የኢድን በአል በስቴዲየም ለማሳለፍ፤ ለኢህአዴግ ታማኞች የጥሪ ካርድ ተዘጋጀ (“ድምጻችን ይሰማ” ያልሰማው ዜና)

EMF – ሃሙስ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀውን የኢድ አልፈጥር በአል በስቴዲየም ውስጥ ለሚያሳልፉ “ታማኝ” ሙስሊሞች ልዩ የመጥሪያ ካርድ ተዘጋጀ። ካርዱ የተዘጋጀው ሃያ ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች ብቻ ሲሆን፤ እነሱም ላለው ገዢ መንግስት ታማኝ መሆን እንዳለባቸው ጥብቅ መመሪያ ተላልፏል። ኦገስት 8 ቀን የሚከበረው ኢድ አልፈጥር በአል ለኢህአዴግ አስተዳደር ራስ ምታት ሆኖበታል። በዚህ እለት እንደከዚህ ቀደሙ ህዝቡ ድምጹን ሊያሰማ ቢዘጋጅ እንኳን፤ የወያኔ ወታደሮች ሆን ብለው ረብሻ አስነስተው ከህዝቡ ጋር ሊጋጩ እንደሚችሉ የብዙዎች ስጋት ሆኗል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሙስሊሙን በማስተባበር መመሪያ የሚሰጠው “ድምጻችን ይሰማ” የተባለው አካል ህዝበ ሙስሊሙ በስቴዲየም ተገኝቶ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ጥሪ አቅርቧል። ከትላንት ጀምሮ በስቴዲየም የሚገኙት የኢህአዴግ ታማኝ ሙስሊሞች ብቻ መሆናቸውን በዜናዎች ስንገልጽ ብንቆይም፤ “ድምጻችን ይሰማ” የተባለው አካል ግን በኢትዮጵያ ሚዲያዎች እየወጡ ያሉትን መረጃዎች እየተከታተለ እንዳልሆነ ያስረዳል። ለዚህም ይመስላል፤ በተግባር እየተከናወነ ካለው የኢህአዴግ ታክቲክ አንድ እርምጃ ወደ ኋላ የቀረ የመሰለው። ይህ ብቻም አይደለም። በአርሲ ስለተገደሉት ሙስሊሞች በዚህ መግለጫው ምንም አላለም። ይልቁንም ከኢድ በኋላ የጁምዓ ተቃውሞ ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚቆም ነው የገለጸው። (ሙሉውን መግለጫ ከዘገባችን በኋላ አቅርበነዋል)

የሆኖ ሆኖ በዚህ ታይቶ በማይታወቅ የኢህአዴግ የካርድ ጥሪ ምክንያት ህዝበ ሙስሊሙ ቅር ከመሰኘት አልፎ፤ ኢህአዴግ ሙስሊሙን በግልጽ ለሁለት የመክፈል ጥረቱ ጎልቶ የወጣበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። በዚህም መነሻ በስቴዲየሙ ውስጥ ተገኝተው ሶላት የሚያደርጉትና ከስቴዲየሙ ውጪ ያሉት ሙስሊሞች በግልጽ በሃሳብ እና በአመለካከት የተለያዩ ይሆናሉ። በስቴዲየሙ ውስጥ የሚገኙት በአሁኑ ወቅት ታስረው ለሚማቅቁት የኮሚቴ አባላት እና ለሞቱት ሌሎች የሙስሊም እምነት ተከታዮች ምንም ደንታ የሌላቸው ሲሆኑ፤ ከስቴዲየም ውጪ ያሉት ደግሞ ለ እምነታቸው እና ለአቋማቸው ጽናት ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል። በዚህም ምክንያት በስቴዲየሙ ውስጥ በሚሰግዱት የወያኔ ታማኞችና ከስቴዲየሙ ውጪ በሚገኙት መካከል፤ ጥላቻ እና ሽኩቻ ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

የወያኔ ኢህአዴግ መንግስት ባለበት ስጋት ምክንያት ባለፈው አመት ቀኑን ሙሉ የፈጀ የቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት ሲያደርግ የነበረ ሲሆን፤ አሁንም ተመሳሳይ የልምምጥ እና የማባበያ ዝግጅት ሳያደርግ እንደማይቀር ተገምቷል። ይህም ሆኖ ቁጥሩ እጅግ የበዛ የፌዴራል እና የአጋዚ ወታደሮች ከወዲሁ አካባቢውን በመቅቃኘት ላይ ናቸው። በእለቱም በስፍራው ተገኝተው ታማኝ ያልሆኑትን ህዝበ ሙስሊሞች ድምጽ ለማፈን፤ ካመቻቸውም ከመምታት እና ከማሰር ወደኋላ እንደማይሉ ግምት አለ። የወያኔ/ኢህአዴግ ሰዎች፤ ህዝቡን ለመከፋፈል ካላቸው ግልጽ ፍላጎት አንጻር የኢትዮጵያ መሆኑ የማይታወቅ ባንዲራ ተቀዳዶ ሲውለበለብ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በማሳየት፤ ባንዲራ ሳይቃጠል “ተቃጠለ፣ አቃጠሉት” ብሎ የውሸት ፕርፓጋንዳ ከማስተላለፍ አልፈው፤ ፍትሃዊ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ያቀረቡ ወገኖችን “ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ አላቸው” በማለት የመከፋፈል ተግባራቸውን ቀጥለውበታል።

ይህ ብቻ አይደለም። የኢህአዲግ ሰዎች ራሳቸው ከፈጠሩት ስጋት በመንሳት በመጪው የኢድ አልፈጥር በአል አዲስ አበባ ውስጥ ብጥብጥ ሊነሳ እንደሚችል፤ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኩል፤ አዲስ አበባ ለሚገኙ የውጭ አገር ኢምባሲዎች አሳውቀዋል።

Invitation card for EPRDF loyalists

Invitation card for EPRDF loyalists

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ በውጭ አገር የሚገኙ ኢምባሲዎቿ በተጠንቀቅ እንዲቆዩ ስታደርግ “ኢትዮጵያ” ስጋት የሌለባት አገር ተብላ ነበር። አሁን ግን ኢህአዴግ “የአሸባሪዎች ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል ደርሼበታለሁ” በማለቱ፤ ኢትዮጵያም አሜሪካ ባወጣችው ዝርዝር ውስጥ እንድትካተት አድርገዋል። ይህን ያደረጉበት ዋናው ምክንያት በአሜሪካ ኤምባሲ ላይ (ለነገሩ የአሜሪካ ኢምባሲ ከስፋቱ እና ከጥበቃው ብዛት የተነሳ ምንም ሊፈጠር እንደማይቻል ይታወቃል። እንዲያውም ጥቃት መሰንዘር ካስፈለገ፤ ከአሜሪካ ኢምባሲ ይልቅ ወያኔ በተቀመጠበት ቤተ መንግስት ላይ ጥቃት መሰንዘር የሚቀል ይመስላል።) አሸባሪዎች ጥቃት ይሰነዝራሉ በሚል ሰበብ፤ በአርሲ ላይ ያደረጉትን አይነት ጭፍጨፋ በአዲስ አበባ ላይ ለመድገም እየተዘጋጁ ያሉ ይመስላል።

እስካሁን በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ ከተሞች ከሃያ ጊዜ በላይ ቦንብ እየተወረወረ እና እየተጥጠመደ ሰላማዊውን ህዝብ በማስፈጀት፤ “የአሸባሪዎች ሴራ ነው” ለማለት ጥረት ቢደረግም፤ ለፈነዳው ቦንብ አንድም ጊዜ፤ አንድም አካል ተጠያቂነቱን እወስዳለሁ ያለ የለም። ከዚህም በመነሳት ህዝቡ፤ “ቦንቡ የወያኔ፣ አፈንጂዎቹም ወያኔዎች ናቸው” ማለት ከጀመረ ውሎ አድሯል። አሁንም በመጪው ኢድ አልፈጥር በአል የሚፈልጉትን ሃያ ሺህ ሰው ወደ ስቴዲየም ካስገቡ በኋላ በቀሪዎቹ ላይ ምን አይነት እርምጃ እንደሚወስዱ ወይም ምን ሊያፈነዱ እንደሚችሉ ስለማይታወቅ “መጠንቀቅ አይከፋም” በሚል በኛ በኩል ያለውን ዘገባ እናበቃለን።

ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ድምጻችን ይሰማ ስለተቃውሞው የሰጠውን ዝርዝር መመሪያ ከዚህ በመቀጠል እንዳለ አቅርበነዋል።
ድምፃችን ይሰማ
አገር አቀፉ የዒድ ተቃውሞ ዝርዝር
መርሐ ግብር
ነሐሴ 2/2005
ይህ መርሐግብር በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ ሁሉ የሚያገለግል ነው፡፡
የረመዳን ዒደል – ፊጥር ቀን የተቃውሞ ውሎ ሁለት ንኡስ ክፍሎች አሉት፡፡
1. የዒድ ሰላት ከመሰገዶ አስቀድሞ
2. የዒድ ሰላት ከተሰገደ በኋላ

1. የዒድ ሰላት ከመሰገዱ አስቀድሞ ይህ ክፍለ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ስታዲየም ከደረስን ከማለዳው 12 ሠዓት ጀምሮ በክፍለ ሀገር ደግሞ እንደ አከባቢው ሠዓት ሁኔታ ለዒድ ሶላት እስከምንቆምበት ያለውን ጊዜ ያካትታል፡፡
* ሁላችንም ከማለዳው 12 ሠዓት ላይ ተጠናቀን በስታዲየም እንገኛለን፣
* ሥርዓት ያለው ተቃውሞ ለማካሄድ እንዲረዳን ስታዲየም እንደደረስን ቦታችንን እንይዛለን፣
* መከራና ስቃይ ቢደራረብብንም ዛሬም ሠላማዊነታችንን ለማስመስከር ከመድረክ የሚባለውን ተክቢራ በጋራ እያልን የያዝነውን ነጭ ወረቀት/ ጥምጣም ቀጥ አድርገን እንይዛለን፣
* ከመድረክ አካባቢ በመጅሊስ ሹመኞች ምንም ዓይነትንግግር ከተሠማ በተክቢራ እናስቆማለን፣
* የመንግስት ባለስልጣን ተጋባዥ እንግዳ ካለ በእስር፣ በግፍና በእንግልት ላይ መሆናችንን በሚያንፀባርቅ መልኩ ጆሮዎቻችንን በመዳፎቻችን በመያዝ ‹‹ድምፃችን ይሰማ!›› የሚል መፈክር ንግግሩን አቋርጦ መድረኩን ለቅቆ እስከሚወርድ ድረስ እናሰማለን፡፡
* የዒድ ሰላትን በጋራ እንሰግዳለን፡፡

2. የዒድ ሰላት ከተሰገደ በኋላ ይህ ክፍለ ጊዜ የዒድ ሶላት እንዳበቃ የሚጀምርና ተቃውሞ ጀምረን እስከምናጠናቅቅ ያለውን አጭር ክፍለ ጊዜ ያካትታል፡፡
* ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ባለንበት ሳንንቀሳቀስ እንቆማለን፡፡ ይህ ለረብሻናግርግር የመጡትን ኃይሎች በቀላሉ ለመቆጣጠር ከማስቻሉም በላይ ተቃውሟችን አንድነቱንና ስርዓቱንበጠበቀ ሁኔታ እንዲካሄድ ያግዘናል፡፡
* ባለንበት ምንም እንቅስቃሴ ሳናደርግ አዘጋጅተን የመጣነውንና ‹‹ሹመኞችን..አውርደናል ›› የሚለውን ወረቀት ለ 3 ደቂቃ በማሳየት የመንግስት የመጅሊስ ሹመኞች ከእንግዲህ በይፋ መውረዳቸውን እናውጃለን፡፡
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹አላሁ አክበር!›› እንላለን
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹ድምፃችን ይሰማ››
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹ጥያቄው ይመለስ!››
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹የታሰሩት ይፈቱ!››
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹በአቋማችን እንፀናለን!››
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹በእምነታችን – ጣልቃ አትግቡ!››
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹ሀስቡን አላህ – ወኒዕመል ወኪል!››
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹ድራማው ይብቃ!›› እንልና እንጨርሳለን፡፡
ከላይ የተቀመጡት መርሐግብሮች እንደተጠናቀቁ ሕገ መንግስቱ የሰጠን ሃይማኖታዊ መብታችን ተጥሶና ሰብአዊ መብታችን ተረግጦ በመስከረም 27 በቀበሌ የተቀናበረው የመጅሊስ ሹመት ላይ ተምሳሌታዊ ስርአተ ቀብር ቀጥሎየሚፈጸም ይሆናል፡፡ይህም ግለሰቦች በተናጥል ወረቀት ላይ በመጻፍም ሆነ ትንሽ ጨርቅ በመጠቅለል ሊፈጽሙት የሚችል ሆኖ ተምሳሌታዊነቱን የሚያሳይና የጋራ ማሳያዎች ያሉት ስርአተ ቀብርም ይካሄዳል፡፡ ይህ አንደተካሄደም የዒድ አልፊጥር አገር አቀፍ ሠላማዊ ተቃውሟችን ይጠናቀቃል ማለት ነው፡፡

ማስታወሻ!
1. ሁላችንም ‹‹ሹመኞችን..አውርደናል !›› የሚል መፈክር በወረቀት ላይ ፅፈን ይዘን እንመጣለን፡፡
2. መንግስትና መጅሊስ የሚያደራጇቸው ቡድኖች እኛን ወደ ሁከት ለመቀስቀስ ቢጥሩ እንደከዚህ ቀደሙ በምንም መልኩ ምላሽ ባለመስጠት እና ስራቸውን በማጋለጥ ዓላማቸውን እናከሽፍባቸዋለን፡፡

3. በማንኛውም ቦታ ኹከት ቢፈጥሩ (በሴቱም በወንዱም በኩል) በምንም ዓይነት ሁኔታ ሳንደናገጥ ባለንበት ቦታ ረግተን ቆመንና እጅ ለእጅ ተያይዘን ግርግራቸውን እናከሽፋለን፡፡
4. መሃላችን ገብተው ህዝቡን ‹‹ሰልፍ እናድርግ›› ከተጠቀሰው ሰዓት ውጪ ‹‹እንቆይ›› ብለው የሚቀሰቅሱ ካሉ እናጋልጣቸዋለን፡፡
5. ዝናብ ቢኖር አንኳ ከዚህ በፊት እንዳሳየነው ሁሉ ፀንተን ድምፃችንን ከማሰማት አይገድብንም፡፡
6. ከኢማሙ አቅጣጫ ድምጽ የማይሰማበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ከፊት ያለን ሰዎች የኢማሙን ድምፅ ወደ ኋላ ላሉት እናስተጋባለን፡፡
7. በተለይም በአዲስ አበባ ተቃውሟችንን በእስታዲየምና አካባቢው በሚኖረን ቆይታ ካጠናቀቅን በኋላ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በኩል በምናልፍበት አጋጣሚ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች!
ከላይ የተቀመጠውን የተቃውሞ ሂደት ብቻ ሙሉ በሙሉ በመተግበር ቁጣችንን እንገልፃለን! በዲናችን ላይ እየተደረገ ያለውን የእጅ ጥምዘዛ፣ እስር ድብደባና የህይወት ማጥፋት ወንጀል እንቃወማለን!
በዳዮች ለፍርድ እንዲቆሙም እንጠይቃለን!
ኮሚቴዎቻችን፣ ዱዓቶች፣ ወንድምና በእህቶች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱልን እንላለን! በዚህ አንድነታችንን አናሳያቸዋለን!
እኛሚሊዮኖች መሆናችንን በተግባር እናረጋግጥላቸዋለን፡፡ ዲናችንን ለድርድር እንደማናቀርብ በዓይናቸው አንዲመለከቱ እናደርጋለን!
ይህ የኢድ ተቃውሞአችን ከተጠናቀቀ በኋላ የጁምአ ተቃውሞዎች ላልተወሰኑ ጊዜያት የማይካሄዱ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
በዚህ የኢድ ተቃውሞአችን ለሌላ ተጨማሪ ጊዜ ለመንግስት እና ለሚመለከተው አካላት መልእክታችንን በማድረስ የመንግስትን ተግባራዊ ምላሽ ለመጠበቅ ስንል የጁምአ ተቃውሞዎችን ላልተወሰኑ ጊዜያት የምናካሄድ አይሆንም፡፡ በተለይም በመስከረም 27 የተካሄደው የመጅሊስ የቀበሌ ሹመት በእለቱ ተምሳሌታዊ ስርአተ ቀብር ስለሚፈጸምለት ይህ ነው ተብሎ የሚወጣ አካል ባለመኖሩ መንግስት የጥሞና ጊዜ ወስዶ ሕዝብ ለጠየቃቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሹን እንዲሰጥ የጁምአ ተቃውሞዎች ላልተወሰኑ ጊዜያት
ይቆማሉ፡፡
አላሁ አክበር

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on August 7, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.