻለም፡፡ የዋጋ ተመን የተጣለባቸው አብዛኛዎቹ ሸቀጦች ከገበያ ጠፉ፡፡ ገበያ ላይ የሚገኙትም ዋጋቸው የሚቀመስ አልሆነም፡፡

በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የተጠላው የዋጋ ተመንም ምንም ውጤት ሳያስገኝ እንዲነሳ ተደረገ፡፡ የግሽበቱ ምንጭ ምንድነው? ግሽበቱን ያቀጣጠሉት ነገሮችስ ምንድናቸው? ከሚለው የፖሊሲ ክርክር ይበልጥ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ዋና መፍትሔ ምንድነው? የሚለው ጉዳይ ዋና መነጋገሪያ የሆነ ይመስላል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚታየውን ግሽበት በተመለከተ ፖሊሲ አውጭዎቹን ጨምሮ ማንም ትክክለኛ መረጃ የለውም፡፡ በጉዳዩ ላይ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፣ በግሽበት ላይ ትክክለኛ ፖሊሲ ለመቅረጽ ከተፈለገ መጀመሪያ የኢኮኖሚ መረጃው ጥራት ሊሻሻል ይገባል፡፡

መንግሥት በገበያ ላይ ያደረገውን ጣልቃ ገብነት እንደማሳያ የወሰዱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ፖሊሲ አውጪዎች አንድን ፖሊሲ ከማስፈጸማቸው በፊት ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት በግልጽ ሊረዱት እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

‹‹መረጃው አስተማማኝ እስካልሆነ ድረስ ስለትክክለኛ ፖሊሲ ማውራት አንችልም፤›› ያሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፣ በዚህ ረገድ በፓርላማና ገለልተኛ በሆኑ ባለሙያዎች ደረጃ ግሽበትን የሚከታተል ቡድን ቢቋቋም ጥሩ ነው፤›› የሚል እምነት አላቸው፡፡

ከዶክተር ቆስጠንጢኖስ በተቃራኒ ሌሎች ማክሮ ኢኮኖሚስቶችና መንግሥት የግሽበቱ ምንጭ ምንድነው በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ማብራሪያዎችን ይሰጣሉ፡፡ መንግሥት እንደሚለው ከሆነ የግሽበቱ መሠረታዊ ምንጭ የፍላጐት መጨመር ነው፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ በቅርቡ ለተወካዮች ምክር ቤተ በሰጡት ማብራሪያ በቅርቡ የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ከዓለም አቀፉ ዋጋ ጋር አያይዘውታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ቀደም ሲል በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰተው ግሽበት አንደኛው ምክንያት የዓለም አቀፍ ገበያ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ከፍላጐት መጨመር፣ ከውጭ ከሚገባው ምርትና የገበያ ውድድር ውጪ የመንግሥት “ፊሲካልና ሞኒተሪ” ፖሊሲዎች ግሽበቱ እንዲከሰት አስተዋጽኦ የላቸውም፡፡

ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፣ ግሽበቱ የተከሰተው ለቀረቡት ችግሮች ምላሽ የሚሰጥ ፖሊሲ ባለመኖሩ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት ከገጠመው የፖሊሲ ውድቀት ተምሮ ችግሮችን ለመቅረፍ ካልተሞከረ በስተቀር ግሽበቱ ይስተካከላል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ይናገራሉ፡፡

“ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፖሊሲ ስለቀረቡለት መላሽ የሚሰጥ ቢሆን ኖሮ የስኳር ፋብሪካዎችም ሆኑ የዘይት ፋብሪካዎችን ለማቋቋም ይህን ያህል ጊዜ አይወስድም ነበር፤” ያሉት አቶ ግርማ፣ ትንሽ የሕዝብ ቁጥር ያላት ኬንያ የዘይት ፋብሪካ እያላት ኢትዮጵያ አንድም ትልቅ የዘይት ፋብሪካ የሌላት መሆኑ የፖሊሲ ውድቀትን እንደሚያሳይ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ግርማ የሞኒተሪ ፖሊሲው ለግሽበቱ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለው ያምናሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት የብር የመግዛት አቅም በሁለት ምክንያቶች እየወደቀ መጥቷል፡፡ አንደኛው ተመጣጣኝ ምርት በሌለበት ከፍተኛ ብር ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ እንዲገባ በመደረጉ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሞኒተሪ ፖሊሲው ከሚፈቅደው ውጪ ገንዘብ እንዲታተም መደረጉ ነው፡፡

“ቀደም ሲል በነበሩት የኢትዮጵያ መንግሥታት ሞኒተሪ ፖሊሲው ከሚፈቅደው በላይ ገንዘብ አይታተምም ነበር፡፡ አሁን ግን ገንዘብ ይታተማል፤” ይላሉ ገበያ ውስጥ እየገባ ኑሮውን ያስወድዳል፡፡ ይህ ግን በምርት አይደገፍም፡፡ የዚያን ያህል ስኳር፣ የዚያን ያህል ጤፍ የዚያን ያህል ስንዴ የለም በማለት ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙም፣ ግሽበቱ የተከሰተው በመንግሥት “ፊሲካልና ሞኒተሪ” ፖሊሲ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት መንግሥት ወዲያውኑ ለኢኮኖሚው መልስ በማይሰጡ ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣት ከፍተኛ ግሽበትን እያስከተለ ነው፡፡ ከመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ወጪዎች ጋር ተያያዥ የሆኑ የሞኒተሪ ፖሊሲዎችም የግሽበት ምንጮች መሆናቸውን አቶ ሙሼ ይገልጻሉ፡፡

‹‹ከውጭ የሚመጣ ግሽበት የአገሪቱ የግሽበት ምንጭ ተደርጐ ሊወሰድ አይገባም፡፡ ከውጭ የሚመጣ ግሽበት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚከሰት አይደለም፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ጐረቤት አገሮችም ተመሳሳይ ችግር ሊገጥማቸው ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን አልገጠማቸውም፤›› ብለዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የኢኮኖሚ ባለሙያ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው ግሽበት ዋና ምንጩ ልቅ የሞኒተሪ ፖሊሲ ነው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ግሽበት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በራሱ የሞኒተሪ ፖሊሲ ክስተት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ እንደ አይኤምኤፍ ያሉ ሌሎች ተቋማትም ቢሆኑ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የገንዘብ ዕድገት ደረጃ ስጋት ያደረባቸው ይመስላል፡፡ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው የአይኤምኤፍ ልዑካን ቡድን የመንግሥት ድርጅቶች እየወሰዱት ያሉት ብድር እጅግ አንደሚያሳስበው ገልጿል፡፡

ከቀናት በፊት ከሪፖርተር ጋር ቃል ምልልስ ያደረጉት የኢኒሼየቲቭ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክቡር ገና ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተከሰተውን ግሽበት ለማስተካከል መተግበር ያለበት ፍቱን የፖሊሲ ጣልቃ ገብነት ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

አቶ ሙሼና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የኢኮኖሚ ባለሙያ ግን በአንድ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ መንግሥት የአፈጻጸም ችግር አለበት በሚለው፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያው እንደሚሉት ዋናው ችግር የፖሊሲ እርስ በርሱ መጣረስ ነው፡፡ ‹‹አብዛኛዎቹ ተግባራዊ የሚደረጉ ፖሊሲዎች እርስ በርስ የሚጣጣሙ አይደሉም፤›› በማለት የሚተገበረው ፖሊሲ በጥቅሉ ውድቀትን እንደሚያስከትል ያስረዳሉ፡፡

በቅርቡ ፖሊሲ አውጪዎች ለግሽበቱ መንስዔ ነው ብለው ያስቀመጡት የዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ መሆኑንም እኚሁ ባለሙያ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በውጭ ተፅዕኖ ተከሰተ የሚባለው ግሽበት አስተዋጽኦ ከ10 በመቶ የሚበልጥ አይደለም፤›› በማለት፣ ፖሊሲ አውጪዎቹ ለችግሩ እየፈለጉት ያለው መፍትሔ የገንዘብ አቅርቦት ማስፋፋትን ይመስላል፤ ይህም የፖሊሲዎችን መጣረስ ያሳያል ብለዋል፡፡ አክለውም ምንም እንኳን ከዓለም አቀፍ ገበያ የሚመጣው ግሽበት ለአገር ውስጥ የዋጋ ግሽበት ምክንያት ቢሆንም፣ መፍትሔ ተብሎ የቀረበው የገንዘብ አቅርቦትን ማስፋፋት ግን ከውጭ ግሽበት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ያስረዳሉ፡፡

ይህንን ሲያብራሩም በያዝነው ዓመት ተግባራዊ የተደረገው የ20 በመቶ የብር ምንዛሪ የመግዛት አቅም መቀነስ በዚህ ረገድ ያለውን የፖሊሲ ተለዋዋጭነት እንደሚያሳይ ጠቁመዋል፡፡

በአገሪቱ የተከሰተው ግሽበት እየተባባሰ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከ117 ቢሊዮን ብር በላይ ለመጠቀም መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት የበጀት መጨመር ከግሽበት ጋር የሚያያዘው ነገር የለም፡፡ ይህንን አመለካከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ፖለቲከኞችና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይጋሩታል፡፡

ሚካኤል መላኩ የተባሉ ሌላ የኢኮኖሚ ባለሙያ እንደገለጹት፣ የበጀቱ የፋይናንስ ምንጭና አመዳደቡ በግሽበት ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ ከተመደበው በጀት ጋር በተያያዘ የሚያሳስቧቸው ጉዳዮች ያለ መሆኑን የገለጹት አቶ ሚካኤል፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታ የተያዘው ከፍተኛ በጀት በአጭር ጊዜ ውስጥ በግሽበት ላይ የራሱን ጫና ሊያሳድር ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ሙሼም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት መሠረተ ልማት አስፈላጊ ቢሆንም በራሱ ዕድገት አይደለም፡፡ ‹‹[መሠረተ ልማት] ወደፊት ካልሆነ በስተቀር አሁን በሸቀጦች አቅርቦት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አይፈጥርም፤ በመሆኑም እየተባባሰ በመጣው ግሽበት ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ ሊሆን ይችላል፤›› በማለት መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኢኮኖሚ ምላሽ በማይሰጥ የመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ከፍተኛ ወጪ ማውጣት እንደሌለበት ያስገነዝባሉ፡፡

ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች በአንድ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ለግሽበቱ አንድ መፍትሔ ካልተበጀለት በስተቀር አስቸጋሪነቱ በይበልጥ እየተወሳሰበና እየከረረ እንደሚሄድ ያስገነዝባሉ፡፡

(በዚህ ዘገባ ኃይሌ ሙሉ፣ አስራት ሥዩም፣ ታሰደ ገብረ ማርያም፣ ውድነህ ዘነበና ምህረት አስቻለው ተሳትፈዋል)

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 26, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.