የወጪ ምንዛሪ አለቀ- ብሔራዊ ባንክ አስቸኳይ ድጋፍ ጠየቀ

7 ጃንዋሪ 2009 –የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገሪቱ ለተከሰተው የወጪ ምንዛሪ እጥረት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የአስቸኳይ ጊዜ የብድር ድጋፍ የሚያገኝበትን እና ለጋሽና አበዳሪ አገራት ቃል የገቡትን ገንዘብ በወቅቱ በሚሰጡበት ሁኔታ ላይ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ከሪፖርተር ጋዜጣ ለቀረቡለት ጥያቄዎች በፅሑፍ በሰጠው ምላሽ እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ የተከሰተውን የውጪ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የተለያዩ እርምጃዎችንም እየወሰደ ነው፡፡

“እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገራት የውጭ ምንዛሪ እጅግ ውስን ከሆኑ ሐብቶች አንዱ ነው” ያለው ብሔራዊ ባንክ አገሪቱ ከወጪና ከአገልግሎት ዘርፍ ንግድ፣ እንዲሁም ከሐዋላ የምታገኘው ገቢ እያደገ የመጣ ቢሆንም በዓለም ላይ በተከሰተው የሸቀጦች ዋጋ መናርን ተከትሎ ለነዳጅ፣ ለማዳበሪያ፣ ለኮንስትራክሽንና ለሌሎች አስፈላጊ የጥሬና የካፒታል ዕቃዎች የሚወጣው ከገቢ ንግዱ ከሚገኘው በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ምክንያት በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ላይ ጫና ፈጥሯል ብሏል፡፡ የተፈጠረውን ጫና ለመቋቋምና የውጭ ምንዛሪ ግኝት የሚጠናከርበትን መንገድ ለመሻት በመንግሥት በኩል ጥረት እየተደረገ ነው ብሏል፡፡

ከውጭ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ የማበረታቻ እርምጃዎች መወሰዳቸውን፣ ከአበባ ንግዱ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ በተጨማሪም ውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ የዓለም አቀፍ ሐዋላ አላላክ በተመለከተ መመሪያ መሻሻሉን፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጭ ዜጎች በአገር ውስጥ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ እንዲከፍቱ የሚፈቀድ መመሪያ መውጣቱ ባንኩ እየወሰዳቸው ካሉት ርምጃዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡

ባንኩ አያይዞም በቅርቡ የተለያዩ አገራትን ልምድ በማጥናት ውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና በትውልድ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ የውጭ አገር ዜጎች ብቻ በውጭ ምንዛሪ የሚሸጥ ቦንድ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ኮርፖሬሽን በኩል እንዲሸጥ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን፣ አበዳሪና ለጋሽ ድርጅቶች ቃል የገቡት ገንዘብ በወቅቱ እንዲመጣ፣ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትም የአስቸኳይ ጊዜ የብድር ድጋፍ የሚሰጥበት ሁኔታ ለማመቻቸት በመንግሥት በኩል የተጠናከረ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገል”ል፡፡

በ2001 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ወደ አገር ውስጥ የገቡ የሸቀጦች ዋጋ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ61.4 በመቶ መጨመሩን የገለፀው ብሔራዊ ባንክ ይሁን እንጂ አገሪቱ የምትፈልጋቸውን የኢንቨስትመንት፣ የፍጆታ ሸቀጦችንና ጥሬ ዕቃዎችን በበቂ መጠን ለማስገባት በሚቀጥሉት ወራት ከወጪ ንግድ፣ ከሐዋላ፣ ከዕርዳታና ብድር የሚሰበሰበው የውጭ ምንዛሪ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብሏል፡፡ በተለይ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የማፍራት አቅም የሚጐለብትበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከሚወሰዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች በተጨማሪ ለወደፊቱ በጥናት ላይ የተመሰረቱ የገንዘብና የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት ዝግጁ መሆኑን ባንኩ በፅሑፍ ከላከው መልስ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ምንጭ: ሪፖርተር

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 7, 2009. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.