የኢድ አልፈጥር በዓል በአዲስ አበባ፣ በደሴ፣ በድሬዳዋ እና በሌሎች ከተሞች በተቃውሞ ተከበረ (ኢቲቪ ቀጥታ ስርጭቱን ለማቆም ተገደደ)

EMF – 1ሺ 434ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች ሲከበር የተጠበቀው ተቃውሞ አጋጥሞታል። በቅድሚያ ኢ.ኤም.ኤፍ ለመላው ሙስሊም “ኢድ ሙባረክ” በማለት ዘገባውን ከዚህ በመቀጠል ያቀርባል። በአዲስ አበባ ስቴዲየም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የኢህአዴግ ደጋፊዎች ብቻ እንዲገቡ ሲደረግ ሌሎች ደግሞ ከአዲስ አበባ ስቴዲየም ውጪ ሆነው፤ “አቃጠሉ” ያሏቸውን ባንዲራ እያውለበለቡ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ነበር። በወልቂጤ፣ በአዳማ፣ በደሴ እና በድሬዳዋ ተመሳሳይ የሆነ ተቃውሞ ተደርጓል። እንዲያውም በደሴ በአሉ ሳይከበር በፖሊስ ጣልቃ ገብነት ብዙ ረብሻ ተነስቷል። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በስቴዲየም ይደረግ የነበረውን ዝግጅት በቀጥታ ሲያስተላልፍ ቆይቶ ከውስጥም ከውጭም የሚሰማው የተቃውሞ ድምጽ ስለረበሸው፤ ቀጥታ ስርጭቱን ለማቋረጥ ተገዷል። በሌላ በኩል ግን አዲስ አበባም ውስጥ ፖሊስ ባደረሰው ድብደባ ብዙዎች ተጎድተዋል፤ የታሰሩም አሉ። ከየአቅጣጫው የደረሱንን ፎቶዎች እና ዘገባዎች ከዚህ በታች በዝርዝር እናቀርባለን።
Click here to read on PDF
Addis_august8_2013_11


ከዚህ በታች ያለውን አሰቃቂ የድብደባ ፎቶዎች ለልጆች እና ስሜታቸው ለሚነካ ሰዎች ትልቅ በማድረግ ባያዩት ይመረጣል

የአዲስ አበባ ሙስሊሞች፤ ገና ጠዋት 12 ሰዓት አካበቢ፤ ሱብሂ ሰላት ሰግደው እንዳበቁ ነበር ወደ ስታዲየም ማምራት የጀመሩት፡፡ ሁሉም ከያሉበት ወደ ስታዲየም መገስገሱን ተያያዙት፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ስታዲየም ከመድረሳቸው፤ በኪሎ ሚትሮች ርቀት ላይ የአዲስ አበባ ፖሊሶችና የፌደራልፖሊሶች ወደ ስታዲየም የሚያዳርሱትን ጎዳናዎች ሙሉ ለሙሉ ዘግተው ነበር የጠበቋቸው፡፡ እነዚህ ፖሊሶች በተለያዩ ርቀቶች ላይ ስታዲየም አቅራቢያ እስኪደረስ ድረስ በርካታ የፍተሻ ኬላዎችን ያቆሙ ሲሆን፤ ይህም በስታዲየሙ በአራቱም አቅጣጫዎች ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ፤ ከፒያሳ በቸርችል ጎዳና የሚመጡ ሰዎች ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢየመጀመሪያ ፍተሻ የተካሄደባቸው ሲሆን፤ በመቀጠልም ስታዲየም እስከሚደርሱ ድረስ በርካታ ጊዜ ተፈትሸዋል፡፡ ከአንዋር መስጂድ በተክለሃይማኖት በኩል የሚመጡ ሰዎችም፤ ከጎማ ቁጠባ፤ አካባቢ ጀምሮ ስታዲየም እስከሚደርሱ ድረስ በርካታ ጊዜ ተፈትሸዋል፡፡

ህዝቡ ወደ ስታዲየም እያመራ ባለበት ወቅት ላይ ለበርካታ ጊዜ ፖሊሶች ሙስሊሞችን ለመተንኮስ ቢሞክሩም ሙስሊሙ በትዕግስት አልፏቸዋል፡፡ ወደ እስታዲየም የሚሄዱትን እንዳንድ ሰዎችንም እየመረጡ ለማሰር ሞክረው የነበረ ሲሆን፤ በሙስሊሙ ርብርብ ሊለቀቁ ችለዋል፡፡

ህዝቡ ወደ ስታዲየም አካባቢም ከደረሰ በኋላ ቀድመው የሚፈልጓቸውን ሰዎች መርጠው ካስገቡ በኋላ፤ በስተመጨረሻም፤ የተቀረው ሙስሊም በከፍተኛ ፍተሻ እንዲገባ ፈቅደዋል፡፡ ሰላቱ የተሰገደው በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር 2፡40 አካባቢ ሲሆን፤ ከሰላቱ በፊትም የተለያዩ የህገወጡ መጅሊስ ባለስልጣናት ንግግር ለማድረግ ሞክረው ህዘቡ በተክቢራ በተደጋጋሚ ተቃውሟቸዋል፡፡ በስታዲየም ንግግር ያደረጉት ሼኽ ኪያር መሃመድ አማን፣ ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ እና የአዲስ አበባ ከንቲባ ተወካይ አቶ ኤፍሬም ይግዛው ነበሩ። ተናጋሪዎቹ ግን ሰሚ ሳይኖራቸው ዝም ብለው መናገራቸውን ቀጥለዋል። ህዝቡም እስከመጨረሻው ድረስ፤ ተክቢራ በማድረግና አንዳንድ መፈክሮችን በማሰማት አስቁሟቸዋል፡፡

ሰላቱ ተሰግዶ ካበቃ በኋላም፤ ሙስሊሙ ሰላማዊ ተቃውሞውን በደማቅ ሁኔታ ማሰማት የጀመረ ሲሆን፤ በዛሬው ተቃውሞ ላይ የተለያዩ መፈክሮችን አንግቦ ነበር፡፡ “ሹመኞችን አውርደናል” “መጅሊስ አይወክለንም”፤ “የታሰሩት ይፈቱ” የሚሉና ሌሎችም በርካታ መፈክሮችን በስቴዲየሙ ውስጥ እና ከዚያ ውጪ አሰምቷል፡፡ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በዛሬው ተቃውሟቸው ባለፈው ወቅት አንድ ግለሰብ አሮጌ ባንዲራ ሲያውለበለበ እያሳየ የድምጻችን ይሰማ አባላት ባንዲራ እንዳቃጠሉ አድርጎ ሲዘግብ የነበረውን የመንግስት ሚዲያ ዘገባ ፉርሽ በሚያደርግ መልኩ በባንዲራ አጊጠው ነበር የወጡት፡፡

ከስቴዲየሙ ውጪ ህዝቡ መፈክሩን እያሰማ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ መጓዙን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን ወደ ብሄራዊ ቲያትር ቤት አካባቢ ሲደርስ፤ የህዝቡን ሰላማዊነት ያልወደዱት፤ ፖሊሶች ህዝብን መደብደብ ተያያዙት፡፡እጅግ በጣም ብዛት ያላቸው ሙስሊሞች በወፍራም አጠናዎች ጭንቅላቶቻቸውና መገጣጠሚያዎቻቸው እየተመረጡ በአሰቃቂ ሁኔታ ልክ እንደ እባብ ተደበደቡ፡፡ ትእይንቱ በጣም የሚያሳዝን ነበር፡፡ ሙስሊሞች የዚህ ሀገር ዜጋ አይደሉምን? ከማለትም አልፎ የሰው ልጆችስ አይደሉምን? እስከሚባል ድረስ ጥያቄ የሚያስነሳ ድርጊት ነበር፡፡ ሽማግሌዎች፤ እናቶች፤ ሴቶችና ህፃናት ሳይቀሩ ፖሊሶች በያዙት አጠና ያለ ርህራሄ ተደብድበዋል፡፡

በርካታ ሴት እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን፤ ሌሎች ሲደበደቡ በማየታቸው ብቻ እራሳቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው፤ እሪ ብለው ሲያለቅሱና በእንባ ሲታጠቡ ተመልክተናል፡፡ ብዛት ያላቸው ሴቶች ወድቀው እጅና እግሮቻቸው ተሰብረዋል፤ ቆስለዋልም፡፡ በርከታ ህፃናት ከእናቶቻቸው እና አባቶቻቸው ጠፍተዋል፡፡ ብዙዎቹ ልብሶቻቸውን፤ ጫማዎቻቸውንና ንብረቶቻቸውን ጥለዋል፡፡ እጅግ በጣም የሚያሳዝንና የመንግስትን አረመኔያዊነትን በግልጽ ያሳየ ክስተት ነበር።

በዛሬው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴት እህቶቻችንና ወንድሞቻችን እንዲሁም፤ ህፃናትና አባቶች ሳይቀሩ በፖሊሶች ተይዘው ታስረዋል፡፡ ይህ ዜና በተቀናበረበት ወቅት ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አካባቢ በርካታ ሙስሊሞች ተይዘዋል፡፡ የሳር ቤት፣ የቄራ መንገዶች ከ4 ኪሎ በቤተመንግስት አድርጎ ወደ ስታዲየመው የሚወስደው መንገድ ዝግ ተደርጓል፡፡ በተቃውሞ መጨረሻ አካባቢ በብሄራዊ ትያትር፤ ሜክስክ፤ ለጋሀር፤ ኢቲቪ ፊት ለፊት በድብደባው ብዙ እናቶች እና ህጻናት እንዲሁም ወጣቶች ጉዳት የደርሰባቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የአዲስ አበባው ተቃውሞ በሰላም አጠናቀናል።

ድሬዳዋ—
በድሬ ዳዋ ከተማ ህዝበ ሙስሊሙ ከባድ ተቃውሞውን አሰምቷል። በዚህን ወቅት ህገወጦቹ መጅሊሶች ህዝበ ሙስሊሙን ተቃውሟችሁንን አቁሙ በማለት እያስፈራሩ ነበር፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደርም ተቃውሞውን አቁሙ በማለት ንግግሩን በማይክራፎን ማሰማት ጀምሯል። በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት የታጠቁ ብዛት ያላቸው ፖሊሶች እና አድማ በታኝ ፖሊሶች በቦታው ደርሰዋል::

ደሴ –
በደሴ ከተማ የወያኔ አድማ በታኞች በፈጠሩት ሁከት የኢድ ሰላት ሳይሰገድ ቀረ ። ፖሊሶች ህዝቡን አፍነው ለመደብደብ ሲዘጋጁ ህዝበ ሙስሊም በተለይ ወጣቱ ህዝቡን የከበቡትን ፖሊሶች በተቃውሞ የተከበቡትን ሰዎች ከፖሊስ ቁጥጥር ስር አውጥተዋል። የኢድ ሰላት የሚሰገድበት ቦታ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር። በተለያዩ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ተወስደዋል ።

ደቡብ ሐላባ –
በደቡብ ሐላባ ከተማ የአገሬው ሙስሊም ነቅሎ ሐላባ ስታዲየም ደርሷል፡፡ ዙሪያ ገባው ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› በሚል መፈክር ተሸፍኗል፡፡ የክልሉ ልዩ ኃይል ዙሪያውን አድፍጧል፡፡

(አዳዲስ የምናገኛቸውን ዜናዎች እና ፎቶዎች ጨምረን ዘገባችን ይቀጥላል)

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on August 8, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.