የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ (ዘየአውዱት ከመ ዳመና)

(በሰሎሞን ተሠማ ጂ. – ከአ/አ)

semnaworeq /

የዶ/ር ዕጔለ ገብረዮሐንስ መጽሐፍ፣ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ”፣ (አዲስ አበባ) በ2003/4 ዓ.ም እንደገና ታተመ፡፡ ይህም የመጀመሪያው እትም ከወጣ ከ48 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ዋጋው ኪስ አይጎዳም፡፡ ያንን የሚያህል ቁምነገረኛ መጽሐፍ በ22.00 የኢትዮጵያ ብር ገዝቶ መጨምጨም ይቻላል፡፡ ገጽ በገጽ ሲገልጡት ከ እሰከ ስለሌለው ሃሴትን ያጭራል፡፡ እንደዚህ መጽሐፍ ዘወትር አዲስ ሃተታ የሚሆኑብኝ የአማርኛ መጽሐፍት ከአስራ አምስት ወይም አስራ ስድስት አይበለጡም፡፡ ይኼንኛው ግን የተለየ ነው፡፡ ውብ ነው! ድንቅ ነው!….

የመጽሐፉ መታተም በተለይ እኔን በእጀጉ አስደስቶኛል፡፡ ከአራት ወራት በፊት ለሚዩዚክ ሜይዴይ የመጽሐፍት ውይይት የሚመጥን ግምገማ ለታዳሚዎች ካቀረብኩ በኋላ፣ (በወርኃ ጥር ማለቂያ ገደማ፣ ፈልጌና አስፈልጌ፣ የዶ/ር ዕጔለ ገብረዮሐንስን የቀድሞ (የጥንት ብለው ሳይሻል አይቀርም) ጓደኞች፣ ዶ/ር አበበ ወ/ፃድቅን፣ ፕሮፌሰር ሉሌን (ቅድስት ሥላሴ ቴዎሎጂ ኮሌጅ ባልደረባ ናቸው)፣ እንዲሁም ዶ/ር ምክረሥላሴ (የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር የሚሰሩ ናቸው)፣ ተራ በተራ ደወለኩ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላም፣ ዶ/ር ምክረሥላሴ፣ የዶ/ር ዕጔለ ባለቤት ከባሕር ማዶ መጥተው፣ ይህንን መጽሐፍ በድጋሚ በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት እያሳተሙት መሆኑንና በቅርቡ እንደሚወጣም አበሰሩኝ፡፡ በተጨማሪም፣ ደራሲው የአባታቸውን፣ የአለቃ ገብረዮሐንስንም ታሪክና ስራዎች የሚዘክር መጽሃፍም አዘጋጅተው ስላለፉ፣ እርሱም ጭምር ከላይ በተጠቀሰው ማተሚያ ቤት እየታተመ እንዳለና መገባደጃውም ላይ እንደሆነ ነገሩኝ፡፡

ይህ አሁን የምንገመግመው መጽሐፍ ግን እጅግ ከፍ ያለ የዋጋ ድልድል የሚሰጠው፤ የፍልስፍና፣ የትምህርት፣ የቋንቋና የማህበራዊ ሳይንስ ይዘት ያለው ውብ ስራ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ በሀገራችን የፍልስፈና ነክነት ያላቸው መጽሐፍት ቁጥር በጣም አናሳ ነውና፡፡ ይህም የሆነው፣ ሀገሪቱ ከሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ ከውጭው ዓለም፣ በተለይም የግሪክና የሮም ሥልጣኔዎች ከለማበት አካባቢ ጋር ሙሉለሙሉ ስለተቆራረጠችና፣ የብቸኝነት ኑሮዋን ስለቀጠለች፤ ለፍልስፍናና ለምርምር የተዘረጋ ወንበርና የቆመም ትምህርት ቤት ስለታጣ ነው፡፡

እርግጥ ነው፣ በጥንት ዘመን ኢትዮጵያውያን የትምህርት፣ የንግድና የወታደራዊ ግንኙነቶች ከግሪክ ጋር ስለነበራቸው፣ ፍልስፍናና ፈላስፎቹም ቢሆኑ ለኢትዮጵያውያን አዲስ አልነበሩም፡፡ Socratesን ሶቅራጥ፣ Platoን አፍላጦን፣ Aristotleንም አሪስጣጣሊ፣ እንዲሁም Pythagorasን ባይጣጎር ተብለው ከመጠራታቸውም ሌላ፣ ሌሎቹም ፈላስፎች የታወቁና ይጠቀሱ ነበሩ፡፡ በዚህም ሳይወሰን፣ የተናገሯቸው ኃይለ-ቃላትና ምሳሌዎቻቸው (Allegories) ሳይቀሩ በቅጡ ተቀናብረው፣ “መጽሐፈ ፈላስፋ” በመባል በኢትዮጵያ ሊቃውንት ክበብ የታወቁ ናቸው፡፡

በተቀናበረ ሁኔታ ባይጠናቀርም (አይደራጅ እንጂ)፣ ኢትዮጵያውያን የፍልስፍና አስተሳሰብ ያጠራቸው አልነበሩም፡፡ አይደሉምም፡፡ በየንግግሮቻቸው መካከል ጣልቃ የሚያስገቧቸው ኃይለ-ሃሳብ የታጨቀባቸው ተረቶችና ምሳሌዎች፣ ለዚህ ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ በክርክሮችና በሙግቶች ጊዜም የሚጠቀሟቸው ኃይለ-ቃላት የኢትዮጵያውያኑን ጥልቅ አስተሳሰብና ማመዛዘን የሚመሰክሩ ሃረጎች ናቸው፡፡ ባላምባራስ ማኅተመ-ሥላሴ ወልደ ቂርቆስ ያሳተሙት “ያባቶች ቅርስ” ለዚህ ሃሳብጥሩ አብነት ነው፡፡

ባይሆን እነኳን፣ ይኼኛውን የኛን አዲሱን ኢትዮጵያዊ ትውልድ የሚያጣጥሩት አደገኛ ሁለት ጠባዮች አሉ፡፡ እነርሱም፣ “ዳተኝነት” እና “ምቾተኝነት” ይመስሉኛል፡፡ ሲናገሩም ሆነ ሲወያዩ፣ ብሎም ሲከራከሩ በፀሐይና በመሬት መካከል እንደዳመና እየተንቀዋለሉ ነው፡፡ አንዴ ወዲህ፣ አንዴ ወዲያ መርገጥ መንፈራገጥ ይታይባቸዋል፡፡ ሁሉ ነገር ተዘጋጅቶ፣ ተሰልቆና ተሰልቅጦ እንዲጠብቃቸው የሚልጉም ይመስለኛል፡፡ ብርቱ ጉለበት የሚጠይቅ፣ ረዘም ላለ ጊዜ የሚያደክምን ስራ፣ ተግባር ወይም ምርምር አይዳፈሩም፡፡ በዚህ ፍርዴ ተሳስቼ ብገኝ ደስ ባለኝ ነበር፡፡ (ግና፣ የዛሬውን ዘመን ዘፈኖችና አባባሎች ማጤኑ ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡ “እሩጥ ልጄ!” “ዝፈን ልጄ!” “ሸቅል ልጄ!” ወዘተርፈ ሆነዋል፡፡) ምቾተኝነቱም ቢሆን መላቅጡን ያጣ ነው፡፡ (ልብ አርጉልኝ “መላ ቂጡን” አላልኩም!)

ወተሮ በጎጃም፣ በጎንደር፣ በወሎና በትግራይ “መጽሐፍት ጽዋተወ ዜማ” አስመርቆና አስመስከሮ ወደ ደብሩ የሚመለስ ደብተራ ወይም መሪጌታ፣ በገዛ እጁ ብራና ፍቆ፣ ቀለም በጥብጦ ድጓንና ታምረ ማሪያምን የሚያካክሉ መጽሐፍት ቀድቶ ይመለስ ነበር፡፡ ወደ ባህር ማዶ ሄደው የሚመለሱትም ሆኑ በሀገር ውስጥ ኮሌጆች ትምህርታቸውን ተከታትለው የሚመረቁት ቁጥር በአስር ሺህዎች ቢሆኑም፣ እንኳን እንደዚህ ያለ ጠጣርና ብስል መጽሐፍትን ሊያነቡ ቀርቶ፣ የተማሩባቸውንም መጽሐፍት መልሰው ለማየት (ለመከለስ) ይግደረድራሉ፡፡ ይግተረተራሉ፡፡ በአጠቃላይ ትውልዱ የMTV (የኤም.ቲ.ቪ ትውልድ ) የሆነ ይመስላል፡፡ ምቾት ብርቁ! ብር ሃቁ! ዓይነት ነው፡፡ ወይም “ጭንቅ አይችሉም!” እንደሚባለው፣ ለስላሳ ፍጥረት ለመሆን ይዳዳቸዋል፡፡
“ንሕንኒ እለ ብነ እሙንቱ ሰማዕት ኰሎሙ ዘየአውዱት ከመ ዳመና” እንዳለው ነው፡፡ እንደዳመና በላያችን የሚዘዋወሩ፣ ስለእውቀትና ጥበብ ሊመሰክሩ የሚችሉ ሊቃውንት እንዳሉን አምናለሁ፡፡ ምክርንም ሆነ ድንጋይን አሻቅቦ መሰንዘር ፈፅሞ የማይገባ ነገር እንደሆነም አልዘነጋሁትም፡፡…….የሆነው ሆኖ፣ ስለዳመናው ግን ይህንን በድፍረት መናገር እችላለሁ፡፡ ዳመናው ልክ ዶ/ር ዕጓለ እንዳደረጉት መዝነብ አለበት፡፡ አለበለዚያ ግን፣ በፀሐይና በምድር መካከል (በውጭው ባህልና በተጨባጩ የኢትዮጵያውያን የኑሮ መልክ መኃል) መንገዋለሉ አይረባንም፡፡ ትርፉ የብርድ በሽታ (ጉንፋን) ማምጣት ይሆንብናልና፡፡ ሳል ነው – ትርፉ! ቀኬ ብቻ!
                        ******************************
ወደዋናው ትኩረታችን እንመልስ፡፡……(ነገርን ነገር እያነሳው ይዣችሁ እንደዚህ ጭልጥ ልበል? ያስተዛዝባል የወሬኛነት ነገር!)….“የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ”፣መጽሐፍ ደራሲ ዋናው የትምህርት ጥናታቸው ፍልስፍናና ሥነ-መለኮት በመሆኑ፣ የመጽሐፋቸው ይዘት ምንም ያህል አያስደንቅም ይሆናል፡፡ ነገር ግን፣ መጽሐፋቸው በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፈራንና የተለየን ቦታ የያዘ ለመሆን ችሏል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ በይዘቱ እስካሁንም ድረስ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ ከላይ እንደገለፅኩት፣ መጽሐፉ በፍልስፈና፣ በትምህርትና በቋንቋ የሚሰጠው ፋይዳ የላቀ ነው፡፡ ማለትም፣ ቃላት የሚፈለጉበትን ዘይቤና ሃሳብ በዕምቅ ጥልቀት እንዲገልጡ ሆነው ተደክሞባቸዋል፡፡
በገጽ 13 ላይ እንደገለጹት ሁሉ ሦስቱን የፍልስፍና ጥያቄዎች፡- ለምን? እንዴት? እና ምን? በተቻላቸው መጠን አጥጋቢ መልስ ለመስጠት ጥረዋል፡፡ የመጀመሪያው የመፈላሰፍ ጠባይ መደነቅ ሲሆን፣ ቀጥሎም መረዳት ነውና፣ በዚህ ላይ ደራሲው ሰፋ ያለ ሃታታና ምሳሌዎችን በማስጃነት/በዋቤነት ሰጥተዋል፡፡
ለፍልስፍናቸው መነሻ የሆኗቸውን ሃሳቦች ያገኙት ከኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ነው፡፡ እዚህም እዚያም ተሰባጥረው የሚገኙትን የግዕዝ ሥነ-ጽሑፍ ነጥቦች “ሕሊና” ባሉት ስነ-ሥርዓት አደላዳይ “ሕግ”፣ በፈርጅ-በፈርጁ ሊደለድሉት/ሊያደራጁት ጥረት አድርገዋል፡፡ ሙከራቸውም ፈሩን ያለቀቀ ነበር፡፡…. በአስተሳሰባቸውና በአቀራረባቸውም የገለልተኛነት ስፍራን ለመውሰድ ጥረዋል፡፡ የአንድ ፍልስፈና ትምህርት ቤት ጥገኛ ለመሆን ለፈለጉም፡፡ ከዚህም ከዚያም ጠቃሚ የሆኑትን ሃሳቦችና ነጥቦች ተፈላልገው በማጠናቀር፣ በቀጭኑ የሃሳብ ገመድ ላይ እንደሰረከስ ተጫዋች በብልሃት ለመጓዝ ተፍጨርጭረዋል፡፡ ይሁንና፣ ምንም እንኳን የገለልተኛነት መንገድን ለመውሰድ የሞከሩ ቢሆንም፣ የአንድ ትምህርት ቤት ተከታይ ከመሆን አላመለጡም፡፡ “በተዋህዶ ከበረ” የሚለው ምዕራፍ፣ የደራሲውን የሃሳብ አካሄድና የአስተሳሰብ ፈለግ በይበልጥ የሚመሰክር ነው፡፡
በተለይም፣ በግዕዝ ሥነ-ጽሑፋችን ውስጥ እዚያና እዚህ የተሰራጩትን ድንቅ ሃሳቦች አደራጅተውና አስፋፍተው፣ እንዲሁም በቅጡ አጣርተው በመፃፍ አንድ የቀለበት መንገድ ሰርተዋል/ጠርገዋል፡፡ የኢትዮጵያንና የምዕራባዊያንን የሃሳብና የአስተሳሰብ ጅረቶች እንዴት ለማገናኘት እንደሚቻል አውጠንጥነው ሲያበቁ፣ እንዴት ተደርጎ ሁለቱን ስልጣኔዎችና መንፈሶችም አንድ መልክና ኅብረ-ጠባይ ሰጥቶ፣ የኢትዮጵያውያንን ባህል፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ሃይማኖታዊ ገፅና ማኅበራዊ ሁለንተና “የሚያሻሽል ስልጣኔ” ሊገኝ ይችላል ሲሉ በጥልቅ መርምረዋል፡፡ የሚቻልበትንም መላና ዘዴ ገልጠዋል፡፡ ተፈላጊውም ስልጣኔ፣ ለሃገሪቱና ለህዝቧ በእጅጉ አስፈላጊና ዘላቂም ሊሆን እንደሚገባው አትተዋል፡፡
የትምህርትን ትርጓሜን (በእርሳቸው አነጋገር “ዘይቤ”ን) እና ዓላማውንም አስመልክተው ሲገልጹ፣  ከመነሾው የአሪስቶትልን አነጋገር፣ ማለትም “ሰዎች በመላ ስለዕውቀት የባሕሪይ ፍትወት ወይም ጉጉት ይሰማቸዋል፤” የሚለውን ጥቅስ ያወሳሉ፡፡ በተጨማረም፣ የፕሌቶን “ሰው ትክክለኛውን ትምህርት ያገኘ እንደሆነ ለስላሳና (ኖብል) እግዜርን የሚመስል ፍጥረት ነው፡፡ ትምህርት ያላገኘ እንደሆነ ግን በምድር ካሉት አራዊት ሁሉ የባሰ ነው፡፡” የሚለውን ሃይለ-ሃሳብ ጉልኅ ትኩረት ይሰጡታል፡፡(ገፅ፣ 9)፡፡ ስለ ትምህርት ትርጓሜም አንስተው፣ ሴሴሮ የተባለውን ሮማዊ ደራሲና ተናጋሪ ሃሳብ እንዲህ ሲሉ ይጠቅሱታል፡፡ “ትምህርት ማለት የነፍስ፣ የመንፈስ፤ ወይም የሕሊና እርሻ ማለት ነው፣” ይሉና፤ የግሪክኛውን ተመዛዛኝ ትርጉም cultura animia እንደሆነ ይበይናሉ፡፡ (ገፅ፣ 30)
ሰዎች ወደዚህች ዓለም ሲመጡ አራት ዝንባሌዎችን ይዘው እንደሚመጡ ይተነትናሉ፡፡ እነርሱም፡- የምጣኔ ሃብት ዝንባሌ (Homo Economicus)፣ የኃይማኖተኝነት ዝንባሌ (Homo Religious)፣ የፖለቲከኛነት ዝንባሌ (Homo Politicus) እና የንድፈ-ሃሳብ ዝነባሌ (Homo Theoreticus) ያላቸው እንደሆኑም ይዘረዝራሉ፡፡ ስለዚህም ይላሉ፣ የአንድ መምህር ተግባሩ እነዚህን ዝንባሌዎች ከተማሪው ውስጠ-ልቡና ፈልፍሎ ማግኘት ነው፡፡ (ገፅ፣ 48-49)
ስለዚህም ዕውቀትን በሦስት ረድፍ አቅርበውታል፡፡ 1ኛ. ሰብዓዊ (Humanistic)፣ 2ኛ. መክሊታዊ (Professinalism)ና 3ኛ. ምርምራዊ (Scientific) ናቸው ብለዋል፡፡ (ገፅ 86) ብዙዎቹን፣ የነዚህን የዕውቀት ረድፎች አስመልክተው በአዎንታውም ሆነ በአሉታው የተመራመሩትን ሊቃውንት ሃሳቦች አስፈፍተው አስረድተዋል፡፡ በዚህም ጉዳይ ላይ፣ ደራሲው ሃሳባቸው አስታራቂ ነው፡፡ ማለትም፣ ደራሲው “ሦስቱም የዕውቀት ረድፎች አንድ ናቸው፤ አንዱም ሦስት ነው፡፡” (አንድም ሦስትም፣ ሦስትም አንድም ናቸው እንደማለት ነው፡፡ የትምህርት ስረ-መሰረቱ ሕሊና ውስት የተጠራቀሙትን ዕውቀቶች ማውጣት ነውና፡፡) ይህንንም ሥሉስ አሳብ በተግባር ለማዋል፣ ፕላቶናዊት አካዳሚ መቋቋም እንዳለበት ደራሲው በአጽንዖት ይመክራሉ፡፡
መጽሐፉ በጠቅላላ መልኩ፣ የረቀቀን አሳብና ፈላሰፋዊ በሆነ መልኩ መግለጥ መቻሉን እንገነዘባለን፡፡ እንደመሰለኝ ከሆነ፣ ደራሲው ባማርኛ ተመዛዛኝ ቃል ባጡ ቁጥር እጃቸውን ወደ ግዕዝ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ዘርግተዋል፡፡ ባዷቸውንም አለመመለሳቸው እሙን ነው፡፡ ቀዋሚ ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ ቃላትን፤ ለምሳሌ፣ “ዘይቤ፣ ኑባሬያት፣ አንብሮ፣ አስተፃምሮ፣ ኅብር፣ አኃዝ፣ ሕፀፅ፣ ምልዓት፣ ጽንፋዊ፣…..” ወዘተርፈን ከግዕዝ ወስደዋል፡፡ እነዚህም ቃላት የረቀቀ የፍልስፍና አሳብን ለመግለጥ ተስማሚ ናቸው፡፡ በዚህ አኳኋን ሁለት ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ አንደኛ፣ የባዕድ ቃላትን ከመዋስና በጉራማይሌ ቋንቋ ግራ ከመጋባት ያዳኑን ከመሆኑም በላይ፤ ሁለተኛ፣ አማርኛ ፍልስፈናን ለመሸከም አቅመ-ቢስ ነው፣ ልፍስፍስ ነው ምንትስ ለሚሉትም ኮራጆች ጓዳችሁን ፈትሹ የሚል ይፋ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በእጅጉ የሚያስመሰግናቸውንም፣ ይህንን የመሰለ የቀላዋጭነትና የጠበበ አስተያየት ፈጽሞ ማሰቀረት ባይችሉም ቅሉ፣ በላቀ ብቃትና ትጋት ለአማርኛ ቋንቋ ባለውለታነታቸውን ፈጽመዋል፡፡
“የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ”፣ በቃላት አሰካክና አደራደሩ ስርዓትን የተከተለ ነው፡፡ ቃላቱ፣ ለአጫፋሪነትና ለአዳማቂነት ፈፅሞ ልሰፈሩም፡፡ (“መጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም….” የፈላስፋው አድናቆቱን መግለጫና የተረዳውን መርሆ መተንተኛ ሆነ፣ ብንል ሃሳቡን ሳያጠቃልለው አይቀርም፡፡) “ብዕር ዘፈተነ ወዘወጠነ” የሚለው ብሂል/ ዘዬ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ እያንዳነዱ ቃል ሁነኛ ሙያ ያለው ብቻ ሳይሆን በስተኋላው ጥልቅ ኃሳብንም የተሸከመም ነው፡፡ ብዕራቸው ግጥምንና ስድ ንባብንም የያዘ ስለሆነ፣ አንባቢው በሁለቱም ስልቶች በኩል፣ ደራሲው ያላቸውን ተሰጥዖ ያደንቃል፡፡ መጽሐፉ ኅብረ-ጠባይ ያለው ስለሆነ አንባቢያኑ በእጅጉ ይረካሉ፡፡
አሁን ትንሽ አጠያያቂ ወደሆኑ ነገሮች እንገባ፡፡
የመጽሐፉ እንከኖችም አሉት፡፡ ከ48 አመታት በፊት መጽሐፉ ሲታተም ይዟቸው የመጡት ጉልህ ስህተቶች እንዳሉ ተደግመዋል፡፡ አንደኛ፣ የመጽሐፉ ማውጫ የገፅና የአርዕስት ተራ ቁጥሮች አልተሰጡትም፡፡ በዚህ ረገድ መጽሐፉ በውስጡ የከበሩ ነገሮችን ቢይዝም በትክክሉ ወደ ውስጡ ለመግባት አይችልም፡፡ ሁለተኛ፣ በማውጫው ላይ ሁለት አሳሳቢ ነቁጦች (ማለትም፣ በሦስተኛውና በአስራ አምስተኛው ምዕራፎች ላይ ተስተዋል፡፡) በማውጫው ላይ፣ የሦስተኛው ምዕራፍ ርዕስ፣    “የሥልጣኔ ዘይቤና ትምህርት” መሆን ሲገባው፣ “የሥልጣኔ ዘይቤ” ብቻ ይላል፡፡ በአስራ አምስተኛው ምዕራፍም  ላይ “የዘመናት መለዋወጥ ወይም የታሪክ ዘይቤ”፣ መሆን ሲገባው “የታሪክ ዘይቤ” ብቻ ተብሏል፡፡
እዚህና እዚያ፣ ለምሳሌም ገፅ 17፣ 37 እና 96 ላይ የሰፈሩት የምዕራፎቹ ርዕሶች ከማውጫው ጋር ሲተያዩ የማይሳማሙ ይመስላሉ፡፡ በተለይም፣ በ1956ቱ እትም ላይ ወጥተው የነበሩት ፅሑፎች በሙሉ፣ በአዲስ ዘመን፣ በዛሬይቱ ኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጦች ላይ ወጥተው የነበሩ ናቸው፡፡ ልባም የሆነ አንባቢም፣ “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ ላይ የኅዳር 30/1954ን፣ የታኅሳስ 7 እና 21ን፣ እነዲሁም የመስከረም 26/ 1955 ዓ.ምህረትንና የጥቅምት 10/1955 ዓ.ም. እትሞችን ፈልጎ ቢያገኛቸውና ቢያነፃፅራቸው የመጽሐፉ ደራሲ ምን ያህል አድካሚ ስራ እንደነበረባቸው ለመረዳት ይችላል፡፡ የሆነው ሆኖ፣ በ2003/4ቱ እትም ላይ ያለው የማይታለፍ ስህተት በመሰረቱ የአሳታሚዎቹ ግድፈት ነው፡፡ የ1954ቱን እትም እንዳለ እስካን (scanned print) አደረጉት፡፡ በተለይም፣ ከገፅ 140 በኋላ ያሉትን “ወደፊት የሚታተሙ” የሚለውን የደራሲውን ሦስት የትርጉምና የወጥ ስራዎች ዝርዝር እንኳን እንዳለ ነው ያሳተሙት፡፡ አሳታሚዎቹ እንዳሉት ሆኖ መጽሐፍቱ ወደፊት ካልታተሙ፣ ዶ/ር እጓለን ሳይሆን ወራሾቻቸውን ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ ለማንኛውም እግዚአብሔር እንዲረዳቸው እመኛለሁ፡፡ እኛም አንባቢያን፣ ሌሎቹን የደራሲውን ስራዎች ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በኋላ ለማንበብ ያብቃን፡፡ (ማተሚያ ቤት ገብቷል የተባለውንም የአለቃ ገብረ ዮሐንስን ሕይወትና ስራዎች የሚመለከተውን መጽሐፍ በጥንቃቄ አርመውና አቃንተው እንደሚያቀርቡልን ተስፈኛ ነኝ፡፡ ታላቁ ገጣሚና መምህር ኃይሉ ገብረ ዮሐንስም ያልጠቆጠበ ጥረት አድርገው የወላጅ አባታቸውን ታሪክና የታላቅ ወንድማቸውንም ሌላ ትሩፋት አቃንተውና አሰማምረው እንደሚያቀርቡልን (አሁንም) ተስፈኛ ነኝ፡፡ በተለይ ለገሞራው መንታ ፋይዳ ያለው ደማቅ ተክህኖ እንደሆነ፣ ማንም ሊያስታውሳቸው እንደማይገባ እምነቴ ነው፡፡)
ማጠቃለያ፤

ጽሐፉ 50 አመት ሊሞላው ከሁለት አመት ያነሰ ጊዜ የቀረው ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ የፈጠራና የደራሲ ባለመብትነትም በሕጉ መሰረት፣ ሥራው (ድርሰቱ) የህዝብ ይሆናል፡፡ ያን ጊዜም፣ አሁን የታዩትን እንከኖች አርሞና ነቅሦ ማሳተም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስና የብሔራዊ ቤተ-መጽሐፍትና በተ-መዛግብት የሚሆን ይመስለኛል፡፡ መጽሐፉን በድጋሚ እንዲታተም የጣሩትን የዶ/ር ዕጓለ ገብረ ዮሐንስን ባለቤትና ቤተሰቦቻቸውን በሙሉ፣ “ክብረት ይስጥልን!” ልላቸው እመዳለሁ፡፡

 

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on May 14, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.