የወያኔ የዋጋ ተመን ምንነትና ለምንነት:ታደሰ ብሩ

የወያኔ የዋጋ ተመን ምንነትና ለምንነት

“ሰባራ ዜና” እንደ “ሰበር ዜና”

ሥጋ በኪሎ 52 ብር እንዲሸጥ ተወሰነ!!!

ይህ ዜና ምን ስሜት ፈጠረባችሁ? እንደምሰማው ከሆነ ዜናው ብዙ ሰዎችን አደናግሯል። አንዳንዶች “የተለመደ የወያኔ ማጭበርበሪያ ነው” በማለት ሲያጣጥሉት፤ ሌሎች ደግሞ “ዘገየ እንጂ መልካም ተግባር ነው” ሲሉ አወድሰውታል።

ለእኔ ዜናው ሰባራና አስቂኝ ነበር። አሁን ይህንን ማስታወሻ ስጽፍም እየሳቅኩ ነው። ያም ሆኖ ግን አንዳንዶች በዚህ ዜና መደሰታቸው ገርሞኛል፤ አስግቶኛልም። “ለካስ እኛ እንዲህ በትንሽና በማይመስል ነገር የምንታለል ነን?” እንድል አድርጎኛል። ይህንን ማስታወሻ እንድጽፍ ያነሳሳኝ አንዱ ምክንያትም ይኸው ስጋት ነው። እንዴት ይኸ ሰባራ ዜና ደህና ነገር ያመጣል ተብሎ ይታሰባል?

“ነገር በምሳሌ …” እንዲሉ አስተያየቴን በምሳሌ ላስረዳ። አማካይ ክብደት ያለው ሠንጋ በሬ 5000 ብር እየተሸጠ ባለበት ሰዓት አንድ መወደድ የፈለገ ሹም “ከዛሬ ጀምሮ የአንድ በሬ ዋጋ 3000 ብር ነው” ብሎ አወጀ እንበል። መቸም በሬዎች ሁሉ እኩል አለመሆናቸው ለመረዳት አይቸግረንም። ሻጩም ገዢውም ይህንን ያውቃሉ። እናም አዋጁ እንደወጣ ሰዎች ምን እንደሚያደርጉ ለመገመት አያዳግትም። ሸማቹ አዋጁ እንደወጣ ተሯሩጦ ትልልቁን በሬ በ3000 ብር ይሸምታል። ይህ መብት ለሻጭ የተነፈገው ካልሆነ በስተቀር ሻጭም የራሱን በሬ በ3000 ብር መግዛት ያዋጣዋል (ይህ እንግዲህ “በሬ የመደበቅ ወንጀል” የማያሳስር ከሆነ ነው)። ጥቂት እድለኛች ተሯሩጠው ትላልቅ በሬዎችን በርካሽ መግዛት ይችሉ ይሆናል። ከትንሽ ጊዜ በኋላ ግን ገበያው አዲሱን ሥርዓት ይለምዳል። ትልልቆቹ ተሸጠው ያልቃሉ። ትንንሾቹ ደግሞ ከባለ 3000 ዎቹ በላይ እንዲደልቡ (እንዲወፍሩ) ገበያው አይፈቅድላቸውም። አዋጁ ባይኖር ኖሮ 1000 ብር ያወጣ የነበር ጥጃ ዛሬ 3000 ብር ስለተለጠፈበት ብቻ የሚገዛው ያገኛል ማለት አይደለም (ይህ እንዲሆን ሻጭን ብቻ ሳይሆን ገዢንም ማስገደድ ይጠይቃል)። አዲሱ ሥርዓት ሲለመድ ወደ ገበያ የሚመጡት በሬዎች ድሮም ቢሆን በ3000 ብር ሲሸጡ የነበሩት ዓይነት ብቻ ይሆናሉ። በሌላ አነጋገር በገበያ ውስጥ የምናያቸው በሬዎች እንደፋብሪካ እቃ ተመሳሳይ ይሆናሉ ማለት ነው። ማን ተጎዳ? ከረጅም ጊዜ አኳያ ከታየ ሻጭም ገዢም ሁሉም ተጎጂዎች ናቸው። የገበያ ኢኮኖሚ አንዱ ውበት አማራጮችን ማብዛቱ ነው። ዋጋ ስንወስን የጥራት አማራጮችን እናጠፋለን።

ለመሆኑ ምሳሌዬ ሊሆን የሚችል ነገር ነው? አስቸጋሪነቱ ግልጽ ቢሆንም በጭራሽ አይሆንም ብዬ አልከራከርም። የአላሙዲኑ ኤልፎራ፣ ዶሮዎች ላይ ይህንን ማድረግ ችሏል። በኤልፎራ ዶሮዎች መካከል እጅግም ልዩነት ስለሌለ ገዢዎች ሳይከራከሩ በውስን ዋጋ ይገዛሉ። በዶሮ የሆነው በበሬ ይሆናል?

አንዳንድ ሰዎች የዋጋ ቁጥጥር ያለና ወደፊትም የሚኖር በመሆኑ አዲስ ነገር እንዳልሆነ ይከራከራሉ። እውነታቸውን ነው። ነገር ግን ዝርዝር ውስጥ ገብተው የዋጋ ቁጥጥር መቸ፣ እንዴትና በምን ዓይነት ሸቀጦችና አገልግሎቶች ላይ ሊሆን እንደሚገባው መተንተን አይፈልጉም። በተለይም ደግሞ አሁን ተመን የተደረገባቸውን ሸቀጦች ባህርይ በመተንተን ስለ ተመኖቹ የረዥም ጊዜ ጠቀሜታና ተፈፃሚነት ማብራሪያ ሲሰጡ አላጋጠመኝም። ችግሩ ደግሞ ያለው ዝርዝር ውስጥ ሲገባ ነው። ለኤልፎራ ዶሮዎች የሆነው ለሀረርና ጅማ ሠንጋዎች ላይሆን ይችላል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የገበያ ኢኮኖሚ አይደለምና ለአስተዳደራዊ ዋጋዎች አዲሶች አይደለንም። በአገራችን የመብራት፣ የውሃ፣ የስልክ፣ የፓስታ አገልግሎች …. ዋጋዎች በገበያ ኃይሎች ተወስነው አያውቅም። ሸማች በእነዚህ አገልግሎቶች ዋጋ ላይ ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖ የለውም። [በነገራችን ላይ የካ ክፍለ ከተማ ባለው የቴሌ ሂሳብ መቀበያ ቢሮ ውስጥ “ደንበኛ ንጉሥ ነው!!!” የሚል በትላላቅ ፊደላት የተፃፈ ጥቅስ አለ። ንጉሥነት ቀርቶ በቴሌ ዓይን ለሎሌነት እንኳን እንዳልበቃን ምርጫ 97 አሳይቶናል። በዚያ ወቅት መስማት የተሳናቸው ዜጎች SMS እንዳይዘጋ ለምነው ምላሽ አጥተዋል። መብራት ኃይል ሲያሻው “የዘወትር አገልጋያችሁ የሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና መብራት ኃይል …..” እያለ መብራት እንደሚቋረጥ ይነግረናል። በ97 ከሚያዝያ 30 በኋላ ቅንጅት ስብሰባ በጠራባቸው ቦታዎች ሁሉ መብራት ይጠፋ እንደነበርም መረሳት የለበትም። በእንዲህ ዓይነት የተዛባ ሥርዓት ደንበኛ ንጉሥ ሳይሆን ባሪያ ነው።]

ወደ ሰባራው ዜና ልመለስ። እኔ የሥጋ ብልቶችን አላውቅም። ሆኖም ግን “በሥጋዎች” መካከል ያለው ልዩነት በበሬዎች መካከል ካለው ልዩነት የሰፋ እንደሚሆን እገምታለሁ። ሉካንዳ ቤቶች ብዙ የሥጋ ደረጃዎች እንደሚኖራቸው አልጠራጠርም። የክትፎ ሥጋ 90 ብር በነበረበት ጊዜም 52 ብር ይሸጡት የነበረ የሥጋ ዓይነት አይጠፋም። አዲሱ የዋጋ ተመን ከሠራ (ያውም ከሠራ ነው) የምንሸምተውን የሥጋ ጥራት ድሮ 52 ብር ይሸጥ ወደነበረው ደረጃ መውረዱ የማይቀር ነው።

ሌላው አማራጭ ደግሞ እንደ ቴሌ አይነት የመንግሥት ድርጅት አቋቁሞ ሥጋን የመቸርቸርን ኃላፊነት መስጠት ነው። ይህ ደግሞ የሸማቾችን ባርነት ጎትቶ ያመጣል። [በ97 እንደ ቴሌና መብራት ሁሉ የሥጋ እደላ በመንግሥት እጅ ቢሆን ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር?]

ከላይ ስለ ሥጋ የተባለው ሁሉ ሩዝም ላይ ይሰራል። ከሃያ በላይ የሩዝ አይነቶች ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ እንዳሉ (ወይም እስከ አዋጁ እለት እንደነበሩ) ተነግሯል። አዲሱ ህግ በትክክል ሥራ ላይ ከዋለ የሩዝ ዓይነቶች ምርጫ “ተረት” ይሆናል።
ስለ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ጥራት
ለሁሉም ነገር የጥራት ደረጃ አለው። የአንድ ሸቀጥ ወይም አገልግሎት እሴት የሚወስነው ደግሞ በጥራት ደረጃው ነው።

“ሩጫ ምን ማለት ነው?” ቢባል “ሩጫ በፍጥነት መራመድ ማለት ነው” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። “ፍጥነት” የጥራት መለኪያ ነው። በዚህ የጥራት መለኪያ የተለያዩ “መራመዶች” እጅግ የተለያዩ ደረጃዎች፤ በዚህም ሳቢያ እጅግ የተለያዩ እሴቶች /values/ አሏቸው። ዘገምተኛው መራመድ “በጎታታነት” ሲያሰድብ፤ ፈጣኑ መራመድ ደግሞ ዋንጫ ያስገኛል፤ ሚሊዮን ያሸልማል፤ ጀግና ያስብላል። ሁለቱ “መራመዶች” ገበያ ቢወጡ በገበያ ዋጋዎቻቸው መካከል የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ሊኖር ይችላል። በጩኸትና በዘፈን መካከል ያለውም ልዩነትም የጥራት ልዩነት ነው። ጩኸት ሊያሳምም ይችላል፤ ዘፈን ግን ይፈውሳል። እንዲህ ዓይነት በርካታ ምሳሌዎችን መዘርዘር ይቻላል። ጥራት ልፋትን ይጠይቃል። ጥራት ለሥራ ክብር መስጠትን፤ ለሸማች መጨነቅን፤ ቃል ማክበርን ይጠይቃል።

በአገራችን ያለውን የትምህርት (በተለይም የከፍተኛ ትምህርት)፣ የጤና አገልግሎት፣ የመንገዶችንና የከተማ ህንፃዎች አሰራር ላስተዋለ ወያኔ ያለበትን የጥራት ግንዛቤ ጉድለት የቱን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ይገነዘባል። የሰሞኑ የዋጋ ትመናም “ጥራት” የተሰኘው ጽንሰሃሳብ በወያኔ ፓሊሲ አውጪዎች (ፖሊሲ ካልነው ማለት ነው) ጭንቅላት ውስጥ አለመኖሩ ያሳየናል። ስለዚህም ነው በነሱ ጭንቅላት ውስጥ ሥጋ ሁሉ አንድ ዓይነት፤ ሩዝ ሁሉ አንድ ዓይነት፤ ደብተር ሁሉ አንድ ዓይነት፤ ሻይ ቅጠል ሁሉ አንድ ዓይነት ሆኖ የታያቸው።
ስለ “ስግብግብ” ነጋዴዎች
በሰሞኑ ዜና መነሻነት የኢትዮጵያ ነጋዴዎች የተለየ የስግብግነት ባህርይ አላቸው የሚሉ በርካታ አስተያየቶችን አንብቤዓለሁ። ለምን የኛ ነጋዴዎች እንዲህ ዓይነቱን ባህርይ እንዳዳበሩ ለማብራራት የሞከረ ግን አላጋጠመኝም።

የወያኔ ካድሬ በስነምግባር ጉድለት ነጋዴን ሲከስ መስማት የሚገርምም፤ የሚያሳዝንም ነው። ማን ማንን ነው በስነ ምግባር ጉድለት የሚከሰው? ነጋዴውስ ምን እንዲሆን ነው የሚጠበቅበት?

“በገበያ ኢኮኖሚ ነጋዴው የስነ-ምግባር ተገዥ እንዲሆን አይጠብቅበትም። የራሱን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነጋዴ መኖር ለገበያ ኢኮኖሚ በቂ ነው” እያለ አጥብቆ የሚከራከር፤ እኔ የሱን ሃሳብ ስለምቃወም “ቢዝነስንና በጎ-አድራጎትን ታምታታለህ” የሚለኝ ጓደኛ ነበረኝ፤ መከራከሩን ተውነው እንጂ አሁን አለ። ለኢኮኖሚክስ ተማሪዎች የእሱን ክርክር መረዳት አዳጋች አይሆንም።

መሠረታዊው የኢኮኖሚክስ ቲዎሪ እንዳለ ሆኖ ቢዝነስ (ቢያንስ እኔ በምረዳው መንገድ) ከፍተኛ ስነምግባር የሚጠይቅ ማኅበራዊ ተግባር ነው ብዬ አምናለሁ። እኔ ከዚህም በላይ እሄዳለሁ። ንግድ (ቢዝነስ) ሰውን ትሁት ያደርጋል ብዬ አምናለሁ። ንግድ ደንበኛን (በዚያው ሰውን) ማክበርን ያስለምዳል። ትዕቢተኛ ሰው ነጋዴ መሆን አይችልም። እንዲህ በማመን የመጀመሪያው ሰው አይደለሁም፤ የመጨረሻም አልሆንም። ሁለት የቆዩ ጥቅሶችን እዚህ ጋር እንዳስገባ ይፈቀድልኝ።

Commerce …softens and polishes the manner of men.[1]

It is almost a general rule that wherever manners are gentle, there is commerce; and wherever there is commerce, manners are gentle.[2]

ለእኔ ቴሌና መብራት ኃይል ነጋዴዎች አይደሉም ማለትም የቢዝነስ ኮርፓሬሽኖች አይደሉም። ለእኔ አላሙዲንና የወያኔ “ነጋዴዎች” ነጋዴዎች አይደሉም። ስለ ስግብግብ ነጋዴዎች ስናወራ እነማንን ማለታችን እንደሆነ ግልጽ መደረግ አለበት። የምንናገረው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ስለተቆጣጠሩት ሰዎችና ተቋማት ከሆነ ከስማቸው በስተቀር በሃሳቡ ስለምስማማ ይህንን ነጥብ እዚሁ እጨርሳለሁ። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የተቆጣጠሩት የወያኔና የአላማሙዲን ድርጅቶችና ሰዎች መሆናቸው የማያከራክር ጉዳይ ነው። እነሱ ዘራፊዎች እንጂ ነጋዴዎች አይደሉም። እነሱ የቢዝነስ ብቻ ሳይሆን ምንም ዓይነት ስነ- ምግባር የላቸውም። የምንናገረው ስለ ነጋዴዎች ከሆነ ግን የኢትዮጵያ ነጋዴዎች አሁን ተጋንኖ የሚነገረውን ያህል የጎላ የስነ-ምግባር ችግር አለባቸው ብዬ አላምንም።

እርግጥ ነው በመላው ማኅበረሰባችን ውስጥ እየደረሰ ያለው የስነምግባር መሸርሸር ነጋዴውን መንካቱ የማይቀር ነው። ውሸታም ጳጳስ፤ ውሸታምና ፈሪ “ሽማግሌ”፤ ለሞባይል ቀፎ የመንግሥትን በጀት የሚያጭበረብር የፀረ-ሙስና ኮሚሽነር ባለበት አገር “በገዛሁበት ነው የምሸጥልዎ” እያለ ጥቂት ሳንቲሞችን የሚያጭበረብር ባለሱቅ መኖሩ ለምን ይገርመናል? ይህ የሚያመለክተው በስነምግባር ረገድ ብዙ መሥራት እንደሚኖርብን ብቻ ነው። በአንፃራዊ መልኩ ከታየ ግን በስነምግባር ረገድ የንግዱ ማኅበረሰብ ሰርቶ፣ ለፍቶ፣ ጥሮ በራሱ ጉልበትና ላብ ፍሬ የሚያድር፤ ለሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች አርዓያ መሆን የሚችል ነው።

ይሁን እንጂ የወያኔ ሹማምንት ስለነጋዴዎች ስግብግብነት ሲያወሩ የገዛ ራሳቸውን ወይም በየቢሮው የሰገሰጓቸውን ሹሞቻቸውን ወይም በኮንትሮባንድ የተሰማሩትን የጦር መኮንኖቻቸውን እያሰቡ አይደለም። በስግብግብነት እየተወነጀሉ እየተዘጉ ያሉትም የችርቻሮ ሱቆች ናቸው። “ሩዝ ኪሎው በብር 12.50 ገዝተህ ኪሎው በብር 12.50 ሸጠህ አትርፍ” ተብለው ይህን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበትን ጥበብ ገና ስላላገኙ ስግብግብ ተብለው ብዙ ሱቆች ተዘግተዋል።

ፓሊሲ አውጪዎቹ እና ኢኮኖሚክስ
የወያኔ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ ደንበኛ በሆኑበት ሆቴል የታዘቡትን “ህገወጥ” የዋጋ አጨማመር በምሳሌነት ተጠቅመው የሰጡት ገለፃ አስቂኝ ነው። እንደሚኒስትሩ ገለፃ የቅቤ ዋጋ መጨመር ቅቤ ባልገባባቸው ምግቦች ዋጋ ላይ ተጽዕኖ ማምጣት የለበትም[3]። እንደሳቸው አገላለጽ በክትፎ ዋጋ ላይ የሚመጣ ለውጥ በሌሎች የምግብ ዓይነቶች ላይ ምንም ተፅዕኖ የለውም። ሌላ ምሳሌ ብወስድ “በኮካኮላ ላይ የሚመጣ የዋጋ ለውጥ ፒፕሲን ምን አገባው?” እያሉን ነው። ሰውየው ምን ዓይነት ኢኮኖሚክስ እንደተማሩ እግዜር ይወቀው። ገበያ ሸቀጦችን በተለያዩ መንገዶች የሚያያይዝ መሆኑ የአንደኛ ዓመት ኮርስ ነው።

ይህን አፍረን እንለፈው ብንል እንኳን ሌላም ግዙፍ ስህተት አለ። እንደሳቸው ገለፃ ከሆነ የሸቀጦችና አገልግሎቶች የገበያ ዋጋ የሚወሰነው ሸቀጦቹን ወይም አገልግሎቶቹን ለማምረት በወጣው ወጪ ነው። ይህ በግልብ ሲታይ እውነት ቢመስልም በጣም የተሳሳተ ኢኮኖሚክስ ነው። የገበያ ዋጋን በማምረቻ ወጪ ማሰብ አቅርቦት /supply/ ላይ ብቻ ያተኮረ ግማሽ ኢኮኖሚክስ ነው። ኢኮኖሚክሱን ሙሉ ለማድረግ እሸማቹ ኪስ ውስጥ ያለው የገንዘብ ብዛት ማሰብ ይጠይቃል። በሌላ አገላለጽ ፍላጎትን /Demand/ እና የገንዘብ የመግዛት አቅምን እሂሳብ ውስጥ ማስገባት ግድ ነው። የሸቀጦችና አገልግሎቶች የገበያ ዋጋ የሚወስኑት ሸቀጦቹን ለማምረት በወጣው ወጪ ብቻ ሳይሆን በየሰው ኪስ ውስጥ ባለ የወረቀት ገንዘብ ብዛት ጭምርም ነው። ገበያ ውስጥ የወረቀት ገንዘብ እየበተኑ ነጋዴው ዋጋ ጨመረ ብሎ መውቀስ የሚያሳፍር ነው። ለብሄራዊ ባንክ የወረቀት ብተና ገበያ የሚሰጠው ምላሽ በዋጋ ላይ የሚጨመሩ ቁጥሮች መሆኑ እንዴት ሳያውቁ ቀሩ? ይህ የሶስተኛ ዓመት ኮርስ ነው።
የፓሊሲው ቀዳዳዎች
ፓሊሲው ብዙ ቀዳዳዎች እንዳሉት ካሁኑ እየታየ ነው። አንዳንዱን ቶሎ ቶሎ አንስቼ ልለፍ።

  1. ምርጥ ሥጋ መግዛት ከፈለጉ ለወንበር አሊያም ለአዋዜ ብለው ጠቀም ያለ ገንዘብ ይክፈሉ፤
  2. ጥራት ያለው ሩዝ ከፈለጉ ሩዙን ለሚይዙበት ፌስታል ጠቀም ያለ ዋጋ ይክፈሉ፤
  3. ራሳቸው ወያኔዎቹ ጥራት ያለው ሸቀጥ ይፈልጋሉና ሱፐር ማርኬቶች እንደ “ባለኮከብ” ሆቴሎች ተቆጥረው ከተመን ነፃ እንዲሆኑ የቀረበው “አቤቱታ” ተቀባይነት ማግኘቱ አይቀርም እናም አቅሙ ካልዎት የሚፈልጉትን እቃ ሱፐር ማርኬት ሂደው ይግዙ፤
  4. ረሃብ ቀጠሮ የማይሰጥ ስለሆነ “ይታገሱ” ልልዎት አልችልም እንጂ ይኸ ፓሊሲ ከጥቂት ወራት በኋላ ጨርሶ መረሳቱ የማይቀር መሆኑን አይዘንጉ።

እዚህ ላይ አጽንዖት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ታሪፉ ተፈፃሚ እንዲሆን የሌሎች በርካታ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ዋጋ መወሰን እንዳለበት ነው። አለበለዚያ “ቀዳዳው” ብዙ ነው። በተለይም ኪራይና ምንዳ (wage) ካልተስተካከሉ ታሪፉን ለማስፈፀም ምን ያህል እንደሚያዳግት ለማወቅ ከወር በላይ የሚፈጅ አይመስለኝም፤ የእነሱን ዋጋ መወሰን ደግሞ አረንቋ ውስጥ መግባት ነው። የገዛ ራሱን ኪስ ስለሚጎዳበት ወያኔ የኪራይ ዋጋን ለመወሰን የሚሞክር አይመስለኝም።
“ፓሊሲው” ለምን? ለምን አሁን?
በመጨረሻ ላነሳ የምፈልገው ጉዳይ ወያኔ ይህንን ፓሊሲ ለምን ፈለገ? ለምንስ አሁን ፈለገው? የሚሉትን ጉዳዮችን ነው:: ለእነዚህ ጥያቄዎች ፈጣንና አጭር ምላሽ ለመስጠት አራት ነጥቦችን ማንሳት ይበቃል ብዬ አምናለሁ።

  1. ግቡን ያልመታው የብር ምንዛሪ ምጣኔ ቅናሽ “እፍርት” ለመሸፈን፤

የብር ምንዛሬ በድንገት እንዲቀንስ በተደረገ ሰሞን “ቆራጡ” እርምጃ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚያመነጥቅ ገለፃ ሲሰጥ ነበር። የሚገርመው ልክ እንዳሁኑ የቅቤና ሌጣ ምግቦች ምሳሌ ሁሉ ያኔም የምንዛሪው ለውጥ በገቢ እቃዎች ላይ ካልሆነ በስተቀር ሌሎችን ሸቀጦች አይነካም ተብሎ ነበር። ገበያው አልታዘዝ ስላለ ሰበብ መፈለግ አስፈላጊ ሆነ።

  1. የትራንስፎርሜሽን መፈክር ባልተጠበቀ ፍጥነት መወየብ ያመጣው መደናገጥ፤

ከዚህ በፊት “የመፈክር ኢኮኖሚ” በሚል አጭር ጽሁፍ እንደገለጽኩት የወያኔ ኢኮኖሚ የመፈክር ኢኮኖሚ ነው። የመፈክር ኢኮኖሚ መፈክሩ ሲሰቀል ይሟሟቅና መፈክሩ ሲወይብ እንዘጭ ይላል። የትናንስፎርሜሽን መፈክር ሳንጠግበው መወየብ ጀመረ። ስለሆነም ካሁኑ እቅዱ ያልተሳካባቸውን ምክንያቶች ማዘጋጀት ያስፈልጋል። አዲሱ ፓሊሲ “ስግብግብ ነጋዴ” የሚባል ምናልባትም “ነፍጠኛን” የሚተካ መደብ ፈጠረ።

  1. የቱኒዚያ ክስተት የፈጠረው መረበሽ፤

የቱኒዚያው ሃቅ መለስንና ማፍያ ቤተሰቡን ቢያሸብር ምንም ሊገርመን አይገባም። የንግድ ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ እንደገለጹት “የቱኒዚያው ችግር እዚህ እንዳይደገም” ብለው “የሱሪ በአንገት” ፓሊሲ ነደፉ።

  1. አጀንዳ ማቀበል፤

ወያኔ እንደተለመደው አንድ አጀንጃ አቀብሎን እኛ አጀንዳ ላይ ስንራኮት እሱ አገር የመበትን ሥራዉን ያቀላጥፋል።

  1. እርስ በርስ ማጋጨት፤

ከሁሉም በላይ ዋነኛው ምክንያት የምለው ይህ ነው። ወያኔ በተገኘው መንገድ ሁሉ ከፋፍሎን እርስ በርስ ሲያጣላን ኖሯል። በዘርና በሃይማኖት የማጣላቱን ሴራ የተመኘውን ያህል ባይሆንም ጥሩ ውጤት አምጥቶለታል። አሁን ደግሞ የሥራ ዘርፍ አንዱ የመከፋፈያ መንገድ ሆኖ ቀርቧል። ወደፊት ደግሞ ምናልባት ወጣትና ጎልማሳ፤ ወንድና ሴት ለያይቶ ያጣላን ይሆናል።
ማሳረጊያ
ወያኔ እስካሁን ከተዋጣለት ነገሮች አንዱ በየጊዜው ኢትዮጵያዊያንን እርስ በእስ ማናከስ መቻሉ ነው። አማራና ኦሮሞ፤ አፋርና ሶማሌ-ኢሳ፤ ስልጤና ጉራጌ፤ አኝዋክና ኑዌር …. እስላምና ኦርቶዶክስ፤ ኦርቶዶክስና ፕሮቶቴስታንት፤ ፕሮቴስታንትና ፕሮቴስታንት፤ ኦርቶዶክስና ኦርቶዶክስ፤ እስላምና እስላም … ወያኔ በተገኘው ስንጥቅ ሁሉ እየገባ እርስ በርስ አናክሶን ተንሰራፍቶ ለመግዛት ችሏል። አሁን ደግሞ የመንግሥት ሠራተኛንና ነጋዴን ለማጣላት ቆርጦ ተነስቷል።

አንዳንድ ሰዎች ወያኔ በፈጠረው የኑሮ ችግር እጅግ በመጎዳታቸው መፍትሄ የተባለ ነገር ሁሉ ቢሞክር “ይሠራ ይሆናል” የሚል ባዶ ተስፋ የሚሳድሩ ሆነዋል። ወያኔ ደግሞ የህዝባችንን ተስፈኛነትና የዋህነት ለራሱ ጥቅም ያውለዋል። ትግላችን ውጤት እንዲያፈራ ወያኔ በሚሄበት መንገድ ሁሉ እየተከታተልን፤ የተንኮል ሴራዎቹን ማጋለጥ መቻል አለብን። ሰባራ ዜናዎችን “ሰበር ዜና” ማለትን መተው መቻል አለብን።

ከዚህም በተጨማሪ በየጊዜው በሚወረወሩልን አጀንዳዎች ሳቢያ ትኩረታችን እንዳይዛባ መጠንቀቅም ይኖርብናል። የኢትዮጵያ ህዝብ በከፋ ድህነት ውስጥ እየማቀቀ፤ ሰብዓዊ ክብሩና ነፃነቱ በዘረኞች ተነጥቆ ኑሮውን በባርነት እየገፋ ባለበት ባሁኑ ሰዓት “የዋጋ ማሻሻያ ኣደረግን” ብሎ ማወጅ አንድም የተቃውሞ ኃይልን ለመከፋፈልና የህዝብን ትግል ለማዳከም የሚደረገውን ደባ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ነጋዴን በህዝብ ጋር ለማጣላት ታቅዶ የተደረገ ስለመሆኑ ለኣፍታም መዘንጋት የለብንም።

***


[1] . Robertson, William . 1769. Views of the Progress of Society in Europe.
[2] . Motesquieu, Charles de. 1949. [1748] Sprits of Law. New York: Hafner.
[3] . የሚኒስትር ዴኤታውን ገለፃ በጀንዋሪ 19 ሪፓርተር አማርኛ ጋዜጣ ይመልከቱ

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 21, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.