የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች – በዊኪሊክስ ፋይሎች

(ከአቢይ አፈወርቅ)
ባለፈው ሳምንት የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ዜና ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገውን በአቡነ መርቆሪዎስ የሚመራውን የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን አዲስ አበባ ካለውና በተመሳሳይ መጠርያ በአቡነ ጳውሎስ ከሚመራው ቤ/ክርስቲያን ጋር ለማስማማት የተደረገው ጥረት ነበር። ሁለቱም ቤ/ክርስቲያናት ተወካዮቻቸውን ወደ አሪዞና ልከው መደራደራቸው ቢታወቅም የማይጣጣሙ ቅድመ ሁኔታዎቻቸውን እንደያዙ ለቀጣይ ውይይት በቀጠሮ ነበር የተለያዩት።
Click here to read the artile in PDF
እኛም ዛሬ የሁለቱን ቤ/ክርስቲያናት ፍጥጫ በተመለከተ በዊኪሊክስ አማካኝነት የአሜሪካን ኤምባሲ ኬብሎች ላይ የቃረምናቸውን ጨምቀን እናቀርባለን።
ዊክሊክስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ የተለያዩ የኤምባሲው መልእክቶችን ይፋ ያወጣ ቢሆንም በተለይ ግን በሁለቱ ሲኖዶሶች ክፍፍል ዙሪያ ያተኮረባቸውን ሶስት በተለያዩ ጊዜያት የተላለፉ ሪፖርቶችን ብቻ ነቅሰን አውጥተናል። ሁለቱ ኬብሎች በፌብሪዋሪና በኤፕሪል 2007 ዓ.ም የተላለፉ ሲሆን አንዱ ደግሞ በጃንዋሪ ወር 2009 ዓ.ም ነበር ወደ ስቴት ዲፓርትመንት የተላከው።

በቅድሚያ ቤተክርስቲያኗ በሁለት የተከፈለችበትን መነሻ ምክንያት ለመፈተሽ ኤምባሲው ባደረገው ሙከራ ከሁለቱም ወገኖች የተንጸባረቁትን የተቃረኑ ሃሳቦች ያናጸሩበትን በወርሃ ፌብሪዋሪ የተላለፈውን ኬብል ጨምቀን እንደሚከተለው እንቃኝ።

“ፌብሯሪ 6 ቀን ሁለት የኤምባሲው ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ከሆኑት ከአቡነ ገሪማ እና የመንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን ከሆኑት ከአቡነ ጢሞቲዮስ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል” ይላል ሪፖርቱ መግቢያውን ሲጀምር፦

“እነዚህ ሁለት የቤተ ክርስቲያኗ ሀላፊዎች በቤተ ክርስቲያኗ መሀል የተፈጠረው ክፍፍል አይነተኛ መነሻው 3ኛው ፓትሪያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሞቱበት ከ1988 ዓ.ም የጀመረ ነው ባይ ናቸው። በወቅቱ 4ኛውን ፓትሪያርክ ለመመረጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ሲሰናዳ አንዳንድ የደርግ ባለስልጣናት መርቆርዮስን ለማስመረጥ በሲኖዶሱ አባላት ላይ ተጽእኖ አድርገው ነበር፦ ሲሉ ይከሳሉ።”

እነዚህ ጳጳሳት የአቡነ ጳውሎስ መሾምንና ይህንኑ ተከትሎ አቡነ መርቀርዮስ የተሰደዱበትን ሁኔታ አስመልክተው የሰጡት ገለጻ ግን ከኤምባሲው የምርመራ ውጤቶች ጋር የማይጣጣም ሆኖ ተገኝቷል።

እነ አቡነ ገሪማ “…ህወሃት ደርግን አስወግዶ ስልጣን እንደያዘ አቡነ መርቆሪዮስ በጤና ችግር ምክንያት በሀላፊነቴ መቀጠል አልችልም ሲሉ ለሲኖዶስ አሳወቁ።” በማለት የአዲስ አበባዋን ቤተ ክርስቲያን ኦፊሺያል አገላለጽ ነበር ደግመው ያስተጋቡት።

በኢትዮጵያ ታሪክ አንድ ፓትሪያርክ በፈቃዱ ከሀላፊነቱ የተነሳበት ወቅት ኖሮ እንደማያውቅ ያስታወሰው የኤምባሲው ኬብል በተቃራኒው የቆሙትን የአቡነ መርቆሪዮስን ቡድን አቋም ደግሞ እንደሚከተለው አንስቶታል።

“ሲኖዶሱ አቡነ ጳውሎስን 5ኛው ፓትሪያርክ አድርጎ እንደመረጣቸው ሲገልጽ አቡነ መርቆሪዮስ ከ4 ዋና ዋና ጳጳሳት ጋር በመሆን ከሀገሪቷ ተሰደዱ። ቆይተውም ከቤተ ክርስቲያኗ አመራርነት እንዲለቁ ከህወሀት ባለስልጣናት ማስፈራሪያና ጫና እንደተደረገባቸው ይፋ አደረጉ። አሜሪካ ሆነውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በስደት አቋቋሙ።

“አቡነ መርቆሪዮስ ትክክለኛው ፓትሪያርክ እሳቸው ብቻ መሆናቸውን ሲገልጹ የቤተ ክርስቲያኗ የቀኖና ህግ አንድ ፓትሪያርክ በህይወት እያለ እሱን አስወግዶ ሌላ ፓትርያርክ በላዩ ላይ መሾም አይፈቀድም። እኔን ግን በተጽእኖ አስወግደው ሌላ ሰው በላየ መጫናቸው ስህተት ነው።” በማለት ኮንነዋል።

ይህ የአቡነ መርቆሪዮስ ክስ ትክክለኛ መሆኑን ከሚያረጋግጡ መረጃዎች አንዱ ደግሞ ከሀላፊነታቸው እንዲወገዱ በተደረጉበት ሰዓት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ በጃንዋሪ 2009 ዓ.ም ለአምባሳደር ያማሞቶ የሰጡት ምስክርነት ነው።

አቶ ታምራት የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰውና ሀይማኖተኛ ሆነው ከእስር ቤት ከወጡ በሗላ በመጨረሻዎቹ ጊዜያት ሊሰሩ ያሰቧቸውን ተግባራት ለአሜሪካው አምባሳደር ዘርዝረው ነበር። ከዚህ መሀል የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ እንዲህ ይላሉ።

“ኦሪጅናሉ ፓትሪያርክ ከስልጣናቸው እንዲወገዱ ማዘዣው ላይ የፈረምኩት እኔ በመሆኔና ይህም ቤተ ክርስቲያኗን ለሁለት የከፈለ ሆኖ በመገኘቱ አሁን ሁለቱንም አስማምቶ አንድ ለማድረግ መሞከር እፈልጋለሁ።” አሉ።

ይህ ምስክርነት የአቡነ መርቆሪዮስ መወገድም ሆነ የአቡነ ጳውሎስ መሾም የፖለቲከኞች ውሳኔ መሆኑን ያረጋገጠ ከመሆኑም በላይ አቡነ ጳውሎስ ካለው መንግስት ጋር እጅና ጓንት ሆነው የሚሰሩ በህዝቡም ዘንድ በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ጥላቻ ያተረፉ ሰው ስለመሆናቸው በተለያዩ ቦታዎች ከቀረቡ የኤምባሲው ግምገማዎች ውስጥ ማስተዋል ይቻላል።

በአሁኑ ወቅት እንዳሉት አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባው ቤተ ክርስቲያን ሀላፊዎች ሁሉ ከትግራይ ብሔር የወጡ መሆናቸውን የሚያጣቅሰው የኤምባሲው የፌብሪዋሪ 2007 ዓ.ም መልእክት በሁለቱ ቤተ ክርስቲያናት መሀል የነበረው ልዩነት እንዴት እየተባባሰ እንደኖረ በስፋት የዘረዘረ ሲሆን ዋና ዋናዎቹን ብቻ ነቅሰንና ጨምቀን እናያቸዋለን።

በ1995 ዓ.ም የአዲስ አበባዋ ቤተ ክርስቲያን ከመርቆሪዮስ ጋር የተሰደዱትን 4 ጳጳሳት ማእረጋቸውን ሰርዣለሁ በማለት ቤተ ክርስቲያኗ ሰጥታቸው የነበረውን ስም ለሌሎች አራት አዳዲስ ተሿሚዎች መስጠቷን ገለጸች።

የአቡነ መርቆሪዮስን ፓትሪያርክነት ግን በዚያን ወቅት ለመሰረዝ አልሞከረችም ነበር። “ይህ በሆነ በተከታዩ አመት ደግሞ አቡነ መርቆሪዮስ አዲስ ቅዱስ ሲኖዶስ ከማቋቋማቸውም በላይ የቤተክርስቲያኗን መዋቅርም በአሜሪካ ውስጥ ዘረጉ። የሚለው ዊልገስ በተባለው የኤምባሲው ዲፕሎማት የተጠናከረው ሪፖርት ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የሜይ 2005 ዓ.ምህረቱ ምርጫ እስከተካሄደበት ጊዜ ድረስ ሁለቱ ቤተ ክርስቲያናት እምብዛም በአደባባይ ሳይካሰሱ መቆየታቸውን ይገልጻል።

እንዲያውም ከሁለቱ ፓትሪያርኮችና ቅዱስ ሲኖዶሶች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው ባያበል ሙላቱ የተባለው ታዋቂ ባንከኛ ከኤምባሲው የፖለቲካ ኦፊሰር ጋር ፌብሪዋሪ 7 ቀን 2007 ዓ.ም ተገናኝቶ በሁለቱም ቤተ ክርስቲያናት መሀል ኦፊሽያል ያልሆነ ግንኙነት ሲደረግ መቆየቱን መስክሯል።

“ከኤምባሲያችን ጋር ግንኙነት ያለው ባያበል ሙላቱ በሁለቱም ወገኖች መሀል ኦፊሽያል ያልሆነና በገለልተኛ ሰዎች መልእክት አስተላላፊነት የሚካሄድ ቋሚ ግንኙነት እንደነበር ነግሮናል። ይሁንና ውስጥ ለውስጥ መተቻቸታቸው ግን አልቀረም። የአዲስ አበባዋ ቤተ ክርስቲያን አዲሱ ቅዱስ ሲኖዶስ ህጋዊነት የለውም ስትል የአሜሪካዋ ደግሞ የአዲስ አበባዋ ቤተ ክርስቲያን የኢህአዴግ ተቀጽላ ሆናለች ስትል ነው የቆየችው።

ይህ በአቡነ ጳውሎስ የሚመራው ወገን ከህወሀት ኢህአዴግ ጋር የተገናኘ ነው የሚለው ክስ ደግሞ በህዝቡ ውስጥ ስር የሰደደ ተቀባይነት ያገኘ ስለመሆኑ በኬብሎቹ ውስጥ ተደጋግሞ ተገልጿል።

ለምሳሌ በአሜሪካ ያሉ ምእመናን በአብዛኛው የሚሄዱባቸውን ቤተ ክርስቲያናት የሚመርጡት ከፖለቲካ ስሜታቸው ጋር አገናዝበው ሲሆን የኢህአዴግ ደጋፊዎች በአቡነ ጳውሎስ ስር ወዳሉ ቤተክርስቲያናት ሲሄዱ አገዛዙን የሚቃወሙት ግን በአቡነ መርቆሪዮስ ወደሚመሩት ቤተ ክርስቲያናት ብቻ እንደሚሄዱ ተመልክቷል።

ይሁንና የ2005ቱን ምርጫ ተከትሎ በአቡነ ጳውሎስ ላይ ጠንካራ ህዝባዊ ቁጣ በመቀስቀሱ አብዛኞቹ በሳቸው የሚመሩ ቤተ ክርስቲያናትን ደጋፊዎቻቸው ሳይቀሩ እርግፍ አድርገው እንደተዋቸው የኤምባሲው ጥንቅር ይገልጻል።

“ከ2005 ዓ.ምህረቱ ምርጫ በሗላ የአዲስ አበባዋ ቤተ ክርስቲያን የገዛ ምእመኗን ለመከላከል ሳትሞክር በመቅረቷና ተቃዋሚዎችን የደገፉ አባላታ ላይ መንግስት የወሰደውን የሀይል እርምጃ ለማውገዝ እንኳን ያለመፍቀዷ ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጣ አስነሳባት።

“በአሜሪካ ያሉና በአቡነ ጳውሎስ ስር ይተዳደሩ ወደ ነበሩ ቤተ ክርስቲያናት ይሄዱ የነበሩ ደጋፊዎቻቸው መሀል አብዛኞቹ አመለካከታቸውን ቀይረው በአቡነ መርቆሪዮስ ስር ያሉ ቤተ ክርስቲያናትን ሙጥኝ አሉ።

ይህም የአዲስ አበባዋ ቤተ ክርስቲያን በአሜሪካን ውስጥ የነበራትን ተከታይ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ አመነመነው።

“ሁኔታዋ ያሳሰባት የአዲስ አበባዋ ቤተ ክርስቲያን ጥለዋት የጠፉ የቀድሞ ተከታዮቿን ዳግም ለመማረክ በሚል ሶስት ታዋቂና ገለልተኛ የነበሩ ጳጳሳትን ሊቀ ጳጳሳት በማድረግ ወደ አሜሪካ ሸኘቻቸው። የተቆጣው ህዝብ ግን እነዚህን አዲስ ተሿሚዎች ከአቡነ ጳውሎስ ጋር በመወገናቸው ምክንያት አገሸሻቸው።” የሚለው የኤምባሲው መልእክት በሁለቱም ወገን የቀጠለውን መናቆርና በየፊናቸው የወሰዷቸውን ርምጃዎች ይዘረዝራል።

የአዲስ አበባዋ ቤተ ክርስቲያን የአቡነ መርቆሪዮስን ፓትሪያርክነት ሰርዣለሁ ከማለቷና ከመገዘቷ አስቀድሞ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ ታዋቂ ሰዎችና የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ያካተተ 20 ሰዎች ያሉበት ቡድን ለማደራደር ያደረገው ሙከራ መክሸፉን ያስታወሰው ሪፖርት ግዝቱን በተመለከተም ውስጥ አዋቂ የሆነውና ከኤምባሲው ጋር ግንኙነት ያለው ባያበል ሙላቱ ያቀረበውን ትችት አጣቅሷል።

“የሀይማኖት ማእረግን መግፈፍ ማለት ልክ አንድ ሰው ከፖለቲካ ስልጣኑ እንደማውረድ ቀላል አይደለም። ይህ ከአሁን በፊት ተወስዶ የማያውቅ ግዙፍ ርምጃ ነው። ምክንያቱም ሹመቱ የእድሜ ልክ ነውና።”ብሏል። ባያበል የእርቅ ሙከራውን በተመለከተ ደግሞ እንዲህ ይላል፦

“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በ2ሺህ ዓመት ታሪኳ አይታው የማታውቀው አጣብቂኝ ውስጥ ነው የገባችው ይህንን በሁለቱ ወገኖች መሀል የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት ምንም እንኳን በርካታ ታዋቂ ሰዎች ቢጥሩም ሁኔታው ከመስከኑ በፊት እየባሰበት መሄዱ አይቀርም።” አለ።

እንዳለውም የአሜሪካኗ ቤተ ክርስቲያን በአጸፋ መልስ የአቡነ ጳውሎስን ፓትሪያርክነት ማእረግ ሰርዣለሁ በማለት ገዘተቻቸው። ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው ግን በሀገር ቤት በነበሩ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያኗ ሀላፊዎች አማካኝነት በአደባባይ የወጡ መረጃዎች በተለይም የቤተ ክርስቲያኗን ሀብት እየዘረፉ በግል አካውንታቸው በማስገባትና የጠ/ሚ/ሩን የፖለቲካ ሀይል ተጠቅመው የሲኖዶሱን አባላት ሳይቀር በማስፈራራት ተግባራቸው የሚታወቁት አቡነ ጳውሎስ አሁንም በሰሜን አሜሪካ ያሉት የሀይማኖት አባቶች ጋር በአንድ በኩል ሰላም ለማውረድ እፈልጋለሁ እያሉ በሌላ በኩል ግን የፖለቲካ ጉልበት ተጠቅመው ለማጥቃት የጠነሰሱት ሴራ በኤምባሲው በኩል መጋለጡ ነው።

“የአዲስ አበባዋ ቤተ ክርስቲያን በኤምባሲያችን በኩል የአሜሪካ መንግስትን ርዳታ ለመጠየቅ ማሰቧን ተረድተናል።” የሚለው የኤምባሲው መልእክት፦

“በአሜሪካ ያለው ቤተ ክርስቲያን ‘የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን’ የሚለውን ስም መጠቀም እንዳይችል እንድናግዳቸውና ዋና ዋናዎቹን የቤተ ክርስቲያኗን ሀላፊዎችም ወደ ኢትዮጵያ አስገድደን እንድንመልስላቸው ይፈልጋሉ።

“በእኛ በኩል በአዲስ አበባ ላሉት ፓትሪያርክና ለሲኖዶሱ ይህን መሰሉ ተግባር ህጋዊ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነና የባሰ ጉዳት ከማድረስ የማያልፍ እንደሆነ እናስረዳቸዋለን።” ይላል ወደ ስቴት ዲፓርትመንት የተላከው መልእክት።

ይህ ኬብል በማጠቃለያው ላይ ካሰፈረው አስተያየት መሀል ደግሞ የሚከተለው ይገኝበታል።

“የአዲስ አበባው ፓትሪያርክ የ2005ቱን ምርጫ ተከትሎ የሀይል እርምጃና የጅምላ እስር በተፈጸመበት ወቅት የቤተ ክርስቲያን አማኞችን ለመከላክል ስላልሞክሩ ስር የሰደደ ጥላቻ አትርፈዋል። ምዕመናኑ ጋ ለመድረስም ይህ ነው የሚባል ጥረት አላደረጉም። በዚያ ላይ የጎላ ድምጽ ያላቸው በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጲያዊያን ክፍፍሉን ተንተርሰው ጠ/ሚ/ር መለስንና መንግስታቸውን መኮነኛ ማድረጋቸው የፓትሪያርኩን ሚና ውስብስብ አድርጎባችዋል።

በሌላ የኤምባሲው ኬብል ላይ ደግሞ አቡነ ጳወሎስ ኤፕሪል 23 ቀን ከአሜሪካው አምባሳደር ጋር ተገናኝተው ያደረጉት ውይይት በስፋት ተዘርዝሯል።

በዚህ ውይይት ወቅት “ኢትዮጵያ ትከሻው የሰፋ ታላቅ ወንድም ያስፈልጋታል” በማለት በአሜሪካ ላይ ያላቸውን መመካት የሚገልጹት አቡነ ጳውሎስ አሜሪካ ካሉት የሀይማኖት አባቶች ጋር ሰላም ለማውረድ በወቅቱ ስለተደረገው የድርድር ጥረት ተጠይቀው ነበር።

“ኢህአዲግ ስልጣን ሲይዝ በተፈጠረ ልዩነት ሳቢያ እሱና በአሜሪካ የሚኖሩ “__________ወንድሞቹ” ተከፋፍለው መቅረታቸው እንደሚቆጨው ነገረን። ይህንኑ የሚገልጽ መግለጫም በቅርቡ አሜሪካ ውስጥ እንዲወጣ ማድረጉን ጠቅሶ ይህም በስፋት እንደሚታመነው ሳይሆን አንድም ሰው ከኢትዮጲያ እንዲወጣ ያልተገደደ መሆኑን የሚገልጽ ነው አለን።” በማለት የሚጀምረው የኤምባሲው ሪፖርት ጳጳሱ ለድርድር ወደ አሜሪካ የላኳቸው አራት ሊቀ ጳጳሳት ሳይሳካላቸው ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን አትቷል።
“ብዙ ሰዎች ለዚህ እኔን ነው ጥፋተኛ አድርገው የሚወቅሱኝ። ይሁንና አሁን የኔ ብቸኛ ፍላጎት ሁለቱን ቤተክርስቲያናት አንድ ማድረግ ነው። “ የሚሉት አባ ጳውሎስ በቅርቡ እሳቸው ራሳቸው አሜሪካንን የመጎብኘት ሀሳብ ይኖራቸው እንደው ሲጠየቁ ደግሞ፦

“እፈልግ ነበር። ይሁንና በአሜሪካው ቤተክርስቲያን ያሉ የተወሰኑ ሰዎች ይቃወሙኝ ይሆናል እንጂ።” ነበር ያሉት።

በአንድ በኩል “ከወንድሞቼ ጋር ተለያይቼ መቅረቴ ይቆጨኛል፣ ሰላም እንዲወርድም እፈልጋለሁ እያሉ በሌላ ጎኑ ደግሞ ‘ተቀናቃኞቼን አንቃችሁ አምጡልኝ’ በሚል ሴራ የሚማጸኑት አቡነ ጳውሎስ በስደት ካሉት አባቶች ጋር ለመስማማት ይህ ነው የሚባል በር ሲከፍቱ ታይተው አያውቁም።

ምንም እንኳን ኦርጂናሉ ፓትሪያርክ ህገ ወጥ በሆነ የፖለቲካ ውሳኔ መባረራቸውን በወቅቱ ትዕዛዙ ላይ የፈረሙበት አቶ ታምራት ላይኔ ሳይቀሩ ያረጋገጡት ጉዳይ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት የተሞከረው ድርድር በቀጠሮ ይቋጭ እንጂ የመሳካት ዕድሉ ግን የመነመነ ከመሰለባቸው ምክንያቶች ዓይነተኛው የአቡነ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን አቡነ መርቆሪዮስን “ከስልጣኔ የለቀቅኩት በህመም ምክንያት ወድጄ ነው።” ብለው እንዲዋሹ ቅድመ ሁኔታ በማቅረቧ መሆኑ ይታመናል።__

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 25, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.