የኤደን ፣ የቤቲ እና የሜላት አማርኛ

አዲስ ነገር (አሮን ፀሀዬ) – ኤደን ቤቲና ሜላት ገፀ-ባሕርያት አይደሉም፡፡ የገናናው ኀይሌ ገብረ ሥላሴ ሴት ልጆች ናቸው፡፡ በአመዛኙ በእናታቸው ነው የወጡት፡፡ ሲበዛ ቆንጆ ናቸው፡፡ ቀያይ ናቸው፡፡ ፈረንጅ ነው የሚመስሉት፡፡ በዚያ ላይ አማርኛ ይከብዳቸዋል፡፡ እንግሊዝኛ ይቀናቸዋል፡፡

ከሶስቱ ሴት ልጆቹ መሀል ሁለቱ የመስቀል በዓል ሲከበር አባታቸው ሀዋሳ ላይ ባስገነባው አዲሱ ‹‹`ኀይሌ ሪዞርት›› ተገኝተው ነበር፡፡ ወላጆቻቸው ዓለም እና ኀይሌም ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ተጠጋቸው፡፡ በዓል እንዴት ነው ሲልም ጠየቃቸው፡፡ “ኀይሌ በዓሉን ከህዝቡ ጋር በማክበሩ ልዩ ስሜት እንደፈጠረበት ተናገረ፡፡

እነ ቤቲ ግን አማርኛ አደነቃቀፋቸው፡፡ ጋዜጠኛው ኀይሌን ‹‹ልጆቹ አማርኛ አይችሉም እንዴ?›› ሲል ጠየቀ፡፡ ኀይሌ በዚያ መልካም ፈገግታው ጥያቄውን ለማስተባበል ሞከረ፡፡ ‹‹…ኸረ እንዲያውም ተረት ይነግሩኸል…፣ቅኔም ይዘርፋሉ›› አለ፡፡ ወደ ልጁ ዞሮ፡-

‹‹ተረት ንገሪው እስኪ፤ ግን አጭር ቶሎ የሚያልቅ›› አላት፡፡

ልጅቱ ተጣጣረች፡፡ ምንም አልከሰትልሽ ሲላት ወደ እህቷ ዞረች፡፡ ሀይሌ ትንሽ በሁኔታው የተደናገጠ መሰለ፡፡ እህትየውም ከብዙ ጭንቀት በኋላ አንድ ነገር ተነፈሰች፡፡

‹‹እ…እ…እ….ዞሮ ዞሮ መግቢያው ጭራሮ!›› አለች፤የሞት ሞቷን፡፡

ሀይሌ የተፈጠረው ሁኔታ በትንሹ ሳይረብሸው አልቀረም፡፡

‹‹…ያው እንግሊዝኛ አስፈላጊ ስለሆነ እንጂ እዚህ ተወልደው አድገው አማርኛን በደንብ ነው የሚያወሩት…ጎበዝ ናቸው፡፡…እንደምታውቀው በዚህ ዘመን እንግሊዝኛ…፡፡…ያው እንግዲህ…ዌል…›› ኀይሌ በፈገግታው ውስጥ ብዙ ለማስተባበል ሞከረ፡፡

ጋዜጠኛው ቀጠለ፡፡ ኀይሌ የልጆቹን የአማርኛ ብቃት ለማስመስከር ታገለ፡፡ ‹‹መዝሙር በይለት እስኪ›› አላት አንደኛው ልጁን፣ ጥሩ ድምፅ እንዳላትና ኢትዮጵያን አይዶል ብትወዳደር እንደምታሸንፍ ከተናገረ በኋላ፡፡ የደስ ደስ ያላት ልጁ የአማርኛ ወይንስ የእንግሊዝኛ ዘፈን መዝፈን እንዳለባት ጠየቀች፡፡ ኀይሌ አማርኛ ዝፈኚ አላት፡፡ ትንሽ ካሰበች በኋላ ‹‹…እ…እ…እ..›› ብላ ካጣጣረች በኃላ የሴሌን ዲዮንን ይሁን የማሪያ ኬሪን ለጊዜው የማላስታውሰውን ዘፈን ዘፈነች፡፡ ኀይሌ ፊቱ ቅጭም አለ፡፡

ካ!ካ! አማርኛ!!!

ሞገስ ተፈራ ሁለተኛ ዲግሪውን ከሰራ በኋላ የዩኒቨርሲቲ መምህር ሆነ እንጂ ያለፉትን ዘጠኝ አመታት በግል ትምህርት ቤቶች ነው ያሳለፈው፡፡ ‹‹በእያንዳንዱ ባሳለፍኩት የሥራ ዓመት አማርኛ ሞገሷን እያጣች ነበር›› ይላል የሠራባቸውን ዘመናት በምልሰት እያሰበ፡፡ እንዲህ ይተርካል፡፡

‹‹የትምህርት ቤቶቹን ስም አልጠቅስልህም፡፡ መጀመርያ ተመርቄ እንደወጣሁ ያስተማርኩበት ትምህርት ቤት በጊቢው ውስጥ አማርኛ ከተናገርክ በደሞዝህ ፈረድክ ማለት ነው፡፡ መምህራን በአንድ ዐረፍተ ነገር 15 ብር ይቀጡ ነበር፡፡ ለምሳሌ ረስተህ ‹‹ዳስተሩን አቀብለኝ›› ካልክ 15 ብር ትቀጣለህ፡፡ ‹‹ቾክ ረሳሁ መሰለኝ›› ካልክ ሌላ 15 ብር፡፡ በድምሩ 30 ብር፡፡ ስለዚህ ከመናገር ዝምታን ትመርጣለህ፡፡ አለዚያ ደሞዝህ ተጎማምዶ ይደርስኸል፡፡››

‹‹ተማሪዎች ደግሞ በየሳምንቱ ‹‹language police››የሚባሉ “ሲቪል” ተማሪዎች ይመደብባቸዋል፡፡ ከዩኒት ሊደሩ ቢሮ፡፡ ‹‹ላንጉዌጅ ፖሊሶቹ›› ከራሳቸው ከተማሪዎች የተውጣጡ ናቸው፡፡ በእረፍት ሰዓት እየተጫወቱ ድንገት ሲያወሩ አማርኛ የቀላቀሉ ተማሪዎች ስማቸው በእነዚህ የተማሪ ፖሊሶች አማካኝነት ለ‹‹ዩኒት-ሊደሩ›› ቢሮ ይተላለፋል፡፡ የተለያዩ ቅጣቶች ሲፈፀሙባቸው ትዝ ይለኛል፡፡ ከሁሉም የማይረሳኝ ግን ‹‹I am stupid›› የሚል ባጅ ለጥፈው እንዲዞሩ የሚደረገው የቅጣት አይነት ነው፡፡ በወቅቱ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር በብሪቲሽ ካውንስል ረዘም ላለ ጊዜ አገልግለው በጡረታ የተገለሉ በሳል ሰው ነበሩ፡፡ ይህ አይነቱ ቅጣት ካልቆመ ሥራ እለቃለሁ እያሉ ሲወተውቱ ትዝ ይለኛል፡፡ የትምህርት ቤቱ ባለቤት እና ዘመዳቸው/ዩኒትሊደሩ/ግን ‹‹በጀ›› አላሏቸውም፡፡ ሆኖም እርሳቸው ከመልቀቃቸው በፊት እኔ ለቀቅኩ፡፡ በራሴ ምክንያት ነው ታድያ፡፡››

‹‹ከዚያ በኋላ የገባሁበት ትምህርት ቤት በአንዲት ሙስሊም አሜሪካዊት እና /ባሏ ሶማሌ-እንግሊዛዊ ዜግነት ያለው ነው/ የሚተዳደር ሲሆን አብዛኛው የፓርላማ አባላትና መለስተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበት ዝነኛ ትምህርት ቤት ነበር፡፡

የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ አንቀጥቅጣ ነበር የምትገዛን፡፡ ጥሩ ደሞዝ ብትከፍልም ጥብቅ ዲሲፕሊን ታራምድ ነበር፡፡ በእርሷ ትምህርት ቤት ውስጥ አማርኛ መናገር ክልክል እንደሆነ የሚያሳዩ ማስታወቂያዎች በቅጥር ጊቢዋ በየቦታው በጨርቅ ለጥፋለች፡፡ ገና ስቀጠር በተሰጠኝ የትምህርት ቤቱ ህግ እና ደንብ መግለጫ ላይ ከአማርኛ መምህር ውጭ በክፍል ውስጥ አማርኛ መናገር ያለምንም ማስጠንቀቅያ እንደሚያስባርር የሚገልፅ ዐረፍተ ነገር ተቀምጧል፡፡››

‹‹በእርግጥ ሴትዮዋ በትምህርት ጥራት አትደራደርም፡፡ በጣም ምስጉን ተማሪዎችን አፍርታለች፡፡ ብዙዎቹ ተማሪዎቿ በእንግሊዝኛ ብቃት እኛ መምህራኖቻቸውን ያስከነዱን ነበር፡፡ በዚህም ትበሳጭብን ነበር፡፡››
‹‹ሌላ የማስታውሳቸው ትምህርት ቤቶች አማርኛ የሚናገሩ ተማሪዎችን ፊታቸውን ወደ ግድግዳ አዙረው እንዲቆሙ ያደረጉ ነበር፡፡ በአንድ ትምህርት ቤት ደግሞ አንድ የአማርኛ ቃል ተሳስቶ ክፍል ውስጥ የተናገረ ተማሪ አንድ ገፅ ሙሉ ‹‹I am sorry›› እያለ እንዲጽፍና እንዲያስፈርመን ይደረግ ነበር፡፡››

‹‹በአጠቃላይ በብዙ ትምህርት ቤቶች አማርኛ ትወገዝ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ወላጆችም ይህ በመደረጉ አድናቆት እንጂ ቅሬታ ሲያቀርቡ ሰምቼ አላውቅም፡፡ በትርፍ ሰዓቴ ልጆቻቸውን አስጠናላቸው የነበሩ ወላጆች ፊደል ያልቆጠሩ ቢሆንም ልጆቻቸው እንግሊዝኛ እያሻሻሉ እንደሆነ ስነግራቸው ይፈነድቁ ነበር፡፡

ሂሳብ እያሻሻሉ ነው ብላቸው ግን እንደዚያ አይፈነድቁም፡፡ ‹‹እሱን ይደርስበታል፣ዋናው እንግሊዝኛ ላይ ይበርታልኝ›› ይሉኻል፡፡

አንዳንዴ ሳስበው ወላጆች ከጎረቤት ጋር ቡና ሲጠጡ በልጆቻቸው እንግሊዝኛ የሚፎካከሩ ይመስለኛል፡፡ ‹‹ ልጄ መቼ አማርኛ ትሰማና፣ እንደው ብታይዋት ጉድኮ ናት፤የፈረንጅ አፍ ነው የሚቀናት›› እያሉ፡፡››

ፈረንጅና ጥቅሙ

አዲስባ ባለፉት አስር አመታት መቶ ሺህ ህፃናትን ወልዳለች፤ መቶ አዳዲስ ሰፈሮችን ፈጥራለች፡፡ ሺ መኖርያ ቤቶችን ገንብታለች፡፡ ይህንንም ተከትሎ በታሪኳ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ብዙ የግል ት/ቤቶች መሽቶ በነጋ ቁጥር በቅለውባታል፡፡ ሰፋ ያለ ጊቢ ያላቸው መኖርያ ቤቶች ድንገት መዋእል ህፃናት ሆነው ይነጋል፡፡ ትምህርት ቤት መክፈት ኪዮስክ ከመክፈት ዘለግ ያለ መሰናዶ የሚደረግለት አይመስልም፡፡
ወላጆች ለአብራክ ክፋዮቻቸው ት/ቤቱ ሲመርጡ የቅድሚያ መመዘኛቸው ት/ቤቱ ለእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚሰጠው ክብደት ብቻ ነው፡፡ ይህን እውነታ የተገነዘቡ አዳዲስ ት/ቤቶች መላ አፈጣጠራቸውን ፈረንጅኛ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ጥረታቸው የሚጀምረው ለት/ቤት ከሚሰጡት ስያሜ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት በህይወት ካሉ ት/ቤቶች ምሳሌ ብጠቅስ ሙግቴን ያጠናከርልኝ ይሆናል፡፡

‹‹ጊብሰን አካዳሚ፣ ስ ኩል ኦፍ አሜሪካ አካዳሚ፣ አሜሪካና አካዳሚ ፣ ካምብሪጅ አካዳሚ ፣ ኦክስፎርድ አካዳሚ ፣ማክሚላን አካዳሚ ፣ ማጂክ ካርፔት አካዳሚ፣ ሂል ሳይድ አካዳሚ፣ ብሪቴይን ት/ቤት፣ ሜርሲ አካዳሚ፣ ፓራዳይዝ አካዳሚ፣ ሆራይዝን አካዳሚ ፣ ሲቲ አካዳሚ ፣ሰንሻይን አካዳሚ፣ …

ት/ቤቶቹ ብዙ ተማሪ እንዲመዘገብላቸው በክረምት ወራት በሚያስለፍፏቸው የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ውስጥ አንድ ፈረንጅ እንዲታይ ያደርጋሉ፡፡‹‹ይህንን አለማድረግ ከፍተኛ ኪሳራን ያስከትላል›› ይላል በተለያዩ የግል ት/ቤቶች ለዘጠኝ አመት በመምህርነት የሰራው አቶ ሞገስ፡፡ እርሱ እንደሚለው ምስላቸው በቴሊቪዥን እንዲታይ የሚደረጉት ፈረንጆች እንዳንዴ ለማስታወቅያው ብቻ በኪራይ መልክ የሚመጡበት አጋጣሚ አለ፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በሚያመጡበት ሰዓትና ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት በሚወስዱበት ሰአት እነዚህ ፈረንጆች በር ላይ ሆነው የማስተባበር ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያነጋገረው አንድ መምህር በአንድ ወቅት ባስተማረበት የግል ት/ቤት የነበረ ጃማይካዊ ወላጆች በሚገኙበት ሰአት ከፈረንጅ መምህራን ኋላ እንዲሆን በትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች ስለተነገረው ቅሬታ ተፈጥሮበት ት/ቤቱን መልቀቁን ያስታውሳል፡፡

ለግል ት/ቤቶች የፈረንጅ ምስል የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ በጉልህ የሚታየው የደሞዝ ልዩነትም ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡ አንድ በግል ት/ቤት የሚገኝ ምንም አይነት ዲፕሎማም ሆነ ዲግሪ የሌለው ፈረንጅ የቆዳ ቀለሙ ነጭ በመሆኑ ብቻ ማስተርስ ካለው ኢትዮጵያዊ በአምስት እጥፍ የበለጠ ደሞዝ ያገኛል፡፡ የአንድ ፈረንጅ አማካይ ደሞዝ ከ 5-11 ሺ የኢትዮጵያ ብር ይደርሳል፡፡ በአንጻሩ ሁለተኛ ዲግሪና ረዥም የስራ ልምድ ያለው ኢትየጵያዊ መምህር 3 ሺ ብር የክፍያ ጣርያው ነው፡፡

በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ከፈረንጆች ቀጥሎ ጥሩ ክፍያ የሚያገኙት ህንዶች፣ ጃማይካዎችና ሌሎች የአፍሪካ ዜግነት ያላቸው መምህራን ናቸው፡፡ ሆኖም በስደት ወደ ሶስተኛ አገር ለመሄድ አዲስ አበባ የሚኖሩ አፍሪካውያን በ‹‹ሀበሻ›› ደሞዝ ሊቀጠሩ ይችላሉ፡፡

Amharophobia

በግል ት/ቤት የሚማሩ ልጆች ጠጠር ያሉ የአማርኛ ቃላትን አይረዱም፡፡ ለምሳሌ ‹‹እርሻ ለአንድ አገር እድገት ይበጃል›› በሚለው አረፍተ ነገር ውስጥ ‹‹ይበጃል›› የሚለው ቃል ግር የሚላቸው የ 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ያጋጥማሉ፡፡ ለአማርኛ ክፍለ ጊዜ የሚሰጠው ክብርና ዋጋም በግል ት/ቤቶች የወረደ ነው፡፡ ለምሳሌ ፈተና እየተቃረበ ሲመጣ ተማሪዎች በስፖርትና አማርኛ ፔሬዶች ሌሎች ትምህርቶችን እንዲያጠኑ ይደረጋል፡፡

የግል ትምህርት ቤቶች አማርኛ ቋንቋን ትቢያ ለማድረግ የዘየዱት ሌላኛው መንገድ በቅጥር ግቢያቸው አማርኛ መናገር ነውር እንደሆነ ማወጅን ነው፡፡ ከጥቁር ሰሌዳው ጎን በጉልህ ‹‹በአማርኛ መናገር ፈፅሞ የተከለከለ ነው›› የሚል ማስታወቅያ ይሰቅላሉ፡፡ አማርኛ መምህራንም ቢሆን ከክፍላቸው ውጭ በእንግሊዝኛ ብቻ እንዲነጋገሩ ይገደዳሉ፡፡

‹‹ኢትዮጲካሊንክ›› የተሰኘ የሬድዮ ፕሮግራም በአንድ ወቅት በዚሁ ጉዳይ ላይ ባቀረበው ዳሰሳ ‹‹አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ክልክል ነው›› የሚል ማስታወቅያ በአንድ የግል ትምህርት ቤት ተሰቅሎ ማየቱን ዘግቧል፡፡

በግል ት/ቤቶች መምህራን ተማሪዎችን በፍፁም አካላዊ ቅጣት መቅጣት አይፈቀድላቸውም፡፡ በመሆኑም አማርኛ የሚናገሩ ህፃናት ፊታቸውን ወደ ግድግዳ አዙረው ለተወሰኑ ሰአታት እንዲቆሙ ይደረጋል፡፡ ይህ ከፍተኛው የቅጣት አይነት ነው፡፡ እኔ በተማርኩባቸው የመንግስት ት/ቤቶች ጆሮ መያዝ፣ እስክሪብቶ በሁለት መሀል ጣቶች ከትቶ መጭመቅ፤ በማስመሪያ ጣቶችን መቀጥቀጥ፣ ኩርኩም እና ወንበር ላይ በሆድ አስተኝቶ በልምጭ መቀመጫን መግረፍ ቀላል ቅጣቶች እንደነበሩ የሚታወስ ነው፡፡

የሀይሌ እንግሊዝኛ

‹‹ዳዲ››ና ‹‹ማሚ›› እያሉ ወላጆቻቸውን የማይጠሩ ህፃናት ‹‹ፋራ›› ተደርገው ይታያሉ፡፡ ‹‹እትዮ፣ እቴቴ፣ እታባ፣እማዬ፣ እታብዬ›› የሚሉትን ውብ ቃላት ከልጆች አፍ ለመስማት በከተማ ወጣ ማለትን ይጠይቃል፡፡ በአማርኛው የሚሸማቀቅ ጎንደሬ፤ አማርኛ የሚንተባተብ ጎጃሜ እንደጉድ እየተፈጠረ ነው፡፡

ህፃናት አገርኛ የሆነ መዝናኛ አይቀርብላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ህፃናት በነ‹‹ባርኒ››ና በነ ‹‹ሰፓይደርማን››፣ በነ ‹‹ሲንዴሬላ››እና በነ‹‹ሲምባ›› ፊልሞች አፋቸውን ለመፍታት ይገደዳሉ፡፡ አባባ ተስፋዬ በቴሌቪዥን ተረት መናገር ካቆሙ ስንት ዓመት ሆናቸው? ለነገሩ በእርሳቸው የመጨረሻ የስራ አምታትም ተረቶቻቸው ላይ የሚሳለቁ ልጆች እየተፈጠሩ እንደነበረ ትዝ ይለኛል፡፡ ‹‹ልጆች-የዛሬ አበቦች የነገረ ፍሬዎች …ቁጭ በሉ…አትጋፉ…! በሚሉበት ሰአት ‹‹ሪሞት›› የያዙ ብዙ የአዲሲቷ እትዮጵያ ህፃናት “WHAT!! “ ማለት ይጀምራሉ፡፡

የኀይሌ ልጆች ከዚሁ ትውልድ ውስጥ ሊደመሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ የኀይሌን ሀገር ወዳድነት በእንግሊዝኛ ብቻ መረዳት ግን የሚከብድ ይመስለኛል፡ አባት ኀይሌ የእንግሊዝኛን ጥቅም በተግባር ያውቃታል፡፡ ልጆቹ እርሱ በቻለበት መንገድ ቋንቋዋን እንዲችሏት የሚሻ አይመስለኝም፡፡ በዚህ የተነሳ ውድ ልጆቹ ኤደን፣ሜሪና ቤቲ አማርኛን እንዲደነቃቀፉ ፈቅዷል፡፡ ለባንዲራው የሚያለቅሰው ኀይሌ ያ እንዲሆን ከፈቀደ ማን ቀረን ታድያ?

ምንጭ: አዲስ ነገር

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on November 28, 2010. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.